ታዛ ዐለማት

ጣና ሃይቅ፡ አንጡራ ሃብታችን

መግቢያ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በ”እምቦጭ” በመወረሩ መንስዔ፣ ስለ ጣና ሃይቅ ብዙ እየተወሳ ነው። በዚህ አጋጣሚ ጣናን ተንተርሶ ሳይንስን ማኸዘብ ይቻል ይሆናል በሚል እሳቤ ነው ይህችን ጽሑፍ ለማዘጋጀት የወሰንኩት። [በዚህች ጸሑፍ ዘመን ሲጠቀስ ዓ.ም (ዓመተ ምህርት) የሚል ካለታከለበት፣ “የግሪጎሪያን” የዘመን አቆጣጠር ነው። ይሄም የተደረገው መረጃዎች በብዛት “የግሪጎሪያንን” ዘመን ስለሚያጣቅሱ ነው።]

ስለጣና ለመጀመሪያ ጊዜ በጣም ውስን ግንዛቤ ያገኘሁት በልጅነት ዘመኔ (በ12 ዓመቴ) ባህርዳር ይኖር ከነበረ አንድ የዕደሜ አኩያዬ ዘመዴ ነበር። ፈለገ ብርሃን ከተማ አብረን ስንኖር፣ ዘመዴ (አንሙት ብርሃኔ) ስለ ጣና በጣም ሰፊነት ሲያወጋን፣ እኛ ጓደኞቹ እምነት እንነሳው ነበር። ከዘመናት በኋላ እንደተረዳሁት፣ እውነትም የጣና ሃይቅ በጣም ሰፊ ነው። (ስለ ርብ እና መገጭ ተፋሰሶች ጥናት ላይ በተሳተፍኩበት ወቅት፣ ስለ ጣና ሃይቅ እና ስለ አካባቢው ብዙ መረጃ ሰብስቤያለሁ)። ጣና ሃይቅ በአማካይ ርዝመቱ 84 ኪሎ ሜትር፣ ወርዱ 66 ኪሎ ሜትር፣ ጠቅለል ብሎ ሲታይ ስፋቱ (area) 3,675 ኪሎ ሜትር ካሬ እንደሆነ “በኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ” ቢገለጥም፣ በብዛት የሚጠቀሰው ስፋት አማካይ በ 3,500ኪሎ ሜትር ካሬ ነው። በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሃይቆች በሙሉ በስፋት ከጣና የሚስተካከል የለም። የጣና ውሃ ሙቀት በአማካይ ከፍተኛው 29.00C ሲሆን ዝቅተኛው 10.00C ነው።

የጣና ሃይቅ በጥንት ግሪካዉያን ይታወቅ እንደነበረ መዛግብት ያመለክታሉ፣ የሚጠቀሱትም በ”ፒሲቦአ” (Pseboa) ወይም “ኮሎዌ” (Keloe) በሚል ስያሜ ነበር። ሆኖም “ኬሎዌ” በሚል ስያሜ የሚታወቅ አንድ ሃይቅ ኤርትራ ውስጥ እንዳለ በቅርብ ጊዜ ሰምቻለሁ።

በኢትዮጵያ ካሉ “ጨው-አልባ” የውሃ ቋቶች፣ ሰላሳ ስድስት በመቶውን (36%) የያዘው የጣና ሃይቅ ነው። የጣና ሃይቅ ተፋሰስ ከሰሜን እና ከምስራቅ የአርማጭሆ እና የጉናን ተራራ ሰንሰለቶች፣ ከደቡብ ምሥራቅ የጮቄ ተራራን ሰንሰለት (ከሰላን) ያካትታል። የጣና ጎረቤቶች የሆኑ ብዙ ትናንሽ ሃይቆች አሉ፣ ለምሳሌ ዛንገና፣ ቲርባ፣ ጉደራ፣ ታች ባህር፣ ላይ ባህር። በዓመት ከጣና የሚፈሰው የውሃ መጠን ይዋዥቃል፣ ሲሞላ (ነሐሴ/ መስከረም) ወደ ሰባት ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ሲል፣ በደረቅ ወቅት ወደ አንድ ቢሊዮን ሜትር ኩብ ዝቅ ይላል፣ በአማካይ መጠኑ 3.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነው።

በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ሃይቆች የሚገኙት በስምጥ ሸለቆ ውሰጥ ሲሆን፣ እነሱም ቱርካና፣ ጨው ባህር፣ ጫሞ፣ አባያ፣ ሃዋሳ-ሻሎ፣ ሻላ፣ ጭቱ፣ አቢጃታ፣ ላንገኖ፣ ዝዋይ፣ የቢሾፍቱ ሃይቆች፣ በሰቃ፣ አፋመቦ-አቤ ስብስብ፣ አፍዴራ፣ አሳሌ፣ ገደቤሳ፣ አሸንጌ፣ አርዲቦ፣ ተናን፣ ወንጭ፣ ደንዲ፣ የባሌ ተራራ ሃይቆች፣ እና ሃሮማያ-አደሌ እና ፍንቅሌ ናቸው።

ሃይቆች በዓለማችን ያለው “ጨው-አልባ ውሃ” ብቸኛ ቋቶች ናቸው። ወንዞች ጨው-አልባ ውሃ ወስደው ከባህር ውስጥ ነው የሚዶሉት፣ ጥቂቶች በርሃ ገብተው ይተናሉ/ይሰምጣሉ። ለመጠጥም ሆነ ለምግብ ማብሰያ፣ ለመፀዳጃ እና ለግብርና የሚያገለግል ጨው-አልባ ውሃ ነው።

የሃይቆች ጠቀሜታ

ጠቅለል ብለው ሲታዩ፣ ሃይቆች አንደ ውሃ ጋን (ማጠራቀሚያ) ሆነው ያገለግላሉ። በክረምት ወራት (ዝናብ ሲያይል)፣ አካባቢውን ከጎርፍ ታድገው፣ የጎርፍ ማገቻ፣ ብሎም የውሃ ማጠራቀሚያ ይሆናሉ። ከዚያም የዝናብ ወቅት ሲከትም፣ ያቆቱትን ውሃ እየቆጠቡ፣ በወንዝ፣ በጅረት መልክ ለአካባቢው ያበረክታሉ። ለምሳሌ “ገደቤሳ” (አፋር ገዋኔ አጠገብ ያለው “ሰፌድ-መሰል”- ክብ ሃይቅ)፣ በዝናብ ወቅቱ ግማዘንጉ (ዲያሜትር/ diameter) ወደ አምስት ኪሎ ሜትር ከፍ ይላል፣ በበጋ ወቅት ወደ አንድ ኪሎ ሜትር ይሰበሰባል (ዝቅ ይላል)። ስለሆነም በክረመት የአዋሽን ወንዝ ጎርፍ አግዶ/አግቶ ከርሞ፣ በበጋ ቀስ በቀስ ውሃ ለአዋሽ ይመግባል።

