ማዕደ ስንኝ

ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር ኢትዮጵያን ባሰበ ጊዜ

ትንንሽ የንግድ መዳረሻዎችን በወደብ አካባቢዎች ከመመስረት፣ “ሚሽነሪዎችን” ከመላክ እንዲሁም የግለሰብ አሳሾችን መረጃዎች ከመሰብሰብ የጀመሩት አውሮፓውያን፤ እ.ኤ.አ ከ1881 እስከ 1970 ድረስ ከኢትዮጵያና ላይቤርያ ውጪ፤ ሁሉንም አፍሪካዊ ሀገራት ቅኝ መግዛት እንደቻሉ ታሪክ ምስክርነት የሚቆምለት ሐቅ ነው፡፡ የዚህ ቅኝ ግዛት ዋነኛ ክፋቱ ከይፋዊ ነጻነት በኋላም እንኳን ተጽእኖው እስካለንበት ዘመን ድረስ ታጥቦ ሊጠራ አለመቻሉ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ የተነሳ ትልልቅ አፍሪካዊ አሳቢያን ከዚህ ተጽዕኖ ለመውጣት ያስችላሉ የሚሏቸውን ሀሳቦች ሲያቀርቡ እንዲሁም ለመተግበር ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ ከእነዚህ ባለ ትልልቅ ሀሳብ ጸሐፍያን መካከል ሴኔጋላዊው ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎር ስሙ ከፍ ብሎ ሲጠራ ይሰማል፡፡

ሴዳር ሴንጎር እ.ኤ.አ. 1960 ሴኔጋል ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ ስልጣን ላይ የወጣ እና እስከ 1980 ድረስ የመራ የመጀመሪያው ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሲሆን በገጣሚነቱ እና “ኔግሪቱድ” በተሰኘው እንቅስቃሴ አቀንቃኝነቱ ይታወቃል፡፡ “ኔግሪቱድ” የፈረንሳይ የቅኝ አገዛዝ ስርዓትን እንዲሁም፤ የፈረንሳይን ባህል ቅኝ ከምትገዛቸው ሀገሮች ባህል ጋር አዋህዶ የመግዛት ፖሊሲ በሚቃወሙ የአፍሪካ እና የካሬብያን ሀገራት ጸሐፊዎች የተጀመረ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የአፍሪካውያንን ህይወት እንዲሁም ማንነት ከፈተኑ ታላላቅ ክስተቶች መካከል የባሪያ ንግድ እና ቅኝ ግዛት በክፋታቸው አቻ የማይገኝላቸው መሆናቸውን ይህ እንቅስቃሴ አጥብቆ የሚያምን በመሆኑ አፍሪካውያን ጸሐፍያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የባህላቸውን እና የእሴቶቻቸውን ጠንካራነት፣ ጥልቅነት እና መልካም ጎን ማንጸባረቅ እንዳለባቸው ያምናል፡፡

እንደ ሴዳር ሴንጎር እምነትም “ኔግሪቱድ” የጥቁር ህዝቦች ባህላዊ እሴቶች ድምር ሲሆን ይህም በህይወታቸው፣ በሚገለገሉባቸው ተቋማት እና በማንኛውም የጥቁር ግለሰቦች ስራዎች ላይ የሚገለጽ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ለእርሱ ይህ እሳቤ ጥቁር የመሆን እውነታ ነው፡፡ የአፍሪካውያን ነጻ የመሆን ዕጣ-ፈንታም በአፍሪካዊነት ባህልና ታሪክ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ምዕራባውያንም የጥቁር ህዝቦችን ባህል ሲቀበሉ “እኩልነትን ተቀብለናል” ለማለት ያህል ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች እሴቶች ዋጋ ያላቸው የሰው ልጆች የጥበብና የክህሎት ውጤቶች መሆናቸውን አምነው መሆን ይገባል በማለት ያስረዳል፡፡ አፍሪካዊነት ከሰማይ ዝምብሎ የወደቀ ምንነት ሳይሆን ሰው የመሆን ጸጋ የሚታይበት ጥልቅ ማንነት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ “ኔግሪቱድ” በአጭሩ ጸረ ዘረኝነት እንደሆነም ጽፏል፡፡ ግጥሞቹን ጨምሮ የእርሱ የተለያዩ ስራዎችም ይህን እሳቤ የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡

