ታሪክ እና ባሕል

የጉንደትና የጉራዕ ደማቅ አሻራዎች

ጉንደት፡ የኢትዮጵያ መስተንግዶ ለግብጽ

መሐመድ ዓሊ ሳያጠናቅቅ የቀረውን የአያቱን “ታላቋን ግብጽ” የመፍጠር ህልም የልጅ ልጁ ኬዲቭ እስማኤል ፓሻ አንግቦ በመነሣት ኢትዮጵያን ጠቅልሎ በመያዝ ከካይሮ እስከ ዛንዚባር ከዚያም እስከ ኒያኒዛ ሐይቅ ለማድረስ ቆርጦ ተነሳ፡፡ ለስኬቱም የግብጽን ጦር በብዛት፡በጥራት፡ በዘመናዊ ትጥቅ፡ በሥነ ምግባር ማነጽና የውጊያ ሞራሉንና የዓላማ ጽናቱን ወደር የሌለው ለማድረግ በትጋት ሰራ፡፡ በተጨማሪ ለዓላማው መሳካት በወታደራዊ ሙያ ስመጥር የሆኑ ቅጥረኞችን ከተለያዩ አገሮች በገንዘብ ገዛ፡፡ ከአሜሪካ ብቻ ወደ 6ዐ የሚሆኑ ቅጥረኞችን በመግዛት ጦሩን በጣም ዘመናዊ አደረገ፡፡

ውስጣዊ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ እያስሰለለ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የዳግመኛ ዘመነ መሣፍንት መከፋፈል ምክንያት በአጼ ዮሐንስ ለይ ያኮረፉና የተነሱ ተቃዋሚዎችን በረቀቀ ስትራቴጅካዊ ዘዴ በመቅረብ የተለያዩ ስጦታዎችን፡ ገንዘብና ትጥቅ በመስጠት ወዳጅ በማድረግ መረጃ አቀባይ አደረጋቸው፡፡ ከዚህ አንጻር በሸዋው አጼ ምኒልክና አጼ ዮሐንስ መካከል የነበረውን የከረረ ቅራኔ በመጠቀም ምኒልክ ከግብጽ ጋር እንዲወግን በረቀቀ አቀራረብ ወዳጅነትን ፈጠረ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የውጭ ዜጎችና ሚስዮናውያን እየሰለሉ ምሥጢር እንድሰጡት አደረገ፡፡ ለዚህም ሙዚንገር የተባለ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መግባባት የሚችል ሰው ቀጠረ፡፡ ሙዝንገር አደገኛ የኢትዮጵያ ጠላት ቅጥረኛ ነበር፡፡

የተለያዩ ጸሐፍት እንደሚሉት የፈረንሳይ ላዛሪስት ሚስዮናውያንም ሌሎች አውሮፓውያን ግብጽ መፍጠን እንዳለባትና አመቺ የውስጥ መከፋፈል በኢትዮጵያ እንዳለ ለግብጻውያኑ ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻም የሁለቱ ሀይማኖቶች አባቶችም ኢትዮጵያ ከግብጽ ርቃ ሌላ ሀይማኖት ውስጥ እንድትገባ እንደማይፈልጉ ግምት ተወሰደ፡፡

ከዚህ ሁሉ ዝግጅትና ድጋፍ በኋላ በ1874 ኬዲቭ እስማኤል በኢትዮጵያ ላይ የጦርነት ክተት አወጀ፡፡ የወረራው ወታደራዊ ስትራቴጂም በሶስት አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን መውጋት ነበር፡፡ ለዚህም ከፍተኛ የጦር ኃይል በምጽዋ፡ ታጁራና ዘይላ ሰፈረ፡፡ በዘይላ ላይ የከተተው ጦር የተመራው በመሐመድ ራኡፍ ፓሻ ነበር፡፡ ይህ ጦር ዓላማው ከዘይላ ተንቀሣቅሶ ሐረርን ለመያዝና በምሥራቅ ኢትዮጵያ ላይ ለሚደረጉ ዘመቻዎች የመንደርደሪያ ሠፈር ለማዘጋጀት ነበር፡፡ ጦሩም ያለ ጠንካራ ተቃውሞ በ1875 ሐረርን ተቆጣጠረ፡፡

