ስርሆተ ገፅ

ጨዋታ ዜማ ከማርኮን ጋር

ተወልዶ ያደገው ሳሪስ፣ ቀይ አፈር አከባቢ ነው። ገና ከአፍላ እድሜው ጀምሮ እሱ እና ሙዚቃ ተነጣጥለው አያውቁም። በልጅነት በቤት ውስጥ በቆርቆሮ እየቆረቆረ ከመዝፈን አንስቶ፣ ከዚያም በትምህርት ቤት በተለያዩ ክበባት ላይ በመሳተፍ ከሰዎች ፊት ቆሞ መዝፈንን ያኔ ጀመረ። ያውም በህሎ ሀሎ ማይክራፎን! በኣፈር ተደርጎ በድንጋይ በተከበበ መድረክ ተዘጋጅቶ ሁሉ መዝፈኑን ያስታውሳል።

ሙዚቃ ተንከባክባ ብታሳድገውም ወደ በኋላ በኣጋጣሚዎች ለሰባት ዓመታት በዋነኝነት ተወዛዋዥ የነበረ ሲሆን በአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ስር የውዝዋዜ ቡድን መሪ እና አሰልጣኝ እስከመሆን ደርሶ ነበር። ጎን ለጎን እጅግ በተጣበበ ጊዜ ከህይወት ጋር በመሮጥ በዲጀነትም ሰርቷል። በውዝዋዜ በመስራት ላይ ባለበት ጊዜ ድምጻዊው እንደ እናቴ ነበረች የሚላትን የሴቶች ማህበር ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ማንያህልሻልን በመኪና አደጋ ማለፍ ተከትሎ ውዝዋዜን በቃኝ ብሎ ወጥቷል።

ከልጅነት ጀምሮ ጥሪው ለሙዚቃ ነበርና የሕይወት አጋጣሚዎች ከአሁኑ ማናጀሩ ጋር አገናኝተውት በድጋሚ ወደ ሙዚቃ በመመለስ የመጀመሪያ አልበሙን ሕሊና’ን 2010 ዓ.ም ላይ ለሙዚቃ አፍቃሪያን እነሆ ብሏል። በልጅነቱ ያደረበት የሙዚቃ ፍቅር አብሮት አድጎ ዛሬ ላይ ያለው ድምጻዊ ማርኮናል ላይ ደርሷል።

ሕሊና አልበም የተሰራው ከአሀዱ ሪከርድስ ጋር ሲሆን “ቡፌ ደላጋሀር” ከሚለው አንድ ስራ ውጪ ሌሎቹን አስራ ሁለት የሚሆኑ ዘፈኖች ሰርተዋል። አልበሙ ከመውጣቱ በፊት ማርኮን የሚለውን ስም በመተካት “ከኋላዋ” የሚለውን ስራ ቀድሞ በመልቀቅ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ ሙሉ አልበሙ ለሕዝብ ጆሮ በቅቶ በስፋት ተደምጧል።

ድምጻዊ ማርኮናል
  • በሙዚቃውም በውዝዋዜም በስፋት ሰርተህበታል እና ያንተ ልብ በይበልጥ የሚያደላው ወደ የትኛው ነው?

ከልጅነቴም የኔ ፍላጎት ድምጽ ላይ ነው። ግን ሙዚቃው ላይ ያለው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነበር። ከትምህርት ቤት ወደ ወረዳ ስመጣ ሙዚቃ ለመስራት ነበር ግን ያየውትን ነገር አልወደድኩትም ነበር። የትሬኒንግ ስርዓቱ ትክክል አልነበረም፣ ሙዚቃ ላይ የሚደረገው ትኩረት ትክክል አልነበረም፣ በባዶ ቮካል ትሰራለህ እንጂ ስቴጅ አታገኝም። ስለዚህ ነበር ወደ ውዝዋዜው የገባሁት። ባህላዊም፣ ዘመናዊም ዳንስ ሰርቻለሁ። የሀገሬን ባህል፣ ትውፊት በጣም ስለምወድ በርግጥ ብዙ የሰራሁት ባህላዊውን ነው። ሀይለማርያም ከሚባል ወንድሜ ጋር ለሁለት ብቻ ሆነን አምስት መቶ ሰው የሚይዝ አዳራሽ ያን ሁሉ ሰው እናስጮኸው ነበር።

  • ከሙዚቃው አንጻር ስለ ሀገራችን ምን ታስባለህ?

