ታዛ ስፖርት

ከሞት አፋፍ

ከተለያየ ከተማ ስለመጡ ቤት ተከራይተው ነው የሚኖሩት። የአዳማ ከነማ ተጫዋቾች ናቸው። ጊዜው ደግሞ 1993 ዓ.ም። ከየቤታቸው መጥተው ልምምድ ከሰሩ በኋላ ምግብ በልተው ወደየቤታቸው ይበታተናሉበሳምንቱ አጋማሽ አንድ የቡድኑ ደጋፊ ቤቱ ለቅሶ ስላለ ለመድረስ ፈለጉ ምሳ እንደበሉ በቡድኑ ሰርቪስ ቦታው ላይ ደረሱና ተሰናብተው ሲወጡ ከመሀል አንደኛው ተጫዋች “እንዲህ ሰብሰብ ብለን አናውቅም ሁሌም ወደየቤታቸን ነው የምንሄደው ዛሬ እንኳን አብረን ሻይ እንጠጣ” ብሎ ሲናገር ይሄ ጉዳይ በሁሉም አእምሮ ውስጥ ስለነበር በአንድ ድምጽ ተስማሙ።

አንድ ላይ መሆን ስለፈለጉ ቡና ቤቱ በረንዳ ላይ ተሰብስበው ማውራት ጀመሩ። ወሬው ጦፏል፣ ጨዋታ በጨዋታ ላይ ተደራርቦ አንዱ ከሌላው አፍ ላይ እየተቀበለ ማውራታቸውን ቀጠሉ። በወሬው መሀል ሁለት ተጨዋቾች ተነሱ። አንደኛው ከረምቡላ ቤት ሰው አይቼ ልምጣ ብሎ ገባ፤ ሌላኛው አንድ ጓደኛውን በመንገድ ሲሄድ አይቶ ሊጠራው ከመሀላቸው ተነስቶ በመውጣት ላይ ነበር። ብርሀኑ ቃሲም የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ ነው። አጠገቡ ካለው ልጅ ጋር እያወራ ነው። እሁድ ከቡና ጋር ስላለባቸው ጨዋታ እየተነጋገሩ ዞር ሲል የሆነ ጭቅጭቅ ይሰማል። “ምንድነው ጭቅጭቁ” ብሎ ጥያቄውን ሳይጨርስ አጠገቡ ቦምብ ተጥሎ ፈነዳ በፍንዳታው ጠረጴዛውን ከበው የነበሩትን የአዳማ ከነማ ተጫዋቾችን በየቦታው በታተናቸው። በዚያ ቅጽበት ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆነ። አካባቢው ተደበላለቀ።

ደህና የሆነው አመለጠ። የተመታው በደም ተለውሶ ተዘረረ። ብርሀኑ ሁሉም ነገር ጨለማ ሆነበት ሁኔታውን እንዲህ ያስታውሳል። “ … ምን እንደሆነ ባለውቅም የሆነ ሰው በመሳሪያ እየረሸነኝ ያለ ነው የሚመስለኝ። ከዚህ ቦታ ማምለጥ አለብኝ ብዬ ተነሳሁና መሮጥ ጀመርኩ። መሰለኝ እንጂ እዛው በተኛሁበት ነው ያለሁት። አንድ ርምጃ ሳልሄድ ወደቅሁ። አንዲት ቆሎ ነጋዴ ስታየኝ አወቀችኝ። ተሸክማኝ ሄደች። ሰዎች ተቀብለዋት ሀይለማርያም ማሞ ሆስፒታል ወሰዱኝ” ይላል ብርሀኑ።

ከአንገቱ በላይ በስተቀር ሰውነቱ ሁሉ በፈንጂው ፍንጣሪ ተበሳስቶ ከሰውነቱ ደም ይወርዳል በቂ ህክምና አላገኘም ማታ ጥሩ ያወራ ነበር። በኋላ ግን ራሱን ሳተ። ሜዳ ላይ ግጭት ደርሶበት የተጎዳ ይመስለዋል። ወይም ሰው መትቶት የተፈነከተ መስሎታል። በኋላ ደግሞ መኪና የገጨው እንደሆነ ገመተ። ግን ይሄንንም ማረጋገጥ አልቻለም። ማን ይንገረው? በእርግጠኝነት በስለት ነገር እንደተወጋ አወቀ። ግን ማነው የወጋው? ለምን ወጋው? የተጣላው ሰው እንደሌለ ያውቃል ግን እንዴት? መልስ የለም።

በፈንጂው የተመታው 30 ሰው ነው። ሆስፒታሉ ከአቅሙ በላይ ሆኗል። ማስተናገጃ ቦታ ስለሌለ አብዛኛውን ጉዳተኛ በየጠረጴዛውና ወንበር ላይ ተኝቶ ያቃስታል። ደጋፊው ወሬውን ሰምቶ ሆስፒታሉን አጨናነቀው። ውጭ ሆነው ባንዲራ ይዘው ያለቅሳሉ። ብርሀኑ በሰመመን ውስጥ ነበር። እንደምንም ሲነቃ አጠገቡ ያለው ሰው ሲገነዝ ያያል።

