በላ ልበልሃ

የአንበጣ መንጋ ወረራ ተፈጥሮያዊ ክስተት ወይስ መለኮታዊ ቅጣት

መግቢያ

የአንበጣ ወረራ ስጋት በሰው ልጅ ታሪክ ከፍተኛ ቦታ እንደነበረው የሚያመለክቱ ቅርሶች አሉ፡፡ ዋናዎቹ የጥንት ዘመን ግብፃውያን በመቃብር ድንጋዎች ላይ የቀረጽዋቸው የአንበጣ ምስሎች ሲሆን፣ ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት በፊት 2470 አስከ 2220 ዓ.ዓ. ነበር፡፡ በአንበጣ መንጋ መንስዔ የተከሰቱ የረሃብ ዘመናት በተለያዩ ሃይማኖቶች ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ሃይማኖቶች ቅዱሳን መጻሕፍት (መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱስ ቁራን፣ “ማሃብሃርታ- Mahabharata”፣ “ኢልያድ- Iliad”) ፣ የአንበጣ መንጋ ወረራዎች፣ በመለኮታዊ ቅጣት መልክ ተሰንደዋል፡፡ እንደቅጣት መወሰዳቸውን የሚያረጋግጥ አንድ ማስረጃ እነሆ፡፡

ለምሳሌ፡- በኦሪት ዘፀአት 10: 1-20 የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ እኔን ማፈርን አስከ መቼ እምቢ ትላለህ? ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፣ አምቢ ብትል ግን እነሆ፣ ነገ በዚህ ጊዜ በተራራዎች ሁሉ ላይ አንበጣ አመጣለሁ፤ የምድርን ፊት ይሸፍናል፣ ምድርንም ለማየት አይቻልም፣ ከበረዶም ተርፎ በምድር ላይ የቀረላችሁን ትርፍ ሁሉ ይበላል፣ ቤቶችህም የሹሞችህም ቤቶች የግብፃውያን ሁሉ ቤቶች በእርሱ ይሞላሉ፣ አባቶችህ የአባትህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደርሱ ያለ ያላዩት ነው ሌሎች ከአደጋ ጋር የተዛማዱ መለኮታዊ መዓቶች በመጽሐፈ ኢዮብ (1:10)፣ በትንቢተ-ኢሳያስ (13:13)፣ በትንቢተ-ሕዝቅኤል (20:47)፣ ኦሪት ዘሌዋውያን (20:19-20) ተጠቅሰዋል፡፡

በመሠረቱ የሰው ልጅ ከኹነቶች ሁሉ በስተጀርባ ያለውን ምክንያት ለማወቅ ይሻል፣ ይመኛል፣ ለመገንዘብ ይሞክራል፡፡ ሆኖም ለአንዳንድ ድንገተኛ ኹነቶች፣ ምክንያት ለማወቅ ስለሚያዳግተው፣ እንደ መለኮታዊ ተግባራት አድርጎ ይረዳቸዋል፡፡ የሰው ልጅ ፍጹም ስላልሆነ እና አምላካዊ ትዕዛዞችን ሙሉ በሙሉ ፈጽሜያለሁ ብሎ ስለማያምን፣ ብሎም ራሱን እንደ ኃጢያተኛ ስለሚፈርጅ፣ ድንገታዊ ኹነቶች ባደረገው ጥፋት ምክንያት እንደደረሱ፣ እንደ መለኮታዊ ቅጣት አድርጎ ይወስዳቸዋል፡፡ እነኚህን ዓይነት ኹነቶችም የመሬት መንቀጥቀጥን፣ እሳተ ገሞራን፣ ጎርፍን፣ ወዘተ… ያካትታሉ፡፡

ጎርፍን እንደ ምሳሌ ወስደን፣ እንዴት እንደሚከሰት በሳይንሳዊ አስተሳሰብ ለማብራራት አንሞክር፡፡ ጎርፍ በከባድ ዝናብ መንስዔ፣ ከነባራዊ ሁኔታ በጣም በላቀ መልክ ዝናብ ሲዘንብ፣ አፈሩ ተጨማሪ ውሃ ስለማይመጥ፣ ነባራዊ የውሃ መንገዶችም (የጅረት፣ ወንዝ፣ ቦይ፣ ወዘተ) በውሃው መጠነ-ብዙነት ምክንያት በተለመደው መንገድ ማስተናገድ ሲሳናቸው፣ ውሃ ከወንዝ፣ ከቦይ …ወ.ዘ.ተ… ውጭ መፍሰስ ይጀምራል። በእንደዚያ ባለ ሁኔታ ነው ከባድ ጎርፍ የሚከሰተው፡፡

ሆኖም ለምን ዝናብ ከበፊቱ በላቀ መጠን ዘነበ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በቅርብ ርቀት ካለ ውቅያኖስ ውሃ ሙቀት ከፍ ስላለ፣ ብዙ ውሃ ተንኖ፣ የተነነው እንፋሎት ደመና ሆኖ፣ ደመናው በነፋስ ወደ የብስ ተገፍቶ ነው የከፍተኛ ዝናብ መንስዔ ለመሆን የበቃ ይሆናል መልሱ፡፡ “የውቅያኖሱ ውሃ ለምን በከፍተኛ መጠን (ከበፊቱ በላቀ መጠን) ሞቀ?” ተብሎ ቢጠየቅ፣ መልሱ ከፀሐይ ወደ ምድር የሚደረሰው ሙቀት አመንጭ ጨረር፣ በከፊል ተመልሶ ወደ ሕዋ እናደይንፀባረቅ፣ የካረቦን ዳይኦከሳይድ (Carbon dioxide) መጋረጃ ስለገታውና፣ ሙቀቱ ምድር ላይ ከበፊቱ በላቀ መጠን ታምቆ ስለቀረ ነው ለምን? ተብሎ ቢጠየቅ የሰው ልጅ ለኃይል ማመንጫነት የሚጠቀምባቸው ግብአቶች (የድንጋይ ከሰል፣ ፈሳሽ ነዳጅ)፣ ኃይል ሲያመነጩ የሚተፉት ጋዝ ካረቦን ዳይኦከሳይድ” (Carbon dioxide) በአየር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ካርቦን ዳይኦክሳይድመጠን ስለሚጨመር ነው፡፡ እንዲሁም ሌሎችም ሰበነክ የሆኑ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ምድርን ለሙቀት የሚዳርጉ ሂደቶች አሉ ይሆናል መልሱ፡፡ ጥያቄው ሊቀጥል ይችላል፡፡

ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ እይታዎች፣ ሁሉም የተፈጥሮ ኹነቶች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንደተገለጠው፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ጠለላ ስር ስለሚገኙ (ያም ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትንና የእነዚህ ግዙፍ አካላት እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ያካትታል) ከመለኮታዊ ዕውቅና ውጭ ኹነቶች አይከሰቱም ይላሉ፡፡

ሳይንስ ግን ገና ያላከበታቸው፣ ለመልስ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎች፣ እንዳሉ ይረዳል። ብሎም፣ ዕውቀት ለማዳበር ይጥራል። የኹነቶች ገላጭ የሆኑ ምክንያቶችን ለመረዳት ይጥራል። ያም በጥናት፣ በምርምር የሚገኙ መረጃዎችን ነው በዋና ግብዓትነት በሂደቱ የሚጠቀም፡፡ ቀስ በቀስ ሳይንስ በምርምር ላይ ተመሥርቶ የሰው ልጅ የዕውቀት አድማስ እያሰፋ ይሄዳል። ስለሆነም ነው ሳይንስ ሁልጊዜም ለአዲስ ዕውቀት ክፍተት የሚተው፣ ፍፁም ድምዳሜ ላይ የማይደርስ፡፡

