አድባራተ ጥበብ

ንሂሊያዊ ንባብ በአዳም ረታ መስከረምና መስከረም አጭር ልብ ወለድ

መግቢያ

አዳም ረታ የአጭር እና የረጅም ልብ ወለዶች ደራሲ ነው፡፡ በዘመናዊው ዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ እያስቀመጡ ካሉ ደራሲዎች ስሙ የሚጠራው አዳም፣ በራሱ አዳዲስ የአጻጻፍ ስልት የራሱን አንባቢዎች መፍጠር እንደቻለ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
አዳም በልብ ወለድ ቅርጽ ላይ የተለያዩ ሙከራዎችን ከማድረግ ባለፈ፣ ለዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ አዳዲስ የሆኑ የትረካ ቅርጾችን ይዞ መምጣት ችሏል፡፡ ብዙዎቹ የአዳም ሥራዎች በዚህ የተነሣ ተመራማሪዎችን የሚጋብዙ የምርምር ርዕሰ- ጉዳዮች መሆን ችለዋል፡፡
በዚህ አነስተኛ ወረቀት እኔም የአዳምን አንድ አጭር ልብ ወለድ ከንሂሊያዊ ፍልስፍና አጽናፈ-መነጽር ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡ ይህ አጭር ልብ ወለድ መስከረምና መስከረም የሚል ርዕስ አለ፡፡ በ2004 ዓ.ም. በታተመው ህማማትና በገና ውስጥ የሚገኝ አጭር ልብ ወለድ ነው፡፡ ልብ ወለዱ በዓለማችን ‘ንሂሊስት ናቸው’ ተብለው የሚታወቁ ፈላስፎች ያራመዷቸውን ሐሳቦች በምን መልኩ እንደተከተለ ማሳየት ነው፣ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፡፡

አስቀድሜ ትንታኔውን ለመሥራት የመረጥኩትን ንድፈ-ሐሳብ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በመቀጠል፣ በመስከረምና መስከረም ውስጥ የተመረጡ ገለጻዎችን በምሳሌነት እያነሣሁ ማሳያዎችን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በስተመጨረሻም፣ አጭር ማጠቃለያ ይኖረኛል፡፡

ፅንሰ-ሐሳብ

ንሂሊዝም Nil ወይም ባዶ፣ ማለትም ‘ምንም’ ከሚል ሥርወ-ቃል የወጣ ነው፡፡ ምንም እንኳን ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ሩሲያዊው ደራሲ ኢቫን ቱርጌኔቭ ልብ-ወለድ ድርሰት በሆነው Fathers and Sons (1862) ላይ በጉልህ ሰፍሮ ብናገኘውም፣ እንደፅንሰ-ሐሳብ በፍልስፍና ብሎም በሰፊው የሰው ልጅ የሐሳብ ታሪክ ውስጥ ሁሉ ሠርጎ ገብቶ እናገኘዋለን፡፡ እንደየዘርፉ፣ ማለትም በሥነ-ጽሑፍ፣ በሥነ-ሥዕል፣ በሥነ-ዕውቀት፣ በሥነ-ዲበአካል፣ እንዲሁም በፖለቲካ አበያየኑ ቢለያይም፣ የንሂሊዝም እሳቤ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሁሉም ውስጥ ይገኛል፡፡ እንደጥርጣሬ፣ አለማመን፣ ባዶነት እና በሕይወትና በውስጧ ባሉ ነገሮች ትርጉም ማጣት ያሉ የንሂሊዝም ፍልስፍና ማጠንጠኛ ነጥቦችን ሳይንተራሱ፣ አሊያም ሳይነቅፉ ገሸሽ አድርጎ ማለፍ ከሰው ልጆች የሐሳብ ተፈጥሮ ጋር የሚቃረን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ከጥንታዊቷ ግሪክ ፈላስፎች አንዱ የሆነው አፍላጦንን (ፕሌቶ) ብንወስድ፣ ዓለምን ከንጹሕ ፍጽምና የጎደለች የምሉዕነት እና ባዶነት ድፍርስ ቅይጥ አድርጎ ሲመለከታት እናገኘዋለን፡፡ በተለይም፣ Republic በተሰኘ ድርሰቱ ላይ ምድርን ፍጹም ንጹሕ ከሆነ ውበት፣ ፍቅር፣ ፍትሕ እና ዕውቀት ጎድላ የምናገኛት እነኚህ የላቁ ነገሮች ሁሌም በፉንጋነት፣ በጥላቻ፣ በኢ-ፍትሐዊነት እና በድንቁርና እንዳይለዩ ሆነው ተበርዘው ስለሚገኙ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ለዚህ ሁሉ መንሥዔው ደግሞ፣ ጊዜያዊ የሆነው ሥጋዊ ሕይወት እንደሆነ በማሳየት የዘለዓለማዊቷ ነፍስ ተግባር ወደሆነው ፍልስፍናዊ (መንፈሳዊ) ሕይወት በማድላት ብቻ ከሥጋ ባርነት ነጻ መውጣት እና ፍጹም የሆነውን ማጣጣም እንደምንችል ይጠቁመናል፡፡

