ፍልስፍና

መንፈስ በጊዜ እና በቦታ ላይ

1. መግቢያ

በታዛ ቁጥር 38 እትም ላይ “የዘመን መንፈስ፣ የጋራ ህልውና እና ለውጥ” በሚል ርእስ በቀረበ ጽሑፍ “ለመሆኑ በዚህ የለውጥና ቀጣይነት እሳቤ አላፊ ዘመኖች ወይም የዘመን መንፈሶች እንዴት ይነበባሉ፤ እንዴትስ ከዛሬው ጋር ይናበባሉ? በቀጣይ የዘመን መንፈስን እሳቤ በታሪክ ንባብ ማሳያነት እንመለከታለን” በሚል ቀጠሮ ነበር የተለያየነው። ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች በህሊናዬ እየተመላለሱ፣ በዚያም ላይ ትንሽ ነገር መናገር አስፈላጊ መስሎ ስለተሰማኝ፣ ይህንን ጉዳይ አሁንም በይደር በማቆየት አንድ ሁለት ጉዳዮችን ማስቀደም ግድ ብሎኛል። የመጀመሪያው፣ መንፈስ በጊዜ፣ በቦታና በቁስ ላይ አድሮ በከበራ፣ በአምልኮ፣ በማሕበረሰባዊ ክዋኔ አማካኝነት የህይወት አንድ ዘውግ የሚሆንበትን ጉዳይ ከእኛነት ኑባሬ፣ ከማንነት ትርጓሜ፣ ከነጽሮተ/ርዕዮተ ዓለም ጋር ያለውን ስውር-ስፍ መፈተሽ ነው። ሁለተኛው የዘመንን መንፈስ፣ መንፈስ በቁስ፣ በቦታ ወይም በጊዜ ላይ ሲያድር፣ መንፈሱን ለማንበብ፣ ለመረዳት እንዲሁም ለመተርጎም የምንከተላቸውን ዘዴዎች የሚመለከት ነው። በዚህኛው ጽሑፍ የምንመለከተው መንፈስ በጊዜ ውስጥ፣ መንፈስ በቦታ ላይ፣ ህሊና (አስተሳሰብ፣ ርዕዮተ ዓለም ወይም ሥልጣኔ) በቁስ ላይ፣ ያለውን ቦታ ማተት ነው። መንፈስ ከባህል፣ ከሃይማኖት፣ ከፍልስፍና፣ ከማኅበረሰብ ተኮር ጥናት፣ ከሐተታ-ተፈጥሮ፣ ከነገረ-ሰውነት አንጻር መታየት ያለበት ጉዳይ ነው።

ይህ ጽሑፍም መንፈስ በቦታና በጊዜ ውስጥ ያለውን አንድምታ ከፍልስፍና አንጻር ይመለከታል። ለዚህ ጽሑፍ አንዱ መነሻ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት (ለምሳሌ በወርሃ መስከረም፣ የጸደይና የመኸር ወቅትን ጠብቀው) የሚከበሩ፣ ሃይማኖታዊ እና ማሕበረ-ባህላዊ ይዘት ያላቸው ሕዝባዊ በዓላት ሰውና ተፈጥሮ፣ ሰውና አማልክት ያላቸው መስተጋብር በመንፈስ አማካኝነት የሚገለጹበት አግባብ ምንድን ነው? የሚል ነው። እንዲሁም በተለያዩ ብሔረሰቦች ዘንድ አድባራት፣ ወንዞች፣ ውሃዎች፣ ጥቅጥቅ ደኖች፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቁሶች መንፈስ ያደረባቸው እንደሆኑ ይታመናል። ይህ አስተሳሰብ ከሰው ልጆች የሥነ-እውቀት፣ የነገረ-ሕልውና፣ የሥነ-ምግባር አስተሳሰቦች፤ በሰውና በሌላው ተፈጥሮ፣ በሰውና በልዕለ-ተፈጥሮ አካላት መካከል በሚኖር መስተዋድድና ተግባቦት (Solidarity and communication) መንፈስ ምን ቦታ ይኖረዋል? የሚሉ መነሻ ጥያቄዎች የዚህ ሐቲት ማጠንጠኛ ጉዳዮች ተደርገዋል። ለዚህም መንፈስ በጊዜ ውስጥ ሰፍኖ እና መንፈስ በቦታ ላይ አድሮ በሰዎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ እንዲሁም በጋራና በግል ማሕበረ-ስነ-ልቡናዊ አስተሳሰብ ላይ የሚያሳድረውን አገብሮት (influence) በአጭሩ ለመዳሰስ ተሞክሯል።

