ሌሎች አምዶች

አንዳንድ ነጥቦች ስለሕግ የበላይነትና የሕግ ገዢነት

መግቢያ

“ከቃላት ድርብና አሻሚ ትርጉም መያዝ የበለጠ ለዕውቀት ማደግና መስፋፋት ትልቅ ዕንቅፋት የሆነ ነገር የለም” – ቶማስ ሬይድ

ስለማንኛውም ፅንሰ-ሐሳብ (በተለይም ስለሕግ) ተገቢው መረዳት ከሌለን ወይም ግንዛቤያችን የጠራ ካልሆነ፣ እንደዜጋ ማግኘት የሚገባንን የተደነገገ ጥቅም ልናጣ እንችላለን፣ ወይም ፅንሰ-ሐሳቡ እንድናደርግ ያዘዘውን ባለመፈጸም፣ የሚከለክለውን በመጣስ ተጠያቂ እንሆናለን፡፡ በዚህ ጉዳይ እየተደነጋገርን ሌሎችንም ማደነጋገር ጉዳት አለው:: ብዙ ሰዎች ምንነታቸውን በሚገባ ሳይረዱ ስለተጠቀሙባቸው ብቻ እኛም ትክክለኛ እንደሆኑ ወስደን መጠቀማችን መቅረት አለበት፡፡ ስለማንኛውም ጉዳይ በልማድና እንዲሁ በመደዴ ተቀብለን ማንጸባረቅ ሳይሆን ባለሙያዎችና ዐዋቂዎች በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ የምናገኛቸውን ማብራሪያዎች መመልከት እጀግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ “የተማሩና ዐዋቂዎች” የተባሉ ጭምር በአግባቡ ሳይሆን በልማድ እንጠቀምባቸው ከነበሩት ፅንሰ-ሐሳቦች አንዱን እንደምሳሌ እንውሰድ፡፡ በግልም ሆነ በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት በሥራው ዓለም በመስክ ተሰማርተው ተግባራዊ ልምድ እንዲያገኙ ታሰቦ የንድፈ-ሐሳብ ዕውቀታቸውን በተግባር ለማበልጸግ እንዲችሉ “apparentship” ይወጡ ነበር፡፡ ይህን ቃል መምህራንም (ፕሮፌሰሮችንም ጨምሮ) ሆኑ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተማሪዎች ትርጉሙ ምን እንደሆነ ሳይረዱ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ Apparentship የሚለው ቃል ይወክላል ተብሎ የተወሰደው በትምህርትም በተግባራዊ ልምድም የካበተ ሙያዊ ክህሎት ካላቸው ሰዎችና ድርጅቶች ሥር ተጠግቶ ሙያ ለመቅሰም የሚያስችለውን ተግባራዊ ትምህርትና ሥልጠና የሚያመለክተውን apprenticeship (experiential learning) ትርጉም ይመስላል፡፡ ነገር ግን፣ apprenticeship በተጠቀሰው ትርጉሙ በሁሉም የእንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላት እና ኤንሳይከሎፒዲያ ውስጥ ይገኛል፤ apparentship የሚል ቃል ግን የለም፡፡ በመጥፎ ምሳሌ ነገር መጀመር ባይወደድም፣ እያደገ የመጣውን ችግር ለመፍታትና ቆም ብሎ ለማሰብ በጥቂቱም ቢሆን ይጠቅመናል፡፡

