ታሪክ እና ባሕል

አጼ ዮሐንስ ‹‹በሰይጣኑና በሰይጣኑ ፈረስ›› መካከል

አጼ ዮሐንስ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኢትዮጵያ ወደ ዳግመኛ ዘመነ መሳፍንት አዙሪት ውስጥ ገባች፡፡ በመሆኑም የንጉሱ የውስጥ ፖሊሲ ማዕከላዊ መንግሥት ለመፍጠር ጸረ-መሳፍንት ትግል መቀጠልና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውም ተመሳሳይ ሀይማኖትን ከሚከተሉ የአውሮፓ ሀያላን መንግሥታት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ድጋፍ ማግኘት ነበር፡፡

ግብጽ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ክፍፍል ለጥቅሟ ለማዋል የአጼ ዮሐንስ ተቀናቃኝ የነበሩ ኃይሎችን በማገዝ አገሪቱ ከፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ እንዳትወጣ ለማድረግ በርትታ ትሠራ ነበር፡፡ ለዚህም ስለ ኢትዮጵያ ጠንቅቆ የሚያውቀውን ሙዝንገር የሚባል ቅጥረኛዋን አሰለፈች፡፡ ሰውዬው ምጽዋና ከረን ውስጥ ነጋዴ ሆኖ ለረጅም ዓመታት የኖረ፣ የአካባቢውን አንድ ባላባት ልጅ ያገባ፣ በበርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መግባባት የሚችልና ቁልፍ የአገሪቱን አካባቢዎች ከነውስጣዊ ሁኔታዎቻቸው የሚያውቅ ነበር፡፡

ሙዚንገር በኢትየጵያ የነበሩ አርባ ያህል አውሮፓውያንን አጼ ቴዎድሮስ አስረው በነበሩ ጊዜ በዲፕሎማሲያዊ ድርድር ለማስፈታት ለመጣው የእንግሊዝ መልእክተኛ ቡድን መንገድ በመምራት፣ ስንቅ በማቅረብና የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር ለእንግሊዝ መንግሥት ከፍ ያለ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በጄኔራል ናፒር ወረራ ጊዜም አብሮ ዘምቷል፡፡

‹‹የሰይጣን ፈረስ›› እና አጼው

አጼ ዮሐንስ የግብጽ ቅጥረኛ የነበረውን ሙዚንገርን ‹‹የሰይጣን ፈረስ›› ይሉት ነበር፡፡ የናፒር ጦር ከኢትዮጵያ ሲወጣ ይህ “የሰይጣን ፈረስ፤ የሰይጣን ቁራጭ” እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀረ፡፡ ንጉሱን ያኔ ገና ደጃዝማች ከነበሩ ጊዜ ጀምሮ ተዋውቆ ወዳጅ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ እሳቸውም ከብዙ የውጭ መንግሥታት ጋር ታስተዋውቀኛለህ በሚል ዓላማዬን እስከደገፈ ድረስ ከሰይጣንም ጋር እዋዋለሁ ወይም ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል እንደሚባለው የሰይጣኑን ፈረስ አቀረቡት፡፡ ሙዚንገር የማያውቀው የአውሮፓ ባለሥልጣን፣ የማይወዳጀው መሪ እንደለሌ በቅቤ አንደበቱ እያባበለ ለተስፈኛው ንጉስ ታማኝ መሰሎ ገባ፡፡ አጼ ዮሐንስ ከነገሱ በኋላ ‹‹የሰይጣን ፈረስ›› በራስ ማዕረግ የቦጐስ፣ የሐባብና የመንሳ ገዥ አድርገው እንዲሾሙት ለምኗቸው ነበር፡፡ አልተሣካለትም፡፡ ንጉሱ ብልህ ሆነው ፊት ነሱት፡፡

