አድባራተ ጥበብ

ሙዚቃ በኢትዮጵያኒዝም ትርክት

በ20ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያን መሰረት አድርገው ሲሰሩ የነበሩ ሙዚቃዎች ይሁኑ ዝማሬዎች የኢትዮጵያን ውበት ከአድዋ ጦርነት ድል በፊትም ይሁን ከዚያ በኋላ የነበረውን በጥቁሮች ዘንድ ያኮራናል የሚሉትን ታሪክ እንደ ማሳያ ተጠቅመውበታል። በቅኝ ገዥዎች ዘንድም ይሁን በባሪያ ንግድ የተሳታፉ ፈጥረውት የነበረው “አፍሪካ ታሪክ አልባ” የተሳሳተን ትርክትም በዚሁ ውድቅ ማድረጊያ መንገድ ሁኗል።

በተለይ ከ1915 ጀምሮ ጥቁሮች ለነፃነታቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት በከፈሉባቸው ዓመታት ሙዚቃ እንደ የአርበኝነት ስሜት ማነሻሻ ብቻ ሳይሆን የታሪክ መንገሪያም መንገድ ተደርጓል። ከዚህም ባለፈ ደግሞ “ኢትዮጵያ” በሚል ዘውግም የሀገሪቱን ታሪክ ለማጥናት ሰፊውን በር ከፋች ሆኗል። ሙዚቃ ደግሞ በአንትሮፖሎጂስቶች እንደ አንድ የጥናት መሰረት ተወስዷል። እንዴት የሚለውን ለመዳሰስ ቀጣዩን እንደ መንደርደሪያ እናድርግ።

ከአድዋ ጦርነት ፥ ከድሉ በፊት ኢትዮጵያ በጥቁሩ ጭቁን ሕዝብ ዘንድ በተስፋ ተጠባቂ ነበረች። አሜሪካዊው ገጣሚ ዋልት ዊትማን ከግጥም ስብስቦች ውስጥም ይህንን አንፀባርቋል። በአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ጀነራል ሸርማን ሲያንቀሳቅሱት ለነበረው ሰራዊት ጥቁር አሜሪካዊቷ ለአሜሪካ ሰንደቅ አላማ የክብር ሰላም ሰጥታለች። ሰራዊቱ ግን በአግራሞት ተመልክቷታል።

ገጣሚው ዋልት ያቺን ጥቁር ሴት በግጥሙ ሲገልፃት ሙሉ የሰውነት ክብር ያልተሰጣት እንደነበረች በድርድሩ ይናገራል። የግጥም መልዕክቱ ፍቺ ቀላል ነው። እንደ አገልጋይ፣ ታዛዥ፣ በቆዳ ቀለማቸው ልዕልናን የሰጡ ያሰቡትን የምትተገብር እንጂ አመዝናና የምትተገብር ተደርጋ አልተቆጠረችም። ጥቁር አሜሪካዊቷን “ኢትዮጵያ” ብሎ ጠርቷታል። “Ethiopia saluting the color” በሚለው ግጥሙ የዛችን ሴት ውስጣዊ ማንነቷ እና ነፃ የመሆን ፍላጎትዋን ራሷ ላይ በጠመጠመችው ባለ ቢጫ፣ ቀይ እና አረንጓዴ ቀለም ጨርቅ ይስተጋባል። የቀለም ድርደራው ደግሞ ከቅድመ ዳግማዊ ምኒልክ የነበረውን የኢትዮጵያ መለያ ቀለማትን ይወክላል።

ሮበርት አሌክሳንደር ያንግ የተባለ የመብት ተሟጋች ደግሞ ለጥቁር ጭቁኖች ለነፃነታቸው ማንቂያ ያዘጋጀውን በራሪ ወረቀት “The Ethiopia Manifesto” ብሎ ሰይሞታል። ጥቅል ሃሳቡ የፖለቲካ መብት ሳይሆን ሰብኣዊ መብት በባርነት ንግድ ለተያዙት እንዲሰጥ ያትታል።

ከምድራቸው በግፍ የተወሰዱት አፍሪካዊያንም በዋልት ግጥም ይሁን በሮበርት ያንግ የጋራ መስማሚያ ሰነድ “ኢትዮጵያዊያን” ተብለው ተጠርተዋል። ይህ ደግሞ ነፃነታቸውን መናፈቃቸውን እና ነፃነታቸውንም ነፃ ከሆነችው ምድር እንደሚያገኙ ማሰባቸውን ያሳያል።