የዚህች ጽሑፍ ዓላማ የጠለቀና የመጠቀ የሕግ ትርጉምና ትንታኔ ማቅረብ አይደለም – ይህን ማድረግ የሚችሉ (ከፈቀዱም ሊያቀርቡልንና ሊያሰተምሩን የሚገባቸው) እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ የእኔ ውስን ዓላማ እንደአንድ ዜጋ (ትንሽም ብትሆን የተማረ ዜጋ) ስለጉዳዩ የሚያስተውለውን መደነጋገርና ከዚህ ጋር የሚመጡ ብዥታዎችን ማስተካከል እንዲቻል ለውይይት መጀመሪያ ጥቂት ሐሳቦችን ማንሣት ብቻ ነው፡፡ የሠለጠነ በሚባለው ዓለም ተቀባይነት ያላቸውን (እየተተገበሩም ያሉትን) መርሆዎችና ፅንሰ-ሐሳቦች ተረድተን ልንጠቀምባቸው ይገባናል፡፡ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የተለያዩትን ሐሳቦችና ጉዳዮች አንድ እንደሆኑ በመቁጠር የፅንሰ-ሐሳቦቹን መሠረታዊ ምንነት ተረድተን ሳይሆን ብዙዎች ስለደጋገሙት ብቻ ተቀብለን ማንጸባረቃችን መለወጥ ይገባዋል፡፡ ቁልፍ የሆኑ፣ ነገር ግን ትክክለኛ ትርጉማቸው ምን እንደሆነ ያልተገለጠ/የደበዘዘ አባባሎቻችን እየጐዱን እንጂ እየጠቀሙን አይደለም፡፡ ጋዜጠኛው፣ ፖለቲከኛው፣ ስሜተኛው… ወዘተ. የተመካከሩ/የተመከሩ ይመስል ስለአንዳንድ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳች አስተያየት እንዲሰጡ ሲጠየቁ የሁሉም ዕውቀትና የነገሮች ትርጉሞች ብዙም አይራራቁም፡፡ ልሂቃኑም ሊቃውንቱም ቦታቸውን የሚመጥን የጠራ ግንዛቤና ዕውቀት እየሰጡን አይደለም፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ጥልቀትና ጥራት ያነሰው መደዴና ግርድፍ ንግግር ይጠቅመናልን? “የሐሳብ ልዕልና ይኑር” እየተባለ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንኳ የሚታየው የግንዛቤያችን ጥራት ማጣት ለምንሰማም ለሚሰሙንም አንዳች ትርጉምና ተገቢ መረዳት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡

ሕግ ምንድነው?

