ታዛ ስፖርት

ሶሻሊዝም በመረብ ኳስ

ጥያቄው ግልጽ ባይሆንም እየቀረበ ነው፡፡ ዋንጫውን ለመውሰድ እየተዘጋጀ የነበረው ቡድን ግፊት እየደረገበት ነው፡፡ የመጣው ጥያቄ ስርአቱን ከፍ ለማድረግ ቢሆንም ለመቀበል አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሰውየው ከፍተኛ ባለስልጣን ሲሆኑ ለዘብ ባለ ሁኔታ ግን ቀጭን ትዕዛዝ ባለበት ስሜት ለመጠየቅ ነው የመጡት፡፡ ባለስልጣኑ የቡናው ሰው እየተናገሩ ነው‹‹በወንዶች ዋንጫ አገኛችሁ አይደል?››
‹‹አዎ››
‹‹እንኳን ደስ አላችሁ!!!››
‹‹እንኳን አብሮ ደስ አለን››
‹‹በጣም ነው ያኮራችሁን እኮ››
‹‹እኛም ደስ ብሎናል››
‹‹አንዱ ይበቃችኋል አይደል?!!!››
‹‹ምኑ››
‹‹ዋንጫው››
‹‹የሴቶቹንም ለመወሰድ ተዘጋጅተናል››
‹‹እሱን ብተተውትስ?››
‹‹ምን ማለት ነው?››
‹‹ለሌላ ብታካፍሉ››
‹‹ለማን?››
‹‹ለእርሻ ሰብል››
የባለስልጣኑ ንግግር ለቡናው አለቃ ቀልድ ነበር የመሰለው፡፡እንዲህ አይነት ጥያቄ ቀርቦለትም አያውቅም፡፡ ደግሞም ከባለስልጣኑ እንዲህ አይነቱን ነገር አልጠበቀም፡፡ ባለስልጠኑ ለስፖርቱ ሩቅ ሆነው እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ይዘው እንደመጡ ገርሟቸዋል፡፡ደግሞም እኮ ቁርጥ ፍርጥ ያለ መልስ አሁኑኑ ይፈልጋሉ፡፡ ሁኔታው ለቡናው ሰው አስቸጋሪ ነበር፡፡ እምቢም እሺም የማይባልበት ሁኔታ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፦
የዘንድሮ የአዲስ አበባ ሻምፒዮና ጥሩ ፉክክር የታየበት ነው፡፡ የመረብ ኳስ ስፖርት አፍቃሪው በጨዋታዎች የሚታየውን ትንቅንቅ ለመመልከት የውድድሩን ስፍራ አጣቦት ይታያል፡፡ በመጨረሻዎቹ ፉክክር ቡና የበላይነቱን ይዞ በመውጣቱ ይገባዋል፤ ብዙ ለፍቷል፣ ታልቅ ችሎታውንም አሳይቷል በማለት የመሰከሩበት ግዜ ነበር፡፡ የሀገር ውስጥ ውድደር በዚህ ታላቅ ፉክክር አልቆ በምስራቅ አፍሪካም ዋንጫ የተሰየመው ጨዋታ ድንቅ ነበር፡፡ የዚህ አመት የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና የተዘጋጀው አዲስ አበባ ነበር፡፡ የሀገር ኩራት የሆነውና የስፖርት ቤተሰቡንም ኢትዮጵያ በሚወክል ውድደር እምነት የጣለበት ቡና በሁለቱም ጾታ ለፍጻሜ በመቅረቡ ‹‹ይገባዋል›› ከማለቱ ባሻጋር ዋንጫውንም እንደሚወስድ ሙሉ እምነት ነበረው፡፡ ከዚህ በፊት በኢንተርናሽናል ደረጃ ማንኛውም የኢትዮጵያ ክለብ ዋንጫ ማግኘት ቀርቶ በፍጻሜ የታየም አልነበረም ፡፡ ቡና ግን ለዚህ ብቁ በመሆኑ ሁሉም ሰው በእርግጠኝነት ነበር ወደ ሜዳ የመጣው ፡፡