‹‹የሰይጣን ፈረስ›› እና ፈረንሳይ

ፈረንሣይ በአፍሪካ ቀንድ ቅኝ ግዛት የመፍጠር ህልሟን እውን ለማድረግ የሚያግዛት አካባቢውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው እየፈለገች የነበረበት ወቅት ስለነበር ፖለቲካን የማባዘትና የመፍተል ችሎታው ከፍተኛ የሆነውን ‹‹የሰይጣን ፈረስ›› አገኘች፡፡ እሱም ራሱን በራሱ እጩ አድርጎ አቀረበ፡፡ ፈረንሣይም በደስታ ተቀበለችው፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ የፈረንሣይ ካቶሊክ ሚስዮናዊያን አስተባባሪ ሆኖ ተሾመ፡፡ ሚስዮናዊያንን የወንጌል ሰበካን ችላ እንዲሉና የፈረንሣይ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጐቱን የሚያራምድበትን የፖለቲካ ስትራቴጅናታክቲክ እንዲያሰላስሉ ይገፋፋቸው ጀመረ፡፡

ከዚህ በኋላ ሰውዬው የፈረንሣይ መንግሥት አጼ ዮሐንስ አንድ አገርና አንድ ሀይማኖት ፖሊሲ የሚከተሉ በመሆናቸው ካቶሊክ ሚስዮዊያንን እየጮቆኑ ስለሆነ ሚስዮናዊያንን የሚጠብቅ ወታደር በአስቸኳይ እንዲላክ ጠየቀ፡፡ ሆኖም ፈረንሣይ ወታደር ባለመላኳ አኩርፎ ከአጼ ዮሐንስም ከፈረንሣይም በመራቅ ለግብጹ ኬዲቭ እስማኤል ታማኝ ሎሌ በመሆን ግብጾች ኢትዮጵያን በጦር ሃይል እንዲይዙ መትጋት ጀመረ፡፡ ምጽዋን እንዲይዙ አደረገ፡፡ ስለውለታው ኬዲቩ ወታደራዊ ማዕረግ ሰጥቶት የምጽዋና የአካባቢው አገር ገዥ አድርጎ ሾመው፡፡ ከአጼ ዮሐንስ ያጣውን ከግብጾች አገኘ፡፡ ከዚያም በገንዘብ አቅሙና በንግግር ችሎታው እያባበለ የአካባቢው ባህላዊ መሪዎችና ሹሞች አጼ ዮሐንስን እንዲክዱና ለግብጽ እንዲገብሩ አድርጓል፡፡

‹‹የሰይጣኑ ፈረስ›› ግስጋሴ

ቅጥረኛው የቀጣሪዎቹን የመስፋፋት ፖሊሲ ለመተግበር ምጽዋን መቀመጫና መንደርደሪያ በማድረግ በራሱ መሪነት ቦጐስን፣ ሐባብንና መንሳን በ1864 እና ጊንዳን በ1865 ያዘ፡፡ በ1864 በምዕራብ ሱዳን በኩል በኤደም ፓሻ መሪነት የተንቀሳቀሰው የግብጽ ጦር መተማን አልፎ ቋራንና ደንቢያን ያዘ፡፡ ማስገበር ጀመረ፡፡ ከወሎ ባላባቶችና ከሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጋር ገጸ በረከትና ደብዳቤ በመላክ ይወዳጅ ጀመር፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ሁኔታ የተፈጠሩ ቅራኔዎችንና ልዩነቶችን በመጠቀም የአጼውን መስተዳድር ከሥሩ በመገዝገዝ ለዘመናት ግብጾች የሚያልሙትን የአባይን ምንጭ የመቆጣጠር ህልም እውን ለማድረግ በትጋት ሰራ፡፡ በሌላ በኩል አጼ ዮሐንስን ለማዘናጋት የወዳጅነት ደብዳቤ ይጽፍ ነበር፡፡

የኢትዮጵያውያን ገዢዎች አለመግባባትና ግብጽ ፍላጎት

ምኒልክ፡ ተክለሃይማኖትና ዮሐንስ በዘውድ ፖለቲካ ተፎካካሪነት ሸዋ፣ ጎጃምና ትግራይ ሆነው ይተያዩ ነበር፡፡ ባህሩ እንደጻፈው ምኒልክና ተክለሃይማኖት ባላጋራዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ›› በሚል በ1880 ታርቀው በንጉሠ ነገሥቱ በአጼ ዮሐንስ ላይ በአመጽ ተባበሩ፡፡ አንዱ የሌላውን አጼነት የማይቀበልበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡

