አድባራተ ጥበብ

ሥነጽሑፋዊ ቱሪዝም፤ ምንነቱና ለኢትዮጵያ የሚኾን በረከቱ

ጥላሁን በጅቷል (ዶ/ር)

ሥነጽሑፋዊ ቱሪዝም ምንድነው?

ሥንጽሑፋዊ ቱሪዝም ከባህላዊ ቱሪዝም ወገን የሚመመደብ ኾኖ ልቦለዳዊ በኾኑ ሥራዎች እና ከደራሲዎቻቸው ሕይወት ጋር የተያያዘ የቱሪዝም ዓይነት ነው፡፡ ሥነጽሑፋዊ ቱሪዝም ማንበብንና መጓዝን በማስተሳሰር ሰዎች ከዚህ ቀደም ያነበቧቸውን ሥነጽሑፋዊ ሥራዎች መቼቶች፣ ገጸባህሪያት በገሃዱ ዓለም ‹‹ሥጋ ነስተው›› እንዲመለከቷቸው ያስችላል፡፡ በተጨማሪም አንባቢዎች የሚያደንቋቸው ደራሲዎች ሥራዎቻቸውን በምን ኹኔታ እንደጻፏቸው፣ ደራሲዎቹ ምን ዓይነት ሕይወት ሲመሩ እንደነበረ፣ ምን ዓይነት ቤት ውስጥ እንደኖሩ ወዘተ መረጃ በመስጠት ትውስታንና ቦታን የማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በሌላ አነጋገር የሥነጽሑፍ ቱሪዝም በልቦለድ ውስጥ ያሉ ምናባዊ ቦታዎችንና ገጸባህሪያትን ሳይቀር ወደ ገሃዱ ዓለም በማምጣት ሰዎች ያነበቡትን በእውኑ ዓለም እንዲኖሩ ከማስቻሉ ጎን ለጎን ለቦታዎች ልዩ መታወቂያ በመኾን ቱሪዝምን ያጠናክራል ብሎም የገቢ ምንጭ ይኾናል፡፡ ባደጉት አገራት በተለይም በአውሮፓ ሥነጽሑፋዊ ቱሪዝም የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲኾን ብዙ አገራት ከዚህ የቱሪዝም ዘውግ መጠቀም ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህች ጽሑፍ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን አገራት ተሞክሮ በማየት እንደምን ይህንን የቱሪዝም ዓይነት በአገራችን መተግበር እንደምንችል የሚጠቁም አጭር ቅኝት አደርጋለሁ፡፡

