አድባራተ ጥበብ

ኪነጥበብ ለልማት ስንል እንዴት?

ኪነጥበብ ስንል ስነፅሁፍ(ልበወለድ አጭር ታሪክ ስነግጥም ድራማ(ትያትር የቲሌቭዥን የሬድዮ ድራማ ፊልምና ፎቶ ኮሚክ)፣ ስዕል ፣ሙዚቃ እና ዳንስን አቅፎ የያዘ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ በውስጡ የተለያ የጥበብ ዓይነቶችን የያዘ ዘርፍ በእርግጥም ለልማት የሚያደርገው አስተዋፅኦ አሌ የሚባል አይደለም። ስለኪነጥበብ ፋይዳ ለመናገር ከዚህ በፊት በተለያዩ የህትመትና ኤልክትሮኒክስ ሚዲያዎች ብዙ ብለዋልና ምንም መጨመር አለፈልግም ይልቁንም እኔ በምን መንገድ የሚለውን ለመዳሰስ እሞክራለው።

ከላይ የተጠቀሱት የኪነጥብብ ዓይነቶች በጊዜ ሂደት ቅርጻቸውን እየቀየሩ ይምጡ እንጂ መነሻቸው ከሰው ልጆች መፈጠር ጋር የቀረበ ቁርኝት አላቸው። ታሪክ መንገር። ኪነጥብብ ከባህል መገለጫ ክፍሎች አንዱ ነው። ይህንንም በባህል ጥናት ዘርፍ ትልቁን ድርሻ የያዙት የፎክሎር ጥናት ተመራማሪዎች ያብራራሉ።

ፎክሎር የህዝቦች የማህበረሰቦች በቃል በቁስ በእንቅስቃሴ ከዘመን ወደዘመን የሚተላለፍ እውቀት ነው። በእነዚህ ባህላዊ የእውቀት መተላለፊያ መንገዶች ከሚባሉት ውስጥ ደግሞ አራቱ የፎክሎር ዘርፎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህም ኦራል ሊትሬቸር፣ ሶሻል ከስተም፤ ማቴሪያል ካልቸርና ፎልክ አርት ናቸው። ታዲያ እነዚህ አራቱ የፎክሎር ክፍሎች በየትኛውም ዓለም ያሉ ማህበረሰቦች ተፈጥሮን ተቋቅመው ለመኖር በባህላዊ መንገድ እውቀቶችን ከትውልድ ወደትውልድ ከሚያስተላለፉባቸው መንገዶች ውስጥ ዛሬ ኪነጥበብ የምንላቸው ስነጽሁፍ ድራማ ስዕል ሙዚቃና ዳንስ ይዘው እናገኛቸዋለን። በኦራል ሊትሬቸር ውስጥ የምናገኛቸው ‹ሚቶች›፣ ‹ሌጀንዶች›፣ ‹ተረቶች›፣ እንቆቅልሾች አፋዊ ከመሆናቸው ውጪ ዛሬ ልበወለድ አጭርታሪክ ግጥምና ድራማ ይዘዋቸው የምናገኛቸው አላባዊያንን የያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን። በሶሻል ከስተም ውስጥ የምናገኛቸው ባህላዊ እምነቶች ፌስቲቫሎችና የህብረት ጨዋታዎች ደግሞ ዳንስን ሙዚቃን የያዙ ሲሆን፣ በሶስተኛው ማቴሪያል ካልቸር ውስጥ ደግሞ ቅርፅን ስዕልን የያዙ ናቸው። በአራተኛው እና ፎክ አርት በሚባለው የፎክ አርት ውስጥ ድራማን ሙዚቃንና ዳንስን ይዘው እናገኛቸዋለን። ታዲያ እነዚህ ማህበረሰብ በራሱ ፍቃድና ፍላጎት መረጃን በመለዋወጫ መንገድ የፈጠራቸው የኪነጥበብ ዓይነቶች ዛሬ ከዓለም እድገት ጋር ቅርፃቸውንና አቀረራባቸውን እየቀየሩ ዛሬ ድረስ በመምጣት በፊት የሚሠጡትን መረጃ የማስተላለፍ ስራ እየተሰራባቸው ይገኛሉ። ከዚህ የኪነጥብብ መሰረታቸው ተነስተን ኪነጥብብና መሰረቷን ስናይ ኪነጥብብ ከአንድ አካል ወገን ጋር ሳይሆን ግንኙነቱ ከህዝብ ጋር ሆኖ እናገኘዋለን።

መሰረታቸውን ከፎክሎር ያደረጉት የኪነጥበብ ዘርፎች ከቃል ወደፅሁፍ በመሻገርና የተለያየ ሳይንሳዊ ክህሎቶችና ቴክኖሎጂዎችን በመጨመር ዛሬም ድረስ ቀድሞ ይሰጡ የነበሩትን ግልጋሎት በመስጠት በየትኛውም የለውጥ ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ በመጫወት ላይ ይገኛሉ። ኪነጥብብ መሠረቱ ከህዝብ ጋር በመሆኑ ብቻም ሳይሆን ጥበባዊ ለዛን ተላብሶ መቅረቡ፤ መረጃን አስተሳሰብንና እውቅትን በማስተላልፍ ትልቁ የመረጃ መለዋወጫ እንዲሆን አስችሎታል። ይህ የራሱ የሆነ እውቀትና ፍልስፍና የያዘ የሙያ ዘርፍ ከመሠረቱም ህዝቦች እውቀትን አስተሳሰብን እምነትን ለማስተላለፊያነት ተብሎ የሚሰራ መሆኑ ጥብብ ምክንያታዊነቱንና ዓላማ ያለው እንዲሆን አስችሎታል።

