የጉዞ ማስታወሻ

ያልተገለጠው ምድር፤ ጉዞ ጅማ

ወደ ቃልኪዳን ምድር እንደሚገሰግስ ምዕመን በፀሎት የጀመርኩት ቀኔ መዐዛው በሰውነቴ መዝለቅ የጀመረው ገና ወደ ከተሞች ሳይገባ ነበር። ጊቤ በረሀን እንዳቋረጥን የጉራጌን መሬት ለመልቀቅ ታላቁ ደዴሳን ቁልቁል እያየሁ በማለፍ ሂደት ላይ ብዕሬን በጣቶቼ መሀል እያሽከረከርኩ ማስታወሻዬ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጅማ (ጂረን) ስጓዝ የማየውን አዲስ ነገር ከስሜቴ ጋር እያዋዛሁ ለመፃፍ ቸኩያለሁ።

Baga Nagaan Duftaani (እንኳን ደህና መጣችሁ)! ፍዘት ይዞኝ ይሁን ስለሌለ ያቋረጥኳቸው ከተሞች ሰኮሩ፣ ጢሮአፈታና ቀርሳን ወረዳን ጨምሮ ፅሁፍ አላየሁም። ብቻ ዝም ብሎ መጓዝ፣ ከሰኮሩ እስከ ጅማ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ በተሰራ አስፋልት መንገድ፣ የተቆላለፉ የሀረግና የዛፍ ቅርንጫፎች “በጋ ነጋን ዱፍተኒን” ተክተው የሠው ልጅ ማቆላለፍ ያቃተውን በተፈጥሮ መንገድ ለመፍታት በሚመስል ሁኔታ ንፁህ አየር እየወሰድን ሄድን። አረንጓዴ መሬት ሲያልቅ ሌላኛው እየተካው ከፍሠሀ ወደ ፍሰሃ ኣይናችን እየተንገዋለለ ቀጠልን። ተጓዦች ከተለያዩ ቦታ እንደመምጣታችን እርስ በርስ እንኳ ለመተዋወቅ እድል የማይሰጥ ውበት መሬቱ ለአይናችን አይናችን ደግሞ ለህሊናችን አቀበለ።

ብዕሬን ኪሴ ዉስጥ ደነጎርኩት። ”የምን ፅሁፍ ነዉ የምከውነው በዚህ ሠዐት?” ብዬ ጥቂት ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ። ለጉዞ ይዛቸው የሄድኩትን መፅሀፍ ቦርሳዬ ውስጥ አድርጌ ቡድኑን እየመራ እንዳለ የእግር ኳስ ደጋፊ በፍቅር የአባ ጎሞር ፣ የአባ ጅፋርን ፣ የከድር ስተቴን ሀገር በስስት እመለከታታለሁ። በ5 አመቱ የጣሊያን ወረራ ጊዜ መብራት የነበራት ከተማ ምን ልትመስል እንደምትችል ብጓጓም ትዕግስት ነበረኝ። እዉነት ለመናገር ጅማ የተከደነች ገነት ነች። ታላቁ “ሙዚቃ” ኤልያስ መልካ

ዝምታሽ በለጣቸው
ቆንጆዎቹን አስናቅሻቸው
ደብዝዘሽ አጋለጥሻቸው

ብሎ የዘፈነላት አንዲት እንስት ለኛዋ ጅማ ቢሆን ይገባታል እላለሁ። ለአለም በቡናዋ ንቃትን ያስተማረው ህዝቧ እርሻውንና መልክዐ ምድሩን በመጠበቁ በእውነቱ ምስጋና ይገባዋል ።

ወደ ገነት በር ቀረብ ለማለት በረሀውን ማቋረጥ ሳይታለም የተፈታ ነው። አምስቱን ቀደሞት ታሪካዊ ግዛቶች ወደ ጅማ እያቀናሁ አስታወስኳቸው። ገነት ጅማ ለመግባት ጊቤን ማቋረጥ ያሻል፡፡ከለምለም ማህፀኗ የሚመነጨውን ቡናዋ ውብ ሀሳቦች እያዋለደኝ ሊሙን ፣ ጉማን ፣ ጎማንና ጌራን ጂረንን ከወንዞች ጊቤ እና ደዴሳን ወንዞች ሰያፍ በመሰንጠቅ ሰፊዋን ጅማ እንደ