በተጨማሪ ሃይቆች የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትን ያጎለብታሉ። የብዝሃ ሕይወት ማዕከሎችም ናቸው። እንዲሁም ለመዝናናትም ሆነ፣ ለስፖርት እንቅስቃሴዎች፣ ለጀልባ ትራንስፖረትም ምቹ አካባቢን ያበረክታሉ።

ሃይቆች የአካባቢውን የአየር ሁኔታ (ቅዝቃዜ/ሙቀት) ይቆጣጠራሉ። በተፈጥሮ፣ ውሃ ብዙ ሙቀት የማመቅ ባህርይ አለው፡ ስለሆነም ቀን ከፀሐይ ኃይል ያገኘውን “ሙቀት” አምቆ ይይዛል (ውሃ ለመትነን 1000C ሙቀት ያሸዋል)። ቀን ቀን በፀሐይ ኃይል በሃይቁ አካባቢ ያለው የብስ ይሞቃል ። የብስ ከውሃ ጋር ሲነፃፀር በቀላሉ የመሞቅ፣ እንዲሁም ፀሐይ ስትጠልቅ ቀን ያከማቸውን ሙቀት በቀላሉ የማጣት ባህርይ አለው። ውሃ በተቃራኒው፣የሙቀት ማከማቸትም ሆኖ ያመቀውን ሙቀት ለማጣት ያለው ባህርይ ቀስ በቀስ ነው የሚከናወነው (ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልገዋል)።

ቀን ቀን፣ በየበስ ላይ ያለውን ግለት ተጋርቶ፣ አካባቢውን ያቀዘቅዛል። ሌሊት፣ ሌሊት፣ ሃይቁ ያመቀውን ሙቀት፣ በሃይቁ ገፅታ (ሰሌዳ)፣ በሚከንፍ አየር አቀባባይነት ለየብስ በማጋራት፣ በየብስ ላይ ያለውን የመቀዝቀዝ ሁኔታ ይገታል፣ ኗሪዎችን ከቆፈን ይታደጋል። ይህም ተግባር የሚስተናገደው ቀን፣ ከየብስ ወደ ሃይቅ፣ ሌሊት፣ ከሃይቅ ወደ የብስ በሚንሸራሸረው አየር (ነፋስ) ነው። ስለሆነም የአካባቢ የውሃ አካል፣ ሃይቅን ጨምሮ፣ የአካባቢውን ያየር ሁኔታ ይቆጣጠራል። የሃይቅ አካባቢ ነፋሻ ነው የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው።

ባህርዳር ከተማ በሃይቁ ዳርቻ የተገነቡ ፎቆች (ለምሳሌ የአማራ ክልል ልማት ቢሮ)፣ የሃይቁን የአየር ሁኔታ (ሙቀት/ቅዝቃዜ) የመቆጣጠር ባህርይ ይገታሉ። በሃይቁ ዙሪያ የሚካሄድ ግንባታ ከሃይቁ በተወሰነ ርቀት መሆን ይገባዋል፤ ያም ሲደረግ የነፋስ እንቅስቃሴን ሁኔታ ግንዛቤ ባካተተ መንገድ መሆን ይገባዋል።

የሃይቆች ነባራዊነት ጉዳይ

በመሠረቱ ሃይቆች ዘላለማዊ አይደሉም፣ ባህሪዎቻቸው ይቀያየራሉ፣ በሂደትም ከገፀ-ምድር ይጠፋሉ (ይወድማሉ/ይሞታሉ)። ሂደቱም እንደ የሰው ልጅ ሕይወት ሊመሰል ይችላል፤ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ አሮጌ ሆነው በመጨረሻ ለሞት ይዳረጋሉ። ሃይቆች ለመውደም (ለመሞት) ዘመናት ይወስድባቸዋል፣ በሺዎች፣ አንዳንዴም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዘመን። ሆኖም በሰው ልጅ ተፅእኖ ዕድሜያቸው በጣም ሊያጥር፣ ባጭር ሊቀጭ ይችላል።

የሃይቆች ህላዌ ጉዞ እነሆ። ሃይቆች የህያው አካላት ባለሃብቶች ናቸው፣ በሃይቆች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ጥቃቅን እና ግዙፍ የዕፀዋት እና እንስሳት ዝርያዎች አሉ። በሃይቁ ውስጥ ህልውናቸውን የመሠረቱ እነኝህ ህያው አካላት ሲሞቱ፣ ቅሬቶቻቸው ሃይቁ ወለል ላይ ነው የሚከማቸው፣ የሚጠራቀመው።

እንዲሁም ሃይቁን መጋቢ የሆኑ፣ ወንዞች፣ ጅረቶች፣ ብዙ ኮተት ተሸክመው አምጥተው ነው ከውሃ ጋር ሃይቁ ውስጥ የሚዶሉት። ከጎረፍ ጋር ተደባልቆ ወደ ሃይቅ በቀጥታ የሚገባው ቆሻሻ የትየሌሌ ነው። ስለሆነም የሃይቁ ወለል ከውስጥ በሞቱት የህያው ቅሬቶች፣ ከውጭ በጎረፍ እና በወንዞች አጋዥነት ወደ ሃይቁ የሚገባው ቆሻሻ እየጨመረ ሲሄድ፣ የሃይቁ የወሃ ይዘት በጣም እየቀነሰ ይሄዳል (ውሃ ባለበት ብርጭቆ ውስጥ አሸዋ ቢጨመር፣ውሃው ወደ ላይ እየተገፋ በመጨረሻም ውሃው ከብርጭቆው ወጥቶ ይፈሳል፣ ብሎም የብርጭቆው ውሃ መጠን ይቀንሳል)።

በጎርፍም ሆነ በወንዝ አጋዥነት ወደ ሃይቁ የሚገባው ውሃ ተሸክመው የሚያመጡት ደረቅ ቆሻሻ ጥርቅም እንደ መጠናቻው ቅደም ተከተል ሃይቁ ዳርቻ ወለል ላይ ላይ ያርፋሉ፣ ትላልቆች በመጀመሪያ ሃይቁ ዳርቻ ጥግ፣ በጣም ጥቃቅኖች ደግሞ በመጨረሻ፣ ከሃይቁ ዳርቻ ራቅ በለው ሃይቁ ወለል ላይ ይጠራቀማሉ። በሂደት የሃይቁ ዳርቻ በትላልቅ ኮረቶች የተገነባ ወደ የብሰነት እየተቀየረ ይሄዳል። ማለት ቀስ በቀስ ጥልቀቱ እየተቀነሰ፣ ስፋቱ እየጠበበ፣ የውሃ ቋትነቱ እየመነመነ ይሄዳል፣ ያም ሃይቁ አረጀ ማለት ነው። በሂደት ውሃው ከነባር ዳር እየሸሸ መኻል ወደ ነበረው አካባቢ ይዘልቃል። ብሎም አካባቢው ወደ ረግረግነት ይቀይራል፣ ከዚያም ይደርቃል። ጥልቅ የነበሩ አካባቢዎች ለተወሰነ ጊዜ ውሃ አቁተው ይቀጥላሉ፣ በሂደት እነሱም ደርቀው ወደ የብስነት ሲቀየሩ፣ ሃይቁ፣ ከሰመ፣ ሞተ ማለት ነው።

