በላ ልበልሃ

ዓድዋን በዛሬ፣ ዛሬን በዓድዋ

ጥበበ አእምሮ

“History loves exceptions. […] Exceptions create that rare opportunity to separate the contingent from the inevitable, to recognize in discrete choices and chance occurrences the branching paths of human endeavor. The story of Adwa represents one such opportunity, for in pitting one of the most integrated of African states against a latecomer to the scramble for Africa, it strips away the gloom of inevitability and— like the battle itself— put history back into play” (Raymond Jonas, 2011).
(“ታሪክ ልዩ ክስተቶችን ትወዳለች […] እንደዚህ ዓይነቶቹ ልዩ ክስተቶች ዘፈቀዳዊውን ከአይቀሬው ለመለየት፣ በሰው ልጆች የሕይወት ጉዞ ውስጥ በምርጫው የሚያደርጋቸውን እና ድንገቴ ሁነቶችን ለማንጸር የሚያስችሉንን ብርቅዬ እድልን ያጎናጽፉናል። ዓድዋ እንደዚህ ዓይነቱን እድል ይሰጠናል፤ ምክንያት ቢባል፣ የተቀናጀች ጠንካራ አፍሪካዊት ሀገር አፍሪካን ለመቀራመት ከዘመቱት ዘግየት ብላ የመጣችውን ወራሪ ድል በማድረግ አይቀሬ የተባለውን ቀቢጽ ተስፋ ማስተባበል አስችሏል እና ነው። ይህም በዓድዋ እንደነበረው ውጊያ፣ ታሪክን ልዩ ጫወታ እንዲጫወት አስገድዶታል።”)

መግቢያ

አንዳንድ ታሪካዊ ክስተቶች ስለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ዘመናቸው፣ ከነሱ በፊት ስለነበረው ዘመን እንዲሁም የመጭውን ዘመን ባህርይ፣ ሂደት የማስረዳት፣ የመግለጽ፣ የመቀየስ ኃይል አላቸው። እንደ ዓድዋ ድል ያሉ ከዘመናቸው ነጥረው የወጡ ልዩ ታሪካዊ ክስተቶች እና ኢትዮጵያውያን ከቅኝ ግዛት ሙከራዎች ራሳቸውን የተከላከሉባቸው እና ድል ያደረጉበት የጋራ ሥነ ልቡና በርግጥም ሁኔታው ከተፈጸመበት ቦታና ጊዜ ባሻገር የሚነግሩን አንዳች እውነት፣ እውቀት፣ እና ትምህርት አለ። ይህንን የታሪካዊ ክስተቶች ሁለንተናዊ ፋይዳ ለመረዳት እና ግሃድ ሆኖ እንዲታይ ማድረግ የታሪክ ባለሙያዎች ድርሻ ቢሆንም የተደራስያኑ የኅሊና ልሕቀት እና የልቡና ቀናነት፣ ከታሪክ ለመማር ያላቸው ቁርጠኝነት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ይህ አጭር ጽሑፍ ዓድዋን በዛሬ ውስጥ፣ ዛሬን በዓድዋ ውስጥ መመልከት ይቻላል ወይ? ከሚል ምልከታ ለማጠናቀር የተሞከረ ነው።

ዓድዋ እንደታሪካዊ እውነት እና እንደተምሳሌታዊ ክስተት ከዓድዋ በኋላ ላለው ትውልድ ሊሰጠው የሚችለው ትምህርት፣ በትወራ እና በትግበራ በኩል የሰው ልጆችን የእውቀት እና የምግባር ቋት ለማሻሻል የዓድዋን ድል እንደ መነሻ በመውሰድ የሚቻል እንደሆነ የሚፈትሽ ዲስኩር ነው። የጽሑፉ መነሻ ሐሳብ አንባቢን ለውይይት በመጋበዝ ከዓመታዊ የይስሙላ ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ከሚደረግ ስሜት የተጫነው ከበራ፤ የኛ አባቶች እንዲህ አደረጉ፣ የአንበሳው ድርሻ የኛ ነው ከሚለው መናቆር ባሻገር በሰከነ አካዳሚያዊ እና ምሁራዊ መንፈስ ታሪክን በመተንተን፣ ወደ ጋራ መግባባት እና ነጻ አውጭ ትምህርት መቅሰም ይቻላል የሚል ነው። የጋራ ዳራዊ መሠረትን ከአሁናዊ ፈተናዎች እና ጸጋዎች ጋር አስተጻምሮ መመልከት የተሻለ እና ተፈላጊ ነገን ለመትለም እና እውን ለማድረግ ይረዳል። በዚህ በኩል ዓድዋ ላይ ከ125 ዓመታት በፊት ከፍ ባለ ድምጽ እንዲሰማ የተደረገ ጥሪ፣ እና በጉልህ ብርሃን እንዲነበብ የተፈለገ መልዕክት እንደነበረ መገንዘብ ያስችላል።

