ታዛ ወግ

መንገድ የጠፋበት መንገድ

እንድሪያስ ተረፈ

እናንተ ያላችሁትን በሉ፤ እኔ ግን መንገድ ስለጠፋበት መንገድ አንድ አፍታ የምለውን ልበል። የ134 ዓመት ባለጸጋ የሆነችው አዲስ አበባችን መንገድን ያህል የመገናኛ አውታር አምጦ መውለድ አልቻለችም። እንደምንም ቢሳካላት አፍታ ሳይቆይ ቁፍርፍር ጉርጉድጉድ ይልባላታል ጥሎባት። ዝናብ ጠብ አይበልብኝ የሚሉት አውራ መንገዶቿ የውኃ መተኛ አልጋ ሆነው የሚታዩበት አጋጣሚ ብዙ ነው። የተጎራበጡት መንገዶቿ መንገደኞችን በጎማ ቆሻሻ ውኃ እየረጩ እግረኛን ከባለመኪና እያጋጩ የሚውሉበት ጀምበር ሞልቷል። እናም ሰውም፣ እራሷ ከተማዋም መንገድ ጠፍቶባቸው ሲደነባብሩ ይታያሉ። የእግረኞች መንገድ የነዳያን፣ የነጋዴዎች ተለጣፊ እና የሱቅ በደረቴዎች መቆሚያ፣ የቆሻሻ መጣያ… ከሆነና የመኪና መንገዱ አደጋን በፉጨት በሚጠራ መልኩ እግረኞች እየተሳቀቁ፣ ሹፌሮች እየተጨነቁ ውለው የሚያመሹበት ህይወት ከሆነ ሸገር በጤናዋ ከወዴት አለች? ያሰኛል። የፖሊሶች፣ የደንብ አስከባሪዎች እና የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ልያዝህ አልያዝም ዘመን ተሻጋሪ ትርኢት (እንደ በሳል የጥበብ ሥራ) ፒያሳን፣ ጊዮርጊስን፣ ለገሃር፣ ሜክሲኮን፣ መርካቶን፣ መገናኛን… እና ሌሎችን ነባር እና አዳዲስ የከተማዋን ሰፈሮች መቼ ይለቃቸው ይሆን? ሙስና ሲቀንስ ብሎም ሲጠፋ እንዳትሉኝ ብቻ.. ቂቂ.. ቂ..

ነፍሰጡሮች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች አቅመ ደካሞች ሁሉ በግርግሩ እና በወከባው የሚደርስባቸውን አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት እና ጫና ላጤነው ሰው ችግሩ ቀለል ብሎ ተንቆ የሚታለፍ ላይሆን ይችላል። እኛ የማንችለው የማንለምደው የለም እና በእለት ተእለት ኑሮአችን እንደ ዋዛ ተዋህዶን እንጂ! መንገድ በጠፋበት መንገድ ስንት ነገር አለ፣ ያጋጥማልም። አይጣል እኮ ነው የዘወትር መሳቀቃችን..

ትናንት ህገወጥ ተብሎ የፈረሰው እና በእግረኛ መንገድ ላይ የተገነባው ሱቅ (ኪዎስክ) ዛሬ እንደ ትናንት ወዲያው በላስቲክ ዳስ ተወጥሮ መሰረት ሲጣልለት፣ በጨረቃ ሲደጋገፍ፣ በድንጋይ ሲወተፍ፣ ጥግ ላይ ሲለጠፍ አላፊ አግዳሚው እንደዋዛ የሚያየው ጉዳይ ነው። ፖሊሱም ደንቡም ሌሎቹን ሲያባርር በዚሁ ደጃፍ ተራምዶ ሮጦ እያለፈ ነው። እረ እንደውም ከህገወጡ ሱቅ ጀርባ ተደብቆ ብቅ ጥልቅ እያለ አጮልቆ ሱቅ አልባዎቹን ህገ ወጦች አድፍጦ ሲጠባበቅ ልታዩት ሁሉ ትችላላችሁ። ህገ ወጥ ሱቅ መገንባት ከተቻለ በእጅ አንጠልጥሎ በጀርባ በደረት አንቀርቅቦ በመሸጥ እንዴት አባራሪ እና ተባራሪ ሊፈጥር ቻለ?! ብላችሁ ማንን እንደምትጠይቁ በዚህ መንገድ በጠፋበት መንገድ እጅግ ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል። ስንት ዘመን ተጠይቆ አልተመለሰምና።

እንደ አቅሟ ፎቅ በዝቶባታል እየተባለች የምትታማው አዲስ አበባ የጽዳት እና የውበቷን ጉዳይ ሁሌም እንደዘነጋችው ነው። ከአራት ኪሎ እና ከታችኛው ቤተመንግስት አጥሮች በቀር ብዙዎቹ የከተማዋ አጥሮች እና ጥጋ ጥጎች እንደ አትክልት ሽንት ሲጠጡ፣ ቆሻሻ ሲደገፋቸው፣ ሲጠጋቸው ነው ውሎ የሚያድረው። መቼ ይሆን እንጦጦ፣ አንድነት፣ ወዳጅነት… ፓርኮችን ባሰብንበት መንገድ አጢነን ለከተማችን ሁለንተናዊ ውበት የምንተጋው?! ካለበለዚያማ “ግማሽ ተላጭቶ፣ ግማሽ ተቀብቶ” አሊያም “… ገልቦ ክንብንብ” ብለው እንዳይሳለቁብን ገረቤቶቻችንና የሩቆቻችን። ከዘመናዊነት ተራርቀን እስከመቼ?

እንደ አቅማችን እንደ ነገሩም ቢሆን የገነባናቸው መንገዶች እኛም ከተማዋም ተጠፋፍተን እስከ መቼ ድረስ ነው የምንዘልቀው? በመኪና አደጋ አንደኛ መሆናችን እንዴት ያን ያህል ላይቆጨን እና እስከዛሬ ምንም ላይመስለን ቻለ? እኛ እኮ ጉደኞች ከሆንን ከረምን። ይህንንም ልምድ አደረግነው እንዴ?! እረ እባካችን! እረ እባካችን! ስንፈተ ንባብ እና ንቃት በጽኑዕ አይጠናወተን! ልባሞች እንሁን እንጂ! በቸር እንክረም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top