ሰውየውን አስታወሰው። ቡና ቤት ውስጥ አጠገቡ ነው የተቀመጠው። አዲስ ሎንችና ከገዛ ገና ወር አልሆነውም። ሳምንት ያገባል፤ ስለ ሰርጉ አንዳንድ ነገር ተወያይተዋል። በመሀል አምቦ ውሃ አዝዞ የቀዳውን ለመጠጣት እያነሳ ሳለ ነበር ቦምቡ የፈነዳው ብርሀኑ ሰውየው መሞቱን ካየ በኋላ ደነገጠ። አሁን እርሱንም ሞት ሊገንዘው ስለመጣ ለመታገል መዘጋጀት አለበት። ብርሀኑ ስለሞት ሰማቶ አየፈጀው ሰውነቱ ውስጥ መስራት ጀምሯል። እያዳከመው፣ እያፍረከረከው ነው። ፍንዳታው በአብዛኛው ፍንጣሪ እርሱ ላይ አርፏል። ተዳከመ። በጣም ተዳከመ። አይኑ ስልምልም አለ። መቃዠት ጀመረ።

እርዳታ ሲጠይቅ ማግኘት አልቻለም። የሆነች ሴት እንደርሱ ተመትታ አደጋ ደርሶባታል። አጠገቡ ነው ያለችው። ከእርሱ ትሻላለች፤ ደጋግማ አየችው። “እረ ይሄ ልጅ ሊሞት ነው!! አንድ ነገር አድርጉት” ትላለች። ሰሚ ግን አላገኘችም። እንደምንም አንስታ ደህና ቦታ ላይ አስተኛችው። አጠገቡ ያለውን ሰው ብርሀኑ ትኩር ብሎ አየው በቃ እንደርሱ ሊገነዝ ነው። ማንንም ማስቸገር የለበትም ለግነዛ እንዲመች እራሱን አስተካክሎ ተኛ። ሞት ከወሰደው እንዳይቸገር ወይም እንዲመቸው ኮቱን ተንተርሶ ለጥ አለ። ድምጹ ባይሰማም “ደህና ሁኑ ጓደኞቼ” አለ። ጥቂት ቆይቶ መሞቱን አወቀ። በህልሙ ሲቀበር አየ። በሰማይ ቤት ለጊዜው ሰው ስለማያውቅ ቅድም የተገነዘውን ሰውዬ በቶሎ ማግኘት እንዳለበት አመነ። አብረው በመሆን ማን አደጋውን እንዳደረሰባቸው ያጣራሉ። ሰውዬውን የት ብሎ እንደሚፈልገው አሰበ። በጣም ያዘነው ደግሞ እሁድ ከቡና ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ያለመሰለፉ ነበር። እስካሁን በሊጉ ስድስት ግብ አስቆጥሮ ከክለቡ ይመራል። እነዚህን ግቦች ትቶ መሄዱና ለፍሬ ሳያበቃቸው መቅረቱ አሳዝኖታል። በዚህ አያያዙ ኮከብ ግብ አግቢ እንደሚሆን ያምን ነበር። “ምን ያደርጋል ሞት ቀደመኝ” ብሎ ተኛ።

ከሃያ ቀን በኋላ ብርሀኑ አጠገቡ ጋር ሰው ሲንቀሳቀስ አየ “የት ነው ያለሁት?” ብሎ ጠየቀ።
“ባልቻ”
“ባልቻ የሚባል ቦታ አለ እንዴ?”
“አዎ”

አካባቢውን በጥልቀት ተመለከተ። መቃብር ቦታ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ፈለገ። የሚያውቀው ሰው ማግኘት አልቻለም። ድንገት የሆነች ሴት አየ። ቀረብ ብሎ ሲመለከት እናቱ ነች። የሞተ ቀን እናቱን ያለማግኘቱ በጣም አዝኖ ነበር። ከብዙ ቆይታ በኋላ ሆስፒታል ውስጥ መሆኑን አረጋገጠ። ምን እንደደረሰበት ሲነገረው ነገሩ ከመሆኑ በፊት የሆነውን አወቀ። ቦምቡ ሲወረወርና አካባቢውን ድብልቅልቁን ሲያወጣው እንደነበር አስታወሰ። ማን ይሄን እንዳደረገው ግን ማወቅ አቃተው።

ከሁለት አመት በኋላ ለወጣት ቡድን ተመርጦ ሆቴል በነበረበት ጊዜ ሰውነቱን ያሳክከው ጀመር። ያከከበት ቦታ እያበጠ መጣ። እብጠቱ ፈነዳና ድቡልቡል ነገር ወጣ። የፈንጂው ብረት ነው። ነገሩ አሰጋው። ወደ ሀኪም ቤት ሄደ። ሀኪሙም ብረቶቹን አየና “እነዚህ የመከኑና መርዙ የወጣላቸው ስለሆኑ ችግር የለውም” አለው። በአራት አመት ስምንት ብረት አወጣ። ዛሬ ብርሀኑ ትዳር ይዞ ልጆች ወልዶ ከብዶ በሰላም ይኖራል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top