በሌላኛው ጽንፍ የጀርመኑ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ እንዲህ ያለውን ዓለምን እና ሥጋን ማንኳሰስ በጥቅሉ ንሂሊዝም በሚል ፈርጆ ይሔሰዋል፡፡ በተለይ Human All too Human በተሰኘው ሥራው ላይ የሰማያዊ ዘለዓለማዊ ዓለም ተስፋን የሚሰብኩ ፍልስፍና እና ሃይማኖቶችን (በተለይ ክርስትናን) ምድርን የሚጸየፉ፣ የሰው ልጅን ዐቅም የሚያኮስሱ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ተሸናፊነትን የሚያስተምሩ ናቸው ይላል፡፡ ለኒቼ ሰው ክፉም ሆነ ደግ በሕይወቱ የገጠመውን እና የሆነውን አምኖ በመቀበል፣ እልፍ ሲልም በመውደድ (amor fate ይለዋል – ያለፈውን መቀየር የማንችለውን ዕጣ ክፍላችንን መውደድ ማለቱ ነው) ከሰውነትም ከፍ ወዳለ ልዕለ-ሰብእነት (Superman) ያሻግረናል፡፡
ኤግዚስቴንሻሊዝም እና ንሂሊዝም

ኤግዚስቴንሻሊዝም በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ብዙ ከተሠራባቻው ፍልስፍናዊ ንድፈ-ሐሳቦች አንዱ ነው፤ በአንዳንድ ምልከታዎቹ ከንሂሊዝም ጋር የሚጋራቸው ነጥቦች ስለሚኖሩ ሁለቱን ንድፈ-ሐሳቦች ቁልጭ አድርጎ ማሳየት ባይቻል እንኳ ተዛምዶውን እና ተቧድኖውን ለማሳየት መሞከር ተገቢ ነው፡፡ ኤግዚስቴንሻሊዝም አሁን እና እዚህ በሚሉ ነጥቦች ያምናል፡፡ ንሂሊዝም ግን፣ በምንም አያምንም፤ ካመነም በምንም ነው፡፡

ንሂሊዝም የትኛውንም ዓይነት ዓለማዊ ሐቅ አይቀበልም፤ በ19ኛው ምዕተ-ዓመት በሩሲያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ እንዳበበ ወይም እንደተመሠረተ ይታሰባል፡፡ በዘመኑ ሩሲያ ተቋማዋዊ መዋቅሮች ዐመፅ ከማስነሣት አልፎ፣ ማንኛውንም መንግሥታዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ መዋቅርን መቃወም ችሏል፡፡

ኤግዚስቴንሻሊዝም በየትኛውም የሕይወት ትርጓሜ የማይስማማ፣ ሆኖም እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዓለም መሥራት እንደሚችል የሚያስረዳ ወይም በዚህ እውነት የሚያምን ነው፡፡ በጠቅላላው፣ ሁለቱም እሳቤዎች መነጽራቸው የሚለያየው ግባቸው ላይ ነው፡፡

