የጉዞ ማስታወሻ

ገራገር በጠና ታሟል

666 መውረዱንና በአካል ማየታቸውን የነገሩንን ለማረጋገጥ በኢትዮጲያ ገጠሮች ለ4 ቀናት ቆይታ አደረግሁ። የተባበሩት አማራ በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ባሠናዳው የበርሃ አንበጣ ያደረሠውን የሰብል ውድመት የአሣሣቢቱን ደረጃ አውቆ መፍትሄ እንዲፈለግለት ለማድረግ የአርቲስቶችን እና የጋዜጠኞችን ቡድን ወደ አማራ ክልል ጥቅምት ስድስት ቀን ይዞ ተንቀሳቀሰ። ለጋዜጠኞች ወደተመደበው ኮስትር ገባሁ። በቲቪ መስኮት የማውቃቸውን ለየኋቸው። የኢሳቱ ጋዜጠኛ ጎበዜም አለ፣ በቀላሉ ይለያል። ጋዜጠኞችና አጋዥ ካሜራ ማኖቻቸው ካሜራ ማቀፊያዎቻቸውን ወንበር ውስጥ መሠተሩን ተያያዙት። ቀሪው ወይ እንደኔው ህትመት ላይ አልያም ሬድዮ ላይ የሚሰሩ ነበሩ። አዲስ አበባን ለቀን ብርዳማዋ ደብረ ብርሃን እስክንደርስ ወግ አልተጀመረም። ገፆቻችን ላይ ያረበበውን ድብታ ብቅ ያለችዋ ጀንበር እንኳ ልታነቃቃው አልቻለችም። መኪናዋ መንጫጫት የጀመረችው ደብረ ብርሃንን እንዳለፈች ነው። ድባቴውና መተፋፈሩ ቆሞ መጽሀፍ፣ ሙዚቃ፣ ፖለቲካ በየዘርፍ በየዘርፉ መነሣት ጀመረ። ይሄኔ ነው ሬድዮ ላይ ድምጻቸው የሚታወቁ ግን በመልክ የማይታወቁት መለየት የጀመሩት። ወጉ ደርቶ ሣቅ ፣ ጬኸት እና ሹክሹክታ በርክቶ ሰሜን ሸዋ ኤፍራታ ግድም ጃውሃ ቀበሌ ስንደርስ ቀዘቀዘ፡፡

ከመኪናዋ ወርደን ”ኣንበጣው አለ” ወደ ተባለበት ቦታ ማሽላ እና ስንዴውን እያቋረጥን ተጓዝን። አብዛኛው ተክል አንበጣ ተከምሮበታል። ከአስተባባሪው የተሰጠንን ፊሽካ እየነፋን ወደ ማሳው ገሠገሰን። ከገበሬዎቹ አንዱ ፈገግ ብሎ ”መፍትሄው ከአውሮፕላን የሚረጭ ኬሚካል እንጂ የያዛችሁት ፊሽካ አይደለም አንበጣው ከፊሽካው የሚወጣውን ድምፅ ለምዶታል” ብሎ ትግላችን ላይ ወኃ ቸለሠ። ጥቂት የረገፉ አንበጦች አይቼ ጠየቅኩ። የመንግስት አውሮፕላን የሚረጫቸው ኬሚካሎች ትንሽም ቢሆን አንበጦችን እንደገደለ እና ከመጡ 4 ቀን እንደሆናቸው ከገበሬዎቹ ተነገረኝ፡፡ ኦሮምኛና አማርኛ ተናጋሪ ህብረተሠብ ያለበት አካባቢ ሲሆን ከ10 – 15 ፐርሰንት የሠብል ምርት መወደሙን ከወረዳው አስተዳዳሪ ተነገረኝ። ከእይታችን በኋላ ለሌላ ጉዞ መኪናችን ዉስጥ ስንገባ አብዛኛው ተጓዥ ላይ ጠዋት የነበረው ድባቴ ተመለሠ። የከሰዐቱ ልዩነት ድባቴው ላይ ቁጭት መጨመሩ ነው። በረዥሙ የሚተነፍስ፣ ትካዜ የሚያበዛ እና ጭንቀት የሚያሳብቅ ፊት እንደተያዘ ጉዞአችንን ወደ ወሎ ኣደረግን። ምሽቱን ደሴ አድረን ለጠዎቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ ወሎ ጉብኝት ተሰናዳን።

