ታዛ ዐለማት

“ተፈጥሮ” እና “ፈጠራ” (ተዝቆ የማያልቅ በረከት)

መግቢያ

በመጀመሪያ ለመግባባት እንዲያመች፣ በጽሑፉ “ተፈጥሮ” እና “ፈጠራ” ምን ማለት እንደሆኑ ማብራራት ያሻል፣ ስለሆነም “ተፈጥሮ” “ሰበ-ነክ ያልሆኑ ክስተቶችን” (ሕያው እና ግዑዝ) እና “ፈጠራ” “ሰበ-ነክ የሆኑ ክስተቶችን” ገላጮች ናቸው፣ የሚል ትርጉም ነው በጽሑፉ የሰጠኋቸው፡፡ “ፈጠራ” “ተፈጥሮን” አስመስሎ ወይም የተፈጥሮን “ነባራዊ” እይታ አንግቦ፣ በተፈጥሮ የተገኘን አካል አስመስሎ ቀርፆ ፣ ከተፈጥሮ ጋር የሚያገናኝ፣ የሚያመሳስል ድልድይ መዘርጋት እንደ ማለት ይወሰድ፡፡

መጋቢት 1/ 2013 ዓም የአዲስ አበባ አካል በሆነው፣ “በአለ ሥነጥበባት እና ዲዛይን ትምህርት ቤት”፣ አንድ “የፓነል” ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ “የፓነሉ” አባላት የተውጣጡ፣ ከኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ ሕንፃ ግንባታ፣ እና ከተማ ልማት ተቋም፣ ከሥነ ጥበባት እና የዲዛይን ኮሌጅ፣ ከአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ እና ከተፈጥሮ ሳይንስ ፋካልቲ ነበር፡፡ “የፓነሉ” ውይይት የተዘጋጀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰባኛ ዓመቱን ሲያከብር፣ በዩኒቨርሲቲው የታቀፉ ኮሎጆች እና ፋካልቲዎች፣ ሦስት አራት እየሆኑ በቡድን ተደራጅተው፣ የበዓሉ አካል ሆነው፣ ለበዓሉ ግብዓት የሚሆኑ ትምህርታዊ መሰናዶዎች ለማስተናገድ ነበር፡፡ “በፓነሉ” ውይይት ላይ በጨረፍታም ቢሆን የተፈጥሮ ሳይንስ እና የሥነ ጥበባት፣ ብሎም የቴክኖሎጂን ቁርኝት ለመፈተሽ ተሞክሮ ነበር፡፡ በዚያ መንስዔ በጨረፍታ ተወስቶ የነበረውን፣ ማለት “የተፈጥሮን” እና “የፈጠራን” ግንኙነት ሳይንስን ከማኸዘብ አንፃር ተነስቼ፣ ይህችን ጽሑፍ ለአንባብያን ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡

“የአሳብ” (Idea) እና “የእውን” አካል/ “እውናዊ” (Reality) ቅደም ተከተል “ፈላስፋዎችን” ለዘመናት እያወዛገበ ይገኛል፣ ጎራው ለሁለት ተከፍሎ “በአሳብ” ቀዳሚነት የሚያምኑ “አሳብያን” (idealist)፣ “በእውናዊ” ቀዳሚነት የሚያምኑ “እውናዊ” (realist / materialist)፣ ተብለው ይመደባሉ፡፡ በ “እውናዊያን “(realists) የሰው ልጅ ከነባር ሁኔታ ውጭ ማሰብ አይችልም ሲሉ፣ “አሳብያን” (idealist)፣ ደግሞ፣ የለም በተቃራኒው ነባር ሁኔታ የሚባለውን የሚወስነው “አሳብ” ነው ይላሉ፡፡ በእኔ አስተያየት የሰው ልጅ የሌለን ነገር ሊያስብ አይችልም፤ “የአሳብ” መሠረቱ፣ “ጽንሰ ሃሰቡ” (concept) “እውን ዓለም” ዙሪያ ያጠነጠነ፣ ያሉ፣ የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ፣ የሚሰሙ ጉዳዮች እና አካለት (Real objects) ላይ ነው፣ ስለሆነም እነሱ “የአሳብ” መሠረት ናቸው፡፡ “እውን” ጉዳይ ነው ወደ “አሳብ” የሚመነዘረው፡፡ ለምሳሌ የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ “እውን” ያልሆነ አካል (አካሉን መሰል በዓለማችን ላይ የማይታይ/የማይታወቅ) የቀረፀ፣ ከዛሬ 35ሺ ዓመት በፊት እንደነበረ ይነገራል፡፡ ያም ከእንሰሳ ጥርስ የተቀረፀ ምስል፣ ከላይ የአንበሳ ጭንቅላት እና የቀረው አካሉ የሰው ገላ መሰል የነበረ ነው፣ “አንበሳው ሰው” (The Lion Man) በመባል የሚታወቀው፡፡ ይህም ቢሆን “አሳብ” “ከእውናዊው” በፊት እንደተገኘ አያመለክትም፣ ምክንያቱም፣ ምንም የተቀረፀውን ዓይነት ፍጡር ባይኖርም፣ አንበሳ አለ፣ ሰው አለ፣ ስለሆነም ከሁለት እውን ከሆኑ አካላት የተደባለቀ/የተደቀለ እንጂ የሌለ አካል፣ “ከአሳብ” የመነጨ አይደለም፡፡ መሠረቱ እውን አካላት ናቸው፣ አንበሳ እና የሰው ልጅ፡፡ የፍልስፍና ውዝግቡን ተወት አድርገን ወደ ትረካው አንመለስ፡፡

