ጥበብ በታሪክ ገፅ

አፍታ ጨዋታ ከአየለ ማሞ ሥራዎች ጋር

ናፍቆቷ ነው ያስቸገረኝ
ሌት በህልሜ እየመጣ፣ እየታየችኝ
ቁም ነገሯን ሳስብ በልቤ መርምሬ፣
የረሳኋት ወጣት ትዝ አለችኝ ዛሬ፡፡
ትቻት እሷም ረስታኝ ተራርቀን ሳለ፣
ዛሬ ትዝታዋ ድንገት ከቸች አለ፡፡
መቼም የጥላሁን ገሠሠ ዘፈኖች ነፍስን እንደ ህፃን የመኮርኮር፣ ህይወትን እንደ ማር የማጣፈጥ፣ ትዝታን እንደ መስታወት የማስቃኘት ምትሀትን የተቸራቸው ናቸው፡፡ አንዱን ካንዱ ለማበላለጥ፣ ይህኛውን ከዛኛው ለማወዳደር እስክንቸገር ድረስ፡፡ ይህን የጥላሁንን አቅም የሚረዱ፣ የሰጡትን ግጥምና ዜማ ከሚጠብቁት በላይ ነፍስ ዘርቶበት እንደሚጫወተው የሚገነዘቡት ደራሲያንም በእውነት የተፈተነ የልብ ስራቸውን፣ የፍቅር ታሪካቸውን፣ ትዝታቸውን፣ የህይወት ከፍታና ዝቅታቸውን፣ የሀገር ፍቅራቸውን ወዘተ በሱ ድምጽ በኩል ማስተላለፉን ቀዳሚ ምርጫቸው ያደርጉታል፡፡
አየለ ማሞ ይህን ግጥም የፃፈው ለባለቤቱ ነበር- ለልጆቹ እናት፡፡ ባለቤቱ ካረፈች በኋላ ናፍቆቷ እንቅልፍ ቢነሳው፣ ትዝታዋ ቢያሳሳው፣ ልጆቹን እየተመለከተ ይህንን ከተበ፡፡ ምትሀተኛው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ደግሞ እንደ ብዙዎቹ ተናፋቂ ዘፈኖቹ ሁሉ ድንቅ አድርጎ ተጫወተው፡፡ ይኸው ዛሬ ዘፈኑ ከባለታሪኩ አልፎ የብዙዎች መቆዘሚያ ሆኗል፡፡ ባለ ቅኔው ጸጋዬ ገብረ መድህን በአንድ ቃለ መጠይቁ “ጸሐፊ በህዝብ መሀል ሆኖ ነው ስለ ህዝብ የሚጽፈው” እንዳለው፤ የአየለ ማሞ ስራዎች በአብዛኛው በእውነተኛ አጋጣሚዎች ላይ የተመረኮዙ ናቸው፡፡ አንድም በራሱ፣ አንድም በሌሎች ገጠመኞች ላይ ተመስርቶ ግጥም ይጽፋል፣ ዜማ ይደርሳል፡፡ ከሁሉ በፊት ግን አየለና ሙዚቃ፣ አየለና ማንዶሊን ከወዴት ተወዳጁ…

የቀ.ኃ.ሥ ሽልማት

አየለ የተወለደው በ1930ዎቹ መጀመርያ ሰላሌ አካባቢ ሲሆን፤ አዲስ አበባን የረገጠውም ገና በልጅነቱ ነበር፡፡ በጊዜው የዲቁና ትምህርት ስለነበረው በተክለሐይማኖት ደብረ አሚን ቤተ ክርስቲያን ይቀድስም ነበር፡፡ በዚህ አኳኋን፤ አየለ ማሞ የቤተ ክህነት አገልግሎቱን እየከወነ ሳለ፤ ከእለታት አንድ ማለዳ እንዲህ ሆነ፡፡ ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተክለሐይማኖት ቤተክርስቲያን ለማስቀደስ ከሹማምንቱ ጋር ይገኛሉ፡፡ በቅዳሴው መሀል ታዲያ ግርማዊነታቸው በአንድ ወጣት ቅዳሴ እጅግ ይማረካሉ፡፡ በልጁ ድምጽ ሁናቴ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አጃቢዎቻቸውም አብረው ይደመማሉ፡፡ ንጉሱ ይህንን ልጅ ዝም ብለው ሊያልፉት አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም በቅዳሴው መጨረሻም ማራኪውን ልጅ ያስጠሩትና ይሸልሙታል፡፡ ሽልማቱ ሃያ ብርና መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፡፡ ተሸላሚው ደግሞ ብላቴናው አየለ ማሞ፡፡
