አድባራተ ጥበብ

ዳዊት ቸርነት – ሙዚቃን ከሥነ-ፈለክ ያዛመደ ሙዚቀኛ

እንደመንደርደሪያ

አከራካሪው ሐሳብ አሁንም ተነሥቷል። በመጀመሪያ፣ ሳይንስን እና ሃይማኖታዊ እሳቤን ሊያስታርቅ የተቀመረ ቢመስልም፣ በሳይንስ ዘርፍ በፕላኔቶች አፈጣጠርም ይሁን አወቃቀር አብዮት አስነሥቷል። ፍልስፍናውም በሃይማኖት እና በሳይንስ ጎራዎች ለሁለት ተከፍሏል። The Creator and the Cosmos መጽሐፍ ደራሲ Hugh Ross ሦስቱም እሳቤዎች አንዳቸው በሌላኛው ላይ የበላይነትን ለማንጸባረቅ በቃላት ተጎሻሽመዋል ይላል፤ ኮስሞሎጂ ሾቪኒዝም (Cosomology Chauvinism) ብሎም ሰይሞታል። በድምዳሜው ግን፣ “በጠበበ አረዳድ የሚደረግ ንትርክ እንጂ፣ ተቃርኖ የላቸውም” ብሏል።

ይህን አከራካሪ ሐሳብ ዳግም ያነሣው ደግሞ፣ ዳዊት ቸርነት ነው። “ፍቅር” ደግሞ፣ ይኸው ሐሳብ የተካተተበት ነጠላ ዜማ።

መነሻ

ዳዊት ቸርነት ስስ በሚመስል ድምፅ (vocal power) ከፍ ያሉ ሐሳቦችን በሙዚቃ ሥራዎቹ ላይ ያነሣል። ዳዊት ቃል መንዛሪ ነው፤ ሥነ-ጽሑፋዊ በሆነ አረዳድ “አርክታይፕ”ን እንደመሣሪያ የሰው ልጅ አንድነታዊ መስተጋብሮችን ለማጉላት ይጠቀማል። መጽሐፍ ቅዱስን ደግሞ፣ የሐሳብ መዋሻ ያደርገዋል።

“ፍቅር” ብሎ የሰየመው ነጠላ ዜማም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በዚሁ ዘፈኑ እምነትን፣ ተስፋን እና ፍቅርን ደመቅ ባለ ስልተ-ምት ያሳይበታል። አዝማቹ ላይ ያለው የግጥም ስንኝ ግን፣ ልዩነታዊ ሐሳቡን ዳግም ያስታውሳል።

ፀሐይ ትቆማለች ካዘዝናት”

እርግጥ ነው፣ ዳዊት “በዘፈን ሲዜም” የፀሐይ መቆም ታሪክን ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ብሉይ ኪዳን፣ መጽሐፈ ኢያሱ 10:13 ላይ ተውሷል። ሆኖም፣ ከ16ተኛ ምዕተ-ዓመት በፊት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ በኋላም ይህ አስተሳሰብ በሳይንሱ፣ እንዲሁም በሃይማኖቱ ላይ ክፍፍልን ፈጥሯል፤ በፀሐይ፣ በምድር እና በጨረቃ መዋቅራዊ አረዳድ ዙሪያ የሐሳብ ክርክር ተደርጓልና።

ሳይንሳዊ አብዮቱን እንዘክር

ኒኮላስ ኮፐርኒከስ እና ጋሊሊዮ ጋሊሊ የተደራጀ ሐሳቦችን ከማቅረባቸው በፊት የሰው ልጅ ስለጠፈር የነበረው ዕውቀት ለሁለት ተከፍሎ ነበር። በእርግጥ፣ ከ1400 ዓመታት በላይ ገዥው ሐሳብ ሥርዓተ-ምድር ወይም ማእከለ-ምድር (geocentric) ነበር።