ንሂሊዝም በምንም ከማመን ይልቅ ምንምን የሚያመልክ ነው፡፡ በምንምነት ማመን በክብ ውስጥ ላለ ነገር ሁሉ ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ ኤፕሲቲሞሎጂካል ፍልስፍናቸውም ራሽናሊዝም እና ማቴሪያሊዝም ነው፤ የግለሰብ ነጻነት ደግሞ፣ የመጨረሻ ግባቸው፡፡ አይዲያሊዝም ወይም እምነታዊነት ለእነሱ ዋጋ የላቸውም፡፡

ንሂሊስት ሰዎች “ግዚአብሔር የለም” ብለው የሚያምኑ ሰዎች አይደሉም፤ ይልቁንም፣ የእግዚአብሔርን መኖር ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ በእግዚአብሔር መኖር እርግጠኞች አይደሉም፡፡ በሌላ ምሳሌ ለማየት ደግሞ፣ አንዲት ሚስት በባሏ ላይ ብትቀለውጥ ባል “ግድ የለም አይጐዳኝም” ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም፤ ነገር ግን፣ ጉዳዩ የሚመሠረተው ሚስት በሕይወት ውስጥ ትቀለውጥ እንደሆነ ማስረጃዎች በመኖራቸው እና ባለመኖራቸው ላይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ፣ ሚስት መቀልወጧ በማስረጃ የተረጋገጠም ቢሆን ባል የሆነ ጊዜ በእሷ ላይ ስላለመቀላወጡ ማስረጃው ምንድን ነው? ስለዚህም፣ “እርግጠኛ የምንሆንበት ሕይወት የለንምና ሚስት ቀላውጣ ብትገኝ የሚደንቅ ሊሆን አይችልም” ይላሉ፡፡

ይሄንን ነገራቸውን ሊገልጹ የሚችሉ ሁለት ምሳሌዎችን ማየት እንችላለን፡፡ What he wished to believe, that is what each man believes; ሊያምን የሚመኘው ማንም የሚያምነውን ነው፤ እና The life of mortals is so mean a thing as to be virtually un-life; የሟች መኖር ማለት አለመኖር ነው ወይም ሟች ሕይወቱ አለመኖር ነው፡፡ (ሁለቱም አባባሎች በሃይዲገር የተጠቀሱ ናቸው።)

ንሂሊስቶች ለዚህ እሳቤያቸው አስረጅ የሚያደርጉት የሰው ልጅ ምኞትን እና ቅዠትን ከሕይወቱ ካስወጣ ምንም መሆኑን ይገነዘባል ከሚል ነው፡፡ ለመሆኑ የንሂሊስቶች መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል? እነሱስ በምን ሊገለጡ ይችላሉ? “ሕይወት ትርጉም የላትም፣ ይህች ዓለምም ምንም ናት” ብለው የሚያምኑ ንሂሊስቶች ከእነዚህ በአንደኛው ጥላ ላይ ያርፋሉ፡፡

ፍልስፍናዊ ሞት፥ እጅ ይሰጣሉ። “ሕይወት ትርጉም አልባ ናት፤ ስለዚህም፣ መፈላሰፌ ዋጋ የለውም” ከሚል መነሻ ራሳቸውን በሃይማኖት ጥላ ስሥር ይደብቃሉ፣ ወይም በአንድ ሌላ መንፈሳዊ ዋሻ ውስጥ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

አካላዊ ሞት፥ ትርጉም አልባ በሆነ ዓለም ውስጥ በሕይወት መኖር አሰልቺ እና የሥቃይ ምንጭ ስለሚሆንባቸው ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ መቀበል፥ ሕይወት እውነተኛ እና የመጨረሻ ትርጉም እንደሌላት እያወቁ መኖር፡፡

ይህን ፍልስፍና በተመለከተ ሦስት ተመሳሳይ የሚመስሉ፣ ሆኖም የተለያዩ ፅንሰ-ሐሳቦችን እንመልከት።
ኤግዚስቴንሻሊዝም፥ ‘በግለሰባዊ ግንዛቤ፣ ግለሰባዊ መልካም ፈቃድና ግለሰባዊ ኃላፊነት ውሑድ ኑረት አንድ ሰው በዓለም ውስጥ የራሱን የሕይወት ትርጓሜ መስጠት ይችላል ወይም ይገባዋል’ ብሎ የሚያምን ነው፡፡