ወሎ ኢትዮጲያ

እርቅ መንገዱ በወሎ በኩል ሳይሆን አይቀርም፤ የተለያዩ ብሄሮች ድልድይም ነች። አራት እና አምስት ቋንቋ የሚናገሩባቸው የገበያ አውዶች አሉ። ሁለት እና ሶስት ቋንቋ መናገር አዲስ ነገር አይደለም። ህብረ ቀለማት ከብሄር እስከ ሀይማኖት አለባት። ወጥነት በወሎ ነውር ነው። ቅልቅል ስልጣኔ ነው። በአንድ ቤተሰብ ሁለት ሀይማኖት ይኖራል። በቤቱ አንዋርና ራጉኤል ግንብ ያልታጠረባቸው፣ ወጥ ተለይቶ የማይቀመጥባቸው፣ አብይ ፆምና ረመዳን በጋራ የሚፆምባቸው አያሌ ቤቶች አሉ፡፡ “አለሀምዱሊላህ ታቦታችን መጣልን” የሚል ሙስሊም (ደሴ ገብርኤል) ለዚህ ምስክር ነው። መስኪድ ሲሰራ ገንዘብ የሚያዋጣ ቄስ ብርቅ አይደለም።

ሙሃባ፣ መርሀባ፣ ይውድስዋ እና ድርሳን በወሎ ማዕድ የማይገለሉ ውብ ጌጦች ናቸው። ኢትዮጲያ ያለ ወሎዬ አስቧት!! አንደበት ያለ ወሎዬ? አስቡት! ይህች ቦታ እነጥላሁን ግዛውን፣ ዋለልኝ መኮንንን፣ ልደቱ አያሌውን የመሠሉ ትንታግ አንደበት ያላቸውን ፖለቲከኞች አፍርታለች። ወሎ መሠረት ነው። ይህ መሰረት ነው የተናጋው። የሚያበሳጨው የነዚህ ውብ እሴቶች ባለቤት እህሉ ስለተበላ ነው። እንደተለመደው በጠዋት ተነስተን ወደ ደቡብ ወሎ አቅጣጫ ጉዞ ጀመርን። ጦሳን በቅርብ ርቀት እያየን ደሴን አለፍን። ሩጫ በሚመስል ፍጥነት መኪናዋ መገስገስ ጀመረች። ስለ ሠይጣን የሰማነው፣ ስለ ስድስት ስድሳ ስድስት ያደመጥነው እውነት እንዳይሆን ፀለይኩ። አባጣ ጎርባጣውን ኮስትሯ እየታገለች መንገዱን ተያያዝነው፡፡ የሚያማምሩ ተራሮችና የደረሡ ሰብሎች ለጥ ብለው አግድም በቁመታቸው ልክ የተከረከሙ የሚመስሉ ሳራማ ሜዳዎች እንኳ እምብዛም ድብርታችንን አልቀነሡትም።

ቅዳሜ ነውና ወረባቦን በተለይም ቦካክሳ እንደለመደባት አገኘናት። ሶስት ቋንቋዎች በየፈርጁ ሠማን። አማርኛው፣ ኦሮምኛው፣ አፋርኛው ተቀላጠፈ፡፡ ከሞላ ጎደል ሽርጥ የለበሡና ጊሌ የሸጎጡ ተገበያዮች ሠላምታ ሠጡ። ጥምዝምዝ መንገዱን ጨርሰን አካባቢውን ለማየት ወረድን። 140 ሺህ ሠው በሚኖርባት ወረዳ ሀምሳ አራት ሺህ ሠው የርሃብ አደጋ እንደተጋረጠበት ከወረዳው አመራር ሠማን። የወደሙ እህሎችን በአይን በብረቱ ተመለከትን። አርባ ሺህ ብር የሚያወጣውን በሬውን በአስራ ሶስት ሺህ ብር ሊሸጥ እንደሚችል ከጓደኛው የሰማው ገራገር እምባ እየተናነቀው አወጋን። ስንመለስ የጠበቀን ዳገት ከባድ ቢሆንም ተያያዝነው። ድንገት ዝምታችንን “ቀይ ባህር ላይ ጀምበር ስትወጣ” የመሠለች ወጣት እንስት ሠበረችው። እኛ ዳገት ስንወጣ እሷ ቁልቁለት ስትወርድ ያገኘናት ውብ ”ሸግዬ አያችሁን አይደል እንዴት እንደሆንን?” አለችን። የአዲስ ማለዳው መርሻ እምባ እምባ ሲለው ታዘብኩ። ማንም ሠው ምንም ማድረግ በማይችልበት ሁኔታ መልስ በዝምታ እንደሚሰጠዉ ከብዙ ንግግር አልባ እርምጃ በኋላ ለሌላ ጉዞ መኪናችን ዉስጥ ገባን።

