ታሪክ እና ባሕል

ሻለቃ ግርማ ይልማ – የሰውነት ተምሳሌት

አለቃዬ ብቻ አልነበሩም፣ ከዚያ ያልፋል። የአለቃዬ የአለቃው አለቃ ነበሩ። ሚኒስትርነት እንዲህ ቀላል ሥልጣን አልነበረም፣ አይደለምም። ሰውዬው ግን ቀለል ያሉ ነበሩ፣ ፈረንጆቹ “Simple” የሚሏቸው አይነት። ዛሬም ናቸው። ሻለቃ፣ በዚያን ጊዜው አጠራር ጓድ ግርማ ይልማ የባህል ሚኒስትራችን ነበሩ። በአጋጣሚ ደግሞ ቀደም ብለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጀመሩትን ትምህርት ያጠናቀቁትና የተመረቅነውም በተመሳሳይ ወቅት፣ በሐምሌ 1978 ዓ.ም ነበር። ታዲያ ስለሳቸው ባህሪና ማንነት ማወቅ የጀመርኩት ያኔ ነበር ማለት ይቻላል። በሕግ ትምህርት ቤት አብረዋቸው የሚማሩ ወዳጆቼ ስማቸውን በበጎ ያነሱልኝ ነበር። ሚኒስትር ቢሆኑም የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር ግቢ ሲረግጡ ራሳቸውን እንደማንኛውም ተማሪ ነበር የሚቆጥሩት። ያደረሳቸውን ሾፌር ያሰናብቱና ደብተራቸውን ይዘው፣ አስፈላጊም ሲሆን ወንበራቸውን ራሳቸው ተሸክመው እያመጡ ይማሩ ነበር። ሊረዷቸው የሚሞክሩ ተማሪዎችንም “ምንም ችግር የለም። እኔም እንደናንተው ተማሪ ነኝ፣ እናንተ የምትሆኑትን ሁሉ መሆን እችላለሁ” የሚሉ አይነት ሰው ነበሩ።

በሥራ ዓለም ከተሰማራሁ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ የተከራየሁት ቤት ከዋናው ፖስታ ቤት ጀርባ፣ ኦርማ ጋራዥ የሚባለውን አለፍ ብሎ ነበር። የሻለቃ ግርማ መኖሪያ ደግሞ ከንግድ ማተሚያ ቤት ፊት ለፊት ነው። በግምት በአንድ መቶ ሜትር ርቀት ላይ ነበርን ማለት ይቻላል። ይህ እንግዲህ ለእግረኛው ሚኒስትርና ለያኔው ወጣትና ተራ ሠራተኛ መገናኘት ምክንያት ነበር። ስለዚህ ዛሬ ስለእኚህ ታላቅ ሰው የማጋራችሁ ወጎች ከዚህና ከሥራ ዓለም የግል ትዝታዎቼ የሚቀዱ ናቸው።

ጎረቤት ነበርኩ ማለቴ ካልቀረ ከዚሁ ልጀምር። አንድ ቀን ጠዋት ከተከራየሁበት ግቢ በር ላይ ቆሜ ፀሐይ ስሞቅ ሻለቃ ግርማ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ አለሚቱ ገዳ ዋኬኔ ጋር ሆነው በእግራቸው ወደሥራ ሲሄዱ እንተያያለን። ያ ቀን እዚያ ሰፈር እንደሚኖሩ ያወቅኩበትም ነው።