ጣልያን፣ ቬሮና ከተማና የሼክስፒር ሥራዎች

በሰሜን ምስራቅ ጣልያን የምትገኝ ቬሮና የተሰኘች ከተማ እድሜ ለሼክስፒር የሚያሰኝ ጸጋ አግኝታለች – ምስጋና ለሥነጽሑፋዊ ቱሪዝም! የሼክስፒር ሮሜዎና ዡልየት እና ዘ ቱ ጀንትልሜን ኦቭ ቬሮና የተሰኙ ሁለት ተውኔቶች መቼቶች በዚህች በቬሮና ከተማ በሞኾናቸው ከተማዋ በሥነጽሑፍ ቱሪዝም ረገድ ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ ያስመድባታል፡፡ በተለይ ከሮሜዎና ዡልየት ተውኔት የተቀዱት የዡልየት ሀውልት፣ ሮሜዎና ዡልየት በሚስጥር ይገናኙበታል ተብሎ የሚታመነው የቅዱስ ዜኖ ማጂዮሬ ባዚሊካ ቤተክርሰቲያን፣ ዡልየት የምትቆምበት ሰገነት/ባልኮኒ ከብዙ በጥቂቱ በዚህች ከተማ ጎብኚዎች የሚመለከቷቸውና አስጎብኚ ድርጅቶችም ሊያዩአቸው የሚገቡ ከሚሏቸው ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህች ከተማ የዡልየት ክለብ (Club di Giulietta) የተሰኘ በጎ አድራጊ ማኅበር ከተለያዩ የዓላማችን ክፍሎች ሰዎች ምናባዊ ለኾነችው ዡልየት የሚጽፏቸውን ደብዳቤዎች እያነበቡ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ሰዎች ለዡልየት በደብዳቤዎቻቸው ከሚገልጹላት ጉዳዮች መካከል በፍቅር ሕይወታቸው የደረሰባቸውን የልብ ስብራት እና ያፈቀሩትን ሰው ስለማጣት አለያም ሰለማግኘት ጨምሮ በርካታ የፍቅር ሚስጥሮቻቸውን በማካፈል መፍትሄ የሚሹ ጥያቄዎችን ጭምር ይጠይቋታል፡፡ ይህ ክለብ በዓመት ከስድት ሺህ በላይ ደብዳቤዎች የሚደርሱት ሲኾን ወደ 15 የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞች ደብዳቤዎቹን እያነበቡ በእጃቸው/በእስክሪፕቶ በመጻፍ መልስ ይሰጣሉ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ደግሞ የዚህን ልማድ ፋይዳ ከከታማዋ መታወቂያነትና ከቱሪዝም አንጻር በቅጡ ስለተረዳ የመልስ መላኪያውን የፖስታ ወጪ ይሸፍናል፡፡ ይህ ትውፊት ክፍለዘመናትን ያስቆጠረ ሲኾን ደብዳቤ መላክ ሳይጀመር ጎብኚዎች የምናባዊቷ የዡልየት መቃብር እንደኾነ በሚታመነው ሥፍራ ለዡልየት ስለግል የፍቅር ሚስጥሮቻቸው ማስተዋሻ ይጽፉ እንደነበር ይነገራል፡፡ የዡልየትና የቬሮና ከተማ ቁርኝት ከቱሪዝም አልፎ፣ ተርፎ ተውፊቱ ላይ መሰረት ያደረገ ሌተርስ ቱ ዡልየት (Letters to Juliet) የተሰኘ ተወዳጅ ፊልም በ2010 እ.አ.አ. ለመሰራት ምክንያት ኾኗል፡፡

አየርላንድ፤ ደብሊን እና ጀምስ ጆይስ

አየርላንዳዊው ጀምስ ጆይስ በጻፈው፣ በምዕራባውያን ሥነጽሑፍ አዲስ መንገድ እንደከፈተ የሚታመነውና በ1922 እ.አ.አ በታተመበት ወቅት በሀያሲያንና አንባቢዎች ዘንድ በወቅቱ እጅግ አወዛጋቢና አነጋጋሪ የነበረው ዩሊሲዝ (Ulysses) የተሰኘው ልቦለድ ሊዮፖልድ ብሉም የተባለ ገጸባህሪ አለው፡፡ ይህ ልቦለድ የብሉምን የአንድ ቀን ውሎ (ጁን 16፣ 1904 እ.አ.አ) የሚተርክ ሲኾን በአየርላንድ ደብሊን ጁን 16 ቀን ብሉምዝዴይ (Bloomsday) በሚል ዓመታዊ በዓል ኾኖ ይከበራል፡፡ በዚህ በዓል ምንባዊው ብሉም ደብሊን ከተማ ውስጥ የተጓዛቸውን ሥፍራዎች መጓዝ፣ ከመጽሐፉ ምዕራፎችን ማንበብ፣ እና ከልቦለዱ ቅንጫቢዎች መተወን ከበራው ከሚያካትታቸው ክዋኔዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህ በዓል በርካታ ቱሪስቶችን ከተለያዩ አገራት ወደ ደብሊን ከተማ በየዓመቱ ይስባል፡፡ ይህ ልቦለድ-ወለድ በዓል ከአየርላንድ አልፎ በበርካታ አገራት (በጣልያን፣ በሀንጋሪ፣ በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ፣ በአውስትራልያ፣ በእንግሊዝ፣ወዘተ) የሚከበር ሲኾን በተለይ በሀንጋሪ የልቦለዳዊው ሊዮፖልድ ብሉም አባት የኾኑት የአቶ ብሉም የትውልድ ሥፍራ የኾነችው ስዞምባትሊ (Szombathely) ሀንጋሪ ውስጥ በመኾኗ ከ1994 ጀምሮ ይህ በዓል በዚች ከተማ በየዓመቱ ይከበራል፡፡