ንጉሰ ነገስቱን ካጀቡት ሹማምንት መካከል የክብር ዘበኛው ሙዚቃና ትያትር ክፍል ኃላፊ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ አንዱ ነበሩ፡፡ ሻምበል አፈወርቅ ልክ እንደ ንጉሱ ሁሉ በልጁ ድምጽ ተገርመው ነበር፡፡ ሆኖም እንደ ንጉሱ እጃቸውን ለሽልማት አልዘረጉም፡፡ ይልቁንም የዘላለም የህይወት መስመሩን አመላክተውት ተመለሱ እንጂ፡፡ እንዲህ ሲሉ- “ነገ ወደ ጃንሜዳ ብቅ በል፡፡”
ጃን ሜዳ የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡ የሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ቢሮም እዚያው ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስም እጅግ የተወደዱ ድርሰቶን ለጥላሁን ገሠሠና ለሌሎችም ይሰጡ የነበሩ፤ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ናቸው፡፡ ትንሹ አየለ እንደተባለው ወደ ጃንሜዳ አቀና፡፡ ሻምበል አፈወርቅን በቢሯቸው አገኛቸው፡፡ በደስታ ተቀብለው ፈተኑት፡፡ “የኔ ውብ ዐይናማ፣ ነይማ ነይማ” የምትል ህዝባዊ ዘፈን አዘፈኑት፡፡ አለፈም፡፡
እንሆ ከዛች ዕለት ጀምሮ፤ አየለ ማሞ በተወዛዋዥነትና በሙዚቀኝነት ክብር ዘበኛ ኦርኬስትራን በ23 ብር ደሞዝ ተቀላቀለ፡፡ ዘመኑም 1949 ዓ.ም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ አየለና ክብር ዘበኛ አልተለያዩም፡፡ ጊዜ ደርሶ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ እስኪበተን ድረስ አብሮ ከ30 ዓመታት በላይ ቆየ፡፡

አየለና ማንዶሊን

አየለ ማሞ ሲባል፤ ብዙዎች ማንዶሊኑን ያስታውሳሉ፡፡ ከዘፋኝነቱ፣ ከግጥምና ዜማ ደራሲነቱ በላይ ይህቺ መሳሪያ ብዙ አሳውቃዋለች፡፡ በርግጥም ከዚች ድንቅ የሙዚቃ መሳሪያ ጋር እሱም ጥብቅ ቁርኝት ነበረው፡፡ ይሁንና ብዙዎች እንደሚሉት አየለ የመጀመርያው የማንዶሊን ተጨዋች ግን አይደለም፡፡ ቀዳሚው መምህሩ ነው-ግርማይ ሀድጉ፡፡ እሱ ራሱ በተለያዩ ቃለ-መጠይቆች ላይ እንደመሰከረው የማንዶሊን መምህሩ ግርማይ ሀድጉ ነው፡፡ ግርማይ ሀድጉ የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ምሰሶ የነበረ ሰው ነው፤ በተለይ በዜማ ደራሲነት፡፡ ጥለሁን ገሠሠ ገና ወደ ህዝብ ልብ ዘልቆ ከመግባቱ በፊት፤ በዛ በልጅነቱ ዘመን የማይነቃነቅ የመሰረት ድንጋይ ያኖረለት ሰው ነው ግርማይ-ከህዝብ ልብ የማይሸሹ ጣፋጭ ዜማዎችን በመስጠት፡፡
