በላ ልበልሃ

የሁለት ውጭ ፖሊሲዎች ወግ: ኢትዮጵያ እና ግብጽ

የውጭ ፖሊሲ አንድ አገር ከጎረቤቶቹ፣ ከአካባቢው አገሮችና በተለያዩ አህጉራት ከሚገኙ አገሮች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት፣ የሚያከናውናቸውን ተግባራትንና ጥቅሞቹን መሰረት አድርጎ የሚወስንበት መሳሪያ ነው። ይህ መሳሪያ የሚቀረጽበት መንገድ በየአገሩ ዘርፈ-ብዙ ውስጣዊ ፍላጎቶች ላይ በመመስረት ነዉ። መሳሪያው ትርፍና ኪሳራን አስልቶ የአገርን ብሔራዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚያስችል እሳቤ ላይ ይመሰረታል።

የአገርን ጥቅም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንዲጠበቅ የማድረግ ተግባር ግን በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ነው። የውጭ ፖሊሲ የሚተገበርበት ዓለም አቀፍ ግኑኝነት እጅግ ውስብስብ፣ እርስ በርሳቸው በሚፎካከሩና በሚጋጩ ፍላጎቶች እንዲሁም አሻሚ እውነታዎች የተሞላ በመሆኑ መመላለሻው አልጋ ባልጋ አይደለም። በአቀበትና ቁልቁለት፤ በእሾህና በጋሬጣ የተሞላ ነው።

የየአገሩ አንጻራዊ ኃይልና ጉልበት፣ የአቅምና ጥንካሬ ሁኔታዎች እንዲሁም የድርድርና ሙግት፣ የማስፈራራትና ማባባል አቅሞች ሁሉ ተመሳጥረው ተጽዕኖ የሚያደርጉበት ነው። እነዚህን ሁሉ ውጥንቅጦች ባካተተው አውድ ውስጥ የተፈጠሩት ዓለምአቀፋዊ ሕጎች፣ ደንቦችና መርሆዎችም የውጭ ግኑኝነቶችን የመወሰን ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ሕጎቹ፣ ደንቦቹና መርሆዎቹ እንዳሉ ሆነው የዓለምአቀፍ ግኑኝነት አውድ መጠናቸውና ጉልበታቸው፣ ፍላጎቶቻቸውና አቅማቸው ልዩ ልዩ የሆኑ አሳዎች በአንድነት የሚዋኙበትን ውቅያኖስ የሚመስልበት ሁኔታም አለ።

የውጭ ፖሊሲ እንዴት ይቀረጻል?

ከየትኛውም ዓይነት ፖሊሲ ይልቅ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መቅረጽ እጅግ አስቸጋሪ ነው ይባላል። ለዚህም ምክንያቱ ለፖሊሲው ቀረጻ የሚሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ግብዓቶች አሰባሰብ፣ አጠናን፣ አቀማመር፣ አደረጃጀትና ሥነ-ዘዴ ውስብስብ በመሆኑ ነው። የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አቀራረጽ ክህሎት፣ ጥበብ፣ የዳበረ ልምድና ሂሣዊ አመለካከትን ይጠይቃል። የውጭ ግንኙነት አንድ አገር ከሌላ አገር ጋር የሚኖረውን ሁለገብ ግንኙነት የሚያመላክት ሲሆን ፖሊሲ ደግሞ አንድ አገር በዓለም አቀፍ ግንኙነት ከሌሎች አገሮች ጋር በሚያደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ሊጐናጸፋቸው የሚያስባቸውን አገራዊ ፍላጎቶች፣ ዓላማዎችና ግቦች ዝርዝር ነው። የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርሆዎች የሚባሉትም አንድ አገር የቀረጸውን ብሄራዊ ዓላማ ለመጐናጸፍ የሚመራበት መሳሪያዎች ናቸው።