ምድርን በፈለኮች (በፕላኔቶች) የዑደት ሥርዓት ቋሚ ቦታ ያላት እና ፀሐይን ጨምሮ በወቅቱ በምርምር የተለዩ አምስት ፕላኔቶች ምድርን እንደሚዞሯት የሒሳብ ቀመር ዐዋቂው በጦሊሞስን (ፕቶሎሚን) ጨምሮ አሳምኗል። የጥንታዊት ግሪክ ታላቁ ፈላስፋ አፍላጦን (ፕሌቶ) ተማሪውን አርስጣጣሊስ (አሪስቶትል) አመክኒዮውን አሳምኖታል። ፕቶሎሚ መሬትን በምሕዋራቸው የሚዞሯት፣ ፀሐይ እና ጨረቃ ጨምሮ፣ አምስት ፕላኔቶች በጂኦሜትሪክ ቀመር በፍጹማዊ ዑደት ላይ እንደሚገኙ፣ ቅርጻቸው እና ሹረታቸው የሙዚቃ ውሕደታዊ ስምምነት (harmony) እንደሚገልጻቸው ያስረዳል።

በእርግጥ፣ የሥርዓተ-ምድር እና የሥርዓተ-ፀሐይ ንድፈ-ሐሳብ አቀንቃኞች የጋራ መስማማትን አሳይተዋል። በምድር ቅርጸ-ክብነት ላይ ልዩነት የላቸውም። በገዘፈው የgeocentric ሐሳብ አረዳድ ግን፣ እንደእነፊሎላስ ያሉ የሕዋ ተመራማሪዎች ሰሚ ጆሮ ባያገኙም፣ አፈንጋጭ ምልከታን አራምደዋል፤ ይህም አፈንጋጭ ንድፈ-ሐሳብ ምድር ፀሐይን ባትዞርም፣ በአንዳች ማእከላዊ ነበልባል (central fire) ዙሪያ ዑደት እንደምታደርግ የሚጠቁም ነው።

ከ16ተኛው ምዕተ-ዓመት በፊት በነበረው አረዳድ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን በአስተምህሮዋ/የመጽሐፍ ቅዱስ አረዳድ ላይ ያን ያክል ተጽእኖ ባልተፈጠረው የማእከለ-ምድር ግንዛቤ ዙሪያ ተቃውሞዋን አልገለጸችም ወይም የሐሳብ እገዳ አልጣለችም። በሌላ አጽናፍ ግን፣ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ተሰብኳል። ለዚህም እንደምክንያት የተገለጸው ደግሞ፣ ምድር ላይ ያለው ፍጡር (የሰው ልጅ) በፈጣሪው ዘንድ እንቅስቃሴው በግልጽ እንዲታይ ምድር ጠፍጣፋ እና አራት ማዓዘን ተደርጋለች የሚል ነው። በእርግጥ፣ ይህን አቋማቸውን ለማጠናከር ከመጽሐፍ ቅዱስ ማሳያ ምዕራፎችን ቢጠቀሱም፣ የነገረ-መለኮት አረዳዱ ቀጥታዊ ንባብ እንደሆነ በማስረዳት ውድቅ እየተደረገ መጥቷል። “ምድር ጠፍጣፋ ነች” የሚለው ንድፈ-ሐሳብ አቀንቃኞች ግን፣ ዘመን ተሻግረው በ21ኛው ምዕተ-ዓመትም ይህንኑ እምነታቸውን እንደያዙ ዘልቀዋል። እነኝህ ወገኖች ከቀደምቱ “ምድር ጠፍጣፋ ነች” አስተሳሰብ የሚለዩበት ምድር አራት ማዓዘን ሳትሆን፣ የሙዚቃ ማጫወቻ ሸክላ (disc) መምሰሏ እና የአርክቲክ በረዶ ግግርም በምድር ዙሪያ እንደግንብ የተገነባ አጥር ሆኖ ያያገለግላል በሚለው መከራከሪያቸው ነው። በዚህም ናሳ (የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም) የሤራ ንድፈ-ሐሳብ ትንታኔ ማእከል እንደሆነ እና የሰው ልጅ በግንቡ ተንጠላጥሎ እንዳይዘል የተሸረበ እና የምድር ክብነትን የሚያሳዩ ምስሎችም በምስል ማቀነባበሪያ እንደተሠሩ ይይናገራሉ። አሜሪካዊው የሂፕ ሃፕ ሙዚቃ ስልት አቀንቃኝ B.O.B. ይህንን ንድፈ-ሐሳብ እንደሚያምንበት ከመግለጹም ሌላ፣ ሙዚቃም ሠርቶበታል። Flat Line በተሰኘው የሙዚቃ ሥራውም መሬትን በክብነት እንድትሣል ለሚፈልጉ ወገኖች መልእክቱን እንዲህ ሲል አስተላልፎበታል፦

