ታዛ ስፖርት

ከምኒሊክ በኋላ

በ1989 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሞሮኮን ለመግጠም ጉዞ ጀመረ፡፡ ጣሊያን ትራንዚት አደረገ፡፡ተጫዋቾቹ ሮም አውሮፕላን ማረፊያ ለ18 ሰዓታት እንደሚቆዩ ተነገራቸው፡፡ በዚያ የነበሩትን መንገደኞች ፖሊስ በድምፅ ማጉያ ወደሆቴል እንዲሄዱ ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡ ቡድን መሪውና አሠልጣኞቹ ልጆቹን ምን ማድረግ እንደሚገባቸው መነጋገር ጀመሩ፡፡ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡድን ወደሰሜን አፍሪካ ሲጓዝ ጣሊያን ትራንዚት ሲያደርግ የተጫዋች የመኮበለል አጋጣሚ ይፈጠር ነበር፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት እዚህ ሮም ውስጥ 16 ተጫዋቾች ተገኙ፡፡ ከአውሮፕላን ማረፊያ ወጥተው መኝታ ያዙላቸው፡፡ ጠዋት ወደአውቶብስ ሲገቡ 6 ተጫዋቾች በመጥፋታቸው ቡድኑ 10 ሰው ብቻ ወደሞሮኮ ይዞ ለመሄድ በመገደዱ በሰው እጥረት አሠልጣኙ እስከመሰለፍ ደርሶ ነበር፡፡ አሁን በሮም አውሮፕላን ማረፊያው ምክክር የሚያደርጉት ቡድን መሪውና አሠልጣኙ የትናንቱን ኩብለላ እያሰቡ ‹‹እንዴት እናድርግ?››በሚል ተወያዩ፡፡

ተጫዋቾቹንም ደጋግመው ተመለከቷቸውና አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ “እዚህ 18 ሰዓት መቆየቱ አስቸጋሪ ነው” ብለው ተነጋገሩ፡፡ ምክንያቱም “ደረቅ ወንበር ላይ ተኝተው መጫወት አይችሉም” ብለው አመኑ፡፡ ልጆቹን ደጋግመው ሲያዩዋቸው ጨዋ ሆኑባቸው፡፡ በመጨረሻም፣ ይዘዋቸው ከግቢው ሊወጡ ወሰኑ፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው አጠገብ ‹ፓላስ› ሆቴል ወስደው መኝታ ያዙላቸው፡፡ ፓስፖርታቸው ግን፣ በቡድን መሪው እጅ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ የሆቴሉ ኃላፊ ቡድን መሪውን ጠራውና፣ ‹‹ፓስፖርቱን አምጣ›› አለው።
‹‹ለምን?››
‹‹እኛ ጋር ይቀመጥ።››
‹‹አይሆንም።››
‹‹ለምን?››
‹‹ችግር አለ።››
‹‹እንግዲያውስ፣ ልጆቹን ይዘህ ሂድ።››
‹‹ምንድን ነው ነገሩ?››
‹‹ፓስፖርት ካልሰጠኸኝ አታድሩም።››
‹‹እንዴት?››
‹‹የሀገሪቱ ሕግ ነው።››

ቡድን መሪው ግራ ተጋባ፤ ‹‹ይሄ ሰውዬ በማስገደደድ ፓስፖርቱን ከእኔ ተቀብሎ ለልጆቹ ሊያድል ነው እንዴ? ›› ብሎ ሠጋ፡፡ ኃላፊው ግን፣ ‹‹ፓስፖርቱ እንግዳ መቀበያ ክፍል ይሆናል፡፡ ስትወጡ ላንተ እናስረክብሃልን›› ይለዋል፡፡ እንዴት እንደሆነ ባይታወቅም፣ አንድ ተጫዋች ይሄን ንግግራቸውን ይሰማና ወደክፍል ሄዶ ተኛ፡፡

