ጥበብ በታሪክ ገፅ

የአፍሪካ የጥበብ ዋርካው ክቡር ዶክተር ሎሬት ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ተለዩን

ክቡር ዶ/ር ሎሬት ሠዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ከአባታቸዉ ከአቶ ጉያ ገመዳ እና ከእናታቸዉ ከወ/ሮ ማሬ ጎበና በአድአ ወረዳ በደሎ ገጠር ገበሬ ማህበር በ1921 ዓ.ም በህዳር ወር ተወለዱ። በህጻንነት እድሜአቸዉ የወላጆቻቸዉን ከብቶች በመጠበቅ በእረኝነት ካሳለፉ በኋላ በቢሾፍቱ አጼ ልብነ ድንግል ት/ቤት ገብተዉ የቀለም ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል። በመቀጠልም አዳማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተዉ ባሉበት ወቅት ከልጅነታቸዉ ጀምሮ ያደረባቸዉን አዉሮፕላን የማብረር ፍላጎት እዉን ለማድረግ ንጉሠ ነገሥቱ ቢሾፍቱ ሲመጡ የአዉሮፕላን ቅርጽ ሰርተዉ በማበርከታቸዉ፤ ንጉሱ ፍላጎታቸዉን በመረዳት በኢትዮጵያ አየር ኃይል እንዲቀጠሩና ስልጠና እንዲሰጣቸዉ ስለፈቀዱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል ሆኑ። በዚሁ መሰረትም በ1945 ዓ.ም የእጩ መኮንንነት ኮርስ ወስደዉ የሰለጠኑ ሲሆን፤ በ1958 ዓ.ም. ለጦር መሳሪያ ቴክኒሻንነት የሚያበቃ የአምስት ዓመት ስልጠና ተከታትለዉ በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቅቀዋል። በመቀጠልም ወታደራዊ ግዴታቸዉን ለመወጣት በአስመራ ከተማ የአየር ኃይል ቤዝ ለአስራ አንድ ዓመት ካገለገሉ በኋላ ቢሾፍቱ በመመለስ የጦር መሳሪያ ቴክኒሽያን ብርጌድ አባል ሆነዋል። በአየር ኃይል የህዝብ ግንኙነት ክፍልና በተለያዩ የኃላፊነት ስራዎች ላይ በመመደብም አገራቸዉንና ህዝባቸዉን በቅንነት አገልግለዋል።

ክቡር ዶ/ር ሎሬት ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ከዉትድርና ኃላፊነታቸዉ ጎን ለጎን በተፈጥሮ የተለገሱትን የስዕል ጥበብ ተሰጥኦ የእጅ ጥበብ ስራዎችን እየሰሩ ለገበያ ያቀርቡ ከነበሩ ወላጅ እናታቸዉ ትጋትና የስራ ዉጤት በመመልከት ወደ ስዕል ስራዉ የበለጠ እየተሳቡ መጡ። የስዕል ጥበብ ሙያቸዉን ለማዳበርም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ራሳቸዉን በራሳቸዉ ያስተማሩ የድንቅ ችሎታ ባለቤት መሆን ቻሉ። የስዕል ሙያን ለማዳበር ያደርጉት በነበረዉ ከፍተኛ የግል ጥረት፤ አስመራ በአየር ኃይል አባልነት ሲያገለግሉ ካገኟቸዉ ጣሊያኖችና እንግሊዞች ለመማርና ልምድ ለመዉሰድ ያሳዩት ተነሳሽነት ከፍተኛ ድርሻ ነበረዉ።