በምርምር ውጤት ላይ ተመሥርቶ ሳይንስ ያ ስለሆነ፣ ይህ ተከሰተ ብሎ አይደመድምም። ውጤቱን እና ምክንያት ነው ተብሎ የተገመተውን ግንኙነት መርምሮ፣ “ይህ ክስተት በአጋጣሚ ለመከሰት ያለው ሁኔታ”፣ ለምሳሌ “ከመቶ አምስት ነው (5%)”፣ ወይም “ከመቶ አንድ (1%) ነው” የሚል፡፡ በአጋጣሚ የመከሰቱ ሁኔታ እየመነመነ ሲሄድ፣ የኩነቱ እና የምክንያቱ ግንኙነት አየጠነከረ ይሄዳል፡፡ በተለምዶ ግንኙነት በአጋጣሚ ሊሆን የሚችለው “ከመቶ አምስት (5%)” ብቻ ከሆነ፣ ኹነት እና የተጠረጠረው ምክንያት ግንኙነት እንዳለቸው መውሰድ ተቀባይነት አለው፡፡ ሳይንስ ብዙ ጥያቄዎችን ያነሳል። ያስተናግዳል። ለጥያቄዎችም መልስን ይሻል። እምነት ጥያቄዎችን ስለማያስተናጋድ፣ በሁለቱ መሃል፣ ማለትም በሳይንሳዊ አስተሳሳብ እና በእምነት ያለው ልዩነት መሠረቱ ይኽ ጉዳይ ነው፡፡

ሰሞኑን ከ2012 ዓም መቋጭ አካባቢ ጀምሮ እሰከ 2013 የቀጠለ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች (ከትግራይ አንስቶ፣ በምሥራቅ አቅጣጫ እስከ ደቡብ ጫፍ) በአንበጣ መንጋ ተወርሮ ነበር፡፡ ብዙ የማህበረሰቡ አባላት ይህን ዓይነት ክስተት የሚገነዘቡበትን ሁኔታ በመፈተሽ፣ ሳይንስ ለማኸዘብ ይቻል ይሆናል በሚል እሳቤ ነው፣ ጽሑፉን ለማዘጋጀት የወሰንኩ፡፡ የአንበጣ መንጋን መከሰት አጋጣሚ ተጠቅሞ፣ ማለት በተጨባጭ ሁኔታ ላይ መሥርቶ፣ የአንበጣ መንጋ ሥነ-ሕይወታዊ ሂደት፣ ብሎም በሰብል ላይ የሚያደርሰውን ውድመት፣ በሳይንሳዊ መንገድ መተንተኑ፣ የሳይንሳዊ አስተሳሰብን ባህል ለማዳበር ያመቻል፡፡ የአንበጣ መንጋ ድንገተኛ ደራሽ መሆን፣ ከብዛቱ ጋር ተዛምዶ፣ እንደ መለኮታዊ ቅጣት እንዲታይ ምክንያት መሆኑ የአንበጣ መንጋ በተመሳሳይ ወቅት ብዙ አካባቢዎችን ሲያጠቃ፣ በአካባቢው መዓት ወረደ ይባላል፡፡

ለእነኝህ ዓይነት ክስተቶች፣ የተለያዩ ምክንያቶችን የሚሰጡ አልጠፉም፡፡ አምላክ ክስተቶች ከመድረሳቸው በፊት ስለሚያውቅ (የአምላክ ዕውቀት በጊዜ የተወሰነ ስላልሆነ)፣ ቅጣቶቹን ከጊዜያዊ የሰው ልጆች ጥፋቶች ጋር ማዛመድ ይቸግራል ይላሉ፡፡ እንዲሁም ጥፋት እንዲከሰት ለምን አምላክ ከመጀመሪያው ፈቀደ ይላሉ፡፡ ለእነኝህ ዓይነት ትችቶች፣ በሃይማኖት አባቶች የሚሰጣቸው መልስ፣ አምላክ ኃጥያት መተግበርን ባይከለክልም፣ የእሱ ፈቃድ አይደለም ይላሉ፡፡

በተጨማሪ ይኽን ዓይነት እይታ አወዛጋቢ የሚያደርገው፣ አጥፊዎች አዋቂዎች ሆነው ሳለ፣ እንዴት ሕፃናት አበረው ይቀጣሉ፣ እንስሳትስ ለምን ይወድማሉ? መሰል ጥያቄዎችን ማስነሳቱ ነው፡፡ እንዲሁም እንደዚህ ያሉ ክስተቶች፣ ኹነቶች፣ የአምላክን ሩህሩህነት አያመላክቱም፣ ስለሆነም የመለኮታዊ ኃይል መገለጫ ሆነው መወሰድ የለባቸውም የሚሉም አልጠፉም፡፡

የምድረ በዳ አንበጣ ሥነ-ሕይወታዊ ግንዛቤ

በሕይወት ትግል፣ ህልውና ገላጭ የሆኑ ተግባራት ሁሉ በዘር መተካት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ የአንበጣ መራባትም፣ ብሎም መንጋ መሥርቶ፣ በሰው ልጅ አዝመራ፣ በከብቶች መኖ ላይ ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትል፣ የህላዊ ግዴታ ሆኖበት ነው፡፡

እኛ በጥቅሉ አንበጣ ብለን የምናውቀዉ “የሦስት አፅቄዎች” (Insects)፣ የተለያዩ ሃያ ሰባት የእንበጣ ብቸኛ ዝረያዎችን (Species) ዝርያዎችን ያካተተ ነው፡፡ እነኝህም ዝርያዎች በዓለማችን የተለያዩ አካባቢዎች (ከሰሜን ጫፍ አሜሪካ እና ከምድር ዋልታዎች አካባቢዎች በስተቀር) ተሰራጭተዋል፡፡ ሆኖም በዘመናችን ከባድ ጥፋት የሚያስከትሉት ብቸኛ ዝርያዎች ጥቂት ናቸው፣ ከአነሱም አንዱ፣ “የምድረ በዳ አንበጣ” (Desert Locust)፣ ሳይንሳዊ ስያሜው ሽስቶሴርካ ግሪጋርያ (Scistocerca gregaria) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ይኸ የአንበጣ ብቸኛ ዝርያ ከመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ አስከ ሩቅ ምሥራቅ፣ እና በአፍሪካ (በተለይ በሰሜን አፍሪካ እና በክፈለ-ዓለሙ ወገብ አካባቢ፣ ከምሥራቅ አስከ ምዕራብ፣ የሚገኙ አገሮች) ዝርያው መንጋ መሥርቶ ከፍተኛ የሰብል ውድምት ያስከትላል፡፡ በኢትዮጵያም ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰው ይኸው ዝርያ ነው፡፡ ይህ የአንበጣ “ብቸኛ ዝርያ” ከፍ ያለ ርቀት የመጓዝ አቅም የተጎናፀፈ ስለሆነ፣ በተመሳሳይ ወቅት ከምሥራቅ አፍሪካ ጫፍ እስከ ምዕራብ ዳርቻ ድረስ ያሉ አገሮችን ደጋግሞ ያጠቃባቸው ዘመናት ተመዝግበዋል፡፡

በሚያስከትለው ጥፋት ተመሥርቶ፣ በሁለተኛ ደረጃ የሚመደበው “ስደተኛው አንበጣ” (Migratory Locust) በመባል የሚታወቀው ሳይንሳዊ ስያሜው “ሎከስታ ማይግራቶሪያ” ( Locusta migratoria) የሚባለው ነው፡፡ ይኸም “ብቸኛ ዝርያ” ዝርያ ሰፊ አካባቢዎችን (አፍሪካን፣ እስያን፣ እንዲሁም አውስትራሊያን እና ኒውዚላንድን ያጠቃልላል) ያጠቃል፡፡ ምንም ይኸ የአንበጣ “ብቸኛ ዝርያ” የሚያጠቃው አካባቢ ከምድረ-በዳ አንበጣ ጋር ሲነፃፀር የላቀ ቢሆንም፣ የሚያደርሰው ጉዳት ግን ከምድረ በዳ አንበጣ ከሚያደርሰው ጉዳት ዝቅ ይላል፡፡

