ታዛ ስፖርት

የሱዳኑ ተጓዥ

በቅዱስ ጊዮርጊስ ፋብሪካ ውስጥ የመጣውን ሰው ሰላምታ ለመስጠት ሰራተኛው ብቅ እያለ ‹‹ጌቾ እንዴት ነው …ሰላም ነህ›› እያሉ ያዋሩታል። ሰዓቱ ስለደረሰ ቆሞ ሊያናግራቸው አልቻለም። ነገር ግን በርቀት ለሰላምታ እጁን እያውለበለበ ወደ ቢሮው ገሰገሰ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በረኛ የነበረው ጌታቸው አበበ(ዱላ) የሚሰራው እዚህ ፋብሪካ ውስጥ ነው። የስራ መደቡም የሽያጭ ሰራተኛ ነው።

አለቆቹ ጋር ገብቶ ደሞዝ በብድር ወስዶ ቶሎ ብሎ ወደ ሆቴል መመለስ ፈልጓል። ከዚያም ወደ ትሬኒንግ ይሄዳል። ከሱዳን ጋር ላለባቸው የማጣሪያ ግጥሚያ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ካርቱም ይሄዳሉ። አሁንም የመጣው አሰልጣኙን አስፈቅዶ ነው። ብድሩ ተፈቅዶለት ወደ ሂሳብ ክፍል እያመራ ሳለ አንዱን ጥብቅ ጓደኛውን አገኘው። ከበደ ይባላል። እንደተገናኙ የናፍቆት ተቃቅፈው ተሳሳሙ።
‹‹ጌቾ እንዴት ነህ? ›› አለው።
‹‹ደህና ነኝ…. ከቤ!!!››
‹‹ዛሬ ከየት ተገኘህ?››
‹‹ብር ልወስድ መጥቼ ነው››
‹‹ደሞዝ አትጠብቅም እንዴ?››
‹‹እንዴት?››
‹‹ሁለት ቀን ነው የቀረው››
‹‹ባክህ!! አሁን ስለፈለግሁ ነው››
‹‹ምን ያረግልሀል?››
‹‹እቃ ለመግዛት ነው››
‹‹ከየት? ››
‹‹ከሱዳን››
‹‹ልትሄዱ ነው?››
‹‹አዎ…..እንዲያውም ሰው ተፈቀደልን››
‹‹አልገባኝም››
‹‹አንድ ተጫዋች አንድ ጓደኛውን ይዞ መሄድ እንዲችል ዛሬ ተነገረን››
‹‹ጌቾ!!! በናትህ››
‹‹ምን ?››
‹‹እኔን ይዘህ ሂድ››
‹‹ለምን?››
‹‹በአውሮፕላን ሄጄ አላውቅም››
‹‹ሌላስ?››
‹‹ሱዳንን ማየት እፈልጋለሁ››
‹‹ለአንድ ጓደኛዬ ቃል ገብቻለሁ››
‹‹ማንስ ቢሆን ከኔ ይብልጥብሃል?››
‹‹እንዴት?››
‹‹ከኔ ጋር ብዙ አሳልፈናል….. ላንተ ስል ተደብድቤ…. ሰራ ቦታ እየሸፈንኩልህ…. ታመህ ስጠይቅህ..››
‹‹ኡፍ !!! ባልነግርህ ይሻለኝ ነበር››