“አንተ ጎረምሳ፣ አንሄድም እንዴ?” ሲሉኝ፣ እሺ ብዬ አብሬያቸው ሄድኩኝ። ባለቤታቸው እዚያው ሰፈር በሚገኘው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ስለሚሰሩ ተሰናብተናቸው እኛ መንገዳችንን ቀጠልን። ስለሥራ እየጠየቁኝ እየመለስኩ ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ከብሔራዊ ባንክ በስተጀርባ ባለው የመ/ቤታችን የኋላ በር ገባን። በማናወራበት ጊዜ ያፏጫሉ። በተለይ እኔ በጣም እየከበደኝ፣ ለሚጠይቁኝ ሁሉ አጫጭር መልስ ነበር የምሰጠው። እሳቸው ግን እንደ አባት ፍጹም አቅርበው ነበር የሚያነጋግሩኝ። (ዛሬም አንዳንድ የጽሑፍ ማስታወሻ ሲልኩልኝ “ውድ ልጄ” ሲሉኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ።) ግቢው ውስጥ ከገባን በኋላ የወዳደቀ ጋዜጣና የመሳሰለውን ሲያዩ አያልፉም። እያነሱ፣ አንዳንዴም እየለቀሙ ማለት ይቻላል፣ ነበር የሚሄዱት። እኔም ከዚያ በፊት አድርጌው የማላውቀውን እሳቸውን ተከትዬ ማንሳት ጀመርኩ። ከዚያ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ በርሜል ውስጥ ጥለነው እንሄዳለን። ብዙውን ጊዜ ከሁለት ሰዓት ቀድመን ነበር የምንደርሰው። ስለዚህ እሳቸው በዋናው በር በኩል ሆነው ጫማቸውን ሲያስጠርጉ፣ እኔ ማዶ ወደሚጠብቁኝ የሥነጥበብ መምሪያ ባልደረቦቼ መንገዱን ተሻግሬ እሄዳለሁ። ታዲያ ጉርብትናችንና የአብሮ መንገዳችን ከተደጋገመ በኋላ ባልደረቦቼ አንዳንድ ነገር ይጠይቁኛል። “ለመሆኑ መንገድ ላይ ምን ታወራላችሁ?” ይሉኛል። እውነቱን እነግራቸዋለሁ። ብዙውን ጊዜ ሻለቃ ግርማ “ምን እየሠራህ ነው? ስብሃት ገ/እግዚአብሔር አዲስ ዘመን (ወይንም ሄራልድ) ላይ የጻፈውን አየኸው? አዲስ የወጣውን የእከሌ መጽሐፍ አነበብከው?” ይሉኛል። ማታ በቴሌቪዥን የተላለፈና የመሰጣቸው ፕሮግራም ካለም መመልከቴን ይጠይቁኛል። እመልሳለሁ። እንነጋገርባቸዋለን። ይህንኑ ለባልደረቦቼ ስነግራቸው “ከዚያስ?” ይሉኛል። “ከዚያ ደግሞ ያፏጫሉ” እላቸዋለሁ። ይስቃሉ። ከዚያ ወዲያ እንዲሁ ጠዋት ጠዋት ስንገናኝ “የዛሬው ፉጨት ትዝታ ነበር?” ይጠይቁኛል። “አይ አንች ሆዬ ነው” እላለሁ። እንሳሳቃለን።

የእግረኝነታቸውን ነገር ለመቋጨት አንድ ነገር ልጨምር። ሻለቃ ግርማ ጠዋት ወደሥራ ሲመጡም ሆነ ማታ ወደቤታቸው ሲመለሱ በእግራቸው ነበር የሚሄዱት። የመ/ቤቱን መኪና የሚጠቀሙበት ለምሳ ብቻ ነበር። ያኔ የምሳ ሰዓት ከስድስት እስከ ሰባት ሰዓት ነበር። የሚገርመው ሾፌራቸው፣ ቦጋለ የሚባል ጥሩ ሰው ነበር፣ ወደቤታቸው ሲወስዳቸው አብሮ ማእድ ቀርቦ፣ ምሳውን በልቶ ነበር የሚመጣው። ምንጊዜም። ይህን የሚያደርግ ባለሥልጣን ያኔም ዛሬም ያለ አይመስለኝም። ካሉም ምናልባት ባንድ ጣት የሚቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ። በአንድ ሌላ ጽሑፌ ላይ እንደጠቆምኩትም የመኪና እጥረት ሲያጋጥመን ለእሳቸው በተመደበው አውቶሞቢል እንድንጠቀም ይፈቅዱልን ነበር። በአንድ ወቅት የሰማነው ወሬም ነበር። ይኸውም ከሚኒስትሮቻችን ጋር የተያያዘ ነው። ነፍሳቸውን ይማረውና ምክትል ሚኒስትራችን አቶ ዘውዴ ጉርሙ ፈረንሳይ ሃገር የተማሩና ካኪ ልብስ የሚያዘወትሩ ነበሩ። ታዲያ ይህ ጉዳይ ከሻለቃ የእግር ጉዞ ጋር ተደምሮ አንዳንድ የዚያ ዘመን ሚኒስትሮች፣ “ያኛው ካኪ እየለበሰ ካኪ በካኪ አስደረገን፣ ይኼኛው ደግሞ በእግሩ እየሄደ ምን ያመጣብን ይሆን?” አሉ ሲባል ሰምተናል።

