መጽሐፍ ዳሰሳ

ወረርሽኝ

መግቢያ

ሳይንስን ለ‹ማኸዘብ› (የአብላጫውን ህዝብ ተቀባይነት ለማስገኘት) የሚጻፉ መጽሐፍት ዓላማቸው ከዋነኛው የሳይንስ ምርምር ጽሑፍ ለየት ባለ መልኩ ብዝሃ- ሕዝቡ በሚረዳው ቋንቋ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና ግኝቶችን ማቅረብ ነው። በአብዛኛውም ለየት ያሉ ግኝቶችና ማህበረሰብን አነጋጋሪ የሆኑ ርዕሶች ላይ ያተኩራሉ። ዝርዝር ሳይሆን አጠቃላይ የሳይንስ እሳቤዎችን ይገልፃሉ። ሳይንስን የማኸዘብ ሂደት በጣም ጠቃሚ መሣሪያ ሲሆን፣ ዘመናዊ ማህበረሰብን ለመገንባት ሁነኛ ዘዴ ነው። የጋራ የሆነ ባህልን ለማሳደግም ያግዛል። የምንኖርባትን ዓለም ለመረዳት ሳይንስ ቁልፍ መሣሪያ ነው። ሆኖም ሁሉም ሰው ሳይንስን የመማር ዕድልና ፍላጎት ስለማይኖረው፣ ሳይንስን በማኸዘብ አብዛኛውን ሰው ለመድረስ ይቻላል። ከዚህም አንፃር “ወረርሽኝ” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የተጻፈው መጽሐፍ አንድ አብነት መሆኑን እንመለከታለን። ጸሐፊው ሳይንስን በማኸዘብ ከዚህ በፊት የ‹ህያው ፈለግ› እና ‹ከየት ወዴት› በሚል ርዕስ ያዘጋጇቸው ሁለት መጽሐፍት ተጠቃሾች ናቸው። ወረርሽኝ አራት ምዕራፎችን ይዞ መግቢያውን ሳይጨምር በ122 ገጾች የተሰናዳ ነው። እያንዳንዱን ምዕራፍ እንደሚከተለው እንቃኛለን።