ኪነጥበብና ልማት

በየአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ተቋም ማዕከል ተሰናድቶ በ1993 በታታመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ‹ልማት› የሚለውን ቃል ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እድገት ብልፅግና መልካም ተግባር በማለት ያብራራዋል። በዚህ ቃል ትርጉም ሁለት ትልልቅ ሐሳቦች ተገልጸው እናገኛቸዋለን። የ‹ኢኮኖሚ›ና ‹ማህበራዊ› እድገት የሚሉትን። ይህንን የልማት ትርጉም ካየን ኪነጥበብ ለልማት ስንልስ ምን ማለት ነው፤ የሚለውን እንመልከት። መሰረቱን ከሰው ልጆች ጋር አድርጎ የተነሳው ኪነጥብብ ሰዎች በእለት ተእለት ኑሯቸው የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድ የሚተርኩበት ተፈጥሮን የሚታገሉበትንና ችግርን ደስታቸውን የሚጋሩበት መንገድ ነበር። ይህ ፋይዳ ኖሮት የተነሳው ጥብብ ከልማት ለይቶ ማየት የማይታሰብ ነው። በእርግጥ ጥብብ ለጥብብ ፋይዳና ለማህበረሰብ የሚሉ አስተሳሰቦች በተለያዩ ግዜ ተነስተዋል። ይሁንና ጥብብ ከተጀመረችበት ግዜ ጀምሮ ፋይዳ የሌለውና ጥብብ ለራሷ ብቻ ውላ የምታውቅበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም። በምሳሌ የተቀመጠ ስራም የለም። ወደፊትም አይኖርም። ለምን ቢሉ ደግሞ ጥብብ መሰረቷም ልማታዊ ነበርና ነው። የድራማ መሰረት ነው ተብሎ ከሚታወቀው በግሪክ የዳይኖሰር ባህል ለይ ከሚቀርቡ ትያትሮች ጀምሮ የግሪኮቹ ሶፎክለስ፣ ኤስክለስ ከዛም በትያትር ዓለም ላይ ትልቅ ስፍራ ያለው እንግሊዛዊው ዊሊያም ሼክስፒር፣ ሲቀጥልም የራሻዎቹ አንቶን ቼሆቭ የጀርመኑ ብረሽት እና የቅርቦቹ አሜሪካዊያን አንደርሰን አትዮጵያዊው አብዬ መንግስቱ፤ ሎሬት ፀጋየ፤ እና በሀገር ፍቅር የቀረቡት ‹ሰዓት እላፊ› እንዲሁም ‹ፎርፌ› እና ‹ሰማያዊ ዓይን› ድረስ የተሰሩ የትያትር ስራዎች። (ምንም እንኳን ትያትር ቤቱ ለይተው እነ ፎርፌን.. ልማታዊ ብለው ቢጠቅሷቸውም) ያለፋይዳ የተሰሩ ልማታዊ ያልሆኑ ለመባል የሚያስችል አንዳችም መስፈርት የላቸውም። ይልቁንም በሁለቱ መሃከል ላይ ያለው ልዩነት ልማታዊ መሆንና አለመሆን ሳይሆን ግለሳበዊ ሐሳብ መሰረት ልማታዊና አጀንዳ መር /የንቅናቄ/ ድራማ መሆናቸው ነው። የትኛውም ዓይነት በየቀኑ በዓለም ላይ የሚመረቱ የኪነጥብብ ስራዎች፤ ፋይዳ ሳይኖራቸው ይሰራሉ ብሎ ማሰብ ሙያውን እንደሙያ አለመቀበል፤ አልያም ስለሙያው ያለው ግንዛቤ አናሳ ከመሆን የሚመጣ ነው። እዚህ ላይ ‹ዲቨሎፕመንት› የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ዕድገት መስፋት መጎልበት በሚል ሲተረጉመው አማርኛው ደግሞ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ማደግ የሚለውን ትርጉም ይሰጠዋል። የእነዚህ ቃል ትርጉም ይህ ከሆነ ታዲያ ኪነጥብብ ለኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ለማምጣት የምንጠቀምበት መንገድ እንዴት ባለው መንገድ ነው የሚለው በስፋት መወያየት ያለብን ይመስለኛል። የትኛውም ዓይነት የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ እድገት የሚመጣው ሰው የተባለው ፍጡር በሚያካብተው እውቀት ልክ ነው። ሰዎች እውቀትን ከሚለዋወጡበት መንገድ ደግሞ ቋንቋ አንዱ ነው። ሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዘመን ጀምሮ ነገሮችን በመሞከርና በሙከራ የተገኙትን በፅሁፍ አልያም በቃል መረጃዎችን በመለዋወጥ ከቤት ቁስ ጀምሮ ዛሬ የደረሰባቸውን ዘመናዊ መሳሪያዎች ለመፍጠርና ከተፈጥሮ ጋር ታግሎ ህይወቱን ለማቆየት ችሏል። ቋንቋን ተጠቅሞ መረጃን እውቀትን በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ ደግሞ ለማህበራዊውም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ኪነጥበብ ትልቁን ስፍራ ትይዛለች።

ኪነጥበብ ለሰው ልጅ መግባቢያ መንገዶች ከሆኑት መሳሪያ አንዱ ነው። መረጃ በእለት ተዕለት ንግግር፣ በስብሰባ፣ በትምህርት፣ ቀጥታና ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ሊተላለፍ ይችላል። አርስቶትል ሪሂቶሪክ በሚለው መፀሀፉ የትኛው ዓይነት መረጃን ለማስተላለፍና አድማጭ ወይም ተመልካች ጋር ለማድረስ ሶስት ነገሮች ሊሟሉ ይገባል ይላል። አቅራቢው ሊል የፈለገውን ጉዳይ እውነታዊነት ስሜታዊነትና ተደማጭነት ሊኖረው ይገባል በማለት። ታዲያ ይሄንን ከክርስቶስ ልደት በፊት 346 ዓ.ዓ. ላይ አርስቶትል ያስቀመጠው ሐሳብ ዛሬም በዘመናዊው የመረጃ መለዋወጥ ሂደት ውስጥ ወሳኝና አስፈላጊ ሆነው ተቀምጠዋል። ታዲያ ይህንን ዓይነቱን የመረጃ መለዋወጫ መንገድ በአግባቡ ለመጠቀም፤ ዛሬ በየትኛውም ዓለም ላይ በስፋት በመጠቀም ደረጃ ኪነጥበባዊ ስራዎች ትልቅ ድርሻ ይዘው እናገኛቸዋለን። ለምን ቢባል ደግሞ ኪነጥብብ በሰዎች የቀረበና ለስሜት በቀረበ መልኩ ስነውበታዊ ለዛ ይዞ የሚቀርብ በመሆኑ ነው። ታዋቂዋ አማሪካዊት ደራሲ ‹አይን ራንዳ› ኪነጥብብ “art is the indispensable medium for the communication of morale idea” በማለት የኪነጥብብ መሠረታዊ የመረጃ መለዋወጫ መንገድነትን ታብራራለች። ይሁንና ኪነጥብብ መረጃን የማስተላለፊያ መንገድ ነው ሲባል ኪነጥብብ ዓለምን እንዳለ በመኮረጅ ሳይሆን አውነታውን መሰረት አድርጎ አሪቲስቱ ስሜት በመጨመር ጥበባዊ ክህሎቱን በመጠቀም አርስቶትል ያስቀመታቸውን ስሜት፣ እውነትነትና ሳቢ ተደማጭነት በተሞላ መንገድ ነው። ይህ ይሆን ዘንድና ከላይ የተጠቀሰውን ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ብልፅግና የሚመጣው በምንድን ነው የሚለውን በአግባቡ ማወቅና ስምምነት ላይ መደረስ አለበት።

በዓለም ለይ በከፍተኛ ደረጃ ያደጉት ሀገራትን ለማደጋቸው ዋናውና ቀዳሚው ድርሻ ትምህርት መሆኑ ግልፅ ነው። የትምህርት ዋናው ዓላማ ደግሞ አዕምሮን እንድናስብበት ቀድመው የነበሩትን እውቀቶችንና ክዋኔዎችን ምክንያታቸውን ፋዳቸውን በመመርመር በአዲስ ለመተካት አልያም እነሱኑን አጎልብቶ ወደተሻለ ነገር ለመቀየር ከዚያም ሲያልፍም ለተሞከሩና ለሰው ልጅ የእለት ተእለት ኑሮውን የሚያሳድጉ ህይወቱን ሊያቀልሉ የሚችሉ ፈጠራዎችን ማዘጋጀትና ለማህበረሰብ ጠቀሜታ ያለው ስራ ማበርከት ነው። ይህ ፈጠራ በቁስ ብቻ ሳይሀን በአስተሳሰብ ፍልስፍናም ሊገለፅ ይችላል። ታዲያ በትምህርት የሚገኘውና የሰው ልጅን በቁሳዊውም ሆነ በስነልቦና የአእምሮ ልማት ለማምጣት ኪነጥብብ አንዱ መንገድ መሆኑ እሙን ነው። ይህ ለሰው ልጅ አዕምሮ ልማት ትልቅ ድርሻ ያለው ለልማት ለማዋል፤ ከየት መጀመር አለበት የሚለው ጥያቄ መመለስ ተገቢ ይመስለኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አዲስ ግኝት በሀገራችን ውስጥ በሚገኙ አዳራሾችና መገናኛ ብዙሃን የሚነገረው ኪነጥብብን ለልማት ለማዋል የሚለው ውይይት በእርግጥም አግባብነት ባለው መንገድ ነው የሚቀርበው የሚለው ሳስብ ለእኔ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል።

