ታዛ ዐለማት

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተልዕኮ፣ ተግባር እና አደረጃጀት

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰባኛ ዓመቱን ጊዜው ዘግየት ቢልም ከቅርብ ጊዜ በፊት ሲያከብር “የዩኒቨርስቲው ተልዕኮ፣ ተግባር እና አደረጃጀት በሚል ርዕስ” ያደረኩትን ንግግር ለብዙ ሰዎች እንዲዳረስ፣ በጽሑፍ መልክ አንዳበረክት በተደጋጋሚ ምክር ስለተበረከተልኝ፣ ምክሩን ተቀብዬ፣ ይሀችን ጸሑፍ ለአንባብያን ለማበርከት ወሰንኩ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች፣ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲንም ይጨምራል፣ በመሠረቱ የማያቋርጥ የዕውቀት እና የግንዛቤ ምንጮች መሆን አለባቸው፡፡ በዕውቀት ፍለጋ ሂደት፣ “እውነት” ተብሎ የታመነበት ጉዳይ፣ ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት፣ ነባር “እውነት”፣ በአዲስ “እውነት” የሚተካባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ለምንም ይሁን፣ ለማንም ጥያቄ የሚሰነዘርባቸው መድረኮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡

ስለሆነም በዩኒቨርስቲ ውስጥ የሃሳብ ልዩነት እንደ እድገት እንጅ እንደ እንቅፋት አይፈረጅም፡፡ ሆኖም ልዩነቶች ቁልጭ ብለው ነጥረው ወጥተው መፈተሸ፣ መመርመር፣ አለባቸው፡፡ ልዩነቶች መመርመር ያለባቸው ከመረጃ ጥልቀት፣ ጥንካሬ እና አሳማኒነት አንፃር ነው፡፡ “ሰንካላ” መረጃ ያለው አሳብ እንደ “እምነት” እንጂ እንደ “ዕውቀት” ብሎም እንደ “እውነት” አይወስድም፡፡

በ1962 ዓ/ም ለከፍተኛ ትምህርት የተቋቋመ አማካሪ ኮሚቴ በሪፖርት ላይ ያሰፈረው አጭር አስተያየት ለዩኒቨርሲቲዎች ዋና ተልዕኮ እና ተግባር እንደ መመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ —አንድ ዘመናዊ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ዓይነት ኃላፊነት አለበት፡፡ የመጀመሪያው ኃላፊነት ለሚያገለግለው ሀገረ-ሰብ፣ ማህበረ ሰብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ለዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች ወንድማማችነት ነው። የመጀመሪያው ደካማ ከሆነ ዩኒቨርሲቲው የሕዝቡ ድጋፍ አይገባውም። ሁለተኛው ደካማ ከሆነ የዩኒቨርሲቲው ዲግሪዎች ሊከበር የሚገባው የትምህርት ደረጃ አይኖራቸውም። የዩኒቨርስቲው ምሩቆችም በዓለም ውስጥ የሚገኙት ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጡት ዕድል ሊጠቀሙ፣ በዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ሊሳተፉ አይችሉም። የመጀመሪያውን ኃላፊነት ዩኒቨርሲቲው ለማካተት ወይም ለማከናወን የሚችለው ለሀገሪቱ ፍላጎት አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ በማስተማር ምርምር በማድረግ ነው። ሁለተኛውን ለማስከበር ይህንኑ ትምህርትና ምርምር ዓለም በተቀበላቸው በትክክለኛነት በታማኝነት ደረጃዎች በማከናወን ነው፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበትን ሁኔታ እንፈትሽ፡፡እኔ የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በተመሰረተ በአስር ዓመቱ ገደማ፣ ያም በ1952 ዓ/ም በመስከረም ነበር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተማሪነት ገብቼ፣ በአስታሚሪነት፣ በተመራማሪነት በተለያዩ ደረጃዎች አላፊነት ተሰማረቼ በ1986 ዓ/ም መቋጫ ዩኒቨርሲቲውን የለቀቅሁ፡፡ከሩብ መቶ ዓመት በላይ የአአ ዩኒቨርሲቲ አባል በነበረኩበት ዘመን ኑሮዬም ተግባሬም ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተቆረኜ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦረድ አባል ሆኜ ስለነበር፣ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለዘመናት ቅርብ ግንኙነት ነበረኝ፣ ስለሆነም ስለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስን አሰተያየት ለመስጠት እችላለሁ፡፡

አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እንደሌሎች የአገሪቱ የልማት ተቋማት ሁሉ፣ ብዙ መሰናክሎችን አልፎ ነው እዚህ የደረሰ፡፡ እንዲያም ሆኖ እስከዛሬ በሰው ኃይል ግንባታ ያበረከተው አንቱ የሚያሰኘው ነው፡፡ ለዩንቨርሲቲው አባላትም ይህ የኩራት እንጂ የአፍረት፣ የእርካታ እንጂ የመሸማቀቅ ምንጭ መሆን የለበትም፡፡ ሆኖም የተሻለ ሊተገበር ይችል እንደነበረም መዘንጋት የለበትም፡፡

ስለዩኒቨርሲቲው ያለኝ አጠቃላይ እይታ ከብዙ ትችቶች የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ዩኒቨርሲቲው በሚያመርታቸው ምሩቆች ብቁ አለመሆን፣ በብዙ ሰዎች ሲዘለፍ፣ ሲወቀስ፣ እሰማለሁ፤ ይህ ትክክል አይመስለኝም፡፡ዩኒቨርሲቲ ለምረቃ የሚያሰናዳቸው ተማሪዎች፣ እዚያው ፈልተው፣ እዚያው ያደጉ፣ ብሎም የተመረቱ አይደሉም፡፡ ከየቦታው ፈልተው፣ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ትምህርት ሰንቀው፣ በተለያዩ የዕውቀት፣የሙያ ስምሪት ለመታነፅ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ናቸው፡፡በዚህ ሂደት የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ቋት የሰጡትን ተቀብሎ ፈጭቶ ነው፣ ዱቄት የሚያበረክተረው፤ ዩኒቨርሲተው ቋቱ ውስጥ “ዳጉሳ” አስገብቶ፣ “የነጭ ጤፍ” ዱቄት መጠበቅ ጭፍን ምኞት ነው፡፡የትምህርት ጥራት ጉዳይ የሚነካካቸው ተቋምት እንዲሁም ግለሰቦች ብዙ ናቸው፣ ወላጆችንም ይጨምራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ጣቶችን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች አቅጣጫ ብቻ መቀሰር ተገቢ አይመስለኘም፡፡

እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መወቀስ አለበት የምለው ከሌላ አንፃር ነው፡፡ ለምሳሌ የቦርድ አባል በነበርኩበት ዘመን ዩኒቨርሲቲው የገቢ ምንጭ ይሆኑኛል ብሎ በየዓመቱ ያቀርበቸው የነበሩ ጉዳዮችን ላውሳ፣ ለምሳሌ፣ እነሱም «ቲ-ሸርት» ሽያጭ፣ «ሰንጋ አስብቶ መሸጥ»፣ እና ተመሳሳይ ተግባራት ነበሩ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የገንዘብ ገቢ ብሎ የተለማቸው መንገዶች ብዙ ሌሎች ግለሰቦች እና ድርጅቶች ሊያካሂዷቸው የሚችሉ ተግባሮች ናቸው፡፡ ለእነኝህ ዓይነት ስምሪቶች ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አካላት የተሻለ አቅምም፣ ተግባራዊ ችሎታም የለውም፡፡

በእኔ አስተያየት የዩኒቨርሲቲው የገቢ ምንጭ መሆን ያለባቸው፣ ሌሎች ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከዩነቨርሲቲው ጋር ሊፎካከሩ በማይችሉባቸው መስኮች መሆን ይገባቸዋል፡፡ ድርጊቶችም እንደ ስልጣኔ መንገድ ተምሳሌትነት መታየት መቻል አለባቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ለምሳሌ ለማስተማሪያነት የሚያገለግሉ መረጃዎችን ማዘጋጀት፣ ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት ግብዓት የሚሆኑ መጻሕፍትን እና በተመጣጣኝ መንገድ ሊመረቱ የሚችሉ የላቦራቶሪ ግብአቶችን ሊያሰናዳ ይችላል፣ ውስብስብ ያልሆኑ የራዲዮ፣ የስልክ መሣሪያዎችን ለማምረት ይችላል፡፡