የጣና ሃይቅ ታሪክ

ጣና ለተመሠረተበት ጊዜ ሳይንሳዊ ግምት ሲሰጥ፣ አንዳንድ ምሁራን በዘመነ “ፕላዮስቶሲን” (Pleistocene) ሲሉ፣ ያም ከአመስት ሚሊዮን ዓመታት በፊት ማለት ሲሆን፣ ሌሎች ምሁራን ዘመኑን በጣም ቀነስ አድረገው፣ ጣና የተመሠረተው ከሁለት ሚሊዮን ዓመት በፊት እንደነበረ ዘግበዋል። በጽሑፎች በብዛት የሚጠቀሰው ሁለተኛው (ሁለት ሚሊዮን ዓመት) ነው።

ከሁለት ሚሊዮን ዓመታት በፊት በአካባቢው በተከሰተ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ ከከርሰ ምድር በተወረወረ ነበልባል የድናጋይ ጎርፍ “ገሞራትፍ” (lava)፣ ቀዝቅዞ ወደ አለትንት ተቀይሮ፣ በአካቢው የነበረ ወንዝን (አባይ) መፋሰሻ አካባቢ በ50 ኪሎ ሜትር ርዝመት ገድቦ፣ ጣና ሃይቅ ለመመሥረት በቃ ይላሉ። በአካባቢው የነበረ የተንጣለለ ሜዳ ለሰፊ ሃይቅ ምሥረታ ሁኔታውን አመቻቸው ይባላል። አባይ ከጣና ወጥቶ በሚፈስበት አካባቢ፣ አሁንም ትላልቅ ቋጥኝ የድንጋይ ክምሮች ይስተዋላሉ።

ሆኖም ጣና ባህርዩን ሳያዛባ አስከዘመናችን አልዘለቀም። ሃይቁ በዝናብ እጠረት ምክንያት ለስድስተ መቶ ዓመታት (ከ15,700 እስከ 15,100 ዓመት በፊት) ደርቆ እንደነበረ በቂ ሳይንሳዊ መረጃ ተገኝቷል። የዚያን ዘመን የዝናብ መጠን ከዘመናችን ዝናብ መጠን ጋር ሲነፃፀር፣ አርባ በመቶ (40%) እንደነበረ ይገመታል። ይህ ሁኔታ ለምዕተ ዓማታት ዘልቆ ለሃይቁ መድረቅ መንስዔ ሆኖ ነበር። ሃይቁ በደረቀበት ወቅት፣ የወንዙ (አባይ) ፍሰት ሙሉ በሙሉ ተግትቶ (ተቋርጦ) እንደነበረም ይገመታል።

ከ14,750 ዓመት በፊት ገደማ የዝናቡ መጠን ስለጨመረ፣ የአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ሁሉ ከድርቅ እንደተላቀቁ አመልካች የሆኑ መረጃዎች ተገኝተዋል። ከዚያም ከዘመናት በኋላ፣ የዝናቡ መጠን እየጨመረ ሲሄድ፣ ውሃ ባቆረባቸው አካባቢዎች፣ “ደንገል” እና መሳይ የሳር ዝርያዎች ማንሰራራት ጀመሩ። የዝናቡ መጠን እየጨመረ፣ አካባቢው ውሃ ይዘት እየሰፋ ሲሄድ፣ “ደንገል” እና ሌሎች የሳር ዝርያውች በውሃ ተዋጡ፣ ብሎም በስብሰው፣ የሃይቁ ወለል አካል ሆኑ። እነኝህን ዓይነት ቅሬቶች ናቸው ስለ ሃይቁ ታሪክ መረጃ የሚያበረክቱት። ሰማይ ዝናብ በሰፊው መለገስ ሲጀምር፣ ወንዞች ጅረቶች፣ ፍሰታው መልሶ አንሰራራ፣ ብሎም ጣና ሃይቅም ሞላ፣ አባይም መደንፋት ጀመረ ይባላል።

እንዲሁም እንደገና ከ4,200 ዓመት በፊት የአካባቢው የዝናብ መጠን የአባይ ፍሰት በጣም ዝቅ ብሎ ነበር። ይሀም ሁኔታ በዘመኑ ገናና የነበረውን የምሥር (ግብፅ) ሥልጣን ለመንኮታኮት ዳረገው ይባላል። የጣና ጥልቀት አሁንም ውስን ነው። ዋናው ምክንያት የተገደበ በተንጣለለ ሜዳ አካባቢ መሆኑ ነው። በጣም ጥልቅ የሆነው የጣና ወለል 14 ሜትር ጥልቀት ሲኖረው፣ በአማካይ የሃይቁ ጥልቀት ዘጠኝ ሜትር ገደማ ነው። ሆኖም ጥልቀቱ በክረምት ከፍ፣ በበጋ ዝቅ ይላል። ከላይ አነደተጠቀሰው፣ የጣና ስፋት በአማካይ 3,500 ኪሎ ካሬ ሜትር እንደሆነ ይገመታል (ስፋቱም እንደ ጥልቀቱ ሁሉ ይዋዥቃል፣ በክረምት ሰፋ፣ በበጋ ጠበብ ይላል)። ከጣና ሃይቅ ወጥቶ የሚፈሰው ውሃ (አባይ) መጠን፣ ወንዙ ሱዳን ጠረፍ በሚደርስበት ጊዜ ካለው የውሃ ይዘት (መጠን) ጋር ሲነፃጸር ስምንት በመቶ (8%) ብቻ ነው፣ ዘጠና ሁለት በመቶ (92%) ከገባሮቹ የሚያጠራቅመውን ውሃ ይዞ ነው አባይ ወደ ሱዳን የሚገባው።

ጣና ያለውን ቁመና የመሠረተው በገባር ወንዞቹ ላይ ነው፣ ምክንያቱም ጣና ራሱ ላይ ከሚዘንበው የዝናብ መጠን፣ ከሃይቁ ገፅታ ላይ የሚተነው ውሃ ይልቃል፣ ገባር ከሌለው ደረቅ ሜዳ ነው የሚሆነው። ምንምወደ ሃይቁ የሚገቡ ጅረቶች እና ወንዞች ቁጥር ወደ ስድሳ ቢሆንም፣ መጠኑ ዘጠና ሦስት በመቶ (93%) የሚሆነውን ውሃ የሚገብሩት አራት ወንዞች ብቻ ናቸው፣ እነሱም ግልገል አባይ (ከጎጃም)፣ ርብ፣ ጉመራ እና መገጭ (ከጎነደር) ናቸው። በብዛት አፈር ተሸክሞ ወደ ሃይቁ የሚገባው ግልገል አባይ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ርብ ወንዝ ይፈረጃል።