ግብጾች ይህን የውስጥ ክፍፍል ለራሳቸው ዓላማ ለመጠቀም ሲሉ ከምኒልክ የወገኑ መስለው ቀረቡ፡፡ ሙዚንገር ወደ ምኒልክ ተላከ፡፡ የግብጹ ኬዲቭ ምኒሊክን እንደሚደግፍና የሚጠይቁትን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኛ መሆኑ በመልእክተኛው ሲነገራቸው የሸዋው ንጉስ ተደሰቱ፡፡ ከመልእክተኛው ጋር ተጨዋውተው የመጣላቸውን ገጸ በረከት አመስግነው ተቀበሉ፡፡ ምኒልክ በኢትዮጵያ ልማትና ሥነ-ጥበብ ለማስፋፋት ምኞት እንዳላቸው የሚገልጽና ምክር የሚጠይቅ ደብዳቤ በሙዝንገር ላይ ለኬዲቭ እስማኤል ላኩ፡፡ ኬዲቭ እስማኤል በምላሹ የጻፈው ደብዳቤ በስህተት ከምጽዋ ለአጼ ዮሐንስ ተላከ፡፡ አጼ ዮሐንስም በግብጾች የተያዘባቸውን የቦጐስ፡ ጊንዳና መንሳ ግዛቶች ጉዳይ ምንም ሳያነሱ ከግብጾች ጋር እንደሚስማሙ መልስ ሰጡ፡፡ ይህም በግብጾች ዘንድ የፖለቲካ ብዥታ ፈጠረ፡፡ ሆኖም ይህ ግንኙነት ግብጽ አጼ ዮሐንስን ለመውጋት ያላትን እቅድ አላስቀየረም፡፡

በ1875 ሚያዚያ ወር ምኒሊክ ለኬዲቭ እስማኤል በሙዝንገር አማካይነት እንዲደርሰው ሌላ የዲፕሎማሲ ደብዳቤ ላኩ፡፡ ደብዳቤው በእሳቸውና በግብጽ መካከል የተጀመረው ግንኙነት እንደሚቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልጽ ሆኖ የምኒሊክ መልእክተኛ በሆኑት ራስ ብሩ በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል የወዳጅነትና የንግድ ውል እንዲፈረም የሚጠይቅ ነበር፡፡ እንደገና ቦጐስ በሚባል አርመናዊ የኬዲቩ ባለሟል አማካይነት ሌላ ተጨማሪ ደብዳቤ ተላከ፡፡ ደብዳቤው አንድ ጳጳስ ለሸዋ እንዲላክላቸው የሚጠይቅ ነበር፡፡ ኬዲቭ እስማኤል በላከው መልስ የምኒልክን ፍላጐት እንደሚያሟላ አረጋግጦ የጳጳሱ ምልመላ እንደተጠናቀቀ ወዲያው እንደሚላክ ገልጾ አምስት መቶ ጠመንጃ ድጋፍ እንደላከላቸው አስታወቀ፡፡

የግብጹ ኬዲቭ እስማኤል አጼ ምኒልክ ከሱ ጋር በመወገን አጼ ዮሐንስን እንዲወጉ ፈልጓል፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመያዝ ምንም ፍላጐት እንደሌላት፣ ነገር ግን አጼ ዮሐንስን አስወግዳ ምኒልክን ለማንገስ እንደምትፈልግ የሚገልጽ ደብዳቤና ገጸ በረከት ይልክ ጀመር፡፡ ምኒልክ ምንም እንኳ የአጼ ዮሐንስን ንግስና ለመንጠቅ ምኞት ቢኖራቸም የግብጾች የተንኮል ዓላማ የሚገባቸው ቆቅ ነበሩ፡፡ ግብጾች እሳቸውን ሊያሞኙ ስደክሙ ምኒሊክ ግብጽን ይበልጥ ያሞኙ ነበር፤ ‹‹ምላጭ ለምላጭ›› እንዲባል፡፡

