ታዛ ወግ

የአካባቢ ብክለት ምርምር እና ጥናት ወሳኝነት

ሰውየው ‹‹ይግቡ›› ተብለው፣ በሥርዓት ተጋፍረው፣ መዝጊያም ተከፍቶላቸው ወደ ውስጥ ይዘልቃሉ፡፡ ፊት ለፊት ተቀምጠው የነበሩትም ተቀባይ ‹‹ታዲያስ ሰላም ነው?›› ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡ እርሳቸውም እንደ ነገሩ እንጅ እንደ መንሣት ብለው ነበርና ገድገድ ብለው አንገታቸውን ቀና እንዳደረጉ ‹‹ሰላም ነው አሉኝ!! አዬ ጌታዬ ሰላም ቢኖረኝማ እርስዎ ዘንድ ምን ያመጣኝ ነበር?›› ሲሉ ለጥያቄው እንደገና ጥያቄ መሰል ምላሽ ይወረውሩባቸዋል፡፡

ባለወንበሩም መልሰው ‹‹ጤና ነዎት ወይ ማለቴ ነው›› ሲሉ ዳግመኛ ይጠይቋቸዋል፡፡ እርሳቸውም ጥቂት የመገረም ፈገግታ ያሳዩና ‹‹ምነው ጌታዬ አሁንስ ጥቂት አበዙብኝ፡፡ ሰላምና ጤና ቢኖረኝ ባይሆን እንኳ እርስዎ እኔ ዘንድ ይመጡ ነበር እንጂ እኔ ከእርስዎ ምን ስሻ እንደ ሕፃን በዳዴ እመጣ ነበር›› ብለው መለሱላቸው ይባላል፡፡ ተቀባዩ አካሚ እንግዳው ታካሚ መሆናቸው ነው፡፡

ሐኪሙ በርግጥ በተለምዷዊ ‹‹የዘመኑ ሰላምታ›› ‹‹ሰላም ነው›› አሉ እንጂ ክፉ በማሰብ፣ የሰውን ሕመም ባለመገንዘብ ነው›› ለማለት አያስደፍርም፡፡የታካሚው ምላሽም በዚያው ልክ ‹‹ረብ የለሽ ነው›› ለማለት አያስችልም፡፡

አንድ ሌላ ታካሚ ደግሞ ‹‹የአካባቢው ሁኔታ እንዴት ነው›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹አዬ ዶክተር እርሱን እንኳ ከቀበሌው ሰዎች ይበልጥ ለመረዳት ይቻላል›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ የሕክምና ባለሙያ ሲባል ብዙውን ጊዜ የአንድን በሽታ ሥርወ መሠረት ለማወቅ፣ በምርምር ለመጥለቅ የአካባቢን ሁኔታ ይጠይቃል፡፡ ማኅበራዊ አኗኗርን፣ ቤተሰባዊ አወቃቀርን ለማወቅ ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ዓቢይ ነገር ነው፡፡ ይሁንና ጥያቄው በምን ምክንያት እንደተሰነዘረ፣ ለምን የዙሪያ ገቡ ሁኔታ ከሌላው ተለይቶ እንደተሰነጠረ ባለማወቅ ይህን መሰል ደረቅ ምላሽ የሚሰጥበት ወቅት አልጠፋም፡፡ ነገር ግን ጠያቂው የጥያቄውን አስፈላጊነት በቅድሚያ ቢያስገነዝቡ ኖሮ ምናልባት የተሻለ አመላለስ ሊገኝ ይችል እንደነበረ መገመት ዳገት አይሆንም፡፡

እንግዲህ እኔም ወደ አንድ ጥያቄ ላምራና ‹‹ከተሜነት በጤና አጠባበቅ ረገድ ጉዳት አለውን?›› በማለት ልሰንዝር፡፡ ይህ ጥያቄ በቁጥር ያላነሱ ሰዎች አሁን ባለንበት ዘመን በተደጋጋሚ የሚያነሡት፣ ምላሽም የሚሹለት ነጥብ ነው፡፡ አንድ በጉዳዩ መጠነኛ ፍተሻ ለማካሄድ የበቁ ባሕር ማዶኛ በሰል እንዳስቀመጡት የሕዝብ ወደ ከተማ እየፈለሰ፣ ከገጠር እንደ ጎርፍ ውሃ እየፈሰሰ መታየት ሲታሰብ ‹‹ያልተጠበቀ ግርግር›› ከማለት አያንስም፡፡