ምዕራፍ አንድወረርሽኝና የወረርሽኝ ታሪካዊ ግንዛቤ

ወረርሽኝ ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር የተያያዘ መሆኑን ግንዛቤ ይሠጣል። በዓለም ከተካሄዱ ጦርነቶች በበለጠ ወረርሽኝ የሰው ልጆችን ጨርሷል። ጉዳዩ ወቅታዊም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎችን ለሞት የዳረገውን ኮቪድ-19 እንድናስታውስ ያስገድደናል። ገና ጣጣው ስላልለቀቀን፣ በሚቀጥሉት 6 ወራት ይህ የሞት መጠን ወደ 2 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ ተገምቷል። መጽሐፉም ስለወረረሽኝ የሚሰጠው ግንዛቤ ወቅታዊ በመሆኑ ፋይዳውን የጎላ ያደርገዋል። ሳይንስ የጀርምን ምንነት ከማወቁ በፊት፣ ሰዎች በወረርሽኝ ሲጠቁ፣ በመናፍስት እንደተለከፉ ይታመን ነበር። ተጠቂውን የማግለል ሂደት (ኳረንቲን) ቀደም ብሎ ከሃይማኖት ጋር ተዛምዶ መሰየሙንም እንረዳለን። የተለያዩ የዓለም አገራት የወረርሽኝ ታሪኮች ከተጠቀሱ በኋላ፣ በታሪክ ዋና ዋና ተብለው የተመዘገቡ 20 ወረርሽኞችን ቅልብጭ አድርጎ ያብራራል (ገጽ 8-13)። እዚህ ጋር መፍትሄ ያልተገኘለት ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በስተመጨረሻ ተጠቅሷል። በእርግጠኝነትም ከአንታርክቲካ በስተቀር ሁሉንም አህጉራት ያዳረሰውን ኮሮና 21ኛው ወረርሽኝ ብሎ ታሪክ እንደሚዘግበው አያጠራጥርም። ደጋግሞ እየመጣ የሰው ልጆችን የሚጎበኝ ወረርሽኝም አለ። ኮሌራ ይባላል። አገራችንን በተደጋጋሚ ካጠቋት መካካል ፈንጣጣ የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዝ፣ ኮሌራ ይከተላል። በ24 ሳምንታት ውስጥ በዓለም ለ200 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የህዳር በሽታ (ስፓኒሽ ፍሉ)፣ በኢትዮጵያ እስከ 40ሺ የሚደርሱ ሰዎችን ለሞት እንደዳረገ ይገመታል። አልጋወራሹን ራስ ተፈሪ መኮንንንና ባለቤታቸውን ወ/ሮ መነንንም ጎብኝቷቸው ማለፉ ይታወቃል። እስካሁንም ድረስ በየዓመቱ ህዳር 12 በየመንደሩ ቆሻሻ ሰብስቦ በማቃጠል ባህል ሲዘከር ይውላል። ጸሀፊው የበሽታው መንስኤ ክፉ መናፍስት እንደነበሩ መታመኑን (ገጽ 21) የአለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራን ጽሑፍ ጠቅሰው ሲያስረዱ፡- ”በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ቀን 20 እና 30 ሰው ይሞት ነበር። የሕማሙ ባህል ደግሞ ሳልና ነስር፣ ተቅማጥና ውጋት 4 ዓይነት ነበረ። አመሉና ምግቡ ደግሞ እኩሉ ቋንጣ፣ እኩሉ ጠጅ፣ እኩሉ ኑግና ቆሎ፣ ገንፎ፣ እኩሉ ቂጣና ቡን ይል ነበር። ትረፍ ያለው ክርስቶስ ያልቆረጠው በቅቤ ቡና አዳነው። በወህኒ ቤት ታስሮ የነበረው ሁሉ አስታማሚ እያጣ ከነሰንሰለቱ ተቀበረ….” ይሉናል። አሁንም ቢሆን ከመሰል ዓይነት እምነት ጨርሰን አለመላቀቃችንን የመጽሐፉ ደራሲ ይጠቅሳሉ። ይህንን ዓይነት ከዕውቀት የራቀ፣ መፍትሄ ለማግኘት ጋሬጣ የሆነ አመለካከት ለመለወጥ፣ እንደዚህ ዓይነት ሳይንስን ለማኸዘብ የሚረዱ ጽሑፎችን በተለያየ የእውቀት መስክ በማዘጋጀት ለህብረተሰብ እንዲደርስ ማድረግ ተገቢ ነው። ወረርሽኝ ረሃብን ሊያስነሳ እንደሚችል የክፉ ቀን የረሃብ ታሪክ ተጠቅሶ ተገልጿል። በአንፃሩም በረሃብ የተነሳ ወረርሽኝ እንደሚከሰት የወሎ ረሃብን ጠቅሰው የዓይን ምስክርነታቸውን ያጋሩናል (ገጽ 22- 25)። ከ1950 – 1951 ዓ.ም. ድረስ በአገራችን 3 ሚሊየን ሰዎችን አጥቅቶ፣ 150 ሺዎቹን ለሞት የዳረገው ደግሞ የወባ ወረርሽኝ ነበር። የወባ ወረርሽኝ የተለያዩ የአገራችንን ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት እያጠቃ፣ እስካሁንም የዘለቀ ነው። በዓመት ከ5-9.5 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ እንደሚያጠቃ ይገመታል። እንዲህ ዓይነቱን ሳይንሳዊ መረጃ የሚያቀርብልን ይህ ምዕራፍ፣ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባንንም ጉዳይ አመላካች ሆኖ እናገኘዋለን።

