ታሪክ እና ባሕል

ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረገ፣ ጀግናውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ያከበረ አቀባበል!!

እንደ መንደርደሪያ

ኢትዮጵያ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀዉ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ዉድድሮች በምታስመዘግበዉ ድሎች ነዉ። ቀሪዉ ዓለም የኢትዮጵያውያን ረጅም ርቀት ሯጮች ስሞችን በደምብ ያዉቃቸዋል። ከሮም እስከ ሞስኮ፣ ከሜክሲኮ እስከ ቶኪዮ፣ ከሲዲኒ እስከ አትላንታ፣ ከባርሴሎና እስከ ዶሃ… ወ.ዘ.ተ. በክብር እንዲውለበለብ ያደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችን ይጠቀሳሉ። አበበ ቢቂላ፣ ዋሚ ባራቱ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ በላይነህ ዴንሳሞ፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ… እንዲሁም እዚህ ጋር በስም ያልተጠቀሱ ሌሎች ጀግና አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠሩ አኩሪ ድሎችን አስመዝግበዋል።

አበበ ቢቂላ፤ በ1960 (እ.ኤ.አ.) በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ ያስመዘገበዉ አንጸባራቂ የማራቶን ድል መቼም ቢሆን የማይረሳና “ዳግማዊ ዓድዋ በሮም አደባባይ” ያሰኘ አንጸባራቂ ድል ነበር። አበበ ቢቂላ ያስመዘገበዉ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካን በመወከል በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ በጥቁር አትሌት የተገኝ የወርቅ ሜዳሊያ በመሆን በታሪክ ሠፈሯል።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ያሰብከው ባይሳካም የሁልጊዜ ጀግናችን ነህ!

በኦሎምፒክ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ መንደር የሀገራችን ኢትዮጵያ ስም ከፍ ካደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችን መካከል አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በግንባር ቀደምትነት ስሙ ይጠቀሳል። አትሌት ቀነኒሳ ከጠንካራ መንፈሱና ከፍ ካለው የአሸናፊነት ስነ-ልቦናው ባሻገር ሰብአዊነቱ፣ ቀናነቱና መልካምነቱ ከፍ ይላል። የሲዲኒ ኦሎምፒክ የምንጊዜም የረጅም ርቀት የዓለም ጀግና የሆነውን ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴን ወደኋላ ዞሮ በዓይኑ እያማተረ ጀግናቸው ከጎናቸው እንዳይለያቸው በማሰብ ያሳየው ጥልቅ የሆነ ፍቅር፣ የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የመተሳሰብ መንፈስ የብዙዎችን ልብ በፍቅር የረታ ነበር ማለት ይቻላል።

ይህን የመተሳሰብና የኢትዮጵያዊ አንድነት መንፈስ ወኔውን የቀሰቀሰው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ከድሉ ማግስትም የተዜመለትን “ቀነኒሳ አንበሳ” ዜማም ከዚሁ ኢትዮጵዊነት የአንድነት፣ የፍቅርና የመተሳሰብ ጥልቅ የፍቅር ስሜት ውስጥ የተቀዳ ዜማ ነው። ይሄን ዜማ ስንሰማ በውስጣችን ልዩ ሐሴት ይሰፍናል። ጀግናው አትሌት ቀነኒሳም ይህን ዜማ ለውለታው የተዜመ ልዩ ስጦታው አድርጎ እንደሚቆጥረው ደጋግሞ ተናግሯል።

“እልል በል ያገሬ ጎበዝ ለእምዬ ውለታ
ወርቅ አመጣሁላት ልጇ ለክብሯ ስጦታ…”

“… ይቺ ባንዲራ (አንበሳ)ናት ዕድለኛ፣
ዛሬም አኮራት (አንበሳ)ቀነኒ ኬኛ…”

በረጅም ርቀት ውድድር የመጨረሻውን ዙር እንደ አጭር ርቀት የሚደመድም፤ በታላላቅ የውድድር መድረኮች በከፍታ የነገሠ፣ እንደ አቦ ሸማኔ በፈጠኑ ጠንካራና ቀጫጭን እግሮቹ ተዓምር የሠራ፤ የአገሩን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በክብር ከፍ አድርጎ ያወለበለበ፤ ሕዝብ በእርሱ ድል እንዲፈነድቅ፣ ከያኒው ስለሱ አብዝቶ እንዲቀኝ ምክንያት የሆነ ኮከብ አትሌት ነው ቀነኒሳ በቀለ። ትጋት ጥንካሬና ፍጥነቱ “አንበሳው” የሚል ቅጥያ ያንሰዋል። ሀገር የሰጠውን ታላቅ አደራ አተልቆ የከፈለ ጀግና ነውና!!

ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ በርሊን በተካሄደው ማራቶን በ2፡01፡41 ሰዓት ውድድሩን አሸንፎ የነበረው ቀነኒሳ የለንደኑ ከዚያ በኋላ ሁለተኛ ውድድሩ ቢሆንም በዚህ ውድድር ላይ አለመሳተፉ ዜና ሲሰማ ብዙዎችን አሳዝኖ ነበር። ራሱ ቀነኒሳም ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ በሕመም ምክንያት በለንደኑ ማራቶን ላይ ባለመሳተፌ በጣም አዝኛለሁ ሲል ተናግሯል። በዚህ በለንደኑ ማራቶን ላይ ቀነኒሳ ባይሳተፍም ብዙም ግምት ያልተሰጠው ኢትዮጵያዊው ሹራ ቂጣታ አሸናፊ በመሆን ሁላችንንም አኩርቶናል።

አንበሳውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ያከበረ አቀባበል!!

በለንደኑ ማራቶን በሕመም ምክንያት ያልተሳተፈውን ጀግናውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ‘‘ምንም እንኳ ሕልምህ ባይሳካም ለሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ለእኛ የሁልጊዜም ጀግናችን እና ኩራታችን ነህ!’’ በሚል የአካባቢው፣ የሰፈሩ የላምበረት ልጆች የጀግና አቀባበል አድርገውለታል። የላምበረት ሰፈር ወጣቶች አስተባባሪ የሆነው ደጉ መኮንንና ጓደኞቹ ለጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከዋናው አስፋልት እስከ መኖሪያ ቤቱ ድረስ በሀገራችን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና አትሌቱ በተለያዩ የኦሎምፒክ መድረኮች ያሸነፈባቸውን ፎቶግራፎች ‘‘ያሰብከው ባይሳካም የሁልጊዜ ጀግናችን ነህ’’ በሚል ጥቅስ ባሸበረቀ ቢልቦርድ አካባቢውን አስውበው ነበር ጀግናውን አትሌት ከፍ ያደረጉት።

ይህ በብዙዎቹ ኢትዮጵውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን መሥዋዕትነት የከበረው ሰንደቅ ዓላማችን በጀግኖች አትሌቶቻችን በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ ስናየው ወኔን ያስታጥቃል፣ ታታሪነትንና የአልበገር ባይነተ ስሜትን ያጎናፅፋል። ከምንም በላይ ለባንዲራው ክብር ሲባል እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት የተከፈለበት መሆኑን ስናስብ፤ ውስጣዊ ስሜታችንን ኮርኩሮ ለተግባር እንደሚያነሳሳን ልንክደው የማይቸለን ሐቅ ነው። ሀገራችን ከጀግንነቷ ጀርባ ባንዲራዋ ዓርማዋ ሆኗል። ጀግኖች አትሌቶቻችን ለአሸናፊነት ሲበቁ ቀዳሚ ተግባራቸው የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ባይናቸው እያማተሩ መፈለግ ነው። ካገኙትም በኋላ ባንዲራውን በኩራት፣ በጥልቅ ስሜትና ፍቅር ተከናንበው ስቴዲዮሙን እየዞሩ እያውለበለቡት በመሮጥ ለሚመለከታቸው የዓለም ሕዝብ ያሳያሉ። ይሄ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ ዛሬ ላይ ወደ ባህል ወይም ልማድነት ተሸጋግሯል። ምሥጢሩም የሀገር ክብርን ፈላጊነት፣ የሀገር ፍቅርን ግለት፣ የማንነትን ተግባር አስመስክሮ ለማሳወቅ የሚደርግ ክዋኔ ነው።

ስመጥር ጀግኖች አትሌቶቻችን ድል አድርገው የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ፤ በሀገራችን ብሔራዊ መዝሙር ታጅቦ ወደ መስቀያው አናት ሲያሻቅብ ሲመለከቱ፤ የደስታ ሳግ ተናንቋቸው የእንባ ዘለላቸውን ከጉንጫቸው የሚያፈሱ ጀግኖች አትሌቶቻችንን መመልከት፤ የባንዲራን ስሜት ኮርኳሪነትና ኃያልነት ይመሰክርልናል።

የላምበረት ወጣቶች አስተባባሪና ይህን ለቀነኒሳ በቀለ የተደረገውን አቀባባል በማስተባባር ግንባር ቀደም ሚና የነበረው ደጉ ሲናገር “እኔና የላምበረት ሰፍር ልጆች ለጀግናው አትሌት ያለንን ፍቅርና ክብር ለመግልጽ ያነሳሳን ምክንያት፤ የኢትዮጵዊነት የአሸናፊነት መንፈስ፣ ሰው የመሆን ክብር እና ጀግኖች አትሌቶቻችን በኦሎምፒክ አደባባይ በተደጋጋሚ በክብር ከፍ ያደረጉት የሀገራችንን ሰንደቀ ዓላማ ለሁላችንም ኢትዮጵውያን የኩራት ምንጭና የአንድነታችን ተምሳሌት በመሆኑ ነው” ይላል።