የሰው ልጅ እንደ አእዋፍ ለመብረር ምኞት ካነገበ ዘመናትን አስቆጥሯል፣ ምኞቱም “በግሪክ ሚቶሎጂ” (Greek mythology)፣ ቅደመ ታሪክ ትርክት ተወስቷል፣ እነሆ፡፡ ጥበበኛው “ዴዳሉስ” (Daedalus) ጠላትን ረድተሃል ተብሎ በወገን ተጠርጥሮ፣ ከልጁ ከ”ኢካሩስ” (Icarus) ጋር ወህኒ ቤት ታግተው ሳለ፣ ጥበበኛው “ዴዳሉስ”፣ ለራሱ እና ለልጁ፣ በሰም በተጠባበቁ ላባዎች ክንፎች ሠርቶ፣ አባት እና ልጅ በበረራ ከእገታ (ወህኒ ቤት) ለማምለጥ ቻሉ፡፡ ሆኖም ወጣቱ “ኢካሩስ” ከልምድ ማነስ፣ ብሎም ምክርን ካለማጤን መንስዔ፣ በጣም ከፍ ብሎ ስለበረረ፣ የክንፎቹን ላባዎች ያጣበቀው ሰም፣ በፀሐይ ኃይል ቀልጦ፣ ክንፎቹ ተበታትነው፣ ባህር ላይ ወድቆ ለሞት ተዳረገ፡፡፡
በቅድመ ታሪክ ህዝቦች፣ በብዙ አካባቢ ለምሳሌ በግብፅ፣ “በፐርሽያ”፣ “በሜሶፖታሚያ” አማልክቶቻቸው ባለ ክንፎች እንደነበሩ ያምኑ ነበር፡፡ “ቸሩቢሞች” (Cherubim) እና “ሴራፊሞች” (Seraphim) ዓለማዊ (ምድራዊ) ያልሆኑ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው ተብለው ነው “በዘርፈ-አብርሃም” ሃይማኖቶች (ይሁዲ፣ ክርስትና እና እስልምና) የሚታመኑት፡፡ እነሱም አብዛኻኙ ባለክንፎች እንደነበሩ ነው የሚታመን፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው የሰው ልጅ ምኞት፣ ጉጉት፣ የሕይወት ባለፀጋዎችን መሰል አቅም ለመገንባት ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምሳሌ አእዋፍን ተመልክቶ፣ እነሱን መስሎ መብረር መመኘት ነበር፡፡ ምንም ቀደምት “የሚበር መኪና” (flying machine) መገንባት ባይችሉም፣ በጣም የታወቀው የጣሊያን ሊቅ፣ “ሊዮናሮዶ ዳ ቪንቺ” (Leonardo da Vinci/1452-1519) የአእዋፍን የአካላት ተግባር እና መዋቅር በደምብ አጢኖ፣ ትዕይንቱን/ ሃሳቡን (Observation) ለመብረር የሚያገለግል መሣሪያ ፍብረካ የሚውል እቅድ፣ ስዕል፣ ነድፎ ነበር፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመብረር የቻሉት “የራይት ወንድማማቾች” (the Wright Brothers)፣ ብዙ ግንዛቤ የቀሰሙት የእርግቦችን በረራ በማስተዋል/ በማጥናት ነበር፡፡ ዘመናዊ የአይሮፕላን ክንፎችን ቅርፅ የመቅረፅ ሃሳብ የመነጨው በአእዋፍ፣ እንዲሁም በሌሊት ወፍ ክንፎች የበረራ ስልት ላይ ተመሥርቶ ነው ይባላል፡፡

የሰው ልጆች በመሠረቱ ስለ አካባቢዎቻቸው መረጃ ለማግኘት ይጥራሉ፣ ብሎም መረጃ ያካብታሉ፡፡ አንዳንድ ጠቃሚ የሚመስሉ ኩነቶችን አስተውለው፣ ለችግር መፍቻ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱትን ከተፈጥሮ ለመኮረጅ ይሻሉ፡፡ ቢሊዮን ዓመታት ወስዶ፣ በዝግመተ ለውጥ (evolution) የተገኘን ችሎታ፣ ተፈጥሮን በመኮረጅ፣ የሰው ልጆች ያንን ዓይነት ችሎታ በአጭር ጊዜ እየተቀናጁ ይገኛሉ፡፡

የሕያውን የገላ መዋቅር ኮርጆ፣ አምሳያ መፈብረክ (“ባዮሚሚክሪ”/ Biomimicry) ይባላል፡፡ በቴክኖሎጂ ጥናት ላይ የተሰማሩ ብዙ ባለሙያዎች፣ ከሕያው አካል ቅርፆች ላይ የተመሠረተ፣ የቴክኖሎጂ ግብዓት (ምንጭ) ለመሆን የሚችሉ የሕያው ተግባራት እንዳሉ ያምናሉ፡፡ ባጭሩ የሕያው አካል ብሎም ተግባር የቴክኖሎጂ እድገት ማመንጫ፣ ማዳበሪያ ቋቶች እንደሆኑም ያምናሉ፡፡

በዝግመተ ለውጥ ሕያው የተጎናጸፏቸው የአካል ክፍሎች፣ ተግባር ተኮር ሆነው የታነፁ ናቸው፡፡ ተግባሮች በሚከናወኑበት ጊዜ፣ ብክነት-አልባ ሆነው፣ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር ተጣጥመው/ተስማምተው/ ተሳልጠው ነው የሚካሄዱት፡፡ ሂደቱም ብዙ ኃይል፣ ብሎም የተለየ የኃይል ምንጭ (ነዳጅ) አያስፈልገውም፡፡

“ከተፈጥሮ ተኮርጀው” በተግባር የተተረጎሙ ኩነቶች

የሰው ልጅ ጥቂት የሕያው ባህርያትን በማጥናት እና በመገንዘብ፣ መሰል ተግባራትን ለመፈጸም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን እየፈበረከ ነው፡፡ እንስሳትን በማጥናት የጀልባ ቅርጾች መዋቅር ለመቀየስ፣ የሰው ሠራሽ ተንቀሳቃሽ አካልን “ሮቦት” (robot) እግር እና እጅ ለመገንባት፣ የአውሮፕላን አካል ቅርፅ ለመቀየስ ተችሏል፡፡ ሰው ሠራሽ “አእምሮ-አከል” ችሎታ ያነገቡ “ሮቦቶች” በብዙ አካባቢ በመፈብረክ ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ሂደት በአውስትራሊያ የሚገኙትን “ካንጋሩ” (kangaroo) የሚባሉ እንስሶችንም የሚመስል እንቅስቃሴ፣ እመርታ ያላቸው “ሮቦቶች” ተገንብተዋል/ ተፈብርከዋል፡፡ “ሮቦቶች” በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ፣ ቴክኖሎጂው “ባዮኒክ ካንጋሩ” (Bionickangaroo) የሚባል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ እንዲሁም የአቦሸማኔን እንቅስቃሴዎች በማጥናት፣ ፈጣን እና ከፍ ያለ የመዝለል ችሎታ ያላቸው “ሮቦቶችን” ለመገንባት ታስቧል፤ አሁን 15 ኪ.ሜ በሰዓት የሚጓዙ፣ እንዲሁም መጠነኛ ከፍታ ዘለው ማለፍ የሚችሉ “ሮቦቶች” ተፈብርከዋል፡፡

