አድባራተ ጥበብ

ተስፋዬ ገሠሠ – አንጋፋ የጥበብ ሰው

በዛሬው ዕለት የቀብር ሥነሥርዓቱ የተፈጸመው አንጋፋ የጥበብ ሰው ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ብዙዎች እንደሚያምኑት እውነተኛ፣ ቅንና ግልጽ ተፈጥሮ የነበረው ሰው ነው። ከዓመታት በፊት በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ሁለቴ የክብር ምሽት አዘጋጅተንለት ነበር። እና አሁን የማካፍላችሁ ጽሑፍ በዚያ መድረክ የቀረበ ሲሆን፣ እሱን ራሱን አነጋግሬ፣ ሌሎች ብዕረኞች የጻፏቸውን አጣቅሼ ያዘጋጀሁት ነው። የጋሽ ተስፋዬን ቀልድና ጨዋታ፣ ሳቅና ፈገግታ በጽሑፍ ማቅረብ እንዴት ይቻላል? እነሆ ከሕይወቱና ከሥራው የተጨለፈ አጭር ታሪክ።

ሁለገቡ የጥበብ ሰው አቶ ተስፋዬ ገሠሠ ደመራ በሚለኮስበት፣ በዓለ መስቀል በሚከበርበት ዕለት መስከረም 17 ቀን 1929 ዓ.ም በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በጉሮ ጉቱ ተወለደ። አባቱ አቶ ገሠሠ ቆለጭ፣ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ በለጠች ያየህ ይራድ ይባሉ ነበር። ተስፋዬ ሰባት ዓመት እስኪሆነው ደደር ውስጥ ያደገ ሲሆን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጠናቋል። በ1951 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በጠቅላላ ትምህርት የቢ.ኤ. ዲግሪ ተቀብሏል። በ1953 መጨረሻ ደግሞ አሜሪካ በሺካጎው የኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ በቴያትር ኪነጥበባት የኤም. ኤ. ዲግሪ አግኝቷል።

የተስፋዬ የልጅነት ጊዜና አስተዳደግ ግን አልጋ ባልጋ አልነበረም። ገና በስምንት ወሩ እናቱን አጣ። የሁለት ዓመቱን ሻማ ከማብራቱ በፊት ደግሞ አባቱን። ከወላጆቹ በወረሰው መሬት ላይ እያስተዳደሩ ያሳደጉት የአባቱ ጢሰኞቹ ነበሩ። የቄስ ትምህርቱንም የተማረው እዚያው ነበር። ሶስት ዓመት ገደማ ሲሆነው፣ የጣሊያን ወራሪዎች ደደርን ሲያቃጥሏትና ባንዶቻቸው ሲዘርፏት ተመልክቷል። ከዚያ በጊዜው አዲስ አበባ የሚኖሩ አክስቱ (የእናቱ ታላቅ እህት) እሳቸው ዘንድ ሆኖ እንዲማር ይልኩበታል። በዚህም መሠረት በ1937 ዓ.ም. – የሰባት ዓመት ልጅ ሆኖ – በባቡር ይሳፈርና ወደ አዲስ አበባ ይጓዛል። አዲስ አበባ ከሄደ በኋላ ስሜቱን የሚበጠብጥ አንድ ጉዳይ አጋጠመው። ይኸውም ከቅላቱና ከጠጉሩ ዞማነት ጋር የተያያዘ ነው። ተስፋዬ በጠላት ወረራ ወቅት በመወለዱ “አባቱ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የጣሊያን ወታደር ነው” የሚል ወሬ ይነፍስና በእጅጉ ይረበሻል። ታሞ ሆስፒታል እስከ መግባትም ይደርሳል። ምክንያቱም የጣሊያን ወራሪዎች በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀሙት ግፍ ገና ያልተረሳበት፣ ቁስሉም ገና ያልጠገገበት ወቅት ነበርና ነው። አቶ ተስፋዬ በአንድ ወቅት ለሚስተር ሞልቬር እንዳጫወተው አክስቱ ጉዳዩ ሃሰት መሆኑን እስኪያረጋግጡለት ድረስ የኅሊና እረፍት አልነበረውም። ነገሩ እንዲህ ነው። አክስቱም እንዲሁ ወሬውን ሰምተው ስለነበር እህታቸው በሞት አፋፍ ላይ ሳሉ ጉዳዩን ያነሱባቸዋል። ያገኙት መልስ ግን “እንኳንስ በውኔ በህልሜም ከፈረንጅ ጋር አልተኛሁ” የሚል ነበር። የተስፋዬም አባት ይህንኑ ኑዛዜ አምነው ስለተቀበሉ ሲሞቱ ሃብታቸውን ሁሉ ያወረሱት ለተስፋዬ ነበር። የተስፋዬ አያት ፊታውራሪ ቆለጭ አስቀድሞ የራስ መኮንን የጦር አበጋዝ ለጥቆም የራስ ተፈሪ (በኋላ ቀ.ኃ.ሥ.) አማካሪ ስለነበሩ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተሰቦቹን ያውቋቸው ነበር።