ኪነጥብብ ለልማት

ኪነጥብብ ለልማት የሚለው ሀሳብ እኔ ወይም ማናቸውም የኪነጥብብ ሰዎች ስላሉት ሳይሆን ራሱ ኪነጥብብ መሰረቷ ልማት ላይ ነውና ምንም መከራከሪያ ነጥብ የለኝም። ኪነጥብብ ያለልማት ሊኖርም ሊታሰብም አይችልም። ስለዚህ ለልማት የሚለውን እንተወውና ኪነጥብብ ለልማት እንዴት ይውላል የሚለው ላይ እንነጋገር። ስለኪነጥብብ ስናወራ በመጀመሪያ ግልፅ የሆነ ሐሳብ ይዘን መሄድ አለብን። ይህም ኪነጥብብ ለመኖሯ ምክንያት የሆኑት ሶስት መሰረታዊ ባለድርሻዎችን በግልፅ ማወቅ ነው። የትኛውም ዓይነት የኪነጥብብ ዓይነቶች ለመኖራቸው፤ አርቲስት (ከያኒው)፣ ባለሙያ፣ ተመልካች እና ሃያሲ የሚባሉ ጎራዎች አሏቸው። የእነዚህ ሶስቱ ባለድርሻዎች መኖር የኪነጥብብ ስራዎች እንዲኖሩ ያስችላል። ከማህበረሰብ የወጡ ከያኒዎች ለወጡበት ማህበረሰብ የሚሆን የኪነጥበብ ስራዎች ይዘው ይቀርባሉ። ብዛት ያለው ማህበረሰብም ከእነሱ በወጡ ከያኒዎች የተሰሩ የጥብብ ውጤቶችን በመመልከት፤ በማድመጥ ያጣጥማሉ። የሚያወቁትን እንደተጨማሪ እውቀት አዲሱን ለህይወት የሚሆናቸውን መርጠው ይወስዳሉ። እነዚህ ማህበረሰብ ጋር የደረሱትን አልያም የሚደርሱትን ስራዎች ከባህል እና ከተጨባጭ የዓለም እውቀት በመገምገም የጥብብ ስራዎች እንዲያድጉ ፋይዳቸው ከፍ እንዲል ደግሞ ሃያሲዎች ስራዎችን ይገመግማሉ። እነዚህ ሶስቱ ባለድርሻዎች ሲኖሩ የዳበሩና ጠንካራ የአዕምሮ ልማት የሚውሉ የኪነጥብብ ስራዎች ይኖራሉ። ታዲያ እነዚህ ሶስት ባለድርሻዎች የተለያዩና የተራረቁ አይደሉም። ይልቁንም የጋራ የሆነ ፍላጎት አላቸው፤ ‹ጥብብ› የሚባለው ሙያ። ታዲያ ይህ የጋራ የሆነው ሙያ ላይ የስራ ድርሻቸው ይለያይ እንጂ ሶስቱም የዳበረ የኪነጥብብ ስራዎች የዓላማና ፋይዳ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል። እንግዲህ ኪነጥብብ ለልማት ዋለ የሚባለው ሀያሲዎች በቀመሩት ህግ መሰረት ተደርገው በከያኒዎች የተሰናዱ የኪነጥብብ ስራዎች ተመልካች ጋር ሲደርሱና የአዕምሮ መጎለበት ፋይዳ ሲኖራቸው ነው። ኪነጥብብ እነዚህን ባለድርሻዎች ይዞ ለልማት ይውል ዘንድ በመጀመሪያ የኪነጥብብ የማድነቅ ፋይዳውን የሚያውቅ ማህበረሰብ መፈጠር አለበት። ጫማ በማያደርግ ማህበረሰብ ውስጥ የጫማ ፋብሪካ ምንም እንዳልሆነ አልያም ትርፋማ ለመሆን ብዙ ግዜ እንደሚፈጅ ሁሉ፤ ኪነጥብብን የማያደንቅ ማህበረሰብ ውስጥ ኪነጥብብ ምንም ናት። ስለዚህ ኪነጥብብን ለልማት ስናስብ ልናተኩርበት የሚገባን ዋናው ነገር ኪነጥብብን የሚያደንቅ የሚያፈቅርና ፋይዳውን የሚያውቅ ማህበረሰብ መፍጠር ዋናው ሆኖ እናገኘዋለን።

ዛሬ ዛሬ በተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ኪነጥብብ ለልማት ማዋል የሚል ከፍ ባለ ድምፅ ሲነገር እሰማለው። እውነት ግን ኪነጥብብን ለልማት ማዋል ምን ማለት ነው? አሁን አሁን ኪነጥብብን ለልማት ማለት መንግስት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች ከማስታጋባት ጋር በማያያዝ ከልማትነት ይልቅ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት እንዲውል ሲደረግ ይታያል። በርግጥ ኪነጥብብን ለልማት ማዋል ፖሊሲዎችን ማስተጋባት ነውን? የመሪዎችን ንግግርና አስተሳሰብ ማስታጋባት ነው? ያለእሳቸው ሀገር ዉሀ በላት እያሉ መፎከር ነው። ሌሎች ሚዲየሞች አውርተው የጨረሱትን መደመር ቀጥተኛ እና ብቸኛ መንገድ ነው እያሉ መፈክር ማሰማት ነውን? ኪነጥብብ የአንድን ብሔረሰብ የሙዚቃ ምት የያዘ ሙዚቃ ማሰናዳት ነውን? የአንድን ብሔረሰብ ዳንስ የሚደንሱ ቅንድባቸውን የተቀነደቡ ዳንሰኞች የብሄሩን አልባሳት ለብሶ ሲደንሱ ማሳየት ነውን? ለአባይ ግድብ ያላዋጣ ሰው አይደለም የሚል ግጥም የያዙ ዘፈኖች መዝፈን ነውን? ማሳለጫ መንገድ ተገንብቷል የሚል በማንኛውም ዜና ሊነገር የሚችልን ሐሳብስ በዜማ መንገር ነውን? ከተለያዩ መንገዶች የሚገኝ እርዳታን መሰረት አድርጎ ትላልቅ የኪነጥብብ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ብቻ በዜና ከመነገር ባልተለየ መልክ መሪዎችና ፈንድ አድራጊዎች የሚሉትን ሐሳብ መንገር ነውን? አይመስለኝም!!! ኪነጥብብ ለልማት ማዋል ከዚህ የዘለለ ሩቅና ከተሰራበት ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችል ሐሳብ ነው።