ንሂሊዝም፥ ‘ዓለም ትርጉም አልባ ናት’ ብሎ ማመን ብቻ ሳይሆን፣ ‘ለዚህ ዓለም እና ሕይወት ትርጉም ለመስጠት መሞከር በራሱ ምንምነት ነው’ ብሎ የሚያምን ነው፡፡
አብሰርዲዝም፥ ለሕይወት ትርጉም ለማግኘት የሚደረገው ትግል ሁሉ ከተፈጥሮ የተነሣ ሁሌም ከትርጉም አልባነት ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው። ነገር ግን፣ ሕይወት ማለት ሁሌም ቢሆን ይህንን ተቀብሎ ልትሰጥ የምትችለውን አዎንታዊነት ሁሉ ለማግኘት መፍጨርጨር ነው፡፡

መስከረምና መስከረም

ይህ አጭር ልብ ወለድ 17 ያህል ገጾች ያሉት ሲሆን፣ አዳም ረታ በ2004 ዓ.ም. ባሳተመው ህማማትና በገና የአጫጭር ልብ ወለዶች ስብስብ በስተመጨረሻ የመጣ አጭር ልብ ወለድ ነው፡፡ ታሪኩ የሚያጠነጥነው በሁለት መስከረሞች ዙሪያ ነው፡፡ የመጀመሪያው መስከረም ተራኪው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለ በክፍሉ እና በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ የታዘበውን የሚተርክበት ነው፡፡
ዋናዋ ገጸ-ባሕርይ አስቴር ቆንጆና የልቧን መኖር የምትፈልግ፣ የግብረገብ ትምህርት ጊዜ ደስ የሚላት ግን ገብረ ገብነት የጎደላት ናት፡፡ የግብረ-ገብ መምህሩ ደግሞ፣ ግልጽ ከሆነ ነገር ይልቅ የማይገባ ነገርን (ግእዝ ጉራማይሌ) የሚያዘወትሩ ናቸው፡፡ የስፖርት መምህሩ አስቴርን የሚወድ ነው፡፡ በክፍል ውስጥ ደግሞ፣ ዘውዱ መርኬና ግርማ አስቴርን ይወዳሉ፡፡ የአስቴር የክፍል ጓደኛ ለምለም አስቴርን ታከብራለች፡፡ የአስቴር ውበትና ነጻነት አንዱን ጐረምሳ አነሳሥቶት ኖሮ ለመሳም ወይም ለመዳበስ ሲሞክር በተማሪዎች ዕይታ ሥር ወደቁና በድንጋይ እየተቀወሩ በአደባባይ ተዋረዱ፡፡

ተራኪው ሁለተኛው መስከረም ደግሞ፣ ሥራ ተቀጥሮ የመጀመሪያ ደመወዙን በቢራ ለማወራረድ ወደፒያሳ ባመራ ጊዜ ያጋጠመውን የሚተርክ ነው፡፡ አስቴር የቡና ቤት አስተናጋጅ፣ ግርማ ደግሞ የአስቴር ደምበኛ ሆነው የተገኙበት ነው፡፡

