ታዛ ወግ

የጎን አጥንት

በድሮ ዘመን ነው አሉ.. ድሮ የሚባለው ዘመን መጀመሪያ ላይ.. አማልክት አንድን ሰውዬ አስክረው፣ የሆነ ነገር አቅምሰው.. ወይም ደግሞ ሰውዬው ከባድ እንቅልፋም ነበር ይሆናል.. በተኛበት የጎን አጥንቱን ሰረቁት። የግል ተበዳይ አቶ ሰውዬ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በየመንገዱ፣ በየቤቱ (ትምህርት ቤት፣ መስሪያ ቤት፣ ምግብ ቤት፣ ቡና ቤት፣ ጠንቋይ ቤት… )፣ እንደገና በየመንገዱ አጥንቱን ሲፈልግ ሊያገኘው አልቻለም። በርግጥ ፈለኩት አለ እንጂ ሲፈልግ ያየው የለም። እንደውም.. ተሰረቅኩ አለ እንጂ.. እረ እስከነጭራሹ ሲጀምር ያልነበረውን አጥንት ይሆናል ይሄኔ የሚፈልገው። “ሰውን ማመን ቀብሮ ነው” አለ.. ያ መቃብር ቆፋሪ።

ለአጥንት ሲያነፈንፍ የነበረ ውሻ.. በመንገዱ የዳሌ ስጋ አይቶ ተንከርፍፎ ቀረ። ለሃጩ ተንጠባጥቦ አሸዋ ላይ ሳር እስኪበቅል ድረስ ተዝረከረከ። ትንሽ ቆይቶ እንደውም “የምን አጥንት.. ማን ጠፍቶበት ነው” ምናምን አለ። ቀባጠረ። ሰዎች በመከራ አስታወሱት። ቀጥሎ “አሃ.. አዎ አዎ.. አገኘሁትኮ.. ይኸው እሷ ነች.. አጥንቴ.. ራሷ።” ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አጥንቴ፣ ንብረቴ ብሎ ድርቅ አለ። የሌባ አይነ ደረቅ.. ሰው እንዴት አንድ ሙሉን ሰው አጥንቴ ነች ብሎ ድርቅ ይላል? የባለቤትነት ውሉን ራሱ ጽፎ፣ ራሱ ፈርሞ፣ በራሱ ማኅተም አጸደቀ።

የአዳም ዝና፣ ክብር፣ ጥበብና እውቀት በተለይ ደግሞ ባለጠግነት ሲመሰከርለት.. “ሰባት መቶ ሚስቶች ነበሩት” ይባልለታል.. መቼ ይሄ ብቻ “በሰባት መቶ ሚስቶቹ ላይ የሚወሰልትባቸው ሦስት መቶ እቁባቶችም ነበሩት” ተብሎ ሲታከልበት.. እንዴት ያለ ታላቅነት ነው ተብሎ ይጨበጨብለታል። አማልክትም “እንዳንተ ያለ ጠቢብ.. ካንተም በፊት፣ ካንተም በኋላ ሊነሳ አይችልም” ብለው ዝናውን፣ ጀግንነቱን.. ወንድነቱን ያጸድቃሉ።

ይሄ ዘግናኝና.. ብዙው ሕዝበ አዳም የሚኮራበት ሰው ሰራሽ ስርዓት የሕጻናት የቆርኪ (የጠርሙስ ክዳን) ጨዋታ ጋር ይመሳሰላል። በመጀመሪያ ሁሉም ሕጻናት በመንደራቸው ውስጥ እየዞሩ ያገኙትን ያህል ቆርኪ ይሰበስባሉ። በመቀጠል ጨዋታው ይጀመራል.. እኩል መጠን ያለው ቆርኪ እየደረደሩ የሚያሸንፍ የተደረደሩትን ቆርኪዎች ሰብስቦ ይወስዳል። በተደጋጋሚ የሚያሸንፍ ልጅ የቆርኪ ባለጠጋ እየሆነ.. ተሸናፊዎቹም የቆርኪ ድሆች ይሆናሉ። ሕጻናቱ በማንኛውም ጊዜ በሚኖራቸው የቆርኪ መጠን.. ጀግንነታቸው፣ ሀብታቸው፣ ክብራቸው፣ ተሰሚነታቸው ይወሰናል። ላለው ይጨመርለታል.. የሚለው ብሒል እንደተጠበቀ።

በቅኝ ግዛት ዘመን.. ከዚያም አስቀድሞ የባርያ ሕግ በነበረበት ዘመን ሁሉ.. የአንድ ጌታ ባለጠግነት ባሉት የባርያዎች መጠን ይወሰናል። የሃምሳ ባሪያዎች ጌታ ለሁለት መቶ ባርያዎቹ ጌታ ሸብረክ ብሎ እጅ መንሳቱ የግድ ነው። ባሪያዎቹ የጌታው ንብረቶች መሆናቸው.. ለውይይት የሚቀርብ አይደለም። ጌታውም የትኛውንም ባርያ ባሻው ገንዘብ.. ያዋጣኛል ብሎ ባሰበው ዋጋ ይሸጠዋል። ያገለገለ፣ አዲስ፣ ልምድ ያለው፣ ልምድ የሌለው፣ ጠንካራ፣ ደካማ፣ ታማኝ፣ የማይታመን፣ ጨዋ.. የመሳሰሉት የዋጋ መተመኛ መነጽሮች ናቸው።