አንድ መጠነ-ውስን የሆነ አሳ አጥማጅ ወፍ አለ፣ “ኪንግ ፊሸር” (kingfisher) የሚባል (ይህን የወፍ ዘር በብዛት ሃዋሳ ሐይቅ አካባቢ ማየት ይቻላል)፡፡ “ኪንግፊሸር” (Kingfisher) ከውሃው በላይ ሆኖ፣ ውሃ ውስጥ ያለን አሳ ተመልክቶ፣ ድምጽ ሳያሰማ ወደውሃው እንደጦር ተወርውሮ ገብቶ፣ ያደነውን አሳ አንጠልጥሎ፣ ከውሃው ውስጥ ተመንጥቆ ይወጣል፡፡ ይህ የወፍ ዝርያ፣ ከውሃ ውስጥ አሳ ለማውጣት “ምንቃሮቹን” (መንቆር) አሹሎ፣ እንደ ጥይት ተወርውሮ ወደ ውሃ ውስጥ ሲገባ፣ ድምፅ አያሰማም፣ ውሃውንም አያንቦራጭቅም፡፡ ይህንን በማስተዋል፣ በማጤን፣ አንድ የጃፓን ተመራማሪ፣ “ኢጂ ናካትሱ” (Eiji Nakatsu) የሚባል፣ የዚህን ወፍ “ምንቆር”/ “ምንቃር” አስመስሎ፣ የባቡርን የፊትለፊት አካል በመገንባት፣ “ሽንካሴን” (Shinkansen)/ በመባል የሚታወቅ፣ ጥይት መሰል ባቡር (Bullet train) ሊፈበርክ ችሏል፡፡

ይህ ጃፓን አገር የተፈበረከው፣ “ጥይት ባቡር” (bullet train) የሚያወጣውን ፍንዳታ መሰል ድምፅ፣ በጣም ለመቀነስ አስችሏል፡፡ ፍንዳታ መሰል ድምፅ ይከሰት የነበረ፣ ባቡሩ በከርሰ ምድር ሲጓዝ፣ ከፊቱ የሚገኘውን አየር እየገፋ፣ እያመቀ፣ ተጉዞ፣ “ከምድር-ከርስ” ሲወጣ፣ ታምቆ የነበረው አየር በፍንዳታ መልክ ይበተናል፡፡ መፍትሄው ከባቡሩ ፊት ያለው አየር እንዳይታመቅ ማድረግ ነበር፡፡ የባቡሩን አፍንጫ፣ የፊት ቅርፅ የ”ኪንግፊሸር” (Kingfisher) የፊት አካል አስመስሎ በመቅረፅ፣ ባቡሩ አየሩን ገለል እያደረገ፣ በአየሩ መኻል ሾልኮ እንዲሄድ (ማለት አየሩን ወደ ፊት ሳይገፋ)፣ ብሎም አየሩ እንዳይታመቅ ማድረግ መቻል ነበር፡፡ እፍንጫው “የኪንግፊሸርን” የፊት ቅርፅ አስመስሎ ለመሥራት ስለተቻለ፣ ባቡሩ ከከርሰ- ምድር ሲወጣ፣ የፍንዳታው አቅም፣ መጠን፣ በጣም ቀነሰ፣ የአካባቢውም ሰው ከድንጋጤ ተገላገለ፡፡

“ሄሊኮፕተር” አሠራር የተኮረጀው ከበራሪ እንስሳ ነው፡፡ ወንዝ አካባቢ አራት ክንፎቻቸው እንደተዘረጉ፣ ከአለት ወደ አለት ብር/ ቱር የሚሉት “ደራጎን ፍላይስ” (dragonflies) በመባል የሚታወቁት፣ ከሦስት አፅቄዎች (insects) ዝርያዎች ነው የተኮረጀው:: እነኝህ ሦስት አፅቄዎች በበረራ ላይ እያሉም፣ አንድ ቦታ ላይ ብቻ (ሳይንቀሳቀሱ) ሊንሳፈፉ ይችላሉ፡፡ ባጭር ጊዜ (ጊዜ ሳይፈጁ)፣ ዞረው፣ በተቃራኒው አቅጣጫ ሊበሩ ይችላሉ፡፡ ከየትኛውም “የሄሊኮፕተር” ዓይነት በላቀ ይዘት፣ ሁኔታ፣ ስልት፣ መዘዋወር (ማረፍ/ መነሳት፣ አቅጣጫ መቀየር) ይችላሉ፡፡

“ደራጎን ፍላይ” (dragonfly)
“ሄሊኮፐተር”(helicopter)

በጣም የተለያዩ የሕያው አካላት (መዋቅሮች)፣ ለምሳሌ አጥንት፣ ዛጎል፣ ቀርቀሃ፣ወዘተ በቀላሉ አይፋቁም፣ አደጋ የመቋቋም ባህርይ አላቸው፡፡ ስለሆነም በቀላሉ የማይፋቅ፣ የማይርስ፣ የማይበሰብስ፣ ቁሳቁስ ለመፈብረክ፣ የሰው ልጅ የነኝህን ሕያው አካላት ባህርይ እየኮረጀ ነው፡፡

የብዙ እፅዋት ቅጠላቅጠል በውሃ አይርሱም፣ አይበሰብሱም፣ የውሃ ጠብታዎች ሲያርፍባቸው ኮለል ብለው ነው ጠብታዎች ከቅጠሉ የሚከሉ፡፡ ይህን በማስተዋል እና በመኮረጅ፣ ውሃ የማያጥባቸው (የማይከላቸው) የግድግዳ ቀለሞችን (“ውሃ አይደፈሬ”/ Water repelling / Water proof) እና ሌሎች ቀለማትን ለመፈብረክ ተችሏል፡፡

የቀንድ አውጣ የሚያመነጨው “ልጋግ/ ንፍጭ” መሰል ዝልግልግ ፈሳሽ የማጣበቅ አቅሙ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ በተጨማሪም መርዛማ አይደለም፣ በጤና ላይ እንከን አያስከትልም፡፡ ስለሆነም ይህንን ዓይነት ፈሳሽ በኩረጃ በመፈብረክ፣ በልብ ላይ የሚከሰቱ ክፍተቶችን ለመድፈንም ሆነ “ልም-አፅም” (cartilage) ለመጠገን፣ሐኪሞች እየተጠቀሙበት ነው፡፡

የመጨረሻው ኩረጃ “ሰውን” ራሱን መኮረጅ ነው፣ሰው ሠራሽ ሰው መሥራት (መፈብረክ)፡፡ ይህንንም ፍላጎት ለማሟላት የሰው ልጅ ብዙ ተጉዟል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ቀደም ብዬ ካሳተምኩት “ከየት ወደ የት?” ከሚለው መጽሐፍ በገፍ ልዝረፍ፡፡ “በዘመናችን ሁለት ዓይነት ሰው-ሠራሽ ብሩህ አእምሮ (Artificial Intelligence) ለመገንባት ምርምር እየተካሄደ ነው፡፡ አንደኛው ጠባብ ተብሎ የሚታወቀው ምርምር በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድን ግለሰብ ፊት መለየት (ገፅታ ለይቶ ማወቅ)፣ ወይም በኢንተርኔት መረጃ ፍለጋ ሂደት ወይም መኪና መንዳት ላይ ያተኮረው ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ምርምር ጠቅለል ያለ እና ሰፊ ይዘት ያለው ነው፡፡ ሰፋ ላሉ ተግባራት ትኩረት የሚሰጥ ሰው-ሠራሽ ብሩህ አእምሮን ለመፈብረክ የሚያስችል ምርምር ነው፡፡

