ታሪክ እና ባሕል

በሽምግልና ባህላችን ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶች

በፍላጎት፣ በእሴትና በአመለካከት ልዩነቶች ምክንያት በግለሰብ፣ በጎሳ፣ በብሔረሰብ ወይም በፓርቲ መካከል አለመግባባት ይከሰታል። አለመግባባቱ ሰፍቶ ወደ ግጭት ይገባል። ግጭቱም የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት በተለያዩ ዘዴዎች በቁጥጥር ስር እንዲውል ጥረት ይደረጋል። ከእነዚህ መንገዶች መካከል ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም አንዱ መንገድ ነው።

በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ዘንድ ከሚገኙ ባህላዊ እሴቶች መካከል የሽምግልና ባህል አንዱ ነው። በሽምግልና ባህል መሰረት የእርቅ ስርዓቱ፣ ስርዓቱ ያለው አወቃቀር፣ የአስታራቂ አካላት ድርሻ፣ አስታራዊ አካላት ያላቸው ስያሜ፣ ማህበራዊ ደረጃ፣ ግጭቶቹ ባላቸው መጠን መሰረት ጉዳዩን የሚያየው አካል በየብሔረሰቡ የተለዩና የታወቁ ናቸው። የሽምግልና ባህላችን የተለያዩ አካላት ወደ ግጭት ሲገቡ፣ ግጭቱ ተባብሶ የከፋ አደጋ ከማስከተሉ በፊት መቆጣጠር የሚያስችሉ አይነተኛ የሰላም ዋስትና ነው።

በሽምግልና ባህል አማካኝነት የተፈጸሙ ወንጀሎች ይጣራሉ፣ አጥፊው ወገን ይለያል፣ የጉዳት መጠን ይለያል። እንደባህሉም በሀገር ሽማግሌዎች፣ በኃይማኖት አባቶች፣ በአባ ገዳዎች፣ በአበጋሮችና በማህበረሰቡ ውስጥ ልዩ ክብር በሚሰጣቸው መሰል አካላት የተከሰቱ ግጭቶች ይበርዳሉ፤ የተጋጩ ወገኖች ይታረቃሉ። ይህ ባህል ማህበረሰቡ ለዘመናት ያካበተውን ልምድ፣ እውቀት፣ የሕይወት ዘመን ተመክሮ መነሻ በማድረግ የመንደሩን፣ የአካባቢውን፣ የብሔረሰቡን እንዲሁም የአገርን ሰላም ሲያስጠብቅ ለዘመናት ቆይቷል፤ አሁንም እያስጠበቀ ነው።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች ተባብሰው ለአገር ሰላምና አንድነት እንቅፋት ከመሆናቸው በፊት የሽምግልና ባህልን መሰረት በማድረግ በቀላሉ መፍታት ያስችላል። ነገር ግን የሽምግልና ባህልን በአግባቡ ተግባራዊ እንዳይደረግና ያለውን ከፍተኛ ሀገራዊ ሚና እንዳይወጣ የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉበት። ይህ ጽሑፍ የሽምግልና ባህላችንን በአግባቡ ለመጠቀም ተግዳሮት የሆኑ ሶስት አብይ ጉዳዮችን ለማሳየት ያለመ ነው።

I. ሕጋዊ እውቅና መነፈግ

በአገራችን ባለው መደበኛ አሰራር በሚፈጠሩ ግጭቶችና በሚፈጸሙ ወንጀሎች ዳኝነት የሚሰጠው አካል በመንግስት የተቋቋመ መደበኛ ፍርድ ቤት ነው። መደበኛ ፍርድ ቤት የተከሰተውን ወንጀል አጣርቶ ጥፋተኛ የሆነን አካል ‹‹አስተማሪ›› ነው የሚለውን ቅጣት ይቀጣል። ለተጎጂ ወገን ካሳ የሚያሰጥ ከሆነም ካሳ ያሰጣል። ይህ የመደበኛ ፍርድ ቤት አሰራር ወደ ግጭት የገቡ አካላት እርቅ ስለመፈጸም ወይም ወደ ፊት ሊከሰት የሚችልን ቂም በቀል ለማስቀረት አቅም የለውም። እርቅ ለማስፈጸም ሆነ ቂም በቀልን ለማስቀረት ባህሪው አይፈቅም። በዚህም ምክንያት ግለሰቦች ጥፋተኛ ተብለው የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ወይም የተጣለባቸውን ቅጣት ከተቀጡ በኋላ ወደ በቀል የሚገቡበት ሁኔታ የተለመደ ነው።

የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናቴን በባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ላይ በምሰራበት ወቅት የገጠመኝ አንድ ማሳያ (case) ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል። ይህም በአንድ ወቅት በግለሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት ነፍስ ይጠፋል። ገዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት ተከስሶ፣ የአስራ ስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶበት ማረሚያ ቤት ይገባል። የሟቹ ወንድም ጠያቂ መስሎ ፍርደኛውን በማረሚያ ቤት ገደለ። እሱም ተፈርዶበት ገባ። እንደገና የሟች የአጎት ልጅ በተመሳሳይ የገዳዩን ወንድም ገደለ። በዚህ ሁኔታ በሶስት ዓመት ውስጥ ብቻ ከሁለቱም ወገን የአምስት ሰው ሕይወት ጠፋ። ይህ ማሳያ መደበኛ ፍርድ ቤት አጥፊውን የመቅጣት ስራ እንጂ ወደ ግጭት በገቡ ወገኖች መካከል እርቅ እንዲፈጥር፣ ዘላቂ ሰላም እንዲኖርና ቂም በቀል እንዳይገቡ የማድረግ አቅም እንደሌለው ያስረዳናል። ይህን ክፍተት የሚሞላው ባህላዊ የሽምግልና ስርዓት ነው። በባህላዊ መንገድ፣ በሀገር ሽማግሌ፣ በባህላዊ ስርዓት የተፈጸመ እርቅ አጥፊውን ከመቅጣት፣ ተጎጂውን ከማስካስ ባለፈ ከቂም በቀል የጸዳ ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍን ነው። ይህን መሰል ክፍተት የተፈጠረው መደበኛ ፍርድ ቤት ለባህላዊ የሽምግልና ስርዓት እውቅና ለመስጠትና ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ ክፍተት በመኖሩ ነው። ይህ የሕግ ክፍተት በአገሪቷ በሚገኙ ሕግጋት ውስጥ በስፋት የሚገኝ ነው። ለምሳሌ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገመንግስት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ‹‹ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር በመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም›› ተብሎ ተደንግጓል።

በሕገመንግስቱ አንቀጽ 91 ንዑስ አንቀጽ 1 ‹‹መንግስት መሰረታዊ መብቶችን፣ ሰብዐዊ ክብርን፣ ዲሞክራሲንና ሕገ መንግስትን የማይቃረኑ ባህሎችና ልማዶች በእኩልነት እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ የመርዳት ኃላፊነት አለበት›› ተብሎ ተደንግጓል። የእነዚህን ባህላዊ ደንቦችና ባህሎች አሰራርን በተመለከተ አንቀጽ 34 (5) ‹‹ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል›› ቢልም ይህን የሚመለከት ዝርዝር ሕግ እስካሁን አልቀረበም። ይህ የሕግ ክፍተትም ባህላዊ ሽምግልና ከሕጎችና ከፍርድቤት ስራ ጋር በምን እንደሚጻረር በግልጽ የቀረበ ሀሳብ እንዳይኖር አድርጎታል።

