ጥበብ በታሪክ ገፅ

አርመናውያን ሙዚቀኞች በኢትዮጵያ

መግቢያ

የ20ኛው ክፍለ-ዘመን መባቻ አያሌ አርመናውያንን ወደኢትዮጵያ እንዲያማትሩ አስገድዷል፡፡ በእርግጥ፣ ወደኢትዮጰያ ብቻ ሳይሆን፣ ወደሌሎች ሀገራትም አማትረዋል፡፡ በጊዜው የዑስማንያ ቱርክ ክርን በአርመናውያኑ ላይ መጠንከሩን ተከትሎ በርካታ አርመናውያን ሀገራቸውን ጥለው መሰደድን መርጠዋል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ በተለይም እንደአውሮጳውያኑ አቆጣጠር ከ1894- 1896 ዓ.ም. ባሉት ተከታታይ ዓመታት በርካታ አርመናውያን የኢትዮጵያን ምድር ረግጠዋል፡፡ በንግድ፣ በባህል፣ በእምነት፣ በሙዚቃና በሌሎች ሙያዎች በመሰማራት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዲፈጥሩ ይህ የታሪክ አጋጣሚ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ኖሪች ዲላንቺያን የተባለ ጸሐፊ Musical Cousins: Armenia, Ethiopia and Jamaica በሚል ጽሑፉ እንደሚገልጸው፣ የአርመናውያኑ የሙዚቃ አሻራ ማረፍ የጀመረው ዘግይቶ ነው፡፡ ወቅቱም በ1916 ዓ.ም. በንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመ-አገዛዝ፣ በራስ ተፈሪ መኰንን አልጋ ወራሽነት ጊዜ ነው፡፡ ይህን ዝነኛ ታሪክ ከመተረካችን በፊት ግን፣ የውጭ ሙዚቀኞችንና የባሕር ማዶ ሙዚቃ መሣሪያዎችን በተመለከተ ጥቂት መንደርደሪያዎችን እናስቀድም፡፡ ከአርባዎቹ የአርመን ልጆች በፊት፤ አርባዎቹ የሩሲያ ሙዚቃ መሳሪያዎች እንደምን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻገሩ?

40ዎቹ የሙዚቃ መሣሪያዎች

የዳግማዊ ዐጼ ምኒሊክ ዘመነ-አገዛዝ የኢትዮጵያን ቅርጽ በብዙ መልኩ የቀየረ ነው፡፡ በተለይ፣ የአድዋ ጦርነት ድልን ተከትሎ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች፣ በጥበብ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲው ዓለም ያልተጠበቀ እመርታን አስመዝግባለች፡፡ አንዲት ጥቁር አፍሪካዊት ሀገር የታላቋን አውሮጳዊት ሀገር፣ ማለትም ኢጣልያ፣ ኃይል በጦር ማንበርከኳ የብዙ ምዕራባውያንን ቀልብ ስቧል፡፡ ኢትዮጵያን ለጠብ ሳይሆን ለፍቅር እንዲመኟትም በር ከፍቷል፡፡ ለስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ደጅ ጠኚው እንዲበዛ ምክንያት ሆኗል፡፡ “ትናንት የት ነበርሽ?” ያላላት ሁሉ “አለሁ አለሁ” ብሏል፡፡ ዲፕሎማቶቹን ልኳል፡፡ ኤምባሲ ከፍቷል፡፡ ታዲያ፣ አዲሱ ዓለም ዓቀፋዊ ግንኙነት ለዘመናት ታፍሮ የቆየውን የሀገሪቱን ሁለንተና ማነቃነቁ አልቀረም፤ በክፉም በደግም፡፡ አዳዲስ አስተሳሰቦችና ሸቀጦች ጎርፈዋል፡፡ ነባሩ ከአዲሱ ጋር ተደባልቋል፡፡ በዚህ ምክንያት እንደኩሬ ከረጉበት ዓለም በድንገት ከተነቃነቁ ዘርፎች መካከል አንዱ ሙዚቃ ነው፡፡

