የጉዞ ማስታወሻ

ጉዞ ወደ ላልይበላ

ጷጉሜ አንድ ቀን 2012 አምና መሆኑ ነው፤ ባህልና ቱሪዝም ባመቻቸው ጉዞ ላይ ተሳታፊ ሆንኩ። መነሻ ሰዓቱ ገና 4:00 ስለነበር ቦሌ አከባቢ ቀድሜ ተገኝቼ ቁርስና ቡና ፍለጋ ከጥቂት ዙረት በኋላ ከአንዱ ካፌ አረፍ አልኩኝ። ቁርሱን ተመግቤ የምወደውን ቡና ቀመስኩ። ከእግር ኳስ ተጫዋች እስከ አቀንቃኝ፣ ከአትሌት እስከ ደራሲ፣ ከታዋቂ የስነልቦና ሐኪም እስከ አንጋፋ መሃንዲስ በሚበዙበት ካፌ ዓይኔ እንደ ከዚህ ቀደሙ አልተንቀለቀለም። ለቃለመጠይቅ ሌላ ጊዜ የሚንከላወሰው ልቤ ዛሬ ረግቷል። እባካችሁን ለቃለመጠይቅ ስልካችሁን ስጡኝ የሚለው የዘወትር አፒታይቴ የለም። ምክንያቱ ደግሞ የምሄድበት ቦታ ነው፡፡ ለመደመም መንደርደር ።

መራ ተክለሃይማኖት መስርቷት ስመ-መንግስቱ ገብረመስቀል ህያው አድርጓታል። በዓለም መዝገብ ላይ በነበረው የመስቀል ጦርነት (8 ጊዜ ያህል ተካሂዷል) ገለልተኝነት ኢትዮጲያዊ የመንፈስ ልዕልናችን ነበረች። ግብፅን ከነገስታቷ እስከ መሰሪ ጳጳሳቷ በአመራር ጥበብ ተገዳዳሪነታቸውን አሳይተዋል። አባይን እያሳዩ “ዋ! ትነኪንና” ብለዋል። ለምስራቃውያን ክርስትያኖችም መጠለያ ነበሩ። መራ ተክለሃይማኖት፣ ጠጠውድም፣ ጃን ስዩም፣ ግርማ ስዩም፣ መይራራ፣ ሐርቤ 1ኛ፣ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ሐርቤ 2ኛ፣ ቅዱስ ነአኩተለአብ እና ይትባረክ የራሳቸውን ጡብ ቢያቀብሉም እንደ ገብረ መስቀል ግን ረቂቅ ያደረጋት አልተገኘም፤ ላስታ ላሊበላን።

አውሮፕላኑ ውስጥ ቀድሜ ገብቻለሁ። ለሚድያ ፊታቸው አዲስ ያልሆኑ ሰዎች የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች እንደ ደሣለኝ እና ጋሽ አበራ ሞላ፣ ከደራሲ ጋሽ አያልነህ ሙላት የታሪክ ምሁሩ ረ/ፕሮፌሰር አበባው ቀስ በቀስ መቀመጫቸውን ያዙ። ተጓዥ ጋዜጠኛው ሄኖክ ስዩም ሠላምታ እየሰጠ ገባ። ማን ቀረ? የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሂሩት ወ/ማርያም የተለመደ ፈገግታቸውን አሳይተው ገቡ። ሠራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትሯ፣ ተከታትለው እንደገቡ ጢያራዋ ተንደረደረች። የበረራ አስተናጋጇ የአደጋ ጊዜ ጥንቃቄ መንገር እንደጀመረች ከያዝኩት ሁለት መፅሀፍ አንዱን ገለጥኩኝ። የፍሰሃ ያዜን “የኢትዮጲያ የ5ሺ ዓመት ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ” መጽሐፍ። የአፄ ላሊበላ ዘመነ መንግስት ላይ እንደነገሩ ንባብ ጀመርኩ። እንደ አያሌ ስለ ላሊበላ እንዳተፃፉ መፅሐፍት ከስሙ ትርጉም ጀመረ። መፅሀፉ ላልይበላ ማለት “ንብ ፀጋውን / ገዢውን/ አወቀ ማለት ነው” እያለ እንደ ጄራርድ ሮልፍ፣ ቢል ግርሀም፣ አችሊ ራፍሬይና ፍራንሲስ አልቫሬዝ ያሉ የውጭ ጸሃፍት ያሉትን እያጣቀሰ ስለ አስራአንዱ አብያተ-ክርስትያናት በቃላት የማይገለፅ ውበት ላይ በአፅንዖት ይናገራል። ማስክ የተሸፈኑት የበረራ አስተናጋጆች መጥተው የሚቀመስ ነገር ሲያማርጡን ንባቤን ገታሁ። የሚቀመሰውን እያጣጣምኩ ምድርን ቁልቁል አየኋት። ቡኒ አስፋልት የመሰለ ወንዝ፣ አረንጓዴ ሸራ ላይ ተበጥብጦ የተደፋ እርድ ይመስላል። ዎሊ መሆን አማረኝ። በራስ መቅናት ልጀምር ስለሆነ ልቤ መምታት ጀመረ። እንዲህም ሠርተን ነበር ለማለት፣ ሠማይ ላይ አንድ ሰዐት ቆይተን አረፍን።