የእንግዳ መቀበያ ክፍል ኃላፊው ፓስፖርቱን መዝግቦ ጠዋት እንደሚሰጠው ነገረው፡፡ ቡድን መሪው ግን፣ “እኔ ካረፈድኩ ለምክትል አሠልጣኙ ስጠው” በሚለው ተስማሙ፡፡ ከምክትሉ ሌላ ለማንም ሰው መስጠት እንደሌለበት አስረግጠው ተነጋግረዋል፡፡ በተለይ፣ ማንም ተጫዋች መጥቶ ቢጠይቅ መስጠት እንደሌለባቸውና ቢሰጡ ሆቴሉ ተጠያቂ እንደሚሆን አሳወቋቸው፡፡ ሌላም ነገር አለው፤ ‹‹ተጫዋች ከጠየቀህ፣ ማንነቱን ለኔ ትነግረኛለህ›› አለው፡፡ ፓስፖርት የሚጠይቅ ተጫዋች የሚጠፋ እንደሆነ ያውቃል፡፡ ስሙን መዝግቦ በቀጣዩ ለብሔራዊ ቡድን እንዳይመረጥ ሪፖርት ያደርጋል፡፡

ፈረቃውን የጨረሰው የእንግዳ መቀበያ ክፍል ኃላፊው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ለተረኛው አስረከበና ወደቤቱ ሄደ፡፡ ፓስፖርቱ እንግዳ መቀበያ ክፍል መቀመጡን ያየው ተጫዋች ለጓደኞቹ ሁኔታውን ነግሮ ተቀያሪው ቦታውን ሲይዝ የተወሰኑት አድፍጠው መጡና ቡና ቤት ውስጥ መንጎራደድ ጀመሩ፡፡ ለሙከራ አንዱ ተጫዋች፣ “ፓስፖርቴን አምጣ” አለው። እንግዳ መቀበያ ክፍል ያለው ሰው የተጫዋቹን ስም ጠየቀው፡፡ ፓስፖርቱን አወጣና ፎቶውን አየው። በእርግጥም የእርሱ ነው፡፡ አቀበለው፡፡ ልጁ ተረጋግቶ ወደውጭ ወጣ ፡፡

ፈረቃውን የጨረሰው ሰው ለተረካቢው ፓስፖርቱን ለማን ማስረከብ እንዳለበት ስላልነገረው ልጁ ሲጠይቀው ያለምንም ጥርጣሬና ማንገራገር ነው የሰጠው፡፡ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ፓስፖርት ሲታደል በማየታቸው ሁሉም ከመኝታው እየተነሣ ከልካይ ከመምጣቱ በፊት ሌሎችም ለመውሰድ መሯሯጥ ጀመሩ፡፡ ከዚያም ሁለትና ሦስት እየሆኑ በመምጣት እየተቀበሉ መውጣት ጀመሩ፡፡ አልጋ ከያዙት 18 ተጫዋች ውስጥ የተወሰኑት ብቻ ሆቴል ውስጥ ቀሩ፡፡

ጠዋት ቁርስ እንዲበሉ ቡድን መሪው በየክፍሉ እየገባ ሊቀሰቅስ በር ሲከፍት መኝታ ላይ አንድም ሰው አጣ፡፡ ‘ከተማውን ለማየት ወደውጭ ወጥተዋል’ ብሎ ስለገመተ ወደዚያው ሄደ፡፡ ለማንኛውም ፓስፖርቱን ልያዝ ብሎ እንግዳ መቀበያ ክፍል ሲጠይቅ ያገኘው የሁለት ተጫዋቾች ብቻ ነበር፡፡ ነገሩ በጣም አስደነገጠው፡፡ቡድን መሪው ተጫዋቾቹ መጥፋታቸውን ስላረጋገጠ እንዲያዙለት ለፖሊስ አመለከተ፡፡ ፖሊሶችም በአጭር ጊዜ በጣሊያንኛ የተጻፈ ወረቀት አመጡና ለቡድን መሪው፣ “እንካ ይሄን” አሉት።
‹‹ምንድን ነው እሱ?››
‹‹እዚህ ላይ ፈርም።››
‹‹ጣሊያንኛ አልችልም።››
‹‹እና?!››
‹‹እንግሊዝኛ አድርግልኝ።››
‹‹የጠፉት እኮ እንግሊዝ ሀገር አይደለም።››
‹‹ቢሆንስ?››
‹‹ሮም ስለጠፉ በጣሊያንኛ ነው ደንቡ የሚዘጋጀው።››