በቆዳ ላይ ስዕል የመሳል ጥበብን ለአገራችን ያበረከቱ የኢትዮጵያ የአፍሪካና የመላ ዓለም ባለዉለታ ለመሆን የበቁበት ሁኔታ፤ ተምሳሌትነቱ ለትዉልድ የሚሸጋገር ምንጊዜም የምንኮራበት ታላቅ ተግባር ነዉ። በቁጥር ከአስር ሺህ በላይ የተለያዩ ስዕሎችን በተለያዩ የአሳሳል ዘዴዎች በመሳልና በመላዉ ዓለም እየዞሩ በማሳየት አገራችንን ያስተዋወቁ፤ በዓለም የጥበብ ወዳድ ህዝቦች ዘንድ እጅግ የተከበሩ፤ ሁሌም የምንኮራባቸዉ አንጋፋ የጥበብ ባለሞያ ነበሩ። በተፈጥሮ የተለገሳቸዉንና በጥረታቸዉ ያዳበሩትን የስዕል ጥበብ ሞያ ሌሎች ወገኖቻቸዉ እንዲማሩና ፈለጋቸዉን እንዲከተሉ በነበራቸዉ ፍላጎት፤ አራት መጻህፍትን በአማርኛ፤ በአፋን ኦሮሞና በእንግሊዝኛ በመፃፍ ትዉልድን በስእል ጥበብ ዕዉቀትና ክህሎት ለማነጽ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በርካታ ባለሞያዎችን አፍርተዋል። በዚህ ረገድም እኚህ ታላቅ የጥበብ አባት፤ ለማ ጉያ የጥበብ ማዕከልን በማቋቋምና የለማ ጉያ ቀለም ትምህርትቤት በመክፈት ያከናወኑት ስራ ተጠቃሽ ነዉ። መላ ቤተሰቦቻቸዉ ሰዓሊ እንዲሆኑ በማስተማር ለሰአሊነት ያበቁት ክቡር ዶክተር ሻምበል ለማ ጉያ፤ በስዕል ሞያቸዉ ከተለያዩ አፍሪካ አገራት የመጡ የስዕል ባለሙያዎችን በማሰልጠን ለፍሬ አብቅተዋል። በዚሁ መሰረት ከደቡብ አፍሪካ ዘጠኝ የአስተዳደር አካባቢዎች (ፕሮቪንሶች) ተማሪዎች መጥተዉ በለማ ጉያ የጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል ሰልጥነዉ ተመልሰዋል። እነዚህ ተማሪዎች የተማሩትን የቆዳ ላይ ስዕል አሳሳል ‹ለማይዝም› አርት ብለዉ በመሰየማቸዉ ይህ የእሳቸዉ የስዕል አሳሳል ዘዴ ‹ለማይዝም› ተብሎ ለመታወቅ በቅቷል። ከናይጄሪያ መጥተዉ በእሳቸዉ የስነጥበብ ማዕከል ከሰለጠኑት መካከል ሙፉ አኒፉዴ የተባለ ሰልጣኝ እስከ ዛሬ በናይጄሪያ ዩኒቨርስቲ የስነጥበብ መምህር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ከሁሉም በላይ ክቡር ዶ/ር ሎሬት ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ለህዝብ መብት፤ ለእኩልነት፤ ለፍትህና ነጻነት በመታገል የሚታወቁ ታላቅ የህዝብ ልጅ ናቸዉ። የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደ ተደራጀ ደረጃ ማደግ በጀመረባቸዉ 1950ዎቹ ዓመታት በተቀጣጠለዉ የመጫና ቱለማ የኦሮሞ ህዝብ የትግል እንቅስቃሴ ዉስጥ በመሳተፍ የትግሉን ችቦ ወደ አደአ አካባቢ በመዉሰድና የንቅናቄዉ ተጠሪ በመሆን ባከናወኑት ድንቅ ተግባር ሁሌም በክብር ከሚጠሩ አንጋፋ የኦሮሞ ታጋዮች አንዱ ለመሆን የበቁ የትዉልድ ተምሳሌት ነበሩ። በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ማለትም ለወሎ ድርቅ እርዳታ ማሰባሰቢያ ለጨረታ የዋለ ስእል በማበርከት፤ በቢሾፍቱ ከተማ የመጀመሪያ የሆነዉን ቤተ-መጻህፍት በማሰራት፤ በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በማሰራት፤ የቀድሞዉን የደሎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በማሰራት፤ የኦሮሚያ ሠዓሊያን ማህበር መስራች ፕሬዚደንት በመሆን እንዲሁም በፑሽኪን ማዕከል በዳይሬክተርነት ለተወሰነ ወቅት በመስራት ህዝብንና አገርን አገልግለዋል።

