ታሪክ እና ባሕል

የአባይ ሸለቆን የመቆጣጠር ህልም

ራስጌዋ ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ራስጌ ነች፤ የናይል ራስጌ፡፡ የአባይ ምንጭ፡፡ የአባይ ተፋሰስ ዋነኛ የውሀ ማማ፡፡ በግርጌዋ የሚያዋሰናትን ምስራቃዊ የሰሀራ በረሀ የምታጠጣ የህይወት ምንጭ፣ የህልውና አክሊል ናት፡፡ ከሥርዓተ-ወንዞቿ መካከል ሦስቱ የናይል ወንዝ ዋነኛ የውሀ ምንጮች ናቸው፡፡ ካለነሱ ናይል የሚባል ወንዝ ደረቅ ጅረት በሆነ ነበር፡፡ አሁን ካለው ውሀ ከመቶ አስራ አራቱን ብቻ የሚይዝ ባዶ ፈፋ በነበር፡፡ ካለእነሱ ግብጽ የምትባል አገር ጭራሽ ባልኖረች ነበር፡፡

አባይ ለናይል ወንዝ 50 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፣ ባሮ-አኮቦ 12 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፣ ተከዜ 10 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ያበረክታሉ፡፡ በብዙ ጥናቶች እንደተረጋገጠው የናይል ወንዝ ዓመታዊ ፍሰት 85 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ከዚህ ወስጥ 72 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ኢትዮጵያ የምታበረክተው ነው፡፡ ስለዚህም ነው ኢትዮጽያ የናይል ወንዝ የደም ሥር፤ የተፋሰሱ ፍጡራንና የቀጠናው ስነምህዳራዊ ሚዛን ዋስትና ናት የሚባለው፡፡

የአባይ ውለታና ፈተና

የዚህን ቁልፍ ተፈጥሯዊ ጸጋ ጥልቅ ፋይዳ ቀድሞ የተገነዘበው ግሪካዊው ታሪክ ዘጋቢ ሄሮዶተስ ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ አራተኛው ምዕተዓመት ላይ ‹‹ግብጽ የአባይ ስጦታ›› ብሎ ባቆየው ዝነኛ አባባሉ የአባይን ውለታ ጥንት የተናገረው ቢሆንም የአባይን ውለታ ከግብጾች የበለጠ ማንም አያውቀውም፡፡ ምክንያቱም ግብጾች አባይን የሚያውቁት ከታሪክ ሳይሆን ጉሮሯቸውን አቋርጣ በምታልፈው በእያንዳንዷ ጠብታ ውሀና በእያንዳንዷ ቁራሽ ዳቦ ነው፡፡ ያገሬ ገበሬ ስለበሬ ውለታ ያለውን እዚህ ላይ ማንሳት ውለታ ነጋሪ የራሱ አውድ እንዳለው የሚያመለክት ነው፡፡

የበሬን ውለታ
ይጫወቷል ማታ
በሰፊ ገበታ
በዋንጫ ቱማታ፡፡

ብዙ ግብጻውያን ግን የአባይን ውለታ ከኢትዮጵያ ጋር ማገናኘት አይሹም፡፡ አባይ ካንድ ምስጢራዊ ከፍታ ቁልቁል እየወረደ በረከት እንደሚሆናቸው ግን በየተረቶቻቸው ለልጆቻቸው ያስተምራሉ፡፡ ለእነሱ አባይ በሚፈልቅበት ሰማየ ሰማያት ከፍታና በግብጽ መካከል አንድ ጉም አለ፡፡ ሁሉንም ምስጢርና ተረት አድርጎ የሚጠብቅ፡፡

ግብጻውያን ያባይ ወንዝ ለናይል የሚያበረክተው የውሀ ድርሻም ትኩረት እንዲሰጠው አይፈልጉም፡፡ ይልቁንም ያባይ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን መቆጣጠር ህልማቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡ ላሟ የሌላ ሆና ወተቷን ብቻ መጠበቅ ዋስትና የለውም ብለው ሲያስቡ ቆይተዋል፡፡ ላሟን መቆጣጠር የሁሌም ምኞታቸው ሆኖ ቀረ፡፡ የዘመናት የኃይል ፍላጎታቸው እውን ሊሆን ባይችልም ለዘመናት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ መረጋጋት ሲፈታተኑ ኖረዋል፡፡