ተስፋዬ በተፈሪ መኮንን ሲማር የክቡር አቶ ከበደ ሚካኤልን “የትንቢት ቀጠሮ” ቴያትር ተመልክቶ ከመደሰቱ ሌላ ለረጅም ጊዜ ያስታውሰውም ነበር። “ከይቅርታ በላይ”ንም አንብቧል። እንደ ሌሎቹ ተማሪዎችም “እሮሮ” የተሰኘውን የከበደ ሚካኤል ተወዳጅ ግጥም በቃሉ አጥንቶት ነበር። ይሄ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ህግ የማጥናት ፍላጎት ቢኖረውም ስሜቱ ወደ ሥነጽሑፍና ወደ ቴያትር ሳይሳብ አልቀረም። ወደ ትወና ሙያ እንዲገባ የገፋው ግን ከተፈጥሮ ዝንባሌው ባሻገር በ”ከማን አንሼ” ስሜት የሚሠራው ነገር እንደነበር ራሱ ይናገራል። ሌሎቹ ያነበቡትን ያነባል፣ ያደረጉትን ያደርጋል። ከዚያን ዘመን ባልንጀሮቹ አንዱ የነበረውን ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ‘የመጽሐፍ ቀበኛና ቀስ ያለ’ ብሎ ሲገልጸው እሱ ግን ተጫዋችና ለፍላፊ እንደነበር ያስታውሳል። አቶ ስብሃት ራሱ ባንድ ወቅት በ“ኢትዮጵያን ሄራልድ” ጋዜጣ “Tess Fantastic” ብሎ ባወጣው መጣጥፍ ያን የወጣትነት ዘመናቸውን ሲያስታውስ ተስፋዬ ተጫዋችና ኮሚክ ስለነበር በዙሪያው የሚኮለኮሉ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል እንዳልነበር ዘግቧል። አቶ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ለ”መልክአ ዑመር፣ የዑመር ኻያም ሩብ አያቶች” በጻፈው መግቢያ (1987 ዓ.ም፣ ገጽ 5) ላይ “ተዋናዩ ተስፋዬ ገሠሠ ገና የትያትር ቤት መድረክ ላይ ሳይወጣ፣ ገና ተውኔት ትምህርት ቤት ሳይገባ፣ ገና ተዋናይ እሆናለሁ ብሎ ሳያስብ፣ አራት ኪሎ ኮሌጅ የኑሮ መድረክ ላይ ኮሜዲ መጫወት ያዘወትር ነበር።” ሲል አጠናክሮታል።