ሁለተኛው የጦር ግንባር የተመራው በቅጥረኛው ሙዚንገር ነበር፡፡ በእሱ የሚመራው ጦር በጣም የተደራጀ፤ የወቅቱን ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ 5ዐዐ ተዋጊ ኃይል የነበረበት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 400 ከሱዳን ቅኝ ግዛት የተመለመሉ ነበሩ፡፡ የተሰጠው ግዳጅም በመሀል ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ዓላማው አሰብንና የመሀሉን አገር ንግድ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ በአጼ ዮሐንስ ላይ ከግብጽ ጋር ግንባር በመፍጠር እንዲዋጉ ለማድረግ ነበር፡፡ የታሪክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ሙዚንገር ብዙ የአካባቢ ቋንቋዎች የሚናገር፡ የሚዋጋበትን አካባቢ ጠንቅቆ የሚያውቅና ሚስቱም ኢትዮጵያዊት የሆነች በመሆኑ ያለ ችግር በቀላሉ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት ኬዲቭ ነበረው፡፡ ይህ ግን ለቅጥረኛው ምንም አልጠቀመውም፡፡

የአፋር ድግስ ለሙዚንገር

ጦሩ ከታጁራ ከመንቀሳቀሱ በፊት የአፋር ህዝብ በደስታ እንደሚቀበለው ተነግሮት ሁመት ሎይታ በሚባል በአጉባት ሱልጣን እየተመራ በ1875 አፋርን አቋርጦ 40 ኪሎ ሜትር በእግር ከተጓዘ በኋላ ለጥ ያለ ሜዳ ላይ ድንኳን ተክሎ አረፈ፡፡ ርዕሰ ጉዳዩን በተለያዩ ጊዜያት ያጠኑት ጸሐፍት (ጌታቸው፣ ዓለማየሁ፣ ተወልደ) እንደነገሩን አፋሮች ወተት፡ ቅቤ፡ ፍየል፡ በሬ ገጸበረከት በማቅረባቸው ሙዚንገር በጣም ተደሰተ፡፡ ስለድል አድራጊነቱ ሙሉ እምነት ተሰማው፡፡ ጦሩም በደስታ ተሞልቶ መሣሪያውን ጥሎ መዝናናት ጀመረ፡፡ ነገር ግን በአፋር ሱልጣን መሀመድ ሀንፍሬ የታዘዘው የአፋር ጦር በጉዞ የደከመውን የሙዚንገርን ጦር በተኛበት ሌሊት በመውረር ደመሰሰው፡፡ ሙዚንገር፡ ሚስቱና ልጁም የጥቃቱ ሰለባ ሆኑ፡፡ ከ2ዐ የማይበልጡ ወታደሮች ብቻ ለወሬ  ነጋሪነት ተርፈው ታጁራ  ደርሰዋል፡፡ ሁመት ሎይታ ከተረፉት መካከል ነበርና የእልቂቱን ዜና ታጁራ ደርሶ ተናገረ፡፡ በሙዚንገር ሞት የኬዲቩ የቄሣር ግዛት የማስፋፋት ህልም ቅዠት ሆኖ ቀረ፡፡

የጉንደት ውሎ

ሶስተኛ የወረራ ግንባር ከሌሎቹ ግንባሮች በታጠቀው የመሣሪያ ጥራት፣ ብዛትና በአመራር ላይ ከተሾሙት አንጻር እጅግ በጣም ጠንካራ ተብሎ በኬዲቭ እስማዔል ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ በዚህ ግንባር የተሰለፈው የግብጽ ጦር ወደ 25ዐዐ ሆኖ በዘመናዊ ትጥቅ የተደራጀ ነበር፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ ዜግነት ያላቸው ቅጥረኛ ወታደራዊ አዞዦች የሚመራ ነበር፡፡ ይህ ጦር ከምጽዋ ወደብ ተነሥቶ ወደ ትግራይ በማምራት ከመረብ ወንዝ ደረሰ፡፡ በጉዳንጉዲ ሸለቆ ውስጥ ጉንደት በሚባል ቦታ ጠንካራ ምሽግ መሽጎ ጠበቀ፡፡