ዋቃጉራቻ ፈቃድ ውበቷን በብዕሬ እመጣለሁ፡፡ ማፍራት ከሚችሉት ዛፎቿ ተንጠልጠይ ባንድ ዛፍ ላይ የተለያያ ጣዕም አጋራችኋለሁ። ስልጡን ህዝቦቿን በረከት እዘይራለሁ ። ይበልጥ ደግሞ ኢሉ አባ ቦርም አለ። ሱር ፏፏቴና ሱጴን አስመለክታችኋለሁ ። የተፈጥሮን ሀሳብ እየከታተልኩ እገልፃለሁ ። አሸማ

ሱጴና የዛ ሠው ቤት

ከአምስት አመታት በፊት በተደምኩበት ዝግጅት ላይ ለሬድዮዬ ግዙፍ እንግዳ ስላገኘሁ መቅነዝነዜን አስታውሳለሁ። እንግዳዬ ክልስ መልክ ያለው ሲሆን በርካታ አመታትን በየመን አየር መንገድ በአመራርነት አገልግሏል። ሆኖም ስልኩን ለመውሰድ መጣደፌ ሠውዬው ስለ መምህራንና ስለ ህይወቱ ታላቅ መፅሀፍ ስለነገረኝ ነበር ። ” ሲዖል ግባ ግን አንድ መፅሀፍ መርጠህ ያዝ! ብባል ያለማወላወል ይህንን መፅሀፍ እላለሁ ” ብሎ በእጁ የያዘውን መፅሀፍ አሣየኝ።

መፅሀፉ የደራሲ በዓሉ ግርማ መጽሀፍ “ሀዲስ” ሲሆን ፕሮግራሜ ላይ መቅረብ ያልቻለው እንግዳ ታዋቂው ሀያሲ አብደላ ዕዝራ ነበር ። መሬት ይቅለለውና በተገናኘን ጥቂት ሣምንት ውስጥ ምርጡ ሀያሲ አረፈና የሬድዮ ዝግጅቴ ላይ አልቀረበም። ስለ ሱጴ ቦሮ ውበትና መልከዐ ምድር የነገረበት ሁኔታ ከተማዋን ሳላውቃት እንድናፍቃትና ሀዲስ መጽሐፍን በድጋሚ እንዳነብ እድል ቸረኝ። ከተማዋንም ሳላይ መጽሐፉንም ሳልደግም እነሆ ጊዜ ገስግሶ በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በኩል “ውዴ የመጀመሪያ የስነ ፅሁፍ መምህርህ በዕሉ ግርማን ያፈራሁ ማህፀን የሆንኩትን እኔንና ተመልከተኝ !! ናና መላእክቶቼ የለቀሙትን ጥቁር ወርቅ ቅመስልኝ !! የተገፈፍኩትን ክብር ለአለም ንገር!!” የሚል ጥሪ ቀረበልኝ፡፡ ብዙ ሺህ ሀሣብ አእምሮዬ ዉስጥ ተሰገሠገ ።

እንዳለጌታ ከበደ “የበዕሉ ግርማ ህይወትና ስራዎቹ ” በተባለው መፅሃፉ ልጁን ፣ አማርኛ የማይችለውን ፣ ከሱጴ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ጅምናዳስ በሚባል ህንዳዊ አባቱ ልጅነቱን ተክዶ ረዥም እንባ ያፈሰሰውን በዕሉ አሳይቶናል፤ እናቱ ያደኔ ቲባ ይባሉ

እንደነበረም ተገልጿል። ታላቁ ደራሲ ከዊንጌት እስከ አዲስ አበባ ከአዲስ አበባ እስከሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ዘልቆ ማስትሬቱን አግኝቷል። በስልጣን እርከንም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት አገልግሏል። ሆኖምእራሱ