ሀይማኖትና የአጼ ዮሐንስ ፈተና

አጼ ቴዎድሮስ ከተሰዉ በኋላ የመጡት አጼ ዮሐንስ ተቀብተው ሳይነግሱ ብዙ ቆይተዋል፡፡ ምክንያቱ በአጼ ቴዎድሮስ ወህኒ ቤት በእስር ላይ በሞቱት ግብጻዊ ጳጳስ (አባ ሰላማ) ምትክ ግብጽ ሌላ ጳጳስ ለመላክ ፈቃደኛ ሳትሆን መቅረቷ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ነገስታት የአባይን ውሀ በማቀብ ግብጽን በውሀ እንደሚቀጡ ያስፈራሩ ስለነበር የፈርዖን ልጆችም ኢትዮጵያውያን ነገስታትን በጳጳስ መቅጣታቸው ነበር፡፡ አጼ ዮሐንስ በብዙ ደጅጥናትና ገጸበረከት ግብጻውያን ገዢዎችን አባብለው ከታረቁ በኋላ አትናቲዎስ የሚባሉ ጳጳስ ተላኩላቸው፡፡ በጳጳሱ ተቀብተው በ1880 ንጉሠ ነገሥት ሆኑ፡፡

በሀይማኖት አጥባቂነታቸው፣ በለስላሳ የውስጥ ፖለቲካ ርዕዮታቸው፣ ዕርቅን፣ ሰላምንና ይቅር ባይነትን በመምረጣቸው የሚታወቁት አጼ ዮሐንስ በግብጻውያን በብዙ ተፈትነዋል፡፡ ፈተናዎቻቸው በብዙ መልኩ ከመንፈሳዊነታቸው ጋር የተያያዙም ነበሩ፡፡ በጳጳስ ሳይቀቡ ላለመንገስ ወስነው መቆየታቸውም በትዕግስትና በጽናት ያለፉት የመጀመሪያው ፈተና ነበር፡፡

አጼው ለውጭ አገር መሪዎች ይጽፏቸው የነበሩ ደብዳቤዎች የበረታ ሃይማኖታዊነታቸውን ያሳዩ ነበር፡፡ በዘመናቸው ቤተክርስትያናትን በማሳነጽ ብዙ ሰርተዋል፡፡ በወር አርባ አራት በዓላት እንዲከበሩ በማድረግ የሳቸው አስተዋጽኦ ጉልህ ነበር፡፡ መንፈሳዊው ምግባር ለስራና ለአገር ልማት ሊሰጥ የሚገባውን ትኩረት ጎድቶታል፡፡ ኢትዮጵያ በዚያ ዘመን በልማት መራመድ የሚገባትን ያህል መራመድ ያልቻለችበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነበር፡፡ ከሀይማኖት ጋር የተያያዘው የግብጾች ስውር ፖሊሲ ውጤትም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሰሩ ያድጋሉ፡፡ ካደጉ ይፎካከሩናል የሚል ሥጋት ግብጾች ነበራቸው፡፡ በረቀቀ ዘዴ ‹ስንፍናን› አስፋፍተዋል፡፡

አጼ ዮሐንስና የጦርነት ዋዜማ

አጼ ዮሐንስ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኢትዮጵያ ዳግመኛ ወደ ዘመነ መሳፍንት አዙሪት እያመራች ነበር፡፡ በመሆኑም የአጼው የውስጥ ፖሊሲ ማዕከላዊ መንግሥት ለመፍጠር ፀረ-መሣፍንት ትግል መቀጠል ሲሆን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውም ተመሳሳይ ሀይማኖትን ከሚከተሉ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ጋር ግንኙነትን በመፍጠር ለውስጥ ፖሊሲያቸው ማስፈጸሚያ ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ ማግኘት ነበር፡፡ ወዳጅ እንደሚሆኗቸው ወዳሰቧቸው አገሮች ደብዳቤና ገጸ በረከት እያስያዙ መልዕክተኛ በመላክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የማጠናከር ተግባር አከናውነዋል፡፡