“ሽስቶሴርካ ግሪጋርያ” ከሌሎች የአንበጣ ዝርያዎች በላቀ መጠን ጥናቶች ተካሂደውበታል። ስለሆነም ሰፊ ዕውቀትም ተካብቶበታል፡፡ እንስት የምድረ-በዳ አንበጣ እንቁላል የምትጥል፣ ምደረ-በዳ ውስጥ ቢሆንም፣ እርጥበት በተጎናፀፈ አሸዋ እንዲሁም አፈር ውስጥ ነው፡፡ በከባድ ዝናብ መንስዔ የምደረ በዳ አካባቢ፣ በተለይ አንዳንዴ ከባድ ዝናብ ሲጥል፣ በአሸዋ የተከበቡ ኩሪዎች ይፈጠራሉ፡፡ በእነኝህ ኩሬዎች ተፅእኖ፣ አካባቢው እርጥብ ይሆናል፡፡ እንዲዚህ ያሉ አካባቢዎች ናቸው ለአንበጣ መራባት አመች የሚሆኑት፡፡

እንስት የምድረ-በዳ አንበጣ፣ በከረጢት አያሸገች (ቁጥራቸው ከሰማንያ እሰከ መቶ የሚዘልቅ እንቁላሎች) በድምሩ (በአማኻኝ) አንድ ሺ እንቁላሎችን ትጥላለች፡፡ የምድረ-በዳ አንበጣ ብቸኛ ዝርያ እንስቶች እንቁላል በቡድን (በአንድ አካባቢ) ነው የሚጥሉ፡፡ ስለሆነም አካባቢው የአንበጣ ማርቢያ መሰል ይሆናል፡፡ አንቁላል በሚጣልባቸው አካባቢዎች በየካሬ ሜተሩ እስከ አንድ ሺ አንቁላሎች ይገኛሉ፡፡

እንቁሎች ሲፈለፈሉ የመብረር አቅም ገና ያለተጎናፀፉ ኩብኩባዎች (Nymph) ነው የሚሆኑ፣ ኩብኩባዎች ከቦታ ቦታ በዝላይ መሰል ስልት ነው የሚንቀሳቀሱ፡፡ በዝናብ መንስዔ አካባቢውን የሸፈነውን ቅጠላ ቅጠል እየተመገቡ ክብኩባዎች ያድጋሉ፣ እደገታቸውም ደረጃ በደረጃ የተከፈለ ነው፣ በአማካኝ አምስት ደረጃዎችን ያካትታል፡፡ ከአንድ ደረጃ ወደ ከፍተኛው ደረጃ እድገት ሲጎናፀፉ፣ ኩብኩባዎች ነባሩን፣ የጠበባቸውን ልባስ ከልተው፣ አዲስ ይላበሳሉ፡፡ በልባስ ቅያሬ መሃል በእድገት የሚገኙት ግልፍ (Instars) ይባላሉ። ጠቅለል ባለ መልኩ፣ በሁሉም ደረጃ የሚገኙት ኩብኩባ በመባል ነው የሚታወቁት፡፡

ሁኔታው አመች ከሆነ፣ ከሁለት አስከ አራት ሳምንት ባለ ጊዜ ኩብኩባዎች እድገታቸውን አጠናቅቀው “ጉልምሶች” (Adults) ይሆናሉ፡፡ የኩብኩባዎች የእድገት ፍጥነት ከምግብ አቅርቦት ጋር የተቆራኘ ነው። ምግብ በሽ በሽ ሲሆን፣ እደገታቸው ይፋጠናል። በተቃራኒው፣ ምግብ ውስን ሲሆን የእድገታቸው ሂደት ይኮስሳል፡፡ የሕይወት ዑደቱም አንቁላል፣ ኩብኩባ፣ እና ጉልምስን ሲያካትት፣ ሂደቱ በጠቅላላ የሚጠናቀቅበት ከአንድ ወር አስከ ሦስት ወራት ሊዋዥቅ ይችላል፡፡ አንድ የምድረ በዳ አንበጣ ከሦስት አስከ አምስት ወራት የሚዘልቅ ዕድሜ አለው፡፡ የሚራባበት አካባቢ ምቹ ከሆነ፣ በወራት ውስጥ የመንጋዎች አባላት ቁጥር በሃያ እጅ ሊንር ይችላል፣ ያም ማለት ውስን መንጋ የገነባ፣ ለምሳሌ ሁለት ሚሊዮን አንበጣዎች ብቻ ያካተተ፣ በወራት አርባ ሚሊዮን ያቀፈ መንጋ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በአንድ አካባቢ የተጣሉ እንቁላሎች፣ በተመሳሳይ ወቅት ሲፈለፈሉ፣ እድገታቸውን አጠናቀው ጉልምስ ሲሆኑ የጉልምሶች ተጠጋገቶ መኖር አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ (መጠጋጋት)፣ አንድ አንበጣ ከሌላ አንበጣ ጋር በተደጋጋሚ መነካካትን ያስከትላል፡፡ ይህም ሁኔታ፣ በተለይ በኋላ እግሮች መነካካት፣ “ፌሮሞን”(Pheromone) ማመንጨትን ያስከትላል። ያም “ሴሮቶኒን” (Serotonin) የሚባል “ፌሮሞን” በአንበጣ ገላ ውስጥ አንዲዘጋጅ እና ወደ ውጭ እንዲረጭ ማደረግን ያስከትላል፡፡ “ሴሮቶኒን” በመዓዛ (ሽታ) የሚያስከትለው ተፅኖዕ ላይ፣ እይታ (በማየት) ታክሎበት፣ ጉልምሶች የባህርይ ለውጥ ያደርጋሉ፡፡ ያም ገለልለተኛ የነበሩ በመንጋ መልክ መደራጀት ነው (በተመሳሳይ “ፌሮሞን” ነው፣ የንብ መንጋ የሚገነባ እና በሥርዓት የሚተዳደር)፡፡ አንበጣ ነጠላ፣ ገለልተኛ፣ ሆኖ (መንጋ ሳይመሰርት) ሊኖር ይችላል፡፡ መንጋ ምሥረታውን የሚቀሰቅሰው፣ ከላይ እንደተጠቀሰው የቁጥር ብዛት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የባህርይ ለውጥ እንዲከሰት ተፅእኖ የሚየደርገው ኬሚካላዊ ውህድ “ፌሮሞን”፣ እንደ ሽቶ በአካባቢው የሚተን፣ ለሦስት አፅቄዎች እንደ መረጃ ማሰራጫ የሚያገለግል ኬሚካላዊ ውህድ ነው፡፡

ሴሮቶኒን ከመንጋ መመሥረት ተፅእኖ በተጨማሪ ሌሎች ተፅእኖዎችን ያስከትላል። ዋናው የገላ ቀለም ቅያሬ ነው። ቢጫቀመስ አረንጓዴ የነበረው ገለልተኛ አንበጣ ወደ ጥቁርአዘል ደማቅ ቢጫነት ይቀየራል፡፡ በተጨማሪ የጉልምሶች የምግብ ፍላጎት በጣም ይንራል። በየቀኑ የራሳቸውን ክብደት መጠን ያህል ምግብ መመገብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም በአካባቢዉ ያለውን ቅጠላ ቅጠል በአጭር ጊዜ ያወድመዋል፣ ከዚያም ጉልምሶች ለምግብ ፍለጋ በመንጋ ሥርዓት ተደራጅተው ለስደት ይዳረጋሉ፡፡

