ከቀንዱም ከሸሆናውም

ቦብ ማርሊ እና ‹‹አፍሪቃዊቷ ልዕልቱ››

መግቢያ

ፈረንሳዊቷ ጋዜጠኛ አን-ሶፊ ያህን Bob Marley and the Dictator’s Daughter በሚል ርዕስ በቅርቡ በጻፈችው መጽሐፍ የሬጌ ሙዚቃው ንጉሥ ቦብ ማርሊና የቀድሞው የጋቦን ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ ሴት ልጅ ፓስካሊን ቦንጎ ያሳለፉትን ጥልቅ የፍቅር ግንኙነት መለስ ብላ ቃኝታለች፡፡ ይኸው የፍቅር ግንኙነት አቀንቃኙ አፍሪቃዊ ሥረ-መሠረቱን እንዲያጠናክር አግዞታል፡፡

የሁለቱን ፍቅረኛሞች ታሪክ በዋነኝነት የምታስቃኘን ፓስካሊን ራሷ ናት፤ ታሪኩ የተመሠረተውም በ2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ዕይታ በቀረበ አንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ ነው፡፡ በወቅቱ ትምህርቷን በአሜሪካ ትከታተል የቆየችው የ23 ዓመቷ ኮረዳና የቀድሞው የጋቦን ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ ሴት ልጅ፣ ጃማይካዊውን አቀንቃኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታገኘው አንድ ተለቅ ያለ የዕፀ-ፋሪስ ሲጋራ እያጨሰ ነበር፡፡ ቦብ በወቅቱ ለፓስካሊን የተናገረው ነገር፣ ‹‹አስቀያሚ ነሽ›› የሚል ብቻ ነበር፡፡

ቦብ ይህን መሰሉን አስተያየት የሰነዘረው ኮረዳዋ ጸጉሯን በመተኰሷ ነበር፤ የሬጌ ሙዚቃው ንጉሥ ይህን ሁኔታ በአፍሪቃዊነቱ ላይ ያነጣጠረ ተቀባይነት የሌለው ስድብ አድርጎ ወስዶታል፡፡ የሁለቱ ትውውቅ ይህን በመሰለ አሳፋሪ ሁኔታ ቢጀምርም፣ እስከ ግንቦት 11/1981 ዓ.ም. የቦብ ኅልፈት ድረስ በጋለ ስሜት የታጀበ የፍቅር ግንኙነት አሳልፈዋል፡፡ ፓስካሊን በመጽሐፉ ላይ እንደገለጸችው፣ ግንኙነታቸው በጋለ ስሜት የታጀበ ቢሆንም፣ አስቸጋሪ ነበር፡፡

የሁለቱ ፍቅረኛሞች ሰብእናና ሥረ-መሠረት የተለያየ በመሆኑ የፍቅር ግንኙነታቸው ሙሉ በሙሉ ይፋ አልወጣም፡፡ ከቦብ ጋር በዌይለርስ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ የተሳተፈው ጃማይካዊው ጊታር ተጫዋች ጁኒየር ማርቪን ይህን አስመልክቶ ሲናገር፣ ‹‹የሁለቱ ፍቅር ድብቅ አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ፣ በሕዝብ ዘንድ የሚታወቅም አልነበረም›› ብሏል፡፡

የፍቅር ግንኙነታቸውና ያጋጠሙት መሰናክሎች በዘመኑ ከአውሮጳውያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ ስለወጣው የአፍሪቃ ክፍል አስተሳሰብና ስለወቅቱ የጋቦን ሕይወት እውነታዎች ብዙ ነገሮችን ይነግሩናል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ የጃማይካ፣ የካሪቢያን ደሴቶች፣ አልፎ ተርፎም የአሜሪካ ጥቁር ሕዝቦች እምብዛም ከማያውቋትና በአብዛኛው በምናባቸው ከሚያስቧት አህጉር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይጠቁመናል፡፡

በአድናቆትና የግንዛቤ ማነስ

የቦብና የፓስካሊን የፍቅር ግንኙነት የሚጀምረው አድናቆትና የግንዛቤ ማነስ በሰፈነበት ድባብ ነው፡፡ የሁለቱ ግለሰቦች ትውውቅ እንደነገሩ ቢሆንም፣ በወቅቱ የዌይለርስ ባንድ ሎስ አንጀለስ ውስጥ የሚያቀርበውን የሙዚቃ ኮንሰርት ለመከታተል በቦታው የተገኘችው ፓስካሊን፣ የቡድኑ አባላት ምሽቱን ከእኅቷ ጋር ቤቨርሊ ሂልስ ውስጥ በተከራዩት ውበትንና ምቾትን በተላበሰው ቪላ እንዲያሳልፉ ግብዣ አቅርባላቸዋለች፡፡