ግብጽ የኢትዮጵያን የውስጥ የፖለቲካ ክፍፍል ለራስዋ ፖለቲካ ዓላማ በመጠቀም የአጼ ዮሐንስ ተቀናቃኝ የነበሩ የውስጥ የፖለቲካ ኃይሎችን በትጥቅ፣ በሀሣብ፣ በሞራልና በቁሳቁስ በመደገፍ አገሪቱ በፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ በርትታ ትሰራ ነበር፡፡ ለዚህም ስለ ኢትዮጵያ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሙዚንገር የሚባል ሰው ቀጠረች፡፡

ሙዚንገር ምጽዋና ከረን ውስጥ ነጋዴ ሆኖ ለረጅም ዓመታት ኖሯል፡፡ ከአካባቢውም የአንድ ጎሣ ባላባትን ልጅ አግብቷል፡፡ ለንግድ ወደ ሐረር እየተመላለሰ አካባቢውን በሚገባ አጥንቷል፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ቋንቋም ተምሯል፡፡ በኢትየጵያ የነበሩ ወደ አርባ የሚሆኑ አውሮፓውያንን አጼ ቴዎድሮስ አስረው በነበሩ ጊዜ በዲኘሎማሲያዊ ድርድር ለማስፈታት ለመጣው የእንግሊዝ መልእክተኛ ቡድን መንገድ በመምራት፣ ስንቅ በማቅረብና የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር እንግሊዞችን በማገዙ በእንግሊዞች ታማኝነትን ተጎናጽፏል፡፡

በጄኔራል ናፒር ወረራ ጊዜም ከወራሪው ኃይል ጋር አብሮ ዘምቷል፡፡ የናፒር ጦር ከኢትዮጵያ ሲወጣ ይህ “የሰይጣን ፈረስ፤ የሰይጣን ቁራጭ” (አጼ ዮሐንስ የሰጡት ስም) ኢትዮጵያ ውስጥ ቀረ፡፡ አጼ ዮሐንስን ገና ደጃዝማች ከነበሩ ጊዜ ጀምሮ ተዋውቋቸው ወዳጅ አድርጓቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ከብዙ የውጭ መንግሥታት ጋር በማስተዋወቅ እንደሚረዳቸው በመገመት ዓላማቸውን አስከደገፈ ድረስ ከሰይጣንም ለመዋዋል ወስነው አቅርበውት ቆዩ፡፡ ሙዚንገር የማያውቀው የአውሮፓ ባለሥልጣን፤ የማይወዳጀው መሪ እንደለሌ በቅቤ አንደበቱ በእሳት ምላሱ እያቀለጣቸው የአጼው ፍጹም ታማኝ መሰሎ ገባ፡፡ አጼ ዮሐንስ ከነገሱ በኋላ በራስ ማዕረግ የቦጐስ፣ የሐባብና የመንሳ ገዥ አድርገው እንዲሾሙት ለምኗቸው ነበር፤ ግን አልተሣካለትም፡፡ እዚህ ላይ አጼው ብልጥ ሆኑ፡፡

የፈረንሣይ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ቅኝ ግዛት የመፍጠር ፖሊሲዋን ለመተግበር አካባቢውን ጠንቅቆ የሚያዉቅ ሰው እየፈለገች የነበረበት ወቅት ስለነበር ፖለቲካን የማባዘትና የመፍተል ችሎታው ከፍተኛ የሆነዉን ሙዚንገር ራሱን በራሱ እጩ አድርጎ አቀረበ፡፡ የፈረንሣይ መንግሥትም በደስታ ተቀበለው፡፡ ከዚያም ሙዚንገር በኢትዮጵያ የፈረንሣይ ካቶሊክ ሚስዮናዊያን አስተባባሪ ሆኖ ተሾመ፡፡ ሚስዮናዊያን የወንጌል ሰበካን ችላ እንዲሉና የፈረንሣይ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጐቱን የሚያራምድበትን የፖለቲካ ስትራቴጅና ስልት እንዲያሰላስሉ ያበረታታቸው ጀመር፡፡