የሽምግልና ባህላችን እውቅና ቢኖራቸውና የመደበኛ የፍርድ ቤት ስርዓትን መብትና ስራ በማይጋፉ መልኩ ሊሰሩ የሚችሉትን የስራ ድርሻዎች በግልጽ ለይቶ በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርጉ አልሆነም። ይህም ባለመሆኑ ሊሰጡ የሚችሉትን ሁ ለ ን ተ ና ዊ ሀገራዊ ጠቀሜታ በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም። መደበኛ ፍርድ ቤትና ባህላዊ የሽምግልና ስርዓት ተ ደ ጋ ግ ፈ ው እንዲሰሩ ለሽምግልና ስርዓት በህግ እውቅና በመስጠትና በመጠቀም ከፍተኛ ውጤት ያመጡ በርካታ አገራት አሉ። የእነዚህን አገራት ተሞክሮ መነሻ በማድረግ የሕግ ማሻሻያ ስራዎች ቢሰሩ ለአገር እድገትና ለዘላቂ ሰላም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

II. የእሳቤ መጣረስ

የሀገር ሽማግሌ የሚለው ቃል ‹‹ሀገር›› እና ‹‹ሽማግሌ›› የሚሉ ሁለት እሳቤዎችን (concepts) የያዘ ነው። እነዚህን ሁለት እሳቤዎች በተሳሳተ መልኩ በመረዳት ያላቸውን ትክክለኛ ትርጓሜያቸውን ሲያጡ ይስተዋላል። እሳቤዎቹ እንዴት በተሳሳተ መንገድ እንደታዩ በአጭሩ እንመልከት። በ ‹‹ሀገር ሽማግሌ›› ውስጥ አንደኛው እሳቤ ‹‹ሀገር›› የሚለው ቃል ነው። ቃሉ የሚገልጸው በውስኑ ቤተሰብን፣ መንደርን ነው። በስፋት ሲታሰብ ደግሞ ሀገርን ነው። ሀገር የጋራ ነው። ሀገር የወል ሀብት ነው። ሀገር የእከሌ ነው አይባልም፣ ሀገር የሁሉም ነው። ‹‹የሀገር ሽማግሌ›› ስንልም የሁሉምነት ነው። የጋራነት ነው። የእኛነት ነው።

የሀገር ሽማግሌ የሆነ ግለሰብ የጋራ ሃብት ነው። የአንዱ ወገን ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ወገን ነው። የሁሉም ተወካይ ነው። አንድ ግለሰብም የሀገር ሽማግሌ ነው ሲባል የሁሉም የሆነ እንጂ የጥቂቶች ብቻ አይደለም። ሀብትነቱ የጋራ እንጂ የከፊሎች አይደለም። የሚያገለግለው ሁሉንም በእኩል ነው። ፍትሃዊ ነው። እውነተኛ ነው። እሳቤው ይህ ነው። የ‹‹ሀገር ሽማግሌ›› በሚል የማዕረግ ስም የሚጠሩ ግለሰቦች የራሳቸው ግላዊ አቋም ሊኖራቸው አይገባም። ያላቸው የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና ግላዊ አቋም ቦታ የለውም። ያላቸው አቋም የሚኖረው ግለሰብ እያሉ ነው። ከግለሰብ ደረጃ ወደ ሀገር ሽማግሌ ደረጃ ከፍ ካሉ በኋላ የሚታዩት በሌላ እሳቤና ማዕቀፍ ነው። በመሆኑም የሃገር ሽማግሌ ከሆኑ በኋላ የግል የሚሉት አቋም አይኖርም። ምክንያቱም የሃገር ናቸው። የሚያስቀድሙት የሃገር ፍላጎትን እንጂ የራሳቸውን አይደለም። አንድ ግለሰብ የሃገር ሽማግሌ የሚል ትልቅ ኃላፊነትና ማዕረግ ተሸክሞ የገዢውን ፓርቲ የፖለቲካ አቋም ለማስፋፋት ወይም ለመቃወም፣ ለፓርቲው ያላቸውን ፍቅር ወይም ጥላቻ ለመግለጽ ወይም የአንድ ሃይማኖትን ቀኖና ሊደግፍ ወይም ሊቃወም አይችልም። የሃገር ሽማግሌ ነውና።