ቆቦ ራያ

በማግስቱ ወደ ደቡብ ወሎ ሌላ ሰይጣን ማየት የጀመርነው ከተማው ላይ እንደደረስን ነው። ህጻናት በጠርሙስና ኮዳ ውስጥ ከተው ሲጫወቱበት አየን። ሠብል አወደመ ወደተባለው ወረዳ ከግማሽ ደቂቃ በኋላ ደረስን። እንደደረስን 666 ሠማዩ ላይ አንፏለለ። የአካባቢው ገራገር ጥይት ቢተኩስ፣ ቆርቆሮና ሀይላንድ ውስጥ ድንጋይ ከቶ ቢነቀንቅ፣ ክላክስ ቢነፋ፣ ጅራፍ ቢያጮህ ሰይጣኑን የሚነቀንቅ ጠፋ። ቆቦ እሰክንደርስ የወደመ እህል አየን እንጂ በቀጥታ እየወደመ አላየንም። ሳጥናኤል ጮቢ በር፣ አዩ፣ ሁብሎ፣ እና በንኒ መንደሮች ላይ በማን አህሎኝነት አንዣበበ። ጮቢ ከነውድመቷም አምራለች። በአራቱም አቅጣጫ ሠብል ይታያል። ራቅ ብሎ የቆሙ መነኩሲት አየሁ። ጠጋ ብዬ ሠላምታ አቀረብኩ፣ እንደ አብዛኛው ቤተሰብ ሠብላቸው ከወደሙባቸው አንዷ የሆኑት መነኩሴ ጥያቄዬን ስጨርስ በችግር ላይ ችግር ቢያመጣባቸውም እጄን ጎትተው ቁርስ እንድበላ ለመኑኝ። ለፋህ፣ በጣም ደከምክ ማለታቸው ነው። ስመለስ ማኪያቶ የምጠጣ፣ በድራፍት አረፋ የማገሳ፣ ከተማ ከተማ የምሸት፣ ስለገጠሬው ግድ የሌለኝ እኔን “ብላልኝ” ምን አይነት ቅድስና ነው? ስብዕና እስኪበቃን እኔም ባልደረቦቼም ተማርን። ሰይጣኑ እጅጉን አሳሳቢ ነው። እርግጥ በኬሚካል ረግፎ ተመልክቼዋለሁ፡፡ ሆኖም በቂ ሊሆን በጭራሽ አይችልም።

ሮቢት

አንዳንድ መፅሀፍት አሉ። በማይረሳ ታሪክ የታጨቁ፣ ውብ ትረካ የተቀመጠባቸው፣ ወደፊትን የሚያስመኙ አሉ፣ ነበሩ፣ ይኖራሉ። ከነዚህ መካከል “የአሲምባ ፍቅር” የተሰኘው የካህሳይ መፅሀፍ አንዱ ሲሆን ሮቢት ከተማ ስደርስ መጽሐፉን እንዳስታውስ ተገድጄ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው።

ካህሣይ በኢህአፓ ተመልምሎ የኢህአሠ ሠራዊት አባል ሆነ። አሲምባ የነበረው ሠራዊት ለተልእኮ ወልደያ መጥቶ ተልእኮውን ጨርሶ ሠኔ 27 1968 ዓ.ም ሲመለስ ውድዬ የምትባል ቦታ እረፍት አድርገው ወደ ቆላ በመውረድ ጉራ ወርቄ ሲደርሱ በመንግስት የታጠቀ የገበሬ ጦር ደረሰባቸው። ሁሉም ለማለት በሚቻል ሁኔታ ሲማረኩ 3ቱ ተገደሉ። የደርግ ነጭ ለባሾችና ወታደሮች ነገሩን ለማጣራት መጥተው 20 የኢህአሠ አባላትን በቁጥጥር ስር አድርገው ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው። የተላኩት በሙሉ መገደላቸው በብዙሀን መገናኛ ሲሰማ አንድ ከሞት የተረፈ ሠው ግን ነበረ። ካህሳይ።