የህልውና ቁሳዊ መሰረቱ ምንም ይሁን ምን (ለምሳሌ፣ አራቱ ሃልዮቶች ማለትም እሳት፣ ነፋስ፣ ውሃ፣ አፈር) ከጊዜና ቦታ ማዕቀፍ ውጭ ትርጉም አይኖረውምና (ስቴፈን ሃውኪንግ እንደሚለው) መንፈስ በጊዜና ቦታ ላይ ሲያድር ለህይወት እስትንፋስ በመሆን ነፍስ ዘርታ እንድትንቀሳቀስ ያደርጋታል ተብሎ ይታመናል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “መንፈስ” የሚለው ቃል “የዘመን መንፈስ” ከሚለው ትርጓሜ የተለየ ሲሆን የሁለንተናዊ እውነታ አንድ አካል፣ ከቁስ በአንጻራዊነት የሚገኝ የማይታይ፣ ስውር ኃልዮት ነው። እውነታን (reality) በአንድ በኩል ቁስ በሌላ በኩል መንፈስ፣ ሐሳብ ወይም ህሊና (matter and spirit) ብሎ መክፈል የተለመደ ነው። ክርክሩም አንዱን መግደፍ፣ ሌላውን ማግዘፍ ወይም የቱ ይቀድማል፣ የቱ የበለጠ እውነታን ይገልጣል? የሚለው ላይ ነው። በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት ሁለቱን መሳ ለመሳ በማስቀመጥ እውነታን በምልዓት ለመረዳት የሁለቱን መፈራረቅ፣ ቁርኝት ማጥናት ይኖርብናል። ከዚህ ሰፊ የጥናት ሸክም ለዛሬ መነሻ ይሆን ዘንድ የተፈጥሮ፣ ልዕለ-ተፈጥሮ እና የሰው ልጆች ህያው መንፈስ በቁስ እና በቦታ ተመስሎ በህዝቦች ኑሮ ውስጥ ያለውን አንድምታ መመልከት ነው።

1. መንፈስ በጊዜ ውስጥ

መንፈስ በጊዜ ውስጥ ያድራል ስንል ጊዜ በረቂቁ ወይም ጊዜ በዝርው ነው። በዝርው ባለፈው እንዳየነው በልኬት የሚቀርበው ነው። በዚህ አረዳድ መንፈስ በቀጠሮ በሚደርስ ጊዜ አማካኝነት ራሱን እንደሚገልጽ ይታመናል። የዚህ የጊዜና መንፈስ ቁርኝት እሳቤ መነሻው እንደየማኅበረሰቡ እምነት እና አስተሳሰብ ቢለያይም የጋራ የሚያደርገው ሰዎች ለቀናት፣ ለወራት ወይም ለሳምንታት፣ በጊዜ ቀጥተኛ የትናንት፣ ዛሬና ነገ ዑደት ውስጥ በተቀመጡ ቀነ-ቀጠሮዎች መንፈስ ራሱን ይገልጣል የሚል ነው። ወቅቶች የራሳቸው መገለጫ አላቸው፤ በተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ ሁነቶች አማካኝነት ጎልተው የሚወጡ ገቢራት የወቅቶቹን መንፈስ አመላካች ናቸው። ለምሳሌ በሙሴ ሕግ የሚመሩ ሃይማኖት ተከታዮች ከአሰርቱ ትዕዛዛት ውስጥ አንዱ ሰንበትን አክብር ቀድሳትም የሚል ነው። ሰንበት ለምን መከበር አለባት? ለሚል ጥያቄ የሃይማኖት አስተምህሮዎቹ የራሳቸው ማብራሪያ ቢኖራቸውም ማጠንጠኛው ፈጣሪ በረከቱን የሚገልጥባት ቀን በመሆኗ ነው የሚል ነው። እንዲሁም ቅዱሳን የተወለዱበት፣ የሞቱበት እና በተለየ ሁኔታ ገድላቸውን ፈጽመውባቸዋል ተብሎ የሚታመኑ ዕለታት መንፈስ እንደተዋሃዳቸው፣ ለቅድስናቸውም የመንፈስ መሪነት (ቴዎድሮስ ገብሬ የተጋድሎ ጥሪ ይለዋል) ጉልህ ድርሻ ስላለው፣ በመታሲቢያነት የጻድቃኑ፣ የመላእክቱ፣ የሰማዕታቱ በረከት በሰዎች ላይ ያድራል ተብሎ ይታመናል። እንደዚህ ዓይነቶቹ አስተሳሰቦች ሰዎች መንፈስን በቀጠሮ አማካኝነት በጊዜ ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት እንደሚያገኙት ያምናሉ። መንፈስ ምንም እንኳ ሁሌም ያለ ቢሆንም በቀናቶቹ ውስጥ ግን በተለየ መልኩ እንደሚገለጥ ይታመናል።