“በጌታዬ በብብቱ ተኝታ የምታሞቀው ልጃገረድ ፈልጌ ነው” አንደኛው።

“ይህቺን አየሃት.. ወንድ የማታውቅ.. ልቅም ያለች” ሌላኛው።

“ምንም አትል.. ስንት ነው?” አንደኛው በድጋሚ.. አገላብጦ ካያት በኋላ።

በርግጥ በዘመናችን ካለው የሰራተኛና አሰሪ ሕግ ጋር በማመሳሰል የሰዎችን ለሰዎች ንብረትነት ቀጥተኛነት የሚከራከሩ ሰዎች ይኖራሉ። ከላይ ለባርያ ንግድ ዋጋ መተመኛነት የተጠቀሱት መስፈርቶች ሰራተኛ ለመቅጠርም እንደሚያገለግሉ እርግጥ ነው። የሚመሳሰሉ ነገሮች እንዳሉት ሆኖ ሰዎች ስራ ፈልገው.. በደሞዝ ተስማምተው ይሰራሉ.. ስራው ይቅርብኝ፣ ደሞዙ ያንሰኛል ወይም ሌላ የተሻለ ስራ አግኝቻለው ብለው ስራቸውን ይለቃሉ። ባርያ ግን ሀሳብ አይሰጥም፣ አይመርጥም፣ አይወስንም። ጌታው ወስኖ ይሸጠዋል.. መርጦ ይገዛዋል።

በተለያዩ ባሕሎች እና የማሕበረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የወንድ እና የሴት የትዳር ግንኙነት ከባርያ ሕግ ብዙም የተለየ የሚባል አይደለም። የወንዱ ወገኖች እንደ ገዢ.. ወደ ሴቷ ወገኖች እንደ ሻጭ.. እጅ መንሻ (ክፍያ፣ ዋጋ) ይዘው ሄደው.. ይሄ አለው.. ይህም አለው ብለው ይደራደራሉ። በሌላው ወገን ያሉት የሴቷ ቤተሰቦች ይሄን ትችላለች፣ ትታዘዛለች፣ ጌታዋን ታከብራለች እያሉ ይደራደራሉ። ለምሳሌ በቻይና በመሃል ከተማ ትዳር ፈላጊ ወንዶች.. የገቢያቸውን መጠን፣ የትምህርት ደረጃቸውን፣ ያላቸውን ጥሪት.. ሌላም ሌላም መረጃዎችን የሚያሳይ ወረቀት አዘጋጅተው ለአላፊ አግዳሚው ይበትናሉ። የሴት ልጆች ወላጆች ከወረቀቶቹ ላይ ያለውን መረጃ በመመልከት ለልጃቸው ዋጋ አዋጭ ያሉትን በአድራሻው በመገናኘት ይደራደራሉ። ማግባት የሚሻ ወንድ ለራሱ ሲደራደር፣ ለሴቷ ግን አባቷ ይደራደርላታል። ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ የሴቷ አባት ልጁን ይዞ መጥቶ ለሙሽራው የሚያስረክብበት ትዕይንት ነው። “የኔ ነበረች.. አሁን ግን በዋጋ ተደራድረህ የራስህ አድርገሃታል እና ተቀበለኝ” አይነት ድራማ። አንዲት ልጅ ተወልዳ በምታድግበት የሕይወት ዳና ውስጥ የእናቷ ሚና ከአባቷ ቢልቅ እንጂ እንደማያንስ እሙን ቢሆንም.. ከተወለደች ጀምሮ እስክታገባ ድረስ በአባቷ ስም.. ካገባች በኋላ ደግሞ በባሏ ስም መጠራቷ.. በብዙው የአለማችን ክፍል የተለመደ ነው። “የኔ ነበረች.. አሁን ያንተ” ማለት ይሄም አይደል።

ብዙ ወርቅ.. ሳንቲም፣ ብዙ ከብቶች፣ ብዙ ሚስቶች ያላቸውን የሚያከብር፣ የሚያወድስ፣ የሚያመሰግን ባሕልና ሀይማኖታችን.. ከባሏ ውጪ የሄደች ሴት ላይ ይተፋል.. በድንጋይ ተወግራ መገደሏ ፍትህ መሆኑ ላይ ተስማምቷል። ልጃገረድ የደፈረ.. ለአባቷ ካሳ ከፍሎ ሲታረቅ.. ድንግልናዋን ይዛ ያልተገኘች ሙሽራ በአደባባይ ትወገራለች። ብዙ ሰው በሃሳብ ደረጃ በጾታ እኩልነት ላይ ቢስማማም.. እነዚህንና ሌሎች አጸያፊ ተግባራትን በማመወቅ እና ባለማወቅ ይፈጽማል። ሴቶች ከምንም አይነት አካል የተሰጡ ወይም የተወሰዱ የወንዶች ሽልማት፣ ስጦታ እና ንብረት ናቸው የሚለው ሀሳብ ከምላሳችን ላይ ቢደበዝዝም.. ከልባችን ግን በደማቁ ተሰንቅሮ.. በሽታውን አምነን መድኃኒት የማንፈልግለት ነቀርሳ ሆኗል።