በዕውቀትና ግንዛቤ ጥራት ላይ የተመሠረተ ሕይወት ለመኖር መሰል ጥያቄዎችን ማንሣትና መልስ መፈለግ ተገቢና መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቻችን የማንወደው/የማንፈልገው/የማንፈቅደው ተግባር ወይም ድርጊት ሊፈጸም ሲል በተለምዶ “በሕግ/በሕግ አምላክ… ወዘ” አንላለን፡፡ ይህም አባባል ሊፈጸም የታሰበው ድርጊት ሕግ የሚከለክለው እንደሆነ ከማመን፣ ከተፈጸመም ሕጉ የሚሰጠው ቅጣት እንዳለ፣ አሊያም ለሕግ መገዛት ከተተወ እያንዳንዱና ሁሉም ሰው የሚወስደው እርምጃ እንዳለ (ሁሉም የራሱ ዳኛ የሚሆንበት ሁኔታ እንደሚፈጠር) የሚያመለክት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በሕግ አለመመራትና ሕግ ዐቅም ያጣበት ሁኔታ ደግሞ፣ ከሥልጣኔ መውጣትን ወይም “ሰው ያለሕግ ከሆነ አውሬ ነው” ወደሚለው ይወስዳል፡፡ ስለዚህ፣ “ሕግ ምንድን ነው?” የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ስለሚሆን ከሙያው ምሁራን መውሰድ ግድ ይሆናል፡፡ Black’s Law Dictionary (8ኛ እትም )፡- “ሕግ ማለት የአንድን ኅብረተሰብ ሰዋዊ እንቅስቃሴዎችና ግንኙነቶች ሥርዓት ያላቸው እንዲሆኑ የሚያደርግ፣ ይህም ሕግ ራሱ በመልኩ የተቀነባበረና ሀ)በፖለቲካ የተደራጀ ኅብረተሰብ ውስጥ ባለው ኃይል በሚታወቅ ሥርዓትና መንገድ የሚተገበር፤ ለ) ከበጎ ማኅበራዊ ተጽእኖ የተነሣ ሰዎች ተቀብለው የሚመሩበትና ሐ) በመጨረሻም፣ ሕግ በእርግጥ ሕግ ለመሆኑ መለያው በአስገዳጅ ጉልበት (coercive force) የመጨረሻ አማራጭነት የሚተገበር/ሥራ ላይ የሚውል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ፣ ሕግ ማለት፡-
1. ሕግ ለማውጣት ሥልጣን ባለው/በተሰጠው አካል መሠረታዊውን የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ተከትሎ የተቀረጸና የጸደቀ፣
2. ለሁሉም ዓይነት ግለሰቦችና ቡድኖች ባለማዳላት መሠረታዊ መብቶችንና ግዴታዎችን የሚያካትት፤ በመፍቀድና ክልከላ ለሁሉም እኩልነትን የሚያረጋግጥ፣
3. ሁሉም ዜጎች እንዲያውቁትና ሊረዱት በሚችሉት አግባብ በግልጽና በስፋት የታወጀ፣
4. አስፈላጊነቱን ተረድተው ዜጎች የተቀበሉትና የሚመሩበት፣ የሚተዳደሩበት አጠቃላይ መተዳደሪያ የሆነ፣ እንዲሁም
5. ሕጉ ለግለሰቦች የሰጠው መብት ሲጣስ የማስተካከያ መንገዶችን ያካተተና ፍትሐዊነት የሚሰፍንበትን መንገድ በግልጽ ያስቀመጠ ሥርዓትና መርህ ነው፡፡