ቡድን መሪው ወረቀቱ ላይ ያለውን ጽሑፍ አየው፡፡ ቋንቋውና ሰውዬው አይተዋወቁም፡፡ ቡድን መሪው ከወረቀቱ ጋር ተፋጠጠ፡፡ ከዚያም ወደእንግሊዝኛ ካላስተረጎሙለት እንደማይፈርም ነገራቸው፡፡ እነርሱም “እምቢ” አሉት፡፡ ቡድን መሪው ወረቀቱን እንደገና ተቀበለ፡፡ ገጹ ብዙ ነው፡፡ አሁንም ከወረቀቱ ጋር ተያዩ። ምኑም ሊገባው አልቻለም፡፡

ወረቀቱ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ምን እንደሆን ሳያውቅ መፈረሙ ትክክል እንደማይሆን አምኗል፡፡ ባይፈርም ደግሞ፣ ፖሊስ ልጆቹን እንደማይዝለት አውቋል፡፡ ወረቀቱን ተቀበለና እንዲህ ብሎ አሰበ፤ ‘እነዚህ ጣሊያኖች ዐጼ ምኒሊክን በውጫሌ ውል ላይ በተሳሳተ መንገድ አስፈርመው ችግር ፈጥረዋል፡፡ አሁንም እኔን አሳስተውኝ ጉድ ቢያደርጉኝስ?” ‹‹እንዲያውም፣ በእንግሊዝኛ ሳይሆን በአማርኛ አስተርጉማችሁ ካላመጣችሁ አልፈርም›› አለ፡፡

ፖሊሱም ተናደደና፣ “ካልፈረምክ እሄዳለሁ” ብሎ ከወንበሩ ተነሥቶ ሊሄድ ሲል ቡድን መሪው፣ ‹‹በቃ!! እሺ፣ አምጣው›› ብሎ ሊፈርም ተስማማ፡፡ ለመፈረም እስኪሪብቶ አወጣ። እንዲህ ብሎም በአማርኛ ጻፈ፤ ‹‹እኔ በማላውቀውና ምንነቱን ባልተረዳሁት ነገር ተገድጄ ፈርሜያለሁ›› ብሎ ጻፈና ፈረመ፡፡ ፖሊሱም የተጻፈው ስለረዘመበት፣ ‹‹ጻፍ እኮ አይደለም ያልኩህ›› አለው።
‹‹እና?!››
‹‹ፈርም ነው ያልኩህ።››
‹‹ፊርማ እኮ ነው።››
‹‹ቃላቱ በዛ ምንድን ነው?››
‹‹ስሜ ነው።››
‹‹ይሄ ሁሉ?››
“የእኔ፣ የአባቴ፣ የአያቴና የቅድመ-አያቴ ስም ነው፡፡”
በሆዱ ደግሞ፣ እንዲህ አለ፤ ‹‹ቅድመ-አያቴና ቅድመ-አያትህ ደግሞ ይተዋቃሉ…››

ፖሊሱም እየተጠራጠረ ወረቀቱን ይዞ ሄደ፡፡ ስድስት ተጫዋቾች “እንመለሳለን” ስላሉ ቡድን መሪው መግለጫ ሊሰጥ ጋዜጠኞችን ጠራ፡፡ ሆኖም፣ የተገኙት አምስት ብቻ ነበሩ፡፡ ተጫዋቾቹ የጠፉ ቀን መግለጫ ሲሰጥ ከ100 በላይ ጋዜጠኞች ነው የመጡት። ‹‹ለካ፣ ዜና የሚሆነው መመለሳቸው ሳይሆን፣ መጥፋታቸው ነው›› በሚል የጋዜጠኞቹ መቅረት ምክንያቱ ይሄ ነው ብሎ ደመደመ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top