Globalists see me as a threat
Free thinking, got a world at my neck

(ስንኙ ድምፃዊው ካቀነቀነው ዜማ የተቀነጨበ ሲሆን፣ globalists የሚለው ቃል አጠቃቀም መሬትን በክብነት ለሣሏት መጠሪያ ስም ሆኖ በFlat Earth Society የሚያገለግል ሆኗል።)

ውኃ የማያነሣ ሙግት”

Astrophysics for the people in a hurry መጽሐፍ ደራሴ ኔል ዲ ግራስ ታይሰን ግን፣ ውኃ በማያነሣ ሙግት ጊዜዬን አላባክንም በማለት፣ በሥርዓተፀሐይ ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይመክራል። የሥርዓተ-ፀሐይ (heliocentric) ንድፈ-ሐሳብ ከ16ተኛው ምዕተ-ዓመት በኋላ ገዥ ሐሳብ በመሆን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል። የሥርዓተ-ምድር ንድፈ-ሐሳብ ውድቅ ያደረገው ቀላሉ ማሳያ ጁፒተር ያሏት ጨረቃዎች ምሕዋር በፕላኔቷ ዙሪያ መሆኑ ነው። ኮፐርኒከስ እና ጋሊሊዮ ደግሞ፣ ‘ርቱዕ’ ያሉትን ትንታኔ አቅርበዋል። ያም ሆኖ፣ በቤተ-እምነት ዙሪያ የተሰባሰቡት ሰዎች ንድፈ- ሐሳቡን ውድቅ ከማድረጋቸውም ባሻገር፣ በእሳቤው አራማጆች ላይ ቅጣት አስተላልፈዋል። ለዚህም ማሳያው የጋሊሊዮ ቀሪ የዕድሜ ዘመኑን በቁም እስር ማሳለፉ ማሳያ ነው። የወቅቱ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን እሳቤ ነገረ-መለኮትን (theology) የሳይንስ ሁሉ የበላይ እና ገዥ ማድረግ ሲሆን፣ በሌሎች ዘርፎች የሚካሄዱ የሰው ልጅ ምርምሮችም የመራሄ ሳይንሱ ተቀጽላ ተደርገዋል። ስለሆነም፣ ማንኛውም ዓይነት የመጽሐፍ ትርጓሜ አረዳድ እና ውሳኔ በቤተ-እምነቱ ባለው የሥልጣን ተዋረድ የጸደቀ መሆን ይገባዋል። የሥርዓተ-ፀሐይ ንድፈ-ሐሳብም በዚሁ ምክንያት ለዘመናት ውድቅ ተደርጎ ቆይቷል።

ከዚህ በኋላ ሳይንስ የምክንያት እና ውጤት (cause and effect) አካሄድን በተፈጥሮ ዙሪያ በሚያካሂዳቸው ምርምሮች ላይ እየተገበረ ምልከታውን (observation) ሲተነትን፣ በእምነቱ በኩል ያለው አስተምህሮ እውነት ነው ብሎ የመቀበሉ ዝንባሌ ተጽእኖ ላይ እየወደቀ መጥቷል። በእርግጥ፣ ምድር ላይ ለቆመ ሰው ፀሐይ “ስትወጣ” እና “ስትጠልቅ” በማየቱ የሥርዓተ-ምድር ንድፈ-ሐሳብን ማቀንቀኑ ባልከፋ። ነገር ግን፣ ምክንያት አልባ (cause) ውጤት (effect) ከማጤን የዘለለ ትርፍ አላስገኘም። የፕሮቴስታንት (የዘመነ-ተሐድሶ) እንቅስቃሴም በሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን የበላይነት ላይ ተቃውሞውን ሲያነሣ አንዱ መሞገቻው ይሄንኑ ‘የሳይንሱ እና የቤተ-እምነቱ የበላይ ጠባቂ ነን’ በሚሉት መካከል ያለውን ልዩነት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም፣ በሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ያለው የባለሥልጣንነት ምልከታ በቅዱስ መጽሐፉ አረዳድ ላይ ችግሮችን መፍጠሩ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው እምነትም እንዲጎድል አድርጓል በሚል የመሞገቻ ሐሳብ አቅርበዋል – የዘመነ-ተሐድሶ አቀንቃኞች።