የወንዶቹ ቡድን ዋንጫውን በመውሰዱ ሁሉም ኢትዮጵዊ ጮቤ እየረገጠ ነው፡፡ ‹‹ይቀራል ገና!!!›› በሚል ሴቶቹን እየጠበቀ ነው፡፡ የአጋጣሚ ሆኖ ቡና ለዋንጫ የቀረበው ከሀገሩ ቡድን ከእርሻ ሰብል ጋር ነበር፡፡ ቡና ይሄንንም ዋንጫ ለመውሰድ አቅም እንዳለው የስፖርት ቤተሰቡ ያምናል፡፡ እዚህ ከመድረሳቸው በፊት በሀገር ውስጥ ውድድር ቡና ደጋግሞ አሸንፏል፡፡ ቡና ለዚሁ የምስራቅ አፍሪቃ ሻምፒዮና ያለፈው በአዲስ አበባ ሻምፒዮና እርሻን በፍጻሜው አሸንፎ ዋንጫውን በመውሰድ ነው፡፡ አሁንም በኢንተርናሽናል ውድድር ለዋንጫ ሁለቱም ተገናኝተዋል፡፡ ቡና የወንዶቹን አሳምኖ አሸንፎ እንደወሰደ በሴቶቹም ዋንጫው የእርሱ እንደሚሆን ተጋጣሚውም ጭምር እንደሚጠብቅ ነው፡፡
ፍጻሜ ለመድረስ ቡና ያሳየው ብቃት እጅግ የሚደነቅ በመሆኑ ዋንጫውን እንደሚወስድ ሁሉም አምኗል ፡፡ ነገር ግን ቡና ለዋንጫው ተዘጋጅቶ እየጠበቀ ሳለ የፍጻሜው ጨዋታ የሚካሄድበት እለት ተላለፈ፡፡ በእለቱ ውድድር እንዳይካሄድ የሚያደናቅፍ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ከአየር ሁኔታው እስከጸጥታ ድረስ ምንም ችግር አልነበረም፡፡ ተጋጣሚዎች ያቀረቡት ይተላለፍልን ጥያቄ አልነበረም፡፡ ደግሞም ተመልካቹ የእረፍት ቀን በመሆኑ ጨዋታውን ለማየት ፕሮግራም የያዘበት ቀን ነው፡፡ ጨዋታው በመራዘሙ ሁሉም ግራ ተጋባ፡፡ ጠርጣራዎቹ የቡና አመራሮች ግራ እንደተጋቡ ዝም አላሉም፡፡ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴዎቹን ቢሯቸው ድረስ አስጠሩና ‹‹ይሄ የፍጻሜ ጨዋታ ለምን ተላለፈ?›› ብለው ጥያቄ አቀረቡ።
‹‹አናውቅም››
‹‹እንዴት አታውቁም?››
‹‹ምንም ያገኘነው መረጃ የለም››
‹‹እኔ ግን አልተመቸኝም››
‹‹ምኑ?››
‹‹መራዘሙ››
‹‹ምን ችግር ያመጣል?››
‹‹እንዴት ችግር የለውም››
‹‹ተጋጣሚያችን የታወቀ ነው፤ ደጋግመን አሸንፈነዋል››
‹‹ቢሆንም››
‹‹ቢሆንም ምን…?››
‹‹እኔ ጥሩ ስሜት አልሰጠኝም››
‹‹ስጋት ሊገባንም አይገባም››
‹‹መስጋት አለብን እንዳውም በጣም እንስጋ››
‹‹ለምን?››
‹‹የቡና ማንሰራራት የማይመቻቸው ሰዎች የደገሱልን ነገር ሳይኖር አይቀርም››
‹‹ምን?››
‹‹አላውቅም››
‹‹እና ምን ይደረግ››
‹‹መሰለል አላባችሁ››
‹‹እንዴት››
‹‹በየቦታው መራዘሙን በተመለከተ ሰልሉ››