በሙያው የተካኑ፣ ጉዳዩን በቅጡ ያጤኑ ማእምራን እንደሚሉት ‹‹ከተሜነት›› ሲባል ምክንያቱ በአኃዝ የማይዘረዘር የሚያስከትለው መዘዝ ‹‹ይህ ነው›› ተብሎ የማይነገር ብቻም ሳይሆን ‹‹ገና የማይታወቅ››ም ነው፡፡ በተመራማሪዎች አገማገም ውጤቱን፣ ጠንቁን፣ መዘዙን ለይቶ ለማስቀመጥ አሉታዊ ገጽታውን ከአዎንታዊው አነጻጽሮ ለመግለጥ መንሥኤውን ከነመፍትሔው ለመስጠት ሰፊ ምርምር መካሄድ የሚያሻው ሳይሆን አልቀረም፡፡ የእስካሁኑ ፍተሻ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀጣይነቱ ግን አጠያያቂ ሊሆን እንደማይገባ ምሁራን ያስገነዝባሉ፡፡ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ያስፈልጋልና!!

‹‹ገና ሰፊ ምርምር ያሻዋል›› በማለት ብቻ ለሌላ ጥለውና ነገሩን አንጠልጥለው በዝምታ ያልተገለሉ፣ ያላቸውን ከመቸር ወደ ኋላ ሊሉ ያልቻሉ ምስጉን ተመራማሪዎችም አልጠፉም፡፡ በአንድ የጥቂት ዓመታት እድሜ ባለጸጋ ሊሆን በበቃ ወቅት አደባባይ በዋለ ሰነድ እንደሠፈረው ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱት የግብርናው ዘርፍ አተገባበር እንደ ጥንቱ ሳይሆን ሥልጣኔ ባዘመነው የአሠራር ብልኃት በመተካቱ በገጠር የሥራ ቦታ በመታጣቱ፣ በከተማ ማዕከላት አካባቢ የሥራ ቦታ የሚፈጥር ኢንዱስትሪያዊነት በመስፋፋቱ እና በመሰል ጉዳዮች ሳቢያ ሰው ራሱን ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት ምክንያት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ይህ መንግሥት ብርቱ ጥረት በማድረጉ በርካታ ሕንፃዎች መገንባታቸው እንዳለ ሆኖ እንዲያው በስመ ‹‹ከተማ›› የተኮለኮሉ፣ ያለዕቅድና ያለጥናት እዚህም እዚያም እንደ አሸን የፈሉ፣ የተጎሰቋቆሉ መንደሮች በመልማት ላይ ባለችው ሀገራችን ይታያሉ፡፡ እነዚህ ‹‹ከተሞች›› በትክክል ሲስተዋሉ ተገቢ ሆነው ‹‹ለሚዛናዊ እድገት›› አስፈላጊ ነው የሚባለው የመሠረተ ልማት አውታር እጅግ እንደሚጎድላቸውና ይህም ‹‹አሳሳቢ›› ከሚለው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሙያው ተጠባቢዎች ያስረዳሉ፡፡ በአንፃራዊ መልክ ‹‹በኢንዱስትሪ በገፉ፣በለሙ…..›› ተብለው በሚጠሩ ሌሎች ሀገሮች ያለው ሁኔታ ሲገመገም እርሱም የራሱን ጥያቄ ይዞ ይነሣል፡፡ ያ ጥያቄም የከተሞች የሕዝብ የመጨናነቅ ነገሩ አንዱ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ያረጀ የመሠረተ ልማት አውታርም እንቅፋት መሆኑ ይታመንበታል፡፡

ምንም እንኳ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢያ አንዱ ከሌላው የተለየ መሆኑ ባይካድም የጠበብት ሰነዶች እንደሚያስገነዝቡት የከተሜነት ነገር በጤናው ላይ ያለው ከባድ ተጽዕኖ የማይናቅ ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ በገፉ፣ በለሙ አገሮች ያለው መጠን ዘለል ውፋሬ ሲመረመር እጅግ ተጠቂ ሆነው የተገኙት፣ ‹‹በሞራ መጋዘንነት›› የሚጨነቁት ባለጸጎች ያለመሆናቸው ‹‹ግሩም›› ሊሰኝ በቀቷል፡፡ ‹‹ለምን?›› ተብሎ ቢጠየቅ በባለኢንዱስትሪው አህጉር በግዙፋን ከተሞች ያሉ የመባልዕት መሸጫ ቤቶች በአመዣኙ የሚያቀርቡት ‹‹ፈጥኖ ደረስ›› የሚባሉትንና ‹‹የታሸገ›› የሚሰኙትን የምግብ ዓይነቶች ነው፡፡ እነዚህ በአመዛኙ የስብ ክብተት ያላቸው ከሌሎችም የምግብ ዓይነቶች በዋጋቸው ስለሚያንሱ ብዙኋኑ ወደ እነርሱ ማድላቱ ግድ ስለሚሆንበት ነው፡፡ ኪሱ የሳሳ፣ ኮሮጆው የከሳ ምስኪን ርካሹን ፈልጎ ሆዱን ይሞላል፡፡