የኪነጥበብ ባህል

ኪነጥብብ ለልማት ለማዋል በመጀመሪያ ኪነጥብብን የሚያደንቅ ፋይዳቸውን የሚያውቅ ማህበረስብ መፍጠር ማዳበር ቀዳሚው ስራ መሆን አለበት። ስለኪነጥብብ ምንም ነገር ሳይሰማና ሳያይ ያደገን ሰው በአርባና በሐምሳ ዓመቱ ትያትር ቤት ሄዶ ስለ ኢትዮጵያ ገናናነት፣ ቀደምት ሀገርነት፣ ስለኪራይ ሰብሳቢነት፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ስለመደራጀት፤ ስለብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት፤ እና የመሳሰሉትን በስብሰባ አልያ በዜና መልክ ሊነገሩ የሚችሉ እንጨት እንጨት የሚሉ ሐሳቦች ያላቸው ትያትር እንዲያይ ሕግ ማውጣት ድራማን ለልማት እንድትውል ማድርግ አይደለም። ይልቁንም በጭላንጭል ውስጥ አልፈው ያደጉ ኪነጥብብን ፋይዳ የሚያውቁትን ተመልካች ሙያውን እንዲጠሉ ማድረግና ያለውንም ትንሽ ተመልካች ከማጥፋት የዘለለ ጥቅም የለውም። ስለዚህ ይህ ካለሆነ ምን መደረግ አለበት? ኪነጥብብን ለልማት ያሰበ መንግስት ሀገር መጀመሪያ ሊሰራ የሚገባው ስራ የኪነጥበብ ባህልን በህዝብ ውስጥ ማዳበር ነው። ኪነጥብብ ባህል ለማድረግ ምን መስራት አለብን ከየትስ መጀመር አለበት? ኪነጥብብ ለልማት ስንል በቀጥታ መንገድ ከመቆፈርና ክትት አዋጅ ከማወጅ የዘለለ ነው። ኪነጥብብ ለልማት ሲውል በቀጥታ ከአዕምሮ ልማት ጋር የሚገናኝ ነው። ሰዎች እንዲጠይቁ እንዲመልሱ እንዲያስቡ እንዲመራመሩ በምርምር ያገኙትን መንገድ በመጠቆም የሰው ልጅን የማሰብ ክህሎት ከፍ በማድርግ በቀላሉ እውቀትን እንዲቀስሙ ማድረጊያ መንገድ ነው። ይህንን ፋይዳ ይሰጥ ዘንድም በቅድሚያ መሰራት ያለበት ጉዳይ ብዙ ናቸው።

ባህል

ባህል በጊዜ ሄደት እየደባረ የሚመጣ ሰዎች ከቀደሙት እየተማሩት የሕይወት አኗኗራቸው አንዱ አካል የሚያደርጉት ሃሳበቸውን እውቀታቸውን ከአንዱ ዘመን ወደሌላኘው የሚያሻጋግሩበት የአኗኗር ስልተ መንገድ ነው። ይህ እውቀቱ ራሱ ሊሆን ይችላል አልያም መንገዱ ሊሆን ይችላል። (ከባህል ማብራሪያዎቹ አንዱ እንደሆነ ይታሰብ) እንደመታደል ሆኖ ወደ ኋላ ሄደን ለጥብብ መሰረት የሆኑት የፎክሎር ሃብቶቻችን የትየሌሌ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በሀገራችን ኪነጥብብን የማድነቅ የዳበረ ባህል ቢኖረንም፤ ኪነጥብብ እንደ መሠረታዊ የለውጥ መንገድነቱ ቆጥሮ ፋይዳ ያለው ዘርፍ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነገር ባለመኖሩ ኪነጥብብን ከመዝናኛነት በዘለለ ለአዕምሮ ልማት እንዲሆን አድርጎ ባለመስራት፤ ኪነጥብብ የተዛባውን የልማት መሳሪያነቱን እንዲይዝ ሆነ።

ባህል ከየት ይጀምራል

ታዲያ ኪነጥብብ እንደባህል አድርጎ ለመቀጠል ሰዎች እንደሌሎች የባህል አካላት ከልጅነት ጀምሮ እንዲላመዱት ማድርግ አንዱ ዘዴ ነው። ኪነጥብብን ባህል አድርጎ ለማዳበር ደግሞ በቅድሚያ የምናገኘው ወደፊት ሀገርን ይረክቡልናል፣ ለነሱ ነው የምንሰራው ብለው በሚታስቡት ህፃናት ለይ መስራት አንዱና ዋነኛው ተቀዳሚ ስራ ነው። ኪነጥብብን ለልማት ለማዋል በቅድሚያ ዜጎች በህፃንነታቸው ኪነጥብብን እንዲያደንቁ፣ ፍቅር እንዲኖራቸው፣ ፋይዳውን እንዲያውቁ የሚያስችል ባህል እንዲኖራቸው ማስቻል ይገባል። እዚህ ለይ እንዳደጉት ሀገራት ኪነጥብብ ለልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አውቀው በትምህርት ካሪኩለማቸው ውስጥ አስገብተው እየሰሩ እንዳሉ ሀገራት በአንድ ጀንበር እንስራ እያልኩ አይደለም። ይህ ቢሆንና ሙያውንም እንዲያውቁ ሙያውን እያወቁ ሌሎች ትምህርቶችን እንዲማሩበት ማድረግ ቢቻል እሰየው ነበር። ይህንን በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለማየት ከባድ ነው። ይሁንና የኪነጥብብን ባህል ለማዳበር ዋናውና አንዱ መንገድ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ መቻሉ ነው። እዚህ ላይ ከዚህ ቀደም እንዳለው የስዕልና የሙዚቃ ክፍለጊዜ መምህሮቻችን እደጅ አውጥተው ዛፍ በሚያስሉን መንገድ፤ አልያም የሙዚቃ ክፍለጊዜ ፀሀይ ላይ ቆመን የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር እንደምንዘምርበት መንገድ ይሁን እያልኩም አይደለም። በእርግጥ እነዚህን ሁለቱ የኪነጥብብ መስኮች በዚህ መልክ መምጣታቸውን በወቅቱ የነበሩ ሰዎች በርግጥም ፋይዳቸውን ያውቁ ነበርና ሀሳባቸውን ሳላደንቅ አላልፍም። ታዲያ ይህንን ከብዙ ዘመን በፊት የነበረን ስራ መንቀፍ ምንድን ነው የሚለው የብዙዎች ሐሳብ ይሆናል። ይሄን ስል ፈፅሞ እየተቃወምኩኝ አይደለም፤ ይልቁንም እነዚህ ዘርፎች ካሪኩለም ውስጥ ሲመጡ ትምህርቱ ሊሰጣቸው የተሳቡት ተማሪዎች በአቅማቸው የልጅነት ህይወት ጋር የሚተዋወቁበት መሠረታዊና እነዚህን ጥበቦች በመጠቀም ለህፃናቱ የመግባባት፣ ራስን የመግለጥና የፈጣሪነት ክህሎታቸውን ሊያዳብሩ የሚችሉ፤ ባህልን ያማከሉ መማሪያ በባለሙያዎች ማለትም በኪነጥብብ በስነልቦና በማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ተጠንተው የተዘጋጁ መመሪያና መልመጃዎች ያስፈልጋሉ። ይሄ ሲሆን ህፃናት በህፃንነታቸው አንድም ስለሙያው ይዘውት የሚያድጉት ነገር ይኖራል፤ ሁለትም ሙያዎችን ተመርኩዞ ህፃናት ራሳቸውን የመግለጥ፣ የመግባባት እና የፈጠራ ችሎታቸውን ከፍ በማድረግ ጥብብ ልማቱን ይሰራል ማለት ነው። እውነት ጥብብ ለልማት መዋል ከተፈለገ አንድም ባህሉን በህፃንነት ጀምሮ እንዲተዋወቁት በማድረግ፤ ሁለትም የወደፊት ሀገር ተረካቢዎች፤ መልካም ዜጋ፣ ንቁ ፈጣሪና ራሳቸውን እንዲያውቁ በማድረግ ኪነጥብብን ለአእምሮ ልማት ማዋል ይገባል። እዚህ ላይ የኪነጥብብን ባህል ለማስፋትም ሆነ ኪነጥብብን ለልማት ለመጠቀም፤ በትምህርት ቤት ደረጃ ለመስጠት ሲታሰብ፤ ለህፃናት የሚሆኑ የኪነጥብብ ስራዎችን ሊያቀርቡ የሚችሉ ባለሙያዎች አለመኖር እንደጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይሁንና በህፃንነት ህፃናትን ለማስተማር የሚሆኑ ደረጃቸው የላቀ ስራዎች መጠበቅም ሞኝነት ነው። ይልቁንም ኪነጥበባዊ ለዛ ያላቸው ከቀደሙት ትውልዶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ባህላዊ ጨዋታዎችን ደግሞ ሰርቶና ለህፃናቱ በሚመች መልክ ማቅረቡ ሌላው አማራጭ ነው።