ፈረንሳይ፤ ኮልማርና ኦጉስት ባርቶልዲ (1837 ኮልማር– 1904 ፓሪስ)

ኮልማር በምትባል ከተማ አንድ ለጎብኚዎች ክፍት የኾነ ቤት አለ፡፡ ይህ ቤት (የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደጎበኘው) ቀራጺው ፍሬዴሪክ ኦጉስት ባርቶልዲ የተወለደበትና የቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት የነበረ ሲኾን አሁን ወደ ሙዝየምነት ተቀይሮ የዚህ ቀራጺ ሥራዎች የሚጎበኝበት ቤት ኾኗል፡፡ በተጨማሪም ይህች ከተማ እጅግ በጣም ታዋቂዋን የቀራጺውን ሥራ (በኒውዮርክ ያለችው የነጻነት ሀውልትን) አምሳያ በመቶኛ ሙት ዓመቱ ማለትም በ2004 እ.አ.አ በከታማዋ አደባባይ በመትከል ለከተማዋ ልዩ መታወቂያ አድርጋዋለች፡፡ የባርቶልዲን ቤት ለአብነት አነሳነው እንጂ ፈረንሳይ ከ185 በላይ የደራሲያን ቤቶች አሏት፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ በፊት አብዛኞቹ ከደራሲያንና ከኪነጥበብ ሰዎች ጋር የተያያዙ ቤቶች በፈረንሳይ አገር ቤቶቹን እንደ ቅርስ ከመጠበቅ የዘለለ ሚና አልነበራቸውም፡፡ ከ1990ዎቹ በኋላ ግን በተለይ የደራሲዎች ቤቶች የግዛቶችንና የከተሞችን ምስል በማስተዋወቅ በኩል ያላቸውን ፋይዳ በመረዳት ከባህል ቱሪዝም አንጻር ማየት ተጀምሯል፡፡ በመኾኑም ከ1997 ወዲህ የደራሲዎች ቤቶች በልዩ ኹኔታ የጸሐፍት ቤቶች እና የሥነጽሑፍ ቅርስ ብሔራዊ ፌደሬሽን (Fédération nationale des maisons d’écrivain & des patrimoines littéraires) በተሰኘ ፌደሬሽን ስር እየተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ፌደሬሽንም የነዚህን ቤቶች ተገቢ ጥበቃ፣ እውቅናና በባህል በኩል ያላቸውን ተጽዕኖ ለማጎልበት ተብሎ የተቋቋመ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፈረንሳይ የባህላና የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር የታዋቂ ሰዎች ቤቶች (Maison des Illustres) የሚል በመጨመር በ2013 እ.አ.አ 171 የሚኾኑ የታዋቂ ሰዎች፣ የባለስልጣናትና የአርቲስቶች ቤቶች በዚህ ስያሜ ስር የተመዘገቡ ሲኾን ከነዚህ ውስጥ 75 የሚኾኑት የጸሐፍት ቤቶች ናቸው (Bonnoit-Mirloup 2016)፡፡