ቦብና ፓስካሊን ሳይዳሩና ሳይቃበጡ አብረው አስደሳች ምሽት አሳልፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ፓስካሊን የሬጌ አቀንቃኙ በ1980 ዓ.ም. መጀመሪያ በጋቦን ርዕሰ-ከተማ፣ ሊብረቪይ ውስጥ ሥራዎቹን እንዲያቀርብ ጠይቃዋለች፡፡ ታዲያ፣ በሁለቱ መካከል የተፈጠረውን ግንኙነት ያቀጣጠለው ይኸው ክስተት ነበር፡፡


ቦብና የዌይለርስ ባንድ አባላቱ በግብዣው እጅጉን ደስተኞች ነበሩ፡፡ ስለፓን-አፍሪቃዊነት፣ ለአያት ቅድመ-አያቶቸው አህጉር ስላላቸው ፍቅር፣ እንዲሁም ስለአንድነት ሲያቀነቅኑ በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል፤ በነገራችን ላይ፣ በ1979 ዓ.ም. የተለቀቀው Survival አልበም ሽፋን የአፍሪቃ ሀገራትን ሰንደቅ ዓላማዎች የያዘ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከኪንግስተን ደሳሳ ሰፈሮች ከመጡት እነኝህ ጃማይካውያን መካከል አንዳቸውም የአፍሪቃን አፈር ረግጠው አያውቁም፡፡

እንግዲህ፣ ቦብና የዌይለርስ ባንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በወደአፍሪቃ መጥተው የጐበኟት ሀገር ጋቦን መሆኗ ነው፡፡ በቀጣይነትም፣ እስከ 1980 ዓ.ም. ድረስ ‹‹ሮዴዢያ›› በሚል ሥያሜ ስትጠራ የቆየችውን የአዲሲቷን ሀገር ዚምባብዌ የነጻነት በዓል ለማክበር ሐራሬ ተገኝተዋል፡፡

ጋቦን ውስጥ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የተጋበዙት የዌይለርስ ባንድ አባላት ስለጉዟቸው አንድም ጥያቄ አልጠየቁም፡፡ ‹‹ንጉሥ›› ወይም ፕሬዚዳንት መሆናቸውን እንኳን በቅጡ የማያውቋቸውን ኦማር ቦንጎ የልደት በዓል ለማክበር በተዘጋጀው መድረክ ላይ ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ቢያውቁም፣ ጥያቄዎችን ከማቅረብ ተቆጥበዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ጋቦን ሲደርሱ የክብር አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ ፍላጎታቸውም ምንም ሳይጓደል ተሟልቶላቸዋል፡፡

አሳዛኝ ትዝብት

ጃማይካውያኑ የሬጌ ሙዚቀኞች ጋቦን እንደደረሱ ዘመናዊነትን የተላበሰች ርዕሰ-ከተማ በመመልከታቸው በጣሙን ተገርመዋል፤ ለከተማዋ እድገት የወጣው ወጪ የተሸፈነው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከነዳጅ ዘይት ከተገኘው ገቢ ነበር፡፡ ለሬጌ ሙዚቃ እምብዛም አድናቆት የሌላቸው ፕሬዚዳንት ቦንጎ፣ ቡትቷምና ዕፀ-ፋሪስ አጫሽ ጃማይካውያኑን አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሄደው የመቀበሉም ሆነ በክብር እንግድነት የመጋበዙ አስፈላጊነት አልታያውም፡፡

ጸጉራቸው ከቆሸሸውና የስፖርት ቱታ ከለበሱት እነኝህ ሙዚቀኞች ጐን ቆመው ፎቶግራፍ መነሣቱም ቢሆን አልተዋጠላቸውም፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ከልጆቻቸው መካከል አብልጠው የሚወዷት ፓስካሊንን በመሆኑ፣ ፍላጎቷን ለማሟላት ፍጹም አላቅማሙም፡፡ ስለዚህም፣ በመንበረ-ሥልጣኑ እንዲተካቸው የመረጡትን ወንድ ልጃቸውን አሊ እንግዶቹን እንዲቀበላቸው ልከውታል፡፡

የዌይለርስ ባንድ አባላቱ የጋቦን ቆይታ እየተራዘመ ሲሄድ በሀገሪቱ ውስጥ ሥር የሰደደ የሀብት አለመመጣጠን መኖሩን መታዘብ ችለዋል፤ እንዲያውም፣ አብዛኛው ሕዝብ የሚኖረው ከድኽነት ወለል በታች ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱም በቅርቡ በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮችን 99.96% ድምፅ አግኝተው ማሸነፋቸውንም ዐወቁ፡፡

