መጽሐፍ ዳሰሳ

ትንሿ ሀገር

ርዕስ ፡ ትንሿ ሀገር
ደራሲ ፡ ጋይል ፋይ
ተርጓሚ ፡ ገነት አየለ አንበሴ
ኅትመት ፡ 2013
የገጽ ብዛት ፡ 214
የመሸጫ ዋጋ ፡ ብር 91.45

መግቢያ

ከተለመደውና ባሕላዊው የግለ ታሪክ መጽሐፍት ወጣ ባለ መልኩ የሰዎችን በተወሰነ ጊዜና ቦታ ውስጥ የነበራቸውን የሕይወት አጋጣሚና ትውስታ የሚያጋሩ መጽሐፍት (memoir) ዋና አላማቸው ከባለታሪኮቹ የሕይወት ልምድ ሌሎች ተምረውበት በታሪክ የተፈጸሙ ስህተቶች እንዳይደገሙ እና በታሪኩ መስመር ውስጥ መማር ያለብንን ለመማር እንችል ዘንድ ነው። ብልህ ከሰው ይማራል፣ ሞኝ በራሱ ይማራል እንዲል የሀገራችን ተረት በሌሎች ወንድሞቻችን የሰው ልጆች ላይ የተፈጸሙ ታሪካዊ ስህተቶች ከእነዚህ አይነት የአይን ምስክሮች የብእር አንደበት ተቀብለን ሀገርና ትውልድን ማንም የሰው ልጅ ሊያስታውሰው እንኳን ከማይሻው ጥፋት መጠበቅ ብልህነት መሆኑ አያሻማም። በተለይ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ አይነት ሕብረ-ብሄራዊ ሀገራት ከእንደዚህ አይነት የገፈቱ ቀማሾች ወገኖቻችን የሕይወት ተሞክሮ ብዙ የምንማረው እና የምናተርፍበት ትምህርት እንደሚሰጠን ጥርጥር የለውም።

ትንሿ ሀገር (Petit pays) የተሰኘው መጽሐፍ በፈረንሳዊው ራፐር ጋይል ፋይ ተጽፎ ወደ በርካታ ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን ባለፈው የሰኔ ወር ወደ አማርኛ መልሳ ያስነበበችን ደግሞ ጋዜጠኛ ገነት አየለ አንበሴ ናት። ጋዜጠኛ ገነት ከሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ በዓመቱ ከሙያዋ ሃላፊነት ጋር ተያይዞ ወደ ቦታው ለማምራት እና የዚህን አስከፊ የታሪክ አጋጣሚ ገፈት ቀማሽ መሬት እና ህዝቦች ህመም በዓይኗ የማየትና ከአንደባታቸው የመስማት እድል ገጥሟት ነበር። በዚህ መጽሐፍም በሩዋንዳ እና ብሩንዲ ሲቪሎች በሰፊው የተሳተፉበትን የዘር ጭፍጨፋ የአስራ አንድ አመቱ ተራኪያችን እንደሚያስታውሰው ተደርጎ ተተርኮበታል። የዋህ እና ምስኪኑ ሕዝብ በፓለቲከኞች ሴራ በተሸረበ የሞት ድግስ ታዳሚ ለመሆን መገደዱ ክፏኛ አሳዛኝ የነበረ መሆኑን ደራሲው ለመግለጽ እንዲህ የሚል እናገኛለን ፦

የዋህነታቸው ያለመጠርጠራቸው፣ እንደነሱ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዚህ ዓለም ንፁሐን ምስል መጣብኝ። ሳያውቁ ሳይጠረጥሩ አገር ደህና ብለው ከገደል ጫፍ ላይ የቆሙ ንጹሐን ሰላማዊ ሰዎች ታዩኝ። ሰላም ፈላጊ ያልጠረጠሩ ወደ ገደል እያመሩ መሆኑ ሳይታወቃቸው የሚገሠግሡ የዚህ ዓለም በጎች። … (ገጽ 203)

ምሁራን፣ የህግ ሰዎች እና የሀይማኖት መሪዎች ሳይቀሩ በተሳተፏበት በዚህ የመካከለኛው አፍሪካ የ1990ዎቹ እብደት በአጋጣሚ የተፈጠረ አደጋ ሳይሆን በፖለቲካ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተከሽኖ የተሰራ የደም እና የሞት ኢ-ልብወለድ ነው። ጥቁር አፍሪካውያን ወገኖቻችን ደም ምስጋና የሌለው አሸዋ ሲያጠጣ የድረሱልን ጥሪያቸውን ቢያሰሙም የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎት ከፍተኛ እልቂት እንዲፈጸም እንደሆነ ስናስታውስ ደግሞ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንድንሰጠው ይበልጥ የሚያስገነዝብ ነው።