ሴዳር ሴንጎር እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም ከዚህች ዓለም በ95 ዓመቱ በሞት ከመለዬቱ በፊት ለስሙ መጠሪያ የሚበቁ ታላላቅ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የተለያዩ የክብር ሽልማቶችንም ለማግኘት በቅቷል፡፡ መምህር፣ የኪነ-ጥበብ ዳይሬክተር፣ ገጣሚ፣ ፖለቲከኛ፣ ወታደር እንዲሁም የሀገር መሪ የነበረው ሴንጎር የፈረንሳይ ወታደር በመሆን ጀርመንን ለመታገል ተገድዶም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በጀርመን ወታደሮች ተይዞ ለሁለት ዓመታት ለእስር ተዳርጓል፡፡ በእስር በነበረበት ጊዜም በወቅቱ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራት በነጻነት ምሳሌነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከኢጣልያ ጋር ግጭት ውስጥ መግባቷን በመስማቱ ውስጡ ተነክቶ የነበረ መሆኑም ይገለጻል፡፡ ምክንያቱም ገና ከመነሻው የቅኝ ግዛትን አስከፊነት እና ባርነት የሚያስከትለውን የህሊና ጠባሳ ቀላል እንዳልሆነ ሴንጎር ያውቅ ነበርና ነው፡፡

ጣልያን ወልወል የተባለው የኢትዮጵያን ክፍል እ.ኤ.አ. ከ1930ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ለመያዝ መሞከሯ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ ከትቷቸው የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ሰበብ በተለይ በምስራቅና መካካለኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በመግባት ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ሙከራ አድርጋ የነበረ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያውያን አርበኞች ትግል እንዲሁም በዓለም ላይ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ አጋዥነት ሰፊውን የኢትዮያ ክፍል መቆጣጠርና ማስገበር ተስኗት እ.ኤ.አ. 1941 ከኢትዮጵያ ምድር ጦሯን ጠራርጋ ልትወጣ መገደዷ ይታወሳል፡፡

ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንጎርም ይህን የኢትዮጵያ እና የጣልያን ግጭት በሰማ ጊዜ ስጋት እንደገባውና ውስጡ እንደተነካ ተሰምቷል፡፡ ልቡ የተነካ ጸሐፊ ስሜቱን በጽሁፍ ማስፈሩ የተለመደ ነውና “A l’appel de la race de Saba” የተሰኘ ግጥም ጉዳዩን አስመልክቶ እ.ኤ.አ. በ1936 ፅፏል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ መደፈር ቁጭት የተፈጠረ ግጥም በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን በወቅቱ የተሰማውን ስሜት እርሱ ከሚገኝበት ሁኔታ ጋር አጣምሮ ጽፎታል፡፡ ይህን ባለ ስምንት ክፍል ግጥም ይዘቱን እና አውዱን ሳይለቅ ለእናንተ ለአንባብያን በሚከተለው መልኩ ተርጉሜ “ሳባውያን” በሚል ርዕስ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡

ሳባውያን

እ ናቴ ፈጣሪ ይባርክሽ
ይከልልሽ ከመአቱ እ’ሱ ይቁም ከጎንሽ
የቁጣሽ ድምጽ ተሰማኝ ከርቀት ካለሁበት
ቢጫ ቅጠሎች ረገፉ ሚላን ተናጠች በስጋት
የሚሆነውን አታውቅምና መጭው እየታሰባት
እኔ ግን አልቻልኩም ከፍርሀቴ ከስጋቴ ለመሸሸግ
ያንቺ ነጸነት ነጻነቴ፤ ነውና የጥቁር ማዕረግ
መሪው አጓራ በበቀል ጥም፤ ሰብሎችም በጉሪው ነደው
ታዬሽ መሰል አመጣጡ ያንችም ድምጽ ተሰማ ቁጣው
ዓይንሽም በንዴት ቀላ ያ የድሮው ትዝ እያለሽ
ተራሮችሽ ነድደው የበቀለ የጥቁር ዘር ሲታወስሽ
አየሁ እልህ ባፍሽ ሲዞር ፊትሽ መስሎ ቁጡ ነብር
የሆነውን ተረት ማለት አለማወቅ ነው ያንቺን ክብር