ከበደ እጁን እያርገበገበ ጌታቸው ጉልበት ላይ ወድቆ ለመነው። ተማጸነው። ‹‹በናትህ፤ በምትወደው አባትህ፤ በጊዮርጊስ ይዤሀለሁ›› እያለ አስቸገረው ‹‹እሺ ላንተ ስል ለድሮ ጓደኝነታችን ብዬ መርጨሀለሁ›› አለው። ከቤም በደስታ የጌታቸውን አንገት እቅፍ አድርጎ ሳመው። እንደዚያን ቀን ደስ ብሎት አያውቅም። ያልታሰበ ዕድል ነው የገጠመው ‹‹ጌቾ ይሄ ነገር ለእኔ ነው የመጣው። ከፋብሪካው ውጭ ለስራ ልወጣ ስል መኪና ዘግይቶብኝ 30 ደቂቃ እዚህ ቆየሁ። ካንተ ጋር እንድንገናኝ ፈጣሪ ሲያመቻችልኝ ነው። ባይሆን ኖሮ ሄጄ ነበር›› አለው። ጌታቸውም ‹‹ዕድለኛ ነህ›› አለው።
‹‹በጣም እንጂ››
‹‹ሎተሪ ቆርጠህ ታውቃለህ?››
‹‹ለዕድለኝነቴ ነው?››
‹‹አዎ››
‹‹ሎተሪ አይሆነኝም››
‹‹ይሄ ሆነህ አይደል?››
‹‹የሱዳኑ ጉዞ?››
‹‹አዎ››
‹‹እሱ እንኳን ከሎተሪ በላይ ነው››
‹‹ግን አንድ ነገር ያስፈልጋል››
‹‹ምን?››
‹‹ገንዘብ አለህ?››
‹‹ከየትም አመጣለሁ ..እበደራለሁ ባጣ እንኳን››
‹‹ሌላም ነገር አለ››
‹‹ንገረኝ››
‹‹ፎርም ትሞላለህ››
‹‹ምን ብዬ››
‹‹እኔ እነግርሀለሁ››

ከበደ በተነገረው መሰረት የእናቱን፤ አክስቱን፤ አጎቱን… የሩቅና የቅርብ ዘመዶቹን ሳይቀር ጌታቸው ባዘጋጀለት ወረቀት ላይ ሞላና ሰጠው። ከበደ ወደ ቤት እንደተመለሰ ለቤተሰቦቹ ለጎረቤቶቹ ሳይቀር ሱዳን እንደሚሄድ ነገራቸው። ማታ ከጓደኞቹ ጋር የደስ ደስ ቡና ቤት ገብተው ጠጡ ‹‹የሱዳን ዘፈን አድርግ›› በማለት አስከፍተው ሸከሸኩት። ጓደኞቹ ‹‹ጌታቸው ያንተ የልብ ጓደኛ ነው እንዲህ አይነት እድል ማንም አይሰጥህም›› አሉት። ‹‹ብርጭቋችንን ለጌቾ እናንሳ ›› ብለው አወደሱ፤ አሞገሱት ‹‹ረጅም እድሜ ለጌቾ›› አሉ። ጌታቸው ለከበደ ደወለለት ‹‹ልነግርህ ብዬነው›› አለው።
‹‹ምኑ?››
‹‹የነገውን…››
‹‹ተሰረዘ እንዴ?››
‹‹አልተሰረዘም››
‹‹እና››
‹‹እቃ እንዳታበዛ››
‹‹እሺ››
‹‹የሚበላም ያዝ››
‹‹ምን?››
‹‹ደረቅ ነገር ….ቋንጣ ጭኮ…››
‹‹እይዛለሁ››
‹‹ጠዋት ፌዴሬሽን በር ላይ እንገኛኝ››
‹‹ስንት ሰዓት?››
‹‹ሶስት ሰዐት። በረራው……..››
‹‹በረራው ስንት ሰዓት ነው››
‹‹አራት ሰዓት… ደግሞ እንዳታረፍድ››
‹‹አልተኛም… ይሄ እድል ተገኝቶ!!››
‹‹እሺ››
‹‹ጌቾ!!››
‹‹አቤት››
‹‹በአውሮፕላን ሄጄ አላውቅም››
‹‹ነገ ልትሄድ እኮ ነው››
‹‹ማለቴ ግር እንዳይለኝ ካንተ ጋር ብቀመጥ››
‹‹ግድ የለም እኔ አመቻቻለሁ….. ቁርስ ደግሞ እንዳትበላ››
‹‹ችግር አለው እንዴ?››
‹‹የመጀመሪያህ ስለሆነ ያስመልስሃል››
‹‹ምንም አልበላም››