አጼ ዮሐንስ ይህን ወደ ዋና ከተማቸው እየገሰገሰ ያለውን ጦር ለመፋለም የክተት አዋጅ በማወጅ ወደ ሀያ ሺህ ሰራዊት እየመሩ የመረብን ወንዝ ተሻገሩ፡፡ ሁለት ምድብ ከነበረው ጦራቸው አንዱን ራሳቸው ሲመሩ ሁለተኛውን ሊጋባ አሉላ አባነጋ ይመራ ነበር፡፡ ህዳር 7 ቀን 1867 ሁለቱም የጦር ክፍሎች በተቀናጀ ማጥቃት በጉንደት ጠንካራ ምሽግ ተከልሎ ከተቀመጠው የግብጽ ጦር ጋር ፍልሚያ ገጠሙ፡፡ የአጼው ጦር ከምሽግ የጠላትን ጦር በተኩስ ወደ ገለጣ ሜዳ እንዲወጣ አድርጐ በባህላዊ ጦርነት ስልት ቀለበት ውስጥ በማስገባት አዛዡን ጨምሮ 13ዐዐ የግብጽ ጦር ገደለ፡፡ 4ዐዐ አቆሰለ፡፡ ብዙ ወታደር ማረከና ጥቂት ወታደሮች አምልጠው ምጽዋ ገቡ፡፡ አምስት መትረየሶች፣ 15ዐዐ ጠበንጃና በሺዎች  የሚቆጠር ጥይት ተማረከ፡፡ በኋላ በጉራዕ ጦርነት ተሳታፊ የነበረ ዳይ የተባለ አንድ አሜሪካዊ ኮሎኔል ስለ ጉንደት ጦርነት ሲጽፍ የግብጽ ጦር እንደቄራ ከብት በዮሀንስ ጦር እንዲታረድ ተፈርዶበት ነበር ብሏል፡፡

ጌታቸውና ዓለማየሁ እንደጻፉት ከኢትዮጵያ በኩል 552  ሰው ሲሞት 4ዐዐ ያህል ደግሞ ቆስሏል፡፡ አንድም አልተማረከም፡፡ የግብጽ ጦር ቢሸነፍም ሽንፈቱ በምስጢር ተያዘ፡፡ ነገር ግን መረጃው ቀስ በቀስ መውጣቱ አልቀረም ነበርና ኬዲቭ እስማዔል መርዶውን ሲሰማ እብደት ሞከረው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የአጼ ዮሐንስንና የጦራቸውን እልቂት ዜና ሲጠባበቁ የነበሩ የግብጽ ቅጥረኞች ሆኑ የውጭ ደጋፊዎቻቸው ተሸማቀቁ፡፡ የኢትዮጵያ ዝናና ገጽታ በዓለማቀፍ ግንኙነት ገነነ፡፡

የኢትዮጵያና የግብጽ ጦርነት በጉራዕ

ኬዲቭ እስማዔል በቁጭት ተንገብግቦ ለበቀል ተነሳ፡፡ በጉንደት ላይ እንደ ሸከላ የተሰባበረውን ጦሩን ክብር ለመመለስ በጥቂት ወራት ሀያ ሺህ ሠራዊት ከጉንደቱ ጦርነት ጊዜ በተሻለ ሬሚንግተን በሚባል ዘመናዊ ጠመንጃና 4ዐ ክሩፕ መድፎችን አደራጀ፡፡ ጦሩን ሙሐመድ ራቲቭ ፓሻ በበላይነት እንዲመራ ሲያደርግ፤ አሜሪካዊውን ጄኔራል ሎሪንግንና በጀርመን አገር ወታደራዊ ትምህርት የተማረውን ልጁን ሙላይ ሐሰን ፓሻን በምክትልነት ሾማቸው፡፡ ይህ ጦር በ1875 ዓ.ም ምጽዋ ገብቶ እረፍት ካደረገ በኋላ ሁኔታዎችን እያየና መረጃ እየሰበሰበ በዝግታ ተጉዞ በ1876 የመረብን ወንዝ ተሻገሮ ጉራዕ ደርሶ መሸገ፡፡

