የታዛ እንግዳ

ኢትዮጲያዊው ኮከብ በቶኪዮ ምሽት

1979 ዓ.ም ብሄራዊ ቲያትርን ወክለው ታዋቂዎቹ ከያኒያን አለሙ ገ/አብና አለምፀሀይ ወዳጆ ረጲ ሳሙና ፋብሪካ በወጣቶች ለፋብሪካው ሠራተኞች ይቀርብ የነበረውን የሙዚቃ ዝግጅት ይከታተላሉ። የኪነ ጥበብ መዐዛ ሲያዉድ ማሽተት የሚችል አፍንጫ ፣ ጥዑም ዜማ ሲቀመር የሚቀሰር ጆሮአቸውና የጥበብን ፍካት ማየት የሚችል አይናቸው ከከፍተኛ 6 ወጣቶች አንዱን ይማትራል፡፡ ሙዚቃው ሲሞዝቅ ተጀምሮ እስኪያልቅ አይናቸው ተተክሎበት ነበር፡፡ በስሜትና በፍቅር አይኑን ጨፍኖ ሙዚቃን ሲጫወት የነበረውን ጠይም፣ ቀጭን ወጣት እየተመለከቱ እርስ በርስ ተነጋገሩ፡፡ ትኩረታቸው አዲስ የከበሮ ኮከብ በኢትዮጲያ ከፍታ ላይ መታየቱን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ እረፍት ላይ ባንዱን የሚያበረታቱት የወቅቱ የሀገሪቱ ምርጦች በተለይ ከያኒ አለሙ ገ /አብ ወደ ድራመሩ ጠጋ ብሎ ” ሰኞ ብቅ በል ቢሮ” የሚል ግብዣ አቀረበ፡፡ ለክፍል ጓደኞቹ የእስኪርቢቶውን ቀፎ ከዴስክ ጋር ሲፋጭ በሚፈጥረው ሙዚቃ እየተደሰተ የሚያጫውተው ህፃን ወደ ሀገሪቱ ታላቅ ተቋም ያደረገው ጉዞ ህልም ነበር ። በሀሴት ግብዣውን ተቀብሎ ቀደምቶቹ በጠረጉለት መንገድ ተጓዘ፡፡ ሰኞ እፍር ቀዝቅዝ ብሎ ገባ። በጊዜያዊ ቅጥር ጀምሮ ወረት፣ የደመወዝ ዝቅተኝነት እና የውጪ ጉዞ ሆዱን ሳያባቡት ብሄራዊ ትያትርን የህይወት ገፁ ምዕራፍ መጀመሪያና መደምደሚያ ሊያደርጋት እነሆ 32 ዓመታትን ጎሎጎታዋም ፋሲካዋንም ዘልቆባታል። አርቲስት ዘሪሁን በቀለ።

አርቲስት ዘሪሁን በቀለ

ትዕይንተ ጥበባት በብሄራዊ ቲያትር

ብሄራዊ ትያትር የከበሮ ስልቶችን እያቀያየርኩ እንድጫወት አስችሎኛል። ቤዝ ድራም፣ ቶምና ቶምቶሞችን ሠለጠንኩ። በተለይ ታላቁ የጥበብ መድረክ ላይ ሀሙስ ከሠ0ት ከአስር እስከ አስራ ሁለት ሠዐት ትዕይንተ ጥበባት ላይ በባህል ከበሮ መቺነት ሠርቼያለሁ። ከዘመናዊ ድምጻዊያን ጥላሁን ገሠሠ ፣ አለማየሁ እሸቴ ፣ መልካሙ ተበጀና እንዲሁም ከተጋባዥ ድምጻዊያን መሀሙድ አህመድና ፍቅርተ ደሣለኝ አይነት ዕንቁዎች ሲሳተፉ ከባህላዊ ድምጻዊያን አሰፋ ዘገየ፣ ኪሮስ አለማየሁ፣ ደምሴ ተካ ይሳተፉ የነበረ ሲሆን የእኔም ምድብ ባህላዊ ሙዚቃ መጫወት ነበር።

የአፍሪካውያን ምሽት በጃፓን

የመጀመሪያ በረራዬ ነበር። 1981 ዓ.ም። እጅግ በሠለጠነው ከተማ ቶኪዮ ስታዲየም ላይ ጃፓናውያን የአፍሪካን ሙዚቃ ለመስማት ተሰብስበዋል። ሙዚቀኞችና ተወዛዋዦች ባህላቸውን ለማሳየት የክንውኑን ጉዳይ ከአስተባባሪዎቹ ትዕዛዝ ይጠባበቃሉ። አስተባባሪዎቹ ተዘጋጅተን የመጣንበትን የብሄረሰብ ሙዚቃ ለመጫወት የተሰጠን ደቂቃ አስር ብቻ መሆኑን አረዱን። ተስፋ መቁረጥ አልፈለግንም። የወሎውንም ፣ የጉምዙንም፣ የትግርኛውንም ፣ የኮንሶውንም ፣ የኦሮምኛውንም ሙዚቃ ስንጫወተዉ ከሌሎቹ ሀገራት ይልቅ የኛ ሙዚቃ የጃፓንን ስታድየም አነቃነቀ። ቶኪዮ በፉጨት ፣ በጭብጨባና በጩኸት ተደበላለቀች። አስተባባሪያችን በወቅቱ እዛው ቶኪዮ የአበበ ቢቂላን ሪከርድ የሰበረው የበላይነህ ዲንሳሞን መኖር ነገረን። በአይናችን ፈልገን አገኘነው። የክብር እንግዳው መቀመጫ ላይ ስሜታቸውን መቆጣጠር ካቃታቸው ጃፓኖች ጋር ይደግፈናል።

