ሌሎች አምዶች

ዘሚ ዩኑስ – ሰው የመሆን ናሙና

ግንቦት 3፣ 2013 ዓ.ም

በተፈጥሮዬ በጣም ከምመሰጥባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሰው ልጅ ሥነ-ልቦና ጥናት ቀዳሚው ነው፡፡ በተለይ፣ አብኖርማል ሳይኮሎጂ እና ቻየልድ ሳይኮሎጂ ቀልቤን በጣም ይስቡታል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይም ከታሪክ፣ አርኪዮሎጂ እና መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ብዙ የንባብ እና የጥናት ጊዜያትን ያሳለፍኩ ይመስለኛል፡፡

በአብኖርማል ሳይኮሎጂ ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኦቲዝም ጋር የተዋወቅኩት በልጅነቴ ስለጠንካራ ሴቶች ከሚያወሳ አንድ “የቢግነርስ ኢንግሊሽ” ተከታታይ መጽሐፍ ላይ ነበር፡፡ መጽሐፉ ስለአስደናቂ ሴቶች ሲያነሣ ከሄለን ኬለር፣ ሮዛ ፓርክስ እና ጄን ጉድኦል ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ ቴምፕል ግራዲን የተባለች አንዲት ልዩ ሴት ይጠቅሳል፡፡ ግራዲን ኦቲስቲክ ሴት ናት፡፡ በተለምዶ “ስቫንት” በመባል ከሚታወቁት ባለልዩ ተሰጥኦ ኦቲስቲኮች መካከል ትመደባለች፡፡ በእንስሳት ባባሕርይ እና ጤና በኩል ያገኘቻቸው አስደማሚ ግኝቶች ዛሬም ድረስ ዓለምን ትንግርት የሚያሰኙ ናቸው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በስሟ የተሰየመ አንድ ፊቸር ፊልም ሳገኝ የልጅነት ጀግኒቴን ስላስታወሰኝ በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር የተመለከትኩት፡፡ በወቅቱ የተሰማኝን የደስታ ስሜት የማካፍለው የቅርብ ሰው አጥቼ፣ የሚያውቃት ሰው ካለ የልቤን ምት ይካፈልልኝ ዘንድ በፌስቡክ አካፍዬ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ አልተሳካልኝም፡፡

ከቴምፕል ግራዲን ቀጥሎ ደግሞ፣ አሁንም ልጅ እያለሁ “ሬይንማን” በተሰኘው ፊልም ውስጥ ደስቲን ሆፍማን “ኪም ፒት” የተባለ ትንግርታዊ ሰው ወክሎ የሚጫወትበትን ፊልም በኢቲቪ ታላቅ ፊልም ተመለከትኩ፡፡ ኪም ፒት በቅጽል ስሙ “ኮምፒውተር” እየተባለ የሚጠራ ኦቲስቲክ ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት ላይ ያነበበውን ነገር ሁሉ ገጽ እንኳን ሳያዛንፍ በቃሉ ያስታውሳል፤ የሰማቸውን የአደጋ ዜናዎች በሙሉ ከእነዝርዝራቸው ያስታውሳል፡፡ በአንድ ዐይኑ አንድ ገጽ፣ በሌላኛው ዓይኑም ሌላ ገጽ ማንበብ ይችላል፤ ሌላም ሌላም፡፡ በቀጣይነት ደግሞ፣ በቪ.ኤች.ኤስ. ቪዲዮ ዘመን ሾን ፔን የተወነበትን “አይ አም ሳም” የተሰኘ ፊልም አስታውሳለሁ፡፡ ሳም ኦቲስቲክ ገጸ-ባሕርይ ሲሆን፣ አስገራሚ ዕውቀት፣ ንጹሕ ልብ እና ፍጹም ታማኝ ሰብእና ያለው ሰው ነው፡፡ ብዙዎቹ ኦቲስቲኮች የዚህ ዓይነት ማንነት አላቸው፡፡