ከአድዋ ድል በፊት የነበረው ይህ ነፃ የመሆን አስተሳሰብ ኢትዮጵያን ከምድሪቱ ውጪ ባሉት ተምሳሌት ስትደረግ ዋነኛ መነሻ መዝሙረ ዳዊት 68:31 ነበር። ከግብፅ ይመጣሉ ከሚባሉት መኳንንቶች ይልቅ ወደ ፈጣሪ እጆችዋን የምትዘረጋዋን ተስፋ በማድረግ ነው።

አድዋም ኢትዮጵያን በተስፋ ሲያይዋት ለነበሩ ትንቢት የተፈፀመባት ምድር ሆነች። “ዲፕሎማቱ ጳጳስ” መታወቂያቸው ለነበሩት የሮማው ጳጳስ ሊዮ 13ተኛ ግን በአድዋ ጦርነት ወቅት የጦር ምርኮኞች ለነበሩት ከ2000 በላይ የጣሊያን ዘማቾች ከማስለቀቅ ድርድር ( Religion deplomacy ) ጎን ለጎን ትንግርት ለሆነባቸው የነጮች በጥቁር የመሸነፍ እውነታን በዓለም ጆሮ እንዳይሰማ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። “ተደብቀው ያረገዙትን፣ ሰው ሰብስበው ይወልዱታል” እንዲሉ ግን ገድሉ ከአድዋ ብቻ ተቀብሮ አልቀረም።

ከድህረ አድዋ በኋላም ጥቁር አሜሪካዊው ሄሪ Burleign በነጩ ገጣሚ ዋልት የተደረሰውን “Ethiopia saluting the color” በቅንብር አሳምሮ ለአድማጭ ጆሮ በሙዚቃ መልክ አድርሶታል። ሃሳቡም ግልፅ ነው፤ ኢትዮጵያዊያን በህብረት ላሳኩት ድል በተቀሩት ጭቁኖች ዘንድ መነሳሳትን እንዲፈጥር፣ የነበሩበትን በማስታወስ ወደ ፊት እንዲራመዱ ለማድረግ።

በኢትዮጵያኒዝም የነበረው ሃሳብም በፓን አፍሪካኒዝም ድጋፍ አግኝቶ በመላው አለም በተበታተኑት ጥቁሮች ዘንድ በስፋት ተቀንቅኖ የአድዋ ድል ባጭሩ የጭቁኖች ህብረት መፍጠር ማለትም እንደሆነ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል። በዲስኩር እና ማኒፌስቶ ብቻ ሳይሆን ሙዚቃውም የሃሳብ መሸከሚያ መንገድ ተደረጓል። ሙዚቃዎቹም ገድሉን እየዘከሩ የአስተሳሰብ ለውጥንና ወደ ፊት ስለመራመድን ሃሳብ የሚያንፀባርቁ ተደርገዋል።

የኢትዮጵያዊያን ጀብድ የሰሙ ተስፈኞች ምስራቃዊቷን “የአባት ምድር” መጠሪያ አደረጉ። ይህ የአባት ምድር ሃሳብም ለሁለት ተከፍሏል። አንድም ይህ አባታዊ ምድር በሃሳብዊነት (Spiritula father’s land) ከአፍሪካ አህጉር ውጪ በግዳጅ እንዲወጡ የተደረጉ በቅድመ አያቶቻቸው አፍሪካዊ የሆኑ ጥቁር ህዝቦች ባሉበት ቦታ በመሆን የነፃነት ትግላቸው በኢትዮጵያዊ ስሜት በማድረግ ነፃነታቸውን እና ሰብኣዊም፣ ፓለቲካዊም (ዲሞክራሲያዊ) መብታቸውን ማግኘት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወደ ነፃይቱ አባት ምድር በመምጣት ኑሯቸውን ማመቻቸትን እና ወደ ምድራቸው መመለስን ያካትታል። (በዚህ እሳቤ ውስጥም የኢትዮጵያ ምድር መዳረሻቸውን ማድረግ እንደ አንዱ የነፃነት መቀዳጃ መንገድ ቢታሰብም ላይቤርያም መዳረሻ ተደርጋለች።)

