ጥበብ በታሪክ ገፅ

ኒና ሲሞን – “ነጻነት ማለት ያለፍርሃት መኖር ነው!”

መግቢያ

የ20ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካኑ ሙዚቃ የኩራት ምልክት ነች። ፍጹም የሚባል የተሟላ የትረካ ችሎታዋ በሙዚቃ ስራዎቿ ነጻነትን፣ ማንነትን፣ ተነሳሽነትንና ጥልቅ ፍቅርን ለትውልዱ ሁሉ ላይነቀል መትከል፣ ማሳደግ አና ማውረስ ችላለች። የጃዝ ሙዚቃዋ ንግስት ኒና ሲሞን!

ኒና ሲሞን ማን ነች?

ኒና ሲሞን የተወለደችው በ1933፣ የካቲት 21 (እኤአ) ሰሜን ካሮሊና ውስጥ ነው። ወላጆቿ ያወጡላት ስሟ ዩኒስ ካትሊን ዌይሞን ሲሆን አለም የሚያውቃት ግን በመድረክ ስሟ ኒና ሲሞን ብሎ ነው። ድንቅ የሙዚቃ ተሰጥዖ እንዳላት መታየት የጀመረው ገና በሦስት አመት ሕጻን ሆና ጥሩ ፒያኖ መጫወት በመቻሏ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን ያደገችው እድሜዋ ከፍ እስኪል ድረስ ፒያኖ ከመጫወት ውጪ ሙዚቃን በድምጿ ማንጎራጎር አልጀመረችም ነበር። በአፍላ እድሜዋ በጆሮዋ የገባን የሙዚቃ ምት ሁሉ መጫወት ትችል የነበረችው ኒና ሲሞን የነጆሃን ሰባስቲያን ባች፣ ቾፒን፣ ቤትሆቨን አና ሹበርት ፍቅር ያደረባት ገና በአፍላ እድሜዋ ነበር።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ኒዎርክ ከተማ አቅንቶ ጁሊዓርድ በተሰኘ እውቅ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመማር ስኮላርሺፕ ተመቻቸላት። በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረችበት ጊዜ፤ ለሌሎች ድምጻውያን ሲያዜሙ ፒያኖ በመጫወት ታጅባቸው ነበር። ክላሲካል ፒያኖ ካጠናች በኋላ፣ ፊላዴልፊያ በሚገኝ ከርቲስ በተባለ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመማር ብታመለክትም ትምህርት ቤቱ ግን ሳይቀበላት ቀረ። በቆዳዋ ቀለም ምክንያት ከመመዝገብ መከልከሏን የምትናገረው ኒና ሲሞን፤ የዛሬዋን ዝነኛ የጃዝ ሙዚቃ ንግስት ከመሆን ግን ሊያቆማት አልቻለም።

የ1950ዎቹ አና 60ዎቹን በጃዝ ሙዚቃ ከፍተኛ እውቅናን ማትረፍ ብትችልም፤ ከሙዚቃው በላይ ዝናን ያስገኘላት ግን ለሰው ልጆች መብት ተሟጋችነቷ ነበር። የኒና ሲሞን ሙዚቃዎች በጊዜው በመደብ ትግል ላይ ለነበረው ጥቁር ሕዝብ ጋር ልብ ለልብ የሚነጋገሩ ነበሩ። የፒያኖ ሊቅ ለነበረችው ኒና ሲሞን ሰረቅራቃ ድምጿ ተጨምሮበት፤ ቃላትን ስሜት በማላበስ በጃዝ ሙዚቃ ላይ ነገሰችበት። ከጃዝ በተጨማሪ ጎስፔል፣ ብሉስ፣ ፎልክ አና ክላሲካል መጫወት ትችል ነበር። በማህበራዊ መብት ተሟጋችነቷ እና በሙዚቃ ስራዎቿ ተደማጭነት ብሎም ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪነት ማን ከሷ በላይ የተባለላት ኒና ሲሞን፥ የዘፈን ስንኞቿ በሚያዝሉት እውነት እና ለአድማጮቿ ያንንም በመግለጥ ትታወቃለች። የጃዝ ሙዚቃ አክቲቪስት ብቻ ሳትሆን ባለቅኔ ነበረች ቢባል ማጋነን አይሆንም።
በብዙ መልኩ የወቅቱን የሙዚቃ እንቅስቃሴ ላይ የራሷን ከፍተኛ አሻራ አኑራለች። አድናቂዎቿ “High Priest of Soul” እያሉ ቢያሞካሿትም እሷ ግን ይህንን መጠሪያ አትወደውም ነበር። ሌላው ቀርቶ አርቲስቷ የጃዝ ሙዚቀኛ መባሏንም አታምንበትም። ለዚህም መልሷ እሷ የጃዝ፣ ፎልክ እና ብሉስ የሙዚቃ ስልቶች በስፋት ብትሰራም ከሁሉ አብዝቼ የሰራሁት ግን የፎልክ ሙዚቃ ነው የሚል እምነት እንዳላት ትናገራለች።