በዓድዋ በኩል ስናልፍ

ያለፈ ጊዜ ድርብድብ ልባስ ያለው ዳጎስ ያለ ወረቀት ነው ይላሉ። የሆነውን ካልሆነው፣ ተረቱን ከታሪክ፣ የተጨመረውን ከተዘነጋው ወይም ሆን ተብሎ ከተደበቀው፣ በነጽሮተ ዓለም እና ርዕዮተ ዓለም መለዋወጥ ምክንያት የዋጋ ረብ የለሽ እና የትርጉም ወለፈንዲነት የገጠመውን ለመለየት አድካሚ ሥራን ይጠይቃል። እንደ ዓድዋ ያሉ ከዓይን እማኞች ጀምሮ እስከ ዘግይተው የመጡ አጥኝዎች ብዙ ነገር ያሉላቸው ክስተቶች እንኳን ይህንን የትናንትን ደብዛዛነት ሊያጠሩት አልቻሉም። ሄራክሊተስ የተባለ የጥንት የግሪክ አሳቢ “ወድ አንድ ወንዝ ሁለት ጊዜ መሄድ አይቻልም” የሚለው አባባሉ ይጠቀስለታል። የነገሩ ሥልት ወደ አንድ ወንዝ አስር ጊዜ ብትመላለስ በሂደት ላይ ያለው ውሃ ያለማቋረጥ ስለሚጎርፍ ቅድም የመጣህበት እና ተመልሰህ የመጣህበት ወንዝ አንድ አይደለም ለማለት ያለመ ነው። የሰው ልጆች ሕይወትም እንዲሁ ነው፤ በተለዋዋጭ ሁነቶች የተሞላ ነው እና ቋሚ፣ የማይለወጥ የሚባል ነገር በሕይወት ውስጥ ምቹ ቦታ የለውም። ታዲያ ዓድዋ ይሉት ቦታ፣ ድል ይሉት ብሂል፣ ነጻነት ይሉት ቋጠሮ በቦታና በጊዜ ንቡርን እየዘከረ ተጎልቶ ይጠብቅ ይሆን?

በዓድዋ በኩል ብናልፍ፣ ዛሬ ዓድዋን ብንጎበኝ፣ ሶሎዳ ተራራን ሽህ ጊዜ ብንዞረው ያኔ የነበረውን የዓያቶች ስሜት መጋራት ይቻላል ወይ? እንዲህ ያለው ጥያቄ አይ ወይም አዎ ተብሎ እቅጩን የሚነገርለት አይደለም። በተለይ ዛሬ፣ በነዚህ ወራትማ ዓድዋን የመርገጥ ወኔ፣ ስለ ዓድዋ ድል እና ስለ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ጠላት አብሮ መዋደቅ፣ በዓድዋ ምድር ላይ ስለመደረጉ ለመናገር ወይ ጭካኔ አልያም ይሉኝታ ቢስነት ሳያስፈልግ አይቀርም። በዓድዋ በኩል ስናልፍ የምናገኘው የአያት ቅድመ አያቶቻችንን የሚዋጋ ስባር አጽም፣ የነጻነት ዓርማ የበቀለበት፣ የጎመራበት ባንድነት የተቆለለ ሥጋ አፈር፣ መዓዛው የሚያውድ በአንድነት ህብረ ቀለም ያሸበረቀ ደም ነው። ዘፋኟ እንዳለችው “ትናገር ዓድዋ፣ ትመስክር ዓድዋ” ቢባል የሚሰማው ጭብጥ ይኸው ነጻነት እና አንድነት ነው። በቦታው የነበሩት ሲነግሩን ጭፈራና ለቅሶ፣ ሙሾና ቀረርቶ፣ ሐዘን እና ደስታ በአንድ ጭንቅላት፣ በአንድ አንደበት የተስተናገዱበት ወቅት ነበር አሉ፤ ድልን እያሰቡ ከጎናቸው ክርብት ያለውን ወገን እስከወዲያኛው ሲያጡት ለቅሶም በምን ቋንቋ እንደነበር ለመረዳት ያችን ቅጽበት መጋራትን ይጠይቃል።