በማኅበራዊ ሕይወት ረገድስ ምን መልክ አለው? ይህም ዓቢይ ጥያቄ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወት መስተጋብር ያለውን ሁኔታ ብንመለከትም የከተማ ሰውነት ከ ‹‹ብቸኝነት›› ጋር በቅርቡ የተዛመደ›› ሊሆን መብቃቱ ሳይሰመርበት አይታለፍም፡፡ እንዲህም ሲሆን በአንድ ተጠባቢ አገላለጽ ‹‹አእምሯዊ ጤንነት ጎልባታ ሊባል አልበቃም፡፡›› በሰሎች እንዳመለከቱት ‹‹በጭንቀት፣ በመከፋት እና በድብርት….. ሳቢያ በገዛ እጃቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የደረሱ ወጣቶች ተገኝተዋል፡፡›› ‹‹እጅግ አሳዛኝ›› ሊባል በሚበቃ መልኩ በሰሜን አሜሪካ ያሉ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሄደው አእምሯዊ ቀውስ ሳይዘፈቁ እንዳልቀሩም ጥናታዊ ሰነዶች ያስገነዝባሉ፡፡

በኢንዱስትሪ ባልገፋው ወይም እንደ አባባሉ ‹‹በመልማት ላይ ባለው አህጉር›› ያለውን ኅብረተሰብ ብናይ ይበልጡን ሲጨነቅ የሚታየው የተመቻቸ የመፀዳጃ ሥፍራ ባለመኖሩ ንፁሕ የመጠጥ ውሃ እንደ ልብ ባለመገኘቱና በመሳሰለው የተውሳክ መተላለፍ መንሥኤ ሳቢያ በሚከሰተው አደጋ ምክንያት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሀይቲ በተባለችው ደሴት ላይ በሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የኮሌራ በሽታ ሰለባ የሆነበትን አሳዛኝ ክስተት ጠበብት ለአብነት ይጠቅሱታል፡፡

የትላልቅ ከተሞች በሕዝብ መጨናነቅ በተለይም በዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል ያለ ልክ መጠቅጠቅ የሚመጣው ሌላም መዘዝ እንዳልጠፋ ሳይጠቆም አልቀረም፡፡ ዛሬ ደግሞ ኮቪድ 19 ስላለ እሱም የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ የአደንዛዥ እጽዋት አዘዋዋሪነት፣ ዝሙት አደርነት፣ ቀምቶ በልነት፣ ሰብሮ ገብነት፣ ጎዳና ገደምነት እንደሚስፋፋ፣ እንዲያ ሲልም አባላዘር በሽታ እንደሚንሰራፋ የማኅበራዊ ኑሮ ፈታሾች ያሰምሩበታል፡፡

ሌላው ደግሞ የአካባቢ ብክለት ነገር ነው፡፡ የአካባቢ ብክለትም እንዲሁ እንደዋዛ የሚታይ እንዳልሆነ ሳይጠቀስ አልታለፈም፡፡ በምሳሌነት የተጠቀሰችው ቻይና በዚህች በሠፈርንበት ምድር በሕዝብ ብዛት ‹‹በቁጥር 1›› የምትዘከር ሀገር ናት፡፡ ቻይና በሕዝብ ብዛትም ብቻ ሳይሆን በዛሬ ዘመን በኢንዱስትሪያዊ ልማት ረገድ ‹‹ኃያላን›› በተባሉት ተርታ ልትሰለፍ ያልበቃችበት ሁኔታ የለም፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በከተሜነት መዘዝ አካባቢ ብክለት ክፉኛ ሊፈታተናት ዳር ዳር ማለቱ ስወር እንዳልሆነ በዜና ማሠራጫዎች ይነገራል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ ቻይናም ሆነች ሌላው አህጉር በከተሜነት ሳቢያ የሚደርሰውን የአካባቢ ብክለት በቸልታ እንደማይመለከቱት ሞገድ አሳበሮ የሚሠራጨው ዜና መርዶውን ይዞ ብቅ ከማለት የታቀበ አይመስልም፡፡ ስለምን? የአካባቢ ብክለት ጠንቅ ‹‹ቀልድ›› ተብሎ የተረበኞቸ ጨዋታ ሆኖ እንደ ጊዜ መግደያ የሚቧለትበት አይደለምና!

