ጥበብ በታሪክ ገፅ

ጥላ የሆነን ጥላሁን

ያልተሰሙ እና ያልተነገሩ ነገሮች

ለሙዚቃ እና በሙዚቃ ከትንሿ ከተማ ወሊሶ ተነስቶ በሱዳናዊው ርዕሰ መምህር ገርበብ በተደረገለት በር አለምን አናውጧል። አለማየሁ ገብረህይወትና ናትናኤል ከበደ ከጥልቅ የንጉሱ ህይወት ከሙያ ባልደረቦቹና በአጋጣሚ ህይወትን አብረው ከተጋሩ ሠዎች ጋር ተወያይተዋል፣ ቅንጣት ትዝታውን ጨልፈው ያስነብቧችኋል።

(ጥላ ሆኖን ያለፈው ጥላሁን)

በ2001 ዓ.ም. ሚያዝያ ላይ በአንድ ሀገር የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ባልተለመደ መልኩ “ጠላት” በሚሉት ሀገር የሚኖር አንድን ሰው ያንቆለጳጵሳሉ። ኧረ እንደውም የጠሉት ሀገርን ሙዚቃ አቀነቀኑ። መልካም ስራውንም አወሱ። ሀገሩ ኤርትራ ሲሆን አርቲስቶቹ ኤርትራውያን ነበሩ። ውዳሴው ለክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ የነበረ ሲሆን፤ አርቲስቶቹም ያንጎራጎሩት በአማርኛ የራሱን ሙዚቃ ነበር። በማግስቱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት በቴቪ መስኮት ብቅ ብለው ሁኔታውን እንዲህ ሲሉ ገለጹት። “ቴሌቪዥን እያየሁ ነበር። ብዙ የኤርትራ አርቲስቶች በጥላሁን ዙሪያ አስተያየት ሲሰጡ ሰማሁ። ፍቅራቸውን የገለፁት አንዳንዶቹ ታጋይ ነበሩ። አማርኛቸውን ሰምቼ ግርምት ፈጠረብኝ። እንደዛ ጥላሁንን መግለፃቸው የሚገርም ነው። አድናቆት ሠጪዎቹ የጥበብ ሰዎች እንጂ ተራ ሰዎች አልነበሩም” ሰውየው ሩቅ ነው። ጠላቶቹ እንኳን ከወገባቸው እጅ ሰበር ብለው እጅ ነስተውታል:: ስለእሱ ማውጋት ከውቅያኖስ ላይ እንደ መጨለፍ ነው። ሙዚቃን በየትኛውም ገፅታ ኖሯታል ማለት ድፍረት አይሆንም። ብዙዎች ያልዘፈነበት ርዕሰ-ጉዳይ የለም ይላሉ። የሀገሪቱ መልከዓ-ምድር ላይ ያልቧጠጠው ቆንጥር የለም ማለት ይቻላል። እንኳን ኢትዮጲያን ህይወትን ሆኖላታል። በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጲያዊያን ቢጠየቁ በልባቸው የቆመ ኢትዮጲያዊ ሃውልት ጥላሁን ገሠሠ ነው። ዋልታ የረገጡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት “የእኛ ባትሆንም “መቸስ ማልጎደኒ” ብለውለታል። በውጭ ሀገር እንኳ ከፍቷቸው “የገዢው መንግስት ወገን ነህ” ብለው ፈርጀውት “መጣ” ሲባል ሊቃወሙትና ሊጮኹበት ተደራጅተው ትኬት ቆርጠው ሲገቡ ንጉሱ ዘፍኖ እያስለቀሰ የአመፅ ሰንሰለቶቻቸውን በጣጥሷል። የሚያስበው፣ የሚተነፍሰው፣ የሚተውነው ሙዚቃ ነው። ኧረ እራሱም ሙዚቃ ነው። ታሰሮ ሊሆን ይችላል፣ ተበድሎ ሊሆን ይችላል፣ የፍርድ ቤት ደጃፍ ደጋግሞ ረግጦ ሊሆንም ይችላል፣ ተክዶም ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህ የህይወት እንገጭ እንጓ የሚቆጣጠረው ማይኩን እስኪጨብጥ ድረስ ብቻ ነው። ከዛማ በቃ የሆነው እንዳልሆነው ይሆናል። ሀገሪቷ ደፋር ወራሪ ሲመጣባት ወኔ በሚቀሰቅስ ዘፈኑ ወጣቶችን ጦር ግንባር አሰልፏል።