በዓድዋ በኩል ስናልፍ የምናገኛት “ሃይማኖት ከሚያጠፋ፣ ማንነት ከሚበርዝ፣ እንደፍልፈል ጉድጓድ ከሚቆፍር” ጠላት በሉዓላዊነት ፍቅር፣ በአይበገሬነት መንፈስ የተጠበቀች ክብርት ሀገርን ነው (ቢያንስ ከመረብ ምላሽ ወዲህ ያለችዋ)። በዓድዋ በኩል ስናልፍ የምንመለከታት ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች ታጥራ፣ ከሐያላን መንግስታት ጋር በድርድር ወይም በትግል እየተነጋገረች ሉዓላዊነቷን ላለማስደፈር ስትታትር የኖረችዋን ኢትዮጵያ ነው። በዓድዋ በኩል ስናልፍ የምናገኛት ኢትዮጵያ ከዓርባ ዓመታት በኋላ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሀገረ መንግሥቷን የተቆጣተረችውን የኋለኛዋን ጣልያን አላስቆም አላስተኛ ያለችውን የዓርበኞች ረመጥ ምድር ነው። ይህም ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በ”የታሪክ ማስታወሻ”ቸው እንደነገሩን ማይጨው ላይ ለምን እንድንሸነፍ ያደረጉንን የውስጥ ቅሬታዎች እና ቅራኔዎች ባልሰማ ባላየ ያለፍናቸው እንደሆነ ነው። በዓለም ዙሪያ የነበሩ ኢትዮጵያውያን (እንደነ መላኩ በያን እና ሐኪም ወርቅነህ ያሉት) በዚህ በተነቃቃ መንፈስ አገራቸውን ከድል ወደ ሥልጣኔ ለመምራት ወደ አገራቸው የመጡት ከዓድዋ ድል ማግሥት ነው። የዘመኔ ዲያስፖራ (ስደተኛ እና ኮብላይ አኩራፊ) በዚች በኩል ዓድዋን አጮልቆ ቢመለከት ምን ይሰማው ይሆን?

በዓድዋ በኩል ስናልፍ የምናገኘው የጥቁር ህዝቦች በተለይም የአፍሪካውያን የድል ጮራ፣ የማይገፋውን የቅኝ ግዛት ግንብ መናድ እንደሚቻል ነው። ይህም ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ላይ የጨቋኝ እና ተጨቋኝ ቀጣይነት ላይ ታላቅ ጥርጣሬ እንዲያሳድር አድርጎታል። ፓን አፍሪካኒዝም፣ ኢትዮጵያኒዝም እና መሰል የጥቁር ህዝቦች ትግሎች እንዲወለዱ ዓድዋ የራሱን ድርሻ እንደሚወስድ ማንም አሌ የማይለው ሐቅ ነው።

በዓድዋ በኩል ስናልፍ የምናገኘው የተሳሳተውን አውሮፓዊ መንፈስ ነው። አውሮፓውያን የራሳቸውን የውስጥ ችግሮች ለመፍታት እና ኢኮኖሚያዊ ምኞታችውን ለማስታገስ እንደመፍትሄ የወሰዱት በውጭ አገራት (በባዕዳን ምድር) አማራጭን መፈለግ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን የሰይጣን ምክር ሲመክሩ እንደ የተሻለ ሜዳ ሆኖ ያገኙት አፍሪካን ነው። ይህንን በስሜት እና በቀቢጽ ተስፋ የተቀየጠ ምኞት እውን ለማድረግ ማታለል፣ ማሳመን እንዲሁም ማስገደድ እንደ ሁነኛ ዘዴዎች ተጠቅመዋል። የራስን ችግር ለመፍታት በሌሎች ላይ ዘመን የማይሽረው ችግር መዝራት በአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በመላው የዓለም ህዝቦች ሥልጣኔ፣ በሰብዓዊነት ክቡር ጸጋ ላይ ከባድ በደል ማድረግ እንደሆነ ቆይቶም ቢሆን ሊገባቸው አልቻለም። በዚህም በዓድዋ በኩል ስናልፍ የሰውነት ክብር፣ የዜግነት ጸጋ፣ የነጻነት ጥሪ፣ የሉዓላዊነት ጉጉት፣ የአትንኩኝ ባይነት ጩኸት ለሁሉም የሰው ልጆች በማይዘነጋ ማስተጋባት የህሊና ስንቅ የልቡና ጓደኛ ሆኖ እንደቀረ መረዳት እንችላለን። ዓድዋ ከገለጻዊ ትርክቱ፣ የኩራት ድንፋታው ባሻገር ተምሳሌታዊ ውክልናው በለውጥ ውስጥ የማይናወጽ ቀጣይነት እና ታሪክ ራሱን የሚፈትሽበት ጆሮ ዳባ ልበስ እና “ዓይኒ እሙተይ” (አላይም አልሰማም) ተብሎ የማይታለፍ ከባድ ደወል ነው።

ሁሉም አናብስት በነበሩበት ጊዜ የአንበሳውን ድርሻ ስለመሻማት (?)