ትሁቱ የባህልና ቱሪዝሙ ሠው እንደገና ወደኋላ መቅረቴን ተከትሎ የሚያስፈልገኝ ነገር ካለ እንድደውልለት ነግሮኝ ወደ ጉዳዩ ሄደ። ኤርፖርቱ ላይ የሚያምር ልብስ የለበሱ ካህናት እየዘመሩ፣ ወንድና ሴት ወጣቶች የአካባቢውን ባህላዊ ጭፈራ እያስነኩት ተቀበሉን፡፡ ስነስርዓቱ እንደተጠናቀቀ ለከሰዓቱ መርሀ ግብር ለመድረስ ሁላችንም ወደ ሆቴላችን ሄድን። በተራራና በሸለቆ መካከል በሚሽሎከለክ መንገድ እያዘገምን አሮጌ መንደሮችን እየሰነጠቅን ንብረትነቱ የቤተክርስትያኗ የሆነው ቤተ አብርሀም ሆቴል አልጋ ይዘን እዛው ተመገብን። እያባበሉት ካልሆነ ሲይዙት የሚቆረስ እንጀራ አዲስ አበባ ቀረ። ጥዑም ማዕድ ተቋድሰን ማር ሙዝየም ወደ ከተማዋ አዳራሽ አዘገምን። እንደደረስን አዳራሹ ውስጥ በቄሳውስት ፀሎት ተጀመረ። የላሊበላ የኪነት ቡድን አባላት አስደማሚ ዜማ አሠምተው ጥናታዊ ፅሁፍና ውይይት ተጀመረ። ውይይቱ በማግስቱ በከተማዋ በይፋ ስለሚበሰረው የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክትና ስለ ላሊበላ ምርምርና ጥናት ተቋም ነበር።

አዳራሹ ውስጡ በአልባሳት፣ በጌጣጌጥ፣ በቄጠማና ግድግዳ ላይ በተሰቀሉ ፊኛዎች አጊጧል። ከአዳራሹ ባሻገር በድርብርብ መስኮቶች ግጥግጥ ያለ ተዳፋት ላይ የተጣበቁ ጎጆዎች፣ አደይ አበባና ችምችም ያሉ ዛፎች ወለል ብለው ይታያሉ። እራሱ አዳራሹ ገደል ላይ የተገነባ ነው። ከአዳራሹ ወጥቼ ጥቂት አካባቢውን ቃኘሁ፡፡ ስነምግባር የተላበሱ የከተማዋ የጤና መኮንኖች ለኮሮና ጥንቃቄ ያግዙናል። ከመካከላቸው ስንታየሁ የተባለች ድምጻዊ ሙሉቀን መለሰ “ጠይም አሣ መሳይ” ያላት ዓይነት ሴት የጤና መኮንን ስለ ከተማዋ ይህንን ነገረችኝ።