ትንሿ ሀገር መጽሐፍ በሩዋንዳ ከተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ተከትሎ ወደ ጎረቤቶቻቸው የብሩንዲ ዜጎች የተጋባውን ተመሳሳይ ጥላሸት በታዳጊ ሕጻናት ቀናቶች አስታኮ በጥሩ ሁኔታ የተከተበ ሲሆን መጽሐፉ በታተመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ እና በርካታ ሽልማቶች እና ክብሮችንም ማግኘት የቻለ ነው።

መሰል ስራዎች

ተመሳሳይ የሚባል ይዘት ያላቸው ብዙ ስራዎች እንደተሰሩ ይታወቃል። ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ለማንሳት ፦ በኢማኩሊ ኢሊባጊዛ የተጻፈው ሌፍት ቱ ቴል (Left to tell) መጽሐፍ በሩዋንዳ የተፈጸመውን አሰቃቂ ታሪክ በስፋት ካስነበቡን መጽሐፍት አንዱና ዋንኛው ነው። እንዲሁም የሾላስቲክ ሞካሶኛ – ፍሮም ዘ ርዋንዲያን ፐርስፔክቲቭ (From The Rwandan Perspective) እና የሮሜዮ ዳላየር ሼክ ሃንድስ ዊዝ ዘ ዴቪል (Shake Hands With The Devil) የሚጠቀሱ ናቸው። ከመጽሐፍትም በተጨማሪ የቴሪ ጆርጅ ሆቴል ሩዋንዳ (Hotel Rwanda) እና የራውል ፔክ ሰምታይምስ ኢን አፕሪል (Sometimes In April) ፊልሞች የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ በስፋት የሚዳስሱ ናቸው።

ከነዚህ ውስጥ በሃገራችን በስፋት የተነበበውን ሌፍት ቱ ቴል በተወሰነ መልኩ ዳስሼ ለማለፍ ወደድኩ። በመጽሐፉ ውስጥ በማንም ላይ ባይደገም የምትለውን የሕይወቷን ገጾች ያጋራችንን ባለታሪክ እናገኛለን። ሩዋንዳ ውስጥ ከቤልጀም ቅኝ ግዛት ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ ነው። ሀገሪቷ ውስጥ በቁጥር ከሚያንሱት ከቱትሲ ጎሳ የተገኘ መንግስት ላይ ከፍተኛ ቅራኔ የነበራቸውና ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው የሁቱ ጎሳ አባላት መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ሁቱ ሪፐብሊክን አቁመዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ከመንግስታቸው ሲቀለቡ ኖረዋል። የሁቱ ሪፐብሊክ መሪ ከብሩንዲ አቻው ጋር በአውሮፕላን የመመታት አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ድርጊቱ በቱትሲ ጎሳ አባላት ላይ ስለተላከከ በ1994 (እኤአ) እጅግ ከፍተኛ የሚባል የዘር ጭፍጨፋ አስከትሏል። በመቶ ቀናት ውስጥም ብቻ እስከ ሚሊዮን የሚደርሱ ጎበዞች፣ አረጋውያን፣ ሴቶችና ሕጻናት በገዛ ወገኖቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተሰውተዋል። ባለታሪኳ ኢማኩሊ ኢሊባጊዛም ከዚህ የሞት ባሕር በተዓምር ተርፋ የምትስታውሰውን ገሃነም በእኛ ይብቃ ስትል ትናገራለች።

