ታሪክ እና ባሕል

የጥምቀት በዓል አከባበር ከአይህዳ እስከ ጃን ሜዳ

(34 .– 1966 .)

በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ኃይማኖት አስተምህሮ ሁለት ዓበይት የአደባባይ በዓላት አሉ፡፡ የጥምቀትና የመስቀል በዓላት፡፡ በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል ለረጅም ዘመናት ሲከበር የቆየ እንደሆነ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ በየዘመናቱም በበዓሉ የአከባበር ስርዓቶች ላይ የተለያዩ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹን ቀጥለን እንመልከት፡፡

የጥምቀት በዓል የለውጥ አንጓዎች፤ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል መታወቅ የጀመረው የክርስትና ኃይማኖት ወደ አገሪቷ ከመግባቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ34 ዓ.ም የንግስት ሕንደኬ ዣንደረባ የሆነው ባኮስ በቅዱስ ፊልጶስ አማካኝነት ተጠምቆ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ የጥምቀት ስርዓት በአክሱም ቤተ መንግስት በዣንደረባው ባኮስ አማካኝነት ከተዋወቀ በኋላ ከአክሱም ከተማ በ6 ኪሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አይህዳ ተብሎ በሚጠራ ባህር አጠገብ መከበር እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ በዚህ ስፍራ መከበር የተጀመረው የጥምቀት በዓል ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎች መስፋፋት ጀመረ፡፡

የጥምቀት በዓል በአብርሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግስት መደበኛ የአከባበር ስርዓት፣ ህግና ደንብ ተበጅቶለት በቀኖና ቤተክርስቲያን እንዲከወን ተደረገ፡፡ ይህም በዓሉ ይበልጥ እንዲጠናከር ምክንያት ሆነ፡፡ የጥምቀት በዓል በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግስት ደማቅ መልክ እንደያዘ ይነገራል፡፡ ይህም ቅዱስ ያሬድ ለጥምቀት የሚሆን የዜማ ድርሰት ማዘጋጀቱና የጥምቀት በዓል ጥር 11 ቀን በውኃ አካላት ዳር አክብረው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው ቤተ መቅደስ እንዲመለሱ መደረጉ ነው።

ንጉሥ ላሊበላ ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻቸውና በተናጠል በሚቀርባቸው ቦታ ሲፈጽሙት የነበረውን የጥምቀት ስርዓት የሚያስቀር ደንብ አወጡ፡፡ በተናጠል የሚፈጽሙት የጥምቀት ስርዓት ቀርቶ በምትኩ በአቅራቢያ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት ተሰባስበው በአንድ ስፍራ፣ በአንድ ጥምቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። የጥምቀት በዓለ ስርዓትን በአንድ ስፍራ ለመፈጸም እንዲያመች በላሊበላ ፍልፍል ቤተክርስቲያናት አቅራቢያ በሚገኝና የዮርዳኖስና የሔኖን ወንዝ አምሳያ የሆኑ ሁለት ጅረቶች በሚገናኙበት ሸለቋማ ስፍራ መከበር ተጀመረ፡፡ በጥምቀተ ባህር ስፍራ ላይም በድንጋይ የተቀረጸ ትልቅ መስቀል አስቀረጸ፡፡ ይህ በመሆኑ የበዓሉ አከባበር የተሻለ ቅንጅትና ድምቀት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በአጼ ናዖድ ዘመነ መንግስት ማንኛውም የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ ታቦተ ህጉ ወደ ባህረ ጥምቀቱ በሚወርድበትና ከባህረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደስ በሚመለስበት ጊዜ ማጀብ እንዳለበት አዋጅ ታወጀ፡፡ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት ሁለት አበይት ውሳኔዎች ተግባራዊ ተደረጉ፡፡ እነሱም፣ አንደኛ፣ ታቦታት ወንዝ ወርደው በእለቱ ወደ መንበራቸው ቤተ መቅደስ እንዳይመለሱ መወሰኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዋዜማው ጥር 10 ቀን የከተራ በዓል ሆኖ እንዲከበር መደረጉ ነው፡፡ ከዚህ ዘመን ጀምሮ በከተራ እለት ታቦታቱ ከያሉበት ቤተክርስቲያን ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በምዕመናን ታጅበው በአካባቢያቸው በሚገኝ ባህር ወይም ወንዝ ዳር መሄድ ጀመሩ፡፡ ታቦታቱም እዛው ባህረ ጥምቀቱ ስፍራ ማደር ጀመሩ፡፡

የጥምቀት በዓል በዚህ መልክ በደማቅ ስርዓት ማክበር እየተጠናከረ ሄደ፡፡ በየዘመኑ የነበሩ ነገስታት የጥምቀት በዓላትን ያከብሩባቸው የነበሩ ስፍራዎች በታሪክ ሰነዶች ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አጼ ሠርጸ ድንግል የጥምቀት በዓልን በጣና ሀይቅ ላይ ማክበራቸውን ዜና መዋዕላቸው ይገልጻል፡፡ የጥምቀት በዓል እስከ አጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ሳይቋረጥ በየአመቱ በድምቀት ይከበር ነበር፡፡ ይሁንና በዚህ ዘመን የአሕመድ ኢብን አል ጋዚ (በተለምዶ አጠራር ግራኝ አሕመድ) ወረራ ሳቢያ የጥምቀት በዓል በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለአስራ አምስት አመት ያህል በከፊልም ሆነ በሙሉ ለመቋረጥ ተገደደ፡፡