አጼ ዮሐንስ ከጉንደት ድል በኋላ የተበተነ የገበሬ ጦራቸውን ዳግመኛ ክተት ብለው ወደ ስድሳ ሺህ ሞፈር ሰቀል ሠራዊት በአምስት መስመር አንቀሳቀሱ፡፡ ሊጋባ አሉላ ግንባር ቀደም አዛዥና አዝማች ሆኖ እንዲዘምት ታዘዘ፡፡ የግብጽ ጦር ከጉንደት ጦርነት በመማር ከምሽግ አልወጣ ብሎ በከባድ መሣሪያ በማጥቃቱ ብዙ ደም ከኢትዮጵያ በኩል ፈሰሰ፡፡ ብዙ ጉዳት በሊጋባው ጦር ላይ ደረሰ፡፡ በዚህ ትኩስ ድል የተነቃቃው የግብጽ ጦር ከምሽጉ ወጥቶ በግላጭ የኢትዮጵያን ጦር እንዲደመስስ ታዘዘ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በቁጥር ብልጫ ነበረውና በታላቅ የጀግንነት ስሜት የግብጽን ወራሪ ጦር ዳግመኛ ቀለበት ውስጥ በማስገባት ደመሰሰው፡፡

የኢትዮጵያ ድልና የግብጽ ኪሳራ

የጉራዕ ጦርነት ሁለቱ አገሮች የመጨረሻ የተጨፋጨፉበት ሲሆን የአጼ ዮሐንስ ዜና መዋዕል እንደሚለው ዓለም ከተፈጠረ ሆኖ የማያውቅ የመሬትን መሠረት ያናወጠ ጦርነት ነበር፡፡ በዚህ ጦርነት ሙላይ ሀሰን ፖሻ ሩጦ ለማምለጥ ሲሞክር ተማረከ፡፡ ዓለማየሁ እንደጻፈው በጉራዕ ጦርነት የተደመሰሰው የግብጽ ጦር አስራ አምስት ሺህ ወታደሮችን የያዘ ነበር፡፡ ከነዚህ 15ዐዐ ወታደሮች ቆስለዋል፣ 2ዐዐዐ ደግሞ ተማርከዋል፡፡ የተረፈው ሸሽቶ ምጽዋ በመግባት ተርፏል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል 1ዐዐ ያህሉ ሲቆስሉ ከ35ዐዐ በላይ ወታደሮች ተሰውተውባታል፡፡ ምንም ግን አልተማረከባትም፡፡ ከጦርነቱ ኢትዮጵያ 39 መትረየሶች፣ 2ዐ መድፎች፣ 15,000 ልዩ ልዩ ጠመንጃዎችና በብዙ በሺህ የሚቆጠሩ ጥይቶች ማርካለች፡፡

የጉንደትና የጉራዕ ጦርነቶች ለኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ውስጣዊና ውጫዊ ጠቀሜታ ነበራቸው፡፡ በጦርነቱ የአጼ ዮሐንስን ሽንፈት ሲመኙ የነበሩ ኃይሎች እንዲያፍሩና ዳግመኛ እንዲሸማቀቁ በማድረግ የአጼውን የውስጥ የፖለቲካ በላይነት እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ለኢትዮጵያ በድጋሚ በዓለምአቀፍ ግንኙነት ዝናንና ክብር አጐናጽፏታል፡፡ ግብጽ ለዚህ ጦርነት አምስት መቶ ሺህ ስተርሊንግ ፓውንድ አውጥታለች፡፡ ሆኖም በሽንፈት ተዋርዳለች፡፡ የማታገግምበት የኤኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ወድቃለች፡፡ በመሆኑም በ1882 የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሆነች፡፡ ሽንፈቷ ከግራዋ የመረረ ነበር፡፡

ግብጽ በሁለቱ ጦርነቶች ከ16 ሺህ በላይ ወታደሮቿ ተደምስሰዋል፣ ከ2 ሺህ በላይ ተማርከውባታል፣ አምስት መትረየሶች፣ ሀያ መድፎች፡ ከ16 ሺህ በላይ ጠመንጃዎች፤ አራት ሺህ በቅሎና ግመሎች ተማርከውባታል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግብጻውያኑ ከግማሽ ቢሊዮን ስተርሊንግ ፓውንድ በላይ የገንዘብ ኪሳራ ኣጋጥሟቸዋልና ጦርነቱን እርግፍ አድርገው በመተው ሐማሴን፤ አካለጉዛይና ሠራዬን የተባሉ የኢትዮጵያ ከተሞችን ለቀው ወደ ምጽዋ ሄዱ፡፡