ዳዊት ቸርነት አሁንም በዘፈኑ ይዘምራል። ፍቅር የምድር ገዥ ምክንያት ከሆነ፣ እእንዲሁም ጨለማው ተገፍፎ ጎሕ እንደሚቀድ ተስፋና እምንት ካለ፣ “ካዘዝናት፣ ፀሐይ ትቆማለች” በማለት፣ የብሉይ ዘመንን የሚያስታውስ ተአምር ያወሳል። በዚህም ሥራው ያንን ዘመን በሥርዓተ-ምድር (geocentric) አስተሳሰብ ዙሪያ የተካለለ ያደርገዋል።

አከራካሪ ሐሳብ

መጽሐፈ ኢያሱ 10:13 በአስትሮሎጂ የጥናት ዘርፍ አንድ አከራካሪ ታሪካዊ ነጥብ ያነሣል። መጽሐፉ አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ከኢያሱ ጋር ያደረጉትን ጦርነት በምዕራፍ 10 ይተርካል። ቁጥር 13 ላይ ደግሞ፣ በእስራኤላውያን ወገን ያለው ኢያሱ በፈጣሪው እገዛ ፀሐይ እንድትቆም፣ ጨረቃም እንድትዘገይ ያዛል። ጥያቄው ያለው በተአምራቱ ላይ አይደለም፤ ይልቁንም፣ የሰው ልጅ ምርምር ያስከተለው እንጂ። ይህ ደግሞ፣ “መሬት ጠፍጣፋ ነች” ለሚሉት ወገኖች አበረታች ማስረጃ ሆኗል። “መሬት ከፀሐይ እና ከጨረቃ በመጠን የገዘፈች ነች፣ እንዲሁም እነኝህ አካላት ምድርን ይዞሯታል” የሚል መከራከሪያ ያቀርቡበታል። የፀሐይ እና ጨረቃ ስፋት 50 ኪሎ ሜትር (በዲያሜትር) ሲሆን፣ ጠፍጣፋዋንም ምድር በ5500 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ እንደሚዞሯት ይናገራሉ።

ይህ እሳቤ የአይዛክ ኒውተንን የምድር ስበት ሕግ የሚንድ ነው። ምድር ወደታች ሳይሆን፣ ስበቷ መሬት በተንሳፈፈችበት ሕዋ ወደላይ ስታቀና የሚፈጠርና ይህም ፍጥነቷን 9.8 ሜትር በሴከንድ አድርጎታል። “ምድር ጠፍጣፋ ነች” የሚለውን አረዳድ ለመደገፍ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በማልታ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ጠለቅ ያለ ምርምር ለ25 ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል። ተመራማሪው Aristarchus ግን፣ ይህንን ሐሳብ ቀደም ሲል ገና በሁለተኛው ምዕተ-ዓመት ውድቅ አድርጎታል። ይህንንም ያስረገጠው የፀሐይን ግዝፈት በመቀመር፣ ከመሬት የራቀች እና የገዘፈች አድርጎ በማስቀመጥ ነው።

የኮፐርኒከስ አብዮትም የቀደመውን ገዥ ሐሳብ ንዶ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያንን አስቆጥቷል። የኮፐርኒከስ ተማሪው ጆርጅ ዮአኪም ሩቲከስ በheliocentric ንድፈ-ሐሳብ የተፈጠረውን የሳይምስ እና የእምነት ተቋማትን መቃቃር ለማስታረቅ ሙከራ አድርጓል። በዚያ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢያሱ በተሳተፈበት ጦርነት ወቅት ፀሐይን “ቁሚ” በማለቱ፣ በፀሐይ ዙሪያ ዑደቷን የምታደርገው ምድር እንድትቆም ታዘዘች እንጂ፣ ፀሐይ እንዳልቆመች መከራከሪያ ለማምጣት ሞክሯል። ዳሩ ግን፣ በዘመኑ አብዮት ውስጥ የገባው ሳይንስ ማስታረቂያ ሐሳቡን አልተቀበለውም።

