በላ ልበልሃ

ሻለቃ ጉዌንና የኢትዮ-ሱዳን ድንበር

ቅድመ ታሪክ

ስለ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ጉዳይ ሲወሳ ሻለቃ ጉዌን ወሰን መካለሉን ከሰራ ከ110 ዓመት በኋላ ዛሬም ስሙ እንደተነሳ ነው። አንዳንዴም ኢትዮጵያዊ ወይም ሱዳናዊ ሻለቃ እስኪመስለን ድረስ ስሙን እናወሳዋለን። የኢትዮ-ሱዳን ድንበር በአብዛኛው “የጉዌን ወሰን” እየተባለ በተለያዩ ድርሳኖች ውስጥ ይጠቀሳል። ጉዌን ከ1899 – 1900 ከብሉ ናይል ሮዜሪ እስከ ታችኛው ሶባት ጊዜውን በመቃኘት አሳልፏል። ከዚህ በኋላም ነው የጉዞውን ማስታወሻ ከትቦ ያኖረው። ለኢትዮጵያና ሱዳንም ድንበር እሱ የሰራው ካርታ እንደ መነሻ መዝገብነት ይቀርባል። የሰሞኑ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ይበልጥ ስሙን አግኖታል።

ለመሆኑ ጉዌን ማነው? የጉዌን ወሰንስ እንዴት ሊቆም ቻለ? የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል። ቻርለስ ዊሊያም ጉዌን የቤተሰቡ አራተኛ ልጅ ሲሆን በ1870 (እኤአ) ተወለዶ በ93 ዓመቱ በ1963 (እኤአ) ሞቷል። በሲኦን የጦር ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን በ1889 (እኤአ) በምክትል መቶ አለቃ ማእረግ ተመረቀ። ወታደራዊ አገልግሎትን በምእራብ አፍሪካ፣ በአውስትራሊያና መካከለኛው ምስራቅ ያገለገለ ሲሆን በኋላም የመረጃ መኮንን በመሆን በጦር መስሪያ ቤት ውስጥ ማገልገሉን ቀጠለ። እንግሊዝ ሱዳንን ከያዘች በኋላ የካርታ ማንሳት ስራ በመስራት በሱዳን ቆየ። በዚህ የሱዳን ቆይታው የኢትዮ-ሱዳን ወሰንን ካርታ በመቀየስ በዛሬው ጊዜ “የጉዌን ወሰን” የሚባለውን አጨቃጫቂ የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን ያሰመረና በኋላም እስከ ሜጀር ጀነራልነት ማእረግ የደረሰ መኮንን ነበር።

ኢትዮጵያና ሱዳን 1600 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለውን ድንበር የሚጋሩ ሃገራት ናቸው። ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር የተከለሉ ጎረቤታሞች ከመሆን አልፈው ብዙ የሚጋሩት የጋራ ገጽታዎች አላቸው። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በግሪኮች “ጥቁር” የሚለውን ትርጉም እንዲይዝ ሁሉ በዐረብኛ ሱዳን የሚለውም ቃል ተመሳሳይ ትርጓሜን ይዟል። የተለያዩ ብሄረሰቦችም ማለትም እንደ በርታ፣ ኑዌር፣ አኝዋክ ጎሳዎች በሁለቱም ሀገራት ይኖራሉ። የኢትዮጵያ የተለያዩ ወንዞች ወደ ሱዳን በመፍሰስ የሱዳንን በርሃዎች ያጠጣሉ። ያለመልማሉ። ካለ ኢትዮጵያ ወንዞች ሱዳንን ማሰብ እጅግ ይከብዳል። በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበሮች ቅይጣን የሆኑ ብሄረሰቦች ይኑሩ እንጂ ዋነኛ የሚባሉ የአማራና የትግራይ ጎሳዎች በሁለቱ ድንበር ተከፍለው አይኖሩም።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መካከለኛ አጋማሽ እስከ የመጀመሪያ አጋማሽ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሱዳን ወይም ግብጽ ራሳቸውን እንደ ሀገር ችለው የሚደራደሩ አልነበሩም። በቅኝ ግዛት የያዘቻቸውን ሱዳንና ግብጽን ወክላ ከኢትዮጵያ ጋር የምትደራደረው እንግሊዝ ብቻ ነበረች። ነጻ መንግስት ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር እንግሊዝ የኢትዮ-ሱዳንን፣ የኢትዮ-ኬንያንና የኢትዮ-ብሪታንያ ሶማሌ ላንድን ድንበሮች በተመለከተ የተለያዩ ውሎችና ስምምነቶችን ለማድረግ ሞክራለች።