በጅረቶች እና ወንዞች ለጣና የሚገበረው ውሃ መጠን በአማካይ በዓመት፣ በአሜሪካ ቁጥር ስሌት 4.986 ቢሊዮን ሲሆን፣ በእንግሊዞች ስሌት 4,986 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ነው። በብዛት የሚጠቀስ የአሜሪካ ቁጥር ስሌት ስለሆነ በዚያ ስሌት እጠቀማለሁ። የሚወጣው ውሃ መጠን በአማካይ 3.753 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነው። የሃይቁን አማካይ ጥልቀት፣ እንዲሁም አማካይ ስፋት ወስደን የውሃ ይዘቱን (መጠኑን) ስናሰላ (3,500 x1000 x 1000×9= 31.5) ሠላሳ አነድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትር ኩብ (31.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ) ውሃ ይሆናል።

ጣና እና የጣና ዙሪያ ከባህል እና ከታሪክ አንፃር

የጣና ሃይቅ ብቸኛ መመኪያ የሆናቸው ማህበረሰቦች በጣና ሃይቅ ዙሪያ ሰፍረው ለዘመናት ኖረዋል። ከሃይቁ የሚገኝ የምግብ ፍጆታ (አሳ፣ ጉማሬ)፣ “የወይጦ” ማህበረሰቦች የህልውና መሠረት ነበር። የወይጦ ማህበረሰቦች “ታንኳ” (ከደንገል የተዘጋጀ ጀልባ) ገንብተው፣ ከአካባቢው እፅዋት ጭረት መረብ ሸርበው፣ አሳ ለዘመናት አጥምደዋል፣ አሁንም እያጠመዱ ይገኛሉ።

አባይ ከጣና ሃይቅ ወጥቶ በሚፈስበት ደቡብ አቅጣጫ፣ ቀደም “በባህር ጊርጊስ” ስያሜ የተመሠረተች መንደር፣ የዘመናችን ውቢቷ ባህርዳር ትገኛለች። ያንን አካባቢ 18ኛው ምዕተ ዓመት “ጀምስ ብሩስ” (James Bruce) በጎበኘበት ዘመን፣ ከላይ የተጠቀሰችውን መንደር አውስቷል። በ19ኛው ምዕተ ዓመት አካባቢውን የጎበኘ አንድ ፈረንሳዊ፣ አካባቢውን “የሞት ቀጠና” (Deadly Zone) ብሎ ሰንዶታል። ያም “ከንዳድ” (ወባ) አንፃር የአካባውን ሁኔታ አጢኖ ነበር። አካባቢው የሞት ቀጠና ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል። “ሳሙዔል ሄይስ” (Samuel Hayes) የሚባል ሌላ አካባቢውን የጎበኘ (በ1905) ግለሰብ፣ ባህርዳርን በ”ፓፒረስ” (በደንገል/ Cyperus papyrus) የተከበበች ረገረግ መንደር ብሎ ነበር የገለጣት።

በጣሊያን ወረራ ዘመን (በ1938)፣ ወራሪዎች ጣና አካባቢ አንድ ጣቢያ መሥረተው ነበር። ጣቢያውም የፖስታ ቤት የቴሌገራፍ ቢሮ፣ እንዲሁም የጤና አገልግሎት ማዕከል ነበረው። ለትናንሽ አይሮፕላኖችም ማረፊያነት የሚያገለግል፣ የተስተካካለ ጥርጊያ ሜዳ አዘጋጅቶ ነበር። በዚያን ጊዜ የተመሠረተው ጥርጊያ ሜዳ (ከተማው መኻል) አስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለተመሳሳይ ተግባር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይጠቀምበት ነበር። ወራሪዎች በሃይቁ በተለያዩ አካባቢዎች (ለምሳሌ ባህርዳር፣ ጎርጎራ) ወደብ ገንበተው ነበር። የተገነቡት ወደቦች እሰከዘመናችን ድረስ አገልገሎት አበርክተዋል፣ አሁንም እያበረከቱ ይገኛሉ። በጎርጎራ ምዕራብ አቅጣጫ ባለ ኮረብታ ላይ፣ ወራሪዎች፣ ወረራውን አመልካች የሆነ ሃውልት ገንብተዋል፣ ሀውልቱ አሁን አለ። ያም ሆኖ አስከ 1940 ዓም አካባቢ ድረስ በጣና አካባቢ ብዙ ሰፋሪ አልነበረም። ዋናው ምክንያት ወባ(ንዳድ) ከፍተኛ ስጋት ስለነበረ ነው።

የባህርዳር አካባቢ ወባ ሥጋት በጣም ስላሳሰባቸው፣ ወራሪዎች መፍትሄ ፈልገውለት ነበር። መፍትሄውም የወባ ትንኝ እጭ የምትበላ የአሳ ዝርያ ወደ ሃይቁ ማስገባት ነበር። በ1938 (1930ዓም) ወራሪዎች ጣና ሃይቅ ሁለት ብቸኛ የአሳ ዝርያዎች አስገብተው ነበር። አንደኛው የቢምቢ “እጭ-በል”፣ “ጋምቡሲያ” (Gambusia holobrooki) የሚባል ሲሆን፣ ሁለተኛው ዝርያ፣ “ፓይክ” (Pike/ Esox lucius) ነበር። ሁለተኛው ዝርያ፣ “ፓይክ”፣ ወደ ሃይቁ የተጨመረበት ምክንያት፣ ይህ “አሳ-በል” የሆነው የአሳ ዝርያ፣ “ፓይክ”፣ ተመራጭ አሳ ፍጆታን እንዲየበረክት ነበር። ለዚሁ ተግባር ወደ ሃይቁ 250ሺ የ”ፓይክ” ግልገሎች እና አንድ ሺ የ”ጋምቡሲያ” ግልገሎች ተጨምረው ነበር። ይህም ጣምራ ጥቅምን ያበረከታል ብሎ በማሰብ ነበር፣ ማለት ምርጥ አሳ እና የወባ ትንኝ መቆጣጠርን፣ ብሎም የወባ በሽታን መግታት።

ወደ ሃይቁ የተጨመሩት ሁለቱም “መጤ የአሳ ዝርያውች” (exotic species) በመጀመሪያ ወራት አካባቢው የተሰምማቸው ይመስል ነበር፣ ሆኖም ከጊዜ በኋላ ሁለቱም ዝርያዎች ደብዛቸው ጠፋ። ምንም ከሃይቁ በየጊዜው አሳ ቢጠመድም (ቢያዝም) የነኝህ አሳ ዝርያዎች ተጠምዶ (ተይዞ) አያውቅም። ዝርያዎቹ የጠፉበት ምክንያት ባይታወቅም፣ ዋናው ምክንያት አዲሱ አካባቢ ለነኝህ ለአውሮፓ የአሳ ዝርያዎች፣ ለመራባት አመች ሳይሆን ስለቀረ ነው ብሎ መገመት ይቻላል።