በጦርነቱ ወቅት ጉራ ወርቄ ላይ ካህሣይን ይመር ንጉሴ የተባለ ሠው ማርኮት በደርግ ሠላዩች ከመታየት እና ከሞት መልዕአ መናኸሪያ ድረስ ደብቆ ወደ መጣበት አሲምባ ይልከዋል። ካህሳይ ከአሲምባ በኋላ ወደ አሜሪካ አቅንቶ በፋርማሲ ሙያ ጥሩ ደረጃ የደረሰ ቢሆንም ከሞት ያተረፈውን ያን የሮቢት ገራገር ከአእምሮው ሊያወጣ አልቻለም።

ከሠላሳ አመት በኋላ ሮቢት ሲደርስ የሠማው ነገር የጠበቀውን አልነበረም። ጋሽ ይመር ንጉሤ አርፈዋል። ወደ ውድዬ ከተማ ገብቶ አንድ የከተማው ሠው ልጁን አገናኘው። ስለ አባቷ ሲነግራት አለቀሰች። እናቷ እሷን እርጉዝ ሆና እንደሞተባትም ጭምር ነገራት። በህይወት እንዲኖር ከፈቀዱለት አንዷ እናቷ ስለነበረች በህይወት ትኖር እንደሆነ ጠየቃት። ”አለች ግን ያላቸዉ ሩቅ ነው፤ በስልክ አገናኘሀለው” አለችው። በማግስቱ ተገናኙ። ታስታውሰው እንደነበር ጠየቃት። እያለቀሰች ” ’ይመር ንጉሤ የት ደርሶ ይሆን? እምን ደርሶ ይሆን? መንገድ ላይ ቀርቶ ይሆን?’ እያለ ይጠይቅ ነበር። ስላንተ ሁልጊዜ ያስብ ነበር። ወይኔ!! በህይወት ኖሮ ቢሆን እንዴት ደስ ባለው ነበር” አለችው። ሮቢት ጠጅ አለ ተብሎ ወረድን። ገሚሱ ወደ ቡናው ገሚሱ ለቤተሰቡ ማርና ጠጅ ይይዛል። ሮቢትን በካህሳይ መጽሐፍ በኩል አፈጠጥኩባት፣ ሞባይሌን አውጥቼ ጥቂት ፎቶ አስቀረሁ። ገራገር የሞላባት ሮቢት ድምቀት ላይ ነች።

ውድዬና ወርቂቶ ማርያምን ሄጄ ባያቸው ብዬ ተመኘሁ። በተለይ የጋሽ ይመርን ልጅ። ግን ህይወት አላስደረገኝም። የዚህ ውብ ታሪክ ህዝብ ግን አንበጣ ሊያረብበት መሆኑ ያስደነግጣል።

ውብ እንስት

መንደሮቹን ወደ ኋላ ትተን ወደ ቆቦ ከተማ መመለስ ጀምረናል። ተደጋጋሚው ጉዞአችንን ውሃ እየጠጣን፣ ቆሎ እየቆርጠምንና ብርቱካን እየተመገብን ልናለሣልሠው እየጣርን ድንገት ውበት ብቅ አለች። ፍዘቱን የሚነቀንቅ ቁንጅና። ወጣትን ወይ ውበት ያሳድደዋል፣ ወይ ውበትን ወጣት ያሳደው ባላውቅም በልቤ ላደንቅኳት እንስት ካሜራ ማኖቹ ሌንሳቸው ዉስጥ “ቀጭ ቀጭ” አድርገው አስቀሯት። ከጎኔ ተቀምጦ የነበረው የኢትዮ ኤፍኤሙ ሄኖክ “በውበቷ የምትታበይ ገርል ፍሬንድህን ወሎ አምጣት ከሴቶች መካከል እንደ አንዷ እንጂ ብቸኛ አይደለሁም ትልሀለች” አለኝ፡፡ ፈገግ አልኩ። ጥቂት ቆይቶ መኪናው ውስጥ ሬድዮ ተከፈተ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገር ጀመሩ። ችግሩን በጣም አቅልለው መናገራቸው አስከፋኝ። የገራገርን ህመም በአይኔ በብረቱ ላየሁ ለእኔ ንግግራቸው አፅናኝ አልነበረም። በቂ ትኩረት ሊሰጠው ግን ያሻል እላለሁ። ጉዟአችን ተገባዶ ወደ አዲስ በምንመለስበት የመጨረሻው ቀን አንበጣው ሸዋ ሮቢት ላይ ያሳየው ወታደራዊ ትርዒት መሳይ ትዕይንት የነገሩን በፍጥነት መስፋፋት ያሳያል። ትኩረት ለገበሬው! ትኩረት ለገራገር!