አገሮች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውን የሚቀርጹት እንደየአገሮቻቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች ነው። በመሆኑም የሁሉም አገሮች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንድ ዓይነት ሊሆን አይችልም። አገሮች እንደ ውስጣዊ ተጨባጭ ሁኔታዎቻቸውና የደረሱባቸውን የዕድገት ደረጃዎች ግምት ውስጥ አስገብተው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውን ይቀርጻሉ። ለሁሉም የሚሆን የተሰፋ ጃኬት የለም። ሆኖም ሁሉም አገሮች ሊከተሏቸው የሚገቡ የጋራ የሆኑ ወሳኝ ባህሪያት አሉ። እነዚህም በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባሉ። ውስጣዊ ነባራዊና ህልውናዊ ሁኔታዎች፣ ውጫዊ ነባራዊና ህልውናዊ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም የፖሊሲ ቀራጮችና የውሳኔ ሰጭዎች ስነ-ልቦናዊ ባህርይ ናቸው።

ውሃታሪክሀይማኖት

ከኢትዮጵያና ግብጽ ግኑኝነት አንጻር የውጭ ፖሊሲ ወሳኝ ጉዳዮች ከሆኑት መካከል ዋነኛው የአባይ ወንዝ ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ምንጭና የራስጌ ተጋሪ አገር ናት። በምዕራባዊ ተፋሰሷ ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወንዞቿ የናይል ወንዝን ይገብራሉ። በተለያዩ ጥናቶች እንደተጠቆመው ከእነዚህ ወንዞች መካከል አባይ ብቻውን 50 ቢሊዮን ኩብክ ሜትር፣ ባሮ-አኮቦ 12 ቢሊዮን ኩብክ ሜትር እንዲሁም ተከዜ 10 ቢሊዮን ኩብክ ሜትር ያበረክታሉ። የናይል ወንዝ ዓመታዊ ፍሰት መጠን 85 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነው። ከእነዚህ የኢትዮጵያ ወንዞች ወደ ናይል የሚገባው የዉሃ መጠን 72 ቢሊዮን ኩብክ ሜትር ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ዋነኛ ምንጭና ለተፋሰሱ ስነ-ህወይትና ለቀጠናው ተፈጥሯዊ ስነ-ምህዳር መጠበቅ ዋስትና ናት። በአንጻሩ ግብጽ ለአባይ ዉሃ የምታበረክተው ጠብታ ዉሃ ድርሻ ሳይኖራት ከኢትዮጵያና ከሌሎች የተፋሰሱ አገራት በሚወርድላት ዉሃ ላይ ህልዋናዋን መስርታ የምትገኝ የግርጌ ተጋሪ ነች። ቀድሞውኑ የአባይን ዉሃ በሚመለከት ያላት ፖሊሲ ወረራን ጨምሮ ኢትዮጵያን በልዩ ልዩ የኃይል፣ የሴራና የዲፕሎማሲ መሳሪያዎች ተጽዕኖ አማካኝነት የመታገል፣ የመቆጣጠር ፍላጎትና ተግባራት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ታራምዳለች። በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ባሳየችው አንጻራዊ መረጋጋትና ልማት የምጣኔ ሃብት እድገቷን፣ አቅሟንና ወታደራዊ ኃይሏን እንዲሁም የደረሰችበትን ክፍለ-አህጉራዊ የተጽዕኖ ፈጣሪነትና የበላይነት ሚናን አዳምራ በመጠቀም በመልክዓ-ምድር አቀማመጧ የናይል ተፋሰስ የመጨረሻ የግርጌ ተጋሪ ሆና ሳለ በራስጌዎቹ ተጋሪ አገሮች ላይ የበላይነት ፖሊሲን ስታራምድ ቆይታለች። በዚህ ምክንያት የናይል ወንዝ ዋነኛዋ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያና የወንዙ የመጨረሻ መዳረሻ የሆነችው እንዲሁም ጀብደኛና በኃይል ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ያላት ግብጽ በአባይ ዉሃ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ ተቃራኒና ተፎካካሪ ነው። ፖሊሲዎቻቸውና በፖሊሲዎቻቸው የሚመሩት ተግባሮቻቸው በግልጽና በዝርዝር በሚታይና በማይታይ ሁኔታ ስጋቶችና ፍጥጫዎች አሉበት። በሁለቱ ተጋሪዎች መካከል የሃይድሮ-ዲፕሎማሲያዊ ትንቅንቅ ከጥንት እስከዛሬ አለበት። ለናይል ዉሃ የምታበረክተው ጠብታ ድርሻ የሌላት የወንዙ የግርጌ ተጋሪዋ ግብጽ የወንዙን ፖለቲካ በበላይነት የመምራት ግትር ፖሊሲ ታራምዳለች። ለናይል ወንዝ 85 ከመቶ ዉሃ የምታበረክተው የራስጌ ተጋሪዋ ኢትዮጵያ ግን የበይ ተመልካች ሆና ቆይታለች። በዚህ መነሻ አገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአባይን ዉሃ ማልማት ተፈጥራዊ፣ ዲሞክራስያዊ፣ ሕገ-መንግሥታዊና ሉዓላዊ መብቷ መሆኑን በጽኑ በማመንና በይፋ የወጭ ፖሊሲዋ አካል በማድረግ ለፍትሐዊና ርትዓዊ የዉሃ ክፍፍል ቆማለች። በተለይ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ወዲህ በሁለቱ ተጋሪዎች መካከል ያለው የዉሃ ፖለቲካዊ ግንኙነት ከምንም ጊዜ በላይ የከረረ ሆኗል።