ባህላዊ የሕፃናት ዘፈኖች

የህፃናትን የህፃንነት ጨዋታዎችና ዝማሬዎች ህፃናትን ከኪነጥብብ ስራዎች ጋር ከማስተዋወቅም ሆነ ህፃናት ራሳቸውን በቀላሉ መግለፅ እንዲችሉ በማድረግ፣ ራሳቸውን ከህፃንነት ህይወት ጋር እንዲላመዱ አድርጎ የፈጠራ ክህሎታቸውንና የመግባባት ችሎታቸውን በማሳደግ ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው። እዚህ ላይ በሀገራችን እንደማጣቀሻ የተደረገ ጥናት ኖሮ ባለማግኘቴ የውጪዎችን ተጠቅሜ እንዳልፍ ሆኜያለሁ። በጃፓን osak. kyoikub univereseti መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ritsuko kojaima statese of tradtinal song *warab_uta* in Japanese scholl music curiculem በሚል ጥናታቸው፤ ህፃናት ባህላዊ የሆኑትን በእንቅስቃሴ እየታገዙ የሚቀርቡ ባህላዊ ዝማሬዎች እና ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ማደጋቸው በሰው ልጅ የዕድገት ደረጃዎች ውስጥ መሠረታዊ የሆኑትና ለአዳዲስ ፈጠራዎች መነሻ የሆኑትን በቀላሉ ከሌሎች ጋር የመግባባትን፣ የማዳመጥን፣ ራስን በደንብ መግለፅንና አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን የመስራት ኃይልና ክህሎት እንዲያዳብሩ ያስችላል በማለት ይገልፃሉ። ይህ ህፃናትን በኪነጥብብ ስራዎች እያገዙ ማስተማር ኪነጥብብን ባህሉን ማዳበር ብቻ ሳይሆን የህፃናቱን አዕምሮ በማልማት ትልቅ ሚና አለው። እነዚህን ህፃናትን በህፃናት ጨዋታዎች ማስተማር በሀገራችን ያለበትን ደረጃ ስንመለከት እጅግ አናሳ ነው ብዬ መናገር እችላለው። ምክንያም እንደ ዕድል ሆኖ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ኖሬ ስለማውቅና በአካባቢዬ የሚገኙ የእኔ ዘመን ወጣቶችም ሊመሰክሩልኝ ይችላሉና። የኪነጥብብ ስራዎችን ከህፃንነታችን እንድናፈቅራቸው ፋይዳቸውን እንድናውቃቸው ተደርገን ባለማደጋችን አሁን ድረስ የኪነጥብብ ስራዎች ከቀልድና ከቧልት የዘለለ ጥቅም እንዳላቸው እንዳናስብ አድርጎናል። ይህንን ክፍተት በመፍጠር ያለፉትም ሆነ አሁን ያሉት መንግስታት ብቻ ተጠያቂ ናቸው ብዬ አላስብም። ለምን ቢባል ደግሞ በልጅነት የምንጫወታቸውን ጨዋታዎች በማብራራትና በማጫወት ወላጆቻችን ትልቅ ድርሻ ይወስዳሉና ነው። ይህንን በልጅነታችን ወላጆቻችን ወይም ትምህርት ቤቶች ሲያስተምሩን በርካታ የጥብብ ይዘት ያሏቸው ከጨዋታ በዘለለ ውስጣቸው ትምህርት ያዘሉ የልጅነት ባህላዊ ጨዋታዎች፣ ዝማሬዎች ከባህል ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካቶች አሉ።