በዚህ አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ተራኪውን እንውሰድ፡፡ ዙሪያ ገባውን ሲተርክልን ልቡን እናነባለን፡፡ ግድ የለሽ ነው፤ ምንም የሚገደው ወይም ምንም ነገር ቋሚ ስሜት የሚሰጠው ሰው አይደለም፡፡ አስቀድሞ እንዲህ ይላል፥
‘የግብረ-ገብ አስተማሪያችን (ስማቸውን ረስቸዋለሁ) መማሪያ ክፍላችን ውስጥ ከፊት ለፊታችን ያለውን ጠረጴዛ በጐን ተደግፈው ቆመው ስለሃይመኖተ-አበውና ስለመሳሰለው በግእዝና በዐማርኛ የሚያወሩን ሱፐር ጉራማይሌ ገብቶኝ አያውቅም’ (ገጽ 221)
በዚህ አጭር ገለጻ ውስጥ ሁለት ነጥቦችን ማየት እንችላን፤ ግድ የለሽነትና ምንምነት፡፡ ግድ የለሽነቱ ተራኪው የመምህሩን ስም መርሳቱ ነው፡፡ የአስተማሪን ስም መርሳት ግድ የለሽ ያሰኛልን? ይመስላል፡፡ የግብረ-ገብ አስተማሪን ስም መርሳት የሌሎች አስተማሪዎችን ስም እንደመርሳት ቀላል አይደለም፡፡ ሌሎቹ አስተማሪዎች “ጋሼ” ወይም “እትዬ” ተብለው የሚጠሩ፣ በአለባበሰቻው ተመሳሳይ፣ በኑሮ ስልታቸው ሁሉ ወደአንድ ዓይነት የሚያጋድሉ መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ የአስኳላ ተማሪዎች ናቸውና በትንሹም ቢሆን ዘመናዊነት ሳይኖርባቸው አየቀርም፡፡
የግብረ-ገብ መምህር ግን፣ በትምህርት ቤቱ ከአንድ በላይ የመኖር ዕድሉ ጠባብ ነው፤ በዚያ ላይ አለባበሰቸው ለየት ያለ፣ የስም ቅጥያቸውም “ጋሼ” ወይም “እትዬ” ሳይሆን፣ “አባ” ወይም “መሪጌታ” ወይም እንዲህ ያለ ከመሆን አልፎ ስማቸው በቀጥታ የዐማርኛ ስም ስለማይሆን ለየት ማለቱ አይቀርምና የግብረ -ገብ መምህርን ለመርሳት ሰበቡ ግድ የለሽነት ይሆናል፡፡
ሁለተኛው ነገር ምንምነት ነው፡፡ ‘መምህሩ የሚያስተምሩን ነገር ገብቶኝ አያውቅም’ ይላል ተራኪው። ግብረ-ገብ አስተማሪው የሚያስተምሩት የክርስትና አስተምህሮ መሆኑን ጠቆም አድርጓል። ይህ “አይገባኝም” ካልን፣ የፍሬደሪክ ኒቼን ‘እግዚአብሔር ሞቷል’ መፈክር እየደገመልን ነው ማለት ነው፡፡

በዚህ አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ሌላ የተራኪውን ገለጻ እናንሣ፡፡ በመጽሐፉ ገጽ 223 በአጭር ልብ ወለዱ ሁለተኛ ገጽ ላይ ተራኪው እንዲህ ይላል፥
‘የመዝሙር ነገር ከተነሣ ሦስተኛ የመዝሙር ደብተር ነበረን፡፡ ይሄ ደግሞ፣ መዝሙር አስተማሪያችን ጋሽ እንግዳ አስጽፎ የሚያስጠናን የእንግሊዘኛ ሶንግስ የተሰበሰቡበት ነው፡፡ መዝሙር አንላቸውም ሶንግስ ነው፡፡ ሶንግ ደግሞ፣ ከመዝሙር የሚበልጥ ይመስለናል፡፡ ያ ሶንግ አለህ ብሎ አንዱ ከጠየቀ የእንግዳ እንግሊዝኛ ነው ማለት ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እንግሊዘኛ አምላኪ ዝንጀሮ የሆንበት ምክንያት ቀላል ነው፡፡ አባቶቻችንና እናቶቻችን ዝንጀሮ ስለነበሩ ነው፡፡ የእነዚህ ሶንግስ ቁጥር ሃያ ይደርሳል’
በዚህ ገለጻ ውስጥ ሁለት ነገሮችን ልብ ማለት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው፣ ማኅበራዊ ሂስ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዲበአካላዊ ጥያቄ (metaphysical quest) ነው፡፡ በዐማርኛ መዝሙር ሲባል ስሜት የማይሰጣቸው የሚመስሉቱ ሶንግ ተብሎ በእንግሊዘኛ ሲጠራ እንደአዲስ ወይም ትልቅ ነገር መውሰዳቸውን መጥቀሱ ማኅበራዊ እውነታ ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ከዚህ ማኅበራዊ እውነታ ላይ ይነሣና ‘ማኅበረሰቡ እንግሊዘኛ አምላኪ ዝንጀሮ ነው’ ብሎ ይሄሳል፡፡ ከዚህ ሂስ ላይ ተነሥቶ ደግሞ፣ ሌላ ዲበአካላዊ ጥያቄ ያነሣል፤ ‘ስለምን እንግሊዘኛ አምላኪ ሆንን?’ የሚል፡፡ ለዚህ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ‘ያው ዝንጀሮ ስለሆንን ነው’ የሚል ነው፡፡