የሙዚቃ ስራዎቿ

ከኮሌጅ መልስ ፊቷን ከክላሲካል ሙዚቃ ወደ ድምጻዊነት በማዞር በምሽት ክለቦች ሙዚቃን መጫወት ጀምራ፣ የመጀመሪያ አልበሟን በ1957 (እኤአ) ለቀቀች። ከዚህ ስራዋ ውስጥም “Plain Gold Ring”, “Little Girl Blue” እና “I Loves You Porgy” የሚሉት ስራዎቿ ከፍተኛ እውቅናን ካስገኙላት መሀል ይጠቀሳሉ። በተለይም “I Loves You Porgy” የሚለው ስራዋ ምርጥ ሀያ የፖፕ ሙዚቃ ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሎ ነበር። በ1960ዎቹ ለማህበራዊ መብቶች ተሟጋችነቷ ተጨምሮ አጉልቶ አውጥቷታል።

ሚያዝያ 21፣ 2003 (እኤአ) ከዚህ አለም በሞት ስትለይ፤ ከአርባ በላይ የሙዚቃ አልበሞች ብቻ ሳይሆን ለግማሽ ምእተ አመት አከባቢ የተደመጠ ጊዜ የማይሽረው የሙዚቃ ሀብት ለአለም አበርክታ ነው። በ1959 የለቀቀችው ምርጥ አስር ክላሲክ ሙዚቃ፤ ከ “I Love You Porgy” እስከ “A Single Woman” ድረስ በስፋት ተደምጠውላታል። የመጀመሪያ እና የመጨረሻ የሙዚቃ አልበሞቿ መሀል የሠላሳ ሦስት ዓመት ልዩነት ቢኖርም ሁሉንም ስራዎቿን በአንድ የሚያስራቸው ፍጹም ሀቅን ባለዘ ስሜታዊነት መጠመቃቸው ነው።

የሲዲ ሙዚቃ መምጣት እና በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ተከትሎ በሕይወቷ የመጨረሻዎቹ ምእራፎች በስፋት መደመጥ አና ከፍተኛ የእውቅና ሽልማቶችን መሰብሰብ ችላለች። ከዚያም የኢንተርነት መጀመር፣ ብሎም የቴሌቪዥን ስርጭት ከብዙዎች ስላስተዋወቃት በመጨረሻዎቹ አስር አመታት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሙዚቃ ስራዎቿ ያለበት ሲዲዎች መሸጥ እና በወቅቱ በአለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ለአድማጭ መድረስ ከቻሉ አርቲስቶች አንዷ ነበረች። በ1980ዎቹ ከሀገር ወጥታ የኖረችም ሲሆን የአይምሮ እክል ያጋጠማት ሲሆን የኢኮኖሚ ችግርም ውስጥ ገብታ ነበር።
ሌሎች ተወዳጅ የነበሩት የሙዚቃ አልበሞቿ ውስጥ “The Amazing Nina Simone”

በ1959ዓ.ም፣ “Wild is The Wind” በ1966 ዓ.ም፣ “Silk and Soul” በ1967 ዓ.ም ተጠቃሽ ናቸው። ከራሷም ስራዎች በተጨማሪ ለእውቅ አርቲስቶች ስራዎች የሽፋን ሙዚቃ ትጫወት ነበር። ከዚህም ውስጥ የቦብ ዳሊያን “The Times They Are A-Changin” እና የቢትልስ “Here Comes The Son” ተጠቃሽ ናቸው። ከሁሉ በላይ የሙዚቃዋ ንግስት መሆኗን ያስመሰከረችባቸው ስራዎቿ በ1965 የለቀቀችው “Take Care of A Bussiness” እና የ1967ቶቹ “I Put A Spell on You” እና “I Want A Little Sugar In My Bowl” ናቸው።

በ1970ዎቹ አጋማሽ ለተወሰነ ጊዜ ከሙዚቃ ስራዎች ተገላ ብትቆይም ከዚያ መልስ በ1978 የሰራችው “Baltimore” የተሰኘ አልበም በሙዚቃ ባለሙያዎች ሙገሳ የተቸረው ነበር። በ1980ዎቹ ይበልጥኑ ወደ ሙዚቃው በማተኮር በእንግሊዝ በአንድ የሽቶ ማስታወቂያ ላይ ለረጅም አመት ጥቅም ላይ መዋል የቻለውን “My Baby Just Cares For Me” የሰራች ሲሆን የሕይወት ታሪኳን የሚያትት መጽሐፍ በእውቁ ሙዚቃዋ ስም “I Put A Spell On You” በሚል ርዕስ ታትሞ ለንባብ በቅቷል።