ግብጾች በምኒሊክ ለመጠቀምና በእነሱ ሞግዚትነት የሚትገዛ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያላቸው ምኞት አልተሰወረባቸውም፡፡ ያም ግብጽ ራሷ በቱርክ ሥር እንደነበረች ዓይነት ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ምኒልክ በ1868 ለግብጹ ገዢ በላኩት ደብዳቤ የግብጽ ጦር መስፋፋት እንደሚያሰጋቸው ገለጹ፡፡ ከዚያ በኋላ ከግብጽ ጋር በሥጋትና ጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ማራመድ ጀመሩ፡፡ ምክንያቱም የሚቀጥለው ጦርነት ከርሳቸው ጋር እንደሚሆን ያወቁ ይመስላል፡፡

የአጼ ዮሐንስን ጠላቶች መደገፍ

ግብጽ በትግራይ የሚገኙ እንደነ ደጃዝማች ወልደሚካኤልና ራስ አርአያ ያሉ የአጼ ዮሐንስ ጠላቶችን በማስታጠቅ፡ በገንዘብ በመደገፍና ከጂዎችን በባንዳነት በማሰማራት ጸረ-ዮሐንስ ግንባር በመፍጠርና በማጠናከር ለንጉሱ የጎን ውጋት ሆኑ፡፡ የአጼ ዮሐንስ መንግሥት ከውስጥም ከውጭም እጅና ጓንት ሆነው በተነሱት ጠላቶች ተወጣጠረ፡፡ ከሀዲዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች የጦር መሣሪያ ለማግኘት ሲሉ ሁሉም የአገርን ሚስጢር መሸጥ ተያያዙ፡፡ ከዚህ አጠቃላይ የውስጥ ፖለቲካ ሁኔታ የተነሣ ግብጽ የአጼ ዮሐንስ መንግሥት እጅግ በጣም የተዳከመና በቀላል የሚወድቅ አድርጋ በመገምገም ቀጥተኛ ካልሆነ ጦርነት ይልቅ በቀጥታ ወረራ ማድረግን መረጠች፡፡

የፈረንሣይ ላዛሪስት ሚስዮናዊያን ቄሶች በግልጽና በድብቅ የሚያስተምሩት አስተምሮና የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጼው አልጣማቸውም፡፡ ከዚህም የተነሳ የካቶሊክ ቄሶች እንደበፊቱ በነጻነት እንዳይቀሳቀሱ በትዕዛዝ ከለከሉ፡፡ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሚሲዮናዊው ፔሩ ዱፍሎስ ከአጼ ዮሐንስ ቤተመንግሥት መጥቶ ንጉሡ ክልከላውን የሚያነሱ ከሆነ የፈረንሣይ መንግሥት ግብጽ ኢትዮጵያን እንዳትወር መተማመኛ እንደሚሰጥ ለድርድር አቀረበ፡፡ ንጉሱ የመደራደሪያ ሀሳቡን አልተቀበሉም፡፡ በዚህ ወቅት በሚሲዮናዊነት፣ በአሳሽነትና በልዩ ልዩ ስሞች የሚንቀሳቀሱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች በሰሜን ኢትዮጵያ ነበሩ፡፡

አጼ ዮሐንስ ወደ ሥልጣን የመጡበት ጊዜ በዓለም ላይ ቅኝ ገዥዎች ተነስተው ደካማውን የአፍሪካና ሌሎች ዓለማት ሕዝቦችን በመቀራመት ቅኝ የሚያደርጉበት ወቅት ነበር፡፡ እንግሊዞች፡ ፈረንሣዮችና ኢጣሊያኖች በአፍሪካ ቀንድ ላይ እርስ በርስ የሚሻኮቱበት ወቅት ስለነበር የኢትዮጵያ ነጻ አገር ሆኖ የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ከውስጥና ከውጭ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች አንጻር ሲገመገም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነበር፡፡ ግብጽ የአባይን ሸለቆ ከቅኝገዠዎች ቀድማ ለመቆጣጠር ፖለቲካውን በማባዘት ላይ ነበረች፡፡