ጠበብ ያለው ምርምር ውጤት “በቸስ”(Chess) ውድድር የሰው ልጅ “ቻምፒዮኖችን” የሚያሸንፍ፣ መኪና ካለምንም እገዛ የሚነዳ ወዘተ. አበርክቷል፡፡ ይህም እንደተማረ ሰው ሊቆጠር ይችላል፡፡ የተማረ ሁሉ አስተዋይ አይደለም፣ አስተዋይነት የሚዳብር፣ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ከልምድ፣ ከተሞክሮ ጋር ተዋህደው፣ ጥቅሙን እና ጉዳቱን ለመለየት ሲቻል ነው፡፡ ያ ነው አስተዋይነት የሚባለው፡፡
ሰፋ ያለው ምርምር ግን የሰው ልጆች ልዩ ተገግባሮች (ባህርይዎች) ናቸው ተብለው የሚገመቱትን ሁሉ ሊያስተናግድ የሚችል ሰው-ሠራሽ ብሩህ አእምሮ በመፈብረክ ላይ ያተኮረ ነው፣ ለምሳሌ ከፍተኛ የማገናዘብ ችሎታ ያለው፣ ውስብስብ ሁኔታዎችን በአጭር ጊዜ አጥልሎ መረዳት፣ ብሎም ግንኙነቶቻቸውን እና ልዩነቶቻቸውን አጥርቶ የሚለይ ነው፡፡

ይህ ሁለተኛው ዓይነት ምርምር ከሰው በጣም በላቃ ሁኔታ የሰው ልጅን መሠረታዊ ተግባራት ሁሉ የሚያከናውን፣ ተዓምር ለመፍጠር የሚችል፣ «መለኮታዊ መሰል» ተግባራትን ለማስተናገድ የሚችል ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ ስለሆነም “አልጎሪዝም” ያስከተለው ከፍተኛ ስጋት ከዚህ ምርምር ጋር በተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ችሎታ ያካበተ ሰው ሠራሽ ብሩህ አእምሮ የሰው ልጅን የሚተካ፣ ሕያው ሰውን ከራሱ የበታች አድርጎ የሚመድብ (የሚቆጥር)፣ የሰው ልጅን ሊገዛ የሚችል ይሆናል ተብሎ ነው የሚሰጋው”፡፡

በተፈጥሮ ኩረጃ ሂደት የወደፊት ምኞቶች

የሕያው ተግባራት ረቂቅ እንደ ባህር ሰፊም ስለሆኑ፣ ለችግሮች መፍትሄዎችን ለመፈለግ ሰፊ እድል ያበረክታሉ፡፡ ቴክኖሎጂ በምግብ እና በኃይል ማመንጨት አካባቢ፣ እንዲሁም በመረጃ ማከማቸት (ቋት) እና ጤና እንክብካቤ ላይ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ ቅጠላቅጠልን በማስተዋል፣ ተግባራቸውን በጥሞና በማጤን፣ ከፀሐይ በቀጥታ ኃይል ለማግኘት/ ለመጠቀም ሙከራ እየተደረገ ነው፡፡ እንዲሁም የሕዋስ (cell) ተግባራትን በማጤን፣ “በኮምፒውተሮች” ፍብረካ የሕዋሳትን ዘዴ መጠቀም (cell functions) አስመስሎ ለመሥራት ሙከራ እየተካሄደ ነው፡፡ የሰው ልጅ ለሕያው ተግባራት ትኩረት ሰጥቶ ምርምር የሚካሄድባቸውን ጥቂት ጉዳዮችን ላውሳ፡፡

መረጃ ማሰባሰብ/ማቀናጀት

ብዙ የተለያዩ እንስሳት ድምፅ አመንጭተው፣ አሰራጭተው፣ ከዚያም አካባቢው ከሚገኝ አካል ጋር ተጋጭቶ በሚመለሰው “ሞገድ” (የገደል ማሚቶ) አማኻኝነት፣ በአካባቢው ስለአሉት አካላት መረጃ መሰብሰብ ይችላሉ፡፡ (የገደል ማሚቶ ማለት በአንድ ድምፅ አመንጭ አካል የተሰራጨ ድምፅ ሞገድ፣ ከሌላ አካል ጋር ተጋጭቶ፣ ሞገዱ ተመልሶ ድምፁን ካመነጨው አካል ሲደርስ የሚሰማው ድምፅ ነው)፡፡ ተጋጭቶ በሚመለስበት ጊዜ እንደ ርቀት መለኪያነት ያገለግላል፣ለመመለስ ብዙ ጊዜ ከፈጀ ሩቅ፣ ቶሎ ከተመለሰ ቅርብ ካለ አካል ጋር እንደተጋጩ ግንዛቤን ያስጨብጣል፡፡ ይህም መረጃ ለብዙ ተግባራት ግብዓት ይሆናል፣ የጉዞ አቅጣጫን ለመምረጥ (አካባቢ ካለ አካል ጋር ላለመጋጨት)፣ ለምግብ ስብሰባ (አደን) እንዲሁም ከጠላት ለመሰወር፡፡

የገደል ማሚቶ ድምፁን ካመነጨው አከል ሲመለስ፣ ያመንጭው እንስሳ ሁለቱም ጆሮዎች ዘንድ በአንድ ጊዜ ተመልሶ አይደርስም፣ ጊዜው ውስን ቢሆንም፣ አንዱ ጆሮ ቀድሞ ይሰማል፣ ሁለተኛው ቀጥሎ ይሰማል፡፡ ስለሆነም አንድ ድምፅ አመንጭ እንስሳ ሁለት መልስ ተቀባይ መዋቅሮች አሉት፡፡

የተለያዩ የሌት ወፍ ዝርያዎች፣ የሚያመነጩዋቸው ድምፆች፣ የተለያየ የድምፅ ሞገድ ነው ያላቸው፡፡ ይህን የድምፅ ሞገድ በመመዝገብ፣ ለየሌት ወፎች ተመራማሪዎች የሌት ወፎች ዝርያዎች መለያ ለመሆን እያገለገለ ነው፡፡