ጊዜ በረቂቁ ደግሞ መንፈስ ራሱን የሚገልጠው ሰዎች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች አማካኝነት፣ ወይም በፈጣሪ ፈቃድ በኩል ነው። ሰዎች ጽድቅ ሲሰሩ አማልክቱ በመደሰት በረከታቸውን፤ ሰዎቹ ኃጢአት ሲሰሩ ደግሞ ቁጣቸውን ይልካሉ ተብሎ ይታመናል። ይህ መንፈስ በጊዜ ውስጥ የሚገለጠው በቀጠሮ ሳይሆን ለሰዎች ገቢራዊ እንቅስቃሴ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ይታሰባል። በዚህም አንዳንድ ወቅቶች በሚያሳዩዋቸው ምልክቶች አማካኝነት ሰዎች በመደንገጥ ወይም በመደሰት የአማልክቱን ቀጣይ ምላሽ ወደጠቃሚነት የሚያመሩ ክዋኔዎችን ያደርጋሉ። ለምሳሌ አደጋ ባንዣበበ ጊዜ በልመና፣ በመስዋዕት፣ እና በምልጃ አደጋው እንዲጠፋ ወይም እንዲቀንስ ይማጸናሉ። የፈጣሪ በረከት ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆነ ሲገምቱ ደግሞ ይህ በረከት ሙሉ ፍጹም እንዲሆን የምስጋና እጅ መንሻ ያቀርባሉ። በዚህ በቀጠሮ ባልተያዘ ከበራ ውስጥ መንፈስ ራሱን እንዲገልጥ የሰዎች እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ አለው የሚል እምነት አለ። በኢትዮጵያ የሚከበሩ ህዝባዊ በዓላት የዚህ መንፈስ በጊዜ ውስጥ ይገለጣል የሚል መሰረታዊ እምነት የወለዳቸው ናቸው። ለምሳሌ፣ እንደ መስቀል፣ ጥምቀት፣ አረፋ፣ ትንሳኤ፣ መውሊድ፣ ኢሬቻ፣ ዱበርቲ፣ ዛር ድግስ ያሉ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት የዚህ ማሳያዎች ናቸው። በዚህ ውስጥ የሚስተዋለው ነገረ-ሕልውና እና ሐተታ-ተፈጥሮ ምንድን ነው? እነዚህ ክዋኔዎች ሰዎች በተለያየ ጊዜ ከፈጣሪያቸው ጋር፣ ከአያት ቅድመ-አያት መንፈሶች ጋር የሚነጋገሩባቸው መንገዶች ናቸው። በዚህም ፈጣሪ በመንፈስ አማካኝነት በረከቱን ይገልጣል፣ ሰዎችም በከበራው አማካኝነት በሚቀርቡ እጅ መንሻዎች፣ ለሌሎች ሰዎች በሚያሳዩት ፍቅርና አበርክቶዎች፣ በደስታና ምስጋና መግለጫ ክዋኔዎች (ጸሎት፣ ምህላ፣ ጭፈራ፣ዝማሬ፣ ፌሽታ) ለፈጣሪያቸው ያላቸውን ተገዥነት እና የቃል-ኪዳንን ውል ያድሳሉ ማለት ነው። ይህም ብቻ አይደለም እንደ ተዝካርና ሰደቃ ያሉ የመታሰቢያ በዓላት በመንፈስ አማካኝነት በሙታን እና በህያዋን መካከል ያለ ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን የታለሙ ናቸው። ህያዋን የሙታን ነፍስ ይመቻት ዘንድ ለፈጣሪ ይለምናሉ፤ ሙታን በምላሹ በረከታቸው በህያዋን ምድራዊ ሕይወት ላይ አንዳች አዎንታዊ ፋይዳ ይኖረው ዘንድ ይራዳሉ የሚል እምነት አለ። በዚህም የሰው ልጆች ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ በጽኑ እንደሚያምኑ ማሳያ ነው።