በስደት (በዘመቻ) ላይ አመች ቦታ ከተገኘ፣ እንስት አንበጣዎች እንቁልላል ይጥላሉ፣ እንቁላሎችም በሂደት የአንበጣ መንጋ ይመሠርታሉ። ብሎም ተጨማሪ የአንበጣ መንጋዎች ያንሰራራሉ፡፡ በስደት ላይ የተሰማራ የአንበጣ መንጋ፣ በቀን 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ሊጓዝ ይችላል፡፡ ግዙፍ የሆነ የአንበጣ መንጋ በበረራ አስከ ሺ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ካሬ (1,200 ኪሜካ) ሊሸፍን ይችላል፣ በየኪሎ ሜትር ካሬውም፣ ከ “አርባ ሚሊዮን”(40,000,000) እስከ “ሰማኒያ ሚለዮን” (80,000,000) የሚሆኑ አንበጣዎች ይካተታሉ፡፡ ስለሆነም፣ መንጋው ደመና መስሎ፣ ከባድ ደመና አክሎ ነው የሚተመው፡፡ የአንበጣ ጉዞ ከነፋስ አቅጣጫ ጋር የተቆራኘ ነው። ነፋሱ ወደ ሚነፍስበት አቅጣጫ ነው፣ የአንበጣ መንጋ የሚተምም፡፡

አንበጣ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ፣ አንድ መጠነኛ ስሌት ላቅርብ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ አንድ ጉልምስ የምድረ-በዳ አንበጣ በቀን፣ የራሱን ክብደት ያህል የሚመዝን ምግብ ይበላል፣ ያም ሁለት “ግራም” ገደማ ነው፡፡ እዚህ ግንዛቤ ላይ መሥርተን አንድ ግዙፍ የአንበጣ መንጋ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አናውሳ፡፡

መንጋው 1,200 ኪሎ ሜትር ካሬ ከሸፈነ እና በያንዳንዱ ኪሎ ሜትር ካሬ፣ 40,000,000 አስከ 80,000,000 አንበጠጣዎች ከታቀፉ፣ ከፍተኛውን ቁጥር ግብዓት አድርገን እናስላ፡፡

80,000,000X1,200 X2=192,000,000,000 “ግራም” ማለት ነው፡፡ ያ ክብደት ወደ “ኪሎ ግራም” ሲቀየር (በ አንድ ሺ ሲካፈል) 192,000,000 “ኪሎ ግራም” ይሆናል፡፡ ይህ ክብደት በመኪና ጭነት ቢሰላ፣ እና አንድ መኪና ከነ ተሳቢው 400 ኩንታል (አንድ ኩንታል 100 ኪሎ ግራም ነው የሚመዝን) ቢጭን፣ በድምሩ 4,800 የደርቅ ጭነት መኪናዎች ከነተሳቢዎቻቸው ያስፈልጋሉ፡፡ ዝቅተኛውን ስሌት ብንወስድ (40,000,000 አንበጣዎች በኪሎ ሜትር ካሬ) 2,400 የደርቅ ጭነት መኪናዎች ከነተሳቢዎቻቸው ያስፈልጋሉ፡፡

አንበጣ ምንም ዓይነት ሰብል ለመብላት ይችላል። ዘንጋዳ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ሸንኮር አገዳ፣ የጥጥ አዝመራ፣ የተምር ዛፍ፣ ወዘተ፡፡ አንድ መጠነኛ የአንበጣ መንጋ፣ በአማኻኝ ወደ “አርባ ሚሊዮን” የሚሆኑ አንባጣዎችን ያካተተ፣ ለ35ሺ (35,000) ሰዎች ምግብ ሊሆን የሚችል አዝመራ፣ በአንድ ዕለት ለማውደም ይችላል፡፡

በሰላማዊው ዘመን (አንበጣ መንጋ መሥርቶ በማይሰደድበት ዘመን)፣ አንበጣ የሚገኝባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ ናቸው፡፡ እነሱም በረሃማ ወይም ከፊል በረሃማ የሆኑ አካባቢዎች ሲሆኑ፣ በአማኻኝ 200 “ሚሊ ሜትር” አካባቢ ዝናብ የሚጥልባቸው አካባቢዎች ናቸው (ማለት በርሃ ወይም በረሃ ቀመስ)፡፡ አካባቢውም ሰሜን አፍሪካን፣ ቅርብ ምሥራቅን፣ ምዕራብ እና ደቡብ ያሉ፣ 16 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ካሬ ስፋት የሚሸፍን ሲሆን፣ ያም ወደ ሰለሳ አገሮችን ያካትታል፡፡ በስደት ዘመን ግን 29 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ካሬ የሚሸፍን እና ወደ 60 አገሮችን በሚያካትት አካባቢዎችን ያዳርሳሉ፡፡ ይኸም የዓለም ገፅታን አንድ አምስተኛ ማለት ነው፡፡

የአንበጣ መንጋ ከነፋስ ጋር በሰዓት ከ16 እስከ 19 ኪሎ ሜትር ሊበር ይችላል፣ በአንድ ቀን እስከ 150 “ኪሎ ሜትር” እንደሚጓዝ ይታወቃል፡፡ ከተነሳበት ቦታ በጣም ራቅ ወደ አሉ ቦታዎች ለመጓዝ ይችላል፣ አንዳንዴ ሳያርፍ፡፡ ለምሳሌ ከየመን ወደ አፍሪካ ቀንድ 300 ኪሎሜተር ስፋት ያለውን የቀይ ባህርን አንበጣ ደጋግሞ አንዳቋረጠ ይታወቃል፡፡

ቀደም ባሉ ዘመናት፣ የአንበጣ መንጋ ከምዕራብ አፍሪካ ተነስቶ፣ የእንግሊዝ ደሴትን ይወር እንደነበረ ተመዝግቧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከምዕራብ አፍሪካ ተነስቶ ካሪቢያን ደሴቶችን፣ አምስት ሺ ኪሎ ሜትር ርቀት፣ በአሥር ቀናት ውስጥ እንደተጓዘ ተመዝግቧል፡፡

የወቅቱ የአካባቢያችን “ምድረ-በዳ አንበጣ” ወረርሽኝ

በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ አንበጣዎች ያቀፉ የየምድረ በዳ አንበጣዎች፣ መንጋ መሥርተው አፍሪካን በ2012 ዓ.ም. መቋጫ አካባቢ ጀምሮ ወርረው፣ ያጠቋቸው አካባቢዎች ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲን፣ ኬንያን፣ ዩጋንዳን፣ ታንዛኒያን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳንን ያጠቃልላሉ፡፡ በዚሁ ወቅት የአንበጣ መንጋዎች ሌሎች አካባቢዎችንም አጥቅተዋል (ፓኪስታንን፣ ኢራንን፣ የመንን፣ ኦማንን፣ ስኡዲያን፣ እና ሌሎች አካባቢዎችን)፡፡

የመንጋ ምሥረታ ዋናው ምክንያት ለአንበጣ ርቢ ምቹ በሆኑ አካካቢዎች ክፍተኛ መጠን የነበረው ዝናብ ስለጣለ ነበር፡፡ ይህ ብቸኛ የአንበጣ ዝርያ፣ የምድረ-በዳ አንበጣ ተብሎ ቢሰየምም፣ ለመራባት የረጠበ አሸዋ/ አፈር እንዲሁም ተስማሚ ሙቀት ያስፈልገዋል፡፡ ክፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መጣል ጋር ቅርብ ቁርኝት አለው። ያም ለእንቁላል መጣል አመች ይሆናል። ከዝናብ መጠንከር ጋር የተዛመደ አካባቢው በለምለም ሳር/ቅጠል ይሸፈናል። ስለሆነም ለአንበጣ መንጋ ምግብን ያበረክታል። ብሎም የአንበጣ መንጋዎች ያንሰራራሉ፡፡