የሌት ወፎች የአካባቢ ሁኔታ መረጃ ለማግኘትም ሆነ ለማሰራጨት የረቀቀ ስልት አላቸው፣ ድምፅ ከላንቃ ነው የሚያመነጩ፣ ልዩ እና ደመቅ ያለ ድምፅ አሰራጭተው፣ ከአካባቢው ጋር እየተጋጨ የሚመለሰው ሞገድ (የገደል ማሚቶ) የሚፈለገውን መረጃ ያበረክትላቸዋል፡፡ የሌት ወፎች ይህ ድምፅ በገደል ማሚቶነት ተመልሶ ሲመጣ፣ ድምፁን አጣርቶ ለመለየት የሚያስችል የጀሮ መዋቅሮች ባለቤቶች ናቸው፡፡ በአካባቢ ያለች “ትንኝ” እንኳ ብትሆን፣ ከገደል ማሚቶ በሚገኘው መረጃ መሠረት የት እንዳለች፣ ያለችበትን አቅጣጫ፣ ርቀቷን፣ የአካሏን መጠን፣ ወዘተ. ያካተተ መረጃ ያገኛሉ፡፡

የሌት ወፎች ላንቃ ድምፅ የሚያመነጭ “በተከመከመ ሞገድ” ድግግሞሽ “ሲግናል” “ኤፍ ኤም” [Frequency modulated (FM) signals] እና “በኢተለዋዋጭ” ድግግሞሽ “ሲግናል” “ሲ ኤፍ” [Constant frequency (CF) signal] ነው፡፡ “ኤፍ ኤም” ሞገድ ሰፋ ያለ ቦታ አዳርሶ ዙሪያውን በጠቅላላ ለመቃኘት ያስችላል፣ “ሲ ኤፍ” ደግሞ ጠበብ ያለ “ሠቅ” (band) ረዘም ላለ ጊዜ የሚለቀቁ ናቸው፡፡ በተለይ ጫካ ውስጥ “ሦስት አፅቄዎች” የሚያድኑ የሌት ወፎች በ “ሲ ኤፍ” “ሲግናል” ይጠቀማሉ፡፡ ስለሆነም የሌት ወፎች በ “ኤፍ ኤም” እንዲሁም በ “ሲ ኤፍ” “ሲግናሎች” በመጠቀም በጣም ከፍ ያለ የአካባቢ መረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡

በተጨማሪ በጣም የሚገርመው የሌት ወፎች የሚኖሩት ከሌሎች የሌት ወፎች ጋር በሚጋሩት፣ ጨለም ያለ ሥፍራ (ብዙውን ጊዜ ዋሻ) ውስጥ ነው፤ ቦታው ጠባብም ነው፡፡ የአካባቢው ደባሎች በመቶ ሺዎች ሊቆጠሩ ይችላሉ፤ ሁሉም ተመሳሳይ ድምፅ በአካባቢው ይረጫሉ፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ የሌት ወፍ ድምፅ ተጋጭቶ በገደል ማሚቶ መልክ የሚደርሰውን መረጃ ከየግል የድምጽ ሞገዶቻቸው እንደመነጩ የመረዳት (የመለየት) ችሎታ አላቸው፣ የግል የሬዲዮ ጣቢያ ዓይነት፡፡

የድምጽ ሞገድ መለያ መዋቅር መሰናዶ፣ የረቀቀ “ኮምፒዩተር-መሰል” “የሞገድ ተንታኝ” መዋቅር ነው፤ አንድ የሌት ወፍ በዚህ ዘዴ ተጠቅማ በአካባቢው የምትበር “ቢምቢን” አሳዳ ይዛ መመገብ ትችላለች፡፡ ይህ ሁሉ የሚስተናገደው፣ በይም ተበይም እየበረሩ ስለሆነ፣ የገደል ማሚቶውን ርቀትንም ሆነ ቅርበትን ይቀያይረዋል፡፡

የሌት ወፍ በበረራ ላይ፣ የጆሮ ሁኔታን ማስተዋል ይበጃል
የሚሰራጨው ድምፅ ሞገድ እና የሚመለሰው የገደል ማሚቶ

በተጨማሪም የሌሊት ወፎች በምድርም ሆነ በአየር ላይ የሚንቀሳቀሱ ትላትል እና “ሦስት አፅቄዎች” የሚያመነጩትን (የሚያስከስቱትን) ድምጽ የመመዝገብ፣ ከዚያም ከምን ዓይነት እንስሳ (ታዳኝ) ያ ድምጽ እንደመነጨ መረዳት ይችላሉ-ይህ ድምፅ “ከአባ ጨጓሬ”፣ ይህ “ከፌንጣ”፣ ይህ “ከቢራቢሮ” እያሉ! ይህ ቴክኖሎጂ ተኮርጆ፣ ማየት ለተሳናቸው ግለሰቦች እንዲያገለግል ሙከራ እየተደረገ ነው፡፡

አሳነባሪዎች ውሃ ውስጥ ሆነው መረጃ የመለዋወጥ ባህርይ አላቸው፣ መረጃው የሚተላለፈውም በድምፅ አማካኝነት ነው፡፡ የድምፁ ይዘት እንደ ቋንቋ ሀሉ ለመግባቢያነት ያገለግላል፡፡ ድምፅ በመሠረቱ በውሃ ውስጥ ሲጓዝ በአየር ውስጥ ከሚያደርገው ጉዞ በጣም በፈጠነ ይዘት ነው፣ ለምሳሌ በአየር ውስጥ 100 ኪ.ሜ በሚጓዝበት የጊዜ ተመን በውሃ ወስጥ 400 ኪ.ሜትር ይጓዛል፡፡ በውሃ ውስጥ ያለ ተንሳፋፊ አካል ሁሉ እይታ፣ በውሃ ውስጥ የብርሃን መጠን ውሱንነት ምክንያት፣ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ እንዲሁም የሽታ አመንጭ “ሞሊኪዩሎችም” ጉዞ፣ ስርጭት፣ ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት፣ ሁለቱም ውስኖች ናቸው፡፡ ስለሆነም በውሃ ውስጥ ድምፅ፣ ከማየትም ሆነ ከሽታ/ መዓዛ የተሻለ መልዕክት ማሰራጫ መሣሪያ ነው፡፡ ያም በውሃ ውስጥ ድምፅን ብዙ የሚገታው ስለሌለ እና ውሃም እንደ ድምጽ ማስተላለፊያ ስለሚያገለግል ነው፡፡

‘ባሳነባሪ ዓለም፣ በሰፊ ባህር ሆድ፤
በሌ’ት ወፎች ዋሻ፣ በሞላበት ሞገድ፤
ባዳኝ/ ታዳኝ፣ መድረክ፤
ተቃራኒ ፆታ፣ አማ’ሎ መማረክ፤
ቋንቋ ሙዚቃ ነው፤
ሞገድ ነው፣ መቃኛው፤
ቋንቋ መዓዛ ነው፤
ቋንቋ ድምፆች ናቸው፤
ሕላዊነት ወሳኝ፣ በደመ-ነፍስ ዓለም፤
“ባይተዋር” የሆኑ፣ ፊደላት አይደሉም፡፡