ትንሿ ሀገር መጽሐፍ ከላይ ካየናቸው ስራዎች ለየት የሚያደርገው የታሪኩ ባለቤቶች በሩዋንዳ ሳይሆን በጎረቤቶቻቸው በብሩንዲ ሀገር የነበሩ ሲሆን፣ ጋይል ፋይ በዚያ በነበረው ጊዜ ያየውን፣ የሰማውን እና የኖረውን ያካፈለበት ነው። ከሩዋንዳ አስቀያሚ የታሪክ ጥቁር ጠባሳ መማር ያልቻሉት የብሩንዲ ወንድሞቻቸው የሩዋንዳው ክስተት ጥላ ተጭኗቸው በአዕምሮ እና በአካል እንኳን ያልበሰሉ ሕጻናቶች በተካፈሉበት ጭፍጨፋ ለማመን የሚከብዱ ዘግናኝ ታሪኮች ተመዝግበውበት አልፏል። ይህም ነገሩን እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የሚያስረግጥና ነግ በኔ እንድንልና በእኛ እንዳይደገም የማረጋገጥ ስራ እንድንሰራ ከማንቂያ ደውልም በላይ የሚሆን ነው። ለህጻናት የሚሰበክ የመከፋፈል እና ጎጠኝነት እንደቀልድ በጨዋታ መኃል ሊፈስ እንደሚችል በመጽሐፉ ለማሳየት ተሞክሯል።

አያችሁ ልጆች ቡሩንዲ ውስጥ ልክ እንደ ሩዋንዳ ነው። ሦስት የተለያዩ ግሩፖች አሉ። ብሔሮች ይባላሉ። … (ገጽ 1)

መጽሐፉ ሙሉ ለሙሉ እንደ ማንኛውም ግለታሪክ መጽሐፍት በቀጥታ የተጻፈ ሳይሆን የልቦለድ ይዘት ተጨምሮበት የተዘጋጀ እንደመሆኑ ደራሲው የህይወት ልምዱን ቆንጆ በሆነ የስነጽሑፍ ይዘት አድምቆ ለማካፈል ነጻነቱን ሰጥቶታል።

ጋይል ፋይ ማነው?

ከፈረንሳዊ አባቱ እና ከሩዋንዳዊ እናቱ ጋር በብሩንዲ ባሳለፋቸው የሕጻንነት ጊዜው ያሳለፈውን የግል ገጠመኞቹን በዚህ መጽሐፉ የሳለልን ጋይል ፋይ ከእርስ በርስ ጦርነቱ በኋላ ከታናሽ እህቱ ጋር ወደ ፈረንሳይ በመሰደድ በዚያም የሂፕ-ሆፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ራፐር ለመሆን የበቃ ነው። ይሄን መጽሐፍ ከመጻፉም በፊት በተመሳሳይ ርዕስ የተሰራና ከፍተኛ እውቅና ያገኘበት ሙዚቃ አለው። ራሱ በሚጽፋቸው የሙዚቃ ግጥሞቹ ከፍተኛ ትኩረት መሳብ የቻለው ጋይል ፋይ ወደ ድርሰት ጎዳናም መጥቶ ስኬታማ መሆን ችሏል። እኤአ አቆጣጠር በ2016 ዓ.ም የታተመው ይህ መጽሐፍ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ቅጂዎች ተሽጦለታል።

ትንሿ ሀገር በውስጥ ገጾቿ

ተራኪያችን ገብርኤል የተሰኘ የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ሲሆን ከደራሲው ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ፈረንሳያዊ አባት እና ሩዋንዳዊ እናት ያለው ነው። ገብርኤል በብሩንዲ ቡጁምቡራ ከተማ ሲያድግ በአከባቢው ተጽእኖ ባስተናገዳቸው የማንነት አስተሳሰብ ለውጦች እና ውዥንብሮች ውስጥ ሆኖ የብሩንዲን የዘር ጭፍጨፋ የሱን አይኖች አይናችን፣ ጆሮዎቹን ጆሮዋችን አድርገን ያሳየናል፣ ያስደምጠናል።

በመጽሐፉ ውስጥ እንደምናገኘው ገብርኤል እና እኅቱ ሲኒማ ገብተው የሚመለከቷቸውን የድራማ ገጸ ባህርያት ጨምሮ በመንገድ የሚያዩትን ሰው ሁሉ በጎሳ መመደብ የተማሩት.. ለለ ሁለቱ የዘር-መደቦች አፍንጫ ልዩነት ከአባታቸው የተሰጣቸውን መረጃ በመጠቀም እንደነበር በታሪኩ ውስጥ በግልጽ እንዲህ ተቀምጧል ፦

… “ታዲያ ምን አጣላቸው?”