በየትምህርት ቤቶቻችን ያሉ ላቦራቶሪዎች (ካሉ)፣ ያላቸው ይዘት መጠናከር አለበት፤ ብዙ የላቦራቶሪ መሣሪያዎች ባገር ቤት ውስጥ ሊመረቱ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንደዚህ ያሉ ተግባራት ላይ ነበር መሠማራት የሚገባው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ አንዳንድ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን መፈብረክ የሚችሉ በአካባቢያችን ብዙ «ዎርክሾፖችም» አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ተባብሮ፣ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን መፈብረክ ይቻላል፡፡ በተመመሳሳይ ሂደት በመስኩ እውቀት እና አቅም ካላቸው የውጭ አገር ድርጅቶችም ጋር በመስማማት፣ እንዲሁም ጉዳዩ ከሚያገባቸው መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ብዙ የትምህርት መሣሪያዎችንም መፈብረክ ይቻላል፡፡ ይህን መሰል ተግባሮች ናቸው የዩኒቨርሲቲው የገቢ ምንጭ መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

በግብርና አካባቢ ነባር ችግር እንዳለብን አገነዘባለሁ፡፡ የግብረና ትምህርት በ1940ዎች ሲጀመር ትኩረት የሰጠ “ለዘመናዊ ግብርና” ስለነበረ፣ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በጣም የራቀ ነበር፡፡ቀስ በቀስ ትምህርቱን ተጨባጭ ለማደረግ እየተሞከረ ነው፡፡ ቀደም በነበረው በነባሩ ሂደት፣ በማሳ ላይ “የስንዴን ቡቃያ” “ከገብስ ቡቃያ” ለይቶ የማያውቁ ምሩቆች ለማበርከት በቅተን ነበር፡፡

የአአ ዩኒቨርሲቲ የወደ ፊት እቅጣጫ (ስምሪት)

የትምህርት አሰጣጥ፡-ዩኒቨረሲቲዎች የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ እውነታውን በተገቢ መንገድ እያስተናገዱ እንዳለሆኑ ይወሳል፡፡ እንዲሁም ለመደበኛ የዕውቀት ዘርፎች (ለምሳሌ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ. ሂሳብ፣ ወዘተ) በቂ ትኩረት እየተሰጠ አይደለም፡፡ “ታሪክን” አዛብቶ መገንዘብ እንዳንሰራራ ይታወቃል፡፡ ስለአገራችን ተገቢ እና ትክክለኛ ግንዛቤ ትውልድ እንዲጨብጥ የሁላችንም አላፊነት ቢሆንም፣ ዩኒቨርሲቲዎች ግን የተልዕኮቻቸው አካል ስለሆነ፣ ልዩ አላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህ ሂደት አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የመሪነቱን ሚና መውሰድ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በአአ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ክፍል አደረጃጀት፡-በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንዳንድ የትምህርት፣ የምርምር ዘርፎች በተሻለ አደረጃጀት፣ ሸንቀጥ ብለው፣ወጥ ሆነው፣ ሊዋቀሩ ይችላል፡፡ይህም መታየት ያለበት አቅምን አሰባስቦ፣ አቀናጅቶ፣ በአገር ልማት “ስትራቴጂዎች” ላይ ለማተኮር አመችነቱን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ መሆን አለበት፡፡ አቅምን በአንድ ጥላ ሥር ማሰባሰብ ልምድን ከማካፈል አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ሃብትን፣ በሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀምንም ያካትታል፡፡ ይህም አደረጃጀት ችግርን በጋራ ለመቃኘት እና መፍትሄ ለመፈለግ ምቹ ይሆናል፡፡ ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥሞና ተረድቶ፣ ሁኔታዎችም የምርምር እና የትምህርት አቅጣጫ መፈተሻነት አገልግለው፣ የተሻለ፣ በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያተኮረ፣ ትምህርት እና ምርምር በቅንጅት እንዲተገበሩ እና ብሎም እንዲጠናክሩ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ለምሳሌ “የአካባቢ ክብካቤን ጥናት” (Enviromental Studies) ዘርፍ ብንወስድ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “የኤንቫይሮንሜንት ጥናት” (“የአካባቢ ክብካቤን”/ Environmental Studies) የትምህርት ዘርፎች የሚያስተናግድበት መንገድ እንደገና መፈተሸ አለበት የሚል እይታ አለኝ፡፡ ከዓመታት በፊት በኣማከሪ ደረጃ በአዲስ አበባ ዩነቨርሲቲ ተሰማርቼ በነበረበት ወቅት፣ ነበር ይህን የተረዳሁ፡፡ “የኤንቫይሮንሜንት ጥናት” የትምህርት ዓይነቶች የሚሰጡ በአስራ አምስት ገደማ የትምህርት ክፍሎች ነበር፤ያም ሲደረግ እነኝህ የትምህርት ክፍሎች ከአምስት ባላነሱ “ፋካልቲዎች” እና “ኮሌጆች” ውስጥ የተመሰረቱ ነበሩ፣ በተጨማሪ እነኝህ የትምህርት ክፍሎች ይህ ነው የሚባልም የጎንዮሽ ግንኙነቶችም አልነበሩዋቸውም፡፡