በግራኝ አሕመድ ወረራ ምክንያት አጼ ልብነ ድንግል መናገሻ ከተማቸውን ቦካን ለቀው ለስደት ተዳረጉ፡፡ አጼ ልብነ ድንግል በስደታቸው ወቅት የጥምቀት በዓልን በአክሱም አንድ ጊዜ ማክበራቸውን ዜና መዋዕላቸው አስፍሯል፡፡

በ17ኛው ክ/ዘመን አጼ ፋሲል ባስገነቡት ገንዳ ላይ የጥምቀት በዓል ማክበር ተጀመረ፡፡ በአንድ ማዕከል ይከበር የነበረው የጥምቀት በዓል በዘመነ መሳፍንት ወቅት በነበሩ በየአካባቢው በሚገኙ መሳፍንት የመኖሪያ አካባቢ መከበር በመጀመሩ በየአካባቢው በርካታ የጥምቀት ማክበሪያ ማዕከላት ተቋቋሙ፡፡

ጥምቀት በጃን ሜዳ፤ በአጼ ምኒልክ ዘመን

በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት አንኮበር፣ እንጦጦና ፍል ውኃ ሜዳ ንጉሱ የጥምቀት በዓል የሚያከብሩባቸው ስፍራዎች ነበሩ፡፡ አጼ ምኒልክ ቤተ መንግስታቸውን በእንጦጦ ከገነቡ በኋላ በ1888 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን በመውረሯ ምክንያት በ1888 ዓ.ም በንጉሱ መናገሻ እንጦጦ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ንጉሱ ወደ ጦር ዘመቻ በመሄዳቸው ምክንያት አለመገኘታቸውን ዜና መዋዕላቸው ያሳያል፡፡

የጥምቀት በዓል በየአመቱ ጥር 11 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች በድምቀት ይከበራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በዓሉ ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል ጃን ሜዳ አንዱ ነው፡፡ ጃን ሜዳ፣ የጃንሆይ ሜዳ ወይም የንጉስ ሜዳ ማለት ነው፡፡ ስፍራው ይህን ስያሜ ያገኘው በ1895 ዓ.ም ሲሆን ጃን ሜዳ ብለው የሰየሙት አጼ ምኒልክ ናቸው፡፡ ጃን ሜዳ ለተለያዩ ኃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁነቶች መከወኛ ሕዝባዊ ቦታ እንዲሆን ወደ ስምንት መቶ ሺኽ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት ለብቻው ተከለለ፡፡

በጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል መቼ መከበር እንደተጀመረ የሚገልጽ መረጃ አላገኘሁም፡፡ ይሁንና በ1903 ዓ.ም አጼ ምኒልክ የጥምቀት በዓልን በጃን ሜዳ ሲያከብሩ የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎች አሉ፡፡ እነዚህ የፎቶ ማስረጃዎች የጥምቀት በዓል በጃን ሜዳ ንጉሱ ተገኝተው ያከብሩ እንደነበር ማሳያ ናቸው፡፡ በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት የጥምቀት በዓል በጃን ሜዳ ሲከበር የገና ጨዋታ አንዱ የበዓሉ ድምቀት ነበር፡፡ በወቅቱም በጃን ሜዳ የገና ጨዋታ ከታህሳስ መጀመሪያ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ በየእለቱ ይካሄድ ነበር፡፡

ጥምቀት በጃን ሜዳ፤ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን

በጃን ሜዳ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በርከት ያሉ መረጃዎች የሚገኙት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ወደ ስልጣን ከመጡበት ወቅት ጀምሮ ነው፡፡ በወቅቱ የጥምቀት በዓል እንዴት እንደተከበረ የታሪክ ምስክር ከሆኑት የመረጃ ምንጮች መካከል ብርሃንና ሰላም እና አዲስ ዘመን ጋዜጦች ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡ ከጋዜጦች፣ ከመዛግብትና ከተለያዩ ግለሰቦች በቃለ መጠይቅ ያሰባሰብኳቸውን መረጃዎች መነሻ በማድረግ የጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል አከባበር በዘመኑ ምን መልክ እንደነበረው በጥቂቱ ለማሳየት እሞክራለው፡፡

በከተራ እለት (ጥር 10) በየቤተክርስቲያኑ ያሉ ታቦታት በካህናትና በምዕመናን ዝማሬ፣ በዘፈንና በሆታ ታጅበው ወደ ማደሪያ ቦታቸው ጃን ሜዳ ይሄዳሉ፡፡ በዚህ እለት አጼ ኃይለ ሥላሴ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ታቦታትን ከኋላ አጅበው ወደ ጃን ሜዳ ይሄዳሉ፡፡ በማግስቱም ጥር 11 ጃን ሜዳ በመሄድ ታቦታትን አጅበው ይመለሳሉ፡፡ በወቅቱ የነበረው ስርዓትና የንጉስ አጀብ ልዩ ነበር፡፡