ኮሚቴዎቹ ግራ ተጋቡ። መራዘሙ ለእነርሱ ስሜት በሳይሰጣቸውም አሁን ስራ አስኪያጁ የተናገሩትና የጠረጠሩትን ጉዳይ መበርበርና መሰለል፤ ወሬ በየትኛውም መንገድ ማነፍነፍና ጥቂት ስባሪ የምትሆንም መረጃ ሰንደው አበጥረውና መመርመረው ማቅረብ እንዳለባቸው አውቀዋል፡፡ ኮሚቱዎቹ የድርጅቱ ሰራተኛ ናቸው፡፡ ብዙ የስራ ሀላፊነት አለባቸው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ሲታዘዙ ቦታውን በሌሎች ሰዎች እንዲሸፈን አድርገው መሄድ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ስራ አለብን ብለው ለሌላ ግዜ የሚሉት ጉዳይ አይኖርም፡፡ ይሄ የታዘዙት ጉዳይ ከባድ ነገር እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ እንደ ሰንሰሰለት በመያያዝ እንደ ቡድን ሆነው መስራት በመቻላቸው ነው ቡድኑ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ የቻለው፡፡ እናም ያሁኑ ጉዳይ አንገብጋቢም ይሁን ትንሽ ከቢሮ ወጥተው በየቦታው መሰለልና ማጣራት ጀመሩ፡፡ አንድ አውራ የሚባል መረጃ ተገኘ፡፡ የመረጃው ሰው ወደ ስራ አስኪያጁ ቢሮ አመራ፡፡ ስራ አስኪያጁ ‹‹የተገኘ ነገር አለ?›› አሉ፤
‹‹አዎ››
‹‹ምንድነው?››
‹‹የሆነ ነገር አለ››
‹‹ንገረኛ››
‹‹እርሻ ሰብል ዋንጫው ሊሰጠው ነው››
‹‹ለምን?››
‹‹ቡና የወንዶቹ ይበቃዋል ብለዋል››
‹‹ማነው የወሰነው?››
‹‹አዲስ አበባ እንደሆነ የተጨበጠ መረጃ ተገኝቷል››
‹‹ኢንተርናሽናል ውድድር ሆኖ አዲስ አበባ እዚህ ውስጥ ለምን ገባ?››
‹‹አወዳዳሪው አካል ማወዳደር ሲሆን አዲስ አበባ ደግሞ የእኛ አለቃ ነው››
‹‹እና››
‹‹ሁለታችንም የአዲስ አበባ ክለቦች ስለሆንን ዋንጫውን መካፈል አላባቸው ነው የተባለው››
‹‹የመጨረሻው ውሳኔ የማነው››
‹‹የአዲስ አበባ ነው››
‹‹ይካፈሉ ነው ያሉት››
‹‹አዎ››
ስራ አስኪያጁ ተበሳጩ። መጀመሪያም የሆነ ደባ እንዳለ ስሜታቸው ሳይነግራቸው አልቀረም፡፡ አሁን ግን ህግ ተጥሶ ነገሮች እያፈጠጡ መምጣታቸው ታወቀ፡፡ ቡና ከሌሎች የሀገራችን ክለቦች የተለየ በጀት የለውም፡፡ እንደማንኛውም ክለብ እኩል በጀት ነው ያለው፡፡ የያዛቸውን ተጫዋቾች በሚገባ አሰልጥኖ ሀላፊነት እንዲሸከሙና ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ነው ከሌሎች የተለየው ፡፡ ነገር ግን በራሱ ብቃት እዚህ ደርሶ አለአግባብ ዋንጫ ሊነጥቁት ሲመጡ በዝምታ መመልከት አልቻለም፡፡ እናም ስራ አስኪያጁ ደባ ተሸረበበት ወደተባለው አዲስ አበባ ስፖርት አስተዳደር እየበረሩ ሄዱ፡፡ወደቢሮ ገቡና ሀላፊው ማነጋገር ጀመሩ ‹‹እንዴት ነው›› አሉ