3. መንፈስ በቦታ ላይ (የተቀደሰ ቁስ ወይም ቅዱስ ቦታ)

“ሰብ ይቄድሶ ለመካን ወመካንሰ ይቄድሶ ለሰብ” (ሰው ቦታን ይቀድሳል ቦታም ሰውን ይቀድሰዋል)

አንድ ተግባር በጊዜ አማካኝነት በቦታ ምንጣፍ ላይ እንደሚንከባለል ኳስ ነው። ጊዜ ያለ ቦታ፣ ቦታን ያለ ጊዜ ክዋኔን ደግሞ ያለ ቦታና ጊዜ ማሰብ አይቻልም። መንፈስ በጊዜ ውስጥ ያድራል ስንል፣ እንበለ መካን (ያለ ቦታ) ሊታሰብ አይችልም። በዚህም መንፈስ በቦታ ላይ፣ በቁስ ላይ ራሱን ይገልጣል። ዴቪድ ፕሮውን የተባሉ የባህል ተመራማሪ “Mind in Matter: An Introduction to Material Culture Theory and Method” በሚለው መጣጥፍ ውስጥ መንፈስን በቁስ ላይ አድሮ የግለሰቦችን ወይም የማሕበረሰቦችን ህሊናዊ፣ ባህላዊና ልቡናዊ አሻራቸውን ይገልጣል፣ ከቦታ ቦታ፣ ከዘመን ዘመን ያሸጋግራል ይሉናል። በቁስ አማካኝነት የሚተላለፍ መልዕክት ወይም የሕይወት ውክልና አለ። “Therefore, objects are signs that convey meaning, a mode of communication, a form of language” (ገጽ 16) መንፈስ በቦታ ላይ ወይም በቁስ ላይ ያድራል ሲባል በአንድ የተከለለ የተፈጥሮ ንፍቀ-ክበብ፣ የእደጥበብ ወጤት በሆነ ሥሪት፣ ለአምልኮት ተግባር በተዘጋጀ ቁስ ላይ፤ በፈቃድ ወይም ያለ ፈቃድ፣ በድንገትም ይሁን ሆነ ተብሎ በሚደረግ እቅድ፤ የአንድ ማህበረሰብ ባህል፣ እምነትና አስተሳሰብ፤ የአንድ ዘመን አሻራ፣ እንዲሁም የልዕለ-ተፈጥሮ ፈቃድ ያረፈበት መሆኑ፤ እና የማይታየው ስውር መንፈስ ግዝፍ ነስቶ የሚታይበት ውክልናዊ ገበታ ወይም አትሮኖስ መሆኑ ነው።