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ያንሰራሩ የአንበጣ መንጋዎች ማሽላ፣ ስንዴ፣ የበቆሎ ሰብል ቡቃያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። እንዲሁም የከብት መንጋ መሰማሪያ የሆኑ፣ በቅጣላ ቅጥል ወይም ሳር የተሸፈኑ አካባቢዎች፣ ለውድመት ተዳርገዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. እና በ2012 ዓ.ም. በህንድ ውቅያኖስ በተከሰቱ ማዕበሎች ምክንያት፣ በአረብ አገር ምድረ-በዳዎች በአሸዋ ክምር ተከብበው የሚገኙ ቦታዎች፣ ትናንሽ ሐይቆች መስለው ውሃ አቋቱ። ብሎም የአከባቢውን አሸዋ/አፈር ርጥበት ለአንበጣ ርቢ ተስማሚ አደረጉት፡፡ እነኝኽም የምድረ በዳ አንበጣ መራቢያነት አመች የሆኑ ቦታዎች፣ ሰው የማይደርስባቸው አካባቢዎች ስለነበሩ ስለ የአንበጣ መራቢያ አካባቢዎች ምንም መረጃ አልነበረም፡፡ በ2011 እና በ2012 በነበሩ ዘጠኝ ወራት፣ በአካባቢው የተፈለፈሉ የአንበጣ ቁጥር በስምንት ሺ እጅ ወደ ላይ ናረ (አንድ የነበረ ወደ ስምንት ሺ ተመንዝሮ)፡፡ በ2012 መደምደሚያ አካባቢ፣ እነኝኽ በዚያ አካባቢ የተደራጁ የአንበጣ መንጋዎች ፣ በኤደን በኩል አድርገው፣ ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ አፍሪካ ቀንድ አገሮች ዘመቱ፡፡ አዲስ በተወረረውም አካባቢ ለአንበጣ ርቢ አመች በሆኑ ቦታዎች እንደገና ደጋግመው ለመራባት ቻሉ፡፡ ብዙ አዳዲስ የርቢ ቦታዎች በኩብኩባ (በእደገት ያለ ለመብረር የማይችል) አንበጣዎች ተወረሩ፣ ኩብኩባዎች ወደ ጉልምስነት ተቀይረው በርረው ሌሎች አካባቢዎችን ለማጥቃት ቻሉ፡፡

የ”አየር ቅጥ ለውጥ” (Climate change) እና የአንበጣ መንጋ ግንኙነት

አንበጣ ምንም ደረቅ በሆኑና እና በከፊል ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች ለመራባት ቢችልም፣ ከላይ እንደተጠቀሰው የአንበጣ መራባት ከአካባቢ ርጥበት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በ”አየር ቅጥ ለውጥ” ምክንያት በአንበጣ መንጋ መጠቃት እየናረ ሄዷል። የአካባቢ ሙቀት መናር እንዲሁም ከፍተኛ ዝናብ ተጣምረው፣ ከፍተኛ የሆነ (ብዙ አንበጣዎችን ያቀፉ) የአንበጣ መንጋዎች ምሥረታን ያሳካሉ፡፡

የ”አየር ቅጥ ለውጥ”የማዕበልም ሆነ የሙቀት መንስዔ ስለሆነ፣ በማዕበል መንስዔ ምድረ-በዳ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ ጥሎ፣ አካባቢውን አርጥቦ፣ እንዲሁም ሙቀቱ ከፍተኛ እንዲሆን አስችሎ፣ ከፍተኛ የአንበጣ መንጋዎችን ለማንሰራራት ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሠረቱ ባህር ላይ ከሚከሰት ማዕበል ጋር ተቆራኝቶ፣ በአካባቢው ከሚገኝ የብስ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጥላል፡፡ የ”አየር ቅጥ ለውጥ”የአፍሪካን ክፈለ-ዓለም ለከፍተኛ ጥቃት ያጋልጣል። በ”አየር ቅጥ ለውጥ” ምክንያት በዓለም ውስጥ ከሚጠቁ አገሮች፣ ሃያዎቹ አፍሪካ ውስጥ ነው የሚገኙ፡፡

የወቅቱ የአንበጣ መንጋ ወረራ ከ”አየር ቅጥ ለውጥ”ጋር ያለው ቁርኝት ግንዛቤ አንደሚከተለው ነው፡፡ የ”ህንድ ውቅያኖስ” ጥንድ ዋልታ አለው (Indian Ocean Dipole)፣ ምዕራብ ጠረፍ አካባቢ እና በምሥራቅ የውቅያኖሱ ጠረፍ አካባቢዎች የተመሠረቱ፡፡ ያም ማለት በምዕራብ ጠረፍ አካባቢ እና በምሥራቅ የውቅያኖሱ ጠረፍ አካባቢ፣ የተለያዩ፣ ተቃራኒ የሆኑ የሙቀት/ መቀዝቀዝ መሠረታዊ፣ ተፈጥሮያዊ፣ ሁኔታዎች መኖር ነው፡፡ “አሉታዊ” (መቀዝቀዝ) እና “አወንታዊ” (መሞቅ) ሁኔታዎች በምዕራብ እና በምሥራቅ አቅጠጫዎች በነባራዊ ሁኔታ ተመሥርተዋል፡፡ ለዘመናት ነባራዊ ሁኔታዎች ሳይዛቡ ይዘልቁ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የሚዛናቸው ሁኔታ ካልተቀየረ “ነባራዊ ሁኔታ” ይባላል፡፡ ከአየር ቅጥ ጋር ለውጥ ጋር ተዛምዶ ይኸ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡

የ”አየር ቅጥ ለውጥ”የ”ህንን ኒኞ” (Indian Niño) ለሚባለው ማዕበል መንስዔ ሆኗል፡፡ ይህም ባልተለመደ የውቅያኖስ ሙቀት መዋዠቅ መንስዔ የሚከሰት ሁኔታ ነው፡፡ ሂደቱም እንደሚከተለው ነው፡፡ ለአየር የተጋለጠ “የውቅያኖሱ ፊት”፣ የተንጣለለ ገፅታ (ከአየር ጋር ቀጥተኛ ጉንኙነት ያለው)፣ አካባቢው አየር ሲሞቅ፣ ያ የተንጣለለ ገፅታም ለሙቀቱ ይጋለጣል፡፡ ሆኖም ግን የውቅያኖሱ ሙቀት መጠን፣ በምዕራብ በኩል ያለው ዋልታ (ክፍል) እና በምሥራቅ በኩል ያለው ዋልታ (ክፍል) እኩል አይሆንም፣ ይለያያል፡፡ “አሉታዊ” (መቀዝቀዝ) እና “አዎንታዊ” (መሞቅ) ሁኔታዎች በምዕራብ እና በምሥራቅ አቅጣጫዎች ይከሰታሉ፡፡ የውቅያኖሱ ምዕራባዊ አካባቢ ሙቀት ሲጨምር፤ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያሉ አገሮች ላይ የሚጥለው የዝናብ መጠን ይጨምራል፡፡ ይህ ሲሆን በውቅያኖሱ ምስራቅ አካባቢ ያሉ አገሮች (ኢንዶኔዥያ፣ አውሰትራልያ) የዝናብ መጠን ይቀንሳል። ብሎም እዚያ አካባቢ ድርቅ ይከሰታል፡፡ በምዕራብ አቅጣጫ “አሉታዊ” (መቀዝቀዝ) ሁኔታ ሲከሰት፣ በተቃራኒው፣ በምሥራቅ አካባቢ ያሉት ከመጠን በላይ (ከተለመደው) የሆነ ዝናብ ይጥላል፣ በምዕራብ አከባቢ ባሉት አገሮች ድርቅ ይከሰታል፡፡

ይኸን ዓይነት፣ ማለት “አሉታዊ” እና “አወንታዊ” ሁኔታዎች በአጭር ጊዜያት ውስጥ መፈራረቅ አይታይም ነበር፣ ሀኔታው “ነባራዊ” ሆኖ ነበር (ሚዛኑን ጠብቆ) ለዘመናት የሚዘልቅ፡፡ (ነባራዊ ሁኔታው የሚቀየር፣ ለውጥ የሚከሰት፣ በተራራቁ ዘመናት ነበር፡፡ ቀደም ሲል በሰላሳ ዓመታት በአማካኝ አራት አወንታዊ እና አራት አሉታዊ ሁኔተዎች ነበር የሚከሰቱ፡፡ በቅርብ ጊዜ ግን፣ ከ1980 ወዲህ፣ በምዕራብ የህንድ ውቅያኖስ 12 “አዎንታዊ ሁኔታዎች ሲከሰቱ” አንድም “አሉታዊ” ሁኔታ አልነበረም፣ ወይ “ነባራዊ” ነበር፣ ወይ “አወንታዊ ነበር፡፡ የመፈራረቁ ክስተት በጣም ፈጣን እየሆነ ነው (በአጭር ጊዜ ውስጥ እተደጋጋመ ይከሰታል)፡፡