በባህል ሚኒስቴር አንድ የተለመደ አሠራር ነበር። ምናልባት በሌሎች መ/ቤቶችም ይኖር ይሆናል። አዳዲስ ሠራተኞች ሲቀጠሩ የትውውቅ (Orientation) ፕሮግራም ይዘጋጃል። ከሚኒስትሩ ጀምሮ ያሉ ኃላፊዎች እየመጡ ስለየሚመሩት ተቋም ዓላማና ተግባር ገለጻ ያደርጋሉ። ያን ፕሮግራም በምንከታተልበት ሰሞን ባጋጣሚ የባህል ሚኒስቴር አጠቃላይ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ ይደረግ ኖሮ እንድንገኝ ተነገረን። በወቅቱ አንድ የአፋር ተወላጅ የሆነ ባልደረባችን ምንጊዜም የማልረሳውን ንግግር አደረገ። ቀደም ብሎ ስለአንዳንድ የአፈጻጸም ችግሮች ተነስቶ ነበር። “በአፋር ቅፍለት የሚባል ነገር አለ። ግመል አንዱ ከሌላው ጋር ተሳስሮ ስለሚሄድ ፊት ያለ ግመል ከቆመ ኋላ ያለውን ግመል ብትቀጠቅጠው ውጤት አታመጣም። ስለዚህ የኋላው እንዲከተል ፊት ያለው ግመል የግድ መንቀሳቀስ አለበት።” ብሎ ተቀመጠ። ሳቅም ሁካታም ነገር ተሰማ። ሻለቃ ግርማ ታዲያ አስተያየት ሰጪውን አመስግነው ሲጨርሱ፣ “ፊት የቆመው ግመል ማለት እኛ ነን፣ እንንቀሳቀሳለን፣ የግድ መንቀሳቀስም አለብን” ብለው አስደመሙን። ያለምንም ማመንታት ኃላፊነቱን ወሰዱ። ቀን ላይ አንድ ኃላፊ “አስተዳደርና ነጭ ሽንኩርት አንድ ነው፤ መብላቱም መግማቱም አይቀርም” ሲሉ ሰምተን ደንግጠን ለነበርን ወጣቶች ያ የሻለቃ ግርማ አስተያየት በአያሌው የሚያስደስት ነበር።

አሁን ደግሞ ሰብዓዊነታቸውን ያሳያሉ የምላቸውን ተጨማሪ ምሳሌዎች ልጥቀስ። አንድ የባህል ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መ/ቤት ባልደረባ በሂሳብ ምርመራ ወቅት በተገኘበት የገንዘብ ጉድለት ሰበብ በቁጥጥር ሥር ይውላል። በቅርብ የማውቃት ባለቤቱ ሻለቃ ግርማን ለማነጋገር ትመጣለች። የእሳቸው ቢሮ ምንጊዜም ክፍት ነው። ጸሐፊያቸው ወ/ት እታፈራሁም በጣም ጥሩ ሰው ነበረች። አስገባቻት። ከዚያ አክብረው ተቀብለው ለሚያዳምጧት ሰው ከአራት ልጆቻቸው ጋር በችግር ላይ መሆናቸውን ስታስረዳ እያለቀሰች ነበር። ስትጨርስ ቀና ብላ ታያቸዋለች። ዓይኗን ማመን አልቻለችም። ራሳቸው ሚኒስትሩም እያለቀሱ ነበር። ከዚያ የሚመለከተውን የበታች ኃላፊ አነጋግረው ግለሰቡ እዳውን እየሠራ እንዲከፍል አደረጉ። የበታች ሠራተኛቸውን ብቻ ሳይሆን ምንም የማያውቁ ሕፃናትንም ታደጉ።