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሚደረገው የድንበር ጉዳይ ለሁለቱ ሀገራት የፖለቲካ-ታሪክ ሁነኛ ስፍራ አለው። ወንድወሰን ተሾመ እንደጻፈው የአጼ ቴዎድሮስ የትውልድ ስፍራ የሆነቺው ቋራ የምትገኘው በሁለቱ ሀገራት ድንበር አዋሳኝ ላይ ነው። በሁለተኛ ምክንያትነት የሚነሳው አጼ ዮሐንስ ደርቡሾችን በመዋጋት በ1889 (እኤአ) ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ሰውተውበታል። በሦስተኛ ደረጃ አጼ ኃይለስላሴ ከስደት የተመለሱት በእንግሊዝ ወታደሮች እየታገዙ በሱዳን ኢትዮጵያ ወሰን ላይ በምትገኝው ኦሜሮን ከተማ ሲሆን በፋሽስቶች ጫማ ስራ ወድቃ የነበረችውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓርማ ያውለበለቡበትና የሀገራችን የነጻነት መገለጫ ከተማ ናት። ሌላው ጉዳይ ሱዳን በፋሽስት ጦርነት ዘመን የኢትዮጵያ አርበኞች መጠጊያ መሆንዋ በራሱ ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያ ያላትን ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ቁርኝት ያሳያል። በአጠቃላይ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር አከባቢዎች ለኢትዮጵያ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የተለየ ስፍራ እንዳላቸው እሙን ነው።

አጼ ዮሐንስና የኢትዮሱዳን ግንኙነት

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጥንታዊና ብዙ ታሪካዊ ሁኔታዎችን ያሳለፈ ግንኙነት አላቸው። ሁነኛ የሆነው ግንኙነት ይበልጥ የሚገለጸው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነው። በመጀመሪያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ግብጾች ሱዳንን ከያዙ በኋላ ምጽዋን ይዘዋታል። በጉንዲትና በጉራኔ ጦርነት ጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ የግብጽን ጥቃት በሚያኮራ የጦር ስልታቸው መክተዋል። ግብጽን በቅኝ ግዛትነት እንግሊዞች በ1882 (እኤአ) ከያዙ በኋላ ግብጽ ትገዛቸው የነበሩ ግዛቶችን ሁሉ እንግሊዞች በበላይነት መምራት ጀመሩ። የሱዳን መሐዲስቶች ከፍተኛ የሆነ ፀረ-ኮሎኒያሊዝም ተቃውሞ በማስነሳት የግብጽን ጦር ከሰላ ላይ ከበቡ። እንግሊዞች ጣልቃ በመግባት አድሚራል ዊልያም ሂዌትን ወደ አጼ ዮሐንስ በመላክ የኢትዮጵያን ድጋፍ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት ሑዌት ወይም የአድዋ ስምምነት የሚባለውን ውል በ1884 (እኤአ) ተዋዋሉ። በዚህም ስምምነት ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር የተለያዩ ሸቀጦችን፣ ጥይቶችን እንዲሁም ግብጽ ጳጳሶች እንድትልክ ተመቻቸ። በጎስ የተባለው ስፍራም ከኢትዮጵያ እንዳይነካ ተደረገ። በዚህም አጼ ዮሐንስ የተከበቡትን የግብጽ ወታደሮች ከከሰላ፣ አሚዳብና ሳንሂች ከተሞች እንዲወጡ ማመቻቸታቸውን በወቅቱ የታተመው የኒውዮርክ ጋዜጣ ዘግቦታል።

ይህ አጼ ዮሐንስ የወሰዱት ርምጃ በኢትዮጵያና በደርቡሽ ጦር መካከል ጦርነት እንዲቀሰቀስ መንገድ ከፈተ። ጀግናው ራስ አሉላ በኡትማን ዲንክና የሚመራውን የመሐዲስቶች ሰራዊት በኩፊት ድል አደረገ። ይህን ሁኔታ ለመበቀል ሲሉ መሐዲስቶች አሶሳን ወርረው እስከ ነጆ (ወለጋ) አካባቢ እንደደረሱ ባህሩ ዘውዴ በታሪክ መጽሐፍ ላይ አስፍሮታል። በሰሜን በኩልም ደርቡሾች መተማን በመያዛቸው የጎጃሙ ንጉሥ የተክለ ሃይማኖት ጦር መጀመሪያ ላይ ድል ቢጎናጸፍም አጨራረሱ አላማረለትም ነበር። ከዚያም ደርቡሾች ተጠናክረው ደንቢያና ጎንደርን ተቆጣጠሩ። የደርቡሾች መሪ ከሊፋ አብደላህ ለአጼ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ላከ ፦ “… የምልህን ካደረክ ባንተ ላይ የጀመርኩትን ጦርነት አቆማለሁ፣ ሰራዊቴም ወደ ሀገርህ እንዳይገባ አዛለሁ” ሲል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ላከ።

