ጣዕሞት

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናድጃ ካሳነሽ የስዊድን አይዶልን አሸነፈች

በሙሉ ስሟ ናድጃ ካሳነሽ ሆልም ትባላለች። የተወለደችው ጥቅምት 10፣ 1997 (እኤአ) ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ወደ አደገችበት ስዊድን የሄደችው ገና በልጅነቷ በጉዲፈቻ ተወስዳ ሲሆን በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ በምንገኘው በዚሁ በፈረንጆቹ ዓመት 2020 የስዊድን የአመቱ ‘አይዶል’ / Idol ክብርን የግሏ አድርጋለች።

የስዊድን አይዶል ውድድር የተጀመረው ከ16 ዓመት በፊት በ2004 ሲሆን ቲቪ4 በተሰኘ የስዊድን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሙሉ ሽፋን ተሰጥቶት የሚተላለፈው ይሄ ውድድር በሃገሪቷ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት የቻለ ነው። የመርኃ-ግብሩ አላማ የስዊድን ምርጥ ሙዚቀኞችን ማግኘት ሲሆን የመጨረሻው አሸናፊ የሚለየው ከህዝብ በሚሰበሰብ ድምጽ ነው። የውድድሩ ተሳታፊዎች በህብረት እስካሁን ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሙዚቃ አልበሞች በስዊድን ብቻ መሸጥ ችለዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ዘፋኝ ባሳለፍነው ወር ማብቂያ ላይ በስዊድን ሀገር ትልቁን የሙዚቀኞች ውድድር የሆነውን TV4 singing competition idol 2020 አሸንፋለች። በዚህ ትልቅ መድረክ አሸናፊ ስትሆን በ2014 ዓ.ም ሊሳ አያክስ ካሸነፈች በኋላ የመጀመሪያዋ እንስት አሸናፊ መሆንም ችላለች። በዓለም ዙሪያ የብዙ አንጋፋ ሙዚቀኞችን ስራ በመጫወት የምትታወቀው ናድጃ በውድድሩ ፍጻሜ ለውድድር የሚቀርበውን ሙዚቃም የራሷ ማድረግ ችላለች። በስፋት እየተደመጠላት ያለው ይሄ ስራ ‘ዩስድ ቱ ሚ’ / Used To Me በሚል ርዕስ የተጻፈው በአሌክሳንደር ክሮንለንድ እና ሉካስ ሎውልስ ነው።

ናድጃ ገና የ23 ዓመት አፍላ ወጣት ስትሆን በሙያው ላቅ ያለ ስኬት ከፊቷ እንደሚጠብቃት ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎባታል። ውድድሩን ማሸነፏን ተከትሎ በውጤቱ ደስተኛ መሆኗን ስትገልጽ ልትቆጣጠረው ባልቻለችው የደስታ እንባ ታጅባ እንዲህ ብላለች። “ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም። እጅጉን ደስ ብሎኛል። ባላሸንፍ ራሱ እዚህ በመድረሴ ብቻ እጅጉን ደስተኛ እሆን ነበር። ረዥሙን መንገድ ተጉዤ መጥቻለሁ።”

በኮሮና ምክንያት እንደ ቀድሞው በሺዎች በሚቆጠሩ ታዳሚዎች ፊት ያልተደረገው የዘንድሮው የስዊድን አይዶል የፍጻሜ ውድድር ላይ ናድጃ የቢዮንሴና ኬንድሪክ ላማርን ‘ፍሪደም’ / freedom እና የሎረን አለርድን ‘ኔቨር ኢነፍ’ / never enough የሚሉ ሙዚቃዎችን ተጫውታለች።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top