በአድዋ ድል ማግሥት ፈጥነው ወደኢትዮጵያ ከገሠገሡ ሀገራት መካከል ሩሲያ አንዷ ናት፡፡ የዳግማዊ ዛር ኒኮላይ መልክተኞች ወደኢትዮጵያ ተልከዋል፡፡ ሩሲያ ቀድሞም በአድዋው ጦርነት አጋርነቷን አሳይታለች፤ በጦር መሣሪያ እገዛ፣ በቀይ መስቀል… ወዘተ። በጦርነቱ ዋዜማም እንደዚሁ መልክተኞቿን ወደአዲስ አበባ በመላክ የቀደማት የለም፡፡ በዝነኛው ሀገር አሳሽና የዳግማዊ ምኒሊክ የቅርብ ሰው ኮሎኔል ኒኮላይ ስቲፓኖቪች ሊኦንቲየቭ የተመራው የሩሲያ ልኡካን ቡድን ከዚህ በፊት ያልተለመዱ ስጦታዎችን ለንጉሠ-ነገሥቱ አስረክቧል፡፡ እነዚህ ስጦታዎችም 40 የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ለሀገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ነበሩ፡፡ ምናልባት በ15ኛው ምዕተ-ዓመት “ከፖርቱጋል መጥቷል” ከሚባለው የሙዚቃ መሣሪያ ወዲህ ይህ ሁለተኛው ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእርግጥ፣ የኋለኞቹ ይለያሉ፡፡ አንደኛ፣ በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ ሁለተኛ፣ እንደቀደመው “መጥተው ነበር” ተብለው የሚዘነጉ ሳይሆኑ፣ የሀገሪቱን የሙዚቃ ቅርጽ ወደአዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው፡፡

የሆነ ሆኖ፣ “እነዚህን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሩሲያ እንዴት ልትልክ ቻለች?” በማለት ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡ ምክንያቱም፣ በዘመኑ ከውጭ ከሚመጡ እጅ መንሻዎች አንጻር ሲመዘኑ ያልተለመዱ ናቸው፡፡ የትኛውም አገር እንዲህ ዓይነት ስጦታ ይዞ አልተገኘም፡፡ ኢትዮጵያም ሙዚቃን ገና ከቁም ነገር አልጻፈችውም፡፡ በዚህ የተነሣ፣ አንዳንዶች “በለውጥ ፈላጊው ዳግማዊ ምኒሊክ ጥያቄ የመጡ ሳይሆኑ አይቀሩም” የሚል መላ ምት ያስቀምጣሉ፡፡ ሌሎች ግን፣ ሩሲያ በፈቃዷ ያደረገችው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በዚያው ዘመን ወደኢትዮጵያ የተጓዙ የእንግሊዝ መልእክተኞችን ታሪክ የከተበውና ከተጓዥ እንግሊዛውያን መካከል አንዱ የሆነው ካውንት ግሌቺን ግን፣ ነገሩ ወዲህ ነው ይላል፡፡ With the Mission to Menelik ሲል በከተበው ዳጎስ ያለ መጽሐፉ ውስጥ እንደሚጠቅሰው፣ የሸዋው ምኒሊክ በእነሊኦንቲየቭ ስጦታ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ እንዲያውም፣ እንግሊዞቹ ያመጡላቸውን የጦር መሣሪያ ስጦታዎች በማድነቅ፣ “ሌሎች ሀገራት እንደሕፃን ቆጥረውኝ የሙዚቃ ሣጥንና አሻንጉሊት ያመጡልኛል” ብለው እንደነገሯቸው ግሌቺን እንዲህ ይከትባል፦
“Other nations,” he said, “have treated me like a baby, and given me musical boxes, and magic lanterns, and mechanical toys; but you have given me what is really useful and valuable—I have never seen such things before.”
ግሌቺን ይህን ቢልም፣ ሊኦንትየቭ ኢትዮጵያውያንን ሙዚቃ ለማሠልጠን ደፋ ቀና ማለቱ አልቀረም፤ ነገሩ ያልተሳካ ቢሆንም፡፡ ቢሆንም፣ ሙከራው “ሙከራ” ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ የኋላ ኋላ ሚሌውስኪ በተባለ ሌላ ሩሲያዊ አሠልጣኝ አማካኝነት ከቤኒሻንጉልና ወላይታ አካባቢ በመጡ ሠልጣኞች ጥቂት ለውጥ ታይቷል፡፡ ንጉሠ-ነገሥቱም ይህንን ለውጥ ዐይተው ይመስላል በሌላ ጊዜ ወደቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በላኩት ደብዳቤ ስለሙዚቃ ጉዳዬ ብለው መልእክት መስደዳቸው በታሪክ ተከትቧል፡፡