የሙዚቃ ቡድኑ አባል ማርቪን፣ ‹‹ኦማር ቦንጎ አምባገነን መሪ መሆናቸውን አላወቅንም፡፡ በወቅቱ የዋሆች ነበርን፡፡ ወደአፍሪቃ እንድንጓዝ በመጋበዛችን በጣም ደስተኞች ነበርን›› ሲል የተሰማውን ቅሬታ ገልጿል፡፡

ዐጃቢ አቀንቃኟ ጁዲ ሞዋት በበኩሏ፣ ‹‹ ሕዝቡ በቅኝ አገዛዝ ሥር ባይሆንም፣ ነጻ አልነበረም፡፡ ጋቦን በጥቁር አፍሪቃዊ የምትገዛ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የሰፈነባት ሀገር ነበረች›› ብላለች፡፡

ፓስካሊን ራሷ የአሜሪካ ማእከላዊ የስለላ ድርጅት (ሲ.አይ.ኤ.) ክትትል ሊደረግበት የሚገባ ዐመፀኛ አድርጎ የፈረጀው ‹‹አብዮተኛው›› ቦብ ይህን አጣብቂኝ እንዴት አድርጎ እንደፈታው በመጽሐፉ ውስጥ ለማብራራት ሞክራለች፡፡ የፕሬዚዳንት ቦንጎ ሴት ልጅ ይህን አስመልክታ፣ ‹‹ስንገናኝ ኃይለ ሥላሴ ከዙፋናቸው ከወረዱ በኋላ ወደሀገራቸው ጋቦን መምጣት እንደሚችሉ የተናገረው አባቴ ብቻ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ራስተፈሪያኑም ለዚህ ሐሳብ ክብርና አድናቆት ሊሰጡት የሚገባ ጠንካራ እርምጃ አድርገው እንደወሰዱት ገልጾልኛል›› ብላለች፡፡

ፍቅር በፍቅር

ቦብና ፓስካሊን የፍቅር ግንኙነታቸውን የጀመሩት በሊብርቪይ ከተማ ነው፡፡ ከዚህን ጊዜ ወዲህ ፓስካሊን ከሊብርቪይ ወደምትማርባት ሎስ አንጀለስ፣ እንዲሁም ኪንግስተን በግል አውሮፕላኗ በመመላለስ አብዛኛውን ትርፍ ጊዜዋን የምታሳልፈው ከቦብ ጋር ሆነ፡፡ በሕዝብ ፊት የፍቅር ስሜቱን ለመግለጽ የሚቸገረው የሬጌ ሙዚቃው ንጉሥ፣ ልጅ እንድትወልድለት ከተመኛት ‹‹አፍሪቃዊቷ ልዕልት›› ጋር ኃይለኛ ፍቅር ይዞት ነበር፡፡

በ36 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ቦብ፣ ከሰባት የተለያዩ ሴቶች 11 ልጆች መውለዱን አምኗል፡፡ ያም ሆኖ፣ ሌሎች 25 ልጆች የእሱ አብራክ ክፋይ እንደሆኑ አሁንም ድረስ ይናገራሉ፡፡

ቦብ የዌይለርስ ሙዚቃ ባንድ ዐጃቢ አቀንቃኝ ከሆነችው ሪታ ጋር በ1966 ዓ.ም. በትዳር ተሳስሯል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ጥቂት ከማይባሉ ሴቶች ጋር ይወሰልት ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ በ1976 ዓ.ም. ከሚስ ወርልድ የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋና ከሁለት ዓመታት በኋላ የወደፊቱን አቀንቃኝ ዳሚየን ከወለደችለት ሲንዲ ብሬክስፒር ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነበረው፡፡

በሌላ በኩል፣ ፓስካሊን በድብቅ የወሊድ መቆጣጠሪያ አንክብል ትጠቀም ነበር፡፡ አብረው እንደማይዘልቁም በሚገባ አውቃ ነበር፡፡ ‹‹ቦብ፣ ‹አባትሽ እኔን እንድታገቢ ፈጽሞ አይፈቅድልሽም› ይለኝ ነበር፡፡ እኔም ብሆን ‹ያ ሁሉ ሴት በሕይወቱ ውስጥ እያሉ ምን ዕድል ይኖረኛል… የራስተፈሪያን እምነት ተከታይ በመሆኑ ያለውን ነገር የማካፈል ፍልስፍና ነበረው፡፡ ሴቶች ቢፈልጉትም፣ እሱ ራሱ ያመጣው ችግር አልነበረም፡፡ ሴቶቹ ሁሉ ባለትዳር እንደሆነ ያውቃሉ… ያም ሆኖ፣ በሙያው ኮከብነቱን ያስመሰከረ ነው› ብዬ አስብ ነበር›› ብላለች ፓስካሉን፡፡