ዝግጅቱ ሲያበቃ የሀገራት ደረጃ ይፋ ተደረገ። አንደኛ “አይሰዩፒያ” አለ። በላይነህ ዲንሳሞ ድል ያደረገባት ሀገር ላይ የሙዚቃ ቡድናችን ከአፍሪካ ሙዚቀኞች አንደኛ ሲባል ድርብ ድል ነበር። ለኔ ደግሞ ሶስተኛ ድል ነበር ። ምክንያቱም የውድድሩ ምርጥ ድራሚስት መባሌ ነበር።

ኤርትራውያን በጀርመን

ከ20 ዓመታት በፊት በኢትዮጲያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ነበር። በዚያን ወቅት በጀርመን ሀኖቨር ከተማ የአለም የቱሪዝም ኤክስፖ ሊደረግ ስለነበር ኢትዮጲያን ወክለን ለመሄድ ሙዚቀኞች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ ስልጠና ወሠድን ። ስልጠናው ” ኤርትራውያን ዝግጅት ስታቀርቡ ሊረብሿችሁ ስለሚችሉ ተጠንቀቁ ” የምትል ማሣሠቢያ ነበር። ጥንቃቄውን አይምሮአችን ውስጥ አስቀምጠን ጀርመን ገባን። ከአለም ሀገራት የተሰባሰቡ ሠዎች ሀገራቸውን ለማስተዋወቅ በሀኖቨር ከተማ ለየሀገራቱ ቦታ ተሠቷል። እኛም ቦታችንን ይዘን ሙዚቃችንን በስሜት መጫወት ጀመርን። የታዳሚያንን ቀልብ ገዝተን መምጣት ጀመርን። በሙዚቃ መሳሪያዎቻችን ስንጫዎት የተለያዩ ሀገር ዜጎች ከበውን ይመለከቱን ነበር። ፈርሙልን የሚሉ ዜጎች አያሌ ነበሩ። በሙዚቃችን ሀገራችንን አስጠርተን ከአለም ሀገራት መካከል በዝግጅቱ ሁለተኛ ወጣን። ሁኔታው ቢያስደስተንም ይበልጥ ሀሴታችንን ያደመቀው ግን “ተጠንቀቋቸው ” የተባልናቸዉ ኤርትራውያን ሁኔታ ነበር። ቀድሞውንም እኔ ኤርትራውያን ጓደኞች ነበሩኝ። ታዋቂው ኤርትራዊ ድምፃዊ የማነ ባርያው ወዳጄ ነበር።

ታዲያ ሙዚቃ ስንጫወት በለቅሶ ታጅበው ያዩን ነበር ፣ ጭብጨባውና ፉጨታቸው ይገርማል፣ ”መሬታችን እንጂ የተለያየው እኛ አልተለየንም” ብለው አቅፈውናል፣ እኔም ከአንዳንዶቹ ኤርትራውያን ጋር ተወዳጅቼ ቤታቸው በማሣደርና ልብስና ጫማም በመስጠት ፍቅራቸውን አሳይተውኛል። ታዲያ ዶ/ር አብይ አስመራ ሲገባ የነበረው የህዝብ አቀባበል ሀኖቨርን በትዝታ እንዳስብ አድርጎኛል።

የመጀመሪያ በረራ ወደ ጁሀንሰበርግ

ስራዬ ወደ ታላላቅ ሀገራት ወስዶኛል፤ ታላላቅ ሠዎች ፊትም እንድቀርብ ሆኛለሁ። ለምሳሌ እነ ሴፍ ብላተር ፊት ቀርበው በ98 የአለም ዋንጫ ላይ ለፊፋ ሠዎች ስራቸውን ካቀረቡ ሙዚቀኞች አንዱ ነኝ። የደቡብ አፍሪካው ግን ይለያል።

ውብ አውራ ጎዳናዎች ፣ አብረቅራቂ ህንፃዎች ያሏት ደቡብ ኣፍሪካ በነጻነት ማግስት በአፍሪካ ያልተለመደ ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር የተከወነበት ሁነት ላይ ተገኘሁ። ሳቅ የሞላበት ፊት ብዙ ነበር። የመጀመሪያው የቀጥታ በረራ ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ጆሀንስበርግ የኢትዮጰያ አየር መንገድ ተጓዦች ሆንን። አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ሲነሣ የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት የወቅቱን የመጀመሪያዋ የኣፍሪካ የ10,000 ሜትር ሴት ሻምፕዮና “ልያት” ብለው ስለነበር ሀራሬ ቤተ መንግስት ግብዣን ያካተተ የአንድ ቀን ቆይታ አደረግንና ወደ ጆሀንስበርግ ሄድን።