እዚህ ጋ አንድ ነገር ልብ ማለት ይቻላል፤ ተራኪው በራሱ ጊዜ ያመጣውን ዲበአካላዊ ጥያቄ ለመመለስ እንኳ ወኔው የሌለው መሆኑን፡፡ ‘ለካ እንግሊዘኛ አምላኪ የሆንነው ከልጅነት ጀምሮ እንግሊዘኛ ትልቅ ነገር እንደሆነ አድርገው ስላሳደጉን ነው’ ብሎ ይደመድማል ብለን ስንጠብቅ ‘እንግሊዘኛ አምላኪ ዝንጀሮ የሆንነው ያው እናት አባቶቻችን ዝንጀሮ ስለነበሩ ነው’ ብሎ መመለሱ አንድ ከፍተኛ ደረጃ ስልቹነት ያለበት፣ ሁለትም ዕይታው ቁስ አካላዊ (materialist) መሆኑን ያሳያል፡፡

መሰልቸት ከሕይወት ላይ ትርጉም ማጣት ወይም ‘ሕይወት ትርጉም አልባ ናት፤ ዓለምም እርባና ቢስ ናት’ የሚለው ንሂሊያዊ ዕይታ የመነጨ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ሌላው ነጥብ ደግሞ ንሂሊስቶች ኤፕስቲሞሎጅካል ፍልስፍናቸው ወይም የዕውቀት ንድፈ-ሐሳብ መንገዳቸው ማቴሪያሊዝም መሆኑን በንድፈ-ሐሳባዊ ማዕቀፋችን እንዳየነው ሁሉ በዚህ ገለጻ ውስጥም ተራኪው ንሂሊያዊ ዕይታ የተጠናወተው መሆኑን ልብ ማለት ይቻላል፤ ‘ዓለምን ፈጣሪ ፈጠራት’ ከሚለው እምነታዊ (idealism) በተቃራኒው ‘ዓለም ቁስ አካላዊ አፈጣጠር አላት’ የሚል አመለካከትን ያራምዳልና፡፡
የተራኪውን ሌላ ገለጻ መመልከቱ ‘ተረኩ በንሂሊያዊ ፍልስፍና የተቃኘ ነው’ የሚለውን መከራከሪያ እውነት ሊያደርገው ይችላል፡፡

“ጋሽ እንግዳ ሲቀይረው ያላየሁት ጥቁር ሱፍ ኮት ይለብሳል፡፡ (ልብ ሳልል ቀርቼ ካልሆነ) የሸሚዙ ክሳድ በኮቱ ክሳድ ጭነት ያለሥርዓት ሁልጊዜ እንደተጣጠፈ ነው፡፡ አቶ እንግዳ በትንሹም በትልቁም ጉዳይ በጩኸት ተናግሮ መግባባት ይፈልጋል፡፡ ከእያንዳንዱ እዚህ ግባ ከማይባሉ ቁርጥራጭ ጉዳዮች ትልቅ አንድ ወጥ ታሪክ ይሠራል፡፡ ይሄ የማገናኘት ችሎታው ያስቀናል፡፡ የሚያያዝ የማይመስለውን ሲያያይዝ በፈገግታ ይከፋፍተናል” (ገጽ 223)

ተራኪው በዓለም ውስጥ ትርጉም አልባነት የተጠናወተው ትዝብትን የሚታዘብ ንሂሊስት ነው፡፡ በዚህ ንሂሊያዊ ዕይታው ጋሽ እንግዳን ሲመለከተው ለውጥ የሌለው ሰው ነው፤ ክሳዱ የተጣጠፈ አንድ ኮት የሚለብስ፣ የማይገገጣጠም ታሪክን እየገጣጠመ ለመሣቅና ለማሣቅ የሚሞክር፡፡