ጣና በምሥራቅ እና በሰሜን በኩል በሰፋፊ ለጥ ባሉ ሜዳዎች የተከበበ ሲሆን፣ በክረምት፣ እነኝህ ሰፋፊ ሜዳዎች (በሰሜን ደምብያ፣ በምሥራቅ ፎገራ) በውሃ ይጥለቀለቃሉ፣ በበጋ ምቹ የከብት መዘጫዎች ናቸው። የታወቀው የወተት ከብት ዘር፣ “የፎገራ ዘር” በሚባል ሚታወቀው የሚገኝበት አካባቢ ነው።

ከከብት ርቢ በተጨማሪ፣ አካባቢው ጠቀም ያለ የሰብል ምርት ያበረክታል። ከቅርብ ዘመን ወዲህ፣ የግብርና ማሳው እየሰፋ፣ የከብት መዘጫው እየቀነሰ መጥቷል። በግብርና መስፋፍት መንስዔ ሸርሸር፣ ወለላ፣ ደጋ ታኩዋ ረግርግ አካባቢዎች በመመናመን ላይ ይገኛሉ። አንዲያም ሆኖ፣ አሁንም የአውሮፓን ክረምት ሸሽተው ለሚመጡ አዕዋፍ እንደ መዘጫነት፣ መጠለያነት፣ ያገለግላሉ።

በጣና ዙሪያ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ሽምብራ፣ ምሥር፣ ሽንኩርት እንዲሁም ቃሪያ ይመረታል። በርብ ወንዝ ተፋሰስ በመስኖ መጠቀምም ከተለመደ ሰንብቷል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የርብም፣ የመገጭም ተፋሰሶች ለመስኖ ተግባር ውለዋል። በተለይ በክረምት በውሃ ተሸፍኖ የከረመው አካባቢ በበጋው መባቻ ውሃው ወደ መሀል ሲሸሽ፣ መሬቱ ለእርሻ ተግባር (recession agriculture) ይውላል። የአካባቢው ገበሬዎች የተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ስለሚጠቀሙ፣ ይህም ሁኔታ ሃይቁን ለኬሚካል ብክለት ዳርጎታል።

የአካባቢው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው። በ20ኛው ክፍል ዘመን መቋጭ፣ በየኪሎ ሜትር ካሬው ከ150 ሰዎች ያላነሱ ሰፍረውበት ነበር። የህይወት አለኝቶቻቸውም የተቀናጀ እርሻ እና ከብት ሪቢ ናቸው። ሊቦ ከምክም እና ፎገራ ወረዳዎች ለዘመናት ለከብት መዘጫ ሆነው አገልግለዋል (“የቦረና ሰንጋ” እንደሚባል ሁሉ ከላይ እንደተጠቀሰው “የፎገራ የወተት ከብት” የሚባል ስያሜ አለ)።

በጣና ሃይቅ ብዙ ሰው የሰፈረባቸው እና “ሰፋሪ-አልባ” የሆኑ ጥቃቅን ደሴቶች ይገኛሉ። በሃይቁ የውሃ መጠን መቀነስ ወይም መጨመር መንስዔ ይመስላል፣ በተለያዩ ጊዜያት የተመዘገቡት ደሴቶች ቁጥር ይለያያል። በ17ኛው ምዕተ ዓመት አካባቢውን የጎበኘው “ማኑዔል ዲ አልሜዳ” (Manoel de Almeida)፣ በሃይቁ ውስጥ ሃያ አንድ ደሴቶች እንዳሉ ገልጦ፣ ከነኝህም ሰባቱ ወይም ስምንቱ ገዳማት እንደነበሩባቸው ያስረዳል። “ጀምስ ብሩስ” (James Bruce) በ18ኛው ምዕተ ዓመት ሠላሳ ሰባት (37) ደሴቶች እንደነበሩ ያወሳል (ይህ የዘመናችንም ትክክለኛ ቁጥር ነው)፣ ከነሱም ውስጥ አሥራ ዘጠኙ (19) ገዳማት የተመሠረቱባቸው እንደነበሩ መዝግቧል። በዘመናችን ሃያ (20) ደሴቶች ገዳሞች እንዳሉባቸው ይታወቃል።

ገዳማቱ መመሥረት የጀመሩት በ13ኛው ክፍለ ዘመን ነበር። እንኝህም ገዳማት ለዘመናት ለኢትዮጵያ ቅርሶች፣ በተለይም ለመጻሕፍት ከአጥፊዎች መሰወሪያ ሆነው አገልግለዋል። በተጨማሪ የጥንት ነገሥታት አፅሞች ማከማቻዎች የነበሩ ናቸው። ከነዚህ ገዳማት ውስጥ ጎላ ጎላ ያለ ታሪክ ያላቸው፤ “ብርጊዳ ማርያም”፣ “ደጋ እስጢፋኖስ”፣ “ደቅ”፣ “ናግራ”፣ “ጣና ቂርቆስ”፣ “ምስለ ፋሲለደስ”፣ “ክብራን ገብርዔል” እና “ደብረ ማርያም” ናቸው። በቱሪስቶች በብዛት የሚጎበኘው፣ በ17ኛው ምዕተ ዓመት የተመሠረተው “ክብራን ገብርዔል” ነው።

እነኝህ ገዳማት የመጻሕፍት ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ የውብ ስዕሎች ማከማቻዎችም ናቸው። የእንግሊዝ ንግሥት፣ “ንግሥት ኤልሳቤጥ ዳግማዊት” ኢትዮጵያን በጎበኙበት ዘመን (1965) ባህርዳር ላይ ለእይታ የቀረቡላቸው የገዳማቱ ደማቅ ስዕሎች ነበሩ። የተግባሩ ዋና አስተባባሪ ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያም ሲሆኑ፣ ስዕሎች የመረጡት ብሎም የገዳሙንም ሹማምንት ያግባቡት የታዋቂው ሰዓሊ የአለቃ ኅሩይ የልጅ ልጅ፣ ምርጡ ሰዓሊ አለፈለገ ሰላም ኅሩይ ነበሩ። ንግሥቲቱ ከባህላዊ ቅርሶች በተጨማሪ፣ ተፈጥሯዊውን ቅርስ “ጢስ አባይን” ጎብኝተዋል። ከፏፏቲው ፊት ለፊት፣ ትይይ በሆነ ኮረብታ ላይ፣ ንግሥታዊ ድንኳን ተተክሎ፣ አንድ ሌሊት አሳልፈዋል ሲባል ሰምቻለሁ (ይህን ያጫወቱኝ ሰዓሊ አለፈለገ ሰላም ሲሆኑ፣ ከዚሁ ተግባር ጋር ተያይዞ ሌላም ብዙ ያጫወቱኝ ጉዳይ ስለአለ፣ ያ በሌላ አጋጣሚ ሊተረክ ይችል ይሆናል)።