የሕግ አስፈላጊነትና ዓላማ

የሕግን አስፈላጊነትና ጥቅም ሰዎች ሁሉ በየግላቸው በተመሳሳይ ደረጃ ይቀበሉታል ተብሎ አይታመንም፡፡ የማይፈልጉት ብዙም ሆኑ ጥቂት የሕግ አለመኖር ወይም የነበረውን ሕግ ማክበርና ማስከበር የማይቻልበት ሁኔታ ሲከሰት ከሚፈጠረው ቀውስ የተነሣ ተወደደም ተጠላም የሕግ ጠቃሚነትና የማይታለፍ አስፈላጊነት ከመቼውም በላይ ያኔ ጎልቶ ይወጣል፡፡ ታዋቂው የጥንታዊት ግሪክ ፈላስፋ አሪስቶትል (አሪስጣጣሊስ)፣ “ሰው መሆን በሚገባው ሁኔታ ሲገኝ እጅግ የላቀና የከበረ ነው፤ ከሕግና ፍትሕ ከተለየ ግን፣ እጅግ የከፋ ይሆናል” ይለናል፡፡ የመንግሥትና ሕግ አመጣጥ “በኮንትራት” ፍልስፍና ቀማሪና ጀማሪ ቶማሰ ሆብስ (Thomas Hobbes) የመንግሥትንና የሕግን አስፈላጊነት ሲገልጽ ሰዎች ከመንግሥትና ከሕግ በፊት የነበሩበትን ዘግናኝ ኑሮ “የሁሉም ጦርነት በሁሉም ላይ” (The war of all against all) በማለት ገልጾታል፡፡ ስለዚህ፣ የግለሰቦች፣ የማኅበራትና የኅብረተሰብ ጤናማ መስተጋብሮችና ግንኙነቶች ከግጭት፣ ከቀውስና ከሥርዓት-የለሽነት የነጹና የተጠበቁ እንዲሆኑ፣ ሰዉ ሁሉ እንደሰው እንዲኖር ከተፈለገ፣ የሕግ ፍጹም ጠቃሚነትና አስፈላጊነት አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ከላይ በአጭሩ የተጠቀሰው ከሆነ፣ መልካምና ተፈላጊ የተባለ ሕግ ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን ክቡር ግቡን ለማሳካት ብቃት እንዲኖረው የሚከተሉትን መመዘኛዎች በአግባቡ ማለፍ ይገባዋል፡፡
1. የግለሰቦችን መብቶችና ነጻነቶች ከማኅበረሰብ የጋራ መልካም ጥቅሞች ጋር በሚገባ ያገናዘበና ያጣጣመ መሆን ይኖርበታል፡፡
2. በጥበቃ፣ በመቅጣት፣ በአጠቃላይ በፍትሕ አሰጣጥ ያለአንዳች ልዩነት ሕግ ለሁሉም እኩልነትን ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡
3. በመፍቀድ፣ በክልከላና በሌሎች ድንጋጌዎቹ ሁሉ ግልጽና የማያሻማ ትርጉም ያለውና ዜጎች በግልጽ ያወቁት መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በውስጣዊ ድንጋጌዎቹም ወጥነት ያለው (internal consistency) መሆን ይገባዋል፡፡
4. በሕግነቱ ሊተገበር የሚችል መሆን አለበት፡፡ ምክንያታዊ ያልሆነ፣ በጣም የላላ ወይም ከሚገባው በላይ የጠበቀና የጠነከረ፣ የማያንቀሳቀስና አፋኝ ከሆነ፣ ሰዎች ሊታዘዙት/ሊገዙለት አይችሉም፡፡ ስለዚህ፣ ከእንዲህ ዓይነት ባሕርያት የጸዳ ሊሆን ግድ ነው፡፡
5. ማኅበራዊ/ሰዋዊ ሕግ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ መለወጥ/መሻሻል የሚችል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን፣ ትናንሽ ግፊቶች ሲመጡና ሁሉን በማይወክሉ ጥቂቶች ፍላጎት የሚናድና ያልተረጋጋ (unstable) መሆን የለበትም፡፡
6. ሲተገበርም ሆነ ድንጋጌዎቹ ሲጣሱ ቅጣት በሚሰጥበት የአካሄድ ሥርዓቶች የማያወላውልና የጸና (rigorous) መሆን አለበት::
7. አንድ ሕግ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ፣ በግብረ-ገባዊ ይዘቱ ጠንካራ መሆን ይገባዋል፡፡ ከኅብረተሰቡ ልዩ ልዩ ሥር የሰደዱ መልካም እምነቶችና እሴቶች ጋር የሚጋጭ፣ ፍትሐዊነቱ ጐዶሎ ከሆነ፣ “ሕግ” መባልም አይችልም፡፡
8. ማንኛውም ሕግ በሕግነት ከወጣበትና ከተደነገገበት ወቅት ጀምሮ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር እንጂ ስላለፈ ጉዳይ የሚናገርና ቀድሞ የተፈጸመ በደልን/ጥፋትን ለመቅጣት ያለመ ሊሆን አይገባም፡፡
9. ሕግ ፍትሕን፣ እኩልነትን፣ ግብረ-ገባዊነትን፣ ሰላማዊ ኑሮን የሚያራምድና የሚያሳድግ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሕንዳዊው መሪና ፈላስፋ ሞሃንዳስ ካራምቻንድ (ማህተማ) ጋንዲ እንዳለው፣ “ፍትሐዊ ያልሆነ ሕግ ዝርያው ዐመፅ ነው፡፡” – “An unjust law is itself a species of violence.”

ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ምንነት፣ ዓላማና ጥቅም ከተረዳን፣ ሕጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ኅብረተሰቡና መንግሥት የሚገዙበት/የሚተዳደሩበት/የሚመሩበት ለመሆን መመዘኛዎቹንም በሚገባ ካሟላ፣ አንዱና ፈጽሞ የማይታለፍ ባሕርይው የበላይነቱ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት

በዜግነታችን በሕግና ሕጋዊነት ለመጠቀም እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መርሆዎች አንዱና ዋነኛው የሕግ የበላይነት መኖርና መሥራት ነው፡፡ ግን፣ የሕግ የበላይነት ምንድን ነው? የሕግ የበላይነት ንግግርና እውነታ (rhetoric and reality) ምን ያህል ይቀራረባሉ? ስለሕግ የበላይነት በቂና ተገቢ ዕውቀትና ግንዛቤ ያለን ስንቶቻችን ነን? ቀደም ሲል የሕግ የበላይነትንና የሕግ ገዢነትን (supremacy of law and rule of law) አንድነትና ልዩነት ምን ያህል ተገንዝበናል? ስለዚህ ከባድና መሠረታዊ ጉዳይ በተለምዶ ከምንሰጠው አስተያየት ይልቅ በሙያውም ሆነ በዕውቀታቸው የተሻሉና የበሰሉ ሰዎች (ከቀደሙትም ሆነ አሁን ካሉት) ማብራሪያ መሻትና መማር ተገቢ ይሆናል፡፡ በየዘመኑና በየሀገራቱ በነበሩት የሕግጋት ሥርዓቶች መካከል ልዩነቶች ነበሩ/አሉም፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ‘የሕግ የበላይነት መገለጫ’ ተብለው የሚጠቀሱ በጣም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ ልዩነት እንዳለ ሆኖ፣ የሕግ የበላይነት መርህ የሚከተሉትን መሠረታዊና ሁለንተናዊ ነገሮች ያካትታል፡፡
1. መንግሥትና ልዩ ልዩ አካላቱ፣ እንዲሁም ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ዜጋ ሁሉ ለታወቀና ቋሚ ለሆነ (በሥራ ላይ ላለ) አጠቃላይ የሀገሪቱ ሕግ የበታች ናቸው፡፡ ከሕግ በላይ ወይም ከሕግ ውጪ የሆነ/የሚሆን ማንም/ምንም አይኖርም፡፡ ይህ መርህ የሕጎች ሁሉ የበላይ ለሆነው ለሕገ መንግሥት ብቻ የሚጠቀስ ሳይሆን፣ ለሁሉም ዓይነት አጠቃላይ ሕጎች ነው፡፡
2. ለሕግ የበላይነት መኖርና መረጋገጥ አንዱ ማሳያ፣ ሁሉም የተቀበሉትና ሁሉንም የሚገዛ በሥራ ላይ ያለ ሕግ እያለ፣ በሆነ መንገድ (ሕግ ለማውጣት ሥልጣን ባለው አካልም ሆነ በግለሰብ ባለሥልጣን) ሌላ ሕግ የሚወጣበትና ባለው ሕግ ላይ ተጨማሪ የሚደረግበት ወይም በከፋ ጐኑ የነበረውን ሕግ በከፊልም ሆነ በሙሉ በመሻር ሥራ ላይ የሚውልበት መንገድ ሁሉ ሕገ-ወጥ ተብሎ የሚዘጋበት ሥርዓት መስፈን አንዱና መሠረታዊ ነገር ነው፡፡1
3. ማንም/ምንም መቼም፣ የትም ከዚህ ሕግ በታች እንጂ በሁኔታዎች በማመካኘት፣ የሕግ ማስከበሪያ ተቋማት አለመኖር ወይም በሕግ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ አለመፈጸም እያዩ ሳይሆን የሕግንና የሕግ የበላይነትን መኖር የተቀበሉና የሚያምኑ ሁኑ የሚሟገቱለት ባህል ሲኖር ነው:: የሕግ የበላይነት ካለ፣ እነዚህ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ካሉ በሕግ የሚጠየቁበት ሥርዓት ይኖራል ይሠራል፡፡
4. ሕግና የሕግ የበላይነት ካለ መንግሥትም ሆነ ልዩ ልዩ አካላቱ ወይም ተቋማቱ፣ በየደረጃው ያሉ ግለሰብ ባለሥልጣናቱ፣ እንዲሁም ዜጎችና ማኅበራት የሚያደርጉትና የማያደርጉት ተግባር በቅድሚያ ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት በደኅናውም ሆነ ከመደበኛው ለየት ባሉ ሁኔታዎች ማንኛውም አካልና ግለሰብ በሕግ መሠረት ምን እንደሚደረግ ስለሚገነዘብ ግራ ከመጋባት ይልቅ የተረጋጋ ይሆናል፡፡
5. የሕግ የበላይነት ከሌሎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና መሰል ጉዳዮች ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መርህ መኖርና ተግባራዊነት ለሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መከበር ወሳኝ ነው፡፡

የሕግ ገዢነት (Rule of Law)