ንጉሱ በዋንዛ ዛፍ ስር

ጉራዕ ላይ ከምሽግ ወጥቶ ከተደመሰሰው የግብጽ ጦር ጀርባ ምሽጉን የሙጥኝ ያለውን የግብጽ ጦር አስከብበው አጼ ዮሐንስ በትልቅ ዋንዛ ስር ተቀምጠዋል፡፡ እዚያ እያሉ መሐመድ ሪፋት የሚባል የወራሪው ጦር አዛዥ አስተርጓሚ የሆነ ሰው ወደ ንጉሱ መጣ፡፡ ተቀበሉት፡፡ አመጣጡ ስለእርቅ ሊያናግራቸው ነበር፡፡ አስተዋዩ ንጉስ አሸናፊ ነኝ ብለው መልዕክተኛውን አልናቁትም፡፡ መልእክቱን ተቀበሉት፡፡ ከባለሟሎቻቸው ጋር ተመካከሩ፡፡ ግብጽ አዲስ ደጀን ጦር ማስጠጋቷን ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ ከቀጠለ በመስዋትነት የተገኘው የጉራዕ ድል እንዳይነጠቅ ሰጉ፡፡ የኢትየጵያ ጦር በነፍስ ወከፍ ስንቅና ትጥቁን ይዞ፣ የቅርብ ጌታውን ተከትሎ፣ እርሻውን ትቶ የዘመተ የገበሬ ጦር በመሆኑ ለረዥም ጦርነት አስተማማኝ እንደማይሆን አሰቡ፡፡ ከዚያም በላይ የአውሮፓ ኃያላን በኢትዮጵያ ድል ስለማይደሰቱ የቅኝ ገዥዎች “አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሣል” እንደሚባለው ተያያዥነታቸውን አስተዋሉ፡፡ ተባብረው ግብጽን ቢደግፉ የጦርነቱ ሁኔታ ሊቀየር የሚችል መሆኑን ከግምት አስገብተው በተገኘው ድል ረክተው የእርቅና የሰላም ድርድሩን ተቀበሉ፡፡

አሉላ ራስ ሲሆን

ከግብጽ ጦር ሰዎች ጋር የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ውይይት ያመጣው ውጤት አልነበረም፡፡ ሆኖም የሰላም ድርድር ከተጀመረ ስጋት አይኖርም በሚል አጼ ዮሐንስ የከበቡትን ጠላት ትተው ወደ አድዋ ተመለሱ፡፡ ከመመለሳቸው በፊት በየቦታው ተበታትነው የነበሩትን የግብጽ ጦር ትርፍራፊዎችንና በምሽግ ውስጥ የታሰሩትን ተቆጣጥሮ አካባቢው ሊያስተዳድር የሚችል ሰው መሾም እንዳለበት ከመከሩ በኋላ ለአገር ባላቸው ታማኝነት፣ ፍቅርና በጉንደትና ጉራዕ በፈጸሙት ጀብዱ መዝነው ሊጋባ አሉላን ራስ ብለው የሐማሴን አገር ገዥ አድርገው ሾሙ፡፡

የግብጽ ዓይንአውጣ የድርድር ሀሳቦች

ንጉሱ ከቆይታ በኋላ የሰላም ድርደሩን መቀበላችውን ለጦር አዝማቹ በመልእክተኞቻቸው ደብዳቤ አስይዘው ላኩ፡፡ ተክለጻድቅ እንደጻፈው የንጉሱ ደብዳቤ “ሦስት ቀን ሙሉ ከሁለታችን ወገን በሰውም በአምላክም ዘንድ ያልተወደደ ደም ፈሰሰ፡፡ አሁን የእርቅ ድርድሩን ትፈልጉ  እንደሆነ ሁነኛ  ሰው  አድርጉና  ከኛም  አንዱን  እንድንመድብ ዛሬውኑ  መልሱን  አስታውቁ” የሚል ነበር፡፡ አዛዡም  “መልካም  ነው፡፡ እኛም እርቁን እንፈልጋለንና ሁነኛ ሰው ይላኩልን” የሚል መልስ ላከ፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ በኩል ሊቀ መኳስ ምርጫ ወርቄና ደስታ ተመደቡ፡፡ ከግብጽ በኩል ዓሊ አፈዳድ አል ሩቢ ተመደበ፡፡ ተደራራርዎቹ ከአጼው ዘንድ ቀረቡ፡፡ የግብጽ ተደራዳሪ እንደ ተሸናፊ ሳይሆን እንደ አሸናፊ የማስገደድ ይዘት ያላቸውን ሶስት ዓይንአውጣ የድርድር ነጥቦችን ይዞ መጣ፡፡ የመደራደሪያ ሀሳቦቹ በጉንደትና በጉራዕ ሁለት ጦርነቶች ከግብጽ የተማረከው የጦር መሣሪያ እንዲመለስ፣ ምርኮኞቹ በነጻ እንዲለቀቁና በሁለቱ መንግሥታት መካከል ነጻ የንግድ ልውውጥ እንዲደረግ የሚሉ ነበሩ፡፡