“የጥቁር ድንግል መሬት ሽታ – የጥቁር አረንጓዴ ድንግል ደን ሽታ – አለም ስትፈጠር የተርከፈከፈ ሸቶ” እንዳላት ሊረሳት አቅም አጥሮት መሬት ላራሹ ለት/ቤቷ ሀዲስን መደበላት። ያቺ ውብና እንከን የሌለባት ምድር ደርቃ ይሆን? ውበቷ ከ40 አመት በኋላ ሟሾ ይሆን?ኮስትሯ ውስጥ ድንቅ የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ይንቆረቆራል። ባለፈው አመት በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ያለፈው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ዘፈን የሆነው ጅራ ተከፍቷል። ጉጉቴ ላይ ሀዘን ተጨመረ። ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ዉስጥ ፊያሜታ፣ አበራ፣ ሀዲስ ፣ ሽታም፣ ጫልቱ የተባሉ ገጸ ባህርያት እየተፈራረቁ ይገለጣሉ። ጉዟችን ቡናን ማእከል ያደረገ ነበርና ጊዜ ካለን ብቻ ሱጴን እንደምናያት ተነገረን።

ያዩ ጫካ ዉስጥ መንገዳችን ጥምዝምዝ እያለ ይጓዛል። መንገደኞች እንደየስሜታቸው ያሻቸውን ይከውናሉ። አንድ ታዋቂ የቡና ባለሁብት ማሳ ሰንደርስ ከመኪናው ወረድን። ባለሀብቱ እየመሩወደ ቡና ማሳ ወሠዱን ። የቡና ተክል፣ ቡና ማድረቂያ ፣ ዝንጅብልና የእንሰት ስብጥር ተመለከትን። ፊታቸው ላይ ፈገግታ የማይጠፋቸው የመቱው ባለሀብት ገቢያቸው ውስጥ ካለው ቁንዶ በርበሬ ከዛፎች እየቀነጠስን እንድንቀምስ አደረጉን። ከምላሴ በፍጥነት ድምፅ በሌለው ሁኔታ አስወገድኩት። ያቃጥላል፡፡

የጉዞው ማገባደጃ ላይ ከማሳው የተቀጠፈ ቡናችንን ጠጥተን ቀጣዩ ጉዟአችን ሱር ፏፏቴ መሆኑን አወቅን። ይሄኔ ነው ወደ ባለሀብቱ ቀርቤ

“እባክዎን ይተባበሩኝ ሱጴ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩ። እንደ ሀዲስ ቱሉ የተጋነነ ሳይሆን የተመጠነ ሆኖም ልባዊ ፈገግታ ሠጥተው “እሺ እወስድሃለሁ ” ብለው እኔና የኢትዮ ኤፍ ኤሙ ጋዜጠኛ ሮቤራን መኪናቸው ውስጥ እንድንገባ ነግረው ወደ ህልማችን በረርን። የገባን ወንዝ ድልድይ አቋርጠን ኮረኮንች የሚተፋውን አቧራ ወደ ኋላ ትተን አፋፍ ላይ ወዳለችዋ

ከተማ ገሠገሰን። ያቺን ከተማ ልናገኛት ይሆን? በዕሉ ግርማ ልጅነቱን ልናይ እንቀርብ ይሆን እያልን ከጋሽ ፈጠነ ወግ ጋር የስነ ፅሁፍ ውቃቤያችን እየመራን እነሆ ተከሰትን።

ዳገቱን ጨርሰን ጉብታው ላይ እንደወጣን “ይሄውላችሁ ሱጴ” ተባልን ፤ ከተማዋ የፈረሰ ከተማ ቅሪት ትመስላለች ፤ ታላቅ ዋርካ ከመንደሮች መሀል በቤት ተከቧል፡፡ ከመኪናች ወረድን ። እኔም ሆንኩ ሮቤራ አምሳሉም (የኢትዮ ኤፍ ኤሙ) የበዐሉን እናት ዘመዶች ቢያንስ ብናገኝ የሚል ሀሳብ አቀረብን። አስጎብኛችን ዘመዶቻቸው ሩቅ መሆናቸውን ነግሮን ወደ ከተማዋ ሽማግሌዎች ቀረብን። ግር ብለን አንዲት መንገድ ዳር ወዳለች ቤት ተጠጋን። የቤቷን ባለቆርቆሮ በረንዳ ተላልፈን ወደ ዉስጥ ዘለቅን ። ተፈላጊው ሠው አቶ ኦሊጅራ ቀንአ ይባላሉ። መምጣታችንን አይተው በፈገግታ ተቀብሉን። እድሜ አያሌ ነገሮችን እንዳስተማራቸው ራሰ በራነታቸው ላይ አፍንጫቸው ስር በቄንጥ ጉብ ያለች የጢም ሽበት ያሳብቃል። የከተማዋ ድንቅ ሜካኒክ እንደነበሩና ስለ ከተማዋ አንዳንድ ነገር ሊነግሩን ተሰናድተዋል። ለእንግዶች ወንበር ሊያመጡ ወደ ሳሎናቸው ዘልቀው በአንድ እጃቸው ወንበር በአንድ እጃቸው ከዘራ ይዘው ሲወጡ ጀማው ተከትሎ ሸክማቸውን አቀለለ።