ከተማዋ ቱሪስትን መሠረት ያደረገ ገቢ ስላላት ኮቪዱ አዳክሟታል፡፡ ሰውም እንደምታየው ጥንቃቄ አያደርግም። ላልይበላ የብዙ ነጮች መነኸሪያ ነበር፡፡ ከተማዋን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጪ ዜጎች ሴት ከሆነች ወንዱን፤ ወንድ ከሆነ ሴቷን አግብቶ ወይ ወደ ዉጭ ተያይዘው ይሄዳሉ። አሊያም እዚሁ ሆቴል ከፍተው አብረው ይኖራሉ። ዛሬ ያ የለም። በሽታው የከተማዋን ብዙ ነገር ጎድቷል፡፡

ቤተ-ጊዮርጊስ

ስለመሸብን ቶሎ ለመድረስ ወደ ቤተ-ክርስትያን አዘገምን። በጎርፍ መከላከያ ጎርፋን እንዳለፍን ቁልቁል ተፈልፍሎ ሽቅብ የሚባርክ ቤተክርስትያን እነሆ በሮሃ።

በችፍርጎች፣ በገጠርጌ እና በሰባት ወይራ መካከል ደምቆ ቁልቁል የሚታየው መስቀል ከከተማዋ በስተምዕራብ ከተራራው ስር ልትሰናበት የምትሻዋ ጀንበር ድምቀት ሠጥታዋለች። ተደፋሁ። ወዲያው እኔም የሙያ አጋሮቼም ወደ ውስጥ ከመዝለቃችን በፊት ዙሪያው ፎቶ በዛበት። ባግባቡ ጌታዬን በፅሞና ሳላነጋግር ፎቶ ላይ ጉብ በማለቴ ራሴን ታዘብኩት። ትንፋሽ የሚያሳጥር ውበት፣ ቃል የሚያሳጣ ጥበብ። ወደ ዉስጥ ዘለቅኩ። ሰማያዊ ዩኒፎርም የለበሱ አገልጋዮች በምንፈልገው ልክ አገልግሎት ሰጡን። ቦታው ሲፈጥረው ሲወርዱበትም መባረክ ሲወጡበትም መመረቅ ነው።

የነበረን ጥቂት ጊዜ በመሆኑ ከ3ት በላይ ቤተ-ክርስትያን አላየሁም። ያየሁትን ይባርክልኝ ብዬና ያለጥርጥር ድጋሚ እንደማየው ለራሴ ቃል ገባሁ። ወደ ተያዘልን ሆቴል በእግሬ ስመለስ እንደተገነዘብኩት ከተማዋ አሁን ማመንጨት ከምትችለው በላይ ገቢ እንድታመነጭ የመፀዳጃ ቤት እና የውሃ እጥረቷን ማስተካከል አለባት። ከእሷ ያነሰ ታሪክና የስነ-ህንጻ ጥበብ ያላቸው ሃገራት በተሟላ ለቱሪስት አመቺ ሁኔታ ምክንያት እጅግ የተሻለ ገቢ አግኝተዋል።

ወደ መኝታዬ ተጓዝኩ። ከመተኛቴ በፊት አብሮኝ በጉዞ ላይ በነበረው ተጓዥ ጋዜጠኛ የተፃፈ “ጎንደርን ፍለጋ” መፅሀፍ ዉስጥ “ያላለቁት ውቅሮች” ን ማንበብ ጀመርኩ። ፅሑፉን በአሰደናቂ የስነፅሁፍ ለዛ የጀመረው ጸሀፊው ከላስታ ውጭ በደቡብ ጎንደር ውቅሮና ፈሳሱ በመባል የሚታወቁ በአፄ ላሊበላ ስለተሰሩ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ይናገርና ስለ አፄው ሌሎች አስደማሚ ስራዎች ምርምር እንደሚያሻቸውም እግረ-መንገዱን አፅንኦት ይሰጥባቸዋል፡፡