አጼ ዮሐንስ ደግሞ ግብጾች ሐማሴንን ለቀው ወደ ነበሩበት ወደ ምጽዋ ወደብ እንዲመለሱ ጠየቁ፡፡ የነጻ ንግዱን ተስማሙ፡፡ ነገር ግን የተማረከው የጦር መሣሪያ እንደማይመለስ አስታወቁ፡፡ ምርኮኞቹን ለመመለስ ተስማሙ፡፡ ሆኖም ሁሉም ምርኮኞቹን ከመመለሳቸው በፊት የግብጽ ጦር ከሐማሴን እንዲወጣ ጠየቁ፡፡ ሆኖም ግብጾች ምርኮኞቹን ከተረከቡ በኋላ ቀሪ ምርኮኞች እንዳሏቸውና ቀሪዎቹ ካልተመለሱ ድርድሩ ፍጻሜ እንደማያገኝ በመግለጽ ውዝግብ ፈጠሩ፡፡ በዚህም ግብጽ ኢትዮጵያን አሞኝታና አታላ የራስዋን ብሔራዊ ጥቅም አስጠበቀች፡፡የግብጾች ዲፕሎማሲ ሁልጊዜ ማታለልን ያማከለ እንደሆነ ከዚህም መረዳት ይቻላል፡፡

የግብጻውያን መሰሪነትና ሴራ

በተደጋጋሚ በጦርነት የተሸነፉት ግብጻውያን የጦርነት አማራጩን ትተው የተንኮል ድራቸውን ማድራት ጀመሩ፡፡ የታሰበው የሰላም፡ የወዳጅነትና ንግድ ስምምነት እንዳይቋጭ አደረጉ፡፡ ንጉሱ ግብጽ ስምምነቱን እንድትፈርም ደጋግመው መልዕክተኛ ቢልኩም በማጭበርበርና ምክንያት ፈጥረው በማጓተት ረቅቅ ስምምነቱ ተቀባይነት እንደይኖረው አደረጉ፡፡ ነገር ግን ሁሌም ብልጭልጭ ገጸ በረከቶችን ለንጉሱ ይልኩ ነበር፡፡ ንጉሱን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን ውስጥ ለውስጥ በገንዘብ፡ በትጥቅና በሞራል እየደገፉ የእነሱ ቅጥረኛ እንዲሆኑ መደገፋቸውን ቀጠሉ፡፡ፕሮፌሰር ላጲሶ እንደጻፈው ንጉሱ ትልቅ ስህተት ሰርተዋል፡፡ በብዙ የአገር መስዋዕትነት ያገኙትን ድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ሁለት ትልልቅ ጦርነቶችን ቢያሸንፉም ጠላት የያዘውን መሬት አላስመለሱም፡፡ የጠላትን ምርኮኞችም በነጻ ለቀዋል፡፡

ንጉሱ ወደ መናገሻ ከተማቸው አድዋ ተመልሰው የዲፕሎማሲ ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ ዋናዎቹ የትኩረታቸው ነጥቦች የተያዙባቸው ግዛቶች ማስመለስና ነጻ የባህር በር ማግኘት ነበር፡፡ መልዕክተኛ በመላክ ያደረጉት ጥረትም ከንግድ ግኑኝነት በስተቀር በሌሎቹ ጥያቄዎች ላይ ከስምምነት ሊያደርሳቸው አልቻለም፡፡ ግብጽ በጉንደትና ጉራዕ ላይ የንጉሱን ክንድ ከቀመሰች በኋላ ኢትዮጵያን በጦር ኃይል መሞከር እንደማያወጣት በመማን የአገር ውስጥ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን በማጠናከርና ቅራኔዎችን ለማባበስ ተግታ መስራቷን ቀጠለች፡፡ የሁለቱም አገሮች ግኑኝነትም ‹‹በቀዝቃዛ ጦርነት›› በታሪክ ዘለቀ፡፡ እኔ ግን እዚህ ላብቃ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top