ተስፋዬ ቴያትርን ይበልጥ እንዲወድ ያደረገው የሚሰጣቸው አድናቆትና ማበረታቻ እንደነበር ሲናገር የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪዎች ሆነው ከነመኮንን ዶሪና ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ጋር አራት ኪሎ በሲኒማ ካምቦኒ ያሳዩትን ቴያትር እንደ አብነት ያቀርባል። የሕይወቱን አቅጣጫ የለወጠው አጋጣሚ ግን የአራተኛ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ “ኢዮብ”ን ከመጫወቱ ጋር የተያያዘ ነው። ገፀባህሪውንና ታሪኩን ስለወደደው ጥሩ አድርጎ ነበር የተጫወተው። ቴያትሩን ከተመለከቱና ካደነቁት አንዱም አጼ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ። በማግስቱ ንጉሡ ያስጠሩትና የእጅ ሰዓት ይሸልሙታል። ከዚያ ከወቅቱ የትምህርት ም/ሚኒስትር (ሚኒስትሩ ንጉሡ ራሳቸው ነበሩ) ዘንድ ይቀርብና ምን መሆን እንደሚፈልግ ሲጠየቅ ህግ መማር እንደሚሻ ይናገራል። ንጉሡ የመረጡለት ሙያ ቴያትር እንደሆነና ውጪ አገር ተልኮ እንደሚማር ሲገለጽለት ግን ይስማማል። ያኔ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴያትር (ዛሬ ብሔራዊ ቴያትር) ከተቋቋመ ገና ሶስት ዓመቱ ስለነበር የተማረ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ንጉሡ በሚገባ ተገንዝበው ነበር።

ተስፋዬ ከአሜሪካ ትምህርቱን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ በቴያትር አዘጋጅነትና በመድረክ አስተባባሪነት ተመድቦ መሥራት ጀመረ። የጸጋዬ ገ/መድኅንን “የእሾህ አክሊል” አዘጋጀ፣ ዋናውን ገፀባህሪ ወክሎም ተጫወተ። ቀጥሎ የመላኩ አሻግሬን “ዓለም፣ ጊዜና ገንዘብ” አዘጋጀ። ሆኖም ቴያትሩ አንዴ ብቻ ታዬና “ፖለቲካ አለበት” ተብሎ ታገደ። ተስፋዬም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ እስከምሽቱ አራት ሰዓት ከታገተ በኋላ በአማላጅ ተለቀቀ። ከዚያ “የሺ” የተሰኘውን የራሱን ተውኔትና፣ የመንግሥቱ ለማን “ጠልፎ በኪሴ” አዘጋጀ። አድናቆትም አገኘ።

በ1955 ዓ.ም. መጨረሻ ተስፋዬ በተዋናይነትና በረዳት አዘጋጅነት የተሳተፈበት የጸጋዬ ገ/መድኅን “ቴዎድሮስ” የእንግሊዝኛ ቴያትር ንጉሡ በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው የራስ መኮንን አዳራሽ ከታዬ በኋላ ቋሚ የሆነ የጥበብ ማዕከል እንደሚያስፈልግ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አመነበት። በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይም በዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን አማካይነት ቤተ ኪነጥበባት ወቴያትር (ዛሬ የባህል ማዕከል) ተቋቋመ። ተስፋዬም እዚያው ገባና እስከ 1960 ዓ.ም. ድረስ ፊት በምክትልነት ለጥቆ በዋና ዲሬክተርነት ሲሠራ ቆዬ። ማዕከሉ ታዋቂውን “ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ”ን በውስጡ ያቀፈ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የሥነጥበብ መድረክ ገናን ስም ያተረፉ እንደ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ደበበ እሸቱ፣ ተስፋዬ ለማ፣ አባተ መኩሪያ፣ ተፈሪ ብዙአየሁ፣ ወንድ ወሰን ገ/ኢየሱስ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ እስኩንድር ቦጎስያን፣ ሃይሌ ገሪማ፣ ዘሪሁን የትምጌታና የመሳሰሉት ታላላቅ ባለሙያዎች የየበኩላቸውን አስተዋፅዎ ያደረጉበትና ያደጉበትም ነው።