ባህላዊ ጨዋታ ለልማት እንዴት

ለኪነጥብብ ስራዎች መነሻ በመሆን፤ ባህላዊ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡት የስነቃል ሀብቶች ተጠቃሾች ናቸው። እንደ ማህበረሰቡ እና እንደየዘመናቱ የተለያዩ የኪነጥብብ ዓላማ ያላቸው የልጆች ጨዋታዎችና መዝሙሮች ይፈጠራሉ። እነዚህ ጨዋታዎች የኪነጥብብ ባህልን በማስረፅም ሆነ ለልማት በማዋል ትልቅ ፋይዳ አላቸው። እስቲ አንድ ጊዜ ወደ ልጅነት ጊዜያችን እንመለስና በልጅነታችን የተጫወትናቸውን ከባልና ሚስት እቃቃ ጨዋታ ጀምሮ ማህረቤን ያያችሁ፣ እርግጫ (ቃሉና ሐሳቡ ደስ ባይልም)፣ ሌባና ፖሊስ፣ አኩኩሉ፣ ከመዝሙሮች እቴ ሜቴ፣ መሸበትና፣ ከባህላዊ ክብረ-በዓሎች ደግሞ አበባዮሽ፣ ቡሄን እናስታውስ። እነዚህ የልጅነት ጨዋታዎች በአብዛኛው ኢትዮጲያዊ ዜጋ ህይወት ውስጥ የማይረሱ ጨዋታዎች ናቸው። እነዚህ ጨዋታዎች በሙሉ መቼት፣ ታሪክ፣ ግጭት፣ ሮል፣ ዜማ ዳንስ ስዕል የሚባሉትን የኪነጥብብ ዓይነቶች ዓላማ የያዙ ናቸው። እንደ ልጅ ያዝናኑናል። ማንም ሳይነግረን ከቀደሙት እየተቀበልን ከውነናቸዋል። ይሁንና በእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ኪነጥበባዊ ባህልን ብቻ ሳይሆን በርካታ አዕምሮን ሊያለሙ የሚችሉ እውቀቶች እናገኛለን። ነገር ግን ምን ያህሎቻችን በእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ያለውን ትርጉም ፋይዳ በልጅነታችን አሊያም ካደግን በኋላ ተነግሮናል። ምን ያህሎቹ ጨዋታዎች አሁንም እየተከወኑ ይገኛሉ። ባለመከናወናቸው የአሁኑ ትውልድ ምን ይቀርበታል ብለን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። ልማት የሚጀምረው ከአዕምሮ ነው። ማለትም ሰዎች የማያውቁትን ሲያውቁ ለለውጥ ይነሳሉ። በእውቀት ለይ የተመሰረተ ነገር ደግሞ ለውጡ ጠንካራና ፈጣን ይሆናል። እስቲ ከልጅነታችን ጨዋታዎች አንዱን እንውሰድ፤ አባሮሽ ይህ እኔ ባደግኩበት አካባቢ ብቻ ያለ ሊሆን ይችለላል፤ ነገር ግን ጨዋታው ህፃናት በቡድን ይመረጣሉ፣ የራሳቸውን አካባቢ ይወስናሉ፣ ከክልላቸው ሲወጡ አንዳቸው አንዳቸውን በማባረር በመንካት ምርኮ የማድረግ ስራ መስራት ነው። ጨዋታው ህጎች አሉት የተነካ ተማርኳል፣ ተባራሪው ሮጦ ወደ ክልሉ ከገባ አባራሪው ድንብር አልፎ መንካት መብት የለውም። ልብ እናድርግ እነዚህ ሕጎች በስምምነት የተሰሩ ናቸው። ማንም የተነካ መማረኩን ያምናል፣ አንዳቸው የአንዳቸውን ድንበር ማለፍም አይቻልም ለምን ቢባል ህጉ በስምምነት የተዘረጋ ነውና። ይህን ጨዋታ በልጅነታችን ከጨዋታ የዘለለ ለእኛ ምንም ነው። ግን እዚህ ጨዋታ ውስጥ ምን አለ ቀዳሚውና ለሰው ልጅ መሰረት የሆነው በምድራዊ ስምምነት መሰረት አድርጎ በተዘረጋ ህግ ማመንን ነው። ይህ ጨዋታ ለህፃናት ከጨዋታው በላይ በውስጡ ያሉትን ህግን የማክበር እውቀት፣ በምድር ላይ ሲኖር ማሸነፍና መሸነፍ ያሉ መሆናቸውን አይይዘው እየተነገረ ላደገ ህፃን በጉርምስናውም ሆነ በጎልማሳነቱ አልያም በእርጅናው ግዜ ለህግ መታዘዝን እንግዳው አይሆንም፤ ምክንያቱም የሕግን መኖር ባህሉን አዳብሯልና ነው። እንደነዚህ ያሉ የልጅነት ጨዋታዎች በርካታ ናቸው። ሁላችን ወደ ኋላ ሄደን ውስጣቸው ያለውን ትርጉም እናስብ። እዚህ ለይ አንድ ከቅርብ ዓመታት በፊት በአሜሪካ መንግስት የውድድር ጥሪ ተደርጎ የሁለት ህፃናትን ጨዋታ በማቅርብ ተሸላሚ የሆነውን አጭር ፊልም ማሰብ እንችላለን። በህፃንንት ያንን ጨዋታ ተጫውተን አድገናል። ተያይዞ ትርጉሙ እየተነገረን ብናድግ ዛሬ መቻቻልን መሸናነፍን ተቀብሎ አብሮ መኖር ለኛ ቀላል ነበር። በልጅነታችን የምናደርጋቸው ጨዋታዎች በውስጣቸው በርካታ የኪነጥብብን አላባ የያዙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ማንም ሳይነግረን ሳያስገድደን የምንጫወታቸው የሰፈርና የትምህርት ቤት ጨዋታዎች፣ ከበዓላት ጋር ተያይዘው የምናደርጋቸው እንደ አባባዮሽና ቡሄ የመሳሰሉት በውስጣቸው በርካታ እወቀቶችን የያዙ ጨዋታዎችን በትምህርት ቤትም ሆነ በቤተሰብ ከትርጉማቸውና ፋይዳቸው ጋር እየተነገረን ብናድግ ኪነጥብብ እንደባህል መውሰዳችን ብቻ ሳይሆን በርካታ እወቀቶችን ይዘን ባደግን ነበር። እስቲ በባህላዊ ክብር ባህሎች ወቅት በልጆች ከሚከወኑ ባህላዊ ጨዋታዎች አንዱን እንመልከት። የቡሄ ጭፈራ ቡሄ በዓመቱ መጨረሻ በወንዶች የሚከወን ዜማ ግጥም እና ዳንስን አካትቶ በልጆች የሚከወን ጨዋታ ነው። በቡሄ ጭፈራ ውስጥ ያለው የስራ ክፍፍል ማንም በመሀከላችን ገብቶ የሚደረግ ምርጫ ሳይሆን፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምፅ ያለውን ዜማ አውጪ፣ ጨዋውን ገንዘብ ያዥ፣ ጉልበተኛውን ከአደጋ ጠባቂ… እያደረግን በቡድኑ ውስጥ ባሉ የቡድን አባላት በሚደረግ ምርጫ ሮልን በመከፋፈል የሚከውን ባህላዊ የልጆች ጭፈራ ነው። በዚህ ጭፈራ ውስጥ ያለው የስራ ክፍፍል ከጨዋታነቱ በተጨማሪ ትርጉሙ ተነግሮን ብናድግ ዛሬ ሀገሪቷ ላለችብት አንድ ሰው ሁሉንም ማድርግ እንደሌለበት የሚጠይቅ ትውልድ መፍጠር በቻልን ነበር። ኪነጥብብን ለልማት ለማዋል በህፃናት ላይ ባህላዊ ጨዋታዎችንም ሆነ በባለሙያዎች የተጠኑ ጉዳዮችን የኪነጥብብን ሞያ በመጠቀም ህፃናቱ ከኪነጥብብ ስራዎች ጋር እንዲተዋወቁ፣ ኪነጥብብን ለአዕምሮ ልማታቸው ማሳደጊያ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ኪነጥብብ ለልማት ማለት እንዲህ ያሉ ባህላዊ እውቀቶች ትርጉም ጨምሮ በማስተማር ጠያቂና ምክንያታዊ ማህበረሰብ መፍጠር ማለት ነው። ኪነጥብበ ለልማት ለማዋል እነዚህ የህፃንነት ጨዋታዎችን በማሳደግ ዜጎች ወደ ፊት ሲያድጉ የኪነጥብብ አድናቂ ፋይዳውን የሚያውቁ አድርጎ መስራት ሲቻል ነው እንጂ በስምንት እና በአስር እድሜ ላይ ያሉ ህፃናትን ምንም ስላማያውቁት ፌድራሊዝም ግጥምና ዜማ ሰጥቶ በማዘፈን አይደለም። ኪነጥብብ ለልማት ዋለ የሚባለው ህፃናት በአግባቡ መጥራት የማይችሉትን ማሳለጫ የሚል ቃል ያለው ግጥም በዜማ አዝፍኖ አይደለም። ይልቁንም ኪነጥብብ ለልማት ዋለ የሚባለው፤ ህፃናት በልካቸውና በጨዋታ መልክ ለጥያቄያቸው ራሳቸው መልስ የሚያገኙበት መንገድ መፍጠር ነው። የነገ ሀገር ተረካቢዎች የሚል ግጥምና ዜማ ሰርቶ ህፃናትን ማዘመር ኪነጥበብን ለልማት ማዋል ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ህፃናት በአቅማቸው የሚገባቸውን ነገር በቀላሉ አይረሴ በሆነ መንገድ እንዲያውቁ የሚችሉበት፤ ራሳቸው ተረድተው ለሌሎች የሚያስረዱበት መንገድ ሲኖርና በእድሜ ልካቸው ማወቅ የሚገባቸውን ነገር ለማሳወቂያት መጠቀም ሲቻል ነው። ኪነጥብብ ለልማት ዋለ የሚባለው ህፃናት በልጅነታቸው ከሙያው ጋር የሚተዋወቁበት ስጦታ ካላቸው እንዲገፉበት የሚያስችል ማዕከል ሲኖር፤ አልያም የሚፈልጓቸውን የትምህርት ዘርፍ በቀላሉ እንዲረዱት ለማድረግ ኪነጥብብን እንደማስተማሪያት በመጠቀም ህፃናት ሲያድጉ ከዋኝ ባይሆኑ የሞያውን ፋይዳ አውቀው ደጋፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ሁኔታ ሲፈጠርና የዳበረ የኪነጥብብ ባህል ያለው ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው። ይህ በሌለበት ኪነጥብብን ለልማት ማሰብ ከቀልድ የዘለለ አይሆንም። እነዚህ በካሪኩለም ጋር ተያይዞ መሰጠቱን ትተን እንኳ፤ ህፃናት የኪነጥብብ ፍቅርም ሆነ ባህሉን የሚያዳብሩበት ቦታ ማዕከል አለ ብለን ስናስብ የለም ለማለት በሚያስችል ደረጃ እናገኘዋለን። በቀላሉ በአዲስ አባባ ውስጥ ያለውንና ህፃናትን ኪነጥብብን ሊያውቁበት በልካቸው የሚሆን እውቀት ሊሰጡበት የሚችል አንድ የህፃናት ትያትር ቤት ይዞ፤ ኪነጥብብን ለልማት አውላለው ብሎ ማሰብ በሙያው ለይ መሰላቅ በትውለዱ ለይ ከማሾፍ የዘለለ ነገር የለውም። ባህል በአንድ ጀንበር አይፈጠርም። ስለዚህም የኪነጥበብን ባህል በሌላው ማህበረሰብ ውስጥ ሲመሽ ኪነጥብብን ለልማት አውላለው ብሎ መነሳት በሀገር ንብረትና መቀለድ ነው። ስለዚህ ኪነጥብብን ለልማት የሚያስብ መንግስትም ሆነ ህዝብ መጀመሪያ ሊሰራ የሚገባው ህፃናት ላይ ነው። አሁን ያሉ ህፃናት እኛ የተጫወትናቸው ጨዋታዎች እንደነበሩ የማያውቁበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ያደጉት ሀገራት የቀደሙትን አፈ-ታሪኮች፣ ተረቶች በማሳተምና በትምህርት ካሪኩለማቸው ውስጥ ከማስገባታቸው በተጨማሪ ቤተሰብ እያነበበ ስለሚያሰድጋቸው፤ በኪነጥብብ ፋይዳ ላይ ከፍ ያለ እውቀት ከማኖራቸው በተጨማሪ እንደ አንድ እውቀት በመውሰድ በሀገር እድገት ለይ ያለውን ፋይዳ በማወቅ ዘርፉ ውስጥ ባይገቡ እንኳ ዘርፉን በማገዝ ከኪነጥብብ ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ ይገኛሉ። መንግስታተም ይህንን ጥቅም በማወቃቸው፤ ኪነጥብብን ከልጅነት ለዜጎች በማዳረስ ኪነጥብብን ብቻ ሳይሆን ኪነጥብብ ለሌሎች የእውቀት ዘርፎች በማስተማሪያነት እየተጠቀሙበት ይገኛል። እዚህ ላይ ካናዳ ውስጥ Jan Harasim የተባሉ ተመራማሪ ‹The Value of Arts Education› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሃፋቸው ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ትምርት ቤት የኪነጥብብ ትምህርቶችን የተማሩት ተማሪዎች ኪነጥብብ ካልተማሩት እጅግ በላቀ ፈጠራ በፍጥነት ነገሮችን የመጋፈጥ፣ ሐሳባቸውን የመግለፅና ከሌሎች ሰዎች ጋር በቃላሉ የመኖር አቅማቸው ከፍ ያለ ነው በማለት ይገልፃሉ። ስለዚህ ኪነጥብብን ለልማት ለማዋል ሲጀመር የኪነነጥበብ ባህል የዳበረና የኪነጥብብ ፋይዳን የሚያውቅ ማህበረሰብ መፍጠር አለብን። ይህንን ማድረጊያ ሁነኛ ቦታ ደግሞ ህፃንነት ሲሆን፤ መንገዶቹ ባህላዊ ጨዋታዎችን ዶክመንት አድርጎ ከማሰናዳት ጀምሮ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ማስገባት ናቸው። ይህንን በሀገራችን ስንመለከተው ምንም ያልተሰራበት ሆኖ እናገኘዋለን። ስለዚህም ኪነጥብብን ለልማት በሀገራችን ለማዋል ያልሰራነው ስራ አለና ከባድ ነው ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ተነስተን ወሳኙ የኪነጥብብ ባለድርሻዎች የሚፈጠሩበት የኪነጥብብ ባህል የለንም ማለት እንችላለን።