ግርማይ ሀድጉ ማንደሊንን ጨምሮ አኮርዲዮን፣ ፒያኖና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን የመጫወት ድንቅ ብቃትም ነበረው፡፡ ታላቁ የክብር ዘበኛ ሰው ሁለት ሙያዎችን ለመጪዎቹ አውርሷል፤ ማንዶሊንና የዜማ ደራሲነትን፡፡ አየለ ማሞ እንደ ግርማይ ሀድጉ መሆንን፣ እንደ ግርማይ ሀድጉ መጫወትን አጥብቆ ተመኝቷል፡፡ በመጨረሻም የልቡ ደርሶ የማንዶሊን ጌታ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ለአየለ ማሞ የማንዶሊን ተጨዋችነት የክብር ዘበኛው ሰው ግርማይ ሀድጉ አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ብኋላ ወደ ክራሩ አመዘነ እንጂ ተዘራ ኃይለሚካኤልም ማንዶሊንን ይጫወት ነበር፡፡ ልክ እንደ አየለ ማሞ ሁሉ ባንድ ነገር ግን እሱም የግርማይ ሀድጉን ሙያ ይጋራል-የዜማ ደራሲነትን፡፡
ድምጻዊ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ
በ1949 ዓ.ም የክብር ዘበኛን ሙዚቃ ክፍል ከተቀላቀለ ጀምሮ አየለ ወደ ሌላ ሙያ አላማተረም፡፡ እዚያው የሙያ አድማሱን እያሰፋ ከሙዚቃ ጋር የሙጢኝ ማለትን መረጠ እንጂ፡፡ በግጥምና በዜማ ደራሲነት የታላላቆቹን ድምጻውያን ስራዎች አሳምሯል፡፡ ራሱም በድምጻዊነት ከማንዶሊኑ ጋር በፍቅር ተደምጧል፡፡ የድርሰት በረከቱ ካረፈባቸው ድምጻውያንና ስራዎቹ መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፤ ጥላሁን ገሠሠ-ጥርሰ ፍንጭቷ፣ የቀይ ዳማ፣ ጠይም ናት፣ ስንገበገብላት፣ ሁሉም በሀገር ነው ወዘተ፡፡ ለመሐሙድ አህመድ-መላ ትስጠኝ፣ ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል(ዜማ)፣ ዐይንሽ ያባብላል፣ እኔና አንቺ፣ ዓለምዬ… እንዲሁም ለብዙነሽ በቀለ ምን በደልኩት ምነው፣ ከንቱ ስጋ(ዜማ) እና የመሳሰሉት ሲጠቀሱ፤ ከክብር ዘበኛ ውጭና ለዚህ ዘመን ቀረብ ካሉ ድምፃውያን መካከል ደግሞ ሐመልማል አባተ፣ ህብስት ጥሩነህና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
አስቀድመን እንዳነሳነው፤ የአየለ ማሞ ድርሰቶች በተግባር የተፈተኑ፤ በእውነት የተደገፉ፣ የህይወት ነጸብራቆች ናቸው፡፡ ደራሲ ከሚያየውና ከሚሰማው ተነስቶ ይጽፋል እንደተባለው፤ አየለም እንደዚሁ ነው፡፡ በህይወት አጋጣሚ የሰበሰባቸውን ልምዶች ወደ ግጥምና ዜማ ይቀይራቸዋል፡፡ አንዲት ቅጽበትን ወደ ድርሰት ለውጦ ዘላለማዊ የማድረግ ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው፡፡ ለዚህ አገላለጼ የጥላሁን ገሠሠ “የቀይ ዳማ” የተሰኘችዋ ተወዳጅ ዘፈን የተሰራችበትን አጋጣሚ በእማኝነት አቀርባለሁ፡፡
ቦታው በጥላሁን ገሠሠ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ አየለ ማሞ ከማንዶሊኑ ጋር ጥላሁንን ዜማ ያስጠናዋል፡፡ የተመረጠችዋ ዜማ ደግሞ…
ጠይም ናት፣ ጠይም መልከ ቀና በውበት ያደገች፣
በፍቅሯ ልቤን እንክት አርጋ የበላች እሷው ነች፡፡
የምትል ነበረች፡፡ ይህንን ሁሉ ጓዳ ሆና ትከታተል የነበረችው የጥላሁን ገሠሠ ባለቤት ታዲያ ይሄኔ ብቅ ትልና ለአየለ ማሞ ያልተጠበቀ ጥያቄ ትሰነዝራለች፡፡ እንዲህ ስትል…
“አቶ አየለ”
“አቤት” ይላል አየለ፡፡
“ጠያይሞቹንስ አወደሳችሁ እኛስ?”