ወሬው ሁሉ ኦሮሚፋ ሆነ። ሮቤራ መቅረፀ ድምፁን ይዞ ወደ አዛውንቱ ቀሰረ። ኦሮምኛ አለመስማቴን ከግምት አስገብቶ ሮቤራ የተባለውን እንደሚተረጉምልኝ ነገረኝ። ብዙሀ ቋንቋ ባለመሆኔ ራሴን ወቀስኩ። ትሁቱ አዛውንት ስለ ይህች ከተማ ስለነበረችበት ሁኔታ ፣ በዓሉ ግርማ የሚባል ታላቅ ደራሲ አፍርታ ስለመረሳቷ ፣ ደራሲው በስሙ ምንም መታሰቢያ እንደሌለውና የከተማው ህዝብ ገንዘብ እያዋጣ ፎቶውን እንደሚሰቅል ነገሩን። በተለይ ደግሞ ከተማዋ የጠቅላይ ግዛቱ ምክትል በነበረችበት ጊዜ የነበረዉ ሞገሷ እንዲመለሰላት ጎተጎቱ። ባለስልጣን የሆንን እስኪመስለን ድረስ “እየመጣች ዝምብላችሁ አትሂዱ አንድ ነገር አድርጉ!!”

ብለው ሌላ የተመሰጡ ሽማግሌ አይን አይኔን እያዩ ባማርኛ ነገሩን ገለፁልኝ። የምንችለውን እንደምናደርግና የኛ ሀላፊነት የሆነውን እንደምናደርግ ጠቅሰን ስለራሳቸው ሳይሆን ስለከተማዋ ጀንበር መጥለቅ አበክረው የሚናገሩትን አዛውንቶች ተሠናብተን ወደ በዓሉ የተወለደባት ቤት አቧራማውን መንገድ ቁልቁል ተያያዝነው ።

መኪናው ምቾት አለው። ሲጓዝ በሚፈጥረው አቧራ የዛፍ ቅጠሎችን ቡኒ ያለብሳል። አልፎ አልፎ ፈረስ የያዙ ውብ ባላገሮች ይታያሉ። ውስጤ በሀሴት እየተሞላ ፈገግታ ይረጫል። እንደ ካልዲ ፍየል ያልታወቀ ዳንስ በስልት የምትወዛወዘው ነፍሴ ስጋዬን አስንቃኛለች። ባላገር ህይወት ነው ፤ የከተማውን ጭንቀት አስረስቶ ወደ ራስ በጥልቀት ያስመልሳል። እዚህ ማኪያቶ የለም፣ ድራፍት የለም፣ ሴራ ጉንጐና የለም። ያለው ቡና እና ሠላም ብቻ ነው። ሳናስበው መኪናዋን አቶ ፈጠነ አቆመና “ይኸውና ውረዱ” አለን። ወረድን።በእንጨት አጥር የታጠረ ግቢ ዉስጥ ገባን። ሠውን በመውደድ ልህቀት ያሳየው ደራሲ ቤት እነሆ ። የወላለቁ ዴስኮች እዚም እዚያም አሉ። ተወለደባት የተባለቸው ቤት ዝግ ነበረች። ከቤቱ ኋላ እዚያው ጊቢ ውስጥ መሠረተ ትምህርት ይሠጥበት እንዳነበርና እስከቅርብ ጊዜም እንዳገለገለ ሠማን። ጊቢው ውስጥ ሌላኛው ቤት እናት ያደኔ ቲባ ጠጅ ቤት ከፍተው ይነግዱ ነበር። ጥቂት ስንዘዋወር ቆየንና ያደኔ ቲባ ሲሞቱ ያስታመማቸው የእንጀራ ልጃቸውን አገኘን። ልጃቸው ካረፈ በኋላ ችግርን ተጋፍጠው እንዳረፉ ነገረን። የደራሲው ልጆች መጥተው ያውቃሉ ወይ ስንለውም አንገቱን ነቅንቆ “አያውቋትም ሱጴን” አለን። ገረመን። አስቡት ለስንቱ የእንጀራ ምንጭ እንዳልነበር በዕሉአቸው ከሱ ህልፈት በኋላ በህይወት ተስፋ ቆረጡ።