በወቅቱ ታቦታት ወደ ጃን ሜዳ ሲሄዱ፣ ከፊት ለፊት በርካታ ቁጥር ያለው ወታደር፣ በወታደራዊ ልብስ አምሮና አጊጦ በሰልፍ ይሄዳል፡፡ ከወታደሮቹ ቀጥሎም በወቅቱ ሰይፍ ጃግሬ በመባል የሚጠሩ የክብር ዘበኛ አንጋቾች ይከተላሉ፡፡ ሰይፍ ጃግሬዎች ወታደራዊ ልብስ ለብሰው፣ ጠመንጃቸውን በቀይ መለዮ አስጊጠው በሰልፍ ይሄዳሉ፡፡ ከሰይፈ ጃግሬዎች ቀጥሎም ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፣ ቀሳውስቱና ዲያቆናት የወርቅ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ታቦታትን ይዘው በመካከል ይሄዳሉ፡፡

ከቀሳውስቱና ዲያቆናት ቀጥሎ ንጉሱ ይከተላሉ፡፡ ንጉሱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽ በነበሩበት ወቅት የወርቅ እቃ ባስጨነቃት በቅሎ ተቀምጠው ነው፡፡ እሳቸው በሚሄዱበት ወቅት ፀሐይ ወይም ዝናብ እንዳይመታቸውና ክብራቸውን ለመግለጽ በወርቅ ሙካሽ የተሰራ፣ ባለ ወርቅ አጫዋች ያለው፣ በልዩ ዲዛይን የተሰራና ለነገስታት የሚገባ ቀይ ጥላ አስይዘው ነው፡፡ ለጃንሆይ የሚያዘው ጥላ ባለወርቅ መርገፍ ግምጃ ጥላ በመባል ይጠራል፡፡ ከንጉሱ ቀጥሎም ክቡራን መኳንንት እንደ ማዕረጋቸው ራቅ ራቅ ብለው አጅበው ይጓዛሉ፡፡

ንጉሱ በቅሎ ላይ ሆነው በቀኝ መትረየስ አንጋች ዘበኛ ወታደር ሰማያዊ ኮት ለብሶ፣ ነጭ ሱሪ ታጥቆ፣ እምቢልታና መለከት እየተነፋ (እየተንጠረጠረ)፣ ነጋሪትም እየተጎሸመ ይታጀባሉ፡፡ በወቅቱ ነጋሪት መችዎች ቀይ ኮት የሚለሰብሱ፣ ቀይ ጃዊ የሚጠመጥሙ ናቸው፡፡ ነጋሪት መችዎችም ከፊት ለፊት ሁለት ሰንደቅ ዓላማ ይይዛሉ፡፡

ንጉሱ ታቦታትን ጃን ሜዳ አድርሰው በተመሳሳይ አጀብ ወደ ቤተመንግስታቸው ይመለሳሉ፡፡ ጥር 11 በተመሳሳይ አጀብ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ይሄዳሉ፡፡ ንጉሱ ታቦታቱ ወዳሉበት ስፍራ ተመልሰው በተዘጋጀላቸው ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣሉ፡፡ ንጉሱ በታላቅ ግርማ ሆነው አጎበር ባለው ወንበር ሲቀመጡ በኃይማኖት አባቶችና በመኳንንት ታጅበው ነው፡፡ ንጉሱ በጃን ሜዳ ልዩ የማረፊያ ስፍራ በድንኳን ይዘጋጅላቸዋል፡፡ በድንኳኑ ውስጥም በመርገፍ የተለየ ልዩ ክፍል ይዘጋጃል፡፡ በክፍሉ ውስጥ ቀይ ምንጣፍ ይነጠፋል፣ ዙሪያውን በአበባ የተሽቆጠቆጠና በአጎበር የተሸፈነ ዙፋን ተዘጋጅቶላቸው እንዲያርፉ ይደረጋል፡፡

ንጉሱ ጥምቀት ላይ በተዘጋጀላቸው ስፍራ ሲቀመጡ በቤተ ክርስቲያኗ አቡን አማካኝነት በመስቀል ተባርከው በዙፋናቸው ላይ ይቀመጣሉ፡፡ አቡኑም ንጉሱን ሲባርኳቸው መስቀሉን ወደ ፊት በማስተኛት ነው፡፡ ከእሳቸው በኋላ አጃቢዎቻቸው እንደማዕረጋቸው በቅደም ተከተል ይባረካሉ፡፡ የንጉሱ አጃቢዎች በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ ሲቀመጡ ያላቸውን ማዕረግ፣ ስልጣንና የቤተሰብ ቀረቤታ መሰረት በማድረግ ነው፡፡

ንጉሱ፣ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ወቅት ከእሳቸው በቀኝ በኩል አቡነ ማቲዎስ፣ በግራ በኩል እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ክቡር ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስና ሌሎችም መኳንት አብረዋቸው ይቀመጣሉ፡፡ በንጉሱ አጎበር ፊት ለፊት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይውለበለባል፡፡ ጥምቀተ ባህሩም በአቡነ ማቲያስ ይባረካል፡፡ በአቡኑ አማካኝነት ንጉሱና መኳንንቱ ጸበል ከተረጩ በኋላ፣ ኃይማኖታዊ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ታቦታቱም በአጀብ ወደ ቤተክርስቲያናት ይመለሳሉ፡፡