አቶ ተስፋዬ በቤተ ኪነጥበባት ወቴያትር ቆይታውም ሆነ በመደበኛዎቹ ቴያትር ቤቶች በርካታ ተውኔቶችን ጽፏል፣ አዘጋጅቷል፣ ተውኗል። ከነዚህም ውስጥ የመንግስቱ ለማዎቹ “ያላቻ ጋብቻ”፣ “ፀረ ኮሎኒያሊስት”፣ እና “ባለካባና ባለዳባ”፣ ከበደ ሚካኤል ከሼክስፒር የተረጎሙት “ሮሚዎና ዡልዬት”፣ የጸጋዬ ገ/መድኅን “ኦዳ ኦክ ኦራክል” (በእንግሊዝኛ)፣ የነጋሽ ገ/ማርያም ‘የድል አጥቢያ አርበኛ”፣ የታደለ ገ/ሕይወት “ማነው ኢትዮጵያዊው?”፣ የአቤ ጉበኛ “የደካሞች ወጥመድ”፣ ከእርሱ ሥራዎችም “አባትና ልጆች”፣ “ኡ ኡ”፣ “አስናቀችና ድስቷ”፣ “ቴያትር ሲዳዳ”፣ “ዕቃው”፣ “ፍርዱ ለናንተ” ሼርሼላፋም”፣ “ተሃድሶ”፣ “መንገደኞች”፣ “ሰኔና ሰኞ”፣ እና ከአንቶን ቼኾብ የተረጎመው “አጎት ቫንያ” ይገኙበታል። አቶ ተስፋዬ ከተጫወታቸው ገፀ ባህሪያት መካከል “ሐምሌት”፣ “ማርሻሎ ግራዚያኒ”፣ “ሚስተር ዤሮም” እና “አጎት ቫንያ” ይጠቀሳሉ። ከዚህ ባሻገር አቶ ተስፋዬ “መተከዣ” በሚል ርዕስ አጫጭር ልብ ወለዶችንና ግጥሞችን የያዘ መጽሐፍ በ1967 ዓ.ም. አሳትሟል። አቶ አስፋው ዳምጤ በዚሁ መጽሐፍ መቅድም ላይ (ገጽ 4) እንዳሰፈረው ተስፋዬ ግጥም መጻፍ የጀመረው የአሥራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት ሆኖ ነው። ከኦማር ኻያም “ሩብ አያት” ግጥሞች በተጨማሪ ሕይወት ታሪካዊ ልብወለዱን፣ እንዲሁም የዎልፍጋንግ ጎይተን “ፋውስት” ተርጉሞ አሳትሟል። የኔልሰን ማንዴላን የሕይወት ታሪክም በግሩም ሁኔታ ተርጉሞ ለኢትዮጵያ አንባቢያን አቅርቧል። የወጣቱ ቨርተር ሰቀቀኖች (ትርጉም)፣ ጥንወት፣ ጎሕ ሲቀድ፣ ሽልማቱ፣ ይሉኝታና ፍቅር፣ የመጨረሽታ መጀመርታና መደበሪያ የተሰኙ የግጥምና የልብወለድ ሥራዎችንም ለህትመት አብቅቷል። ከእሱ ሥራዎች ደግሞ ሁለት አጫጭር ልብወለዶቹና ስምንት ያህል ግጥሞቹ በሩሲያኛ ተተርጉመው ታትመዋል።

አቶ ተስፋዬ ቴያትርን ከመተወን፣ ከመጻፍና ከማዘጋጀት በተጨማሪ በአሕዝቦት (Popularize በማድረግ) ረገድም ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ለዚህም “የኪነጥበባት ጉዞ” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ራዲዮ የጀመረውና በኋላ “የኪነጥበባት ምሽት” ተብሎ ለረዥም ጊዜ የዘለቀው ሳምንታዊ ፕሮግራም ቅርብ ምሳሌ ነው።

አቶ ተስፋዬ በዘመነ ደርግም እሥራቷን ቀምሷታል። የተወሰኑ የቴያትር ድርሰቶቹም ሆኑ ዝግጅቶቹ ታግደውበታል። የእዚሁ ዕጣ ከደረሳቸው ሥራዎቹ አንዱ በሆነው “ዕቃው” የተሰኘ ተውኔቱ ውስጥ ከርቼሌ የተወረወረ ዋና ገፀባህሪው እንዲህ ሲል እናደምጠዋለን። መቼቱ ደቡብ አፍሪቃ እንደሆነ ይገለጽ እንጂ ለሃገራችን እውነታ ባዕድ ግን አይደለም።