ቀጥለን የአካባቢውን ልጆች አነጋገርን። ህጻናቱ ከአስር እስከ አስራ ሶስት ዓመት ይሆናቸዋል። ብሩህ ነገር የሚታይበት የፊት ገፅታ አላቸው። አማርኛ ስለማይችሉ ጥቂት ቃለምልልስ በኦሮምኛ በሮቤራ በኩል አደረግን፡፡ አንደኛው ልጅ በጭራሽ በ0ሉን የማያውቀው ሲሆን ሁለተኛ ተጠያቂ ግን ” በዕሉን አውቀዋለሁ በጣም አዋቂ ነው ፤ እኔም ሳድግ እንደሱ መሆን እፈልጋለሁ ” ብሎ መለሰልን :: ጉዳያችን እንዳለቀ

ወደ ሱር ጉዞ ጀመርን። ሁለተኛ ዋና ከተማነቷን ከተነጠቀች ወዲህ ጥልቅ እንቅልፍ ላይ ያላቸው ሱጴ ታሳዝናለች። መንፈሷ እንዲጠገን የምትሻው የሰውየው ከተማ” ቁንጅናዬ ይቅር አትመልሱልኝ ለልጄ መታሰቢያ ግን ኑና ሀውልት ኣቑሙልኝ ” ትላለች።hሠው ኖሮ ለሠው የተሠዋው ሠው ትውልድ መንደር

የተቀባው እጅ በሶር (በቾ )

ከውቢቷ ሱጴ መልስ ጉዞአችን ወደ ሶር ፏፏቴ ነበር። በቡና ኤክስፐርትነት የታወቀው የቡድናችን የአብሮነት ጉዞ ያጣፈጠውን አበራን ከተማዋን ስጎበኝ ላደረግልኝ ነገር ጠርቼው ግንባሩን በመሳም ምስጋናዬን ገለፅኩለት። ቦታውን እንደ አይን ብሌኑ ስለሚያውቀውና ድንቅ ጊዜ ለሰጠን ወንድሙ ደበላ አመንቴም አመስግኜ ወደ ሶር ልውሰዳችሁ፡፡