ይህ የሁለቱ አገሮች ግኑኝነትና የውጭ ፖሊሲዎች ጠባይ ግን የዛሬ ክስተት ብቻ አይደለም። በለውጥና ቀጣይነት ሂደት ውስጥ ተጉዞ የዛሬ ባህሪውን የያዘ እውነታ ነው። ፕሮፌሰር ባህሩ እንደጻፈው በኢትዮጵያ የውጭ ግኑኝነት ታሪክ ውስጥ እንደ ግብጽ ጉልህ ስፍራ የያዘ ኖሮ አያውቅም። በየዘመኑ ኢትዮጵያ ከውጭ አገሮች ጋር ባላት ግኑኝነት ውስጥ ከግብጽ ጋር ያላት ግንኙነት በብዙ ውጥረቶችና ሁነቶች የተሞላ ነው። ለምሳሌ ይህን እውነታ ከቆዩ መረጃዎች ጋር እያነጻጸርን በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ የአባይ ወንዝ ተጋሪዎች መካከል ያለውን ውጥረት የሞላበት ግንኙነት ከታሪክ፣ ከውጭ ፖሊሲ ተከታታይነትና ለውጥ አንጻር ከአንዳንድ ነጥቦች ጋር አያይዞ ማንሳት ይቻላል።