ሕግ የአንድን ኅብረተሰብ/ማኅበረሰብ እንቅስቃሴና ባለብዙ ፈርጅ ግንኙነቶች ሥርዓት የተከተሉ እንዲሆኑ የሚያደርግ ከሆነ፣ ሕግ ለመባልና ለመሆን ከሁሉ በፊት ማሟላት ያለበትን መመዘኛዎች ካሟላ፣ የሕግ የበላይነት መሠረት የያዘና የጸና ከሆነ፣ የሕግ ገዢነት መስፈኑ አይቀርም፡፡
ማንም ፈልጎ መረዳት እንደሚችለው በሕግ የበላይነትና በሕግ ገዢነት መካከል መሠረታዊ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ በርካታ የጋራ የሆኑ ባሕርያት አሏቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዘመናውያኑም የሕግ ገዢነት እጅግ ብዙ ዓይነት ትርጉሞች ተሰጥቶታል፡፡ ሁሉንም መዘርዘር አስፈላጊም ተገቢም ባለመሆኑ የተወሰኑትን ብቻ ማየቱ በቂ ይሆናል፡፡
1. የሕግ ገዢነት ማለት የማናቸውም ጉዳዮች አፈጻጸም መንገድ፣ ሂደት፣ ተቋም፣ ልምድ ወይም ልማድ ሲሆን፣ መሠረታዊ ግቡም የሁሉንም ዜጎች በሕግ ፊት፣ እንዲሁም ከሕግ በታችነት እኩልነትን መርህ ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህም መርህ ሕግ በመፍቀድም በመከልከልም/በመቅጣትም ሁሉንም በእኩል ሚዛን የሚመዝንና በእኩል የሚያይ ሥርዓት የሰፈነበት፣
2. በሰዎች/ዜጎች መካከል ማናቸውም ልዩነት ሳይኖር የሕግ ተደራሽነትና የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት ለሁሉም ዜጋ በተግባር ተረጋገጠበት ሥርዓት፣
3. ያለሕግ እንደመሰለው የሚሠራ ወይም በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ያለአግባብ የሚጠቀም መንግሥት/መስተዳድር እንዳይከሰት ዋስትና በሕግ የተገለጸበትና የሰፈነበት መርህና ሥርዓት፣
4. የሕግ ገዢነት ከላይ የተጠቀሰውን በመንግሥት፣ በልዩ ልዩ ተቋማቱና በግለሰብ ባለሥልጣናቱ ላይ ሕጋዊ የሥልጣን ገደብ የተደነገገበት ብቻ ሳይሆን፣ የተሰጣቸውን ተግባር ማከናወናቸውን፣ ባለማከናወናቸው ጉደለት ወይም ግድፈት ሲኖርም በሕግ ተጠያቂነት እንዲሆኑ የሚደረግበት፣
5. ትርጉም ያለው የመንግሥት የሥልጣን ክፍፍል፣ በተለይም ከሌሎቹ አካላት ነጻ የሆነ የፍትሕ አካል፣ መኖርና ፍርድ ቤቶች በየደረጃቸው በሙያ ብቃታቸው በሚሾሙ ከማናቸውም የፖለቲካና የርዕዮተ-ዓለም ተጽእኖ የጸዱና በሕግና በሕግ ብቻ ብይን በሚሰጡ ዳኞች የተሟሉበት፣
6. ተገቢና በትክክል የሚሠራ የሕግ ሥርዓት አካሄድ (due process) በትክክል የሚሠራበት፣
7. ለሰብአዊ መብቶች በሕግ ዋስትና የተሰጠበትና የነዚህም መብቶች ጥሰት ሲከሰት የእርምትና ማስተካከያ መንገዶች በግልጽ የተደነገጉበት… ወዘተ.

ማጠቃለያ

የሕግን ምንነት፣ ዓላማ፣ የሕግ የበላይነትና የሕግ ገዢነት በጥቂቱም ቢሆን ካየን፣ የሕግ ግንዛቤያችንን/ንቃተ-ሕግን የበለጠ በማዳበር እነዚህን መርሆዎች በዕለት ተዕለት ተግባራችንና በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ… ወዘተ. ግንኙነቶቻችን ውስጥ በተግባር መግለጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬ ሕግን ማክበርና ማስከበር፣ ብሎም ሕጋዊነትንና የሕግ ገዢነትን በግንዛቤም ሆነ በተግባራዊ አካሄዳችን ማየት በምንቸገርበት ዘመን ይህ ለግላችንም ለኅብረተሰባዊ ህልውናችንም አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም።

“The precepts of the law are these: to live honestly, to injure no one, and to give everyone else his due.” – Marcus Tullius Cicero

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top