ምክንያቱም አፍንጫቸው አንድ ስላልሆነ ነው።

ይሄ በዘር-መደቦቹ መኃል በፕሮፖጋንዳ ተጋኖ የሚታየው የአፍንጫ ቅርጽ ልዩነት ግን የሰው ልጆችን በመከፋፈል ያስከተለው አደጋ ለእያንዳዱ ብሩንዲያዊ ከሬት የመረረና በውጤቱም ላይ የትኛውም የአፍንጫ ቅርጽ ለውጥ እንደማያመጣ የአስራ አንድ አመቱ ታዳጊ ሲታዘብ እንዲህ ሲል እንሰማዋለን ፦

ጓደኛሞች አንተ ሁቱ አንተ ቱትሲ እየተባባሉ መሰዳደብ በየሜዳው መደባደብ ጀመሩ። የእያንዳንችን አፍንጫ ቅርጽ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ጠረኑ ደርሶናል። (ገጽ 2 – 3)

በመጽሐፉ መነሻ ገጾች ትረካው የሚጀምረው በፓሪስ ከሚኖር ብቸኝነት የሚያጠቃው እና ደስታ የራቀው የቢሮ ሰራተኛ ነው። ገብርኤል የሠላሳ ሦስተኛ ዓመቱን ልደቱን ያከበረው ለብቻው ነው። ጓደኞቹ ዘወትር ልቦናውን የሚወጋው የሕይወቱ ምእራፍ ውስጥ ብቻ ነው ያሉት። አብረው የኖሩት የደስታ፣ የሐዘንና የቅጀት ጊዜያትን ነው ደግሞ ደጋግሞ የሚኖረው። በርካታ ዓመታት ቢያልፏም ገብርኤል አሁንም ያ ብሩንዲ ውስጥ የሚኖረው እና እነዚያ አሰቃቂ ትዝታዎች የሚያድኑት ታዳጊ ነው። የማንነት ጥያቄዎች ዛሬም ይሻክሩታል። ከየት ነህ ጥያቄዎች የአባቱ ወገኖች እንደ ጥቁር፣ የእናቱ ወገኞች እንደ ነጭ ተመልክተው ላሳደጉት ሰው እንደ ሌላው ሰው ቀላልና ተራ ጥያቄዎች አይደሉም። ያሰቃዩታል። ያበሳጩታል። ያስተክዙታል። በሀሳብ ጀልባ አንቅልበው በከባድ ወጀብ ገፍተው በታዳጊ እድሜው ወደኖረው ሲዖል ይመልሱታል።

የአስራ አንድ ዓመቱ ገብርኤል ቀናቶች ዛሬም በሠላሳ ሦስት ዓመቱ ሰውዬ ትዝታዎች ውስጥ ከሰማዩ ጠርተው፣ ከነፋሱ ረቀው ተሰድረዋል። እያንዳንዱን ቀናት ያስታውሳቸዋል። ማንጎዎች ሲሰርቅ፣ ብስክሌት ሲነዳ፣ ስለልጃገረዶች ሲያወሩ፣ የሚደርስለት አጥቶ ታንቆ ተይዞ ስለተገረዘበት እለትም ጭምር ሁሉን እያከታተለ ያስቃኘናል።

ገብርኤል ስለሁቱ እና ቱትሲ ጎሳ ሕዝቦች ቅራኔ ሀ-ብሎ የተማረው ከአባታቱ ነው። ከዚያም ከእህቱ ጋር የሰውን አፍንጫ ሁሉ በእይታ እየለኩ የጎሳውን አባላት መመደብን ተለማመዱ። እንዲሁም ቤተሰቦቿን በዘግናኝ ሁኔታ ሩዋንዳ ውስጥ ካጣቻቸው እናቱ ቃላት በቀልን ጸነሱ። ከጓደኞቹ ጋር ሆነው በህጻን ልብ በጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ ይዘራ የነበረውን የፕሮፖጋንዳ አረም አጭደው እህል ብለው ተመግበውታል። ተጎራርሰውታል። ዘመናትን ተሻግሮ እንኳን ደም ደም ማስገሳቱን ያላቆመ አረም! ይንንም አይነቱን አረም ወላጆች ሳይቀሩ በማስተዋልም ሆነ በስሜታዊነት በገዛ ልጆቻቸው ላይ ይዘሩ እንደነበር ከዚህ በታች ያለው የባለታሪካችን ኑዛዜ ጥሩ ማሳያ መሆን የሚችል ነው።