40ዎቹ ሙዚቀኞች

አሁን ወደቀደመ ታሪካችን እንመለስ፡፡ ከአርባዎቹ የሩሲያ የሙዚቃ መሣሪያዎች ወደአርባዎቹ የአርመን ሙዚቀኞች ታሪክ እንሻገር፡፡ ከላይ እንዳነሣነው ዘመኑ 1916 ዓ.ም. ሲሆን፣ ወሩም ነሐሴ ነበር፡፡ አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን የዘመኑን ኃያላን የአውሮጳ ሀገራትን ለመጎብኘት ተነሥተዋል፡፡ በጉብኝታቸውም “ከኃያላኑ ሀገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነትን ለመመሥረት፣ ምናልባትም የወደፊቱን የረጅም ዘመን የሥልጣን ጉዟቸውን አሐዱ ብለው የጀመሩበት፣ የሥልጣኔ ማማን ወደኢትዮጵያ ለማስረጽ፣ በጥቅሉ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ከዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ መነጋገርን በይፋ የጀመሩበት ጊዜ ልንለው እንችላለን፡፡

ራስ ተፈሪና ተከታዮቻቸው ወደአውሮጳ አፈር ከመጠጋታቸው በፊት ግን፣ አንዲትን ሀገር መጎብኘት ተቀዳሚ ሥራቸው አድርገዋል፡፡ ጉዞ ወደመካከለኛው ምሥራቋ ከተማ – ኢየሩሳሌም፡፡ ራስ ተፈሪ መኰንን የኢየሩሳሌምን ምድር እንደረገጡ በቀጥታ በኢየሩሳሌም የአርመን ገዳምን ለመጎብኘት ነበር ያቀኑት፡፡ በዚያም በትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ የታጀበ ታላቅ የሙዚቃ ድግስ ተቀበላቸው፡፡ ይህም ለልዑሉ ክብር ሲባል የተደረገ አቀባበል ነበር፡፡ እነዚያ ሙዚቀኞችም በቁጥር 40 የሚሆኑ አርመናውያን ወጣቶች ነበሩ፡፡ ራስ ተፈሪ መኰንን በሀገራቸው አይተውት የማያውቁት የሙዚቃ ስልትና ሥርዓት ትልቅ የመንፈስ ደስታን አጎናጽፏቸው ነበር፡፡

