ቀዳሚ ቃል

በመጯጯህ የተገነባ ሀገር የለም፤ የሚፈርስ እንጂ

እስቲ እንደማመጥ!

ሁላችንም አንድ ላይ ከተናገርን ማን ሊያዳምጥ ነው? የተናገርነውንስ ማን ጆሮ ላይ ልንዘራው ነው? ሊያደማምጥ ሊያወያየን የሚገባ አንገብጋቢ ሀገራዊ የጋራ ጉዳይ አለን እኮ! ሞትን የሚያክል ከባድ ሸክም፤ ጦርነትን የሚያክል አስፈሪና አውዳሚ አደጋ እደጃችን ተገትሮ፤ እንኳን የሌላ ጆሮ የራሳችን እንኳ በቅጡ ሊያዳምጠው በማይችል ሁኔታ መጯጯህ ምን ሊፈይድልን ነው? ምንም አይፈይድም! የሰው ክጅ ክቡር ነው፤ በመፈክር! እውን ግን በተግባራችን የሰው ልጅ ክቡርነትን እያሳየን ነውን? እሺ ሌላው ይቅር በኢትዮጵያስ የሰው ልጅ ክቡር ነው? እየሆነ ያለው ሲታይ፤ ይህ ሐቅ አይመስልም። መክበር መሞት፤ ማክበር መግደል ከሆነ አዎ!! ማክበር ማለት ግን መግደል ማለት አይደለም።

በሃገራችን ወቅታዊ ተግዳሮቶች መጠን፣ ዓይነት እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የቱንም ያህል ልዩነት ይኑረን፤ ሰከን ብለን ተደማምጠን ከተወያየን ግን ወይ እንግባባለን ወይ በልዩነት በሰላም እንለያያለን። ቢያንስ መጠፋፋትን እናስቀራለን። ሞት ቁጥር በሆነበት ሃገር ውስጥ ቁጭ ብሎ ማውራት፤ የፌስቡኩን ገፅ ማጣበብ፤ ኢትዮጵያዊነትም፣ አማራነትም፣ ትግሬነትም፣ ኦሮሞነትም… አይደለም።

በሰው ሞት የሚደሰት፣ ምንም ከመሆኑ በፊት ሰብአዊ ፍጡር አይደለምና የማንንም ማንነት ሊጎናፀፍ አይችልም፣ አይግባባምም። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ከእንስሳት የሚለየው በምክንያት የሚመራ የማሰቢያ አእምሮ በመጎናጸፉ ነው። በእንግሊዝኛ (Rational mind) ይሉታል። ይህ ታላቅ ሀብት መጎናፀፉ ብቻ ደግሞ በራሱ በቂ አይደለም። ሊጠቀምበት፣ ሊመራመርበት ይገባል። ለዚህም ማስተዋልን፣ በጥሞና ማዳመጥን፣ የተለየ ሐሳብ ለማዳመጥ መዘጋጀትን፣ በተረጋጋ መንገድ ሐሳብን መግለፅንና ምክንያታዊ መሆንን ይጠይቃል።

የሰው ልጅ በምክንያት ሲያስብ አይደለም አሁን ያለንበትን ችግር፤ ብዙ ታላላቅ እና ቀና ተግባራትን ሊፈጽም ተሰጥኦ እና ክህሎት ተችሮታል። ከረጅም ጊዜያት በፊት አንስቶ እስካለንበት ዘመን ድረስም ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ብዙ አስደናቂ እና ዓለምን የቀየሩ ታላላቅ ልህቀት ያሳዩባቸውን ተግባራት ፈጽመዋል። ለዚህም የምክንያታዊ ሰዎች አስደማሚ እመርታ፤ እኛ ያሁኖቹ ብቻ ሳንሆን፤ ከእኛ ቀጥለው የሚመጡ ትውልዶችም በእርግጠኝነት ምስክሮች ይሆናሉ። በተቃራኒው ደግሞ የሰው ልጅ ያለምክንያት በስሜት ሲመራ፤ ከአውሬም የባሰ ከሰይጣንም የሚልቅ ክፋትን ሊፈጽም ይቻለዋል። ይህንን ለመረዳት ደግሞ የቅርቦቹን እንኳ ብንተው፤ ባሳለፍነው መቶ ዓመት የተፈጸሙ እኩይና ግብረሰይጣን የሆኑ ድርጊቶችን ወደኋላ ዞር ብሎ ማየቱ በቂያችን ነው። ይህ ደግሞ የሰው ልጅን አደገኛ ያደርገዋል። ታዲያ ሰዎች ሆነን ሳለ የአውሬ ጭካኔን እንዳንፈጽም፤ ራሳችንን ከየትኛውም ስሜታዊ እርምጃ እና ውሳኔ ገታ አድርገን፤ በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ አንዳችን ሌላችንን በማዳመጥና በመወያየት ያሉብንን ችግሮች በሙሉ ልንፈታቸው ይገባናል።

በመጯጯህ የተገነባ ሀገር የለም፤ የሚፈርስ እንጂ… ስለዚህም “መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች” የሚለውን የአበው ብሂል ተግባራዊ አድርገን፤ ሰከን ብለን እናውራ… ተረጋግተን ተደማምጠን ወደፊት እንጓዝ የምንወያየው የጋራችን የሆኑ ብዙ ጉዳዮች ስላሉን ነው። የምንወያየው አብሮነታችን የሚሰጠን ጥንካሬ ስለሚልቅብን ነው። የምንደማመጠው ስለራሳችን የወደፊት ተስፋ ብለን ነው። የነገው ጊዜ ብርሃን ነው፤ ቀና ነው፤ መልካም ነው፤ ሰናይ ዘመን ነው… አንዳችን ለሌላችን ካሰብን። ነጋችንን ከዛሬ የተሻለ እናድርግ፤ እንችላለንም። መልካም ንባብ!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top