ከቤ እንቅልፍ አልወሰደውም። ትንሽ ሸለብ ሲያደርገው በህልሙ አውሮፕላኑ እያመለጠው ሲባንን ቁጭ ብሎ አደረ። መሄዱን የሰሙት ከሱዳን ዕቃ እንዲያመጣ ገንዘብ ሰጥተውታል። የእያንዳንዱን መልዕክት በወረቀት ላይ አስፍሮ በጥንቃቄ ያዘ። ከጓደኛው ካሜራ ተውሶ በካርቱም ከተማ በተለያየ ቦታ ፎቶ ተነስቶ ሊመጣ ፊልም ገዝቶ አስገብቷል።በሸኚዎቹ ታጅቦ ጠዋት ከተቀጠረበት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ደረሰ። ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ቁርስ እንዲበላ ቢለምኑት የጌታቸውን መመሪያ ለማክበር ሲል ብቻ የሚወደውን ቁርስ ለመዝለል ተገዷል።

ከቤ እና ሸኚዎቹ ስለሱዳን እያወሩ ፌዴሬሽን በር ላይ ሆነው መጠበቅ ጀመሩ ።የቀጠሮው ሰዓት ደረሰ። ጌታቸው አልመጣም። እንዳውም ሰዓቱ አለፈ። አሁንም ጌቾ የለም። ሰዓቱ እየገፋ ሄደ ከበደ ‹‹ምን ሆኖ ነው?›› እያለ ሰዓቱን ደጋግሞ ማየት ጀመረ። ኃይሉ (ባርያው) ፌዴሬሽን ነበር የሚሰራው። ከበደን ያውቀዋል። በር ላይ ሻንጣ ይዞ መቆሙ ያልተለመደ በመሆኑ ‹‹ከቤ እንዴት ነህ?›› አለው።
‹‹ሰላም ነው››
‹‹ዛሬ ከየት ተገኘህ?››
‹‹ካርቱም ልሄድ ነው››
‹‹ለትምህርት ነው?››
‹‹አይደለም ከቡድኑ ጋር››
‹‹ከየትኛው ቡድን?››
‹‹ከብሄራዊ!!››
‹‹በምን ምክንያት?››
‹‹አልሰማህም እንዴ?››
‹‹እዚህ ነው የምሰራው የማላውቀው ትዕዛዝ አለ እንዴ?››
‹‹ተጫዋቾቹ አንዳንድ ሰው ተፈቅዶላቸው….››
‹‹እና አንተ ልትሄድ?››
‹‹አዎ። ምነው?››
‹‹ማነው እንዲህ ያለህ?››
‹‹ከጌታቸው ጋር ነው የምሄደው››
‹‹ጌታቸው የቱ?››
‹‹ዱላ›› ሀይሉ ተገርሞ እያየው ከጓደኞቹ ነጠል አድርጎ ‹‹ና እስኪ›› ብሎ ወደጥግ ወሰደውና ‹‹ብሄራዊ ቡድኑ ሌሊት 12 ሰዓት ወደ ካርቱም ሄዷል›› አለው።
‹‹ምን አልክ?››
‹‹በርሯል››
‹‹አውሮፕላኑ?››
‹‹አዎ››
‹‹እኔን ጥሎ?››
‹‹ሄደ››
‹‹አይደረግም››
‹‹ተደረገ››


ከቤ በድንጋጤ በሩ ላይ እራሱን ይዞ ቁጭ አለ። ኃይሉ በከበደ መታለል ተገርሞ ‹‹አንተ!! ጌታቸውን እንዴት ታምነዋለህ? እርሱ በስንት ሰው ነፍስ እንደተጫወተ ታውቃለህ። እኛ የርሱን ተንኮል እያወቅን እንኳን ስንት ጊዜ ነው የሸወደን። አንተ ከልጅነቱ ጀምሮ እያወቅኸው እንዴት ይሸውድሀል›› አለው። ጌታቸው ከሱዳን ተመለሰ። ከቤን አገኘው። ምንም አልተባባሉም። ጌታቸው ‹‹በህይወትህ ሁሌም የምታስታውሰው ገጠመኝ ይሆንሀል›› አለው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top