ማስክ የተወገዘባት ከተማ

በላሊበላ ማስክ ያደረገ ሰው ከታየ ወይ ሰውዬው የመጣው ከአዲስ አበባ ነው አልያም የከተማዋ የጤና መኮንን ነው፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ ራሱ ሳያደርግ ማስክ የሚሸጥበት ቦታ ካየህ እርሱ ላስታ ይባላል፡፡ ከተማዋ እንኳን ኢትዮጵያዊ ለባዳም የሚተላለፍ ድፍረት አላት። በምሽት ለእግር ጉዞ ስወጣ ማስክ ምን ይረባሀል? ውሸት ነው በሽታው የለም ያለ ፈረንጅ ገጥሞኛል። ይህ ማስክ ያላደረገ ፈረንሣዊ እየተሰነጣጠቁ ነው የተባሉትን አብያተ-ክርስትያናት ሊያድስ መምጣቱን አጫውቶኛል። ያገኘኋቸውን ሰዎች ለምን በላሊበላ ማስክ እንደማይደረግ ስጠይቃቸው ከፀሐይ ግርዶሹ በኋላ እንደተዘናጉና እንዲያደርጉም ሲጠየቁ ሳለ ላሊበላ ምን እንሆናለን?” እንደሚባል ነግረውኛል።

የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት

በማግስቱ ወደ አንድ ተራራ ሄደን አሁን በህይወት ባይኖሩም ዶ/ር ጥላሁን ዘውዱ በተባሉ ተመራማሪ ሐሳብ አመንጭነት አዲስ ፕሮጀክት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርዋ ተበሰረ። ፕሮጀክቱ የተበሰረበት አንድ ሰው ውሃ ለሚያጠጡ ሰዎች እየከፈለ የሚተከለውን ችግኝ እንዲንከባከቡና በስማቸው የተተከለውን ችግኝ ቁጥጥርንም በማህበራዊ ሚድያ እንዲደረግ የሚያደርግ ነው።

ነአኩተ-ለአብ

ስለ ላሊበላ ጥናትና ምርምር ተቋም ከመሄዳችን በፊት ‘አደባባይ ‘ ወደሚባለው ቦታ መስቀል ለመግዛት ሄድኩኝ። በእድሜያቸው እጅግ ወጣቶች በአልባሌ ልብስ ውብ እንግሊዝኛ ሲፈስስ መስማቴ አስገርሞኛል። እርግጥ ቱሪስት የሚበዛበት ከባቢ ፊደል ሳይቆጥሩ በእንግሊዝኛ ማፏጨት ልማድ ነው ተብዬአለሁ:: መስቀሌን ገዝቼ ለጥናትና ምርምር መሠረት ድንጋይ ለማኖር በመኪናችን ወደ ነአኩተ-ለአብ ወረዳ ጥቂት ኪሎ ሜትር ተጉዘን ደረስን። ደጉ ህዝብ መሠረት ድንጋይ በሚቀመጥበት ስፍራ እንደተለመደው ያለ ማስክ የሚሆነዉን ያያል። መርሀ-ግብሩ እንደተለመደው በአካባቢው ባህላዊ ዘፈንና ጭፈራ ደመቀ። መሠረት ድንጋዩም ተጣለ። እኔና ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ጥላው ስር አረፍ ብለን ወግ ጀመርን። ፊቱ ቴቪ ላይ ስለሚሰራም ታዋቂ ነው። ጠላ አዝዞ መጣለት። በጎንደርን ፍለጋ መፅሀፉ ሀሳብ የሰጠበት የላሊበላ ቅርስ ይጠና ምክረ-ሀሳቡ ግብ ስለመታለት ፍሰሀው ይሆን ጠላ መጎንጨቱ? መሠረተ-ድንጋዩስ በጊዜ ተሠርቶ ያልቅ ይሆን? ጊዜ መልሱን ይሰጠናል። አበቃሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top