ብሳና ፣ ዋንዛ ፣ ዋርካና ግራር በየቦታው ለአይን እርካታ እየፈጠሩ የበቾን ዳገትና ቁልቀለት ይዘን ጥቅጥቅ ካለው ደን ራሳችንን አገኘን። ያ በማህበራዊ ሚድያ ብዙ ያልተባለለት ሆኖም በፎቶ ሲታይ አቅል የሚያስተውን ውሃማ አካል ገና አልደረሰንበትም። ከጥቂት እርምጃ በኋላ ግን ድምፅ እየገዘፈ ሲመጣ የውሃ መሆኑን ገባን።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታይ ነፍስና ስጋን ወሲብ ያስፈፅማል። አመድማውን መንገድ ለሁለት ሲከፈል የግራውን እንድንይዝ ተነገረን። የግራውን ጠመዝማዛና ቈልቁለታማ መንገድ እየተጓዝን ጥንካሬዬ ተፈተነ ። የአካባቢው ሠዎች በቀላሉ የሚከውኑትን እኔ ከተሜ ተብዬው ከበደኝ። ረዥምና አንሸራታቹን መሬት ሽብሪካዋ እግሬ መቋቋም አቅቷት ወደ ታች ጣለችኝ፡፡ በፍጥነት ሁኔታየን የተከታተለው ሠው ወደ ላይ ስቦኝ በማላውቀው ሁኔታ በኦሮሚፋ አንሾካሸከና ሳቀ፡፡ ቋንቋው ገብቶኛል ። አይዞን መሆኑ ከጥያቄም የሚገባ አይደለም። ለሸለመኝ ፈገግታ በጋራ ቋንቋችን እኔም በመሳቅ አፀፌታዬን መለስኩ። ጥቂት እንደተራመድኩ አሁንም ውልክፍ አልኩኝ። አብሮኝ ያለው የበቾው ቅን ወደ ኋላ ለጠጥ ብዬ ቁልቁለቱን እንድወርድ በምልክት ነገረኝ፡፡ መንፏቀቅ በሚባል አይነት እርምጃ ሶር ሲያጋሳ አየሁት። እይታዬን ከእርምጃዬ ስለተሠናከለ ይመስለኛል እግሬ የማይመቸውን ረግጦ በዛ ምስኪን ሠው ብልሀትና ጥንቃቄ በፍጥነት እየተንደረደሩ መሮጥና መፈጥፈጥ ቀርቶልኛል። ባናገርኩት ፣ ስሜታችንን በተገላለፅን ከገለቶማ ባሻገር ጥቂት ነገር ብለው ብዬ ነበር። በፈገግታ ስሜትን ገለጥኩ።

ግርማ ሞገስ ከሞላው ሶር ግርጌ ደረስን። እንደግሪካዊው ኮምፖዘር ያኒ ሙዚቃ ፏፏቴው ይዘምራል። ሁላችንም አቅላችንን ስተናል። ውሃው ሲወርድ እንደ አመጣጡ የረገና ስክነትን የተላበሰ አይደለም። ተሽሞንሙኖ ተሽሞንሙኖ ድንገት ያጓራል፣ ተሽኮርሙሞ ተሽኮርሙሞ ግርጌው አካባቢ ይመፃደቃል። አረፋ የመሠለ ውሃ እንደ ግድግዳ ለጥ ያለና የህንፃ ደረጃ የመሠለ ጥቁር ድንጋይ ላይ ለሶስትና ለአንድ እየተከፈh ይወርዳል። ብርሀነት ቀለማቸውን ወደ ዉሃው እየተፉ ሀሴትን ለአይን ይመግባሉ። ስክን ያለው ውሃ ሲወርድ ግጭቱ የውሃ እንክብሎችን እየረጨ አበሰበሰን።

ጋዜጠኞች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ፣ ካሜራ ማኖች በተፈጥሮና በህይወት መካከል ባለው መስተጋብር እጅጉን ተመሰጠዋል። ፏፏቴው ዳርቻ ባለው መሬት በስለታማና እርጥብ ድንጋዮች ምክንያት እንደልብ ለመሆን ባያስችልም የሶር ውበት ራሳችንን እንዳንቆጣጠር አድርጎናል። ቪድዩ የሚወስድ ፣ ፎቶ የሚነሣ፣ ያፈጠጠ፣ ከውሃው የሚታጠብ ብዙ ብዙ

በቾ ግን በዝምታ ተውጣለች ።

ግርጌው ጋር የነበረንን ጨርሰን የአካባቢው ማህበረሰብ ወደሚጠብቀን ወደ ፏፏቴው ራስጌ ስንመጣ ቁልቁለት የነበረው ዳገት ሆነና በአራት እግር ተወጣነው።

ውበት ድካምን ቢያስረሳም ድራፍትን ለዚህ አቅመቢስነት ስላበቃኝ እየረገምኩት ለእንግዶች በተዘጋጀችው ዳስ ዉስጥ ከአካባቢው ህዝብ ጋራ ቦታው ፊት ለፊት ለማየት የሚያስችል ሸራ ተዘርግቶልን ተቀመጥን። ራስጌው ላይ ያለው ውሃ ኣይንቀዠቀዥም ። ትዕቢት ያልጎበኘው አረማመድ ኣለዉ። ተመልካቹን በፍቅር የማንበርከክ አቅሙ እያለው ምርጫውን ላንተ ይሠጥሀል። የህይወትን ሪትም በትልቁ መጫወት እየቻለ በከበቡት ሞገሱ ተጋርዶ አሁንም ውስጥ ለውስጥ ይደነፋል። መልኩን ስላልሸጠ መልክ ብቻ ተብሏል፡፡