ከያኒዎችስ አሉን

ስለከያኒያን ስናስብ ልብ ልንለው የሚገባው ከማህበረሰብ ውስጥ የሚወጡ የተፈጥሮ ስጦታ ያላቸው፣ ማህበረሰባቸው ውስጥ ያለውን መልካም ነገር እንዲሻሻል የሚፈልጉትን፣ ለማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን ለመሪዎች ፖሊሲ ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦችን በማንሳት ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ባለሙያዎች ናቸው። የኪነጥብብ ስራዎች የተፈጥሮ ችሎታን ብቻ በመያዝ ከሚሰራበት ዘመን ተወጥቷል። ለምን ቢባል ደግሞ እንደሌሎች ሙያ ሁሉ የኪነጥብብ ስራዎችም በልኬትና መጠን ሳይንሳዊ መለኪዎችን ይዘው የሚሰሩ ስራዎች ሆነዋልና ነው። የኪነጥበብ ባለሙያ ለመሆን ስለ ኪነጥብብ ሞያ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ባለዕውቀት መሆንንም ይጠበቃል። ምክንያቱም የኪነጥብብ ስራዎች እውነትን መሠረት አድርገው የሚሰሩ ስራዎች ናቸውና፤ እውነት ደግሞ ከማንብብ ከመማር ነው የሚገኘው። የኪነጥብብ ባለሙያዎች በትንሹ የጠለቀ የስነልቦናና የማህበራዊ ሳይንስ፣ ታሪክ እውቅት ሊኖራቸው ይገባል። ለምን ቢሉ ደግሞ ስራዎችን የሚያቀርቡለት ማህበረሰብ አስተሳሰብና አኗኗር ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸውና ነው። ከዚህ በተጨማሪ ስራዎቻቸውን የሚያተኩርባቸውን ጉዳዮች በሙሉ ማወቅ ግዴታቸው ነው። ስለዚህም ዘርፈ-ብዙ ባለሙዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል። ታዲያ ይህንን ሁሉ ኃላፊነት የያዙ የሀገራችን የኪነጥብብ ባሙዎች ሀገሪቷ ውስጥ አሉን? የመጀመሪያ ጥያቄ መሆን አለበት። ከላይ እንደጠቀስነው ልማት በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች መበልፀግ ነው። በእነዚህ ጉዳዮች ለመበልፀግ ደግሞ እውቀት ወሳኝ ነው። ታዲያ ሌሎች ሙያዎችን ሳይሆን ኪነጥብብ ራሱን በእወቀት ደረጃ የሚሰጥበት ተቋም በሌሉበት ሀገር እንዴት ተብሎ የዜጎችን አዕምሮ የሚያለሙ ስራዎች መስራት ይቻላል። ምንም እንኳ የሰው ልጅ ሀ ብሎ ከፊደል ዋይ ብሎ ከመከራ ይማራል ቢባልና፤ ከመከራ እየወደቁ እየተነሱ ራሳቸውን ያስተማሩ የኪነጥብብ ባለሙያዎች ቢኖሩንም፤ እነሱም ካሉበት ሙያ በቀር በሌሎች መስኮች ያለቸው እውቀት አናሳ ነው። ለምን ቢባል ደግሞ አይደለም ሌሎች የትምህርት መስኮች ራሱ ኪነጥበብንም ትምህርት አያስፈልገውም የሚል የቆየ ልማድ ውስጥ ነበሩና ነው። ታዲያ የመንግስት ሹማምንታትና የመገናኛ ብዙሀን ፋሸን ያደረጉት ኪነጥብብን ለልማት ማዋል አሁን ይቻላልን። አይቻልም ምክንያቱም የኪነጥብብ ባለሙያ በትዕዛዝ የሚመጡትን ሀሳቦች አስተጋቢ ሳይሆን፤ ራሱ በመመራመር ያገኘውን አልያም ሌሎች የምርምር ውጤቶችን መሰረት አድርጎ የሚበጁ የሚባሉትን በኪነጥበብ ለዛ ቀብቶ የሚያቀርብ ነውና ነው። እዚህ ለይ ልብ ሳይባል መታለፍ የሌለበት በትያትር ሙዚቃና ስዕል ላይ የረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው ተቋማት መኖራቸው ነው። ይሁንና እነዚህ ተቋማት በእርግጥም ለማህበረሰብ ግልጋሎት ሊሰጡ የሚችሉ ባለሙዎች እያፈሩ መሆናቸው አጠያያቂ ነው። ስለነዚህ ተቋማት ወደ ፊት በስፋት ማየት ስለምፈልግ በደፈናው እየሰጡ አይደለም ብዬ ባልፍ ድፍረት አይሆንብኝም። ምክንያቱም በእነሱም ሆነ ሌሎች ችግሮች ውጤታማ አይደሉምና ነው። ስለሆነም መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣቸው መግለጫዎችም ሆነ ፅኑ የሆነ ኪነጥብብን ለልማት የመጠቀሙ ፍላጎት እውን ይሆንለት ዘንድ ከላይ ወደታች የሚወርድ ትዕዛዝና ሰነድ ማዘጋጀት ሳይሆን መፍትሄው፤ የኪነጥብብ ተሰጧቸውን የያዙ ባለሙያዎች በትምህርት የሚያግዙባቸው ተቋማት መክፈት ሁለተኛው አማራጭ ነው። ምክንያቱም ኪነጥብብ ትልቅ የሆነ አሳቢና ሰፊ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ያስፈልጉታልና ነው።