‹‹ሰላም ነው››
‹‹ጨዋታው ለምን ተራዘመ?››
‹‹ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው››
‹‹ለምን?››
‹‹መዝጊያውን ባማረ ሁኔታ እንዲያልቅ ስለተፈለገ ነው››
‹‹በወንዶቹ ውድድር ለምን አልተዘጋጀም?››
‹‹አሁን ነው ሀሳቡ የመጣልን››
‹‹እኛ ግን ደስተኞች አይደለንም››
‹‹ለምን?››
‹‹ሌላ ነገር እየሰማን ነው››
‹‹ምን አይነት ነገር?››
‹‹ዋንጫውን ልትነጥቁን ነው››
‹‹እኛ? ››
‹‹አዎ››
‹‹እንዴት?››
‹‹ለእርሻ ሰብል ልትሰጡ ነው››
‹‹አልገባኝም››
‹‹ይካፈሉ ብላችኋል››
‹‹መካፈል ማለት››
‹‹እኛ የወንዶቹን ስለወሰድን የሴቶቹን ለእርሻ ልትሰጡ ነው››
‹‹ይካፈሉ የሚል ደብዳቤ ደርሷችኋል?››
‹‹እንዲህ አይነቱ ነገር እኮ በደብዳቤ አይገለጽም፤ በሚስጥር ነው››
‹‹እኛ ይሄን አናውቅም››
የቡናው ሰውዬና የስፖርት ሀላፊው ብዙ ተከራከሩ፡፡ ከዚያም አልፎ ጠንከር ያለ ንግግር ተለዋወጡ፡፡ አንድ ችግር እንዳለ የገባው የቡናው ሰው በተለያያ መንገድ ማጣራት ሲያደርግ አንድ ሚስጥረኛ ሰው አገኙ፡፡ ይህ ሰው እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ በኮሚቴነት የሚሰራ ነበር፡፡ ከቡናው ስራ አስኪያጅ ጋር መነጋገር ጀመረ፡፡ የቡናው ሰው ‹‹የሆነ የተደበቀን ነገር አለ አይደል?››አለው
‹‹እንደዛ አትውሰደው››
‹‹ምን ማለት ነው?››
‹‹ላንተ ሚስጥሩን ልንገርህ››
‹‹ምንድነው?››
‹‹ዋንጫው ለእርሻ ተወስኗል››
‹‹ሳንጫወት?››
‹‹አዎ››
‹‹እንዴት?››
‹‹የበላይ ውሳኔ ነው››
‹‹የበላይ ማለት?››
‹‹የፖለቲካ ሰዎች››
‹‹ምክንያቱ?››
‹‹የሶሻሊስት የስፖርት መርህን በመከተል ብዙሃኑን ማእከል ለማድረግ በሚል ነው››
‹‹እና››
‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ውጤታማ ክለቦች አሏት እንዲባል ተፈልጓል››
‹‹አልገባኝም?››
‹‹ሁለቱንም አንተ ከወሰድክ ከመርሁ ያፈነገጠ ነው››
‹‹በሶሻሊስት ስፖርት መርህ አሳበው ሊቀሙን ነዋ!!!!!››
‹‹አንተ መስማማት ነው ያለብህ››
‹‹እኔ በፍጹም አልስማማም››
‹‹እንድትስማማ ይደረጋል››
‹‹እንዴት?››
‹‹ብዙ መንገዶች አሉ››
‹‹መቼም ሳንጫወት ዋንጫውን አይሰጧቸውም አይደል?››
‹‹ጨዋታው ይካሄዳል፡፡ የተራዘመውም ለዚህ ነው››