የበቾ አዛውንቶች፣ ወጣቶች፣ ቅጠልና ዛፎችም ነጋሪት ኣላስጎሠሙም።

አባገዳዎች ከምርቃት በኋላ ባልተንዛዛ ንግግር ስለቦታው ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ የሆነ ነገር እንድንል አሳሰቡ፡፡ የዞኑ ሀላፊዎች “ያያችሁትን ለአለም መስክሩ ” አሉን።

ይህ ሁሉ ሲሆን በቾ ምንም አላለችም። ንግግር ኣለበዛችም።

። የምትፈልገውን ጠብቃ አቆይታለች። ከተፈጥሮ ተስማምታ ታላቁን ምድር ለሀገሬ እንካችሁ ብላ የአእምሮን ሴሎች በእጅ እየዳበሱ የሚያነቁ ቡና አጠጣችን፡፡ አከባቢውን የምትወክል ኣንዲት እንስት ደግሞ በተቀቡ እጆቿ ድንቅ ነገር በማድረግ የበቾን ኦሮሞ መልእክት አስተላለፈች። የበቾ ሠው ከተፈጥሮ ሲማር ለጉድ ነው :: ከጉያው እንደሚፍለቀለቀው የሶር ውሃ ማዕዱ ላይ ስስት አያውቅም ፡፡ ያ ብሩክ እጅ ስለዚ ድንቅ ህዝብ ብዙ ይላል። እህልን ሲሰጥ ለሚቆነጥረው ለራሱ ሲጎርስ ደግሞ ለሚዝቀው ከተሜ በየቀለሙ ማር እየዛቀች ቸረች። እኛም እዛ ደግነት ላይ ጀንበር ስትጠልቅ ምስሉን ሶር ውሃ ላይ እየተመለከትን እንዲህ በማለት ደመደምን። ሶር ይሠራበት፣ ኢንቨስት ይደረግብት ፣ ይጎብኝ !!

* ደራስያን ኑኑ ሶርን እዩ !! እዮና ፃፉ። መፅሀፍችሁን ተጋፍቶ የሚያነብ ታገኛላችሁ።

* ሙዚቀኞች ኑኑ ሶርን ጎብኙ !! እዮና ዘፈን ፍጠሩ ። አልበሞቻችሁ ዘመን ሲሻገር ምስክር ትሆናላችሁ።

* አርክቴክቶች ኑኑ ወደ ሶር ተመልከቱ!! ዲዛይን ምክሩ። ህያው የኪነ ህንፃ ጥበበኞች በናንተ ያልፋሉ።

ተዐምር በመቱ ኢሉ አባ ቦር ታየ።

ከኢሉ አባ ቦሯ መቱ ከዩኒቨርሲቲው አጠገብ ቢሻሪ አለ። ቢሻሪን ማርክስ ቢያያት ቲዎሪ ባበጃጀላት ነበር። ምክንያቱ ወደ በኋላ እንንሳና በቢሻሪ ስለምትገኝ አንዲት መዝናኛ እናንሳ ….

መዝናኛው ሁሉን አቀፍ ነው። ሀይቅ፣ የኢሉ አባ ቦር ባህላዊና ታሪካዊ ምክር ቤት ፣ የህጻናት መጫወቻ እና መመገቢያ ቦታዎች አሉት። ታዲያ ድንገት መዝናኛው ስፍራ ዉስጥ ከሀይቁ የተጠበሱሎትን አሣ እየተመገቡ ፣ የቀረበልዎን ለስላሣ እየጠጡ ፣ በጀልባ ውብ ሀይቅ ላይ መንፈሶን እያደሱ ድንገት አስጎብኝዎ እስረኛ መሆኑን ሲያውቁ ምን ይሰማዎታል ? ከአስር አመት በፊት እየተንሸራሸሩበት ያለው ሀይቅ ፈረስ መጋለቢያ እና እግር ኳስ መጫወቻ