በ1918 ዓ.ም በጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ሲከወን በስፍራው የተገኙት አድባራት ስድስት ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት ታቦታት ያድሩ የነበረው በቀበና ወንዝ አጠገብ ነው፡፡ ጥምቀቱም ይካሄድ የነበረው በወንዙ ዳር ነበር፡፡ ታቦታቱ በስፍራው ሲደርሱ ክቡር ፊታውራሪ ገብረ ማርያም ጭፍሮቻቸውንና የመትረየስ ዘበኞችን አሰልፈው በታላቅ አቀባበል ታቦታትን ይቀበሉ ነበር፡፡

በዚህ አመትም፣ ሊጋባ ወዳጄ፣ የግቢ ዘበኛ አለቃ ፊታውራሪ ገብረ ማርያም፣ ባሻ ግዛው፣ አጋፋሪ ወልደ ማርያምና ግራዝማች ከልክሌ ከተከታዮቻቸው ጋር እንደ ማዕረጋቸው ሽልማታቸውን ለብሰው፣ ክንዳቸውን አውጥተው፣ ዘንጋቸውን ይዘው፣ ጠመንጃቸውን አንግተው፣ ጎራዴያቸውን ታጥቀው ስርዓቱን ይመሩ እንደነበር ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ አስፍሯል፡፡

በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ቀደም ሲል ከተከበሩ በዓላት የ1918 ዓ.ም በዓልን ልዩ የሚያደርገው ሁኔታ እንደነበር አስፍሯል፡፡ ይህም አለቃ ኢዮብ ያስተማራቸው ፈረሰኞች ነጭ ኮት፣ ነጭ ባርኔጣ አድርገው ባማረ ሰልፍ ተሰልፈው ለንጉሱ በጡሩንባ የክብር ሰላምታ መስጠታቸው ነበር፡፡

ጥምቀት በጃን ሜዳ፤ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት

የጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ላይ ለውጥ ከፈጠሩ ታሪካዊ ሁነቶች መካከል አንዱ የፋሽስት ጣሊያን የአምስት አመት ወረራ ነው፡፡ ጣሊያን ሀገራችንን በወረረ ወቅት እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ከንጉሱ ጋር ተሰደዱ፡፡ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ አቡኑ ካረፉ በኋላ የጃን ሜዳን ስርዓተ ጥምቀት ይመሩ ነበር፡፡ በፋሽስት ጣሊያን አማካኝነት አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ተገደሉ፡፡ የዝቋላ አቦ ቤተክርስቲያንና የደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቃጠሉ፡፡ በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ እንግልትና መከራ ተከሰተ፡፡

በፋሽስት ጣሊያን አማካኝነት አቡነ ቄርሎስ እጨጌ ተብለው ተሾሙ፡፡ በጃን ሜዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ እጨጌው ህዝቡ ለጣሊያን እንዲያድር ቀሰቀሱ፡፡ ቀሳውስቱ ለጣሊያን በመቀስቀሳቸውም የገንዘብና የአልባሳት ስጦታ ያገኙ ነበር፡፡ በጣሊያን ሀገርም ጉብኝት ይመቻችላቸዋል፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት የተለየ አመት እንደሆነ የሚነገረው የ1930 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ነው፡፡ በዚህ አመት የሸዋ አርበኞች መሪ ራስ አበበ አረጋይ አቡነ ገብረ ጊዮርጊስን የኢትዮጵያ እጨጌ ብለው መረጡ፡፡ በተመሳሳይም አቡነ አብርሃም በማረፋቸው፣ በእሳቸው ምትክ ፋሽስት ጣሊያን አቡነ ዮሐንስንና አቡነ ፊሊፖስን የኢትዮጵያ እጨጌ ብሎ በመስከረም ወር ላይ ሾማቸው፡፡

በዚህ አመት በተከበረው የጃን ሜዳ ጥምቀትም ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት የኢትዮጵያ እጨጌዎች መሪነት የተከበረ ታሪካዊ የጥምቀት በዓል እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተመሳሳይም አርበኞቹ ባሉበት አካባቢ አቡነ ገብረ ጊዮርጊስን እጨጌ ብለው በመሾማቸው፣ ኢትዮጵያ በጥቅሉ በሶስት እጨጌዎች እንድትመራ ሆነ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በተከበሩ የጥምቀት በዓላትም በሶስት እጨጌዎች የተመራ የመጀመሪያው በዓል ሆኖ ታሪክ መዝግቦታል፡፡

በጣሊያን ወረራ ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ መከራ የደረሰበት ነው፡፡ በርካታ ክርስቲያኖች በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ተጨፍጭፈዋል፡፡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡ ነዋየ ቅዱሳት ወድመዋል፡፡ ከወረራው በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በፓሪስ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ 2,000 ቤተክርስትያናት፣ ነዋየ ቅድሳት፣ መዛግብትና ስዕሎች ወድመዋል ብላ ሪፖርት አቅርባለች፡፡

ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ አጼ ኃይለ ስላሴ ጥምቀት በዓልን ለማክበር ሲመጡ አዘውትረው ቡላ መልክ ያለው ገበርዲን (በወቅቱ የነበረ የወታደር ልብስ) ከነማዕረጉ ይለብሳሉ፡፡ ንጉሱ በወታደራዊ ልብሳቸው ላይ የማርሻል የማዕረግ ደረጃን የሚያሳዩ ምልክቶች ያደርጋሉ፡፡ አጼ ኃይለ ስላሴ የማርሻል ማዕረግ ማድረግ የጀመሩት በጥር 24 ቀን 1957 ዓ.ም የእንግሊዝ ንግስት ኤልሳቤት ከባለቤታቸው ፊሊፕ ጋር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በመጡበት ወቅት የጦር ሰራዊት ማርሻል ማዕረግ በንግስት ኤልሳቤት አማካኝነት ከእንግሊዝ መንግስት ከተሸለሙ በኋላ ነው፡፡

ንጉሱ በወታደራዊ ልብሳቸው ላይም ነጭ ካባ (በወቅቱ አጠራር መንጠልያ ይባላል) ይደርባሉ፡፡ ነጭ ቀለም ያለው ክብ የቡሽ ኮፍያም በብዛት ያደርጋሉ፡፡ የንጉሱ አልጋ ወራሽም የሙሉ ጄነራል ማዕረግን የሚያሳይ ሙሉ የወታደር ልብስ፣ በላዩ ላይ ደግሞ ነጭ ካባ አዘውትረው ይለብሳሉ፡፡ ልዑል ራስ ካሳ ሁልጊዜ የሚለብሱት ጥቁር ካባ ነበር፡፡

በወቅቱ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ጠባቂ የነበሩት የክብር ዘበኛ አባላት የራሳቸው የአለባበስ ስርዓት ነበራቸው፡፡ እነሱም የሚለብሱት እጀ ጉርድ ሸሚዝ፣ ገምባሌ፣ ቁምጣ፣ ጥቁር ቀበቶ፣ ጥቁር ጫማና ክብ ቡሽ ባርኔጣ ሲሆን በባርኔጣው በቀኝ በኩል አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ መሀሉ ላይ የአንበሳ ምስል ያለው ባንዲራ አለው፡፡ የክብር ዘበኛ አባላት በቡሹ ኮፍያ አናት ላይ እንዲሁም በግራና በቀኝ ትከሻቸው ላይ ወደ ታች የሚወርድ የአንበሳ ጎፈር አድርገው እንደማዕረጋቸው በቅደም ተከተል የንጉሱን ድንኳን ይጠብቃሉ፡፡

የክብር ዘበኛ ጦር በስድስት ሻለቃ የተቋቋመ ነው፡፡ ተራ የደረሰው ሻለቃ በጥምቀት በዓል ወቅት በየአመቱ ልዩ ወታደራዊ ሰልፍ ያካሂዳል፡፡ በዕለቱም የክቡር ዘበኛ አባላት ልዩ ልብሳቸውን ከነማዕረጋቸው በመልበስና ጠመንጃቸውን በትከሻቸው ላይ በማድረግ ንጉሱን ግራና ቀኝ በሰልፍ አጅበው ወደ ጃን ሜዳ ይሄዳሉ፡፡ በወቅቱ የነበሩት የክብር ዘበኛ አባላት በሰውነት አቋማቸው ተመርጠው የሚገቡ ሲሆን አብዛኛዎቹ ረጅም፣ ወፍራምና ሰውነታቸው ግዙፍ ነበር፡፡

ለጥምቀት በዓል ከክብር ዘበኛ፣ ከፖሊስ፣ ከጦር ሰራዊትና በከተማ ውስጥ ታዋቂ የሆኑ ፈረሰኞች ተመርጠው የፈረስ ግልቢያና የፈረስ ጉግስ በጃን ሜዳ ይጫወታሉ፡፡ በዕለቱም ከፈረስ ጉግስ በተጨማሪ የገና ጨዋታ በቡድን በቡድን በመሆን ይጫወታሉ፡፡ ቡድኖቹም ከተለያዩ የጦር ክፍሎችና ከከተማው ነዋሪዎች የተመረጡ ናቸው፡፡ የገና ጨዋታው በሁለት መንገድ ይካሄዳል፡፡ አንደኛው በእግር በመሮጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በፈረስ ላይ በመሆን የሚጫወቱት ነው፡፡ በእለቱ የገና ጨዋታን በእግርና በፈረስ የሚጫወቱ ሲሆን ተጋጣሚዎቹም በቡድን ተለይተው ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታውን የሚያስጀምሩት የአዲስ አበባ ከንቲባ ናቸው፡፡