ምዕራፍ ሁለትየበሽታ መንስዔ ተዋስያን እና የወረርሽኝ ሳይንሳዊ ይዘት ምሳሌዎች

የብዙ ወረርሽኞች መንስዔ በልማድ ከአምላክ ቁጣና ፍርድ፣ ሰይጣንና ጋኔን መንፈስ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ቢታመንም፣ የወረርሽኝ መንስዔ ተዋስያን ምን እንደሆኑ በመታወቃቸው፣ የሳይንስ ምርምር ውጤት የቀደመውን ልማዳዊ እምነት ውድቅ ለማድረግ በቅቷል። መጽሐፉም ቀለል ባለ መንገድ የሳይንስ ዕውቀት ላይ ተስፋ እንድናደርግ ይጋብዘናል። በዘመኑ ፍቱን መፍትሄ ገና ላልተገኘላቸው ኤች.አይ.ቪ ኤድስና ኮቪድ-19 ተስፋ እንድንሰንቅ የሚያግዝ፣ የሳይንስን መላ የማግኘት ታሪክ በቀላል ቋንቋ ያወሳናል። ሳይንስን የማኸዘብ ዋነኛ አንጓው ደግሞ በቀላል ቋንቋ ለብዙ የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ የሚያስችል ጽሑፍ ማዘጋጀት በመሆኑ፣ ጸሐፊው ስኬታማ ሥራ እንዳቀረቡልን መመስከር ይቻላል። ቫይረስ፣ ባክቴሪያ፣ ፕሮቶዟ የሚባሉት ጥቃቅን ተዋስያን ለወረርሽኞቹ ዋነኛ መንስዔ ናቸው። እነዚህን ተዋስያን በማስተላለፍ ረገድ አንዳንድ እንስሳት ሚና አላቸው። በተለይ ቁንጫ፣ አይጥና ሌሎችም የዱርና የቤት እንስሳት። የቁንጫ አስገራሚና አስደናቂ ወረርሽኝን የሚከስቱ በሽታን የማስተላለፍ ባህርያት ተገልጿል (ገጽ 40)። እንዲህ አይነቱ አቀራረብ ሳይንስን የማኸዘብ ሁነኛ ዘዴ ነው። ሙጀሌ አንደኛዋ የቁንጫ ዝርያ ናት። ገላ ላይ በመጣበቅ ደም ከሚመጡት ዝ ር ያ ዎ ች በተለየ ሁኔታ ቆዳን ሰርስራ ገብታ እንቁላሏን በመጣል ትታወቃለች። እዚህ ጋር ጸሐፊው በግለ-ታሪክ መጽሐፋቸው ውስጥ የሙጀሌ ናሙናን ለቤተ-ሙከራ አገልግሎት ለማዋል ያደረጉትን ማስታወስ ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። “…ለቢልሃርዝያ ምርምር በተሰማራንበት አንድ ወቅት፣ ጫማዬን አውልቄ፣ አንድ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ፣ ሙጀሌ ለማጥመድ፣ እግሬን ምድጃ አመድ ውስጥ ጨምሬ እሳት እየሞቅሁ፣ ጠላ እየጠጣሁ ብዙ ጊዜ ቆየሁ። በለስ ቀንቶኝ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሙጀሌ እንደያዘኝ ተገነዘብኩ፤ አራት የሙጀሌ ቁንጫዎች እግሮቼ ጣቶች መሃል ተሰክተው እንቁላል መጣል ጀምረዋል። ሁለት ሳምንት ያህል አቆይቼ፣ ተጠንቅቄ በመርፌ ሙጀሌዎቹን አወጣሁና ለትምህርት ናሙናነት አዘጋጀኋቸው…..” ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ (ገጽ 242) በቁንጫ ዝርያዎች የሚተላለፉ የተስቦ ዓይነት ወረርሽኞች፣ አካባቢንና ቤትን በንጽህና በመጠበቅ በቀላሉ የምንከላከላቸው ናቸው። የወባ ወረርሽኝን የሚያመጡ ባለአንድ ህዋስ ፕሮቶዟ እንዴት ያለ ዑደተ- ሕይወት እንዳላቸው በቀላል ቋንቋ ተብራርቶ ተገልጿል (ገጽ 48-52) ዛሬ ዓለምን እያሸበረ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች እ.ኤ.አ. በ1965 ዓ.ም. ቀደም ብሎ የታወቀ መሆኑ ተጠቅሷል (ገጽ 59)። እነዚህ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች እንደ ጉንፋንና ሳርስ ለመሳሰሉት ለሰባት የተለያዩ በሽታዎች መንስኤ ናቸው። ሁሉም የመተንፈሻ አካላትን ያጠቃሉ። የዱር እንስሳት ውስጥ የሚገኙ ቫይረሶች ወደ ሰው ስለሚተላለፉ፣ የኮሮና ቫይረሶችም በዚሁ መንገድ ወደ ሰው እንደተላለፉ ይገመታል። ስርጭቱም በእስትንፋስ በመሆኑ ፈጣንና ሰፊ መሆኑም ተብራርቷል (ገጽ 55)። የመከላከያ መንገዱንም እየጠቆሙ፣ አደራ መሰል ምክር በስንኝ ያስተላልፉልናል (ገጽ 57)፡- “አንተ የምድሬ ልጅ፣ አንተ የዓለም ዜጋ፣ እስትንፋስ ቆራጩን በጋራ እንዋጋ” በዚህ ምዕራፍ ማገባደጃ ኢቦላ ስለተባለው ቫይረስ ያወሳል። ጉዳዩ ጎረቤቶቻችንን ያስጨነቀ ከመሆኑ አንጻር፣ የእኛም ስጋት እንዳይሆን መጠንቀቅ እንዳለብን አመላካች አድርጌ ወስጄዋለሁ።