ተአምራዊ ክስተቱን ለአፍታ እናቆየው። ምድር ብትቆም ምን ሊፈጠር ይችላል? አስትሮፊዚስቱ ኔል የሚከሰተውን ለመገመት ይከብዳል ብሏል። የፊዚክስ ዕውቀትን እንዋስና በእንቅስቅሴ ላይ ያለ ነገር ድንገት እንቅስቃሴው ቢገታ (law of motion and acceleration ) እንቀምርበት። ምድር በምሕዋሯ ስትሾር ፍጥነት አላት። ይህም ፍጥነት በሴኮንድ 30 ኪሎ ሜትር ነው። እንደኔል ገለጻ ደግሞ፣ በሰዓት 800 ኪሎ ሜትር ያደርገዋል። የፀሐይ ስበት ደግሞ፣ እንደግዝፍቷ ብርቱ ነው። የምድርም በዚህ ፍጥነት መጓዝ የፀሐይን ስበት ለማቻቻል ( balance) ለማድረግ እና ምድርን ብቻ ሳይሆን በፀሐይ ዙሪያ ያሉት ፕላኔቶች በምሕዋራቸው ላይ የተሳካ ዑደታቸውን እንዲያደረጉ ይረዳል። መሬት ከዙረቷ ቆመች ማለት በምድር ላይ ያለ በሙሉ ወደሕዋ ሊወነጨፍ ነው። በእርግጥ፣ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ከግዑዝ አካል ጋር እየተላተመ ሕይወት የሚባል ነገር አይተርፍም። ምድር መዞር አቆመች ማለት ደግሞ፣ በሂደት የስበት ሕግን በመጣስ ወደፀሐይ መቅረብ ትጀምራለች። የቬኑስን እና የሜርኩሪንም ምሕዋር ጥሳ የማለፍ ዕድል ይኖራታል። ይህን ጊዜ የምድር የሙቀት መጠን ከ50 እስከ 3000 ዲግሪ ሴልሺየስ ይንራል። የምድር መጨረሻም በፀሐይ መዋጥ – የፀሐይ መዋቅራዊ አፈጣጠር በጋዝ የተሞላ በመሆኑ ግጭት ሊፈጠር አይችልም – ይሆናል ። ይህ ግን፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን የሚፈጅ ትንታኔ ነው፤ ምክንያቱም፣ ምድር ከፀሐይ 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ትርቃለች እና። በgeocentric እሳቤ ፀሐይ ብርሃኗን ብትነፍገን ደግሞ፣ የሙቀት መጠን ቀንሶ በቅዝቃዜ ይተካል። ምናልባት፣ በሰው ልጅ ታሪክ ያልታዩ ዐውሎ ንፋሶች የሰው ልጅን ጨምሮ ሌሎች ግዑዝ አካላትን ከወዲያ ወዲህ ሲያንከራትቱ ልናይ እንችላለን። በዓመታት ውስጥም እስከ -100 ዲግሪ ሴልሺየስ ቅዝቃዜ፣ በሚሊዮን ዓመታትም እስከ -240 ድረስ ቅዝቃዜ ሊመዘገብ ይችላል። ለተወሰኑ ዓመታትም የሰው ልጅ ልብስ በመደራረብ እና በጂኦተርማል ሙቀት በመታገዝ ሕይወቱን ሊያቆይ ይችላል።