ስለኦቲዝም ወደማጥናት የገባሁት እና የበለጠ ግንዛቤ ማግኘት የጀመርኩት ግን፣ ታላቅ እኅቴ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ስለዘሚ የኑስ ልብ የሚያሞቅ ታሪክ ከነገረችኝ በኋላ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እኔም አድጌ፣ ዘመኑም ሠልጥኖ ስለነበር በቀጥታ ስለኦቲዝም ጉግል ማድረግ፣ መጻሕፍትም መግዛት ጀመርኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ዘሚን የማግኘት ፍላጎቴ በጣም አደገ፡፡ በዚህም አስገራሚዋን እናት በወቅቱ በቅሎ ቤት አካባቢ ከሚገኘው ቢሮዋ ድረስ ሄጄ ተዋወቅኳት፡፡ ከልብ የሆነ አድናቆቴን እና ክብሬንም ገለጽኩላት፡፡ በጊዜው በፊልም ሙያ ውስጥ ስለነበርኩ በዚያ ጉዳይ ዙሪያም በስፋት አወራን፡፡ ዘሚ አስተዋይ እና ጠንካራ ሴት ብቻ ሳትሆን፣ ሽንገላ የማይገባት የፊት ለፊት ሴት ሆና ነበር ያገኘኋት፡፡ ጥሎብኝ የዚህ ዓይነት ሰብእና ነፍሴ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መልሼ ባላገኛትም፣ ዘሚ ከልቤ ወጥታ አታውቅም፡፡

ዛሬ ስለኦቲዝምም ሆነ በአጠቃላይ ስለ አብኖርማል ሳይኮሎጂ እና ቻይልድ ሳይኮሎጂ ያለኝ ግንዛቤ በጣም አድጓል፡፡ ያለማጋነን፣ ፈረንጆቹ “ጊኪ” በሚሉት ደረጃ ኦቲዝምን ጨምሮ ስለበርካታ ፐርሰናሊቲ ዲስኦርደሮች ሰፊ ግንዛቤ አለኝ ማለት እችላለሁ፡፡ ከንባብ ባሻገር ለራሴ በምፈጥራቸው ዕድሎች ጥቂት የማይባሉ ኦቲስቲክ ልጆችን በአካል አግኝቼ አይቻለሁ፡፡ በዚህም ኦቲስቲክ ልጆችን ማሳደግ ምን ያህል ከባድ፣ ፈታኝ እና እልኽ አስጨራሽ እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ልጆቹን ስመለከት የወላጆቹ ከምንም በላይ የሆነ ድካም ወደአእምሮዬ ይመጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ እግዚአብሔር እነዚህን ወላጆች ምን ያህል እንደሚወዳቸው አስባለሁ፡፡

ወላጆች ከእነዚህ ውድ ፍጡራን ጋር ካላቸው የዕለት ተዕለት ግንኙነት የተነሣ ከሌሎቻችን በበለጠ ሁኔታ በአእምሮ እና በመንፈስ ጠንካራ እንደሚሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ለዚህም ነው፣ ብዙ ጊዜ ከኦቲስቲክ ልጆች ወላጆች ጋር ሳወራ “You are a very lucky person, because an autistic child makes the best out of you” የምለው፡፡ ዘሚ በዚህ መልኩ ታንጸው የወጡ ወርቅ ሰብእናዎች ሁሉ ተምሳሌት ሳትሆን አትቀርም፡፡ በተጨባጭም፣ ዘሚ ከራሷ አልፋ ለሌሎች “የማይቻለው” እንደሚቻል በተግባር ያሳየች ጠንካራ ሴት ናት፡፡ ብዙዎች እንደእርግማን የቆጠሩትን ክስተት በጸጋ ከመቀበል አልፈው የማይገኝ በረከት መሆኑን በመረዳት ያከብሩት ዘንድ ያስቻለች የሥነ-ልቦና መሃንዲስ ናት፡፡ ከሁሉም አስበልጦ ደግሞ፣ ተቋም ገንብታ የበርካታ ወላጆችን የአካል እና የአእምሮ ድካም መካፈል የቻለች ሰው የመሆን ናሙና ናት፡፡

በግሌ እግዚአብሔር በኦቲዝም ውስጥ ተነግሮ የማያልቅ አንዳች ምሥጢር ለሰው ልጆች ሁሉ ከውኖ እንዳስቀመጠ አምናለሁ፡፡ ይህን ምሥጢር ተንትኖ መረዳት እና ማስረዳት የሰዎችንም ሕይወት መቀየር ታላቅ በረከት አለበት፡፡ ዘሚ የኑስ ስለሮጥሽው መልካም ሩጫ ከማመስገን በስተቀር ከቶ ምን እንላለን!

ፈጣሪ ነፍስሽን በአጸደ-ገነት ያኑርልን፡፡

የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ሁሉ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ፡፡ ውዳችንን ምን እንደነጠቀን አንዘንጋ፡፡

አሸናፊ ፈንቴ (አዲስ አበባ)

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top