ኮረዳዋ ፓስካሊን በስተመጨረሻ ላይ ጸጉሯን መተኰሷን አቁማ ሹርባ ትሠራው ጀመር፡፡ ከመጀመሪያ ባሏ የወለደችው ዲዲዬ ፒንግ፣ ‹‹የጸጉር ስታይሏ ድሬድ አልነበረም፡፡ አባቷ ይህን እንድታደርግ ፈጽሞ አይፈድላትም ነበር›› ብሏል፡፡

የቦብ መጨረሻ

በ1977 ዓ.ም. የተደረሰበት እባጭ በአግባቡ ባለመታከሙ ኒው ዮርክ የሚገኘው ሐኪሙ በታኅሣሥ 1980 ዓ. ም. ወደካንሰር እንደተለወጠ ከነገረው ከዚያች አሳዛኝ ቀን በኋላም አንዳቸው ከሌላኛው ሕይወት አልራቁም፡፡ ሐኪሞቹ ቦብ ከዚህን ጊዜ በኋላ በሕይወት የሚቆየው ለሦስት ሳምንታት ብቻ እንደሆነም ገልጸውት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ፣ ቦብ አንድ ጀርመናዊ ሐኪም አንድ የመጨረሻ የሕክምና አማራጭ በሞከረበት ባቫሪያ ግዛት በሚገኝ ክሊኒክ ውስጥ የሕይወቱን የመጨረሻዎቹን ስድስት ወራት አሳልፏል፡፡ በእነኝህ ስድስት ወራት በእያንዳንዱ የሳምንቱ መጨረሻ ሳትሰለች ጀርመን ድረስ እየተመላለሰች የጠየቀችው ፓስካሊን፣ ከቦብ ልጅ አለመውለዷ በዚህን ጊዜ ቆጭቷታል፡፡ የሬጌ ሙዚቃው ንጉሥ ቦብ የመጨረሻ ትንፋሹን የተነፈሰው ከጀርመን ቀጥሎ ባረፈባት የአሜሪካዋ ሚያሚ ከተማ ግንቦት 11/1980 ዓ.ም. ነበር፡፡ ጋቦናዊቷ ልዕልቱ ፓስካሊን በጃማይካ፣ ኪንግስተን በተካሄደው የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝታለች፡፡ ፓስካሊን በ2008 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየችው የቦብ እናት፣ ሴዴላ፣ ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበራት፡፡

ሕይወት ያለቦብ

ፓስካሊን ትምህርቷን በፈረንሳዩ École Nationale d’Administration ከተከታተለች በኋላ በአባቷ የሥልጣን ዘመን በሚንስትርነት አገልግላለች፡፡ በቀጣይነትም፣ ራሷን ከፖለቲካው ዓለም እስካገለለችበት ጊዜ ድረስ የወንድሟ ዋና አማካሪ ሆና ሠርታለች፡፡ ፓስካሊን በዚህን ጊዜም ቢሆን በስሜት ከቀድሞ ፍቅረኛዋና ከሬጌ ሙዚቃው ፈጽሞ አልራቀችም፡፡

ከዣን ፒንግ ጋር በትዳር የመሠረተችው ፓስካሊን፣ የመጀመሪያ ልጇን ኔስታ ስትል ስም አውጥታለታለች፤ የሬጌ ሙዚቃወቅ ንጉሥ ሙሉ ስም ሮበርት ኔስታ ‹‹ቦብ›› እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ማይክል ጃክሰንና ጄይ ዚ ሊብርቪይ ከተማ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን እንዲያቀረቡ ሁኔታዎችን ያመቻቸችው ፓስለካሊን፣ ከ2015 ዓ.ም. ወዲህ በየዓመቱ ኮት ዲ’ቯር፣ አቢጃን ውስጥ የሚካሄደው አቢ ሬጌ ፌስቲቫል መሥራች ነች፡፡

መደምደሚያ

ቦብ የፓስካሊን የመጀመሪያው እውነተኛ ፍቅረኛ ነበር፡፡ ለቦብ ግን፣ የመጀመሪያው ፍቅረኛው አልነበረችም፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ‹‹ከአፍሪቃዊቷልዕልት›› ጋር ያሳለፈው የፍቅር ግንኙነት ለበርካታ ዓመታት ስለዘፈነላት፣ ሆኖም ብዙም ስለማያውቃ አህጉር የተሸለ ግንዛቤ እንዲኖረው አግዞታል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top