ሌላው በአካባቢ ያለ ከታሪክ አንፃር ሊወሳ የሚችለው፣ ከጎርጎራ በምዕራብ በኩል ከሚገኝ ኮረብታ ላይ የተገነባው የግዛት ማንፀባረቂያ ሃውልት ነው፣ ከላይ አነደተጠቀሰው፣ ሃውልቱ አሁንም አለ። ከአዲስ ዘመን ወደ ደብረ ታቦር የሚወስድም መንገድ ተገንብቶ ነበር፣የአካባቢው ተፋሰስ የዕፅዋት ሽፋን አልባ ስለተደረገ እና የአፈር እጥበቱ ስለገነነ፣ በዘመናችን ያንን መንገድ እየተጠቀምንበት አይደለም። በአፈር መታጠብ መንስዔ ድልድዮች ተሰብረዋል፣ መንገዱም ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

ከሌሎች የኢትዮጵያ ሃይቆች ጋር ሲነፃፀር፣ ጣና ሃይቅ በሕዝብ ትራንስፖርም ሆነ በቱሪስት ጉብኝት ልቆ ይገኛል። ከባህርዳር ወደ ጎርጎራ (ዘጠና ኪሎሜትር ገደማ) ቋሚ የትራንስፖርት አገልግሎት አለ። አሥራ ሁለት የሚሆኑ የጀልባ መዳረሻ ወደቦች አሉ፣ እነሱም ባህርዳር፣ ዘጌ፣ ጉረር፣ ቁንዝላ፣ እሴ ደብር፣ ጎርጎራ፣ ደልጊ፣ ደጋ እስጢፋኖስ፣ ናርጋ ሥላሴ፣ ጣና ቄርቆስ፣ ክብራን ገብርዔል እና ሮታ ማርያም ናቸው።

ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጋር ተዛምዶ፣ የሃቁን ውሃ መጠን የሚቆጣጠር (ይህ ግድብ የሃይቁን ከባህር ጠለል ከፍታ ከ1784 ሜትር አስከ 1787 ሜትር፣ ማለት ሦስት ሜትር) መጠን ግድብ ተገንብቷል።

ስለ ሃይቁ ሳይንሳዊ መረጃ ቀስ በቀስ እየተሰነደ ነው። ሃይቁ በልብ ወለድ ጽሑፍም መሠረትንት እያገለገለ ነው (“ዴርቶጋዳ” በ ይስማእከ ወርቁ)። ከመመነን ጋር ተያይዞ ሃይቁ ይወሳል። ለምሳሌ በአፈ ታሪክ “ራሥ መኮንን ወለደ ሚካኤል (የአፄ ኃይለ ሥላሴ አባት) አልሞቱም፣ ጣና ውስጥ መንነው ነው” እየተባለም ለዘመናት ተናፍሷል። ከእምነት ጋር ተዛምዶ ሌላም፣ ሌላም፣ ይባላል።

ሃይቁ ለባህር ኃይል ሠራዊትም ማስለጠኛ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጣና ሃይቅ ተኮር የምርምር ጣቢያም መሥርቷል። ጎርጎራ አካባቢም “አሳ ሃበት” ጥናትን፣ ልማትን፣ ዋናው ዓላማ ያደረገ አንድ ትንሽ ተቋም ተመሥርቷል።

የጣና እና የጣና ዙሪያ፣ ከተፈጥሮ ሃብት አንፃር

አባይ ከጣና ወጥቶ ሰላሳ ኪሎሜትር ገደማ ከተጓዘ በኋላ፣ አርባ ሜትር ገደማ ጥልቀት ወደ አለው ገደል ውስጥ ይወረወር እና ፏፏቴ ይመሠርታል፣ “ጢስ አባይን”። ይህ ፏፏቴ፣ ከፏፏቴው በታች የሚኖሩ አሳዎችም ሆኑ፣ ሌሎች ወሃ ውስጥ ኗሪ ሕያው፣ ከታች ወደ ላይ፣ ወደ ሃይቁ እንዳይዘምቱ ያግዳቸዋል። ስለሆነም ጣና በዚህ ገደል (ፏፏቴ) ተከልሎ፣ የራሱ ብቻ የሆኑ፣ ብዙ ሕያው (እንስሳት/እፅዋት) ባለቤት ለመሆን በቅቷል። በዚህ ምክንያት ጣና ሃይቅ ብቻ የሚገኙ ዋቀላሚ (algae) እንዲሁም “ዳያቶምስ” (diatoms) እና የአሳ ዝርያዎች አሉ፣ ሃይቁ የብዝሃ ሕይወት ባለ ሃብት ነው።

“በብዝሃ ሕይወት” (biodiversity) ባላሃብትነት ላይ ተመሥረቶ፣ በዓለም ላይ “የብዝሃ ሕይወት” ሃብታሞች ተብለው ከተመዘገቡ ሁለት መቶ አምሳ ሃይቆች፣ ጣና አንዱ ነው። ይህ ሲሆን መታወቅ ያለበት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ (ትናንሾችንም ጨምረው የሃይቆችን ቁጥር ወደ ሚሊዮኖች ከፍ የሚያደርጉ አሉ) ሃይቆች በዓለም መገኘታቸው ነው።

በጣና ሃይቅ ባሉ የአሳ ዝርያዎች የዝርያ አመዳደብ ላይ ሙሉ ስምምነት ባይደረስም፣ በቅርብ ጊዜ በፕሮፌሰር አበበ ጌታሁን (አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ) በተዘጋጀው መጽሐፍ፣ በሃይቁ ውስጥ ሃያ ስምንት ብቸኛ የአሳ ዝርያዎች አሉ፣ ከነኝህም ሃያ አንዱ ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው። በሃይቁ ውስጥ ካሉ ሃያ ስምንት ብቸኛ ዝርያዎች፣ ሰባቱ ገባር ወንዞች ውስጥም እንደሚገኙ ተመዝግቧል። ሃይቁ ውስጥ ከሚገኙ ዝርያዎች ጥቂቶቹ፣ አንቁላል ለመጣል ወደ ገባር ወንዞች ይዘምታሉ። ከረጋ ውሃ ጋር ሲነፃፀር ፣ ፈሳሽ ውሃ (ወንዝ) ውስጥ ያለው “ኦክሲጂን” (Oxygen) መጠን ከፍ ይላል።

ከጣና ሃይቅ በዓመት 13ሺ (13,000) ቶን (13 ሚሊዮን ኪሎ ግራም) ገደማ አሳ ለማምረት ይቻላል። ሆኖም አሁን ከሃይቁ የሚመረተው የአሳ መጠን አንድ ሺ (1,000) ቶን (አንድ ሚሊዮን ኪሎ ግራም) ብቻ እንደሆነ ይገመታል።

በቅርብ ጊዜ ጣናን የወረረ አንድ አረም፣ እምቦጭ የሚባል አለ። ይህ ውሃ ላይ የሚራባ አረም፣ በአካባቢው ቀደም ሲል ስላልነበረ፣ “ወራሪ ዝርያ” (invasive species) ይባላል። ይህ ወራሪ አረም፣ በአካባቢው ነባር የነበረውን የተፈጥሮ ትስስር፣ ሰንሰለት ያዛባዋል (ያቃውሰዋል)። አረሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተራብቶ በሚገኝበት አካባቢ ሁሉ የማንሰራራት ባህርይ አለው (ስለ እምቦጭ ራሱን የቻለ ጽሑፍ ማዘጋጀት ያሻል)።