ሀገሬን በጣም ነው የምወደው። የሚገርምህ ከሀገር የመውጣት ብዙ እድሎች ነበሩኝ ግን እኔ መኖር ምፈልገው እዚሁ ነው። ስለሀገር የተሰሩ ሙዚቃዎች በተለይ የጥላሁንን ስራዎች ስሰማ ውስጤን ይነዝረኛል። አንዳንድ ሙዚቃ ለመስራት ወጥቶ ሰርቶ መመለስ ካልሆነ በቀር መኖር ምፈልገው ሀገሬ ላይ ነው። አሁን ላይ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ያሳስበኛል። እንደ ሙዚቀኛ ግን ሕዝቡን ወደ አንድነት የሚያመጡ ስራዎችን ለመስራት እንሞክራለን። ከዘር በላይ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ለማድረግ እንሰራለን። ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ተዟዙሬ ሰርቻለሁ። ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው፣ ብዙ ያልፈታናቸው ነገሩች ኣሉ ብዬ አስባለው። በሙዚቃው ደረጃ ስለ ሀገር፣ ስለ ባህል የተሰራው ስራ በጣም ገና ነው እና ብዙ ልንሰራበት የምንችለው ነገር አለ።

  • የምትወደው ወይም የምታደንቀው አርቲስት ማነው? ለምን?

በጣም የምወደው አረጋኸኝ ወራሽን ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ እሱን እየሰማሁ ነው ያደርኩት። ቤት ውስጥ ወላጆቼ ሙዚቃ ይሰሙ ነበር። አባቴ ገና ሌሊት 12 ሰዓት ተነስቶ የአረጋኸኝ ወራሽ፣ አስቴር አወቀ ወይም የመሰረት በለጠን ሙዚቃ ይከፍት ነበር እና አረጋኸኝ ውስጤ ቀረ ብዬ አስባለሁ። አድጌ እሱን መሆን ሁሉ እፈልግ ነበር።

  • “ቡፌ ደላጋሀር” ስለሚለው ስራህ እናንሳ

የሚገርምህ በኛ እድሜ ያሉ ወጣቶች ስለ ቡፌ ደላጋሀር አያውቁም። ቡፌ ደላጋሀር ማለት ማለት ለገሀር አከባቢ የሚገኝ ክለብ ሲሆን በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ ክለብ ነው። ወይም በሆቴል ደረጃ ከጣይቱ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው ብለህ ልትወስደው ትችላለህ። በጣም ትልቅ ታሪክ ያለው ቤት ነው። እነ ምኒልክ ወስናቸው፣ እነ አለማየሁ እሸቴ፣ እነ አስቴር አወቀ፣ ቴዲ አፍሮን ጨምሮ በርካታ አንጋፋ ሙዚቀኞች እዛ ቤት ሙዚቃ ሰርተዋል። እኛ ድረስ ነበር ማለት ነው ግን መንግስት አሁን አፍርሶታል፣ ሌላ ጥቅም ይገኝበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በጃንሆይ ጊዜ የአፍሪካ ሕብረት ሲመሰረት የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት ያረፉት ጣይቱ እና ቡፌ ደላጋር ነበር። ብዙ ታሪክ የነበረው ቤት እንደመሆኑ የሚጠበቅበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነበር። ያንን ትልቅ ታሪክ ያለውን ቤት ቢያንስ በጥቂቱ ባነሳው ብዬ ነው እሱን ስራ የሰራሁት።

  • ከራስህ ስራዎች ውስጥ አብልጠህ የምትወደው ስራህ የትኛው ነው

ብዙ የምወዳቸው ስራዎች አሉ። በተለይ አልበሜ ውስጥ በግጥም ደረጃ የምወዳቸው ስራዎች አሉ፣ ራሴም ግጥምና ዜማ የሰራሁላቸው ዘፈኖች አሉን ግን በጣም የምትወደው ካልከኝ “ዘውድ ነሽ” የሚለውን ዘፈን እወደዋለሁ። በደንብ ተረድቼው ስለሰራሁት ነው ብዬ አስባለሁ። ብዙ ጊዜ ለሴት ልጅ አይኗን፣ አፍንጫዋን ልታደንቅ ትችላለህ። ግን ለሴት ልጅ ወይም ስለ ፍቅር ከዘውድ በላይ ምንም ልትሰጣት አትችልም። ዘውድ ነሽ ለራሴ ነው የሚለው እና ለእናቴ ነው። እናቴ ለኔ ዘውድ ናት፤ ሁለነገሬ ስለሆነች ማለት ነው። በዛ እይታ ስለምወስደው በጣም እወደዋለሁ።