አንዳንድ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች የአባይን ወንዝ አቅበው በግብጻውያን ላይ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ በመግለጽ ለግብጽ መሪዎች የዛቻና ማስፈራሪያ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር የሚጠቁሙ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ኃይሉ ወልደ ጊዬርጊስ በ2001 ዓ.ም በታተመ መጽሐፉ እንደጠቆመው አጼ ተክለሃይማኖት መልዕክተኞቻቸው በግብጽ ባለሥልጣኖች መታሰራቸውን ሲሰሙ ተናደው በ1704 ዓ.ም “እናንተን ለመቅጣት ዓባይ በቂ ነው። የወንዙን መጓጓዣውንና የፈሰሱን መጠን የመወሰን ሥልጣን አምላክ ስለለገሠን እናንተን ለመቅጣት ልንጠቀምበት እንደምንችል እወቁት” ብለው ነበር።አጼ ቴዎድሮስ በ1860 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ የመጡት አጼ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ተብለው ተቀብተው ሳይነግሱ ለአራት ዓመታት ያህል ቆይተዋል። ምክንያቱ ግብጻዊው አቡነ ሰላማ በአጼ ቴዎድሮስ ወህኒ ተጥለው በመሞታቸው ግብጽ አዲስ ጳጳስ ወደ ኢትዮጵያ ያለመላክ ‹‹መቀጣጫ›› በማስቀመጧ ነው። የግብጽ መሪዎች የሚያሳስባቸውንና የሚያሰጋቸውን በኢትዮጵያ ሊፈጸም የሚችል የዉሃ ማዕቀብ በልባቸው ይዘው የኢትዮጵያ ነገሥታት አብዝተው የሚፈልጉትን ጳጳስ ከልክለው መቅጣታቸው ነበር። በጣም ሃይማኖት አጥባቂ የነበሩት ዮሐንስም ከብዙ ‹‹ደጅ ጥናት›› በኋላ ገጸበረከት ለግብጽ ፓትርያርክ በተደጋጋሚ ልከው በመታረቅ አቡነ አትናቴዎስ ጳጳስ ተደርገው ተላኩላቸው። ዮሐንስም በጳጳሱ ተቀብተው በ1864 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ሆኑ። አጼ ዮሐንስ በውስጥ ፖለቲካ ርዕዮታቸው በጣም ለስላሳ ነበሩ። ፖሊሲያቸው እርቅን፣ ይቅር ባይነትንና ሰላምን የተከተለ ነበር። ለውጪ አገር መሪዎች የጻፏቸው ደብዳቤዎች ይዘትም የአጼውን የበዛ ሃይማኖታዊነት ያንጸባርቁ ነበር። እሳቸው ብዙ አብያተ-ክርስትያናትን ከማሳነጻቸውም በላይ በዘመናቸው በወር ውስጥ አርባ አራት በዓላትን የማክበር ተግባር ይበልጥ ዋጋ ተሰጥቶታል። ስራ የልማትና የዕድገት መሠረት ነው የሚለው አስተምህሮ ትኩረት ተነፈገው። ኢትዮጵያ በልማት ወደኋላ እንድትቀር ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ ይህ ነበር ማለት ይቻላል። ከግብጽ ይላኩ የነበሩ ጳጳሳት ሃይማኖታዊ በዓላትን የማክበር ወግ እንዲበረታ አድርገው የግብጽን ስውር ፖሊስ አስፈጽመዋል። ኢትዮጵያውያን ከሰሩ ያድጋሉ፤ ካደጉ ይፎካከሩናል በሚል ስጋት ግብጻውያን በሚልኳቸው ጳጳሳት አማካኝነት በረቀቀ ዘዴ ስንፍናን አስፋፍተዋል። ከዘመናት በኋላ ዛሬ ከእንቅልፋችን ነቅተን መስራትና መልማት ስንጀምር ሊያመልጡን ነው በሚል እሳቤ በርትተው እየታገሉን ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትንሽ የመስራታችን ተጨባጭ ውጤትና ማስረጃ ነው። ፕ/ር ባህሩ እንዳለው ኢትዮጵያ ለዘመናዊ ትንሳዔዋ የበቃችው ግብጽን ለመቋቋም ባደረገችው አጸፋዊ እንቅስቃሴ ነው።

የኢትዮጵያ መንቃት

ኢትዮጵያ የዉሃ ሃብቷን አልምታ ከድህነት መውጣት እንደምትችል መገንዘብ የጀመረችው ዘግይታ ነው። ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ምንነት የዳበረ ንቃተ-ህሊና የተፈጠረውም ቀሰ በቀስ ነው። ዉሃንና የዉሃ ፖለቲካን የማጥናትና በዘርፉ ምርምር ማካሄድ የቅርብ ጊዜ ተሞክሮ ነው። አገሪቱ የአባይን ወንዝ ለፖለቲካ ዓላማ ግብነት የመጠቀም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከንድፈ-ሐሳብ ባለፈ በተግባር አድርጋ አታውቅም። በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ መሪዎች የተደረጉ ንግግሮችና መንግሥታዊ ሰነዶች ውስጥ ዉሃ በፈጣሪ ለፍጡራን ሁሉ በነጻ የተሰጠ በረከት እንደሆነ ተገልጿል። ከዚያ ባለፈ ኢትዮጵያ ወንዞቿ ታላቅ የተፈጥሮ ስጦታዎች መሆናቸውን በቅጡ በመረዳት ለልማትና ለህዝብ ኑሮ መሻሻል ለማዋል የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ከጥቂት አስርት ዓመታት የዘለለ ጊዜ ያስቆጠሩ አይደሉም።