‹‹እንዴት ማለት?››
‹‹የተራዘመው እናንተን እንድትስማሙ እስኪያሳምኑዋችሁ ድረስ ነው››
‹‹ዋንጫውን ለመስጠት አንስማማም፡፡ ዋናው ነገር ጨዋታው መካሄዱ ነው››
‹‹ጨዋታው አይቀርም››
‹‹ከተጫወትን አያሸንፉንም›››
‹‹እንደዛ አትበል››
‹‹ፍትህ የለም ማለት ነው?››
‹‹ይሄም እኮ ፍትሀዊ አሰራር ነው››
ሰውየው ሚስጥር ሊነግረው ብቻ ሳይሆን ለማደራደርና ለማሳመን የመጣ ነው፡፡ በውሳኔው እሺ ብሎ እንዲቀበል ለማድረግም ጭምር የተላከ ነገር ነው፡፡ ከዚሁ ሚስጥረኛ ሰውዬ በኋላ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ባለስልጣኖች አንዱ የቡናው ስራ አስኪያጅ ጋር ስልክ ደወሉ፡፡ሰላምታ ከተለዋዋወጡ በኋላ ባለስልጣኑ ‹‹አንዱ ይበቃችኋል አይደል?›› አሉ።
‹‹ውድደር እኮ ነው››
‹‹እባክህ ተባበረን››
‹‹ብዙ ሰው ጨዋታውን እየጠበቀ ነው››
‹‹ምን ችግር አለው ለእነርሱ ብትሰጡ እኛም ጋር ያሉት የፖለቲካ ሰዎች ይሄኑን እየጠበቁነው››
‹‹ማለት ?››
‹‹የሴቶቹን ዋንጫ ለእነርሱ እንድትሰጡ››
‹‹ተጨዋቾቻችን ማሳመን ከባድ ነው››
‹‹እንዴት?
‹‹ሌላ ግዜ ስፖርተኞቻችን ለሀገር ለመጫወት ይቸገራሉ፡ የቀረጽናቸው በመላቀቅ ሳይሆን በእውነተኛ ተወዳዳሪነት ስለሆነ ብዙ ጉዳት አለው››
‹‹አንድ መፍትሄ ፈልግለታ?››
‹‹መፍትሄው ተጫውተን ያሸነፈ ቢወስድ ጥሩ ነው፡፡ እነርሱም እኮ ሊያሸንፉ ይችላሉ››
‹‹የተነግረኝ እንዲህ አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር በእናንተ እጅ ነው››
‹‹በዋናነት የሚያስቸግረን ጉዳይ አለ››
‹‹ምንድነው››
‹‹ይሄን ነገር የስፖርት ቤተሰቡ ከሰማ ለመንግስትም ጥሩ አይደለም‹‹
‹‹በሚስጥር እንዲሆን ይደረጋል››
የቡናው ሰው ብዙ ነገር በማቅረብ ባለስልጣኑን ማሳመን ቢሞክር ባለመቻሉ ተጫዋቾቹን ልቀቁ ማለት የሚሞከር እንዳልሆ ያውቀዋል፡፡ ይሄ ከተደረገ ቡድኑ ከውጤት ይርቃል። ሌላ ግዜ ሀይለኛነቱን ማግኘት አይችልም ፡፡ ስለዚህ ሳይማማ ቀረ፡፡ ግን የተዘጋጀለትን ነገር አላወቀም፡፡ በባለስልጣኖች ደረጃ የታገዘ በዳኝነት መፍትሄ እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በየት መንገድ ይመጡብኛል ብሎ ሲጠብቅ አልቢትሮች በተለያየ መንገድ ነጥብ እያስጣሉ ዋንጫውን ከቡና እጅ አመለጠ ፡፡ የስፖርት ቤተሰቡ ግን ጉዳዩን ባያውቀውቅም ዳኝነቱን ኮንኖ ወጣ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top