የሰው ልጆች መብት ተሟጋቿ አርቲስት

በ1960ዎቹ አጋማሽ ለሰው ልጆች መብት መከበር በምታሰማው ድምጽ መታወቅ የጀመረችበት ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሰራቻቸው ዘፈኖች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል በ1963 የሜድጋር ኤቨርስን ግድያ ተከትሎ ያወጣችው “Mississippi Goddam” አንዱ ሲሆን፤ እንዲሁም በርኒግሃም ውስጥ በቤተክርስቲያን ውስጥ በተደረገ የቦምብ ጥቃት ህይወታቸው ላለፉት አራት ጥቁር አሜሪካዊ ሴቶችን የሚያወሳው “Four Women” የተሰኘው ዘፈኗ መጠቀስ ይችላል። ከዚህም ውጪ በጥቁር ሴቶች ህይወት ላይ ተመርኩዛ ያወጣችው ሌላኛው ዘፈኗ “Young, Gifted and Black” አና የታላቁን የጥቁር ህዝቦች መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ ግድያ ተከትሎ “Why (The King of Love is Dead)” በዌስትበሪ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ተጫውታዋለች።

በ1960ዎቹ መገባደጃ ከሙዚቃዎቿም በላይ በማህበራዊ መብት ተሟጋችነቷ ጎልታ የወጣችበት ጊዜ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት ከማልኮም ኤክስ አና ቤቲ ሻባዝ ጋር ጎረቤታሞች የነበረች መሆኗ ወደ ፖለቲካው ጠልቃ እንድትገባ እንዳስቻላት ይነገራል።

በአንድ ወቅት ባደረገችው ንግግር በስፋት የምትታወስ ሲሆን በዚህም ንግግር ወቅት እንዲህ ብላ ነበር፦ “I will tell you what freedom is to me: No Fear” /”ለኔ ነጻነት ማለት ያለ ፍርሃት መሆር ነው።”

ማጠቃለያ

ኒና ሲሞን ወደ በኋላ ላይ ሀገሯ አሜሪካን ለቃ በመውጣት በላይቤሪያ፣ በስዊዘርላንድ፣ በእንግሊዝ እና ባርባዶስ ከኖረች በኋላ የሕይወቷን የመጨረሻ ምእራፎች ወደ አሳለፈችበት ፈረንሳይ አምርታለች።
በየጊዜው ትላልቅ የሙዚቃ ጉዞዎችን ታደርግ የነበረ ሲሆን በሄደችበት ሁሉ በምታዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አድናቂዎቿ ይታደማሉ። በይዘቱ ጉድ ካስባሉ ኮንሰርቶቿ መካከል በ1998 በኒዎርክ ያዘጋጀችው ኮንሰርት ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዝ ነው። አርቲስቷ በዚያው አመት የደቡብ አፍሪካው መሪ የኔልሰን ማንዴላ 80ኛ ዓመት የልደት በዓል ላይ ተገኝታ ተጫውታለች።
የአርቲስቷ ሴት ልጅ የእናቷን የሙያ መስመር የተከተለች ሲሆን በ1999 በአየርላንድ፣ ዱብሊን ባቀረበችው ኮንሰርት ላይ ሴት ልጇን ወደ መድረክ ይዛ በመውጣት አብረው ተጫውተዋል።

ኒና ሲሞን በ2003 ዓ.ም በጡት ካንሰር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየች ሲሆን ያየችውን፣ የሰማችውን እና የምታውቀውን የውስጧን እውነት እና ሀይል በሙዚቃ ስንኞቿ ውስጥ ባዜመችው ዜማ ሁሌም የምታተወስ የሙዚቃ አብዮተኛ ናት። ከላይ ከጠቀስነው የግለ ህይወት ታሪክ መጽሐፏ በተጨማሪ በቅርብ ጊዜያት “The Amazing Nina Simone” እና “What Happened Miss Simone?” የተሰኙ ሁለት ዶክመንተሪ ፊልሞች ለእይታ ቀርበዋል። ሁለተኛው ፊልም የዓመቱ ምርጥ ዶክመንተሪ ኦስካር ሽልማት እጩ ለመሆን ችሎ ነበር።

የኒና ሲሞን የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሙዚቃ ኣብዮት ከብዙ በጥቂቱ ይህን ይመስላል። የሰው ልጆች መብት በብዙ በሚገረሰስበት በዚህም ዘመን እንደ ኒና ሲሞን ያሉ ጠንካራ የጥበብ ሰዎችን ብንናፍቅ የሚያስገርም አይደለም። በእንደዚህ አይነት ከባድ ጊዜዎችን ለመሻገር የኒና ሲሞን አይነት አሻጋሪዎች ሚና ከፍተኛ ነው። ዘመን የማይሽራቸው የሙዚቃ ስራዎቿን በመጋበዝ ተሰናበትኩ። መልካም ጊዜ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top