ቁሶች ግዑዛን መሳሪያዎች ብቻ አይደሉም። ምልክቶች ናቸውና የሚያስተላልፉት የዘመንና የቦታ መንፈስ፣ የሚናገሩት አስተሳሰብ እና የሚወክሉት ማኅበረሰባዊ የሕይወት ዘይቤ፣ ፍልስፍና እና አስተሳሰብ አላቸው። ታዲያ መንፈስ በቦታ ላይ ይገለጣል ሲባል እንዴት ነው? ማሕበረሰቦች መንፈስ ይገለጥበታል ወይም ለመንፈስ ግብር ይቀርብበታል የሚሉትን ቦታ ራሳቸው ያዘጋጃሉ ወይም በተፈጥሮ ተዓምር የተመረጠ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ከውሃዎች ሁሉ ተመርጦ ለመድሃኒትነት የሚሆን ጸበል በተፈጥሮ ተዓምር የሚገለጥ ሲሆን ሰዎች ከልለው የሚያከብሩት ቦታ ደግሞ ለመንፈስ ማደሪያነት በሰዎች እና በፈጣሪ ትብብር የተመረጠ ነው። እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ተብለው የሚሰሩ አብያተ-ክርስቲያናት እና በዙሪያቸው ያለው አጸድ የመንፈሱ ማረፊያዎች ናቸው። በውስጣቸው ያሉ እንደ ታቦት፣ ስእላት፣ መስቀል፣ እና አልባሳት ደግሞ የመንፈሱ ማደሪያ ውክልናዊ ቁሶች ናቸው። በዚህ አኳኋን በሰው ልጆች አስተዋጽኦ እና በፈጣሪ መሪነት ቦታዎቹ የተቀደሱ እንደሆነ፤ ሰውንም የሚቀድሱ እንደሆኑ ይታመናል። አንዳንዶች እንዲያውም (ለምሳሌ ጆን ኒቫላ) ሰው ሰራሽ አካባቢዎች (built environment) በጥቅሉ መንፈስ የተዋሃዳቸው ከአካላዊ ባሻገር ስነ-ልቡናዊም ናቸው ሲሉ ይደመድማሉ። እንደ ጠልሰም፣ ቆቲ (ከወላጅ ወደ ልጅ የምትተላለፍ በትር)፣ ሌሎች የአምልኮ እቃዎች ደግሞ መንፈስ ከወላጅ ወደ ልጅ ማስተላለፊያ መንገዶች ናቸው።