በጣና አካባቢ ሰፋፊ ረግረግ ቦታዎች (wetlands) ይገኛሉ፣ እነኘህም ረግረግ አካባቢዎች በክረምት ሙሉ በሙሉ በውሃ ይሸፈናሉ። ዋና ዋናዎቹ፣ “ጭምባ”፣ “ይጋንዳ”፣ “ገሪማ”፣ “ኢንፍራንዝ”፣ “ጥሎማ”፣ “ቁንዝላ፣ እና “ዴልጊ” ናቸው። ትናንሽ ረግረጎች በአካባቢው በብዛት ይገኛሉ።

የውሃ ጥገኞች የሆኑ፣ ህልውናቸውን በውሃ ላይ የመሠረቱ አዕዋፍ በብዛት የሚታዩባቸው አካባቢዎች ናቸው። ሁለት መቶ አስራ አምስት “ብቸኛ የውሃ አዕዋፍ ዝርያዎች” (water bird species /Aquatic bird species) በአካባቢው ተመዝግበዋል። ይህም በኢትዮጵያ ከሚገኙ አእዋፍ ዝርያዎች ሩብ ማለት ነው። እነኝህን ውሃ አዕዋፍ በመባል የሚታወቁት ዝርያዎች፣ እሰከ አንድ መቶ ሀምሳ ሺ በአንድ ጊዜ በአካባቢው ሰፍረው ማየት የተለመደ ነው።

ከነባር ያገር ቤት ሰፋሪዎች በተጨማሪ፣ ከውጭ የመጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአውሮፓ ወፎች (አውሮፓን ብርድ ሸሽተው በሙቀት አካባቢ ለመቆየት) ከመጋቢት መጀመሪያ አካባቢ ጀምረው ለወራት፣ በአካባቢው ተሰራጭተው ይታያሉ። የአካባቢው ገበሬዎች፣ አነኝህ የአውሮፓ ወፎች መቸ እዚያ አካባቢ እንደሚደርሱ እና መቸ አካባቢውን ለቀው ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ በጥሞና ያውቃሉ።

በአካባቢው ለውድመት የተቃረቡ አምስት ብቸኛ የአዕዋፍ ዘርያዎች አሉ። ያም ስለሆነ በጣና ዙሪያ ሁለት አካባቢዎች እንደ “ወሳኝ የአዕዋፍ መጠለያ” (Important Bird Areas) ሆነው “በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት እና የተፈጥሮ ሃብት ታሪክ ማህበር” (Ethiopian Wildlife and Natural History Society) ተመዝግበዋል። እንዲሁም ለመጥፋት የተቃረቡ የአሳ ብቸኛ ዝርያዎችም መናኻሪያዎች ናቸው። ስለሆነም በጣና አካባቢ በሚገኙ ረግረግ ቦታዎች የብዝሃ ሕይወት ክምችት ሃብታምነታቸው የጎላ ነው።

የሃይቁ ደቡብ ጠረፍ በደንገል እና በሌሎች የሳር ዝርየዎች የተሸፈነ ነው። በሃይቁ ዙሪያ በብዙ አካባቢ ትላልቅ የዋርካ ዛፎች አንሰራርተው ይታያሉ። ጣና የአርጃኖ (Nile Monitor) መኖሪያም ነው። ደንገል በሚበዛበት በሃይቁ አካባቢም ዘንዶ አለ ይባላል። ሃይቁ ውስጥ አዞ የለም (ውሀው ቀዝቃዛ ስለሆነ ለአዞ መራባት አያመችም)። ጉማሬ በብዛት አለ፣ በተለይ በጎርጎራ አካባቢ።

የጣና ሃይቅ ስጋቶች እና የስጋቱ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባሮች

በቅርብ ዘመን የታየው “የእምቦጭ” ወረራ ከፍተኛ ስጋት አስከትሏል። አንዱ እና ዋናው የችግሩ መንስዔ፣ ከአካባቢው ታጥቦ የሚገባው ለመሬት ማቅለዣነት የሚያገለግሉ ኬሚካዊ ውሁዶች (በተለይ ፎስፈረስ) እንደሆኑ ይገመታል። ጣና ሃይቅ እና አካባቢው ከተፈጥሮ ሃብት አንፃር ሲታይ፣ ለብዙ ተጨማሪ ችግሮች እየተጋለጠ ነው። ዋናው ስጋት የሃይቁ ብክለት (pollution) ነው። ከባህርዳር ከተማ የሚመነጨው “በካይ ፈሳሽ” (liquid waste)/ቆሻሻ በብዛት የሚገባው ወደ ጣና ሃይቅ ነው። እንዲሁም የከተማውን ደረቅ ቆሻሻ (solid waste) የተሸከመ የክረምት ጎርፍ የሚገባ ጣና ሃይቅ ነው። ስለሆነም ሃይቁ የባህርዳር ከተማ “ደርቅ ቆሻሻም” ሆነ “ፈሳሽ ቆሻሻ” ማስወገጃ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በሂደት ሃይቁ “የውሃ ጋንነት” እየቀነሰ ይሄዳል፣ ሁኔታውም የሃይቁን እድሜ በአጭር እንደሚቀጨው ይገመታል። በተጨማሪ ለእርሻ የሚውለው መሬት አስከ ሃይቁ ዳርቻ ድረስ ስለሚዘልቅ፣ ሁኔታውን በጣም አስጊ አድርጎታል።

ምንም ዓይነት በአካባቢው የሚተገበር የልማት እንቅስቃሴ፣ በበቂ መረጃ ላይ መመሥረት ይገባዋል። ስለ አካባቢው ያለው የተፈጥሮ ሃበት መረጃ በጣም ውስን ነው። ያለንን ሃበት በጥሞና ሳናውቀው፣ ሳንመዘግበው፣ ያለንን አማራጭ በሙሉ ሳንገነዘብ፣ ልማት ተግባር ላይ ብንሰማራ፣ ሃብታችንን ለውድመት ልንዳርግ አንችላለን። ካለ በቂ መረጃ የሚከናወን የልማት ተግባር፣ እንደ ጨለማ ጉዞ መቆጠር አለበት። በቂ መረጃ ያላነገብን፣ ድሆች ስለሆን ነው ሊባል ቢችልም፣ ድሆችም ሆነን፣ ድህነት ጊዜ እንደማይሰጥ ተረድተንም፣ ለልማት ተግባራት በቂ መረጃ ለማመንጨት እንችላለን። በጥናት (Environmental Impact Assessment) የልማቱ ሂደት ሊያደረስ የሚችለውን ተፅኖ ተረድተን ተገቢ ውሳኔ ላይ ለመደረስ አቅሙ ይኖረናል።