በኢየሩሳሌም የአርመን ገዳም ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት አቡነ ቱርያን ራስ ተፈሪን በነዚህ ወጣቶች የክብር አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ ስለልጆቹ ሕይወት ብዙ ነገር ነግረዋቸዋል፡፡ በተለይም፣ ቱርኮች በአንደኛው የዓለም ጦርነት እና ከጦርነቱም በፊት በአርመናውያኑ ላይ ስላደረሱባቸው እንግልትና ዘር ማጥፋት፣ ስለስደት፣ ብዙ ሕፃናት ወላጅ አልባ ስለመሆናቸው ለራስ ተፈሪ አስረድተዋቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ፣ የአርመናውያን የዘር ማጥፋት (genocide) ወይም እልቂት (holocaust) እስከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ እንደተካሄደና ወደ1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ አርመናውያን እንደተደመሰሱ (እንደተጨፈጨፉ) መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የድርጊቱም ዋና ተዋናያኖች የያኔዋ ዑስማንያ ቱርክ ገዢዎች እንደነበሩ ተጽፏል፡፡ ሊቀ-ጳጳሳት አቡነ ቱርያን እነዚህ ሙዚቀኛ ልጆችም በቱርኮች ወላጆቻቸውን ያጡና ምንም እንኳ በገዳሟ ሥር ተጠግተው እየኖሩ ያሉ ቢሆንም፣ አስቸጋሪ ሕይወትን እየገፉ እንዳሉ በግልጽ ነገሯቸው፡፡

ራስ ተፈሪ በልጆቹ ችሎታ የተደሰቱትን ያህል ሕይወት በጣለችባቸው መከራም ልባቸው ሳይነካ አልቀረም፡፡ በአንድ ወገን የልጆቹን ሙያ ወደሀገራቸው ለማስገባት፣ በሌላ ወገን በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ያሉትን ልጆች የበኩላቸውን ለማገዝ ፈልገዋልና ለሊቀ-ጳጳሳቱ አቡነ ቱርያን ልጆቹን እንዲሰጧቸው ወዲያውኑ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ተፈቀደላቸውም፡፡

ልዑል ራስ ተፈሪ በአውሮጳ ጣሊያንን ጨምሮ ታላላቅ ሀገራትን በክብር ጎብኝተው በመስከረም ወር 1917 ዓ. ም. አዲስ አበባ ሲመለሱ፣ ሲሄዱ ያስከተሏቸውን ልኡካን ብቻ ይዘው አልነበረም፡፡ ይልቁንም፣ አርባዎቹን አርመናውያን ወጣቶች እና ኪቮርክ ናልባዲያን የተባለ የሙዚቃ አሠልጣኛቸውን ጨምሮ ለእያንዳንዳቸው የመርከብ ወጪያቸውን በመክፈል ይዘዋቸው አዲስ አበባ ገቡ፡፡

አርባዎቹ አርመናውያን ወጣቶች አዲስ አበባ እንደገቡ የልጅ ኢያሱ ግቢ ተብሎ ከሚጠራ አዳራሽ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ እያንዳንዳቸውም በወር 35 ብር ደመወዝ እንዲከፈላቸው ተደርጎ እንደነበርም የተጻፉ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህ ክፍያ ከወቅቱ ጋር ስናነጻጽረው፣ ሌሎች ክፍሎች ከሚፈላቸው ክፍያ አንጻር ትልቅ የሚባል ነበር፡፡

ማርሽ ተፈሪ

አርባዎቹ ልጆች አዲስ አበባ በመጡ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ በአሠልጣኛቸው ኪቮርክ ናልባዲያን እየተመሩ በዘመኑ ድንቅ የሚባል የብራስ ባንድ መፍጠር ችለዋል፡፡ ይህም ተግባር አሠልጣኙን ኪቮርክ ናልባዲያንን እና ልጆቹን እጅግ እንዲወደዱ ከማድረጉም በላይ፣ በንጉሠ-ነገሥቱም ዘንድ ላቅ ያለ ክብርን አስገኝቶላቸዋል፡፡