ባህር ውስጥ የሚኖሩ ሲል (seal) የሚባሉ፣ የአጥቢ አስተኔዎች፣ ረዣዥም የሪዝ ፀጉሮች መሰል አሏቸው፤ እነዚህ የሪዝ ፀጉር-መሰል አካላት የአካባቢ መረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ሪዝ-መሰሎቹ፣ የአካባቢውን የውሃ እንቅስቃሴ መሠረት ያደረገ፣ ተጠማጅ (የሚበላ አሳ/ ምግባቸው አሳ ነው) አሳ የት እንዳለ የሚጠቁም መረጃን መሰብሰብ ይችላሉ፡፡ ዓይን-አልባ አደን ነው፡፡ ይህም የአካል መሰናዶ እስከ 200 ሜትር ርቀት አካባቢ ድረስ ስለሚገኙ አሳዎች (ታዳኞች) መረጃ መሰብሰብ ያስችላል፡፡

“ፕላቲፑስ” (Platypus) የሚባሉ የባህር እንስሳት፣ የአጥቢ አስተኔ ዝርያዎች፣ “በአውስትራሊያ” (Australia) እና “በታዝማኒያ” (Tasmania) አካባቢ ነው የሚኖሩ፡፡ ጥቅጥቅ ያለ የገላ ፀጉር፣ የዳክየ የመሰለ የአፍ አካባቢ ቅርፅ፣ የመዋኛ እግር እና የጠፍጣፋ እና ሰፊ ጅራት ባለቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እንስሳት፣ ከሌሎች እንስሳት የሚመነጨውን ረቂቅ “የኮረንቲ ኃይል የመለያ ቃኝ ሕዋሳት” (sensors) አሏቸው፡፡ ብዙ ዝቃጭ ያለበት ውሃ ስንኳን ቢሆን የኮረንቲውን ቅኝት አይገታውም፡፡

የሠራተኛው ወገን የሆኑ ንቦች በሆድ እቃቸው አካባቢ ባለ “ማግኔታዊ” መረጃ መሰብሰቢያ አማካኝነት በአካባቢው ያለውን “የማግኔት” ኃይል መለዋወጥ (የሚያድግ ወይም የሚኮስስ) በመቃኘት ላይ በተገኘ መረጃ ላይ ተመስርተው፣ የተሠማሩበትን ተግባር (“ወለላ/ ፍሮ ብናኝ” መሰብሰብ፣ ውሃ መቅዳት) ራቅ ባሉ ቦታዎች ላይ ፈጽመው፣ ወደ ሠፈራቸው (ቀፎ) ለመመለስ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ንቦች እንዲሁም ወፎች፣ ወዘተ፣ “ካለካርታ” (ጂኦግራፊ ቦታ አመልካች) ከቦታ ቦታ እንዴት እንደሚዘዋወሩ ሙሉ ግንዛቤ ገና አልተገኘም፡፡

“ዘመሚቶች” (ቀይ ጉንዳን/ red ants) “ከኤሌክትሮ መግነጢሳዊ ሞገዶች” (electromagnetic waves) መረጃ ጠልፈው፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ገና ካሉበት ቦታ ሳይደርስ፣ አመጣጡን በቅድሚያ ተረድተው የመኖሪያ ኩይሳቸውን ለቅቀው ይወጣሉ፡፡ የሰው ልጅ ወደፊት ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ በመሥራት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊደርስ መሆኑን በቅድሚያ ተረድቶ፣ ጉዳት ከመድረሱ በፊት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይችል ይሆናል፡፡

የአእዋፍ ወይም የአጥቢዎች አባላት የሆኑ አንዳንድ እንስሳዎች የምግብ መገኘትን ብቻ ሳይሆን፣ ምግቡ ውስጥ ምን ዓይነት “ንጥረ-ምግብ” (nutrient) እንዳለ መረጃ ማግኘት ይችላሉ፤ ጎምዥተው የሚበሉ በእነርሱ አካል ውስጥ ሊፈበረኩ የማይችሉ “ንጥረ-ምግብ” ያሉባቸውን የምግብ ዓይነቶች ነው፤ ለምሳሌ ልዩ ልዩ “አሚኖ አሲዶችን” (amino acid) የያዙ ምግቦችን፡፡

ብዙ የአይጥ አስተኔዎች (ለምሳሌ ሞል/ moles)፣ ሁለት የተለያዩ ተግባራትን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዱ የአፍንጫ ቃኝ ሕዋሶች (sense) አሏቸው፡፡ አንዱ የአፍንጫ ቀዳዳ አንድ መረጃ፣ ሌላው የአፍንጫ ቀዳዳ ሌላ መረጃ በአንድ ጊዜ ይሰበስባሉ፡፡ በፈንጅ ምርመራ ጥናት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ የነዚህን እንስሳት መረጃ መሰብሰቢያ መሰናዶ፣ ለፈንጅ ፍተሻ (ምርመራ) ተግባር እየተጠቀሙበት ነው፡፡

“ሞል” (mole) የምትባል አንድ የአይጥ አስተኔ ዝርያ፣ ባለ ኮከብ-መሰል አፍንጫ (star nosed mole) አለች፡፡ አፍንጫዋ ላይ 100,000 ገደማ የነርቭ ሕዋሳት ይገኛሉ፡፡ ይህች የአይጥ አስተኔ ጉድጓድ በምትቆፍርበት ጊዜ፣ ይህ መጥረጊያ መሰል የነርቭ ስብስብ፣ ስለሚቆፈረው ጉድጓድ ፈጣን በሆነ መንገድ በቂ መረጃዎችን ይሰበስባል፡፡
አንዳንድ እንስሳት (ምሳሌ እስስት) አካባቢውን ለመምሰል፣ ቅጽበታዊ የአካል ቀለም መቀየር መቻላቸው፣ ከተፈጥሮ ተደናቂ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡

