ስርሆተ ገፅ

ስምንት ጥያቄዎች ለተሸላሚው ባለብሩሽ

መሣል ተሰጥኦው እንደሆነ የተገነዘበው ልጅነቱ ላይ ነበር። “ሳሉ” ሲባል ያለ ካርቦን የሳላቸው ስዕሎቹ በመምህራኑ ሲደነቁ ነበር። ሌላው ቀርቶ በ3 ክፍል የሚበልጠውን የታላቅ ወንድሙን ስዕሎች እየሳለለት ለወንድሙ አድናቆት ሲቸር መምህራኑ ሠዐሊውን ባያውቁም አድናቆታቸው ለወንድሙ ሲገልፁ ወንድሙ ደግሞ ተደንቀሀል ይለው ነበር።

እያሱ ተላይነህ

ሰዓሊ ኢያሱ ተላይነህ

2009 ዓ.ም ከአለ የስነ ጥበብ ት/ቤት የተመረቀው ይህ ወጣት እንደተመረቀ ወደ ስዕል ስራ አላመራም። ህይወቱን ለመምራት ወደሚያስችሉት የንግድ ስራ ላይ ጥቂት ቆየ። በ2020 ወጣት በአፍሪካ ተስፋ የተጣለባቸው ሠዐሊያንን የሚሸልመው አፍሪካ ኢመርጂንግ ፔይንቲንግ ኢንቪቴሽናል የተሰኘ ተቋም እጩ ተወዳዳሪ ሆነ። ጥቅምት 9 ከ17 አፍሪካውያን ሠዐሊያን ጋር ተወዳድሮ አሸናፊ ተባለ። ሽልማቱ ሶስት ሺህ ዶላርና በሀራሬ ዚምባብዌ የብቻ ኤግዚቢሽን ማቅረብና የ3ወር የመኖሪያ ፈቃድን ያጠቃልላል። ኢትዮጵያዊያን ሲያሸንፉ ደስ የሚያሰኝ ነገር አለው። ብሩሽ ደግሞ ሲሽልሟት ማራኪ ሀሳቦችን በቀለሟ እየፈወሰች ሚሊዮኖችን ከአይምሮ ድርቀት ነጻ ታወጣለች።

በቁመቱ ልክ ይዘታቸው ከፍ ያሉ ሀሳቦችን የሚያወጋውን ይህ ወጣት ቦሌ በአንድ ካፌ አግኝቼ አወራሁት። የቅርጫት ኳስ ሌጀንድ ይመስላል እንጂ ሠው ስለ ሠዐሊያን ውጫዊ ገፅታ የሚበይነውን ነገር አላገኘሁበትም። ወሬያችን ላይ ሳደፍጥ ግን እጅ ከፍንጅ ያዝኩት ። የምር ሠዐሊ ነው። እንደውም አይተው ቶሎ የማይረዱት ሲገባዎት ግን “ተዓምር” የሚያስብሉ ስዕሎች አሉት። መልካም ቆይታ!!

* ቀንህ የሚባረከው እንዴት ነዉ?

ዋክ ! ከእንጦጦ እስከ 4 ኪሎ ወደ አንድ ሠዐት ተኩል በእግሬ እጓዛለሁ፣ አራት ኪሎ ቁርሴን ስበላ ደማቅ ቀንና ስራ እንደኖረኝ እቆጥረዋለሁ።

* የራስህ ስቱዲዮ አለህ? የት ይገኛል?

አዎ እንጦጦ ይገኛል።

* ብሩሽህ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ሸራ ላይ ይደምቃል?

ሙዚቃ ካልሰማሁ አልሠራም። ሙዚቃ ውስጤ ነው።

* ምን አይነት ሙዚቃ ያነቃቃሀል?

አፍሮቢት እና ሬጌ በተለይም የቦብ ማርሌና ፓንአፍሪካኒስቱ እና 27 ሚስቶቹን በአንድ ቀን የፈታውን ናይጄርያዊው ፌላኩቲን

* ከሀገር ዉስጥ

ሳሙኤል ይርጋን፣ ዳዊት ጌታቸውና ሙላቱ አስታጥቄን

* ለስዕል የምትሰጠው የጊዜ ገደብ አለ?

ሣምንት ከስቱዲዮ ላልወጣ እችላለሁ።

* የሚመስጥህ ሀሳብ ማለትም ወደ ስዕል የሚያቀርብህ

ጉንዳን መስመር ሠርቶ ሲሄድ ሊሆን ይችላል፤ ወፍ ጎጆዋ ላይ ስትሆን፣ እራት መመገብያ ሣህን ላይ የሚንጠባጠቡ ነገሮች ሣይ ሊሆን ይችላል። ጮክ ብሎ ”አብስትራክት” አለ።

* የምታደንቃቸው ሠዓሊያን

ከሀገር ውስጥ ታደሰ መስፍንን ከውጪ አፍሪካ አሜሪካዊው ዣን ሚሼል ባስኪውታ፣ የሚደንቅህ በቅርቡ መቶ አስር ሚልዮን ዶላር ስዕሉ የተሸጠለት ይህ ባለብሩሽ ጎዳና ላይ እያደረ ሲስል ታይቶ ወስደው ነው ሠዐሊ ያደረጉት።

* ስዕሎቼ ምን አይነት ናቸው ትላለህ?

ስዕሎቼ ኣለም ላይ ያለ ሰው ማለትም ፈረንሣዊውም፣ ግብፃዊውም፣ ማላዊውም የሚገባው አይነት ቢሆን መርጣለሁ። ዩኒቨርሳል ነገር ኣለዉ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top