በእኔ እይታ የሚሻለው “የኤንቫይሮንሜንት ጥናት” (የአካባቢ ጥናት አንድ ባለቤት ኖሮት፣ ማለት “የኤንቫይሮንሜንት ጥናት ኮሌጅ” (College of Environmental Studies) ተዋቅሮ፣ መደበኛ የሆኑ ትምህርቶችን የማስተማር ሃላፊነት የዚህ ተቋም ሆኖ፣ ሌሎች ልዩ “ሙያ-ተኮር” የሆኑት የትምህርት ዓይነቶች በተለያዩ የፋካልቲዎች አበላት ቢስተናገዱ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡

ጉዳዩን ባጠናሁበት ወቅት የነበረው የአዲስ አበባ “የኤንቫይሮንሜንት ጥናት” የሚስተናገድበት መንገድ እንደ “ዘመነ መሳፍንት” ሊታይ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ የትምህርት ክፍል “በነፍጥ ፈናታ” “አንድ ሁለት ፕሮጀክቶችን” አንግቦ ፣ አንዳንድ አመባ ላይ መሽጎ ነው ይገኝ የነበረ፡፡ በነገራችን ላይ አገራችን በመሳፍንት ብቻ ተገዝታ አታውቅም፣ ዘመነ መሳፍንት፣ የደካማ ንጉሠ ነገሥታት ዘመን እንጅ፣ አገሪቱ ነግሠ ነገሥት አልባ የነበረችበት ዘመን አልነበረም፣ ይህም ሁኔታ ለዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደር ገላጭ ሊሆን ይችላል፡፡

የምርመር ትኩረት እና አደረጃጀት፡-አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በየፈርጁ የሚካሄዱት ምርምሮች አብዛኞች ቀጥታውን በአገር ልማት ላይ ያተኮሩ አይደሉም፡፡ በመሠረቱ በምርምር ሂደት ውስጥ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለልማት ግብዓት የሚያገለግሉ መረጃዎች ማካበት ላይ መሆን አለበት፡፡ የልማት ሂደትም ፈረጀ-ብዙ ስለሆነ፣ በተለያዩ በምርምር ዘርፍ ያሉ መምህራንን የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች በቡድን ሊያሳትፍ እና አንድ ልማት ተኮር ግብዓት፣ መረጃ፣ በጋራ ሊያመነጩ ይችላሉ፡፡

ታዳጊ አገሮች ብዙውን ጊዜ የልማት ግብዓት ሊሆን በሚችል ምርምር (Applied Research) ላይ ይሰማራሉ፤ ይህም የሚደረግበት ሁለት ዓበይት ምክንያቶች አሉት፤አንዱ የምርምሩ ውጤት መሠረታዊ ፍላጐት ለማሟላት ለልማት ቀጥተኛ ግብዓት ሊሆን የሚችል በመሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት “ፈር-ቀዳጅ” (Basic Research) ምርምር ላይ ለመሠማራት ብዙ ጠበብት ምሁሮች እና ጠቀም ያለ ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡

ምርምር በመሠረቱ መረጃ አመንጭ ሂደት ነው፤ የመረጃ ክምችት በዳበረ መጠን፣ በዳበረው መረጃ ላይ የተመሠረተ ብዙ ተጨባጭ የልማት እቅድ ሊተለም፣ ብሎም በሥራ ሊተረጐም እና የብልፅግና ሕልምን እውን ለማድረግ ያስችላል፡፡

ምርምር በተቀናጄ ሁኔታ (Thematic Research) ቢተገበር ይመረጣል፡፡ ለዚህም ጎን ለጎን የመረጃ አሰባስብ እና ስርጭት “ስትራቴጂ” መቀየስ ይገባል፡፡ ለተቀናጄ ምርምር ግንዛቤ እንዲረዳን አንድ ምሳሌ ወስደን በግርድፉ እንመልከት፡፡ በስኳር ማምረት እና ገበያ አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ተመራማሪዎች በቡድን ተደራጅተው፣ ጠቃሚ መረጃ ለማበርከት በሚከተሉት መስኮች ምርምር ሊያካሄዱ ይችላሉ፡፡