ይህ ሁሉ የዕለት ከዕለት ሕይወቱ የሆነ ሰው ነው፤ ጋሽ እንግዳ፡፡ በዚህ ትረካ ውስጣዊ መሥመሮች ውስጥ የሚነበበው ተረክ ‘ሕይወት ከዚህ ውጭ አይደለችም፤ ትናንት የተለበሰው ዛሬ እና ነገ፣ ትናንት የምንታወቅበት ዛሬና ነገ የምንታወቅበት፤ ከዚህ የዘለለ የሕይወት ፋይዳ የለም’ የሚል ነው፡፡ ንሂሊስቶቹ ‘ሊያምን የሚናፍቀው ሌሎች እያንዳንዳቸው የሚያኑትን ነው’ ከሚሉት ገለጻ ጋር መሳ

ለመሳ የሚሆን ትረካ ነው፡፡

“እንዳዘዙን ብንዘምርም፣ ሁለቱም አስተማሪዎች እንደሚፈልጉት አምሮልን አያውቅም፤ ከፊሎቻችን አላጠናነውም፤ ከፊሎቻችን ግድ የለንም፡፡ ከፊሎቻችን ሁሉ ነገር ደብሮናል፤ ከፊሎቻችን ሐሳባችን ሁልጊዜ ሌላ ጋ ነው፡፡ ከፊሎቻችን ደክሞናል፤ ታዲያ፣ ሁለቱም አስተማሪዎች ያማረ የተዋጣለት መዝሙር ማዳመጥ ሲፈልጉ አስነሥተው የሚያስዘምሩት አስቴርን ነው፡፡ አንዴ ከተዘመራላት በኋላ ግጥም ይሰጣታል፡፡ በሚቀጥለው ቀን ሁሉንም በቃሏ አጥንታ ደብተር ሳትገልጥ ከአስተማሪዎቹ አሳምራ ትዘምራለች” (ገጽ 224)

የተራኪው ንሂሊያዊ ዕይታ ጫፍ የደረሰበት ገለጻ ይመስላል፡፡ በንድፈ -ሐሳባዊ ማዕቀፋችን ለማየት እንደሞከርነው፣ ንሂሊስቶች የመጨረሻ ግባቸው ግለሰባዊ ነጻነት ነው፡፡ ግለሰቡ ነጻነቱ ከታወጀለት በኋላ ወይም ፍልስፍናውን ይገድላ ወይም ራሱን ይገድላል፣ አለዚያም አምኖ ትርጉም የሌላት ሕይወቱን በባይተዋርነት ይኖራል፡፡ በዚህ የተነሣ ተቋማዊ አሠራሮችን ይጸየፋሉ ብቻ ሳይሆን ይፋለማሉ፡፡ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ማኅበራዊ ተቋሞች ጥቅም አልባ ብቻ ሳይሆኑ ጐጂ ናቸው፤ ለንሂሊስቶች፡፡

የመስከረምና መስከረም ተራኪም ይሄንን ይገልጻል፤ ‘አንድን መዝሙር አብራችሁ ዘምሩ ስንባል ተሳክቶልን አያውቅም’ ይላል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በአንድ ተቋም ሥር መተዳደር አይችሉም፡፡ አንዳንዶች ይሰለቻቸዋል፤ አንዳንዶች ትኩረት ማድረግ አይችሉም፤ አንዳንዶች ሐሳባቸው ሌላ ቦታ ነው፤ አንዳንዶች ሰነፎች ናቸው፤ አንዳንዶች ለጉዳዩ ደንታ አይኖራቸውም። በጠቅላላ፣ በየራሳቸው ዓለም ውስጥ ስለሆኑ በአንድ ተቋም ሥር እነዚህን ሰዎች ማቀፍ ጥፋት ነው የሚል ድምፀት አለው፡፡ የዚህ አስረጅ የሚሆነው አስቴር ለብቻዋ ዘምሪ ስትባል በሙሉ ፈቃድ፣ በጥሩ ሁኔታ ትዘምራለች፡፡ በጋራ ሲዘመር ተበላሽቶ የነበረው መዝሙርም የሚጣፍጥ መዝሙር ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነው፣ ንሂሊስቶች ግለሰባዊ ነጻነት ግባቸው የሚሆነው፡፡