ምዕራፍ ሦስትሳይንስና ወረርሽኝ

ይሄኛው ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ የሳይንስ ምርምር ውጤት የደረሰበትን፤ በበሽታ እንዴት እንደምንጠቃ፣ አካላችን ለበሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዴት ያለ የመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ፣ ህያው አካልን የሰው ልጅ ባህልና ባህርይ በማውረስ ለትረካ እንዲያመች አድርጎ ያወሳል። በዘይቤያዊ አነጋገር እያመሳሰሉ መጻፍ ሳይንስን የማኸዘቢያ አንደኛው ዘዴ ነው። ያ ለምን እንደተደረገ መገለጹ ደግሞ፣ ትክክለኛውን የሳይንስ እሳቤ በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ይታደጋል። የበሽታ መንስዔ የሆኑ ተህዋስያን እንዴት አጭበርብረው የአካልን የመከላከል አቅም እንደሚያዳክሙ፣ ወራሪዎች ያዳበሯቸው የወረራ ስልቶች ሥር አስደናቂ ትረካን እናነባለን። ክትባትና “አይደፈሬ” በሚለው ንዑስ- ርዕስ ሥር የክትባት ዋና ተግባር፣ የክትባት ታሪክ፣ በሽታን እንዴት እንደሚከላከል ተብራርቶ ይገኛል (ገጽ 64)። ሳይንስ ለብዙ ወረርሽኝ ክትባት የሚባል ፍቱን መፍትሄ አበጅቷል። ክትባት እንዴት እንደሚዘጋጅ፣ ወደአካል ገብቶ የመከላከያ ሥርዓትን እንዴት እንደሚገነባ፣ ስለአካላችን የወራሪ መከላከያ መንገድ ያብራራል (ገጽ 75-78) የወረርሽኝ ሥርጭት ስሌትም ቀለል ባለ መንገድ በአጭሩ ቢገለጽም፣ ዝርዝር መረጃውም አባሪ ተደርጎ ተቀምጧል። ሳይንስን ማኸዘብ ዓላማ ያደረገው መጽሐፍ ጠቅለል ያሉ መረጃዎችንና ግኝቶችን ከገለፀ በኋላ፣ ዘርዘር ያሉ አሳቦች መኖራቸውን በአባሪ ማመልከቱ ተገቢነት አለው።