በአንድ ወቅት ደግሞ ለሥራ ጉብኝት ወደ ደሴ ጎራ ይላሉ። እዚያ ካሉት የባህል ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መ/ቤት ባልደረቦች ጋር ከተወያዩና ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ለመመለስ በተዘጋጁበት ሰዓት የቅርንጫፍ መ/ቤቱ ኃላፊ ጋሽ ታዬ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው። “ከዚህ ቀደም ብቸኝነት ያበዛ የነበረ አንድ የሥራ ባልደረባችን ራሱን አጥፍቶ ሁላችንም ደንግጠናል፣ አዝነናል። አሁንም እከሌ የተባለው ባልደረባችን ተመሳሳይ ስሜት እየታየበት ስለሆነ በጣም ተጨንቀናል። እባክዎ ቤተሰቦቹ ወዳሉበት ወደአዲስ አበባ እንዲዛወር ያድርጉልኝ።” ብሎ ይጠይቃቸዋል። ሻለቃ ግርማ ምንም አላመናቱም። “አሁን የት ነው ያለው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “ያው!” ብለው በሩቁ ያሳዩዋቸዋል። ልጁ ፈንጠር ብሎ ቆሞ ነበር። ወዲያውኑ አስጠሩትና፣ “በል ና ግባ!” ብለው ራሳቸው በመጡበት መኪና ወደ አዲስ አበባ ይዘውት ሄዱ። ያን ታሪክ ከሰሙ በኋላ ግለሰቡን ትተውት ለመሄድ፣ ወይንም ሌላ ቀጠሮ ለመስጠት አልፈለጉም። ይህም ጉዳይ ከሰብዓዊነታቸው በዘለለ ወቅታዊ ውሳኔ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ በሚገባ መረዳታቸውን፣ በተጨማሪም ኃላፊነት መውሰዳቸውን ያሳያል።

የቀድሞው የፖሊስ መኮንን የማስታወቂያና መርሐብሔር ሚኒስትር ከሆኑበት ከነሐሴ 1970 ዓ.ም በፊትና በኋላም በተለያዩ የብዕር ስሞች ይጽፉ ነበር። በተለይ በተወዳጁ የእሑድ ጠዋት የራዲዮ ፕሮግራም በ”ቡልቡላ ዘመርካቶ” ስም ጉልህ ተሳትፎ አድርገዋል። በዘመነ ቀይና ነጭ ሽብርም በፈጠራ ክስ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ የነበሩ ጋዜጠኞችን ታድገዋል። በጋዜጦችና በመጽሔቶችም ላይ አዘውትረው ይጽፉ ነበር። ከዚሁ ጋ በተያያዘ ጋዜጠኛ ዘላለም በላይሁን ካናዳ ውስጥ ይታተም በነበረ “ሐዋሪያ” የተባለ ጋዜጣ “ስለሻለቃ ግርማ አጭር ትውስት” በሚል ርዕስ ከሰጠችው ምስክርነት ደግሞ የተመጠነውን ክፍል እንመልከት።

“ስለሻለቃ ቀና ልብና ወገን ወዳድነት ማሰብ የጀመርኩት ገና በሥልጣን ላይ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ይመስለኛል። ሁሌም ግን በእጅጉ የሚደንቀኝና ሊገባኝ የከበደ ጉዳይ ቢኖር እዚያ … ሥርዓት ውስጥ እንደሻለቃ ግርማ፣ ኮሚሽነር ሽመልስ አዱኛና ጄኔራል ታዬ ጥላሁን ዓይነት ጥቂት ቀና ሰዎች ለብርቅ ያህል መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን አስችሏቸው መዝለቅ መቻላቸውም ጭምር ነው። ምናልባት አንድ ቀን የሚያብራሩልን የሕይወት ፍልስፍና (Moral code) ይኖራቸው ይሆናል።”

ጋዜጠኛ ዘላለም የታዘበችውንና ከሰዎች የሰማቻቸውን የሻለቃ ግርማ በጎ ተግባራት ከዘረዘረች በኋላ ከሙያዋ ጋር የተያያዘ ገጠመኟን ደግሞ እንዲህ አቅርባዋለች።

“ነፃውን ፕሬስ በተመለከተ ደግሞ የምንጊዜም ተባባሪና የሚያውቁትን ሁሉ ለማካፈል ማወላወል የማያውቁ እንደነበሩ ይህቺ ፀሐፊ ዋና ምስክር ነች። ለምሣሌ በተደራቢነት ትሠራበት የነበረ አንድ የኪነጥበብ ጋዜጣ ለሥራው ስኬታማነት (በተለይም ከሙያው ጋር የተገናኙ ያለፉ ጉዳዮችን መፈተሽ ሲያስፈልግ) እንደቀድሞ የባህል ሚኒስትርነታቸው የሻለቃ ግርማን ዓይነት በየአጋጣሚው በጥያቄ ማድረቅና አስተያየትና ማብራሪያ መጠየቅ ይገባው ስለነበር የሻለቃን ስልክ ሁሌ መደብደብ፣ የቤታቸውንም በር “መቆርቆር” የግድ ነበር። የተሰላቹበትን ወቅት ግን አላስታውስም። ሁሌም ፈቃደኛ፣ ሁሌም ዝግጁ [ነበሩ እንጂ]።”