“በባዮቴክኖሎጂ” ምርምር “ቲሹ ካልቸር” (tissue culture, etc) ሊሠማሩ ይችላሉ፡፡ በ”የቅድመ-ማሳ” ዝግጅትን የሚያካትቱም ምርምሮችን ማስተናገድ ይቻላል። ለምሳሌ የአፈር ዓይነት፣ በአፈር ልማት ግብዓት አማራጮች፣ የመስኖ ዘዴዎች ወ.ዘ.ተ.ምርምር እና ጥናት ላይ ሊሠማሩ ይችላሉ፡፡ ተባይና በሽታን መከላከል፣ የዘር ምርጫ፣ በተባይ ማጥፊያ ወ.ዘ.ተ. እና የቀን ተቀን ትኩረት እና እንክብካቤ ስልት ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን፣ እንዲሁም የማሳ አዝርዕት እንክብካቤ፣ መረጃዎች በምርምር ሊያመነጩ ይችላሉ፡፡ ለምርት ስብሰባ ስርዓት ሂደቶች (እንዴት/መቼ / በማን /ወ.ዘ.ተ.) የሰው ኃይል ፍላጎትን ያካተተ መረጃ በጥናት ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ የምርትን ውጤት ማሳደግ ይቻላል፡፡

ከዚያም ወደ ስኳር ማምረት ደረጃ ሲደርስ፣ የፋብሪካው ዓይነት፣ የግብዓት አሰጣጥ፣ ገበያ ተኮር፣ የምርት ጥራት፣ ፓኬጅ (መጠን) አቅርቦት፣ ሽያጭ (የት/ መቼ)፣ ለዚህ ሂደት ምርምር እና ጥናት ላይ የተመሰረተ ስልት ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነት ምርምርም ነው “የተቀናጄ ምርምር” (Thematic Research) የሚባለው፡፡ ሂደቱ የብዙ ምርምር ዘረፎች ቅኝጅት ሲሆን፣ ውጤቱ ግን አንድ ምርት ተኮር ነው፣ ያም ስኳር ማምረት፡፡ ሊተገበሩ ከሚችሉ ጥናቶች እና ምርምርች ብዛት ስንገነዘብ፣ ለተመራማሪዎች እንደፍላጎቶቻቸው የሚሰማሩባቸው የምርምር ዘርፎች ይኖራሉ፡፡ ስለሆነም አንድንዴ እንደሚወሳው የግለሰቦች የምርምር ነፃነት አይገታም፡፡

የትምህርት መሰናዶዎች (መጻሕፍት ላቦራቶሪ መሳሪያዎች)

መጻሕፍት፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ መምህራን ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ጋር በመተባበር፣ በተለያዩ የሳይንስና ሌሎች የትምህርት ዘርፎች የማስተማሪያ መጽሐፎችን ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡ በመጽሐፍቱም ውስጥ የሚጠቀሱ ምሳሌዎች በአገር ውስጥ ባሉ በሚታወቁ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም በቂ መረጃ ማሰባሰብ ይቻላል፡፡ ብዙም ባይሆኑ ለምሳሌነት የሚያገለግሉ የልማት ግብዓቶችም የሆኑ ጥናቶች አሉ፡፡

ለዚህም ጉዳይ የተለያዩ ቡድኖች ተደራጅተው፣ የመጽሐፎችን ይዘት ካቀዱና፣ በመጽሐፍቱ መካተት ያለባቸውን የዕውቀት ዘርፎች ከዳሰሱ በኋላ፣ በየፈርጁ ጥቂት ሰዎች እየተመደቡ የማስተማሪያ መጻሕፍትን ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡ ቡድኖች አገር ቤት በሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሊመሠረቱ ይችላሉ፣ ሆኖም በውጭ አገርም ያሉ ኢትዮጵያውያን ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ይህን ዓይነት ሂደትና ድርጊት ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆኑ መጻሕፍት ከማዳበር ባሻገር፣ ለመምህራን አቅም ግንባታ ከፍተኛ አስተዋዕኦ አለው የሚል እምንት አለኝ፡፡

የላቦራቶሪ መሳሪያዎች፡- የሳይንስ ተማሪዎች በላቦራቶሪ የሚቀሰምን እውቀት፣ ክህሎት፣ የማካበት ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ ምክንያቶችም ፈርጀ-ብዙ ናቸው። ሆኖም ዋናው “የመሣሪያ” እና “የኬሚካል” እጥረት ነው ይባላል፡፡ የተወሰነ ችግር መፍቻ አንዱ መንገድ፣ በሳይንስ አካባቢ በየፈርጁ የተሰማሩ መምህራን መሠረታዊ በላቦራቶሪ የሚገኙ እውቀትን ዳስሰው፣ ዕውቀቱ በአገር ውስጥ ሊፈበረኩ በሚችሉ መሣሪያዎች ወይም ከውጭ በመጠነኛ ዋጋ በሚገኙ “መሣሪያዎች” እና “ኬሚካሎች” እንዲስተናገዱ ሊደረግ ይገባል፡፡ ለዚህም ሂደት በየፈርጁ የምሁራን ቡድኖች መቋቋም አለባቸው፡፡ይህም ሲተገበር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መ/ቤቶች ጋር በመተባበር መሆን ይገባዋል፡፡