አንደርሰን እንዳሰፈረው አጼ ዮሐንስም በተራቸው “… ዓላማ ለሌለው ነገር ድሆችን አንጨርስ፤ ከዚያ ይልቅ የጋራ ጠላታችን በሆኑት አውሮፓውያን ላይ እንተባበር። እንሱ የሚወሩኝ ከሆነ አንተንም የሚለቁ አይሆኑም፣ ሀገርህን ያጠፏታል… ስለዚህ ተስማምተን እነሱን መውጋትና መውረር ይኖርብናል” የሚለውን መለእክት ልከውለታል።

የሱዳኑ መሪ የዮሐንስን የሰላም ጥሪ ውድቅ በማድረግ ውጊያ አድርጎ ከአጼ ዮሐንስ ጦር ጋር መተማ ላይ ተዋግተዋል። ንጉሡ ከሰራዊታቸው ጋር ሆነው ጠላትን ፊት ለፊት ተጋፍጠው ሲታኮሱ በጥይት ተመተው ቆስለዋል። ቁስላቸው ጸንቶ በማግስትቱም ሕይወታቸው ያለፈው ንጉሠ ነገስቱ ከአንድ ቀን በኋላ ደርቡሾሽ አትባራ ወንዝ ዳር ሬሳቸውን ማርከው ጭንቅላታቸውን ቆርጠዋቸዋል። ምንም እንኳ አጼ ዮሐንስ እንግሊዞችን በመርዳት በጦር ሜዳ ለመሰዋት ቢበቁም እንግሊዞች ግን ቃላቸውን ባለመጠበቅ አዲስ ኃይል የሆኑት ጣሊያኖች ምጽዋን እንዲቆጣጠሩ አደረጉ።

አጼ ምኒልክና የእንግሊዝ ኢትዮጵያ የድንበር ስምምነት

ምኒልክ ስልጣነ መንግስታቸውን እንደተቆናጠጡ የነበረውን ችግር ስለሚያውቁ ከሱዳን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ፈለጉ። በተለይ ከኢጣሊያ በኩል የታያቸው አደጋ በማየሉ በአከባቢው የሚተባበራቸው ሀገር ማግኘት አስፈላጊ ነበር። ዳሩ ግን የሱዳኑ መሪ ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር የፈለገ አይመስልም። አልፎ ተርፎም ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ አውሮፓውያንን ለመውጋት አልፈለገም። ስለዚህ ኢትዮጵይ የቀራት ነገር በራሷ ጥንካሬ መተማመን ስለነበር ተዋግታ በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን አሸነፈች። የጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መጠናቀቅ የሚኒልክን አለምአቀፋዊ ስፍራ ይበልጥ አጎላው። አብዛኞቹ የአውሮፓ ጠንካራ ሀገራት የሆኑት ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጀርመን ከሚኒልክ ጋር ወዳጅነት ለማጠናከር ፈለጉ። ይህን የተመለከተው የሱዳኑ መሪ ከሊፋ አብደላህ ከሚኒልክ ጋር ግንኙነት ለማጠናከር ሻተ። ከሊፋው መልእክተኛውን መሐመድ ኦትማንን ወደ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ላከ። ከሊፋው መልእክተኛውን ሲልክ ግን ምኒልክ ከአውሮፓውያን ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ የሚጠይቅ ስለነበረው በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀረ። ቤሪ የተባለው ጸሐፊ እንዳስቀመጠው ምኒልክን በምስጢር አንግሎ-ግብጻውያንን ሱዳንን እንዲወሩ አስታወቀው። ይህን አደጋ የተገነዘበው ከሊፋ አብደላህ በቤኒሻንጉል ግዛት ሚኒልክን ያንገራግር ከነበረው የቤኒሻንጉል ሼህ ጋር ግኑኝነቱን አቋረጠ። ይህም ምኒልክን በቀላሉ አከባቢውን እንዲቆጣጠር ረዳው።

ከላይ እንዳነሳሁት የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን የመከለል ስራ ዋናው ቀያሽ ጉዌን ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በፊት በማንም ሌላ አካል ወሰኑን ለመከለል ወይም ለማወሰን አልተሞከረም። ጉዌን ራሱን አምሮ በ1937 (እኤአ) በጻፈው ማስታወሻ ጉዌንና ባልደረቦቹ የማዋሰን ስራቸውን ተረድተው ሲንቀሳቀሱ ከኢትዮጵያ በኩል ግን ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳልነበር አራት ነጥቦችን ጠቅሶ አስፍሯል። እነሱም ፦

  1. የአውሮፕላንና የሞተር ትራንስፖርት አለመኖርና አስፈላጊውን ቅኝት ለማድረግ አለመቻል
  2. የምግብና ውሃ አቅርቦት አለመኖር
  3. የኢትዮጵያ መንግስት የሰለጠነና የተማረ ተወካይ በኢትዮጵያ ወገን ማቅረብ አለመቻልና
  4. የኢትዮጵያ መንግስት በማካለሉ ሂደት አውሮፓውያንን ወክለውት እንዲሳተፉ ለማድረግ አለመፍቀዱ ነው ሲል ዘርዝሯል።