ወደ ተአምራቱ እንመለስ፦ የነገረ-መለኮት ተንታኞች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ኢያሱ 10:13 በቀጥተኛ ንባብ (literal meaning) የተረዳነው እንደሆነ ያስረዳሉ። የብሉይ ኪዳን ሊቅ የሆኑት Claude Mariottini የቀደመው ዕብራይስጥ ንባብን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል። ፀሐይ ትቆማለች ማለት ብርሃኗን ትርጭ፣ ትስጥ፣ ታብራ ሳይሆን፣ ጀምበር ከመውጣት ትዘግይ፣ ብርሃኗን ትሸሽግ እንደማለት ነውም ይላሉ። አስረጂ ንባቡ ደግሞ፣ ኢያሱ አሞራውያን ለመፋለም የመጣበት ጊዜ ማወቁን አስፈላጊ ያደርገዋል። ኢያሱ በጸሎቱ (10:12) ፀሐይ በገባዖን እንድትቆም፣ ጨረቃም በኤሎን ሸለቆ ላይ እንዲሆኑ ነው የጠየቀው። በዚህ ደግሞ፣ አንድም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡን፣ እንዲሁም የተጠየቀበትን ሰዓት ለማወቅ ያስችላል። እንደየብሉይ ኪዳን ሊቁ John H. Walton፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የካርታ አመራርን (Atlas) በመከተል ገባዖን በምሥራቅ፣ ኤሎም ዠም በምዕራብ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል። ስለሆነም፣ የኢያሱ ጸሎት በጠዋት የተካሄደ ያደርገዋል። አምስት የተባበሩ ነገሥታትን ለመምታት ጨለማን እንደተገን መጠቀም መፈለጉንም ንባቡ ያስረዳል። ይህ ደግሞ፣ ጎሕ እንዳይቀድ መከልከልን ያሳያል። ፀሐይ እንድትቆምም በፈጣሪው እርዳታ ጸለየ፤ ስለሆነም፣ የኢያሱ ጸሎት ጨለማው ይዘገይ ዘንድ እንጂ፣ ፀሐይ ሙሉ ብርሃኗን እንድትሰጥ አልነበረም። አለዚያ’ማ፣ አምስቱ ነገሥታት ባልጠበቁበት እንጂ በተዘጋጁበት ሰዓት አጥቅቶ ለማሸነፍ ሌላ ተአምር በተነበበ።

የመጀመሪያው የፀሐይ ግርዶሽ

የሥነ-ፈለክ ተመራማሪዎች እና ጂኦፊዚስቶች ይህን ቀን በተለየ መንገድ አጥንተውታል። መጽሐፍ ቅዱስ “የመጀመሪያ” ሊባል የሚችልን የፀሐይ ግርዶሽ ሰንዶ እንደያዘ በጥናት ይፋ ለማድረግ ይሞክራሉ። ይህም ጥናታቸው Solar Eclipse of 1207 BCE Helps to Date Pharaohs የተሰኘው ነው።

ግርዶሹ በከንዓን ምድር ላይ ያረፈ ሊሆን እንደሚችል ቀደምት ታሪኮችን እያጣቀሱ በሰነዳቸው ላይ አስፍረውታል። በእርግጥ፣ ሳይንሳዊ ጥናቱ ተአምር ነው ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረውን ታሪክ መቀበል አይፈልጉም። ነገር ግን፣ እንደማስረጃ ይህንኑ የመጽሐፍ ቅዱሱን ምንባብ በመጠቀም ላይ ብቻ ትኩረት አድርገዋል። በጥናታቸው ላይም በዕለቱ annular eclipse የተፈጠረበት በማለት መዝግበውታል።

ዳዊት ቸርነት አሁንም ይዘምራል። ፀሐይዋ ስትቆም ብርሃም እየሰጠች ይሁን ተደብቃ እንደሆነ እሱ ይነግረን ዘንድ አተረጓጎሙን እንጠይቀው። በ”ፍቅር” ዜማው ግን፣ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን (ተአምራት) በስንኝ ቋጥሮ አዝማች ያደርጋቸዋል። ሳይንሱም እንዲሁ እውነታውን ለማግኘት እየደከመ ነው። በእርግጥ፣ cosmology chauvinism እነኝህን ሁለት ወገኖች ለማቀራረብ ጥረቱ በዚያው መጠን ጨምሯል።

እንደመደምደሚያ

ዳዊት በ”ፍቅር” እየዘፈነ ይዘምራል፦
ኢያሪኮ ይፈርሳል ስንመጣበት፣
ውቅያኖስ ይከፈላል ስንራመድ፣
ፀሐይ ትቆማለች ካዘዝናት።
‘ለምን?’ ብትል ምድር፣
ፍቅር ሆነ ምክንያት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top