አልፈው ተርፈውም ከውጪ “የአበሻ ጣጣ” ብለው የተረጎሙትን ሆኖም በገንዘብ እጥረት ለማሳተም ያልቻሉትን ባለ አሥራ አራት ምዕራፍ ማኑስክሪፕት በጋዜጣቸው ላይ እንዲያትሙት በነፃ ሰጥተዋቸው እንደነበር ዘላለም በአድናቆት አስታውሳለች። “እናንተን (ነፃ ፕሬሶችን) ተጠናክራችሁ ከማየትና ሕዝቡም ማወቅ ያለበትን ያለማጣቱን ከማየት በላይ እኔን የሚያጠግበኝ አንዳችም ዓይነት ሌላ ዋጋ የለም” ማለታቸውንም ጠቅሳለች። ያም ሆኖ የጋዜጣዋ አዘጋጆች ወደእሥር ቤት በመላካቸውና ኅትመቱም ለተወሰኑ ጊዜያት በመቋረጡ ለማተም አለመቻላቸውን ጨምራ አስረድታለች።

አሁን ከአራት የሥነጥበብ መምሪያ ባልደረቦቼ ጋር ለአቤቱታ ወደሻለቃ ግርማ የሄድንበትን ጉዳይ ላጫውታችሁ። ሥራችን ከቴያትር ቤቶች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነበር። ደራስያን የሚያመጧቸውን ተውኔቶች የጥበብ ደረጃ እየገመገምን ብቁ የሆኑት በመድረክ እንዲቀርቡ ወደ ሃገር ፍቅር፣ ብሔራዊና ራስ ቴያትር ቤቶች ይላካሉ። ዝግጅታቸው ተጠናቆ ለሕዝብ ከመታየታቸው በፊት ደግሞ ሄደን እንመለከታለን። ሃሳባችንን እንሰጣለን። ቴያትሩ ለሕዝብ ከቀረበ ወዲያ ግን ከሕዝብ ጋር ሆነን ለመመልከት እንቸገር ነበር። በመንግስት ትእዛዝ የህዝብ ደህንነት ሰዎች ቴያትርም ሆነ ሲኒማ እንደልባቸው እየገቡ ማየት እንዲችሉ ነፃ የመግቢያ ካርድ ሲሰጣቸው እኛ መግባት የምንችለው በወረፋ በምናገኘው ካርድ ነበር። የመምሪያ ኃላፊያችን ጥያቄያችንን ስላልመለሱልን ወደ ሚኒስትሩ ለመሄድ ተስማማን። ሻለቃ በፈገግታ ተቀበሉን። ሃሳባችንን በግልጽ ካቀረብንና ለጥያቄዎቻቸው ተገቢውን መልስ ከሰጠን በኋላም ለሥራችን አስፈላጊ መሆኑን ተረድተው ትእዛዝ ሰጡልን። በዚህም ከሥር የነበረብንን መሰናክል ለማለፍና የእያንዳንዳችን ፎቶግራፍ ያለበትን የመግቢያ ካርድ ለማግኘት ቻልን።

ከሁለገቧ የጥበብ ሰው ከዓለምፀሐይ ወዳጆ ጋር በዕውቁ የሙዚቃ ባለሙያ ጥላሁን ገሠሠ ሕይወት ዙሪያ በቅርቡ ተወያይቼ ነበር። ታዲያ በዚሁ ጊዜ የሻለቃ ግርማን ሌላ አስተዋጽኦ ስታነሳልኝ፣