ልዩ ተግባራትን ለመፈፀም መቻል፡፡

ለምሳሌ፣ የምስጥ “ኩይሳ” የውስጥ ሙቀት መጠነኛ ሆኖ እያለ፣ ከኩይሳው ውጭ ያለው ሙቀት በጣም ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ የምስጥ “ኩይሳን” የውስጥ አየር ሙቀት በዚያ ደረጃ ለማቆየት የሚያስችለው የሕያውያን ቴክኖሎጂ፣ ለሰው ልጅ እንዲያገለግል በመጠናት ላይ ነው፡፡ ብዙ ኃይል ሳይባክን ያንን ለማድረግ ከተቻለ የዓለማችን ጤንነት/ ደህንነት በተሻለ መልክ ሊጠበቅ ይችላል (በአየር ንብረት ቅጥ ሳይናወጥ)፡፡ ይህም የሚተረጎመው በሕንፃ አወቃቀር (ሥነ ሕንፃ- architecture) ተግባር ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ የገበሎ አስተኔ ዝርያ፣ “ጌኮ” (gecko) የምትባል የጫካ እንሽላሊት መሰል እንስሳ ፣ ቀጥ ባለ ትልቅ ዛፍ ላይ ለመውጣት ትችላለች፤ ስለማትወድቅ “በስበት” (gravity) ህግም የማትገዛ/ የማትታዘዝ ትመስላለች፡፡ “ለምን አትወድቅም”? የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ተነስቶ፣ የእንስሳዋን ጫማ መዋቅር በማጥናት መልሱ ተገኘ፡፡ በጫማዎቿ መርገጫ ላይ ያሉ ጥቃቅን “ፀጉር-መሰል” እና “ፀጉር-አከል” የአካል ክፍሎች ከምትወጣበት ግንድ፣ ግድግዳ፣ ወዘተ፣ ጋር የመጣበቅ ባህርይ አላቸው፡፡ አረጋገጡ (እርግጫው) በጠነከረ መጠን፣ መጣበቁም በዚያው መጠን ይጠነክራል፡፡ ጠረፍ ላይ ለተለያዩ ተግባራት የሚሠማሩ “ሮቦቶች”፣ ሲፈበረኩ “የጌኮ” መሰል ጫማ እንዲኖራቸው እና ህዋ ላይ የሚከንፈውን አካል ጥገና (የጋራጅ ጥገና ዓይነት) እንዲተገብሩ ታቅዷል/ ታስቧል፡፡

የሸረሪት ድር ጥንካሬው፣ ለጥይት መከላከያነት ከሚደረተው፣”ኬቭላር” (kevlar) ከሚባለው ቁስ (substance) አይተናነስም፣ እንዲያውም ጥንካሬው ይልቃል ይባላል፡፡ ስለሆነም “ቴክኖሎጂስቶች” ወደፊት በምርምር ላይ ተመሥርተው፣ የሸረሪት ድርን ለተመሳሳይ ተግባር (ጥይት ለመከላከል) ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ “ለፓራሹት” አውታሮች፣ ለድልድይ አውታሮች/ “ኬብሎች” (cables)፣ እንዲሁም ለሕክምና (ለሰርጀሪ-surgery የሚያገለግል) ሰው ሠራሽ ጅማት፣ ወዘተ. ማምረትን የሚያስችል ዕውቀት በሸረሪት ድር ላይ ከሚከናወን ምርምር ይገኛል ተብሎ ይታመናል፡፡

በባህር ውስጥ ጠንከር ባለመጠን ቁስአካሎችን ማጣበቅ ያስቸግራል፡፡ ሁኔታው እንዲያ ሆኖ ሳለ፣ “መዝልስ” (mussels/ “ዛጎል-ለበስ”/ Mollusks) ካለብዙ ችግር በቀላሉ (ሳይቸገሩ) ጠንከር ባለ መልክ ቁስ አካል ላይ ሊለጠፉ ይችላሉ(መርከቦች/አለቶች ወዘተ. ላይ)፡፡ “መዝልስ” ይህንን ማድረግ የሚችሉትም “ክር-መሰል” ረጃጅም የአካል ክፍሎቻቸውን በመጠቀም ነው፡፡ እነዚህ “ክር-መሰል የአካል ክፍሎች “ከአሚኖ አሲድ” (amino acid) ጥርቅሞች የታነፁ “ፕሮቲኖች” ናቸው፡፡ ይህም በመጠናት ላይ ያለ ሲሆን፣ ወደፊት በባህር ውስጥ ጠንከር ባለመጠን ቁስአካሎችን ማጣበቅ የሚችል ቴክኖሎጂ ከጥናቱ ይመነጫል ተብሎ ይገመታል፡፡

“ሌቴ እንስሳት” (nocturnal animals) አይኖቻቸው ያንፀባርቃሉ፣ በጨለማም የነኝህን እንስሳት አይኖች ከሩቅ ማየት ይቻላል፣ ለምሳሌ ድመት፣ ጅብ፣ ውሻ፣ ወዘተ፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው፣ በእንስሳቱ አይን ውስጥ ልዩ ልዩ “ሃመልምል” (pigment) ስላሏቸው ነው፡፡ ይህ በልዩ ልዩ “ሃመልምል” (pigment) የታነፀ የአይን መዋቅር ፣እንስሳቱ በጨለማ የማየት ችሎታቸውን በጣም ያጎላዋል፣ ስለሆነም በጨለማ ለመጓዝ፣ ለማደን፣ ወዘተ፣ ይችላሉ፡፡

ሕያው ቀን ተቀን ሳያቋርጡ፣ የሚደንቁ ተግባራትን ይፈጽማሉ፡፡ “ናሚቢያ” (Namibia) የምትገኝ አንድ የጢንዚዛ ዝርያ የጀርባ መዋቅር፣ በምድረ በዳ ውስጥ ውሃ ማቋት ስለሚችል፣ ይህንን መዋቅር እስመስሎ ለመሥራት፣ ለመኮረጅ፣ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተፈጥሮ የተገኘን የ”ሉል” (“ፐርል”- pearl) ጥንካሬ በማጤን፣ “ፐርል” አስመስሎ ጠንካራ ቁሶችን ለማነፅ፣ እንዲሁም ጠንካራ (የማይሰበሩ) የሸክላ (ceramics) እቃዎችን ለመፈብረክ ሙከራዎች እየተካሄዱ ናቸው፡፡ “የቫይረሶች” የውጭ ሽፋን፣ ምንም ረቂቅ ቢሆንም ቅሉ፣ ሙቀትን የመቋቋም ባህርይ አለው-እስከ 600C ድረስ፡፡ እንዲሁም “አሲድንም” የመቋቋም ባህርይ አለው፡፡ ስለሆነም በዘመናችን ይህን መሳይ ባህርይ ያነገቡ ረቂቅ መሣሪያዎችን ለመፈብረክ እየተሞከረ ነው፡፡ የሕያውን ተግባር የመኮረጁ ሂደት እንደሚቀጥል አያጠራጥርም፡፡

በቴክኖሎጂ ኩረጃ ሂደት የሰው ልጅ ዋና ስጋት

በቅርብ ጊዜ በሰው ልጅ ብዙ ስጋት ያስከተለ፣ ራሱን ማስተማር የሚችል “ሮቦት” ተበጅቷል፡፡ “ባዮቴክኖሎጂን” እና “አልጎሪዝምን” መሠረት ያደረጉ “ቴክኖሎጂዎች” ከላይ እንደተጠቀሰው የሰው ልጅ ሥጋት ምንጭ ሆነዋል፡፡ የሰውን ልጅ የወደፊት እጣ ምን ሊሆን ይችላል ብለው የሚተቹ ብዙ ናቸው፡፡ ጥቂቶችን ላውሳ፡፡