በአካባቢ ብክለት ሳቢያ የከተማ ነዋሪዎች ይበልጡን ለሳምባ ካንሰር ደዌ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደቻሉ የጤና ባለሙያዎች ከመወትወት አልቦዘኑም፡፡ ሌላው ደግሞ በሀገረ ፈረንሣይ የተካሄደ አንድ የተመራማሪዎች ስብስብ የብሌን እማኝነት ይቸረው ዘንድ ያቀረበው ሰነድ ብዙዎችን እንደ ደራሽ ውሃ ሳያስበረግግ አልቀረም፡፡ ይኸውም የአካባቢ ብክለት መንሥኤ ሆኖ በዋነኝነት የወንዶች አኃዝ መጥቆ በተገኘበት ሥፍራ በተካሄደ ፍተሻ የወንድ የዘር ፍሬ መዳከምና እጅግ ማነስ ነው፡፡ በርግጥ የትኛው ዓይነት የአካባቢ በካይ ነገር ይህን እንዳመጣ ለይቶ ለመንገር የተቻለ አልሆነም፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በዋዛ ፈዛዛነት የሚታለፍ አለመሆኑ በሚገባ ተሰምሮበታል፡፡

የአካባቢ ብክለት በወሊድስ ላይ ያለው ችግር ምን ይመስላል? ይህም አንድ ራሱን የቻለ ነጥብ መሆኑን በሙያው የተሠማሩ ጠበብት ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ አትላንቲክን ተሸግረን በአህጉረ አሜሪካ ያለውን ሁኔታ ለመቃኘት ብንሞክር በሁለት ግዙፋን የካሊፎርኒያ ክፍላተ ግዛት ከተሞች የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው የካርቦን ሞኖክሳይድ እና የናይትሮጂን ኦክሳይድ ርቀት ባሉባቸውና ከፍተኛ የባለሞተር ተሸከርካሪዎች ዝውውር በታዩባቸው ሥፍራዎች የከተሙ ነፍሰ ጡሮች ይበልጡን በነርቭ ደዌ የታወኩ ሕፃናትን የመውለድ አደጋ እንደተረጋረጠባቸው ጥናታዊው ሰነድ ሳያስረዳ አልቀረም፡፡ ‹‹በርግጥ አኃዙ ይበልጥ በትክክል እናብላላው ዘንድ ግን ግድ ይለናል›› ሲል አንድ ሐታቴ ነገር ያሠፈረው ለጥቅስ የሚበቃ ነው፡፡

የእኛስ ከተሜነት ከየት ወዴት ይሆን? ምን ይመስላል? በእዚህች ኢትዮጵያችን ብዙ ጊዜ ስለ ‹‹ከተማ፣ ከተሜነት …..›› ሲነገር እንሰማለን፡፡ ሀገራችን የተያያዘችው ፍኖተ ልማት ‹‹ይበል፣ ይበጅ›› ያሰኛል፡፡ ይህም በብዙዎች ተአሚኒነት ባላቸው ጠበብት ምስክርነት የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ የአንድ ሀገር ልማት ሲታይም ከኢንዱስትሪያዊነት አንፃር ጭምር መመዘን እንደሚገባው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሆኖም ከተሜነት በማኅበረሰባዊ አኗኗር፣ በቤተሰባዊ አስተዳደር፣ በባህላዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ውጥንቅር፣ በጤናና በመሳሰለው ስለመጣው ወይም ሊያመጣ ስለሚችለው ጥቅም ሆነ ጉዳይ፣ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት በምልዓት፣ በስፋትና በጥልቀት አደባባይ የዋለ ሰነድ ከየአቅጣጫው በየጊዜው፣ በየወቅቱ እየተፈተሸ ቀርቦ ይሆን? የአካባቢ ብክለት ምርምር እና ጥናት ወሳኝነት አለውና! ጥያቄውን ግን ለአንባቢ በመተው መሰናበቱን እመርጣለሁ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top