ከፍተኛው የመውደም ስጋት የሚመነጨው ሰበነክ ከሆኑ ተግባራት ነው፣ በተለይ የእርሻ መስፋፋት፣ ያም ከሕዝብ ብዛት መጨመር ጋር የተዛመደ ነው። አንድ የውሃ አካልን፣ በተለይ ሃይቅን፣ ከጥፋት ለመታደግ (የሃይቁ ዙሪያ በተለይ ለግብርና ተግባር ሲውል)፣ ለእርሻ በሚውለው መሬት እና በሃይቁ መኻል ሰፋ ያለ “የጥፋት መግቻ ቀጠና” መመስረት ያስፈልጋል። ያም “መኻከል-ገብ” መሬት፣ “ጥፋት መግቻ ቀጠና” (Buffer Zone) በመባል ይታወቃል። ይህን ዓይነት ቀጠና መመሥረት ለሌሎች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተግባራትም ያገለግላል (ለምሳሌ ለብሄራዊ ፓርኮች)።

ይህ ቀጠና በሦስት ደረጃ ተከፋፍሎ፣ ሊመደብ ይችላል (ከሰው ንኪኪ ነፃ ሆኖ ከምንም ዓይነት የልማት ተግባር ፈጽሞ የማይውል፣ በሁለተኛ በተፈጥሮ ሃብት ተፅእኖ የሌሏቸው ውስን ጉዳዮች የሚከናወንበት፣ በሦስተኛ ደረጃ ለተወሰኑ የልማት ተግባራት የሚውሉ)። ጠቅለል ብሎ ሲታይ ለተፈጥሮ ጥበቃ ሥርዓት ተመስርቶ፣ በሥርዓት አካባቢውን ማስተዳደር ነው።

ይኸም በሚደረግበት ጊዜ የአካባቢው ማህበረሰቦች የኑሮ አለኝታ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት። ለአካባቢው ማህረሰቦች የኑሮ አለኝታ የሆኑ መሠረታዊ መዋቅሮች መመሥረት እና የልማት ተግባራት ማከናወን ይገባል። ለነባር የአካባቢ ኗሪ ለሆኑ ማህበረሰችም ሆነ ለግለሰቦች (በነጠላም ሆነ በጅምላ) የኑሮ አለኝታ የሚውሉ ተግባራት፣ ከልማቱ ጎን ለጎን መካሄድ አለባቸው። በአገር ልማት ስም የአካባቢ ማህበረሰቦች ለችግር መዳረግ የለባቸውም።

ተግባር ላይ አልዋለም እንጅ፣ ከሥራ ጋደኞቼ ጋር ከአሥር ዓመት በፊት ገደማ በአማካሪነት ተሰማርተን፣ “ለአባያ” እና “ጫሞ”፣ ብሎም “ጨፋ” ውሃ እና ረግረግ አካባቢዎችን ሊታደግ የሚችል የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ እቅድ (ስትራቴጂ)፣”ለፌደራል አካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት”፣ አበርክተን ነበር ።

ረግረግ ቦታዎችን አጠንፍፎ ለግብርና ማዋል የተለመደ ተግባር ነው። ረግረግ እንደ ጠፍ መሬት፣ እንደ “ጥቅም አልባ” አካባቢ ሆኖ ነው የሚታይ። በተጨማሪም የበሽታ አቀባባይ መራቢያዎችም (ለምሳሌ የወባ ትንኝ) ሆነው ይወሰዳሉ። የረግረግ ጉዳቱ እንጂ ጠቄሜታው በአካባቢው ህበረተሰብም ሆነ ሕዝቡን የሚያስተዳድሩት ሹሞች የተገነዘቡ አይመስልም። ረግረግ የብክለት ጠንቆችን እንደሚያወድም (ችግር ፈጣሪ አካላትን በባክቴሪያ እገዛ እንደሚበታትን፣ እንደ “መርዝ አምካኝ” እንደሚቆጠር)፣ የከርስ ምድርን ውሃ እንደሚያጎለብት፣ የብዝሃ ሕይወት መደብር እንደሆኑ፣ ወዘተ መገንዘብ ያሻል።

ከባህር ዳር ከተማ እንዲሁም ከጎርጎራም ሆነ ከሌሎች አካባቢዎች የሚመነጨውን ቆሻሻ በተገቢ መንገድ ማሰወገድ ያሻል። ሃይቁ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ማስወገጃ፣ መሆን የለበትም። ዋናው የብክለት መግቻ ተግባር ግን፣ ተፋሰሱ በእፀዋት እንዲሸፈን ማድረግ ነው። የገባር ወንዞችን ተፋሰስ በእፅዋት መሸፈን ያሻል። ያም በሁለት መንገዶች ሊተገበር ይችላል፣ አንዱ እና ቀላሉ መንገድ፣ አካባቢውን ከሰውም ሆነ ከከብት ንክኪ ሰውሮ ራሱን እንዲጠግን ማስቻል ነው። ከንኪኪ መታደግ ፍቱን የማገገም ስልት ነው። በዚህ ስልት፣ ከውስን ዘመናት በኋላ ነባር የዕፅዋት ዝርያዎች በአካባቢው ተመልሰው ሊያንሰራሩ ይችላሉ። ሁለተኛው መንገድ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ዛፎችን መትከል እና አካባቢውን በእፅዋት መሸፈን ነው።

ጎርጎራ አካባቢ የታቀደው “ገበታ ለሃገር” ልማት ይበል፣ ይበል የሚያስብል ነው። አካባቢው ውብ እና የታሪክ ባለፀጋ ነው። የታቀደው ልማት ወደ ተግባር ከመቀየሩ በፊት፣ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ፣ ዙሪያ ጥምጥሙን የፈተሸ፣ ካልታሰበ ጥፋት የሚታደግ፣ በቂ ጥናት እንደሚካሄድ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፣ ይተገበራልም ብዬ አምናለሁ። ያም ማለት ለልማቱ ሂደት ሥረዓት ተመሥረቶለት፣ በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ልማት ይሆናል ማለት ነው።

እንደመደምደሚያ አንድ ምኞቴን ላስተጋባ። “የጣና ሀይቅና ሌሎች ውሀ ልማትና ጥበቃና ልማት ኤጄንሲ (ጣዉጥልኤ)” ስለ መመሥረቱ ግንዛቤ አለኝ። ሆኖምጣና ሃይቅን ብቻ ማዕከል ያደረገ፣ አንድ የልማት ተቋም እንዲመሠረት እመኛለሁ። ያም ተቋም በጣና ሃይቅ እና በአካባቢው ያለንን ሃብት በዝርዘር አጥንቶ፣ ሰንዶ፣ ውጤቱን ለልማት ግብዓትነት ሲያበረከት ማየት እመኛለሁ። ተቋሙም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጋር ተቀናጅቶ ቢመሠረት፣ ቀጥተኛ ለሰው ኃይል መጎልበቻም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። በዚህ ሂደት የሚገኘው መረጃ፣ ለሌች ሃይቆችም ልማት እንደ ግብአትነት ሊያገለግል ይችላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top