ሰዓሊ- ሰሎሞን ገለታ

በተለመደው አባባል “ከእያንዳንዱ ጠንካራ ወንድ ጀርባ.. ጠንካራ ሴት አለች” ሲሉ ሰምተን፣ ወይም አንብበን ሊሆን ይችላል። ማን ከፊት.. ማን ደግሞ ከጀርባ መሆን አለበት የሚለው ግን ለጥያቄ ሲቀርብ አይታይም። “እያንዳንዱ ጠንካራ ወንድ.. ጠንካራ ሴት ከጎኑ አለች” ማለት መቻል አለብን። የቤቱ መሪ፣ የቤተሰቡ ተወካይ.. አባወራ መሆኑ ለድርድር እንኳን የማይቀርብ አድርገን ሳንወያይ መስማማታችን ሀፍረት በማይፈጥርበት አየር ውስጥ ስልጣኔ የለም። አቶ አባወራ ከነባለቤቶ የሚል የተለመደው ጨዋ የድግስ መጥሪያ.. ወይዘሮ እማወራ ከነባለቤቶ ቢሆን ነውር ይሆናል? ወይዘሮ እማወራ እና አቶ አባወራ ተጋብዘዋል.. ቢልስ? ጥንዶቹ ምግብ ሲገዙ ወይም ሲያዙ ሁልጊዜ ወንዱ ከሚከፍልበት.. በቤት ውስጥ ዘወትር ሴቷ ምግብ ከምታበስልበት የልማድ ጥላ ሳንላቀቅ ምሁራን ነን ብንል “እስካልተፈነከትኩ ድረስ ደሜ ሰማያዊ ነው” እንደማለት ነው።

መጽሐፉ እንደሚለው.. አብርሃም ይስሐቅን ወለደ። ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ። ያዕቆብ… እያለ ሲዘረዝር.. ዘጠኝ ወር በማኅጸናቸው የተሸከሙ እናቶቻቸው ለመጠቀስ እንኳል ያልበቁት.. በአይሁድ ባሕልና ስርዓት ሴቶች ስለማይጠቀሱ ነው። ያዕቆብ ሴት ልጅ እንደነበረችው ቢታወቅም መጽሐፉ ግን የሚቀጥለው.. “ያዕቆብ ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ” እያለ ነው። ከዚህ የባሕል፣ የሃይማኖትና የአስተሳሰብ ክብ ውስጥ እስካልወጣን የባርነት ሕገ መንግስት ተሽሯል.. ተሻሽሏል ብሎ መናገር እንዴት ይቻላል? እሷ ሰው በተሰበሰበበት መናገር፣ ማስተማር፣ ማስረዳት እስኪፈቀድላት.. እሱ “ምን ለብሳ ነበር?” ከሚለው ጥያቄ ቀድሞ “እንዴት ነው የማስበው?” ብሎ መመርመር ከመልመዱ በፊት.. በሰብአዊነት ውስጥ ሙሉ ብርሃን ሊኖር አይችልም።

ሰው በሚያሰኝ የክብር ደረጃ ለመኖር ዘረኝነትን መንቀፍ እና መጠየፍ ብቻ በቂ አይደለም። የሔዋንን ሙሉ ሰውነት ማመን እና መቀበል የግድ ነው። ዘረኝነት በቀለም ልዩነት፣ በተለያዩ ጎሳዎች ውስጥ የሚነፍስ መርዛማ ነፋስ እንደመሆኑ ሁሉ.. ጾታ ነክ የባርነት አስተሳሰብ ከዚያም እጅግ ወርዶ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ.. በእህትና በወንድም.. በባልና በሚስት መካከል የሚዘወር የአስተሳሰብ ቫይረስ ነው። ሔዋን ሆይ አይንሽን ግለጪና ወደ ሰውነት ከፍታ ተረማመጂ። አዳም ሆይ ጆሮህን ክፈትና ስማ.. ሰምተህም ልብህን መልስ። ምሉዕ ሰብአዊነትን መላበስ ለእያንዳንዱ ሰው፣ ለቤተሰብና ለሀገር ይበጃል። አንበሳ አድኖ በልቶ ካስተረፈው ላይ ቀበሮ እና አሞራ የፈረሱን አጥንት ‘አጥንቴ’ ብለው ከሚፈጥሩት አይነት ግብ ግብ ተላቀን.. እንደ ሰው በሰውነት ደረጃ በሰብአዊነት ልዕልና ላይ እንኑር።

———— | | ————

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top