ከጥምቀተ ባህሩ ወደ ቤተክርስቲያናት የሚሄዱ ታቦታት በአንድ ላይ በምዕመናን እልልታና ጭፈራ እንዲሁም በካህናት ዝማሬ ታጅበው ከጃን ሜዳ ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና መኳንንት ታቦታትን ከኋላ አጅበው ይሄዳሉ፡፡ ታቦታቱ አንበሳ ግቢ (የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት) ጋር ሲደርሱ የማሳረጊያ ጸሎት ይጸለይና የተወሰነ እረፍት ያደርጋሉ፡፡ ወደ አራት ኪሎ፣ ወደ ስድስት ኪሎ፣ ወደ ፒያሳ መስመር የሚሄዱ ታቦታትም ስንብት ያደርጋሉ፡፡ ታቦታቱ ሲሰናበቱም ታቦተ ህጉን የተሸከሙ ካህናት ፊት ለፊት ይቆሙና ሶስት ጊዜ ከእግራቸው ወደ መሬት ሸብረክ በማለት ነው፡፡

ጃንሆይ የቅዱስ ማርቆስን ታቦት አስገብተው ከግቢው በኋላ በኩል ባለው መውጫ ወደ ቤተ መንግስታቸው ይገባሉ፡፡ እሳቸው ቤተመንግስታቸውን ከገነተ ልዑል ወደ ኢዩቤልዩ ካዘዋወሩ በኋላ የመድሃኒዓለምን (መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል) ታቦት መሸኘት ጀመሩ፡፡ በማግስቱ በጃን ሜዳ ተገኝተው የካ የሚገኘውን የሚካኤል ታቦት ያስገባሉ፡፡

በታህሳስ 4 ቀን 1953 ዓ.ም በአቶ ግርማሜ ነዋይ፣ በብርጋዴል ጄኔራል መንግስቱ ነዋይና በሌትራል ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ አማካኝነት የክብር ዘበኛ አባላት ያካሄዱት መፈንቅለ መንግስት በጦር ሰራዊትና በስሩ የሚገኙ የምድር ጦር ሰራዊት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የአየር ኃይል ሰራዊት እንዲሁም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት ባካሄዱት ዘውዱን የመጠበቅና ለንጉሱ ያላቸውን ታማኝነት ለመግለጽ ባካሄዱት የመከላከል እርምጃ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ከሸፈ፡፡

መፈንቅለ መንግስቱ ከከሸፈ በኋላ ተሳታፊ የነበሩት የክብር ዘበኛ አባላት በጦር ሰራዊት፣ በፖሊስና በፈጥኖ ደራሽ አባላት ከያሉበት እየተለቀሙ ሲገደሉና ሲታሰሩ ቆዩ፡፡ በሕይወት የተረፉትም ክብር ዘበኛ አባላት መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡና ለመንግስት እጅ እንዲሰጡ አዋጅ ተነገረ፡፡ አባላቱም በአዋጁ መሰረት ለመንግስት እጅ ሰጥተው እስር ቤት ገቡ፡፡ ጃንሆይም ከታሰሩት አብዛኛዎቹን ‹‹ወታደር ታዛዥ ነው፣ እነሱ ምን አደርጉ፣ አለቆቻቸው ያዘዟቸውን ነው የፈጸሙት፡፡›› በማለት ምህረት አድርገውላቸው፤ በኤርትራ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በባሌ፣ በትግራይና በሌሎች ቦታዎች በጦር ሰራዊት ስር ተበታትነው እንዲሰሩ ተመደቡ፡፡

ከታህሳስ ግርግር በኋላ በዚሁ ዓመት በጥምቀት በዓል ላይ ጃንሆይን ያጅቧቸው የነበሩ የክቡር ዘበኛ አባላት በግርግሩ ምክንያት በመበተናቸው በጦር ሰራዊትና በፖሊስ አባላት ተተኩ፡፡ የክብር ዘበኛ ጦር ድጋሚ እስከሚቋቋም ድረስም ጃንሆይ በጦር ሰራዊትና በፖሊስ አባላት ይታጀቡ ነበር፡፡ በግርግሩ ምክንያት በተገደሉ ታላላቅ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አርበኞችና መኳንንት በመገደላቸው ምክንያት ህዝቡ ሀዘኑን ለመግለጽ በዚህ ዓመት የተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ የነበረው ባህላዊ ሙዚቃና ጭፈራ የተቀዛቀዘ ነበር፡፡

በ1956 ዓ.ም በተፈሪ መኮንንና በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪዎች አማካኝነት በምስካየ ኀዙናን ቤተክርስትያን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋቋመው የ‹‹ተምሮ ማስተማር›› ማህበር ተማሪዎች አማካኝነት የጥምቀት በዓል ልዩ ድምቀት መፍጠር ጀመረ፡፡ የተምሮ ማስተማር ተማሪዎችም በጥምቀት በዓል ላይ ልዩ ልዩ መዝሙሮችን በማቅረብ፣ የተለያዩ ድራማዎችን በማሳየት፣ አንድ አይነት ልብስ ለብሰው ታቦታትን ማጀብ፣ በጃን ሜዳ ውስጥ ከእንጨት በተሰራ ማማ ላይ በመሆን ለህዝቡ መንፈሳዊ ትምህርት ማስተማርና ባማረ ሰልፍ መዝሙር ማቅረብ ጀመሩ፡፡