…ይኸው … ቃሌን ስሰጥ አለሁ። አውጣ! ምኑን ነው እማወጣው? እኔ እንደሁ ከምንም ነገር የሌለሁ ነኝ። ማንን አምኜ፣ ማንን ልከዳ ነው? ሰው እንደሆነ ባፉ እንጂ በድርጊቱ ዓላማው ሁሉ ራሱን ለመጥቀም ነው። ነጩም ያው፤ ጥቁሩም ያው! ‘ከዝንጀሮ ቆንጆ የቱን ያማርጧል’ አሉ! ታዲያ ይኸን እንዴት ብዬ ላስረዳቸው? በግድ የአንዱ ክፍል ነህ፤ በግድ አዋቂ ነህ ነው የሚሉኝ። የአገር ፍቅርና የነፃነት ነበልባል በውስጥህ ይነዳል ይሉኛል። በኔ የሚነደው ሌላ! መቼ ከሩካቤ ንዳድ፣ ካንስታይ ፆታ ውቃቢ ተላቀቅሁና ነው፤ ለዚህ ለከፍተኛው ጥሪ፤ ለላቀው ግብ ሕይወቴን የምዳርግ? እሱን ይተውት። ሁሉ ነገር በቀረና ደህና ሚስት አግብቼ በተገላገልሁ። ይኸ ጭፈራና የትም አፌን መክፈት ነው እዚህ የከተተኝ። እኔ ስሚዝ ይግዛ ደንጎላ ምን ግድ አለኝ? … ይኸን ከሰማሁ ወዲህ … ይኸን ካየሁ ወዲህ {ግን} … መለወጤ አይቀርም! ወኔ አጥሮኝ፣ አሞቴ ፈሶብኝ ካልሆነ በቀር! … (ዕቃው፣ 1962 ዓ.ም. ገጽ 25)

እያለ ይቀጥላል። የለሁበትም ቢልም ህይወቱን ማትረፍ ግን አይችልም። እና ነፃነት በሌለበት ሃገር ከምንም ነፃ ነኝ ማለት እንደማይቻል ያሳየናል።

ጋሼ ተስፋዬ በግጥሞቹም ሆነ በተውኔታዊ ሥራዎቹ ስለ “ሕይወት” ምንነትና ትርጓሜ ጽፏል። እስኪ ከውጪ ከኦማር ኻያም ከመለሳቸው ግጥሞቹ አንዷን እንመልከት። አስቀድመን የእንግሊዝኛውን ቅጂ እናያለን፣

Into this Universe, and Why not knowing,
Nor Whence, like Water willy-nilly flowing:
And out of it, as Wind along the Waste,
I know not Whither, willy-nilly blowing.
What, without asking, hither hurried whence?
And, without asking, whither hurried hence!
Another and another Cup to drown
The Memory of this Impertinence!

ለጥቀን ደግሞ የአማርኛውን።

ድንገት ዱብ!
በዚች ክብ
ኩዋስ ዓለም!
ለምን ዱብ?
መልስ የለም!!
………
እኮ ከ…የት?
እኮ ወ…የት?
……….
እንዲያው ዝም
እንዲያው ዝም።
……….
እ-ህ-ስ?
እንዲያው ክምብል ክምብስ
እንደ ውሃ ፍስስ…
እንደ ንፋስ ንፍስ…
ስ…ስ…ስ…ስ…ስ
(ጠጅ አምጣ ይልቅስ!!)