እናቴ ፈጣሪ ይሁንሽ
እ’ሱ ይቁም ከጎንሽ
ድንገት አንቺን እያሰብኩ ትዝ አለኝ የዴለር ምሽት
ያለጭንቅ ያሳለፍኳቸው የልጅነት ውብ ጊዜያት
ያባቶቼ ቀን ታወሰኝ ያ የጥንቱ ያወቅኩበት ሰው መሆንን
የሕይወት ጀምበርን ጉዞ ያሳየኝ ያስተማረኝ ነጻነትን
ልጆችሽን ሳሰላስል በዚህ ቀዝቃዛ ምሽት በዚህ ቀዝቃዛ ሰማይ
ፍርሃት ነገሰ በልቤ ሰጋት ፈሰሰ ጅስሜ ላይ
የሰለለ መሰለኝ ነጻነታቸው፤ መሰለኝ ዝሎ ሚበጠስ
ሰንሰለታቸው ታስሮ ሲታዬኝ ከልቤ ደምና መንፈስ
ደግሞ አረፍ ብዬ ሳሰላስል የተቆጣው ደሜን አብርጄ
የኮንባ ሙዚቃ ከሩቅ ይመጣል ወላጅ አልባ የሚለው ድሮ ምሰማው ከደጄ
ምንድነው ደግሞ ነገሩ ያ የድሮው ሊታዬኝ ነው
በአትክልቱ ስፍራ ላይ ይታዬኛል የሾላ ዛፍ የቆመ ለምልክት
ጨረቃዋ ደግሞ ወጥታለች ጥላ ይታዬኛል ከርቀት
ምንድን ነው ደግሞ ነገሩ ትዝ ይለኛል ያ የድሮው
በአትክልቱ ስፋራ ላይ በበቀለ የሾላ ዛፍ ለምልክት በቆመው
ጨረቃዋ ጥላዋን ጥላ ትታየኛለች በርቀት
ደጋጎቹ የሰፈር ሴቶች ሲጫወቱ ተደብቀው በምሽት
በለሆሳስ ይሰማኛል የድምጻቸው ጥልቀቱ
ልክ እንደዓይናቸው ምስጢር አለው የወጋቸው ምንነቱ
አዬሁት አባቴን ደግሞ ራቅ ብሎ ተኝቶ
መንጣፉም ውብ ነው የእጅ ጥበብ የተሰራ በቁመቱ ተለክቶ
የኮራስ ድምጽ ይሰማኛል ውቡ የመንደሬ ዜማ
እየሰሙ ሲጨፍሩ መሪው በመሪ ሞገስ ጀግኖች በጀግና ግርማ
ጠንካራ እና ቆንጆ ህይወት! አልኩኝ ለራሴ በለሆሳስ
ከነጻነቴ አናጠበኝ የሰማሁት የመንጋ ድምጽ የተሞላ በትርምስ
ከሄድኩበት መለሰኝ ይህ የባዕድ አገር ግሳንግስ

እናቴ ፈጣሪ ይርዳሽ
ይከልልሽ ከመአቱ እ’ሱ ይቁም ከጎንሽ
አልሰማሽኝም ስሰማሽ መጥቀሻል በሐሳብ ክንፍ
እንደ ስጉ እናት ልቧ እንደ ከዳት ለመጫን የስልኩን ቁልፍ
ልንገርሽ እናቴ ስሚኝ
አስተውለሽ ተመልከቺኝ
በታሰርኩበት እዚ ቦታ የሚሰማኝ ቋንቋ ሌላ ነው
የግሪክ ነው ወይ ደግሞ ላቲን፤ ሽንፈቴ መገዛቴ የሚታውሰው በዚህ ነው
ያንቺ ቋንቋ ግን ነጻ ነው ልዩ ነው መሰረቱ
ነጻነት ነው ትርጉሙ አርነት ነው ምልክቱ
ጠባቂ አለ እዚህ ፊቴ ስልጡን የሰለጠነ
በጊዜ ብዘት የማይነትብ ተግባሩ ማጥፋት የሆነ
ያንችን ተስፋ የሚያስጥል፤ ባዶ ተስፋ እያዘገነ

እናቴ ፈጣሪ ይርዳሽ
ይከልልሽ ከመአቱ እ’ሱ ይቁም ከጎንሽ
አትሁኝ ተላላ እናቴ እውነቱ ወዲህ ወዲህ ነው
ፊትለፊት የሚታዬው ነገር ለይምሰል የተሰራ ነው
የሮማው ካውንስል መሪ ተወክሎ መምጣቱ
ከሁለት ትውልድ ቀድሞ፤ ተሰርቶ ነው ሹመቱ
ክሬንጅ ትመስክር የጀርመኗ ታውቃለች እርሷ ደባውን
በቀል መሆኑን ተግባሩ ሊወጣ ያሳለፈውን
ይልቅ ለባንዳው አንቢ ለተወሽ በጭንቅ ቀንሽ
ጠላት ጋር ላበረው ልጅሽ ጭንቅ ሲመጣ ለሚሸሽ
ላልሰማቸው ሲጮሁ ቢጫ ውሾች ከከበሩ ላይ
የገዳይ መንፈስ ሲገባ ተረማምዶ ነጻንትሽ ላይ
ጣዕም አጣ ነጻነትሽ ከነከነኝ ጎመዘዘኝ
ጸረኑ ተለውጦ ጀምሯል እኔን ሊያፍነኝ
አይኖቼን ጨፈንኳቸው ተሰማኝ ትራምፔቱ
ሲነፋ የነጻነት ድምጽ የኩራታችን የጥንቱ
ተገለጸለኝ አሁን መሪም የለ ተመሪ
ባሪያም የለ አሰሪ
ብቻውን ጦርና ጋሻ የቆመ ከወታደር ጋር
ፍልምያ ነው ለነጻነትሽ ህዝብ አለ ከራስ ደስታ ጋር
እሱን ሰማሁት ከሩቁ ከተራሮቹ ይሰማል ድምጹ
የአፍሪካ ነጻነት ታሪክ ሊጻፍ ነው ተከፍቷል ገጹ
ሲጣራ በመድፎች መሃል
አፍሪካን እናድን እያለ በጀግንነት ሲያነሳ ሲጥል
ደሞ የጣር ድምጽ ሰማሁ ከለቅሶ ሁሉ ሚጎላ
ወጣቱ ልጅሽ መሰለኝ ከሩቅ ደቡብ ሚጣራ