የሠው ኣንበጣ ለገራገር

የኢትዮጲያ አርሶ አደር እንደ አሰጣጡ ተቀብሎ አያውቅም፣ ሲነገድበት በስሙ ሲሸቀልበት እናውቃለን፣ የገዛ ልጆቹ እርሱ በከፈለው ግብር ተምረው እንኳን የውሃ ጉድጓድ ሊቆፍሩለት የተወለዱባትን ትንሽዬ ከተማ ለመጥራት እንኳ ይቀፋቸዋል፤ እንኳን ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ሊያሳዩት ወደ ኋላ መቅረቱ ላይ ሲሳለቁ እውቀት ይመስላቸዋል። አሁን አሁን ደግሞ ከተፈጥሯዊ አንበጣ ይልቅ የሠው አንበጣ ገራገርን በየገጠሩ እየገደለ ነው። አብሮ ሲኖር ዘመናትን በፍቅር ችግሮችን እንዳልተካፈለ ዛሬ ዛሬ ሜንጫና ገጀራውን እየሳለ ጠበንጃውን እየወለወለ አውሬ ወደ ንፁህ ልብ አነጣጥሮ ይተኩሳል። ሠሞኑን ከወደ ምዕራብ ወለጋ ግምቢ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የተሠማው የንፁሀን ፍጅት ከላይ የተናገርነውን የሚያጠናክር ነው፡፡

ማህበራዊ ሚድያው ከሀገር ውስጥ እስከ ዳያስፖራው ይህንን ቅን አሳቢ ሸውራራ እይታውን ገበሬው ላይ እየጫነ እነሆ ደግሞ ሌላ ዙር ገበሬውን ወደ ፍም እሳት የመጨመር ዘመቻ እየተቀጣጠለ ነው። አብርሀም ወልዴ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ለምን ባላገሩ እንደተባለ ሲጠየቅ ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የመኪና አደጋ ደርሶበት በፍቅር ተቀብሎ ፣ አስታምሞ እና አብልቶ ያስታመማቸውን ገብሬ ለማስታወስ ባላገሩ የሚል ስም እንዳወጣለት ተናገረ። የኢትዮጲያ አየር መንገድ የካቻምናውን አደጋ ተከትሎ የቢሾፍቱ አካባቢ እናቶችና ህዝብ ከማናችንም በላይ ሀዘኑን ሲገልፅ አልነበረም? ይህን ገራገር ለምን ይገድሉታል? ለምንስ ጭንቁን አበዛንበት? ምርቱን ለማስወደድ ስለደበቀብን ይሆን? በእንግድነት ስንሄድ በራፉን ስለጠረቀመብን ይሆን? እውነትና ፍቅር በልባችን ዉስጥ ሞቶ ስለ ተቀበረብን ይሆን ገራገርን ወደ እሳት ለመጣድ መጣደፋችን? የደራው ጨዋታ ፕሮግራም ፋና ሬድዮ ላይ አስታውሳለሁ ከአዘጋጆቹ አንዷ አዜብ ወርቁ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጊዜ በከተሞች “የጅብ ቁጥር በዛ የሠው ቁጥር አነሠ “ ስላላት ከሩዋንዳ የመጣ ሠው ኣንስታ ጅቦቹ የሠውን ቁጥር ማነስ አይተው ሠው እስኪደራጅ በከተሞች ብቻውን የሚሄድን ያጠቁ ነበር። ታላቅ ትምህርት ይመስለኛል። በስብዕና ካልተደራጀን ጅቦች እንኳን ያጠቁናል። ስጋታችን በላዔ ተክል ብቻ አይደለም ፣ በላዔ ሠብዕም ጭምር ነው። የሀገሬ መንግስት ሆይ እባክህን ገራገርን ከጥቃት ጠብቅ!! የሠው ኣንበጣ ለገራገር።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top