የሃገር ሽማግሌ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ወይም የገዢ ፖለቲካ ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ሲጠራ የማዕረግ ልብስ ለብሶ፣ ጭራ ወይም አለንጋ ይዞ፣ የፓርቲ መሪውን ግንባር ሲስም፣ ፓርቲውን ለዘለዓለም ኑርልን ብሎ ሲመርቅ፣ ስዩመ-እግዚአብሔር እያሉ ሲያንቆለጳጵሱ መስማትም ሆነ ማየትን ያህል አሳፋሪ ነገር የለም። የሀገር ሽማግሌ የገዢ ወይም የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይልን ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመቀበል የካድሬ ስራ ሲሰራ ማየት ያሳፍራል። የሀገር ሽማግሌ በባህሉ የተሰጠውን ሚና ከመወጣት አልፎ ከባህል፣ ከደንብና ከወግ አፈንግጦ የፖለቲካ ፓርቲ ተለጣፊነትና የተላላኪነት ባህርይ ሲያንጸባርቅ መገኘት ፍጹም ነውር ነው። የሀገር ሽማግሌ መሆን የሀገር ሀብትነት እንጂ የጥቂት ቡድን፣ ማህበረሰብ፣ ፓርቲ ወይም ኃይማኖት ተወካይ አይደለም። የአንድ ቡድን ነጻ አውጪ አይደለም። ይህ ሁኔታ ግለሰባዊነትን ከሀገር ጋር ያጣረሰ የእሳቤ ስህተት ነው። ሀገር እኮ ብዙ ነው። ሀገር ብዙ ፍላጎት፣ አቋም፣ ልምድና አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች የሚኖሩበት የጋራ ቤት ነው። በሀገር ሽማግሌነት ካባ የራስን ወይም የጥቂቶችን አቋም ማንጸባረቅ የሕዝብ ሀብትን ለግል ጥቅም ማዋል ነው። ይህ ደግሞ ወንጀል ነው። የሀገር ሽማግሌ ሆኖ ወገንተኛ መሆን ነውር ነው። ሐቅን ይሸራርፋል። ፍትህን ያዛባል። ቃልን ያሳጥፋል። በጥቅም ብኩርናን ያሸጣል። በሕዝብ ዘንድም ክብርና ሞገስን ያስገፍፋል። ሁለተኛው፣ በ‹‹ሀገር ሽማግሌ›› ውስጥ ‹‹ሽማግሌ›› የሚለው ቃል ላይ ያለ እሳቤ ነው። የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም በእድሜ የገፋ፣ ትልቅ ሰው፣ ያረጀ፣ አዛውንት የሆነን የሚገልጽ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን በሀገር ሽማግሌ ውስጥ ‹‹ሽማግሌ›› የሚለው ቃል አስታራቂ፣ አስማሚ፣ አቻቻይ፣ ፍትሃዊ፣ ታማኝ፣ ተከባሪና የሀገር ሀብት የሚሉትን እሳቤዎች የሚገልጽ ነው። እነዚህን ባህርያት ያሟላ የተከበረ ግለሰብ ማለት ነው፤ ሽማግሌ። እነዚህን መልካም ባህርያት የሚያሟላና በማህበረሰቡ አባላት ዘንድ የተመረጠ ማንኛውም ግለሰብ የሀገር ሽማግሌ ነው። እድሜው ወጣት፣ ጎልማሳ ወይም አዛውንት ሊሆን ይችላሉ። በአብዛኛው ስለሀገር ሽማግሌ ስናስብ በእድሜ የገፋ ግለሰብን እንጂ ወጣትን አናስብም። በእርቅ ወቅት ወጣቶች እንዲሳተፉ አናደርግም። ወጣቶች የእርቅና የሰላም ልዑክና እንደራሴ መሆናቸውን አንረዳም። የሀገር ሽምግሌነት መስፈርት ልምድ፣ እውቀት፣ ሚዛናዊነት፣ ከአድሎ ነጻ መሆን እንጂ የእድሜ መግፋት ብቻ ተደርጎ መታሰቡ ስህተት ነው። ይህ የእሳቤ ስህተት በመንግስት ደረጃም ይንጸባረቃል። ለዚህም አንዱ ማሳያ በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ይፈታል በሚል በ2011 ዓ.ም. በአዋጅ በተቋቋመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት መካከል ወጣቶች ምን ያህል ቁጥር እንዳላቸው ማየትና በተለያዩ ወቅቶች በመንግስት ደረጃ የተካሄዱ በእርቀ-ሰላም ውይይቶች ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን መመልከት ብቻ በቂ ነው። ይህ በራሱ ወጣቶች በአገር ሰላም ግንባታ ላይ ያላቸውን የሀገር ሽማግሌነት ሚና ከግምት አለመግባቱን አመልካች ነው።