እንደ ማሳያ ለማድረግም በ1919 ለመጀመሪያ ጊዜ በUNIA (universal negro improvement association) ዋና ፅህፈት ቤት የተዘመረው እና ኢትዮጵያዊ መዝሙር የተሰኘው ይሆናል። መዝሙሩም የአፍሪካ ሪፐብሊክ ብሔራዊ መዝሙር ተብሎ ተሰይሟል፤ ከአፍሪካ ውጪ ኑሯቸውን (በስደትም ይሁን በቦታው የረጅም ጊዜ ነዋሪ የሆኑ/ መወለድን ያመለክታል) መዝሙሩን የጥቁር ዘር ብሔራዊ መዝሙር (Anthem of the Negro race) በማለት ተቀብለውታል። ይህ ደግሞ በእነ ማርክስ ጋርቬይ ሲቀነቀን ለነበረው ሃሳብ የመግቢያ ምዕራፍ ተደርጎ ተቆጥሯል። ኢትዮጵያም ብትሆን ይህንን ዝማሬ በአማርኛ ግጥም ተሰርቶለት ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ በትምህርት ቤቶች ይዘመር እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል። የመዝሙሩን ግጥም በመተባበር ከደረሱት ውስጥ ደግሞ አርኖልድ ጄ. ፎርድ ይህንን ስራ በማቀናበር የወቅቱን የትግል ስሜት በሁሉም ዘንድ እንዲጠናከር አድርጓል። ከዚህም ባለፈ የUNIA የሙዚቃ ክፍልንም መምራት ችሏል። ይህ ደግሞ በመፅሐፍ ቅዱስ በተለይ በብሉይ ኪዳን የመፅሐፉ ንባብ ያዳበረውን እውቀት እንደ አንድ አጋዥ መሳሪያ በመጠቀም የሰው ልጅ እኩልነትን በሙዚቃ የመልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ እንዲዳረስ አድርጓል። በአባት ምድር አስተሳሰብም አርኖልድ ጄ ፎርድ ኑሮውን እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ በኢትዮጵያ ቆይቷል። ወደ አባት ምድር የመመለስ ሃሳብ ደግሞ ከኢትዮጵያኒዝም ሃሳብ ትይዩ መሰለፍ የቻለው በማርከስ ጋርቬይ ፍልስፍና መሰረት ያደረገው እና ኋላ ላይም ከብሔርተኝነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ባለፈ የራስተፈሪያን እንቅስቃሴ ይገኝበታል።

የሬጌ ሙዚቃም የስልተ ምቱ መሰረት ሳይለቅ በፍልስፍና ደረጃ እየተነሱ የመጡት የነፃነት ጥያቄዎች ከእምነት አስተሳሰብ ጋር እየተዋሀዱ መቀንቀኑን ማስተዋል ይቻላል። የእነ ቦብ ማርሌይ፣ ፒተር ቶሽ፣ ቡኒ ሊቪንግስቶን የራስተፈሪን እምነት ተከታይ መሆናቸው (መቀበላቸው) የባቢሎን ውድቀትን ወደ አባት ምድር ከሚያደርጉት መመለስ ጋር የተያያዘም ሁኗል። ከመፅሐፍ ቅዱስ ሁለተኛ መፅሐፍ ኤክሶደስ (ዘፀአት) ብሎ ቦብ ማርሌ በ1977 ያቀነቀነው ሙዚቃም ወደ አባት ምድር መመለሻ ሃሳብን በሚገባ ተንፀባርቆበታል።

ለማሳያነት ከቀረበው መንደርደሪያ ሃሳብ ወደ አንትሮፖሎጂ እና ሙዚቃ እንመለስ።

አለን ፒ.ሜሪያም በ1964 በጥናት መልክ ባወጣው ፅሁፉ ላይ (The Anthropology Of Music) በአጠቃላይ ስለ ሰው ልጅ ስር መሰረት ጥናት ሲደረግ ሙዚቃ ባህልን ማንነትን በጊዜ ቅብብሎሽ የነበረውን አስተዋፅኦ መመልከቻ መስኮት መሆን እንደሚችል ይናገራል።

በቅድመም ይሁን በድህረ አድዋም አፍሪካውያን የራሳቸው ባህል፣ ወግ፣ እሴት እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን መልካም ነገርንም ለመቀመር በራሳቸው ዙሪያ ያሉትም ሃገራት በምን ያክል ደረጃ እንደሚመለከቱ ማሳያ ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪም ሙዚቃው ለማህበረሰብ በሙዚቃው የሚተላለፈው መልዕክት የማህበረሰብ ጥምረት የመፍጠር ከፍተኛ አቅም እንዳለው አንትሮፖሎጂስቶቹ ሲያምኑበት በየአካባቢው ቀጠናዊ ከሆኑ አኩሪ ታሪኮች በዘለለ ደግሞ የአድዋ ድል ትልቁ ማሳያ መደረግ ይችላል። የUNIA ከሚያራምደው ፖለቲካዊ አጀንዳ ባሻገር የኢትዮጵያውን ጀግንነት በትግሉ እንዲሰፈርም የተዘጋጀው ብሔራዊ መዝሙር ደግሞ ለአብነት በቂ ማሳያ መሆን ይችላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top