ምዕራፍ አራትየወደፊት የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ

የሰው ልጅ የራሱን ድንበር እየዘለለ ወደ ዱር እንስሳት መኖሪያ መዝመቱን ከቀጠለ፣ ሌሎችም አዳዲስ ወረርሽኞችን ማስተናገዱ አይቀርም። ወረርሽኞች ድንበር ስለማይገድባቸው፣ የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ችግር ተደርገው ይወሰዳሉ። ለምሳሌ፡- የሌሊት ወፎች 130 ለሚሆኑ ቫይረሶች ቋት መሆናቸው ይታወቃል። በቫይረሱ ጉዳት ስለማይደርስባቸው፣ ብዙ ርቀት በመጓዝ፣ የተለያዩ አካባቢዎችን ስለሚያዳርሱ የሰው ልጆች እንዲጠቁ መንስዔ ናቸው። በዚሁ መንስዔ የሌሊት ወፍ የመጽሐፉ ፊት ገጽ ሽፋን እንድትሆን መወሰናቸውን ደራሲው ይገልጡልናል (ገጽ 87) የአየር ቅጥ መለወጥም ለወረርሽኝ መንስዔ ነው። ኢትዮጵያም የዚህ ተጋላጭ በመሆኗ የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ በተዘዋዋሪ ምክር ያበረክታል። ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ክትባት ከመድኃኒት የተሻለ አማራጭ መሆኑ ይታወቃል። እናም ጸሐፊው ለሳይንስ ምልጃ ቢጤ ልከዋል። ይድረስ ለሳይንስ በሚል (ገጽ 85) ፡-

“ፈንጣጣ ሲያውረኝ፣
ፊቴን ሲቆፍረኝ፣ ከላህልኝ ለካ፣
ተስቦ ሲለክፈኝ፣ ገታህልኝ ለካ፣
አስቸገረኝ እንጂ፣ አዲስ እየተካ፣
በነካካው እጅህ፣ ኮሮናንም እንካ።”

ወረርሽኝ በጦርነት ሊመሰል ይችላል። ወደፊትም እንደሚከሰት መደምደም እንደሚቻል በመጥቀስ ወረርሽኝ ይከሰታል ብሎ አምኖ ለመከላከል በተጠንቀቅ የመጠባበቅ አስፈላጊነቱን እያስረዱ እንዲህ በማለት ይደመድማሉ፡- “በኢትዮጵያ ለወረርሽኝ የመከላከል ዝግጅት ሂደት፣ የጤና መዋቅሮችን ማጠናቀር፣ የጤና ባለሙያዎችን ስለወረርሽኝ በቂ ሙያዊ ግንዛቤን ማስጨበጥ፣ መንግሥት ተገቢውን የፖለቲካ ትኩረት እንዲሰጥ ብሎም ተገቢውን ስርጭት ገቺ ተግባራትን እንዲያስተናግድ፣ ማህበረሰቡም ስለወረርሽኝ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያዳብር መቀስቀስና ማስተማር ያስፈልጋል። በጤና ባለሙያዎች የሚለገሱ ምክሮችን መቀበል፣ በመንግሥት የሚደነገጉ ሕጎችንና ደምቦችን ማክበር ያስፈልጋል። ለወረርሽኝ መከላከል፣ ለመንግሥት እንዲሁም ለባለሙያዎች ችግር ፈቺ ጥረት የማህበረሰቡ ድጋፍ ወሳኝ ሚና አለው” (ገጽ 96)

መደምደሚያ

ሳይንስን ለማኸዘብ የሚጻፉ መጻሐፍት ከሞላ ጎደል በዋነኝነት ሊያካትቷቸው የሚገቡ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
ሀ) አዝናኝና ለአንባቢው ፋይዳ ያለው፣
ለ) ለየት ያለና አነጋጋሪ ርዕስና ይዘት ያለው፣
ሐ) የጠለቀ የሳይንስ ዕውቀት ለሌለው የማህበረሰብ ክፍል እንዲደርስ ከዝርዝር ይልቅ ዋነኛ የሳይንስ እሳቤዎች ላይ አትኩሮ የሚገልፅ፣
መ) ለመረዳት የሚከብዱ ውስብስብ ሳይንሳዊ እሳቤዎችን በዘይቤያዊ አነጋገርና በአካባቢያችን ከምናያቸውና ከእለት-ተለት እንቅስቃሴያችን ጋር አዛምዶና አመሳስሎ መግለፅ መቻል፣
ሠ) ተጨባጭ የሳይንስ እሳቤዎችን ሳይንሳዊ ካልሆኑ አስተሳሰቦች በመለየት አጥርቶ ለማቅረብ መትጋትና አደናጋሪ እሳቤዎችን ማስወገድ መቻል ናቸው። ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንፃር ሲቃኝ “ወረርሽኝ” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የተዘጋጀው መጠነ-ውስን መፅሐፍ ሳይንስን ለማኸዘብ እንደሚረዳ መመስከር ይቻላል።

አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top