የአጼ ዮሐንስ ዲፕሎማሲያዊ ትግልና ውጤቱ

ዲፕሎማሲ ፖለቲካና ጥበብ ነው፡፡ ዲፕሎማሲ ህብረተሰብ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ከህብረተሰብ ጋር በማደግ አገሮች ወደ ግጭትና ደም ወደሚያፋስስ ጦርነት ሳይገቡ አለመግባባታቸውን በውይይትና በድርድር የሚፈቱበት ፖለቲካዊ ጥበብ ነው፡፡ ጠመንጃ የማይፈታውን ውስብስብ ችግር ዲፕሎማሲ በሰላም ይፈታዋል፡፡ ዲፕሎማሲ ሰጥቶ መቀበልን፡ ትዕግሥትን፣ አርቆ ማሰብንና በሌላ ጫማ ወስጥ ራስን አስገብቶ ማየትን፣ ቅንነትንና ግልጽነትን የሚጠይቅ የእውቀት ዘርፍ ነው፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ሂደት ነው፡፡ ምክንያቱም ተደራዳሪ ወገኖች ክርር ያለ እኔ ብቻ ላሸንፍ የሚል አቋም ስለሚይዙ ነው፡፡ ለዋነኛ የጋራ ዓላማ ሲባል ጥቃቅን ጉዳዮችን በከፍተኛ ትዕግስት ችሎ የማለፍ ሳይንስና ጥበብ ነው፡፡

አጼ ዮሐንስም አገሪቱን በውስጥና በውጭ ችግሮች ተተብትባ ከነበረበት አጣብቂኝ ለመውጣት ጦርነትን ቀዳማይና ብቸኛ አማራጭ አድርገው ሳይወስዱ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ደም መፋሰስ እንዳይመጣ ለማድረግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግን መረጡ፡፡

አጼ ዮሐንስ አክራሪ ሃይማኖተኛ፤ ትዕግስተኛና መሓሪ እንደነበሩ ተወልደ ሲገልጽ እሳቸው ይከተሉ የነበረው የአስተዳደር ዘይቤ ተቀናቃኞቻቸውን በማጥፋት፣ በመግደል ሳይሆን ታማኝነታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ በማስማል ማረጋገጥ ይበቃቸው ነበር ብሏል፡፡ አጼ ዮሐንስ ዘውድ ከጫኑ ጀምሮ ማንንም የሥልጣን ተቀናቃኝ እንዲገደል ወይም በእስር ቤት ማቅቆ እንዲሞት አላደረጉም ይላል፡፡ ጠላቶቻቸውን አሸንፈውና ማርከው እግሮቻቸው ስር ከጣሉ በኋላ እንኳ ምህረት ያደርጉ እንደነበር የሚገልጹ የታሪክ ሰነዶች አሉ፡፡ ጠላቶቻቸውን ለሊቃውንት ዳኝነት ለፍርድ አቅርበው በሞት ሊቀጡ የነበሩትን በይቅርታ በማለፍ በእስራት እንድሆን አድርገዋል፡፡ ለእናታቸው ገዳይ ምህረት አድርገው ለህዝብ ትዕግስትንና አስተዋይነትን አስተምረዋል፡፡ ቂምና በቀል፣ ጥላቻና ትእቢት፣ ትምክህትና ጀብደኝነት ለሚበዛው ለዛሬው ፖለቲካችን አርያነት ያለው ምግባር ይመስለኛል፡፡ ከትእግስታቸውና አስተዋይነታቸው፣ ብልህነታቸውና ጀግነነታቸው፣ ከታሪክ ፍሰት ጋር ሄዶ የት እንዳደረሳቸው ለማስታወስም እንሞክራለን፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top