ሌላው ይላል ደጉ፤ ቀነኒሳ በሚኖርበት በላምበረት አካባቢ በበጎ ሥራ ላይ የሚሳተፍና ለማንኛውም ችግር ደራሽና ተባባሪ፣ ሰብአዊነት የሚሰማው ‘‘ለወገን ደራሽ ወገን ነው’’ የሚል ቀና አስተሳሰብ ያለው ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሰው መሆኑ ነው። በርግጥም የላምበረት ሰፈር ልጆች በሰፈራቸው ደጋፊ የሌላቸውን፣ አቅማቸው ደካማ የሆኑትን አረጋውያን ወገኖችንና ቤተሰቦችን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት በማገዝ ረገድ አትሌት ቀነኒሳ ሁሌም ከጎናቸው የሚቆም መሆኑን ይመሰክሩለታል። ይህም ድጋፍ የተደረገላቸው አቅመ-ደካሞችና አረጋውያን ወገኖች የመሰከሩት እውነታ ነው።

ለአብነትም የላምበረት ሰፈር ወጣቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ ያደረጉትን እንቅስቃሴ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በሞራልና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ከአንዴም ሁለቴ ከጎናቸው በመሆን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ እያደረገም ነው። አትሌት ቀነኒሳ በተለያዩ መድረኮች እንደገለጸው፤ ቀለል አድርጎ መኖር እና የተካበዱ ጉዳዮችን ሳሳ አድርጎ ማየት፤ የአትሌቱ የኑሮ ፍልስፍናና ልምድ ነው። አዳዲስ ሞዴል ዘመናዊ አውቶሞቢሎችን የራሱ የማድረግ አቅም አለው፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ አይወድም። የመረጠው ቦታ ላይ ቅንጡ ኑሮን መምራት ይችላል፤ ያን መሆን ግን አይፈልግም። ቀለል ያለ ህይወት ምቾት እንደሚፈጥርለት ይናገራል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በህይወቱ ለቤተሰቡና ለሀገሩ ያለው ፍቅርና ክብር እጅግ ከፍ ያለ ነው።

እንደ ማጠቃለያ

የላምበረት ሰፈር ወጣቶች ከየካ ክፍለ ከተማና ከወረዳቸው የሥራ ኃላፊዎች፣ ከአካባቢያቸው ባለሀብቶች፣ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ የሰፈራቸው ኢትዮጵውያን ወገኖቻቸው ባገኙት ትብብርና ድጋፍ ለብዙዎች ተምሳሌነት ያለው ሥራ እየፈጸሙ ነው። ‘‘ወገን ቢረዳዳ ችግርም አይጎዳ፣ ጋን በጠጠር ይደገፋል’’ የሚለውን የቆየውን የኢትዮጵያውንን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል መሠረት በማድረግ በአካባቢያቸው እያደረጉት ያለው የበጎ ሥራ እንቅስቃሴ ለብዙዎች ወጣቶች መልካም አርአያ መሆኑ አሌ አይባልም። እንደ ቀነኒሳ ያሉ የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ ያደረጉ ጀግኖቻችን ለወገኖቻቸው እያደረጉት ባለው በጎ አስተዋጽኦ ክብርና አድናቆት ይገባቸዋል።

“ሰዎች ሌሎች የደግነት ተግባርን ሲፈጽሙ ሲመለከቱ ተመሳሳዩን ለመፈጸም ይነሳሳሉ” ይላሉ ባለሙያዎች። ስለዚህ የምንፈጽማቸው በጎ ነገሮች በእኛ ድርጊት ላይ ብቻ የሚቆሙ ሳይሆኑ፤ በሌላ ጊዜ ለሌሎች ሰዎች በሌሎች እንዲፈጸሙ እያገዝን መሆኑን መረዳት ያስፍልጋል። ግጭቶችና ጥላቻ በተበራከተበት ዓለም የመልካምነት ድርጊቶች ጎልተው ይሰማሉ። ያዩ የሰሙ እንዲሁም የተደረገላቸው ጭምር ሳይቀሩ ደግ ማድረግን ይለምዳሉ፤ ለሌሎችም ያስተላልፋሉ። በአንደኛው የዓለም ክፍል የሚፈጸም የደግነት ተግባር አየርና ባሕሩን አቋርጦ ከአድማስ ባሻገር በመጓዝ በሌላ ቦታ ይሰማል ይፈጸማል። ለዚህ ነው ደግነት/መልካምነት ተላላፊ ነው የሚባለው።

ክብር የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ላደረጉ ለጀግኖች አትሌቶቻችን!

መልካምነት ለራስ ነው! ሰላም!

(ይህን የላምበረት ሰፈር ወጣቶችን መልካምነት አርአያ ያለውን ሥራ መረጃውን በማድረስና ከላምበረት ሰፈር ወጣቶች ተወካይ የሆነውን ደጉ መኮንን በማገናኘት ረገድ፣ የሰፈሩ ነዋሪና የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ድኅረ-ምረቃ ቤተ-መጻሕፍት Head Librarian የሆነችው ወ/ት ይታይሽ ሹመት ቀና የሆነ ትብብር አድርጋለች።)

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top