ከተምሮ ማስተማር ማህበር ተማሪዎች በተጨማሪ የክቡር ዘበኛ አንበሶችም ለጥምቀት በዓል ልዩ ድምቀት ይሰጡ ነበር፡፡ እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ ሞላ በሚል ስያሜ የሚታወቅ አንበሳ ታቦታትን በግልጽ መኪና በመሆን ያጅብ ነበር፡፡ ሞላ፣ ከደቡብ ኦሞ ከበና ጫካ፣ ከማጎ ብሔራዊ ፓርክ የመጣ ደቦል ነው፡፡ ሞላ በጃንሆይ ትዕዛዝ በአባታቸው በባላምባራስ ዶሪ ወልኪ አማካኝነት በልጅነቱ ተይዞ እንደመጣ ፊታውራሪ መኮንን ዶሪ በአሻም ቴሌቪዥን፣ በአናርጅ እናውጋ ፕሮግራም በሰጡት ቃለመጠይቅ ሰምቻለው፡፡

በወቅቱ ሞላ የተባለው አንበሳ ሚስቱን በክርኑ መትቶ ገድሏል እየተባለ በስፋት ይወራ ነበር፡፡ ሞላ ከሞተ ከጥቂት አመታት በኋላ መኩሪያ በሚል ስያሜ የሚታወቅ አንበሳ እስከ ደርግ ዘመነ መንግስት ድረስ ለጥምቀት በዓል ታቦታትን ያጅብ ነበር፡፡

ሞላ ከሞተ በኋላ፣ በ1961 ዓ.ም. የጦር ሰራዊት ቴክኒክ ክፍል (በአሁኑ አጠራር ሲግናል) ወንድና ሴት አንበሶችን በብረትና በቃጫ ክር ሰርተው ለጥምቀት በዓል በክፍት መኪና ታቦታትን እንዲያጅቡ አድርገዋል፡፡ ከቃጫ ክር የተሰሩት አንበሶችም ከትክክለኛ አንበሳ የተቀዳ ድምጽ እንዲያወጡ ተደርጓል፡፡ አንበሶቹ ያሉበት መኪና ላይ ወደ ላይ የሚወጣ ሀዲድ መሰል ነገር ነበረው፡፡ ኦፕሬተሩ ከመኪናው ውስጥ ሆኖ ማሽኑን ጫን ሲለው መጀመሪያ ወንዱ አንበሳ ከወገቡ በላይ ይወጣና ያገሳል፡፡ቀጥሎም ወንዱ አንበሳ ዝቅ ይልና ሴቷ አንበሳ ከወገቧ በላይ ትወጣና ታገሳለች፡፡ በዚህ መልኩ ተራ በተራ እየወጡ በማጋሳት ለበዓሉ ታላቅ ድምቀት ይፈጥሩ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ህዝቡ ትክክለኛ የተፈጥሮው አንበሳ እንደሆነ እንጂ ከቃጫ ክር የተሰራ አንበሳ እንደሆነ አያውቅም ነበር፡፡

ከ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ በተለምዶ ራስ ካሳ ሰፈር የሚገኘው የሚካኤል እና የካ ሰፈር የሚገኘው የሚካኤል ቤተክርስቲያናት ካህናት በጥምቀት በዓል ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ታቦታቱ ጃን ሜዳ መምጣት አቆሙ፡፡ ሁለቱም እዛው በደብራቸው አካባቢ ባለ ስፍራ የጥምቀት ስርዓትን መፈጸም ጀመሩ፡፡ በጃን ሜዳ የሚወጡ ታቦታት ቁጥር አስራ አራት ነበር፡፡ ይሁንና ይህ አለመግባባት በካህናት መካከል ከተፈጠረ በኋላ ጃን ሜዳ የሚመጡት ታቦታት አስራ ሁለት ሆነ፡፡ በዚህ ጠብ ምክንያት የሚካኤል ታቦት በማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በደባልነት እስከሚገባ ድረስ በጥር 12 እለት ከጃን ሜዳ የሚነሳ የሚካኤል ታቦት አልነበረም፡፡

ጥምቀት እንደ ልዩ ማህበራዊ መድረክ፤ በዘመነ ጃንሆይ

በጃንሆይ ዘመነ መንግስት የጃን ሜዳ ጥምቀት ከኃይማኖታዊ ስርዓትነቱ በተጨማሪ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች መከወኛ ነበር፡፡ ከእነዚህ ማህበራዊ ጉዳዮች መካከል የአቤቱታ ማቅረቢያ መድረክ መሆኑ ነው፡፡ በጥምቀት በዓል ላይ ለንጉሱ አቤቱታ ካቀረቡት አካላት መካከል የጉራጌ ማህበረሰብ አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ዕቃ የሚሸከሙ ግለሰቦችን ‹‹ጉራጌ … ጉራጌ›› በሚል መጥራት የተለመደ ነበር፡፡ ይህ ልምድ እንዲቆም በአዲስ አበባና አካባቢው የሚኖሩ የጉራጌ ማህበረሰብ ተወላጆች ተሰባስበው ለጃንሆይ አቤት ለማለት ተዘጋጁ፡፡