ከእነዚህ አስተሳሰቦች ሁለት መሰረታዊ ነገሮች መማር እንችላለን። አንደኛው በእንደዚህ ዓይነቶቹ ማኅበረሰባዊ አስተሳሰቦች አማካኝነት የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ፍጹም የተለየ፣ ራሱን ከሌላው ዓለም ነጥሎ የሚመለከት በዝባዥ ፍጡር ሳይሆን የተፈጥሮ አንድ አካል፣ መልካም ወዳጅ አድርጎ መመልከቱ ነው። በዚህም መላዋ ተፈጥሮ በስውር-ስፍ የተሳሰረች እንደሆነች የሚያሳይ ነው። በታዛ ቁጥር 23 ላይ በቀረበ ጽሑፍ እንዳየነው በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ጥናት ያደረገው ሳምነር እንደደመደመው “የኢትዮጵያውያን ዓለም ሰዋዊ ዓለም ነው” ሰዋዊ ዓለም ሲባል ምንድን ነው? በአጭር ቃላት ዓለም ከሰው የተለየ ወይም ሰው ከሌላው ዓለም ራሱን ነጥሎ የማይመለከት፣ ይልቁን ከተፈጥሮ ጋር የተዋሃደ እና የተፈጥሮን ሂደት በንቁ እየተከታተለ ለመልካም ውጤቷ የሚተጋ ነው እንደማለት ነው። በክላውድ ሲላንድ አማካኝነት የተጠናቀረ ከአስር በላይ ጥናቶችን የያዘ መጽሐፍ ውስጥ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ዛፎች ያላቸውን ቦታ በመጽሐፉ ዋና ርእስ “እንዲያውም ተፈጥሮ ራሷ ባህል ናት” (Nature is Culture) ሲል ይደመድማል። በዚህም ልዩ ልዩ የተፈጥሮ አካላት፣ ወንዞች፣ ጫካዎች፣ ዛፎች ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳና ክስተታዊነት ባሻገር ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ስሜታዊ፣ ታሪካዊ ፋይዳ አላቸው። በኢትዮጵያ እና በሌሎች ዓለማት የሚገኙ ህዝቦች ይህ እምነታቸው ከተፈጥሮ ጋር የተለየ ትስስር እንዲኖራቸው አድርጓል። ሁለተኛው ቁሶች ለተግባራት መከወኛ መሣሪያዊ ዋጋ (instrumental value) ብቻ ያላቸው፣ ሲያልቁ የሚጣሉ ሳይሆን የተመረጡ ቁሶች መንፈስ ያረፈባቸው ስውር እሴት (extrinsic values) ያላቸው ዘመን ተሻጋሪዎች መሆናቸውን ያሳያል። በዚህ የቁሶች ስውር እሴት አማካኝነት ለምግበ-ሥጋ የሚሆን ምርት ሳይሆን ለምግበ- ነፍስ የሚሆን ህሊናን የሚያረጋጋ፣ ልቡናን የሚያጽናና፣ ብኩን ቀልብያን እፎይ የሚያስብል በረከተ-መንፈስ ይገለጣል ተብሎ ይታሰባል። ለዚህም ነው ሰዎች ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ፊቷን ስታዞርባቸው “ኧረ ጥራኝ ጫካው፣ ኧረ ጥራኝ ደኑ” ብለው ይሸፍታሉ። ዓለምን ጥለው ይመንናሉ። ወይም በጋራ ክዋኔዎች ደንቀራ ነው ብለው ያሰቡትን መንፈስ ለማባረር በጊዜ ቀጠሮ፣ በተወሰነ ቦታ፣ በተመረጠ ቁስ ታግዘው መናፍስቱን ይማጠናሉ። የእንደዚህ ዓይነቶቹ አስተሳሰቦች መሠረታዊ ዓምዳቸው ሰዎች ከፈጣሪ ወይም ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኙ መሆናቸውን ማሳያ ነው። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ፣ ቦታና ቁስ አማካኝነት የቅርብ አምላካቸውን ወይም የአያት ቅድመ-አያት መናፍስቱን የሚጠሩበት፣ የሚያነጋግሩበት፣ አደጋን የሚያርቁበት፣ በረከትን የሚቀበሉበት መንገድ እንዳላቸው ማሳያ ነው። እንደዚህ ዓይነቶችን በሳይንስ ወይም በዘመናዊ አስተሳሰብ በንጹሕ ኅሊና ለመረዳት መሞከር ከባድ ነው። አማራጩ ወይ ትርጉም አልባ ከንቱ ክዋኔዎች ናቸው ብሎ መደምደም ነው ወይም በጥርጣሬ ማየት ይሆናል። ከማኅበረሰቦች የሕይወት ቅምምስ (experiences)፣ የሕይወት ትርጉም እና የእምነት ሥርዓቶች አማካኝነት ከተመለከትነው ግን ተፈጥሮ ለሰዎች ሹክ የምትልበት፣ መንገዷን የምትገልጥባቸው፣ ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር የሚነጋገሩባቸው ስውር ቋንቋዎች መኖራቸውን ነው። በዚህም በሰው ልጆች ሁለንተናዊ ታሪክ ውስጥ፤ በዓለም የተቆጠሩ ዘመናት፣ በአካባቢያዊ (ተፈጥሯዊ) ሁኔታዎች፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ውስጥ ህይወት ነፍስ ዘርታ ትንቀሳቀስ ዘንድ ከቁሳዊ አቅርቦት በተጨማሪ የነፍስ ምግብ፣ የኅሊና ቀለብ ይሆኗት ዘንድ የቀረቡ ገጸ በረከቶች ናቸው። እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰቦች ከዘመናዊ ሥልተ-ምርት እና የተግባቦት ሥልጣኔ፣ የጊዜ እሳቤ አንጻር ካየናቸው አባካኝ፣ ጊዜ መፍጃ፣ ወለፈንድ ብለን እንፈርጃቸው ይሆናል። ይህ በራሱ ሕይወትን በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንድትፈስ ከመፈለግ የመነጨ የሉላዊነት ጠቅላይ ፍረጃ ይሆናል። ከውጫዊ የዳር ቋሚ ፍርጃ ይልቅ እንደዚህ ዓይነቶቹን ክዋኔዎች ለመረዳት፣ ለማንበብም ሆነ ለመገምገም የራሱ የሆኑ መንገዶች ይኖራሉ። ይህንን ለመረዳት ከሳይንሳዊ፣ አመክንዮአዊ ንጹህ ኅሊና ወይም ምጣኔ ሃብታዊ ስነ ፋይዳ ብያኔ ይልቅ ስነ ልቡናዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ትርጓሜዎች የተሻለ ቦታ ይኖራቸዋል። በሚቀጥለው መንፈስን ለማንበብ የምንጠቀምባቸውን ዘዴዎች እንመለከታለን። የወር ሰው ይበለን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top