የክብር ዶ/ር ሎሬት ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ በሠሯቸዉ አስደናቂ የጥበብ ስራዎች ከአገር ዉስጥና ከዉጪ አገሮች በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከተሸለሟቸው ሽልማቶች ጥቂቶቹ ፦
1. የጦር መሳሪያ ቴክኒሽያን ስልጠና በከፍተኛ ማዕረግ ሲያጠናቅቁ ከአጼ ኃ/ ስላሴ የወርቅ ሰዓት፤
2. የቀድሞ ሊቢያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ የራሳቸዉ ምስል ያለበት የወርቅ ሰዓት፤
3. በቀድሞ የኩባ መሪ በፊደል ካስትሮ ኩባን እንዲጎበኙ ተጠርተዉ ተሸልመዋል፤
4. ከቀድሞና ከአሁኑ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ዳካር ድረስ ተጋብዘዉ የገንዘብና የክብር ሽልማት ተደርጎላቸዋል፤
5. በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኒልሴን ማንዴላ ግብዣ ደቡብ አፍሪካ ተጋብዘዉ የክብር ሰርቲፊኬት ተሸልመዋል፤
6. ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች በዓል አዋሳ ላይ ሲከበር የክብር የወርቅ ሽልማት ተቀብለዋል፤
7. በቀድሞዉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊ/መንበር ዶ/ር ዲላሚን ዙማ የገንዘብ ሽልማት ተደርጎላቸዋል፤
8. የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከልና የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ ለስነጥበብ እድገት ላበረከቱት የረጅም ጊዜ አገልግሎት ሽልማት ተቀብለዋል፤
9. ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም በስነጥበብ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጥቶአቸዋል፤
10. በ2011 ዓ.ም የአቢሲንያ ኢንተርናሽናል አዋርድ የከፍተኛ የክብር የወርቅ ኒሻንና የሎሬትነት ዲፕሎማ አበርክቶላቸዋል፤
11. የኢትዮጵያዊነት ዉርስና ቅርስ ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ እ.አ.አ. 2013 የፒላቲኒየም ተሸላሚ ሆነዋል፤
12. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማእከል የኢሬቻ የሰላም ተሸላሚ ሆነዋል፤

የክብር ዶ/ር ሎሬት ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ከትንሽ ተነስተዉ ራሳቸዉን በትልቅ የክብር ሰገነት ላይ ያደረሱ፤ በኦሮሞ ህዝብ የትግል እንቅስቃሴ ዉስጥ የአንጋፋነት ሚና በመጫወት ተምሳሌት ለመሆን የቻሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ የኢትዮጵያ የስእል ጥበብ ፈርጥ በመሆን እጅግ የተከበሩ ባለዝናና ተወዳጅ የህዝብ ልጅ ነበሩ። እኚህ እረፍት አልባ የብዙ ፈጠራ ባለቤትና ነባር ታጋይ በህክምና ሲረዱ ቆይተዉ ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ በተወለዱ በ92 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የክብር ዶ/ር ሎሬት ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ከባለቤታቸዉ ከወ/ሮ አስቴር በቀለ አምስት ልጆችን አፍርተዋል። ለባለቤታቸዉ፤ ለልጆቻቸዉ፤ ለወንድሞቻቸዉና ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ በአጠቃላይም ለጥበብ አፍቃሪያን፣ ለመላ የኢትዮጵያና ለአፍሪካ ህዝቦች ሁሉ የታዛ መጽሔት የዝግጅት ክፍል መጽናናትን ይመኛል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top