በትልቅ ሆቴል በአፓርታይድ ጊዜ ስልጣን ላይ የነበሩት ደ ክለርክ እና ማንዴላ ጎን ለጎን ቁጭ ብለው የስልጣን ርክክብ በሚከወንበት ቦታ ላይ እኔ ተገኝቼያለሁ፡፡ ህልም የሚመስለው ቅፅበት ሁላችንም የኢትዮጲያ ሙዚቃን እየተጫወትን ከፕሮግራም መሪው “የአፍሪካን ሙዚቃ በከበሮህ ልትጫወት ትችላለህ?” ብሎ ጠየቀኝ ። እንደምችል ነገርኩት፡፡ ሙዚቃ ቆሞ እኔ ብቻ ከበሮዬን ጠበቅ አድርጌ መጫወት ጀመርኩ። ሁለቱ መሪዎች (ማንዴላና ደክለርክ) ስልተ ምቴን እየተከተሉ መደነስ ጀመሩ፡፡ ኣላመንኩም። መሪዎቹ ሲደንሱ ህዝቡ ያጨበጭባል። ካሜራዎቹ ሌንሶቻቸውን ወደኔና ወደ ሁለቱ መሪዎች ሠደሩ። ልቤ ሞቱ ሲጨምር ይታወቀኛል። ደክለርክ ወደኔ ቀረበና ሁለት ሺህ ዶላር ሸለመኝ።

ኪዮቶ ጃፓን

ጃፓን በተደጋጋሚ ካየኋቸው ሀገሮች መካከል አንዷ ነች። ከበሮዬን እየመታሁ ድንገት የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ከበሮ መጫወቻ ዱላዬ ወድቆ ደንግጬ ሁኔታዬን አይተው ጃፓናውያን አረጋግተውኛል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እዛው ወደ ኦኪናዋ ደሴት ስንሄድ አውሮፕላናችን የአየር ጠባይ መለወጥ ገጥሞት ከሞት ጋር ግብግብ ማለት ይቻላል ፓይለቱ በፈጸመው ጀብዱ ከሞት ተርፈናል። ሆኖም በሠለጠነችው ጃፓን ታላቅ ትምህርት የሰጠኝ አንድ ገጠመኝ ተከሠተ፡፡ ኪዮቶ ቶዮታ የመኪና ኩባንያ የሚሠራበት ሲሆን ወደ ኢትዮጲያ እንዲገባ በኢትዮጲያ በኩል ቢጠየቅም ጉዳዩ እየተራዘመ ቆየ :: እኛ ወደ ከተማዋ ገብተን የሙዚቃ ስራችንን ሄደን ስናቀርብ ያየን የከተማዋ ከንቲባ የቶዮታ ከኢትዮጵያ ጋር ይስራ ፈቃድ ሠጠ፡፡ ወደ ከተማዋ ሄደን ስራችንን እንድናቀርብ ያደረጉን አምባሳደር ማርቆስም ” እኛ 6 ወር ሞክረን ያላሣካነውን እናንተ በደቂቃዎች አሳካችሁ ” ብለው የኪነጥበብን ሀያልነት መስከሩ።

ብቻዬን ቆሜያለሁ

ስታር ባክስ የተባለ ኩባንያ የይርጋ ጨፌን ቡና “የኔ ነው ” በማለት እየሸጠ እንደሆነ ተደረሰበት። የኢትዮጲያ አይምሯዊ ንብረት በብዙ ክርክር አሸንፎ የርክክቡ ቀን ተቆረጠ፡፡ ቦታው ደግሞ ሚኒሶታ ። የኢትዮጲያ መንግስት ባህሉን ለማስተዋወቅና ለምስጋና 30 የሚሆኑ ሙዚቀኞችና ሞዴሎችን ይዞ ወደ አሜሪካዋ ሂውስተን ሄድን። ሂውስተን ላይ ዝግጅቱን ካቀርብን በኋላ ግን ከእኔ ውጭ አንድም ሠው ሳይቀር ከተያዘለት ሆቴል ውልቅ ብሎ ጠፋ። ብቻዬን ቆምኩ። ይህንን የሠሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ደነገጡ። መላ መጣልኝ ። ሙዚቀኞቹ ከሆቴል ሲወጡ ጥለውት በሄዱት የሀገር ባህል ልብስ ቀድሜ የማውቃቸው አሜሪካ ኑሮአቸውን ያደረጉ ኢትዮጲያዊያን ሙዚቀኞችን ጠርቼ አጥንተን በሚኒሶታ ደመቅን። ሚኒስትሯም ከጭንቀት ተገላገሉ፡፡ ወደ ኢትዮጲያ የተመለሰው አውሮፕላን ዉስጥ የነበርነው እኔና የዛሬዋ የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ባለቤት አምለሰት ሙጬ ነበርን። ሆኖም ሚኒስትሯ እንኳን ሌላ የምስጋና ደብዳቤ እንኳን አልሰጡኝም፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top