በ2018 “በህንድ ውቅያኖስ “ምዕራብ ዋልታ” “አወንታዊ” ሆኖ ቆይቶ፣ እንደገና በድንገት ሙቀቱ በጣም ዝቅ ብሎ፣ ወደ “አሉታዊ” ዋልታነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀይሮ ነበር፡፡ ከዚያም ባልታሰበ እና ባልታለመ ፍጥነት፣ ሁኔተው ተቀይሮ፣ በከፍተኛ ደረጃ ያለ “አዎንታዊ” ዋልታ ተከሰተ፡፡ ይህም ከ1870 ወዲህ ከተመዘገቡት “አዎንታዊ” ሀኔታዎች ሁሉ የላቀ ነበር፡፡ በግንቦት አካባቢ ለተከሰተው የአንበጣ መንጋ ማንሰራራት ዋናው ምክንያት በ”አየር ቅጥ ለውጥ” የ”ሕንድ ውቅያኖስ” ጣምራ ዋልታ ሁኔታ መለዋወጥ፣ መዋዠቅ ነው ተብሎ በባለሙያወች ተገምቷል፡፡

የወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ በጎርፍ መጥለቅም እና በአንበጣ መንጋ መወረር የተዛመዱ ናቸው፡፡ ሁለቱም በምድረ-በዳ አካባቢ በወረደው ከፍተኛ የዝናብ መጠን፣ ለአንበጣ መራባት ምክንያት ሆኖ፣ የአንበጣ መንጋዎች ተመሥርተው ብዙ አካባቢዎች ወርረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ምድረ-በዳ አካባቢም፣ ማለት አንበጣ በሚራባቸው አካባቢዎች፣ የመራቢያ ቦታዎች በጣም ተስፋፍተዋል፡፡ የዝናቡ መጠን መጨመር በ”አየር ቅጥ ለውጥ” መንስዔ የተከሰቱ ኩርፊቶች (Cyclones) ናቸው፣ ስያሜውም ኩርፊታዊ ዝናብ (Cyclone rainfall) ነው፡፡ እያንዳንዱ ኩርፊታዊ ዝናብ (Cyclone rainfall) ለአንበጣ መራባት ከፍተኛ መሠረት ነው፡፡ ይህን አይነት ክስተት፣ ከአየር ቅጥ ከለውጥ ጋር ተዛምዶ ወደ ፊት ደጋግሞ ይከሰታል ተብሎ ይገመታል፡፡ ጎርፍም የተከሰተ በዝናብ መጠን መናር መንስዔ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ባህር ማዕበል ተከትሎ፣ በአካባቢው ባሉ አገሮች ከባድ ዝናብ ይጥላል፡፡

ለአየር ቅጥ ለውጥ ምክንያት ዋና ዋና የሆኑት ምክንያቶች፣ ያደጉ አገሮች እንዱስትሪዎች እንዲሁም ጠቅለል ብሎ ሲታይ፤ የኑሮ ባህሎች ሲሆኑ፣ በችግሩ በዋናነት የሚጠቁት ግን ለማደግ የሚፈጨረጨሩ ታዳጊ አገሮች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ቅርብ በታሪክ

በ1996 እና 1997 አካባቢ አንበጣ አፍሪካን በስፋት አጥቅቶ ነበር፡፡ ጥቃቱ የደረሰባቸው አገሮች፣ አልጄሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ የካናሪ ደሴቶች፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ቻድ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋምብያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ ሊብያ፣ ማሊ፣ ሞሪታንያ፣ ሞሮኮ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን እና ቱኒዝያን ያካተተ ሲሆን ሌሎች አከባቢዎችም (ግሪክ፣እስራኤል፣ ጆርዳን፣ ሳውዲያ) ተወርረው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ፣ በተለይ በሰሜኑ ክፍል፣ በአንበጣ መንጋ ወረራ ደጋግሞ ጥቃት ይደረስበት እንደነበረ ተመዝግቧል፡፡ በቅርብ ጊዜ በ1947 ዓም እና ከ1954 እስከ 1957 በኢትዮጵያ፣ በተለይ በሰሜኑ አካባቢ ብዙ ጥፋት አድረሷል። የረሃብ ምክንያትም ሆኖ ነበር፡፡ በዘመናችን (2012/2013 ዓ|ም) የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወረራ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያስከትላል ተብሎ ይገመታል፡፡ የዚህ ወረራ አካል የሆነው፣ በቦረና (ደቡብ ኦሮሚያ) አካባቢ የደረሰው የአንበጣ መንጋ ከሩቅ ሲታይ የቃጠሎ አሳት አምሳያ ነበር ይባላል፣ የአንበጣ መንጋ መሆኑ የሚታወቅ፣ በቅርብ ርቀት ሲታይ ብቻ ነበር፡፡ ያን አካባቢ የወረረው የአንበጣ መንጋ መንግሥት አልባ ከሆነች የመን ተነስቶ፣ በሶማሊያ በኩል አድርጎ ወደ አካባቢው የዘመተ መንጋ ነበር፡፡ የዘመኑ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰቱ የአንበጣ መንጋ ወረራዎች፣ የከፍተኛ ረሃብ መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ፡፡

በ1947 ዓም የተነሳው የአንበጣ መንጋ እኔ የተወለድኩበትንም አካባቢ አጥቅቶ ነበር፡፡ ጥቃቱ የተፈፀመ መስከረም መጀመሪያ አካባቢ ላይ ሲሆን፣ ከጤፍ ቡቃያ ጋር ተዛምዶ የተደረደረ አንድ የገበሬ ስንኝ ላውሳ፡፡

አንበጣ ድገመኝ፤
አፍህ ለመለመኝ፡፡

ገና መብቀል ጀምሮ የነበረው (ለጋ የነበረው) የጤፍ ቡቃያ ሲበላ፣ ከታች የቀረው አካል እንደ ገና አንሰራርቶ፣ ጥሩ አዝመራ ስላበረከተ ነበር ያ ስንኝ የተወረወረ ብየ ገመትኩ፡፡ በመሠረቱ የሳር ዝርያዎች ሁሉ ሲጎዱ፣ የደረሰውን ጉዳት ለመቆቋም የሚጥሩ ከስር በማቆጥቆጥ፣የጠፋውን ለመተማካት በመሞከር ነው (ጤፍ የሳር ዝርያ ነው)፡፡ ያም እንደ ሕላዌ ግዳጅ ይወሰዳል፡፡ ይህ ባህርይ በእንግሊዝኛ ቲለሪንግ (Tillering) ይባላል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ዛፎች ሲቆረጡ፣ ቅርንጫፎች በማብቀል የደረሰውን ጥፋት ለመቋቋም ይጥራሉ፡፡ ይህ የዛፎች ባህርይ በእንግሊዝኛ “ኮፒሲንግ (Coppicing) ያባላል፡፡

ምግብነት

በብዙ አካባቢዎች እንደ ባህል ሆኖ አንበጣ ለምግብነት ያገለግላል። ከዚያም ባለፈ መልክ እንደ ተመራጭ ምግበ ይወሰዳል፡፡ የተለያዩ የአንበጣ ዝርያዎች፣ በአፍሪካ (በብዙ አካባቢዎች)፣ በቅርብ ምሥራቅ እና በእስያ ለዘመናት ለምግብነት አገልግሏል፡፡ ምንም አውሮፓውያን አንበጣን መመገብ እንደ አረመኔነት ቢፈርጁትም፣ በቅርብ ጊዜ በ”ስዊዘርላንድ” መንግሥት አንበጣን ለምግብነት ማዋል ሕጋዊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