እንግሊዝ፤ ለንደን ፒተር ፓን፣ ሼክስፒርና ቻርለስ ዲክንስ

የስኮትላንዳዊው ደራሲና ጸሐፌተውኔት ጀምስ ማቲው ባሪ (1860-1937) የፈጠራ ውጤት የኾነውና በገጸባህሪው ስም የሚጠራው ፒተር ፓን ድርሰት በመላው ዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ሥራዎች አንዱ ነው፡፡ ዋናው ገጸባህሪ ፒተር ፓን ተንኮለኛ ትንሽ ልጅ ሲኾን ዋና መለያው መብረር የሚችል መኾኑና የማያድግ መኾኑ ነው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ፒተር ፓን የልጅነትና የገራገርነት እንዲኹም እውነታን ያለመቀበል ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ገጸባህሪ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ፒተር ፓን ሁሌ የማያድግ ልጅ ኾኖ መሳሉ በሥነልቡና ፒተር ፓን ሲንድረም (Peter Pan Syndrome) በመባል ለሚታወቀውና አንድ ግልሰብ እንዳደገ ወይም አዋቂ እንደኾነ ያለመቀበል ችግርን ለመግለጫ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ወደዋናው ነጥብ እንመለስና፣ ይህ ታዋቂ ገጸባህሪ በለንደን ከተማ ኬንሲንግተን በተሰኘ መናፈሻ ውስጥ በ1902 ሀውልት የቆመለት ሲኾን ሀውልቱን የቀረጸው ሰር ጆርጅ ፍራምፕተን ሲኾን ይህ ሰው የቀረጻቸው ተጨማሪ ስድስት ሀውልቶች ቤልጂየም ብራሰልስ፣ አሜሪካና አውስትራሊያን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ይገኛሉ፡፡ ይህ ሀውልት አንባቢዎች ከልጅነተቻው ጀምሮ ባነበቧቸው የፒተር ፓን ተከታታይ መጻሕፍትና በድርሰቶቹ ላይ ተመስርተው በተሠሩ ፊልሞች የሚያውቁትን ፒተር ፓንን በገሃዱ ዓለም የቆመለትን ሀውልት ማየት ሀውለቱ ባለበት ሀገራት በሚያደርጓቸው ጉዞ ማየት የሚሹት ሥነጽሑፋዊ መዳረሻቸው ለመኾን በቅቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዊሊያም ሼክስፒር ግሎብ ቲያትር እና ቻርለስ ዲክንስ አንድ ሦስት የሚኾኑ ልቦለዶቹን የጻፈበት ቤቱና አሁን የቻርለስ ዲክንስ ሚዝየም የኾነው ቤት ከብዙ በጥቂቱ የውጭ አገር ዜጎችም ኾኑ እንግሊዛውያን በለንደን ቆይታዎቻቸው የሚጎበኟቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ በተለይ የቻርለስ ዲክንስ ሚዝየም በአገራችን የደራሲያንና የታዋቂ ሰዎች ቤቶችን በመጠበቅ ረገድ ጠቃሚ ልምድ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይኸውም በ1923 እ.አ.አ የዲክንስ ቤት የሚገኝበት ሕንጻ ለዘመናዊ ግንባታ መፍረስ የነበረበት ቢኾንም ሁለት አስርት ቀደም ብሎ በ1902 የተቋቋመው ዲክንስ ፌሎውሽፕ የተሰኘ ማኅበር ሕንጻውን ከመፍረስ በመታደግ በ1925 እ.አ.አ የዲክንስ ቤት ሚዝየም በሚል አስመርቆ የደራሲውን ሥራዎች፣ ረቂቆች፣ የተወሰኑ አልባሳቱን ጨምሮ ልዩ፣ ልዩ ቁሳቁሶቹን ለጎብኚዎችና አጥኚዎች በሚዝየሙ ለእይታ አኑሯል፡፡

ከዚህ በላይ ካየናቸው የጥቂት አገራትን ተሞክሮ ተነስተን በዚህ የቱሪዝም ዓይነት ሀገራችን ያላትን አቅምና በምን መልኩ ሥነጽሑፋዊ ቱሪዝምን ማስፋፋት እንደሚቻል አጭር ቅኝት እናደርግ፡፡