ዛሬን በዓድዋ ስንመለከተው በትውልዶች መካከል መተላለፍ፣ አለመገናኘት ያለ ይመስለናል። ዓድዋ እንኳንስ ባለቤቶቹ ተሸናፊዎቹ ያደነቁለት፣ ምንም ለሐሜት የማይመቸው ገጽታው በተጋዳዮቹ መካከል የነበረው መደጋገፍ እና ሕብረት ነው። ሁሉም አናብስት በነበሩበት ጊዜ የኔ አያት ቅድመ አያት ነው የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ማለት ያልተጣሉ ሰዎችን (እንዲያውም እጅጉን የሚዋደዱ ሰዎችን) ለማስታረቅ እንደመቀመጥ ነው። አሸንፈን የአሸናፊነትን ካባ ሳንለብስ መቅረታችን እንዳለ ሆኖ በማሸነፋችን ያጣነው ነገር ጸጸት ከሚቀሰቅሰን ይልቅ ዓድዋ ላይ በአንድ ቀን ጦርነት ድል ያደረግንበትን ህያው ውርስ ለመዘከር እንኳን ብቁ አይደለንም። ይኸ እንደ ሃገር የሚያስከፍለንን ዋጋ፣ እየከፈልን ያለውን በዋጋ የማይተመን ኪሳራ፣ ለወደፊቱ ከተጋረጠብን ዓለማቀፍ ዲፕሎማሲ ከባድ የቤት ሥራ እና ውስጣዊ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የተግባቦት፣ የሰላም ጥያቄዎች አንጻር ሊመለከት የሚችል ያለ አይመስልም።

ኢትዮጵያ እንደ ሃገር፣ ኢትዮጵያውያን እንደዜጋ የጋራ ትውስታችን ላይ ተመስርተን ነጋችንን የተቃና እናድርግ ቢባል በመልካምነቱ የሚጠቀሰው ዓድዋ ነበር። በዚህ ላይ እንኳን ትንሹ መስማማት ላይ አልደረስንም። አንድ ፕሮፌሰር እንዳሉት “ዛሬ የዓድዋን ድል ስንዘክር፣ ዓድዋ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ መዘንጋት የለብንም።” ዓድዋን በየራሳችን መንገድ ለማክበር መሞከር እርስ በርሳቸው እኔ እቀድም እኔ እቀድም እያሉ አብረው የተዋደቁትን ሰዎች ክብር ተቀብሮ እንዲቀር ከማድረጉም በላይ እርስ በርሳችን አንዳችን የአንዳችንን የመቃብር ጉድጓድ በመቆፈር ላይ መሆናቸውን በውኑ የጤንነታችን ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማሳያ ነው።

በመጨረሻም ዓድዋን በዛሬ መመልከቱም ሆነ ዛሬን በዓድዋ ለማየት መሞከሩ ከአገር ሉዓላዊነት ባሻገር ጨቋኝና ተጨቋኝን ከአስተሳሰባዊ ባርነት ነጻ የእውቀት ቋጠሮ ማግኘት እንደሚቻል ያሣያል። ይህንን ለማድረግ ቀናነት፣ ቁርጠኝነት እና ያለንበትን ችግር ስፋት እና ጥልቀት ለመመልከት ትዕግሥቱን ይጠይቃል። ትናንት ተባብረው በጠላት ላይ ቃታ የሳቡ የነጻነት ባለቤት የሆኑ ዓርበኞች ልጆች ዛሬ እርስ በርሳቸው ለመጠፋፋት ቃታ የሚስቡበት አገር ለመጭው ትውልድ ምን እንደሚመስል ለማየት ነብይነት አያስፈልግም። እነዚህ ሰዎች ዓድዋን ሲያከብሩት የለበጣ ወይም የይስሙላ ነው። በትክክል ያላጣጣምነው ድል ድል መሆን ይችላል? በአግባቡ ያልተረጎምነው እና ያልተጠቀምንበት የኩራት ውርስስ ያኮራል ወይ? ዓድዋን በዛሬ፣ ዛሬን በዓድዋ መመልከት ይቻል ይሆንን?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top