“በአንድ ወቅት ጥላሁን የመንፈስ ጭንቀትና መረበሽ ተፈጥሮበት ነበር። … አማኑኤል ሆስፒታል ሁሉ ገብቶ የነበረበት ጊዜ ነው። ስለዚህ በባህል ሚኒስትሩ በሻለቃ ግርማ ይልማ መሪነት አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥላሁንን ወደ ሲቪል መ/ቤት ለማዛወር ጥረት ይደረግ ነበር። ሆኖም በጦሩ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመን። ጥላሁን የሠራዊቱ አርማ ነው፣ ጦሩን ለቆ የትም መሄድ የለበትም የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ አቀረቡ። ደርግም ቢሆን በጦሩ ዘንድ ቅሬታ ያስከትላሉ የሚባሉ ነገሮችን በጥንቃቄ ነበር የሚመለከታቸው። ሻለቃ ግርማና የሚመሩት ኮሚቴ አባላት ደግሞ ጥላሁን የጦር ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን የሲቪሉም፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃብት ነው ብለን ጠንክረን በመከራከራችን ተሳክቶ ወደኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ሊዛወር ችሏል። በልዩ ትዕይንተ ጥበባት ዝግጅቶችና በሌሎች መድረኮች ላይ ተጫውቶም ተመልካቾቹን አስደስቷል። የደመወዙ መነሻም በማስተርስ ደረጃ እንዲሆን ነው የተደረገለት። በዚህ አጋጣሚ ሻለቃ ግርማ ይልማን ለተጫወቱት ትልቅ ሚና ሳላመሰግናቸው አላልፍም።” ብላ ነበር። (ታዛ መጽሔት፣ ቅጽ 4፣ ቁ.38 )

አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ባልደረባ የነበረው አሥራት አንለይ የጻፈላቸውንና ባለቤቱ እቴነሽ አበበ ድኅረ ሞቱ ባሳተመችለት “የመጀመሪያዪቱ” የተሰኘ የግጥም መድበል (2000 ዓ፣ም) “በቧልትም ተዘከር ” በሚል የቀረበውን ግጥም መጥነን እናቅርብላችሁ።

የሰብአዊነትህ ብርታት
የሠፊው ልቦናህ ትእግስት
በሩቅ ለሚታይህ ተስፋ
ሕዝባችን እንዲንሠራራ
ሕይወቱ እንዲያንሠራራ
ባህላችን እንዲያኮራ፤
ነገር ግን የፊት ገጹ
የታዛቢነት ተግሳጹ
ሲቀየም እያገኘሁት
በእርግጥ እኔ ፈራሁት።
ሃሳዊነቴን ነገረኝ
ነውሬን ድክመቴን አሳየኝ
ተምሳሌነትህ ጥናቱ
በሹመት ያለማበቱ
በነገር ያለማየቱ።
ለሃገርህ ፍቅር ክብር
ይልማ ይዋል ጦሙን ሲያድር
ኧረ ያንተ ነገር ውስጥህ
ጭራቅ ሁሉ የሚጠላህ
ነገረኞች የከበቡህ
….
አንተ ሐቅ የምትለኝ፣ ለኔ ከቶ ላይስማማኝ
የእውነት ፍቅር አሳውሮኝ፣ ለድለላ ሳትመቼኝ
ተው ግርማ በሞቴ፣ አንድ ቀን እንኳ ሌባ ሁን።

ኧረ ተው እመን በጎሳ
አጥንታችን እንቋጠር፣ ክርስትና እንናሳ
ግርማ ያይኔ ጋሬጣ
የኛ የሌቦቹ ባላንጣ። …

ሻለቃ ግርማ ይልማ በየካቲት 1975 ዓ.ም ከማስታወቂያ ሚኒስትርነት ወደባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስትርነት በሹመት የተዛወሩ ሲሆን ከሰኔ ወር 1982 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሶቪዬት ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሃገራቸውን አገልግለዋል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የደርግ መንግስት ወደቀና አዲሱ የኢሕአዴግ መንግስት ሥልጣን ያዘ። በየሃገራቱ ያሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ሁሉ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱም ጥሪ አደረገ። ብዙውን ጊዜ በሳቸው ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ዝቅ ባለ የኃላፊነት ቦታ ያሉ ሁሉ በወጡበት መቅረቱን እንደሚመርጡ የታወቀ ነው። እንኳንና ምንነቱ ገና በቅጡ ያልታወቀ አዲስ መንግስት ወደሥልጣን መጥቶ ለወትሮውም ተመላሹ ጥቂት ነበር። በሚኒስትርነት የሥልጣን መንበር ላይ ቢቆዩም፣ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንደነበሩ ቢያውቁም፣ በአሥራት ግጥም ውስጥ እንደተገለጸው በራሳቸው፣ በንጽሕናቸው የሚተማመኑት አምባሳደር ግርማ ይልማ ግን ጥሪውን ተቀብለው ወደሃገራቸው ተመለሱ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በክብር ተቀበላቸው።