ከዚህ በኋላ ሙዚንገር የፈረንሣይ መንግሥት አጼ ዮሐንስ አንድ አገርና አንድ ሀይማኖት ፖሊሲ የሚከተሉ በመሆናቸው ካቶሊክ ሚስዮዊያንን እየጨቆኑ ስለሆነ ሚስዮናዊያንን የሚጠብቅ ወታደር በአስቸኳይ እንዲላክ ጠየቀ፡፡ የፈረንሣይ መንግሥት ለጥያቄው የይሁንታ መልስ ሳይሰጥ ቀረ፡፡ በዚህ የተበሳጨው ሙዚንገር ከአጼ ዮሐንስም ከፈረንሣይ መንግሥትም በመራቅ ለኬዲቭ እስማኤል ታማኝ ሎሌ ሆነ፡፡ ግብጾች ኢትዮጵያን በጦር ኃይል እንዲይዙ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ መስራት ጀመረ፡፡ ሌትና ቀን ተጋ፡፡ ግብጾች ምጽዋን እንዲይዙ እቅዱን ዝግጅቱንና ስምሪቱን መራ፡፡ ለውለታው ኬዲቩ የቤይ ማዕረግ ሰጥቶት የምጽዋና የአካባቢው አገር ገዥ አድርጐ ሾመው፡፡ ከዚያም የአካባቢው ባህላዊ መሪዎችና ሹሞች በገንዘብና በንግግር ችሎታው እያማለለ አጼ ዮሐንስን እንዲክዱና ለግብጽ እንዲገብሩ አድርጓል፡፡

የውስጥ መከፋፈልና የውጭ ጠላት

ግብጾች በ1860ዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ እግሮቻቸውን ተክለው አገር የመከፈፋፈልና ለጥቅሞቻቸው የሚገዙላቸውን ሁሉ በማማለል ተግባር እየተጉ ነበር፡፡ ሙዚንገር ከወሎ ባላባቶችና ከሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጋር ገጸ በረከትና ደብዳቤ በመላክ ከመወዳጀት ደርሷል፡፡ ተክለጻድቅ መኩሪያ እንደጻፈው ግብጻውያኑ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ሁኔታ የተፈጠሩ ቅራኔዎችንና ልዩነቶችን በመጠቀም የአጼ ዮሐንስን መስተዳድር ከሥሩ በመገዝገዝ ለረጅም ዘመናት ሲያልሙ የቆዩትን የአባይን ምንጭ የመቆጣጠር ህልማቸውን እውን ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በሌላም በኩል አጼ ዮሐንስን ለማዘናጋት የወዳጅነት ደብዳቤ ይጽፉ ነበር፡፡

በጊዜው የአጼ ዮሐንስ ተቀናቀኝ የዘውድ ፖለቲካ ተፎካካሪ የነበሩት የሸዋው ንጉስ ምኒልክና የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት ሴራ የንጉሰ ነገስቱ ፈተና ነበር፡፡ ምኒልክ በሸዋ ንጉሠ ነገሥት ነኝ ይሉ ነበር፡፡ አጼ ዮሐንስም በዓድዋ ንጉሠ ነገሥት ሆነው ተቀብተዋል፡፡ አጼ ተክለሃይማኖትም በጎጃም፡፡ ምኒልክና ተክለሃይማኖት በደግ የማይተያዩ ቢሆኑም ባህሩ ዘውዴ እንደጻፈው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ” በሚል እሳቤ በ1880 ይቅር ለግዜር ተባብለው በንጉሠ ነገሥቱ ላይ የአመጽ ግንባር ፈጠሩ፡፡ ወቅቱ ኢትዮጵያ ሶስት አጼዎች የነበሩባትና አንዱ የሌላውን አጼነት የማይቀበልበት ጊዜ ነበር፡፡ በመሆኑም አጼ ምኒልክና አጼ ተክለሃይማኖት አጼ ዮሐንስን በጋራ ለመመከት ተዋዋሉ፡፡