ባለፉት አሥርተ ዓመታት “አልጎሪዝምን” መሠረት ያደረገ “ቴክኖሎጂ” (“”የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ” ጭምር) ከፍተኛ እምርታ አስመዝግቧል፡፡ ይህም በዘመናችን ከላይ እንደሰፈረው “ሰው-ሠራሽ አእምሮ” (Artificial Intelligence) በመባል ይታወቃል፡፡ ከ1950ዎች ጀምሮ “አልጎሪዝምን” መሠረት ያደረጉ “ቴክኖሎጅዎች” ከፍተኛ እመርታ ቢያሳዩም፣ በተፈበረኩት “ቴክኖሎጂዎች” “ከንቃተ ህሊና” (Conscientiousness) ይዘት ምንም ለውጥ አልታየም፡፡ “የቴክኖሎጅ” እመርታ ንቃተ ህሊናን አያካትትም፡፡ ስለሆነም አዲሱ «ሰው-ሠራሽ ሰው መሰል ሮቦት» የሞራል ግዴታ የሌለበት፣ ይቅርታን ይሉኝታን የማያውቅ፣ ግብረ-ገብነት ያልዳሰሰው፣ ትዕግስት አልባ፣ አዙሮ የማያይ ህሊና ቢስ አካል ነው፡፡

በሰው ልጅ ላይ እያንዣበበ ያለው ትልቁ ስጋት ከዚህ ሁኔታ ነው የሚመነጨው፡፡ “ህሊና-አልባ” ፣”ይሉኝታ-ቢስ”፣ “አልጎሪዝም”፣ ውትድርናን መተግበር ሆነ ኩባንያን ማካሄድ፣ ማስተዳደር፤ መሰል ተግባራቱን ሁሉ ማስተናገድ፣ ካለምንም ንቃተ ህሊና በብሩህ አእምሮ ብቻ ሊያከናውን ይችላል፡፡ ለዚህ ዓይነት ተግባር ብሩህ አእምሮ የግድ ያስፈልጋል፣ “ንቃተ ህሊና” ግን ቢኖርም አይጠቅምም፣ ባይኖርም አይጎዳም፣ ቅንጦት ነው፡፡ አዙሮ ለማየት ግን “ንቃተ-ህሊና” ያስፈልጋል፡፡

ቀደም ሲል እንደተብራራው ከላይ የሠፈረው ሁኔታ ሊከሰት የሚችለው የሰው ልጅ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ክህሎት የብዙ ግለሰቦችን (የወታደርነትም ሆነ የኢኮኖሚ ጉዳዮች/ተግባራት) አስተዋፅዖ ፋይዳ ቢስ ያደርገዋል በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የመከላከያ ኃይልን ብንወስድ፣ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ “ሮቦት” ጦረኞች፣ ካለ ሰው ልጅ እገዛ፣ በጠላት አምባ ጥቃት አድርሰው የሚመለሱ፣ ደከመኝን ሰለቸኝን የማያውቁ፣ የማይራቡ፣ የማይጠሙ፣ ፍርሃት፣ ስጋት የማይዳስሳቸው፣ «እብን» ወታደሮች የሰውን ልጅ ይተኩታል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡

መደምደሚያ

የሰው ልጅ “ኪንግፊሸር” (Kingfisher) አስተውሎ፣ “ጥይት ባቡር” (bullet train) ከከርሰ-ምድር ሲወጣ የሚያስከትለውን የፍንዳታመሰል ድምፅ ለመቀነስ ችሏል፡፡ “ደራጎንፍላይ” መሰል “ሄሊኮፕተር” ለመፈብረክ፣ የቅጠልን ባህርይ ኮርጆ በውሃ አይደፈሬ ቀለም፣ የቀንድ አውጣ ዘሮች (መዝሎች/mussels/ ዛጎል-ለበስ/ Mollusks) የሚያመነጩትን ዝልግልግ ፈሳሽ መሰል ቀምሞ፣ ልብ እና አከርካሬ ለመጠገን በቅቷል፣ ወዘተ፡፡ የሰው ልጅ፣ ራሱን፣ ያውም የዓለም “ቻምፒዮኖችን” በቼዝ ጨዋታ ውድድር የሚረታ “ሰው-ሠራሽ” አንጎል (computer) ለመፈብረክም በቅቷል፡፡

እንደ የሌት ወፎች እንደ “አምባዛ” (ጢማም የአሳ ዓይነት) እና እንደ “ሲል” (seal) የአካባቢ መቃኛ መሰናዶ፣ መረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች፣ እንደ “ዋቅላሚዎች” (ውሃ አቅላሚ) ሙቀት አልባ ብርሃን ማመንጨት፣ እንደ “ሃሚንግ በርድ” (humming birds) “ኤነርጂ” መቆጠብ፣ወዘተ፣ ለመፈብረክ፣ ተመኝቷል፣ ምኞቱን እውን ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

ዘመናዊው “ቴክኖሎጂ”፣ እንዳለፈው ዘመን “ቴክኖሎጂው” ቁሳቁስ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ብቻ አይደለም የሚያበረክት፣ አእምሮ ነው የሚለግስ፣ እውቀት ነው በገፍ የሚያውቁት፡፡ “አዲሱ-ባቡር” ላይ ማለት “ዘመናዊው ቴክኖሎጂ” ላይ የተሳፈሩት “መለኮታዊ-መሰል” አቅም ሲጎናጸፉ፣ ያለተሳፈሩት እንደ “ተኮነኑ ነፍሶች” ለዘላለም ለስቃይ ይዳረጋሉ ወይም ጨርሰው ይወድማሉ የሚል ስጋት ነው ያለው፡፡ ይህም ከ70ሺ ዓመታት በፊት፣ «ሆሞ ሳፕያንስ» በወንድሙ «በሆሞ ኒያንደርታል» (ከምድረገፅ እንዲጠፋ የተደረገው አንዱ የሰው ዘር) ካደረሰበት ግፍ፣ ብሎም ውድመት ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል ብለው የሚተነብዩ ብዙ የዘመናችን ምሁራን አሉ፡፡ ስለሆነም ” ዘመናዊ ቴክኖሎጂን “በቀኝ-ጎን” ያውልልን፣ ከስጋቱ ይሰውረን!
(ጽሑፍ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ሥዕሎች/ ፎቶግራፎች እና ብዙ መረጃዎችን ያገኘሁ “ከኢንተርኔት” ነው)፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top