የሥነጽሑፋዊ ቱሪዝም አቅም በኢትዮጵያ

በአንድ ክፍለዘመን እድሜ በላይ ያስቆጠረው የአገራችን ዘመናዊ የሥነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የልቦለድ ሥራዎች ከአይረሴ ገጸባህሪዎቻቸው ጋር አሉን፡፡ ይኹንና የልቦለዶቹን መቼቶችና ገጸባህሪያት ለሥነጽሑፍ ቱሪዝም ማዋል ለጊዜው ባይኾንልን እንኳ የደራሲዎቻችንን፣ የሰዓሊዎቻችንን፣ ወዘተ መኖሪያ ቤቶች፣ የትውልድ ከተማ፣ ቀዬ፣ የተማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች ወዘተ ለዚህ ዓላማ ልናውላቸው የምንችል ሲኾን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የክልል ቢሮዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የቅርስ ጥበቃ አስተዳደር ቢሮዎች የሚከተሉትን ጥቆማዎች ከግንዛቤ ቢያስገቡ የሥነጽፍ ቱሪዝምን በአገራችን መተግበር ይቻላል፡፡

የታዋቂ ደራሲዎችን ቤቶችና ሌሎች ቅርሶችን መለየት፣ መመዝገብ፣ መጠበቅ

በቅርቡ ይህን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ምክንያት የኾነኝ አንድ መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ተመለከትኩ፡፡ ይኸውም ከላይ እንዳየነው በለንደን ከተማ የቻርለስ ዲክንስ ቤት ለዘመናዊ ሕንጻ ግንባታ በ1923 ተጋርጦበት እንደነበረው ያለ የመፍረስ አደጋ ዓይነት ችግር በደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ ቤትም ላይ መደቀኑን በፌስቡክ ላይ ሰዎች ሲቀባበሉት ተመለከትኩ፡፡ ይኹንና የጉዳዩን እውነታነት ለማጣራት ብዙም ሙከራ አላደረግኩም ምክንያቱም ይህ በቅርስ ላይ የመፍረድ ክስተት ለሀገራችን እንግዳ ስላልኾነ የደራሲ ሀዲስ ቤት ገጥሞታል የተባለው ዕጣፈንታ ተጨባጭ ኾነም አልኾነም መሰል እርምጃ በርሳቸው ቤት ላይም ላያቆም ይችላል፡፡ አንድን ቅርስ አፍርሶ ዘመናዊ-ተብዬ የንግድ ሕንጻ ሊሰጥ ከሚችለው ግልጋሎትና ትርፍ ባልተናነሰ ከቅርስና ቱሪዝም ጥበቃ የሚገኘውን ዘርፈብዙ ትርፍ በቅጡ እስክንረዳ ድረስ፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ፕላነሮችና በየደረጃው ያሉ አካላት ባህልና የከተማን እድገት አጣጥሞ ማስኬድ በሚገባ እስኪያስቡበት ድረስ ማፍረሱ ሊቀጥል ይችላል፡፡