አሁን ሁኔታዎች መለወጥ ጀምረዋል። ኢትዮጵያ ለመልማት በቅድሚያ የዉሃ ሃብቷን ማልማት እንዳለባት እየተገነዘበች ነው። የዉሃ ሃብታቸውን ያለሙ አገሮች አድገዋል። የዉሃ ሃብታቸውን ያላለሙ ወይም በቂ የዉሃ ሃብት የሌላቸው አገሮች ኋላቀር ለመሆን ተገደዋል። የዉሃ ሃብትን ማልማት የአንድ አገር ቀዳሚ ግዴታ ነው። ለዚህም የማልማት ግዴታ የህዝብ ቁጥር መብዛት፣ የኢንዱስትሪዎች፣ ፋብሪካዎች፣ ዘመናዊ እርሻዎችና የከተሞች መስፋፋት ምክንያቶች ናቸው። ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ በአየር መዛባት ምክንያት በተደጋጋሚ በተከሰቱ ድርቅና ችጋር ምክንያት የብዙ ዜጎች ህይወት ማለፉ የዉሃ ሃብትን የማልማት ግዴታን የሚጠቁሙ ምክንያቶች ናቸው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ወሰን ተሸጋሪ ወንዞቿን ለልማት ለማዋል የምትመራበት ግልጽ የዉሃ አስተዳደር ፖሊሲ አላት። የፖሊሲው ሰነድ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞችን በሚመለከት በንዑስ አንቀጽ 2.2.8 ተራ ቁጥር 4 የገለጸው “በርትዓዊና ፍትሐዊ የአጠቃቀም መርሆች መሠረት ወሰን ተሻጋሪ ዉሃዎችን በጋራና አባካኝ ባልሆነ መንገድ ለመጠቀም ከዉሃዎቹ ተጋሪ አገሮች ጋር ትርጉም ያላቸውና የጋራ ጥቅምን የሚያስገኙ ፍትሀዊ የሆኑ ቀጠናዊ ትብብርና ስምምነቶችን ማሳደግ” ነዉ ይላል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ የአባይ ወንዝን በሚመለከት “ከግብጽ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ተወደደም ተጠላም የአባይ ጉዳይ የግንኙነቱ ማዕከል መሆኑ አይቀርም። በዚህም ረገድ የምንከተለው ፖሊሲ የአባይ ጉዳይ ጥቅሞችን በማጣጣም መርህ በሰላምና በድርድር የልማት እንቅስቃሴያችንን በማይጎዳ መልኩ እንዲፈታ፤ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች በቂ ጊዜ በሚሰጥ አኳኋን እንዲታዩ ማድረግ ይሆናል” ይላል። ይህም ነባሩ ሁኔታ እየተቀየረ መምጣቱን ያመለክታል። በርካታ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የዉሃ ፖለቲካ ምርምር ስራዎች እንደሚያሳዩት አንድ የግርጌ ተፋሰስ አገር (ግብጽ) በራስጌ ተፋሰስ አገር (ኢትዮጵያ) ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ ያሳደረበት ብቸኛው ክስተት ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው። ኢትዮጵያ ፍትሀዊና ርትዓዊ የዉሃ አጠቃቀም ፖሊሲን ተከትላ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿና በዉሃ ሃብቷ መጠቀም ስትጀምር እንዲሁም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስትገነባ ነባሩ ኢፍትሀዊ ግንኙነት ለአዲስ ዓይነት ግኑኝነት ስፍራ እየለቀቀ መሆኑን ይጠቁማል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top