ግብጾች ይህን የውስጥ ክፍፍል ለራሳቸው ዓላማ ለመጠቀም ሲሉ ከምኒልክ የወገኑ መስለው ቀረቡ፡፡ የግብጹ ኬዲቭ ምኒሊክን እንደሚደግፍና ንጉሱ የሚጠይቁትን ሁሉ ለመፈጸም ደስተኛ እንደሆነ የግብጾች መልዕክተኛ ሲነግራቸው ተደሰቱ፡፡ ከመልዕክተኛው ጋር ብዙ ተጨዋውተው የመጣላቸውን ገጸ በረከት አመስግነው ተቀበሉ፡፡ በኢትዮጵያ ልማትና ሥነ-ጥበብ ለማስፋፋት ምኞት እንዳላቸው የሚገልጽና ምክር የሚጠይቅ ደብዳቤ ከገጸ በረከት ጋር ለኬዲቭ እስማኤል ላኩ፡፡ ወዲያውኑ ኬዲቭ እስማኤል መልስ ሰጠ፡፡ ነገር ግን የመልስ ደብዳቤው በስህተት ከምጽዋ ለአጼ ዮሐንስ ደረሰ፡፡

አጼ ዮሐንስም በግብጾች የተያዘባቸውን የቦጐስ፣ ጊንዳና መንሳ ግዛቶች ጉዳይ ምንም ሳያነሱ ከግብጾች ጋር እንደሚስማሙ መልስ ሰጡ፡፡ ይህም በግብጾች ዘንድ የፖለቲካ ብዥታ ፈጠረ፡፡ ሆኖም ይህ ግንኙነት ግብጽ አጼ ዮሐንስን ለመውጋት ያላትን ፖሊሲ አላስቀየረም፡፡

በ1883 አጼ ምኒሊክ ለኬዲቭ እስማኤል በላኩት ደብዳቤ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል የተጀመረው በጐ ግንኙነት ዘላቂ እንዲሆን ያላቸውን ምኞት የሚገልጽ ሆኖ በመልእክተኛቸው በራስ ብሩ አማካኝነት በሁለቱ አገሮች መካከል የወዳጅነትና የንግድ ውል እንዲፈረም ጠየቁ፡፡ እንደገና ቦጐስ በሚባል አርመናዊ የኬዲቭ ባለሟል አማካይነት ሌላ ተጨማሪ ደብዳቤ ልከው አንድ ጳጳስ ለሸዋ እንዲላክላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ባህሩ እንደጻፈው ኬዲቭ እስማኤል በምላሹ የአጼ ምኒልክን ፍላጐት እንደሚያሟላና ጳጳስም እንደሚልክ ገልጾ ለግዛታቸው ደህንነት ማስጠበቂያ የሚሆን 5ዐዐ ጠመንጃ፣ አንድ መድፍና ባዙቃ መላኩን ገልጾላቸዋል፡፡