በሌሎች አገራት ያለን የሥነጽሑፍ ቱሪዝም በረከት በአገራችን ለመቋደስ ካሉንና ምናልባትም ብዙ ድካም የማይጠይቀው ለደራሲያንና ለታዋቂ ግለሰቦች ቤቶች ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡ ለጊዜው ማደስና፣ መንከባከቡ እንኳ ባይሞላልን ቢያንስ ባለማፍረስ አስተዋጽኦ ማድረግን ብቻ የሚጠይቅ ‹‹ቀላል›› ሥራ ነው፡፡ የደራሲ ቤት አንዱ የሥነጽሑፍ ቱሪዝም መዳረሻ እንደመኾኑ ደራሲው የተወለደበት፣ የኖረበት፣ ወይም የጻፈበት ቤት ነው፡፡ ይኹንና የግድ የተወለደበት ወይም ረጅም ጊዜ የኖረበት ቤት ላይኾን ይችላል፡፡ እነዚህን ቤቶች ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግና ቤቶቹና ቅርሶቹን በሥፍራዎች መታወቂያነት በመጠቀም ከቱሪዝም ከሚገኘው ጥቅም በተጨመሪ እነዚህ የጥበብ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችና ቅርሶች ሥነጽሑፍን ለማበረታታት፣ የጥናትና የምርምር ተቋማት፣ የመማሪያ ማዕከላት፣ በክረምት የወጣቶች መርሀግብሮች ማከናወኛ፣ ለጥበብ ሰዎች ጊዜያዊ መኖሪያ/ማረፊያ፣ ልዩ፣ ልዩ የባህልና የኪነጥበብ ዝግጅቶችና ፌስቲቫሎች ማካሄጃ ሥፍራ በመኾን ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ (Bonnoit-Mirloup 2016)፡፡ ከቤቶች በተጨማሪ ታዋቂ ደራሲዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቁሳቁሶች፣ የድርሰት ረቂቆች፣ እና ልዩ፣ ልዩ ንብረቶች ወደሙዝየም በተቀየረው ቤት ውስጥ ለጎብኚዎችና ለአጥኚዎች ክፍት ማድረግ ይቻላል፡፡ ቤቶቹ ለዚህ ዓይነቱ ዓላማ ከተሰናዱ፣ የደራሲያኑ ቤተሰቦችና ወዳጆችም ደራሲዎቹን የተመለከቱ ንዋያትን ለመለገስ መነሳሳታቸው አይቀርም።

የታዋቂ ደራሲዎችና ከያኒያን የትውልድ ከተማ/መንደር/ትምህርት ቤት

ሌላው የታዋቂ ደራሲያን፣ ጸሐፍት፣ ከያኒያን፣ ሙዚቀኞች፣ ወዘተ የትውልድ ከተሞች፣ መንደሮች፣ ምናልባትም የተማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች ጭምር በመርሀ ጉዞ (travel guide)፣ ጉዞ ካርታዎችና በቱሪዝም መረጃ መጽሔቶች ውስጥ ማካተት ለቱሪዝም መዳረሻዎች ተጨማሪ መታወቂያነት ያላብሳሉ፡፡ ለአብነት ያህል የነአፈወርቅ ገብረየሱስ፣ ሀዲስ ዓለምአየሁ፣ መንግስቱ ለማ፣ ዮፍታሄ ንጉሴ፣ ጸጋዬ ገ/መድህን፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ አቤ ጉበኛ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ዓሊ ቢራ፣ አስቴር አወቀ፣ ወዘተ የትውልድ ከተሞች/መንደሮች የጎብኚዎች የጉዞ ካርታዎችና የቱሪዝም መስህብ መጽሔቶች ላይ ቢካተቱ ቢያንስ የአገርውስጥ ጎብኚዎች ለቱሪዝም ሥፍራው የሚሰጡት ትኩረት ላይ በጎ አመለካከት በመጨመር ጎብኚውን ከሥፍራው ጋር የማስተሳሰር እድል ይፈጥራል፡፡

መቼቶችና የገጸባህሪያት የጉዞ ፈለግን ‹‹የሥነጽሑፍ መዳረሻ›› (“literary destinations”)ማድረግ

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ‹‹ህያው ጉዞ›› በሚል ዝግጅት የፍቅር እስከመቃብርን መቼት ያካለለ ጉዞ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህ ጅምር መልካም ነበር፡፡ እንዲህ መሰል ጉዞዎች ልቦለድንና እውኑን ዓለም በማስተሳሰር የሥነጽሑፍን ኃያልነት በትውልድ ውስጥ መቅረጽ ከማስቻሉ ጎን ለጎን መሰል ዘመን ተሸጋሪ የሥነጽፍ ሥራዎች መቼቶችን በመከተል የሚደረጉ ጉዞዎች የአገርቤት ቱሪዝምን በማሳደግ በትውልድ ውስጥ ማንበብንና መጓዝን ያሰርጻል። ማርክ ትዌይን “Travelling is fatal to prejudice and bigotry…” (“መጓዝ ጥራዝነጠቅነትንና ጠባብነትን ያኮላሻል…”) እንዲል ሰዎች “ከግርዘት እስከ ግንዘት” በአንድ አከባቢ እንዳይታሰሩ ይልቁንም ምናብ-ወለድ ጉዞዎች ሰዎችን ለጉዞ በማነሳሳት ተጨማሪ ቅመም በመኾን ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ውስጥ ጉልህና አይረሴ የኾኑ ገጸባህሪያት ሀውልቶችን ማቆም?