III. የስብዕና መንጠፍ

በማህበረሰቡ የሀገር ሽማግሌነት ክብር ነው። ማህበረሰቡ ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖር፣ ማንነቱን ጠብቆ እንዲቆይ፣ ችግር ሲፈጠር ችግሩን ለመቅረፍ የሀገር ሽማግሌ ወሳኝ ነው። መሸምገል የሚለው እሳቤ በራሱ መብሰልን፣ አርቆ ማስተዋልን፣ አለማዳላትን፣ ፍትሃዊነትን የሚገልጽ ነው። ሽማግሌ የክብር ተምሳሌት ነው። ሽማግሌ የህብረተሰብ ማንነት ቀራጭ ነው። የሀገር ሽማግሌ ማህበረሰብን ከእልቂት የሚያድን ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች እርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው፣ መሬት ተንበርክከው በስሜት የገነፈለን ሕዝብ ከጥፋት ሲያድኑት አይተናል። ይህን የሽማግሌ እሳቤ ባለመረዳት በሀገር ሽማግሌ ላይ የሚፈጸም ክብረ-ነክ ነገር የማህበረሰብን ማንነት ማዋረድ ነው። ሀገር ሽማግሌን መናቅ ማህበረሰቡን መናቅ ነው። በተለያዩ ወቅቶች የሀገር ሽማግሌዎች ተዋረዱ፣ ተደበደቡ፣ ታገቱ እና መሰል ነገሮችን ሰምተናል፤ አይተናል። እውነት ይህን ዓይነት አሳፋሪ ድርጊት በሀገር ሽማግሌዎች ላይ ተፈጽሞ ማየትም ሆነ መስማት ያማል። በተመሳሳይ ‹‹የሀገር ሽማግሌዎች›› የእንቶኔ ፓርቲ መግለጫ ሲሰጥ ተገኙ፣ ‹‹የሀገር ሽማግሌዎች›› ከእነ እንቶኔ ጋር አትገበያዩ፣ አብራችሁ ቡና አትጠጡ የሚል መግለጫ አወጡ እና መሰል ነገሮችን ሰምተናል፤ ዓይተናል። ይህን አይነት አሳፋሪ ድርጊት በሀገር ሽማግሌዎች ስም ተፈጽሞ ማየትም ሆነ መስማት ያሸማቅቃል። እነዚህ ዓይነት ድርጊቶች ከሰውነት መውጣት ማሳያ ናቸው። የስብዕና መንጠፍ (dehumanization) ውጤቶች ናቸው። የሀገር ሽማግሌነትን ያራክሳል። የማህበረሰብ ልዩ ምልክቶችን ያዋርዳል። እንደ ሀገር ያዋርዳል። አንገት ያስደፋል። የማህበረሰብ ማንነት መሰረትን ያናጋል። ለሽምግልና የምንሰጠውን ልዩ ክብር ያጠፋል። ነገ ለሚከሰት ችግር ተው ባይ ይታጣል። ተው ባይ ከታጣ እልቂት ነው። እልቂት ውጤቱ እልቂት ነው። ሁሉንም ያጠፋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top