ፍርድ አሰጣጡን በሳይንሳዊ መረጃ ላይ ብንመሠርት ኖሮ፣ ድርጊቱን ከመኮነን እንታደግ ነበር፡፡ አንበጣን ለምግብነት ማዋል ብዙ ጠቀሜታ አለው፣ ከዚያም ባለፈ የከብት ሥጋ ከመብላትም በብዙ ምክያቶች ተመራጭ ነው ብለን እንደመድም ነበር፡፡ የቀንድ ከብት ማርባት በአካባቢ ላይ ብዙ አሉታዊ ተፅእኖ ያስከትላል፡፡ አንዱ እና ዋናው አየር የሚበክል መጥፎ “ጋዝ” ፣ “ሜቴን” (Methane) የሚባል፣በግሳት መልክ ከብቶች አየርን መበከላቸው ነው፡፡ “ሜቴን” እንደ “ካርቦን ዳይኦክሳይድ”(Carbon dioxide)፣ በሕዋ ላይ መጋረጃ ዘርግቶ፣ የፀሐይ ጨረር ምድር ከደረሰ ወዲያ ተንፀባርቆ፣ መልሶ ወደ ሕዋ እንዳይዘልቅ ይከለክላል፡፡ ቀደም ብሎ አንደተጠቀሰው፣ ይኸም ሙቀት አመንጭ ጨረር አለመወገዱ፣ በምድራችን ላይ ተፅዕኖ በማድረግ፣ የአየር ቅጥ ለውጥን (Climate Change) ያስከትላል::

ሁለተኛ አንበጣ የሚመገበው ሳር ወይም ቅጠል፣ የቀንድ ከብት ከሚመገበው ጋር ሲነፃፀር፣ አንበጣ 1.7 “ኪሎ ግራም” ቅጠላቅጠል በልቶ፣ 1 ኪሎ ግራም ሥጋ ያካብታል፣ በአንፃሩ የቀንድ ከብት (በሬ ላም) አሥር ኪሎ ሳር፣ ቅጠላ ቅጠል በልቶ ነው፣ አንድ ኪሎ ሥጋ ብቻ የሚያካብት፡፡ ስለሆነም ከቀንድ ከብት ጋር ሲነፃፀር፣ አንበጣ ከአምስት እጅ በበለጠ ሁኔታ፣ ሳርን፣ ቅጠላቅጠልን ወደ “ስጋነት” የመቀየር ችሎታ አለው፡፡

ከሃይማኖት አንፃርም ብንመለከት፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች ቅዱሳን መጻሕፍት፣ አንበጣ መመገብ ተቀባይነት እንዳለው እንገነዘባለን፡፡

ኦሪት ዘፀአት ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፬፣ “የዮሐንስ ልብስ የግመል ፀጉር ነበር፡፡ በወገቡም የጠፍር መታጠቂያ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የጣዝማ ማር ነበር” ይላል፡፡ በይሁዳውያንም ቅዱስ መጽሐፍ፣ “ቶራ” (Torah)፣ ምንም የብዙ ሦስት አፅቄዎች በምግብንት መጠቀምን ቢኮንንም፣ ጥቂት የአንበጣ ዝርያዎችን መብላት ይፈቅዳል፡፡

በባህል፣ በብዙ አካባቢዎች (የአፍሪካ አገሮች፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ እንዲሁም በእስያ)፣ ለዘመናት አንበጣ እንዲሁም ሌሎች ሦስት አፅቄዎች ለምግብነት ያገለግላሉ፡፡ አንበጣ አንዱ ተመራጭ የምግብ ዓይነት ነው፡፡ ከላይ አነደተጠቀሰው፣ ስዊዘርላንድ አንበጣ ሊበላ፣ ምግብ ሊሆን እንደሚችል በሕግ ደንግጋለች፡፡ አንበጣ ለምግብነት የሚዘጋጅ፣ ብዙ ጊዜ ጭንቅላቱን፣ ክንፎችን እንዲሁም አግሮቹን ካሰወገዱ በኋላ፣ በጥብስ መልክ፣ ወይም በጢስ ደርቆ፣ ወይም በፀሐይ ደርቆ በቋንጣ መልክ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜ ሳይበላሽ እንዲቆይ፣ በተወቀጠ ቋንጣ (በደቀቀ ደረቅ ዱቄት መሰል) መልክ ይዘጋጃል፡፡ ምናልባት ወደፊት ሦስት አፅቄዎች የሰው ልጆች ምግብ መደበኛ ይሆናሉ ብለው የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው፡፡

የአንበጣ መከላከያ ድርጅት

ከታሪክ አንፃር ጠቅለል ባለ መልክ ዓለምን ስንቃኝ፣ የአንበጣ መንጋ ጥቃት ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በጣም አየቀነሰ መጥቷል፡፡ የአንበጣ መንጋን ለመቆጣጠር በተለያዩ ደረጃዎች የተቋቋሙ ድርጅቶች አሉ፣ በዓለም ምግብ ድርጅት (Food and Agriculture Organization-FAO)፣ ለዚሁ ተግባር የተመደበ ቋሚ ቡድን አለ፡፡ ይህም ቡድን ትኩረት የሰጠው ለመረጃ ማሰባሰብ ብሎም ማሰራጨት ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ፣ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት (Desert Locust Control Organization-DLCO) በመባል የሚታወቅ ድርጅት ተመሥርቷል፣ አባላቱም ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ናቸው፡፡

ዘመናዊ የአንበጣ መከላከያ ዘዴዎች ኬሚካላዊ ፊዚካላዊ እና ሕያው አመጋገብ መረብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ አንዱ እና ዋናው፣ አንበጣ የሚራባባቸውን አካባቢዎች አጢኖ፣ መንጋው ከመሬት ሳይነሳ በኬሚካላዊ መንገድ (ኩብኩባዎች አሉበት አካባቢ ፀረ ሦስት አፅቄ ኬሚካል በኤሮፕላን በመርጨት) ማውደም ነው፡፡ እንዲሁም በመሣሪያ አጥምዶ (እንደ መረብ መሰል) በፊዚካላዊ ወይም ኬሚካላዊ ዘዴ ማጥፋት ይቻላል፡፡ በእሳት ላንቃ መጠቀም አንዱ መንገድ ነው፡፡ ኩብኩባዎችን ከቦታ ቦታ ሲዘልሉ፣ በቦይ ውስጥ አጥምዶ፣ ከዚያም በመዳመጥ (መጨፍለቅ) ነው፡፡ በበረራ ላይ ያሉ ጉልምሶች ካረፉበት ቦታ፣ ያም ጠዋት፣ ገና ፀሐይ ሳትጠነክር እና ጉልምሶች መብርረ ሳይጀምሩ በፀረ ሦስት አፅቄ ኬሚካል ማውደም ነው፡፡

በተጨማሪ የአንበጣ የበሽታ መንስዔ የሆኑ፣ ሸገቶ (“ፈንገስ”/Fungus) ዝርያዎች በመርጨት ነው፡፡ በአካባቢው ያሉ አእዋፍም አንበጣን በመብላት መጠነኛ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ አንበጣ ነዳፊ ሦስት አፅቄወች፣ እንደ ተርብ ያሉ፣ የገበሎ አስተኔ አባላት፣ ግለኛ የሆነቱን (መንጋ ያልመሠረቱተን አንበጣዎች) ማጥቃት ይችላሉ፡፡ መንጋ የመሠረተውን የአነበጣ ስብስብ መግታት ግን ከእነሱ አቅም በላይ ነው፡፡

ምንም ለሕዝብ አገልግሎት የዋሉት ማለት ብብዛት ያሉት ሳተላይቶች የአንበጣ መንጋን መኖር አለመኖር አብሳሪ የሆነ መረጃ ለማበርከት የማይችሉ ቢሆንም፣ በመከላከያ ተቋማት የሚገኙ ሳተላይቶች ግን ያንን ዓይነት መረጃ ለማበርከት ይችላሉ፡፡ በሂደት አሁን “ሚስጥራዊ” የሆኑት ሳተላይቶች፣ ዘመን አልፎባቸው ገሃድ ሲወጡ፣ ለአንበጣ መከላከል ተግባር (ወቅታዊ መረጃ መሰብሰብ) ያገለግሉ ይሆናል፡፡