ከላይ እንዳየነው ምናባዊ ገጸባህሪያት በሌሎች አገሮች ሀውልት ቆሞላቸው፣ ቤትና ሥፍራ ተሰይሞላቸው እንደምናየው በአገራችን የሥነጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ የወል ትውስታ ውስጥ ቦታ ያገኙ ገጸባህሪያት ሀውልት ቢቆምላቸው አንድም ኪነጥበባዊ የርስበርስ ጋብቻ በማጠናከር ለሌላ የኪነት ውጤት መፈጠር ምክንያት ሲኾኑ በሌላ በኩል ደግሞ ለሥፍራዎች፣ ለአከባቢዎች ወይም ለከተሞች ልዩ መታወቂያነት ይተርፋሉ፤ ብሎም የቱሪዝም መዳረሻ ለመኾን ይበቃሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከፍቅር እስከመቃብር ሰብለ ወንጌል፣ በዛብህ እና ጉዱ ካሳ ለዚህ ሊታጩ የሚችሉ ሲኾን የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችን በማማከር ደግሞ ከቆዩት፣ ከመካከለኛ ጊዜና ከቅርብ ልቦለዶች መካከል አይረሴ ገጸባህሪያትን በመምረጥ የአንባቢን ብሎም የዜጎችን የጋራ ምናባዊ ጀግና ህያው ማድረግ ይቻላል፡፡

ይሁንና እዚህጋ አንዳንዶች በእውኑ ዓለም ለአገራቸውና ለወገናቸው ለደከሙ፣ ለታገሉ አጥንታቸውን ለከሰከሱ ደማቸውን ላፈሰሱ ጀግኖች የረባ ሀውልት ወይም መታሰቢያ ላልሠራ አገርና ማኅበረሰብ ለምናብ ዓለም ጀግኖች ሀውልት ይቁም ማለት ምን ይሉት ቅብጠት ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይህን መሰል ጥያቄ ምክንያታዊ ቢመስልም የሥነጽሑፍ ቱሪዝምን ለማስፋፋትና ከዘርፉ ለመጠቀም የገጸባህሪያት ሀውልት መሥራት አንዱ መንገድ እንጂ ብቸኛው እንዳልኾን ግን ልብ ማለት ያሻል፡፡ በሌላ በኩል ሌሎች አገሮች ለታሪካዊና በእውኑ ዓለም ባለውለታ ጀግኖቻቸው ሀውልት ከማቆም አልፈው ለምናባዊ ገጸባህሪያት ሀውልት መቅረጻቸውን ማየታችን በዚህ ረገድ ምንኛ ወደኋላ እንደቀረን ለማየትም እድል የሚሰጥ እይታ መኾኑን ልብ ይሏል፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ከበርቴዎች፣ ባለሆቴሎች፣ ባለሪዞርቶች ወዘተ አልፎ አልፎ ከጥበብ አይሉት ከመልዕክት የተፋቱ የሚመስሉ ቅርጻ-ቅርጾችን ብዙ ገንዘብ አፍስሰው ከሚያሠሩ ለሥነጽሑፋዊ ቱሪዝም አስተዋጽኦ ባለው መልኩ የቅርጽ ሥራዎቹን ቢያሠሩ መልካም ነው፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top