በትረካው ውስጥ አስቴር በጣም ቆንጆ በመሆኗ ጋሽ እንግዳን ጨምሮ ተማሪዎች እና አስተማሪዎች ይመኟታል፡፡ አስቴር ይሄን ስለምታውቅ ትኩራራለች፤ አስተማሪዋን ሳይቀር በተማሪ ፊት ትዘባነንበታለች፤ በውበቷ በጣም ትመለካች፡፡ እንደግርማ ያለው ደግሞ፣ ‘ሌላ ሰው አያት’ እንኳ ብሎ በጣም ይቆጣል፤ ለድብድብ ይጋበዛል፡፡ ይህ ተረክ በመጀመሪያው መስከረም ከተነገርን በኋላ በሁለተኛው መስከረም ላይ አስቴር የቡና ቤት አስተናጋጅ ሆና ትመጣለች። ደራሲው ስለምን ቡና ቤት ላይ ጣዳት?

ያ ብዙዎቹ የእኔ ባደረግሁት ብለው የተመኙለት፣ አስተማሪ ክብሩን አጥቶ በተማሪ ፊት እስኪዋረድ የሰገደለት የአስቴር ውበት ትርጉም አልባ መሆኑን ለማሳየት ይመስላል፡፡ አሁን አስቴር ቡና ቤት ነው ያለችው፤ ገንዘብ ያለው የትኛም ሰው የፈለገውን እንዲያደርግ የምትከለክልበት አቋም ላይ አይደለችም፡፡ አሁን ውበቷን እንዲያዩላት፣ እንዲቀርቧት ብዙ ማባበያዎችን ታደርጋለች፡፡ ‘ዓለም ትርጉም አልባ ነው’ የሚለው ንሂሊያዊ የተራኪው ዕይታ በዚህ የተደመደመ ይመስላል፡፡
“ቦታና ጊዜ ቢለወጥም፣ አንዳንድ ጊዜ የሚስገምትም ይሁን የማያስገምት ‘አለመለወጥ’ ሥር ነቀል ለውጥ የሚመስልበት ጊዜ አለ” (ገጽ 237)

ተራኪው በዚህ ትረካ ነው ተረኩን የሚዘጋው፡፡ ምን ማለቱ ይሆን? ይህን መረዳት ቀላል ይመስላል፡፡ ‘አለመለወጥ ሥር ነቀል ለውጥ የሚመስልበት ጊዜ አለ’ ይለናል፡፡ ትፈርሳለህ፣ ግን የተሠራህ ያህል ነው፤ ትሠራለህ፣ ግን የፈረስክ ያህል ነው፡፡ ንሂሊስቶቹ ‘የሟች ሕይወቱ ሞቱ ነው’ የሚሉት ነው፡፡

ማጠቃለያ

አዳም ረታ በመስከረምና መስከረም አጭር ልብ ወለድ ንሂሊያዊ ዕይታን አንጸባርቋል፡፡ በዚህ አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ሕይወት ይህ ነው የተባለ ወጥ ትርጉም የላትም፡፡ በዚህ አጭር ልብ ወለድ ውስጥ ዓለም እርባና ቢስ፣ ዋጋ የለሽ የዘውዘው፣ የከንቱነት መንከላወሻ ናት፡፡ ተቋማት በዚህ ትረካ ውስጥ ጥቅም አልባ ናቸወ፤ የግለሰቦችን ነጻነት የሚጋፉ ናቸው፡፡ ሕይወት በዚህ አጭር ትረካ ውስጥ እየተኖረ የሚሞትባት ሳትሆን፣ እየተሞተ የሚኖርባት ናት፤ ያኛው መስከረም መኖርን፣ ይህኛው መስከረም መፍረስን የሚናገሩባት፣ የሚሄደው የሚመጣባት፣ የሚመጣው የሚሄድባት ትርጉም አልባ ክፈፍ ናት፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top