የአርመናውያኑ የሙዚቃ ቡድን ወይም ባንድ በዳግማዊ ዐጼ ምኒሊክ ዘመነ-አገዛዝ ከሀገረ-ሩሲያ ከመጡ የሙዚቃ መሣሪያዎች እና ጥቂት የሙዚቃ አሠልጣኞች ወዲህ ከውጭ በመጡ ሙዚቀኞች የተደራጀ ቀዳሚው ባንድ ነው፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ሞንዶ ቪዳሌ የተባለን የዐጼ ምኒሊክ አማካሪ ፈረንሳያዊ ጠቅሶ እንደጻፈው፣ ሚሌውስኪ የተባለ በትውልድ ፖላንዳዊ የሆነ ሩሲያዊ የሙዚቃ መምህር ወደኢትዮጵያ መጥቶ ያስተማራቸው የቤኒሻንጉልና የወላይታ አካባቢ ወጣቶች ለ ማርሴየስ የተሰኘውን የፈረንሳይን ብሔራዊ መዝሙር ተጫውተው እንደነበር ይጠቅሳል፡፡ እንግዲህ፣ ከዚህ ቡድን በኋላ በሀገሪቱ የተደራጀ የሙዚቃ ስብስብ የታየው በኪቦልክ ናልባንዲያን የሚሠለጥነው የ40ዎቹ አርመናውያን ልጆች ስብስብ – ማርሽ ተፈሪ ነው፡፡

ኪቦልክ ናልባንዲያን አርባዎቹን አርመናውያን ልጆች በማሠልጠን እና ለቁም ነገር በማብቃት፣ በኋላ ላይም ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች የሙዚቃ መንገድን የጠረገ ታላቅ የሙዚቃ መምህር ነበር፡፡ በሙዚቃ ሙያ የተራቀቀው ሰው፣ ልክ እንደሚያሠለጥናቸው አርመናውያን ወገኖቹ ሁሉ፣ ወላጆቹን በልጅነቱ ያጣ ሰው ነው፡፡ የትውልድ አገሩም የደቡባዊ ምሥራቋ የቀድሞዋ ዑስማንያ ቱርክ ግዛት አንታብ (Aintab)፣ የአሁኗ ጋዚያንቴፕ (Gaziantep) እንደሆነ ተከትቧል፡፡

ልዑል ራስ ተፈሪ በ1923 ዓ.ም. “ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ- ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው ሲነግሡ ያጀባቸው የኪቮርክ ናልባዲያን ሠልጣኞች የተፈሪ ማርሽ ባንድ ነበር፡፡ የኪቦልክ ናልባንዲያን ጉዞ በዚህ ብቻ የሚቋጭ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ብሔራዊ መዝሙር ላይ ታሪካዊ አሻራውንም አኑሯል፡፡ የክብር ዘበኛን ጨምሮ ሌሎች ክፍሎችን በማሠልጠንም ሙያውን ያለሥሥት አሸጋግሯል፡፡ የቅርብ ዘመዱ ሙሴ ነርሲስ ናልባንዲያን ወደኢትዮጵያ መጥቶ የካበተ የሙዚቃ ስጦታውን ለኢትዮጵያውያን እንዲቸር ምክንያት ሆኗል፤ ሌላም ብዙ ብዙ፡፡ “ኢትዮጵያ ሆይ፣ ደስ ይበልሽ” የተሰኘው የመጀመሪያው ብሔራዊ መዝሙር ዜማና ግጥም ደራሲ ኢትዮጵያዊው ዮፍታሔ ንጉሤ ሙዚቃ ቀማሪውም ኪቮርክ ናልባዲያን ነው፡፡

እንደሚታወቀው፣ ይህ ብሔራዊ መዝሙር የዘውድ አገዛዙ አክትሞ የደርጉ መንግሥት እስከተተካበት 1966 ዓ.ም. ድረስ የሀገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ሆኖ አገልግሏል፡፡ በ”ኢትዮጵያ ቅደሚ፣ በኅብረተሰባዊነት አብቢ ለምልሚ” የተተካውን ይህንን ቀደምት መዝሙር እንደመውጫ እነሆ፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ፣
በአምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ፡፡
ተባብረዋል አርበኞችሽ፣
አይነካም ከቶ ነጻነትሽ፣
ብርቱ ናቸውና ተራሮችሽ፣
አትፈሪም ከጠላቶችሽ፡፡
ድል አድራጊው ንጉሣችን፣
ይኑርልን ለክብራችን፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top