ጃንሆይ በየካ የሚገኘውን የሚካኤል ታቦት አስገብተው ወደ ቤተመንግስታቸው ሲመለሱ፣ ሁሉም የጉራጌ ተወላጆች ልጡ የተላጠ ረጃጅም የባህር ዛፍ ሽመል ይዘው፣ በመንገዱ ግራና ቀኝ ተሰልፉ፡፡ ጃንሆይም ሁኔታውን ሲጠይቁ አቤቱታ መሆኑን ተረዱ፡፡ አቤቱታውም ‹‹ተሸካሚ ጉራጌ እየተባለ መጠራት የለበትም፣ ይህን ይስቀሩልን፡፡›› የሚል ነበር፡፡ ጃንሆይም አቤቱታውን ሰምተው ተሸካሚ ሊጠራ የሚችልባቸው አማራጭ ስሞች እንዲፈለጉ አደረጉ፡፡ በወቅቱ የቀረቡት አምስት አማራጭ ስሞች ሀማል፣ ኩሊ፣ ባቱ፣ ተሸካሚ እና ሰርቶ በሌ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል ‹‹ኩሊ›› የሚለው ስም መመረጡን መሐመድ ደርባቸው (2005)፣ ደንዲ የግዞት አምባ በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡

ታቦተ ህጉን ለማጀብ ወደ ጃን ሜዳ የሚመጣው ሕዝብ እንደ ባህሉ የተለያዩ አልባሳትን ይለብሳል፡፡ ሕዝቡም ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ፡፡›› የሚል ምሳሌያዊ አነጋር አለው፡፡ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገርም ለጥምቀት ከሆነ አዲስ ልብስ ይህ ካልሆነም ካለው ልብስ መካከል የተሻለ ውበት ያለውን አጥቦ ይለብሳል፡፡ ለጥምቀት በዓል ወንዱ በነጭ የባህል ልብስ፣ ተፈሪ ልብስ፣ ተነፋነፍ፣ ባተሁለት በመልበስ ይዋባል፡፡ ሴቶች በነጭ ጥበባቸው ላይ መልጎም በመባል የሚጠራ የብር ጌጥ በማድረግ፣ ጸጉራቸውን በተለያየ አይነት የጸጉር ስራ በመሰራትና ጥሩ ጠረን ያላቸውን ቅጠላ ቅጠል ወይም ሽቶ በመቀባት ውብ ሆነው ወደ ጃን ሜዳ ይሄዳሉ፡፡

የጥምቀት በዓል ከሀይማኖታዊ እሴቱ በተጨማሪ የተለያዩ ብሔረሰቦች ያላቸውን የጭፈራና የዘፈን ባህል የሚያሳዩበት እንዲሁም ወንድና ሴት ወጣቶች ለትዳር የሚሆናቸውን ሰው የሚተዋወቁበትና የሚያጩበት ስፍራ በመሆኑ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ በወቅቱም ወንዱ ለትዳር ትሆነኛለች የሚላትን ልጃገረድ ሎሚ በመወርወር አካሏን ወይም የያዘችውን ጥላ ይመታል፡፡ ልጅቷም ልጁን ለመተዋወቅ ፍቃደኛ ከሆነች የመሽኮርመም ምልክት ታሳያለች፡፡ በዚህ መልክ ወጣቶች እርስ በርስ ይተዋወቁና ትዳር ይመሰርቱ ነበር፡፡

በወቅቱ አንድ ወጣት ለትዳር የሚፈልጋትን ልጃገረድ ለመተዋወቅ ሎሚ ከመወርወር በተጨማሪ ሜታ ከረሜላ፣ ቸኮሌት ከረሜላና ማስቲካ ተወዳጅ የነበሩ በመሆናቸው ገዝቶ ይሰጣት ነበር፡፡ በጃን ሜዳ የሎሚ ውርወራ ሳቢያ ተጫጭተው ለወግ መዓረግ የበቁ በርካታ ግለሰቦች አሉ፡፡ ልጃገረዶች ከቤት የመውጣት፣ ከወንድ ጋር የመተዋወቅ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር የመገናኘት እንዲሁም ውብ ሆነው የመታየት እድል የሚያገኙት በጥምቀት በዓል በመሆኑ ከሌላው ቀን በተሻለ በእለቱ የተወሰነ ነጻነት የሚያገኙበት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ከእነዚህ ባህላዊ ክንዋኔዎች በተጨማሪ የተጣሉ ሰዎች ይቅርታ የሚጠያየቁበትና የሚታረቁበት የ‹‹እርቅ›› በዓል ነበር፡፡

በጃንሆይ ዘመን በጥምቀት በዓል ወቅት የነበረው ዘፈን፣ ጭፈራና ወጣቶች እርስ በርስ የመተጫጨት ባህላዊ ስርዓት እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ታቦተ ህጉን ከዘማሪ ካህናት በተጨማሪ አዝማሪዎች በመሰንቆ ያጅቡ ነበር፡፡ የጥምቀት በዓል አከባበር በጋዜጣና በሬዲዮ ሰፊ ሽፋን ይሠጠው ነበር፡፡ ከተለያዩ አገራት የመጡና የጥምቀት በዓልን በጃን ሜዳ ያከበሩ በርካታ የሀይማኖት አባቶች መካከል በ1961 ዓ.ም የሮማንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ የሆኑት ጁስቲንያን በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top