የአንበጣ መንጋን መከላል አስቸጋሪ የሚያደረጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፣ ዋናዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንበጣ የሚፈለፈልበት አካባቢ፣ በጣም ሰፊ በሆነ ምድረ በዳ ስለሚያካትት ለቅኝት በጣም አዳጋች ነው፡፡ በተጨማሪ ብዙዎች የአንበጣ መራቢያ አካባቢዎች፣ ሰው የማይደርስባቸው ምድረ-በዳዎች ናቸው፡፡ ሌሎች መራቢያዎች ደግሞ ፀጥታ በደፈረሰባቸው አካባቢዎች (ለምሳሌ እንደ የመን ያሉ)፣ ስለሆነ ወደ መራቢያ አካባቢዎች ለመዝለቅ ያዳግታል፡፡

በተጨማሪ ለአንበጣ መከላከል የሚውለው በጀት በጣም ውስን ነው፡፡ ዋናው ምክንያት የአንበጣ ወረራ ለዓመታት ስለማይከሰት፣ ቋሚ ሰራተኛ መድቦ (የአንበጣ መንጋ ቢከሰትም ባይከሰትም) ማስተናገድ ለታዳጊ አገሮች ያዳግታል፡፡ የአንበጣ መንጋ መቼ ነው ጥቃት ሊያደርስ የሚችል ብሎ መተንበይም አይቻልም፡፡ በተጨማሪ ኩብኩባዎችንም ሆነ ጉልምሶችን ለማጥቃት የሚረጨው ኬሚካል፣ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳያደርስ፣ አካባቢውን እንዳይበክል፣ በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፣ ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ተግዳሮቶችንም መዘርዘር ይቻላል፡፡

መደምደሚያ

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ማኸዘብ ነው፡፡ ይህን ተግባር (ሳይንሳዊ ግንዛቤን) ለማዳበር ይረዳ ዘንድ ከአንበጣ ጋር በተዛመደ፣ በቻይና በ311 ምዕተ ዓመት የደረሰን የአንበጣ መንጋ ጥቃት ላውሳ፡፡ በቻይና የአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል 311 ምዕተ ዓመት በአንበጣ መንጋ ተጠቅቶ፣ ከዚያም ዘጠና ስምንት በመቶ (98%) የሚሆነው ሕዝብ ለሞት ተዳረጉ፣ እልቂቱንም በቀጥታ አንበጣ እንዳስከሰተው ሆኖ ነበር የተወሰደ፡፡

ነባራዊ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ግምት ለማቅረብ ይቻላል፡፡

ነባራዊ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ጉዳዩን ስንመረመር፣ የእልቂቱ መንስዔ በአንበጣ መወረር ምክንያት ሰብል ጠፍቶ፣ ብሎም ማህበረሰቡ ለረሃብ ተዳርጎ እንዳልነበረ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ለየት ያለ እንደነበረ ይገመታል፡፡ የአንበጣ መንጋ አባላት ሲሞቱ በገፍ ለአይጥ ምግብ (አይጥ የሞተ አንበጣ ትበላለች) አበረከቱ፡፡ የሚሞቱት የመንጋ አባላት በበረከተ መጠን፣ ምግብ እንደ ልብ ይገኛል፡፡ ይህም ሁኔታ የአካባቢው የአይጥ ቁጥር በጣም እንዲንር ሁኔታውን ያመቻቻል፡፡ አይጦች በብዛት ተራብተው አካባቢውን አጥለቅልቀውት እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡

ከአይጥ መብዛት ጋር ተዛምዶ፣ የአይጥ ጥገኞች የሆኑ፣ በሽታ አስተላለፊ ቁንጫዎች ቁጥርም እንዲሁ ሊንር ይችላል፡፡ ያም በሽታን ከአይጥ ወደ ሰው፣ በቁንጫ አማኻኝነት፣ ለማስተላለፍ አመች ሁኔታን እንደፈጠረ ይገመታል፡፡ የእልቂቱ (ወረርሽኝ ይመስላል) መንስዔ በቁንጫ አቀባባይነት፣ ከአይጥ ወደ ሰው በሚተላለፍ በሽታ ተብሎ ነው ሳይንሳዊ ግምት የተሰጠ፡፡ ምክንያቱም የአንበጣ መንጋ በሚያስከትለው ረሃብ ይህን ዓይነት እልቂት የትም አካባቢ ተከስቶ አያውቅም። ሊከሰትም አይችልም፣ ምክንያቱም ረሃብ ሁሉንም የማህበረሰብ አባላት በአንድ ጊዜ ለሞት አይዳርግም፡፡ ሁል ጊዜም ከቸነፈር የሚተርፉ የማህበረሰብ አባላት አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ረሃብ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰው በሕፃናት አንዱም በአቅመ-ደካሞች ላይ ነው፡፡ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ፣ ይኸን ዓይነት ግምት አሰጣጥ ነው፡፡

ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ምክንያታዊ ነው፡፡ በማህረሰባችን ውስጥ ሰርፆ የሚገኝ አንድ ዋና ጉዳይ፣ ለኩነቶች ትክክል ያልሆኑ ምክንያቶችን መደረደር ነው፡፡ አሁን ለተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስንኳ መለኮታዊ ምክንያት የሚሰጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህን ዓይነት ግድፈት በኛ (በኢትዮጵያውያን) ብቻ የሚተገበር አይደለም፣ በብዙ አካባቢዎችም የተለመደ ነው፡፡ በጥንት ዘመን ይህን ዓይነት አስተሳባብ ከአጥናፍ አጥናፍ አንሰራርቶ ይገኝ ነበር፡፡

ትክክል ያልሆኑ ሌሎች ምድራዊ ምክንያቶችም ይሰጡ ነበር፡፡ ለማብራራት ያህል ጥቂት ምሳሌዎችን ላውሳ፡፡ ስጋ ላይ ትል ሰለሚታይ፣ ትሉ ከስጋው የተገኘ ነው ይባላል፣ ስጋው እንደወለደው መሰል፡፡ ሆኖም የስጋ ትል የዝንብ እጭ ነው፣ ዝንብ ስጋ ላይ ከጣለቸው እንቁላሎች የተፈለፈለ (የተገኘ) ነው፡፡

ዋሽንት የሚነፋ ግለሰብ ፊት ለፊት የሚገኝ ኮብራ (እባብ)፣ ግለ ሰቡ ዋሽንት ሲነፋ፣ እባቡ አንገቱን ስለሚያወዛውዝ፣ በሙዚቃ ተመስጦ እየዘፈነ ነው ይባላል፡፡ በመሠረቱ እባብ እኛ በምናውቀው መንገድ እይደለም ድምጽን የሚገንዘብ፡፡ እባቡ አንገቱን የሚያነቃንቅ፣ በማነጣጠር ላይ (በእይታ ላይ) ተመርቶ ነው፡፡

ሳይንሳዊ አስተሳሰብ በቅን “ልቦና” የታጀለ ከሆነ የሰላም መሠረት ይሆናል። በአንፃሩ ቅን ልቦና ከጎደለው የጥፋት ምንጭ ይሆናል፡፡ ያም ሆኖ አስተሳሰብ በ”ልቦና” ላይም ጫና ማድረጉን መርሳት የለብንም፡፡

ማጭድ ይኾነን ዘንድ፣ ምንሽር ቀለጠ
ዳሩ ብረት ‘ንጅ፣ ልብ አልተለወጠ
ለሣር ያልነው ስለት፣ እልፍ አንገት ቆረጠ፡፡
(ከበዕውቀቱ ሥዩም ስንኞች አንዷ)

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top