ማህበረሰብ አገልግሎት፡-አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማማከርም ሆነ በማህበራዊ አገልገሎት በተደራጀ መልክ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡ ለአገልግሎት ከሚከፈለው ገንዘብ በጣም ውስን የሆነ ቀንሶ፣ ቀሪውን ለታሳታፊዎች ምሁራን የግል ገቢ ሊያደርግ ይችላል፡፡በተጨማሪ የላቦራቶሪ አገልግሎትም አንዲሁ (ውሃ፣ አፈር፣ ወዘተ ምርመራ፣ የካርታ ሥራ፣ወዘተ) ሰነዶች ዝግጅት እና መሰል አገልግሎቶችንም ሊያበረክት ይችላል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ምርምር በአገር ደረጃ ሲፈተሸ

በተቻለ መጠን የዩነቨርሲቲ ተግባሮችን አሳታፊ ማደረግ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች አላፊዎች ይጠበቃባል፡፡ የዩንቨርስቲው ጉዳይ፣ ጉዳዬ ነው የሚለውን እይታ ለኣባላቱ ማጎናፀፍ ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ግብዓት ነው፡፡ ይህንን ግንዛቤ አንግቦ፣ እያንዳንዱ አባል (አገልግሎት ሰጭ፣ ተማሪ እና አስተማሪ) ተሳታፊነቱ ከአገር ልማት ጋር ያለውን ትሥሥር በቅርብ እየፈተሸ፣ የልማት ቅንጅትን ማጠናከር አለበት፡፡

በአገር ደረጃ የዩኒቨርሲቲዎች ስምሬት፡-በዚህ በያዝነው ዓመት አምሳ በላይ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ እነኝህ ዩኒቨርሲቲዎች በትውልድ መሰል ይዘት ተመድበው የመጀመሪያ ትውልድ፣ ሁለተኛ ትውልድ፣ ሦስተኛ ትውልድ እና አራተኛ ትውልድ በመባል ይተወቃሉ፡፡ምንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጀመሪያ ትውልድ ጋር ቢመደብም፣ በእኔ እይታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የብቻውን የወላጅነት መደብን ይዞ፣ ከዚያም አንደኛ ትውልድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የበኩር ልጆች ሆነው፣ ከዚያም አሁን በሚታወቀው አመዳዳብ ቢታቀፉ፣ትክክለኛ የታሪክ አንፀባራቂ አመዳደብ ይሆናል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉንም ዓይነት ትምህርት፣ ማስተናገድ ይገባቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲ የኔ የሚለው፣ እንደ “አርማ” የሚያገለግለው፣ “የትኩረት መስክ” ያስፈልገዋል፣ “የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒሰቴርም” ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠቱን ሰምቻለሁ፣ ያም መልካም የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡በተለይ ወደፊት ዩኒቨርሲቲዎች የግሌ የሚሉት “አርማ” አንግበው እንዲመሠረቱ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ተግባር ከእቅድ ጀምሮ ከታሰበበት ውጤታማ ይሆናል የሚል እይታ አለኝ፡፡ በተለይ የሳይንስ ዕውቀት ተግባራዊ የሚሆንባቸው፣ ለምሳሌ “የውሃ ልማት”፣ “ግብርና”፣ የኢንዱስትሪ (ቴክኖሎጂ የትምህርት ዓይነቶች) የመሰሉትን አርሞቻቸው አድረገው ዩኒቨርሲቲዎች አወቃቀሮቻቸውን ቢቃኙ ይጠቅማል ብዬ እገምታለሁ፡፡

እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ የሚተዳደርበት “ቻርተር” እንደሚያስፈገው ይታመናል፡፡ለዚህ ጉዳይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቂ ዝግጅት እንደደረገ ሰምቻለሁ። ስለሆነም ጉዳዩ ባጭር ጊዜ ውሰጥ ሊተገበር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡

የአአ ዩኒቨርሲቲ ምርምር በአገር ደረጃ ሲፈተሸ፡- በዩኒቨርሲቲ ትምህረት ዘረፍ ብዙ ልምድ አካባተናል፣ በምርመር ተግባር ግን ያለን መዋቅራዊ አቅም ውስን ነው፡፡የአገራችንን የምርምር ሂደቶች የሚመራ፣ ለምርምር ተጠሪ የሆነ፣ አንድ “ብሄራዊ ተቋም” እንደሚያሰፍልግ አሙን ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉንም ዓይነት ምርምር የሚያስተናግድ፣ “ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቢሮ” ተጠሪ የሆነ፣ አንድ “የብሄራዊ የምርምር ካውንስል” መቋቋም አለበት የሚል እይታ አለኝ፡፡ የምርምር ይዘት የተወራረሰ ስለሆነ፣ በተለያዩ ተቋማት መስተናገድ የለበትም ብዬ አምናለሁ፣ ለምሳሌ “የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር” እና “የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር”፣ ሁለት የተለያዩ የምርምር ካውንስሎች ማቋቋም አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ይህ ዓይነት አወቃቀር የምርምርን ሂደት በጣም ውስብስብ ያደርገዋል፡፡

ሁሉንም ዓይነት ምርምር የሚያስተናግድ አንድ ወጥ ተቋም መመሥረት፣ ማለት “የብሄራዊ የምርምር ካውንስል” አማራጭ የለውም፡፡ ከዚየም ተቋም አካል የሆኑ፣ “ዘርፍ-ተኮር” ንዑስ የምርምር “ካውንስሎችን” መመሥረት ይቻላል፡፡ እነኝህ ተቋማት ተግባራቸውን በጥሞና ተገንዝበው፣ አቅማቸውን ገምግመው፣ ቅደም ተከተል እቅዶችን አውጥተው፣ መሬት ረግጠው፣ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡

“ዘርፍ ተኮር” ንዑስ የምርምር “ካውንስሎችን” በየዘርፎቻቸው የምርምር ፕሮጅክቶችን አቅጣጫ መተለም ይኖርባቸዋል፡፡ አንዱ መንገድ የልማት ዘርፎችን ቅደም ተከተል በማውጣት እና በልማት ሂደት የተደነቀሩ ችግሮችን መፍትሄ ግብዓት የሚሆን መረጃ እንዲያመነጩ መመሪያ ማውጣት ይሆናል፡፡ ይኸም መመሪያ “የምርምር ፕሮጅክቶችን ፅንሰ ሃሳብ” (Concept Notes) ማካተት ይኖርበታል፡፡ ለተመረጡ የልማት አቅጣጫዎች ምርምር የሚያስፈልግ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ግብዓቶች አቅም በተገቢ መንገድ መገንባት ይገባል፡፡

ተመራማሪዎች በቡድን በቡድን ተደራጅተው መሆን አለበት ምርምር የሚያካሂዱት፡፡ በየቡድኖቹ የታቀፉ ወጣት ተመራማሪዎች በየቡድኖቻቸው ካሉ በሳል ተመራማሪዎች የምርምር አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጠራል፡፡ ስለሆነም በሂደት ወጣት ተመራማሪዎች ዕውቀት ክህሎትም፣ ያካብታሉ፡፡

በመንግሥት ዩኒቨርሲቶዎች የሚከናውን “የምረቃ ማሟያ ምርምሮች” ለዚህ መመሪያ ተገዢ መሆን አለባቸው የሚል እመነት አለኝ፡፡ ከነኝህ የመመረቂያ የምርምር ውጤቶች፣ ለልማት እንዲሁም መጻሕፍትን ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ መረጃዎችን በብዛት ማበረከት ይችላሉ፡፡ የምርምሮችም ውጤት የሆኑ መረጃዎች በአንድ ቋት መከማቸት ይኖርባቸዋል፤ ያም ድግግሞሽን ለመግታት ያስችላል፡፡

ቀደም ሲል እንደተወሳው፣ ይህ አደረጃጀት ስለ ተመራማሪው ነፃነት (በፈለገው ምርምር ላይ መሠማራት) መገታት እንደ ችግር ሊወሳ ይችላል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ምርምር ሊተገበርባቸው ብሎም የችግር መፍትሄ ግብዓት የሚሆን መረጃዎችን ሊያበረክቱ የሚችሉ የምርምር ርዕሶች በጣም ብዙ ስለሆኑ፤ ብዛታቸው የተመራማሪውን ምርጫ ያሰፋዋል። ስለሆነም ጉዳዩ እንደ ችግር መወሳት የለበትም የሚል እይታ አለኝ፡፡ ካለው የፕሮጀክት ፅነሰ ሃሳብ ቋት፣ የሚፈልገውን ርዕስ ለመምረጥ ያስችላል፡፡ ስለሆነም አደረጃጀቱ የተመራማሪውዎችን ነፃነት አይጋፋም፡፡

የየዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮ ከመደበኛ ትምህርት ባለፈ፡- “ሳይንሳዊ አስተሳሰብን” ማጎልበትና ለቀን ተቀን ተግባር ጠቀሜታ አለው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ በመሰረቱ “ሳይንሳዊ አስተሳሰብ” ምክንያታዊ ነው፡፡ በአገራችን ካሉት አንዱ ግዙፍ ችግር የማህበረሰቡን አስተሳሳብ “ምክንያታዊ” እንዲሆን የሚረዱ ተግባራትን ማስተናገድ ኣለመቻላችን ነው፡፡

“ሳይንሳዊ አስተሳሰብን” በአገር ቤት ቋንቋዎች ለማንሸራሸር ብዙ ጥረት ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ ብዙ ግለሰቦች የተሳተፉባቸው፣ ብዙ እና የተለያዩ ሙከራዎች ተገምግመው የሚወጣው ስልቶች ተነድፈው ተግባር ላይ ቢውሉ ሳይንሳዊ አስተሳሰባችን አየዳበረ፣ እየጠነከረ፣ ይሄዳል፡፡ ከታለመው ግብ የመድረስ ጉዞ ከአንድ ትውልድ በላይ ሊፈጅ ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ ግን፣ ሂደቱ የግድ አሁን መጀመር አለበት፡፡
እንዲሁም ሳይንሳዊ ዕውቀትን በአገር ቤት ቋንቋዎች ማዳረስ ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ በዓለማችን ላይ የተከማቸ እውቀትን፣ ግንዛቤን ለማካፈል፣ በተለይ ዕድል ገጥሟቸው ያንን ዓይነት ግንዛቤ በውጭ ቋንቋ ከተዘጋጁ መጽሐፍት ለመቅሰም የበቁ ግለሰቦች፣ የእነርሱን ዓይነት ዕድል ላላገኙ ወገኖች ማካፈል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

መደምደሚያ

እውቀት ለሰው ልጅ የደስታ፣ የእርካታ ምንጭ መሆን ይገባዋል፡፡ በእውቀት እና ክህሎት ላይ ተመስርቶ የምግብ ፍጆታ፣ የጤና አገልግሎት፣ መጠለያ፣ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ አካባቢ ውስጥ መኖር መቻል አለበት፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የመደማመጥ እና የመቻቻል ባህል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ መዳበር አለበት፤ የማህበረሰቡ አንዱ እና ዋናው የችግር መንስዔ ይኸ ተግራደሮት ይመስለኛል፡፡

በመጨረሻ ንግግሬን ከመቋጨቴ በፊት የሁላችን አደራ የሆነ ጉዳይ ላውሳ፡፡ ትውልድ ተስፋ እንዳይቆርጥ ሁላችንም በየፈረጁ መረባረብ አለብን ብዬ አምናለሁ፣ በተለይ ያንን ለመተግበር አቅም ያላቸው ባለስልጣናት እና ምሁራን ለዚህ ጉዳይ ለአገራቸው ብሎም ለራሳቸው ሲሉ ትኩረት መስጥት ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ጉዳይ አንፃር፣ ወጣቱን ትውልድ ባሳተፈ፣ የመሬት ለአራሹን አዋጅ ለማስታወስ በተደረገ “ኮንፈረንስ” ለተሰነዘረ የወጣቱ ትውልድ ጥያቄ ያቀረብኩት “የተስፋ አደራ” መልስ አነሆ፡-

የቅብብሎሽ ሩጫ

ከአባቶቻችን እጅ፣ ትንታግ ተቀብለን፣
በርስ በርስ ሽኩቻ፣ እሳቱን አዳፍነን፣
ጨለማ ውስጥ ነን፣
አትበሉ!
እጁን የዘረጋው፣ ይኸ አዲሱ ትውልድ፣ ዘላለሙን ቢመኝ፣
ከከሰለ ችቦ፣ ምን ብርሃን ሊያገኝ?
አትበሉ!
መልካሙን ነው ማየት፣
ውቡን ነው መመኘት፣
ብርሃን ይከሰታል፣ ከተዳፈነ እሳት፡፡

አበቃሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top