“በሂደት ይደርሳል” የአየለ መልስ፡፡
አየለ ማሞ የጥያቄው መልዕክት ልቡ ገብቷል፤ ከንክኖታል፡፡ እውነትም ለቀያዮች የሚሆን አልተዘፈነምና-ተብከነከነ፡፡ የዛን እለት ሌሊት ሳይተኛ አደረ፡፡ ሌሊቱን ከብዕርና ከማንዶሊኑ ጋር ሲሟገት አገባዶ ማለዳ ቃሉን በተግባር ይዞ ተገኘ፡፡ አዎ! “የቀይ ዳማ” የተሰኘችዋ ዘፈን ተጸንሳ ተወለደች፡፡ የጥላሁን ባለቤትም ዘፈኑን ሰምታ “አሁን ተግባባን” ብላ የልቧ መድረሱን አበሰረች፡፡ እንሆ በዝች አጋጣሚ የተዘራችው ዜማ ከባለቤቶቹ አልፋ ለትውልድ ጆሮ ተረፈች፡፡ ከቀይ ዳማ ስንኞች ጥቂት ሰበዞች…
ሰማሽ ወይ አንቺ የቀይ ዳማ፣
በፍቅር አደራ እንስማማ፣
ያላንቺ ማን አለ ለህይወቴ፣
እመኚኝ ፍቅሬ ሰውነቴ፡፡
አየለ ማሞ ለሌሎች የሰራውን ያህል ራሱም በድምጻዊነት ብዙ ሰርቷል፡፡ በተለይ “እማማ ድምቡሎ”፣ “ወይ ካሊፕሶ” የሚሉት ቀዳሚ ሰራዎቹ ብዙ ከተደመጡ፣ ከተወደዱ ዘፈኖቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ “ወይ ካሊፕሶ” የሚለው ዘፈን ግጥምና ዜማው የሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ሲሆን፤ መሰረቱን ከወደ ምዕራብ አፍሪካ ያደረገ የአፍሮ ካሪቢያን የሙዚቃ ስልት እንደሆነ ይነገራል፡፡
በነገራችን ላይ አየለ ማሞ የተዋጣለት ዳንሰኛም ጭምር ነበር፡፡ ክብር ዘበኛን ሲቀላቀል በዳንሰኝነት ሙያም ስለነበር፤ አያሌ የዳንስ ጥበቦችን ተምሯል፡፡ ቫልስ፣ ማሪንጌ፣ ታንጎ፣ ማምቦ፣ ሳምባ፣ ትዊስት፣ ሮክ ኤንድ ሮል ወዘተርፈ የዳንስ ዓይነቶችን ያቀላጥፋል፡፡ ለዚህ ሙያው መዳበር የክብር ዘበኞቹ የነ ገላን ተሰማና ዘውገ ገብረመድህን አስቷጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
የክብር ዘበኛና አየለ ማሞ ከተለያዩ በኋላ፤ አየለ አሁንም ከሙዚቃው ዓለም አልተለየም፡፡ የክስታኔ ባንድን ተቀላቅሎ ከአስር ዓመት በላይ አገልግሏል፡፡ እድሜ ሳይገድበው፣ እርጅና ሳይበግረው ካዲሰቹ ወጣቶች ጋር በትጋት መስራትንና ሌሎችን ማስተማርን መርጦ ቀጥሏል፡፡ በክስታኔ ባንድ ውስጥ ከነ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አብነት አጎናፍር፣ ፀጋዬ ስሜ እና ከሌሎች ወጣቶች ጋር ሙዚቃን ሲያገለግል ኖሯል፡፡ እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስም በተለያየ መልኩ ከሙዚቃው ዓለም ሳይለይ የኖረ ሰው ነው-አየለ ማሞ፡፡
ለልጆቹ፣ ለወዳጆቹና ለሙዚቃ አፍቃሪያን ሁሉ መጽናናትን ተመኘሁ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top