  • ስለ አልበም ስራው አጫውተን

አልበም መስራት በጣም ከባድ ነው። ከወጪ አንጻር፣ ግጥምና ዜማ ስብስቡ፣ ሌላውን ሌላውን ትተህ ከሀሳብ አንጻህ ምን ሀሳብ ላንሳ? ምን ላይ ልስራ የሚለው ራሱ አስቸጋሪ ነው። ደግሞ ብዙ አንጋፋ እና ወጣት ሙዚቀኞች አሉ። ስለዚህ ፉክክር አለብህ ማለት ነው። የተሻለ ነገር ይዘህ ለመምጣት ትደክማለህ። ብዙ ነገር ነው ያለው።

  • “ከኋላዋ” የሚለው ዘፈን ብዙ አነጋግሯል፣ ቀድመህም በፍጥነት የሰው ጆሮ ያገኘህበት ስራ ነው እና ስለሱ እናውራ

“ከኋላዋ” ከአልበሙ ላይ ቀድሞ የተለቀቀ እና ማርኮንን ማርኮን የሚለውን ስያሜ የሰጠው ስራ ነው። በርግጥ እኛ የሰራንበት ሀሳብ እና ሰዉ በስፋት የተረዳበት መንገድ ትክክል አይደለም። ቢሆንም ግን ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ስራ ነው። በአንድ ወቅት ከቦሌ መገናኛ በታክሲ እየሄድኩ ስድስት ሴቶች ከኋላ ተቀምጠው “ዛሬማ አርቲስት ነው ሚከፍለው” እያሉ ጮክ ብለው እሱን ዘፈን እየዘፈኑ የስድስት ሰው አስከፍለውኛል። ሌሎችም ብዙ አጋጣሚዎች አሉ ከሱ ስራ ጋር በተያያዘ፤ ብቻ እንዳልኩህ የሰራንበት እና ሰው የተረዳበት መንገድ የተለያየ ነው።

  • ማርኮናል አሁን ምን ላይ ነው ያለው? ምንስ እንጠብቅ

ከሁለት ከሦስት ወር በፊት ሰርካለም የሚሉ ስራዎች ሰርቻለሁ። አሁን ላይ ደግሞ በባህላዊም በዘመናዊም ወደ ሦስት ስራዎች ከነክሊፓቸው እየተዘጋጁ ነው። አሁን ላይ የራሴን ቤት ይዤ ክለብም ላይ እየሰራሁ ነው ያለሁት።

  • የባህር ማዶ መስማት እና መከታተል ላይ እንዴት ነህ

እኔ የውጭ ሙዚቃ ላይ ብዙም አይደለሁም። ከዚያ አምጥቼ የመስራት ፍላጎቱም የለኝም። እንዳልኩህ እኔ እንደ አረጋኸኝ አይነት ዘፋኝ መሆን ነው ምርጫዬ። በርግጥ በልጅነቴ የማይክል ጃክሰን ሙዚቃ የነበረበት ሲዲ እና የዘፋኙም ፎቶ ቤት ውስጥ ነበረን። የሱ ስራዎች አሁንም ድራስ ያዝናኑኛል። ከዚያ በተረፈ ግን በስፋት የምሰማው የሀገር ውስጥ ሙዚቃዎችን ነው።

  • በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ሰው ማነው?

የመጀመሪያዋ እናቴ ናት። እናቴን በጣም ነው የምወዳት፣ በጣም ነው የማከብራት። ለሷ የተለየ ነገር አለኝ። እዚህ ደረጃ እንድደርስ ትልቁን መስዋእትነት ከፍላለች። ከዛ በተጨማሪ ቤተሰቦቼ በተለይ እኔ ትኩረት አድርጌ መስመር ሰቶኛል የምለው፥ ዘሪሁን ታደሰ ይባላል፤ አባቴ ነው። በጣም ነው የምወደው፤ በጣም ነው የማከብረው። በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ትምህርት ያስተማረኝ እሱ ነው። ለህይወቴ መሳካት እና ዛሬ ላይ መቆም ለመቻሌ ከእሱ በተማርኳቸው ነገሮች ነው። እና በሕይወቴ ወይም በኑሮዬ ትልቅ ትርጉም የምሰጠው ለሱ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top