እናቴ ፈጣሪ ይርዳሽ
እ’ሱ ይቁም ከጎንሽ
በእስር ላይ እኛ የሆንነውን እሰኪ ስሚኝ ላጫውትሽ
ከፍተው ሲገቡ ወደኛ የተዘጋውን በር
ቀኑን አስታውሳለሁ ብርሀናማ ነበር
ደማቅ ባንዲራ ተይዟል ጽሁፍ የሰፈረበት
የነጻና ነጻ አውጪ ስሜት የታጨቀበት
እኔና ወንድሞቼ የማላውቃቸው ከዛሬ በቀር
ተሰባሰበን ልንፋለም ከሚመጣው መዓት ጋር
በቆራጥነት ተዘጋጅተን በአንድነት ቆመን ነበር
ህልማችን ግን አልሰመረም የካርቴጅ ፀሐይ ተጋረደች
ምሽቱ ይብስ ጨለመ ጨረቃዋም ጠለቀች
ተከተሏቸው ቪላቸውን ቦርጫሞቹ ሹማምንትም
ዓይታቸው ነጭ ነው አንዳንዶቹ ሮዝ ቀለም
ይለያል ሁኔታቸው ከተፈጥሮ ሁሉ አይገጥሙም
ደማቋ ፀሐይ ተከለለች በእነእርሱ ስራ ተዋጠች
ሞት ጥላውን አጠላ ምድር ሌላ መልክ ያዘች
በአንበሶቹም ፈንታ ተኩላዎቹ ተተኩ
አይናችንን ከልለው ነጻነታችንን ማረኩ

እናቴ ፈጣሪ ይርዳሽ
እ’ሱ ይቁም ከጎንሽ
ኦ ፒንዳር ሆይ! የቅኔህን ማዕበል አምጣ
እንዲህ እያየህ ዝም አትበል ይህን የፈጣሪ ቁጣ
ቫለሚ ፈጣኗ መርከብ ጫነችን ወደማረሴ በረርን ገሰገስን
ምንም ሳንዘገይ እስረኞች ከታንኮች ፈጥነን ደረስን
ጩኸት ነገሰ በውስጣችን አካባቢው ግን ጸጥ ብሏል
አይ ማረሴ ካቶሊኳi ስምን መላክ ያወጣዋል
መቼም ፊደል ሞኝ ነው ከአዋሉት ጋር ይስማማል።
አሳየችኝ አቀላቅላ ሶማሌውን፣ ኦባዬውን፣ ያ የቶጎን አንበሳ
ፋን፣ ፎን፣ ሙር፣ ማዲንጎ፣ ቦንቦው ልቡ በስጋት የከሳ
ማምባራውም አለ እወዲያ ጥግ ይታዬኛል
በእስር መሆን አሳፍሮት እየሰረቀ ያየኛል
አናጺው መርከበኛው ያ የሰው ጥበበኛ
ተሰባስቧል አንድላይ በሊቨርፑል ተጠልፎ፤
በጀርመኑ ተንኮለኛ
አይ ማርሴ ካቶሊኳ ስምን መላክ ያወጣዋል
በሴንት ዴኒዝ በሮች በኩል የወንድማማቹ ደም ባእዳንን ይገነባል

እና ወዳንቺ ልመለስ አንቺ ውዲቷ እናቴ
እንደዚህ እንዳይሆን ነው ያንቺው እጣ ስጋቴና ጭንቀቴ
ልጅሽን አጥኚው እናቴ እይታው ልዩ ነው መልኩ
በግርማው ትለይዋለሽ ከአያቶቹ አንድ ነው ልኩ
ጓደኞቹንም እወቂያቸው ማሸነፍ ነው ተግባራቸው
በአሮጌ ደም በተሰራው ሹራብሽ ውስጥ እቅፍሽ ስር ሸሽጊያቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top