ሙላቱ ውብነህ የጉዌንን ሪፖርት ጠቅሶ እንደጻፈው “… ምንም እንኳ ኮሎኔል ሐሪንግተን ወሰኑን ሰርቬይ ለማድረግ ወስነናል በማለት ለአጼ ምኒልክ ቀድሞ ተደርጎ ደብዳቤ ቢጻፍላቸውም፣ ጉዌን በዚህ በምእራብ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ለአውራጃ አስተዳዳሪዎቹ ስለ ጉዌን መጎብኘት የተላከላቸው መልእክት አልነበረም። ስለዚህ አንዳንዶቹ አስተዳዳሪዎች በጥርጣሬ ሲመለከቱት አንዳንዶቹ ደግሞ ኃላፊነት መውሰድ ስላልፈለጉ በሚዘዋወርበት ጊዜ ተቸግሮ እንደነበር በሪፖርቱ ውስጥ በሰፊው ይገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል ወደ ወለጋ አከባቢ በተቃረበ ጊዜ ጊዳሜ ደርሶ ለመንቀሳቀስ ሲፈልግ የደጃች ጆቴ ሰዎች ምንም እንኳ መጀመሪያ በወዳጅነት መልክ ቢቀበሉትም፣ ከአዲስ አበባ ትእዛዝ እስኪመጣልን ድረስ እዚሁ አርፈህ ተቀመጥ በማለት ከወር በላይ አግተውት እንደነበር ይናገራል። በኋላ ግን ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ ሲመጣላቸው ሸኝተው ሰደውታል።”

ሌላው የሚነሳው ጠቃሚ ጉዳይ ጉዌን የኢትዮጵያን ወገን ወክሎ ነው ወይ ያለምንም ከልካይ ወሰኑን የከለለው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል። በዚህ ረገድ በባህሩ ዘውዴ ጥናት “ሁለቱንም ድንበሮች (የምእራቡ ከሱዳን ጋር፣ የደቡቡ ከኬንያ ጋር) ያለ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የከለለው ይኸው እንግሊዛዊ ሹም ጉዌን ነው። የሱዳንን ወሰን የከለለው በ1895 (1903) ሲሆን እንግሊልዞችና እነሱንም ተከትለው ነጻ መንግስት ካቋቋሙ በኋላ ሱዳኖች ጉዌን የኢትዮጵያ ወገን እንዲወክል ከምኒልክ ስልጣን ተሰጥቶት ነበር የሚል ክርክር ሲያነሱ ቆይተዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ምኒልክ ይህን አይነት ስልጣን ለመስጠታቸው ምንም የሰነድ ማረጋገጫ የላቸውም። ነገሩ የሚመስለው የሚኒልክ ሃሳብ ለጊዜው ከጉዌን ጋር ሆኖ ወሰኑን የሚከልል የራሳቸው ሰው ባለማግኘታቸው ስራው እንዳይስተጓጎል ጉዌን ውሉን ተከትሎ ወሰኑን እንዲከልል፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ሁነኛ ሰው ባገኘች ጊዜ ትክክለኛነቱን ካረጋገጠች በኋላ እንደሚጸና ነው። ይህንንም የሚያረጋግጡ የታሪክ ሰነዶች ተገኝተዋል። ለምሳሌ ምኒልክ መስከረም 12 ቀን፣ 1897 (1905) ለለቃ ቄለም ገዥ ለደጃዝማች ጆቴ በጻፉት ደብዳቤ ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል ይገኝበታል ፦ “የፈረንጁንም የሚጀር ጉዌን ነገር ከዚህ ቀደም ልኬብሃለው። አሁንም አሱ ወሰን ባደረገው እናንተም አትለፉ። እነዚያም ከዚያ ወዲህ አያልፉም። በሌላ ጊዜ ካርታ የሚያውቅ ሰው ሰድጄ ይጨርሳል” ይላል። በአጠቃላይ እንግሊዝ የቀበረው ፈንጂ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላም እያመሰን መቀጠሉ አይቀሬ ነው።

ለዛሬው ቅድመ ታሪኩን በዚህ ላሳርግና በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ምን ተደረገ? በ1972 ዓ.ም ለዘብተኛ አቋም በኢትዮጵያ በኩል ለምን ተወሰደ? በደርግ መንግስትና ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሁለቱ ሀገራት ወሰን ላይ ችካል እንደሚቸከል ካሳወቁ በኋላ ጉዳዩ ምን ደረሰ? የሚለውን ይዤ ለመቅረብ እሞክራለሁ። የከርሞ ሰው ይበለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top