እናቴ ይህንን ዘግናኝ ታሪክ በሹክሹክታ በእርጋታ እያረፈች እየደጋገመች ለአና መንገሯን ቀጠለች። ጆሮዎቼን በሁለት እጆቼ ግጥም አድርጌ ይዤ ትራሴ ውስጥ ተደብቄ ለማምለጥ ሞከርኩ። ይህን ዘግናኝ ታሪክ ላለመስማት ታገልኩ። መስማት አልፈለግሁም። ማወቅ አልፈለግሁም። የአይጥ ጉድጓድ ውስጥ ገብቼ ጥቅልል ማለትን ተመኘሁ። ዋሻ ውስጥ መሸሸግ አማረኝ። ከሠፈሬ ወጣ ብሎ ያለው ዓለም አስጠላኝ። … (ገጽ 184)

ለአስርት ዓመታት በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ተዘርቶ ፓለቲካው እየኮተኮተ ያሳደገው የጥላቻ ተክል አብቦ የጎመራው በአንድ የተረገመ ቀን የሩዋንዳና የብሩንዲ ሀገር መሪዎች የተሳፈሩበት አውሮፕላን ተመቶ ከተገደሉ በኋላ ነው። በዚያን ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዎች ሳይቀሩ ተቀጣጥሎ የበሰለውን የጥላቻ ፍሬ አንድ ሊሉት አልወደዱም።

ገብርኤል አንድ ሕጻን በእደዚህ አይነት አደገኛ የዘረኝነት ሕመም በአጭር ጊዜ ውስጥ በጆሮ ከመስማት ተነስቶ በድርጊቶቹ ወደ መሳተፍ ያደገበትን መንገድ ሲያስጎበኘን እንደዚህ አይነቱን ተዛማች የሃሳብ ጉንፋን አድጎ ነቀርሳ ከመሆኑ በፊት በአጭር ማስቀረት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ልብ ይሏል።

መደምደሚያ

በሀገራችን በኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚታዩት የመከፋፈል እና ዘር ተኮር መካረር ብሎም የንጹሐን ሕልፈተ ሕይወቶች ምናልባትም ሀገራችን በሩዋንዳ እና ብሩንዲ የታየው አይነት እጅግ አስከፊ የዘር ጭፍጨፋ እና የርስ በርስ ጦርነት ልታስተናግድ እንደምትችል የማስጠንቀቂያ ደውል መሆናቸውን ልብ ብለን አፍሪካዊ ወገኖቻችን የሰሩትን ስህተት በእኛ እንዳይደገም እና የታሪክ ተወቃሽም ላለመሆን ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራና ሌላም ሌላም እየተባባለን የመጠቋቆም፣ የጥላቻ እና ለፖለቲካ አላማ የሚዘመር ፕሮፖጋንዳዎችን ወደ ጎን በመተው ዘመናትን ባሻገረን የመተሳሰብ እና ተቻችሎ የመኖር ኢትዮጵያዊ ልምዳችንን ይዘን ልንጓዝ ይገባል። ከባለታሪካችንም በጎጠኝነት እና የበቀል አስተሳሰብ ለተመረዙት ጓደኞቹ ከተናገረው ምንማረው ይሄንኑ ነው ፦

… “እኔ ሁቱም ቱትሲም አይደለሁም። የኔ ጉዳይ አይደለም። አይመለከተኝም። እናንተ ጓደኞቼ የሆናችሁት ስለምወዳችሁ ነው። እንጂ የዚህ ወይም የዚያ ብሔረሰብ አባል ስለሆናችሁ አይደለም። ይሄ እናንተ የምትሉት የኔ ጉዳይ አይደለም። ” … (ገጽ 180)

ትንሿ ሀገር መጽሐፍ በይዘቱ አጠር ብሎ ነገር ግን ከፍተኛ አቅምና ጉልበት ያለው፤ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ቢያነበው በርግጠኝነት የሚያተርፍበት የህይወት ጠቃሚ ትምህርቶችን የያዘ መዝገብ ነው። ሰው የመሆንን ትርጉም፣ የሰብዓዊነትን አደጋና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚፈነጥቅ ውብ የሰብዓዊነትን ሻማ ያስጎበኘናል። በጋይል ፋይ አለም የመሰከረለት ከፍተኛ የስነጽሑፍ አቅም ተከትቦ፤ ጋዜጠኛ ገነት ቀለሙን እና ቃናውን ጠብቃ በአማርኛ እነሆ ብላናለች። መልካም ንባብ!

ህዳር 2013 ዓ.ም

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top