እነዚህን መሰል ግጥሞቹን ወስደን ስንመለከትና ከመጀመሪያዎቹ የኦማር ኻያም ሥራዎች ጋር ስናስተያያቸው ጋሼ ተስፋዬ የራሱንም ፈጠራ አክሎ (Recreate አድርጎ) እንዳበለፀጋቸውና ኢትዮጵያዊ ለዛና ወዝ እንደሰጣቸው እንረዳለን።

ጋሽ ተስፋዬ በሃገር ፍቅርና በብሔራዊ ቴአትር በአስተዳዳሪነት ለረዥም ጊዜያት ከማገልገሉ በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴያትር ጥበባት ትምህርት ክፍልም ውስጥ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ሙያዊ አገልግሎቱን አበርክቷል። “የኢትዮጵያ ቴያትር ከመጀመሪያው እስከ ከበደ ሚካኤል” በሚል ርዕስ ከብዙ አሠርታት በፊት ያዘጋጀው ጥናትም ለቴያትር መስክ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች በር የከፈተ ነው ማለት ይቻላል።

ጋሼ ተስፋዬ ለመሰል የብዕር ሰዎችና የጥበብ ፍቅር ላላቸው ወጣቶችና ለጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ታዳሚዎች ምን መልዕክት እንዳለው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ጠይቆት ሲመልስ፦

“እኔ የምላቸው በቃ ነፍሳችሁን ተናገሩ ነው። እዚያ ዋሺንግተን ላላችሁት ብቻ አይደለም በላቸው። ካሊፎርኒያ፣ ሎስ አንጀለስ ወይም ቦስተን፣ ወዘተረፈ.. ናይጄሪያ፣ ሜልቦርን አውስትራሊያ በዓለም ላይ በየትም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነታችሁን አንፀባርቁ ነው የምላቸው! ኢትዮጵያዊነታችሁን አንድነታችሁን በቋንቋችሁ በባህላችሁ ተናገሩ! እና በተግባር ደግሞ አሳዩ፣ በቃላት ብቻ በቲዎሪ አትወሰኑ፤ ዘምሩ፣ ድርሰት ጻፉ፣ አሳትሙ። እና ደግሞ እዚህ ካለነው ጋር ተገናኙ፣ ተወያዩ፣ እና አንድ ላይ ሆነን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንራመድ፣ ቅርሳችንንና ሥልጣኔያችንን ለልጆቻችን እናስተላልፍ። የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከማንም አያንስም። ለዓለም ያበረከትነው አስተዋፅዎም ቀላል አይደለም” በማለት ከያኔያዊ ምክሩን አካፍሏል።

የጋሽ ተስፋዬ ሞት ቤተሰቦቹን፣ ወዳጆቹንና ተማሪዎቹን ያሳዝነን ያጉድልብን እንጂ እሱ እንደሁ እድሜውን ሙሉ ደስ ያለውን ሲያደርግ ኖሯልና፣ በሙያው ሃገሩንና ወገኑን በሚገባ አገልግሏልና ያጎደለው ነገር የለም። በረዥም ጊዜ አገልግሎቱም የጥበብ ቤተሰቦችን ፍቅርና አክብሮት ተቀዳጅቷል። በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል። ክብር ሞቱ ለሰማዕቱ!”

የተለያዩ ፎቶዎችን በተለይ ታሪካዊ የሆነ አንድ የቡድን ፎቶ አብሬ አያይዤላችኋለሁ። እዚያ ላይ ያሉትን ሰዎች ልግለጽላችሁ። ከፊት፣ ከግራ ወደቀኝ ቫርታኪስ ናልባንዲያን (የነርሲስ ናልባዲያን ልጅ)፣ ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ (በቴዎድሮስ ቴያትር እንደተራኪው ከተጫወተ በኋላ)፣ ጋሽ ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ ከኋላ፣ ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን (ቤተ ኪነጥበባት ወቴያትር -ዛሬ የባህል ማዕከል – ዳይሬክተር)፣ ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ጸጋዬ ደባልቄ፣ ፐሮፌሰር ሃሊም ኤል-ዳብ (ከዶ/ር ካፕላን ጋር የቤተ ኪነጥበባት ወቴያትር መሥራች)፣ እና ወ/ሮ ካፕላን ናቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top