ሃያሲ

ሃያሲ ተጨባጭ በሆነ ነገር ላይ መሰረት በማድረግ ለህዝብ የሚቀርቡ የኪነጥብብ ስራዎች በጎውን ይበል ስህተቱን ደግሞ በምክንያት አይደረግም አይባልም እያለ የተመልካቹንና የከያኒዎችን እውቀት ከፍ የሚያደርግ ባለሙያ ነው። እነዚህን ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የኪነጥብብ ስራዎች ለይ ለማግኘት መጠበቅ የማይታሰብ ነው። ለእነዚህ ባለሙያዎች መፈጠር ተቋማት ትልቅ ፋይዳ አላቸው። ይሁንና ካሉት ተቋማት ውስጥ እንኳን እነዚህን ማግኘት አልቻልንም። ለእዚህም ነው በአሁኑ ሰዓት የሚሰሩ የኪነጠብብ ስራዎች አቤት ባይ አጥተው በቤተሰብ በመደራጀትና በጓደኝነት ያዝ እንግዲ እየተባሉ በሚሰሩ ስራዎች ገበያው ተሞልቶ የምናየው። ስለዚህ ከባለድርሻው አካል ዋናው የሆነው የሂስ ባለሙያዎች ሳይዙ ኪነጥብብን ለልማት ማዋል አሁንም የማይታሰብ ነው። ኪነጥብብ ለልማት ማለት የብሄር ብሄረሰብ ዳንስ የባህል ልብስ አልብሶ ማስደነስ ሳይሆን ዳንስ ውስጥ ያሉ ምክንያቶች፤ አልባሳቱ ውስጥ ያሉ ትርጉሞችና ጥቅማቸውን ለማህበረሰብ ማድረስ ነው። ትልቅ ጉዳይ ማንሳት ትልቅ የኪነጥብብ ባለሙያ አያስብልም ይልቁንም ትንሽ ሀሳብን አንስቶ ትልቅ አድርጎ ማቅረብ ነው የኪነጥብብ ባለሙያ የሚያስብል፤ አባይን ተባብረን እንገንባ የሚል ጋዜጠኛ እንጂ የኪነጥብብ ባለሙያ አይደለም። የኪነጥብብ ባለሙያ አባይን መገንባት ሳይሆን መተባበርን ወደፊት ተስፋን መጣርን በመንገር፤ መፎከር ሳይሆን አዕምሮን የሚያሳምን ስራ የሚሰራ መሆንን፤ ትዕዛዝን ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችል ስራ የሚሰራ መሆኑን የሚናግር ሃያሲ ሲኖር ነው ኪነጥብብ ለልማት መዋል የምትችለው። አለበለዛማ ከላይ በትዕዛዝ የሚመጣውን ሐሳብ በማስተናገድ ካድሪዎች ምን ይሰራሉ። ስለዚህ ኪነጥብብን ለልማት ለማዋል ሀገራት በመጀመሪያ ባህሉን መፍጠር፤ ከዚያም ባህሉ ከፈጠራቸውና የተመረጡ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ እውቀት የሚያገኙበት ተቋማትን ማሰናዳት፤ በህዝቡና በባለሙያዎች መሃል ሆነው የሚሄሱ የተሳሳተውን የሚያቀኑ የበሰሉ የሂስ ባለሙያዎችን ማሰናዳት ይገባል። እነዚህ ለኪነጥብብ መኖር ምክንያት የሆኑት ባለድርሻዎች ሲኖሩ፤ መንግስትና መሪዎች ስላሉ ሳይሆን እራሱ ኪነጥብብ በፍጥነትና በስፋት ለልማት መዋል ይጀምራል። እነዚህ በሌሉበት ኪነጥብብን ለልማት ማዋል ግን፤ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደመውጣት ነው። ስለዚህ እኔ መንግስትም ሆነ ህዝቦች ከኪነጥብብ ማግኘት ያለብንን ጥቅም እናገኝ ዘንድ ነፃና ጠያቂ ከዚያም ሲያልፍ በምክንያት የሚያምን ትውልድ ለማፍራት ሀገር እንደሌሎች ሀገር ታድግ ዘንድ ኪነጥብብን የሚያደንቅና ከቀልድ ጋር ብቻ የሚያያዝ ትውልድ ሳይሆን፤ ፋይዳውን የሚያውቅ ትውልድ መፍጠር ተገቢ ነው እላለው። ለዚህም ደግሞ ሞያዉን ከህፃንንት ጀምሮ እንዲሰጥ በማድረግ ባህሉንም ሆነ ፋይዳውን የሚያውቅ ትውልድ በመፍጠር በእውቀት የበለፀጉ ከያኒያንና ሃያሲያን መፍጠር ቀዳሚ ስራ ማድረጉ ይጠበቅብናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top