ያም ሆኖ በዘመነ ደርግ የደረሰውን ጥፋት ወደኋላ ተመልሰው ሲያስታውሱ የሚሰማቸውን፡-

“የ1966ቱን ሕዝባዊ አብዮት ዓላማ አምኜበትና ተቀብዬ የኢሠፓአኮንና የኢሠፓን ፕሮግራሞች፣ የኢሕዲሪን ሕገመንግስት መነሻዬ በማድረግ ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት አገልግያለሁ። በግሌ ከሕግና ከመርህ ውጭ ያደረግሁት ነገር የለም። … በሠራተኛውና በሕዝብ ስም የተፈጸመው አንዳንድ ግፍና ኢሰብአዊ ድርጊት ግን ያሳፍረኛል። በጋራ የተጠያቂነት ስሜትም ያሳድርብኛል። ሆን ተብሎ ወይም በስህተት፣ በችኩልነት፣ በማንአለብኝነት፣ በቂም በቀልና በአጉል እልህ የተፈጸመው ሁሉ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች የፖለቲካ ትርምስ የሚጠበቅና የሚደርስ ቢሆንም ዛሬ በነፃ ህሊና ሳየው በኢትዮጵያና በልጆቿ ላይ የደረሰው መከራና ስቃይ አእምሮን የሚሰቀጥጥ ነው። ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠላ ነው።” በማለት በጽሑፍ ገልጸውት ነበር። ሻለቃ ግርማ ዛሬም ካሉበት አሜሪካ ሆነው ስለሃገራቸው ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ። በውጪ ላለን ወገኖቻቸውም ሃሳባቸውን በነፃነት ያጋራሉ፣ ይመክራሉ። የተዛባ ወይም የተሳሳተ የመሰላቸው ነገር እንዲቃና ጥረት ያደርጋሉ። በአንድ ወቅት በአቶ አሰፋ ጫቦ ላይ አላግባብ ተሰነዘረ ያሉትን ነቀፋ የሞገቱበት ጽሑፍ በጋዜጣ ላይ ወጥቶ ማንበቤ ትዝ ይለኛል።

በመጨረሻ ከዚችው የታዛ መጽሔት ጋር የተያያዘ አንድ ጉዳይ ላንሳና ላጠቃልል። የታዛ የመጀመሪያ እትም በመስከረም 2010 ዓ.ም እንደወጣ አንድ ቅጂ ለሻለቃ ግርማ ላክሁላቸውና አንብበው አበረታች ሃሳብ ሰጡን። ከዚህም ጋር ወርኃዊ ክፍያ እየፈጸሙ መጽሔቷን በመደበኛነት የሚያገኙበትን መንገድ እንዳመቻችላቸው ነገሩኝ። ሆኖም በእኛ ድክመት ያን ማድረግ ባለመቻላችንና እኔም ኢትዮጵያ ስለነበርኩ ሁለተኛዋ ቅጂ በአንጋፋው ከያኒ ተክሌ ደስታ በኩል እንድትደርሳቸው አደረግኩ። ያኔ ታዲያ ኮስተር ብለው፣ “ይህ መጽሔት ብዙ የተደከመበት፣ ብዙ ምሁራን የሚጽፉበትና ብዙ ገንዘብም የወጣበት ሆኖ ሳለ እኔ በነጻ የምቀበልበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ በኋላ የክፍያ ሥርዓት ዘርግታችሁ ሳታሳውቁኝ መጽሔቱን እንዳትልኩልኝ” አሉን። ይህን ስሰማ መጀመሪያ ደነገጥኩ፣ ቀጥሎ ገረመኝ። ረጋ ብዬ ሳስበው ግን ያንኑ የማውቀውን ሰብዕናቸውን ነው አግዝፎና አድምቆ ያሳየኝ – የሰውነት ተምሳሌትነታቸውን። ባለተሰጥኦው የጽሑፍ ሰው የረዥም ጊዜ የሕይወትና የሥራ ልምዳቸውን፣ ከመኮንንነት እስከ ሚኒስትርነትና አምባሳደርነት የዘለቀ ሙያቸውን፣ ለእኛና ለተከታዩም ትውልድ በጽሑፍ እንደሚያካፍሉን ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። ለዚህም ረጅም እድሜና ጤና እመኝላቸዋለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top