እንደነበርስ ቢሰሙ ? ባንዲት የምዕራብ ኢትዮጲያ ፈርጥ አመራር እስረኞቹ ይህን ደማቅ አሻራ መፍጠራቸውን ቢሰሙስ? የሆነው ግን እንዲያ ነበር።

ኢሉ አባ ቦር ዞን ማረሚያ ለአፍሪካ የተሰጠ ስጦታ ይመስላል። ስለ ብራዚል እስር ቤት አንድን መፅሀፍ ለጨረሰ ታራሚ ከእስራት ቀኑ ላይ 4 ቀን እንደሚቀነስለት ተነግሮን ይደልዎ ብለናል። ከኢትዮጵያ ዞኖች ሁሉ ይህን ሠምታ ያልደነገጠች አንዲት ዞን አለች።

ኢሉ አባ ቦር

ምክንያቱ ደግሞ ልጆቿ ናቸው። በተለይም የመቱዋ አብሪ ኮከብ ወ/ሮ ተናኘ ወልዴን ያፈራው ህዝብ “ኡኡቴ ” ማለቱ አልቀረም። እንስቲቱ ተዐምር ፈጥረዋል። ቢቢሲ ዘሏቸው፣ አልጀዚራ ባላየ ስላለፋቸው፣ የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት ጀርባቸውን ስለሰጧቸው እንጂ ኮማንደሯማ ኦፓልን የሚያስንቅ ማዕድን ስለመሆናቸው ምስክር አያሻውም።እስር ቤት ዉስጥ ህይወት ተስፋ መሠነቅ እንደሚገባ ገብቷቸዋል። ለእስር ቤቱ ገንዘብ ማመንጨት ተስፋው ላይ እርግጠኝነትን ማንበር እንደሆነም ጭምር። ኮማንደሯ እስር ቤቱ ላይ አሰተዳደር ሆነው ሲሾሙ የ10 አመት እቅዳቸው ላይ ሠው ሠራሽ ሀይቅን አስገቡ። የአካባቢውን ሠው አማክረው ጉዞ ጀመሩ። ህዝብ “አለሁ” አላቸው። እስረኛ ድንቅ ነገርን ተባበረ። ሁሉም በምናቡ ተንጫጫ ። ፈረንጅ ሳይመክርበት ሩጫ ተጀመረ። ከዚያ ተዐምራት በመቱ ሠማይ ስር ርችት ፈነጠቀ::

አሀዱ ተብሎ ከእስር ቤቱ ጎን 2003 ዓ.ም በቀን 50 እስረኛ እያሳተፉ የመጀመሪያዋን ጥሪት ዉሃ ቋጠሩ። ዉሃ የሚያቁር ቦታ ላይ ውሃው እንዳይሸሽ ሣርና አፈር ተቆልሎ መሬት ላይ አንድ ሜትር ተከመረ። ሆኖም በ 2004 ክረምት ጎርፍ ህልማቸውን ይዞት ሄደ። ሆኖም ተስፋ አልቆረጡም። ዘመቱበት ። ውሃው እንዳይሸሽ ሣርም፣ አፈርም ድንጋይም ተረበረበ። ዛፎች በአስራ አንድ ሄክታር ርቀት ላይ ተተከሉ፣ ውሃው የሚይዘው ቦታ እንዲሠፋም 3 ሄክታር ተቆፈረ ። በ2009 የምታዮት ሀይቅ ካለመኖር ወደ መኖር ተቀየረ። ፈረንጅ Out of nothing something ይልም የለ ?

ከመጀመሪያው ውድቀት በኋላ ግንቦታው ለተስፋ መቁረጥ መድሀኒት ነው ። ይህን ቦታ ጆርጅ ኦርዌል ቢያየው ምናለ ? “ሠው ወተት አይሠጥም ፣ እንቁላል አይጥልም፣ ማረሻ አይጎትትም፣ ጥንቸል ለመያዝም ቀርፋፋ ነው። ሆኖም የእንስሳት ጌታ ነው።” ያለበትን አንደበት ይረግመው ነበር። ካለም ከቢሻሪ ውጭ ሊል ይችላል እንጂ አይጠቀልልም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ተዐምር በመቱ ማረሚያ ቤት መታየቱ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top