በግብጽና በሸዋው ምኒልክ መካከል በተፈጠረው መቀራረብና መወዳጀት ምክንያት የግብጹ ኬዲቭ እስማኤል አጼ ምኒልክ ከሱ ጋር በመወገን አጼ ዮሐንስን እንዲወጉ ፍላጎት ስለነበረው ነው፡፡ የግብጽ መንግሥት ኢትዮጵያን በቅኝ ለመያዝ ምንም ዓይነት ፍላጐት እንደሌለው በመግለጽ፤ ነገር ግን አጼ ዮሐንስን አስወግዶ ምኒልክን ለማንገስ እንደሚፈልግ ደብዳቤና ገጸ በረከት እየላከ ያግባባ ነበር፡፡ አጼ ምኒልክ ምንም እንኳ የአጼ ዮሐንስን ንግስና ለራሳቸው የማድረግ ምኞት ቢኖራቸውም የግብጽ ገዢዎች ብዙ ሀብት አፍስሰው፣ ጉልበት ጨርሰውና የዜጎቻቸውን ህይወት ከፍለው ኢትዮጵያን ከአጼ ዮሐንስ አሳልፈው ለእሳቸው እንደሚሰጧቸው ቃል ሲገቡ በልባቸው ያለው ሀሳብ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሆነ ምኒሊክ በሚገባ የሚያውቁ ቆቅ ነበሩ፡፡

የግብጾች ፍላጎት መንታ ነበር፡፡ ይህም ከዮሐንስ መወገድ በኋላ ቅኝ ኢትዮጵያን ወይም በግብጽ ሞግዚትነት የሚትገዛ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነበር፡፡ ራሳቸውም በቱርክ ሞግዚትነት ስር በነበሩበት ዓይነት፡፡ ምኒልክ ይህ እንዲሆን ስላልፈለጉ ለእስማኤል ፓሻ የግብጻውያኑ ወዳጅነታቸዉ እንደማይጠቅማቸውና እንዲያውም የእነሱ ወረራ እንደሚያሳስባቸው የሚገልጽ ደብዳቤ ላኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ከግብጽ ጋር ያለው ግኑኝነትም ይበልጥ በሥጋትና ጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ሆነ፡፡

ግብጾች ጸረ አጼ ዮሐንስ አቋም የነበራቸውን እንደነ ልጅ ውቤ፣ ደጃዝማች ወልደሚካኤል፣ ራስ አርአያና ሌሎቹንም በማስታጠቅ፣ ገንዘብ በመርጨትና ከጂዎችን በባንዳነት በማሰማራት ጸረ አጼ ዮሐንስ ግንባር በማጠናከር ለንጉሰ ነገስቱ የጎን ውጋት ሆኑ፡፡ የአጼ ዮሐንስ መንግሥት ከውስጥም ከውጭም እጅና ጓንት ሆነው በተነሱት ጠላቶች ተወጠረ፡፡ ከሀዲውና የውስጥ ቦርቧሪው ሁሉ የጦር መሣሪያ ለማግኘት ሲል የአገርን ሚስጥር የሚሸጥ ሆነ፡፡ ከዚህ አጠቃላይ የውስጥ ፖለቲካ ሁኔታ የተነሣ ግብጾች የአጼ ዮሐንስ መንግሥት እጅግ የተዳከመና በቀላል የሚወድቅ አድርገው በመገመት በእጃዙር ከመውጋት በቀጥታ መውረርን መረጡ፡፡

ለጦርነት የማይቸኩሉት አጼ ዮሐንስ

የግብጽ ወራሪዎችን በጦር ሜዳ ገጥመው ድል በድል ላይ የተጎናጸፉትና ግብጾች ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የነበራቸውን ህልም ያመከኑት አጼ ዮሐንስ ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት ከውጭም ከውስጥም ጠላቶቻቸው ጋር ሰላም ለማውረድ ያደረጉት አስተውሎት የተሞላበት አያያዝ የሚደነቅ ነው፡፡ እንደእሳቸው ፍላጎት ቢሆን ኖሮ አንድም ውጊያ ባልተካሄደ ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ተከፋፍለዋል፣ ተዳክመዋል ብለው ያሰቡት የአገሪቱ ጠላቶች ሰላምን ሳይፈልጉ ቀሩ፡፡ ጦርነቶች ተካሄዱ፡፡ የአባይን ሸለቆ ለመቆጣጠር የታለመው ህልም በጀግናው ንጉስ መከነ፡፡ ህልሙ ግን ዛሬም አልሞተም፡፡ አገሩን ከጠላቶች መጠበቅና የክፉ ህልመኞችን ምኞት ማምከን የትውልድ ግዴታ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top