አንታ ትምህርት አይደለም፤ አንታ ዘፈን ነው”

ዘካርያ መሐመድ “ጥላሁን ገሠሠ የህይወት ታሪክና ምስጢር” ባለው መፅሀፉ ከላይ ያለውን ሐረግ በዚያን ዘመን በራስ ጎበና ት/ቤት ሲማር ሱዳናዊ የነበረው ዳይሬክተር የተናገረው መሆኑን ነግሮናል። ተማሪ ፈርቶ በሚኖርበትና ከቀለም ትምህርቶች ይልቅ ስነ-ጥበባዊ የተሰጥኦ የትምህርት ዓይነቶች እንደ ጎዶሎ ነገር በሚቆጠርበት በዚያ ዘመን መደበቂያው መዝሙር ነበር። እርሱም በኋለኛው ዘመኑ እንደተናገረው የመዝሙር ውጤቱ የሂሳቡንም፣ የእንግሊዝኛውንም የጂኦግራፊውንም ውጤት ያጠቃለለ ነው ይለዋል። ቡሄም ደርሶ መዝሙር ሲዘምር ከሌሎች ይልቅ ድምፁ ጎልቶ ይሠማ ነበር። ያቺ ልምምድ ነበረች፤ የኤርትራው ሙዚቃ አእምሮ (Brain) ተብሎ የሚወደሰው በረከት መንግስተ አብ’ንኳ “ጥላሁን ካርቱም ሲዘፍን አዲስ አበባ ድረስ ይሠማል” ብሎ እንዲያወድሰው ያስቻለችው’ እነ እዮኤል ዮሀንስና ንጋቷ ከልካይን የያዘው የሀገር ፍቅር የሙዚቃ ቡድን ወደ ወሊሶ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ሲመጣ ነበር የጥላሁን ልብ ወደ አዲስ አበባ የሸፈተው። ወደ አዲስ አበባም ከመጣ በኋላ ከሀገር ፍቅር እስከ ብሔራዊ ትያትር በነበረው ዘመን እየፈካና የሙዚቃው ጥልቀት እየጨመረ መምጣቱን የሙዚቃ ሀያሲና ምሁር ሠርፀ ፍሬ- ስብሀት ሲገልፀው እንዲህ በማለት ነበር፡- “የድምፃዊውን ድምፅ እርከን ጊዜ ‹ኢዮኤላዊ›፣ ‹ማርዮ ላንዛዊ› እና ‹ጥላሁን አደጋ ከደረሰበት በኋላ› በማለት በሶስት በመክፈል የአዚያዚያም ሂደቱን (መሻሻል) ማለትም የመጨረሻውን አልበም ባለ ወፍራምና ቀጭን ሬንጅ የያዙ ረዣዥም የዜማ ሐረጋትን መያዙን ተከትሎ ‹ተዓምራዊ›” ብሎታል። ብዙሃን የሙዚቃ ልሂቃን በየትውልድ ዘርፉ ላይ አበርክቶውን እፁብ-ድንቅ እንዲሁም በአግባቡ ያልተመረመረ ይሉታል። አወዛጋቢ በሆነው የህይወት ስንክሳሩ ላይ ኢትዮጲያዊነት በደማቁ ተተይቧል።

ባለ ዛጎሏ እንስት

ደጅአዝማች ሰብስቤ ወሊሶን ሲያስተዳድሩ ያኔ ጎበና ዳጨው አራተኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ጥላሁን ገሠሠ ከደጃዝማቹ ባለቤት እህት (የክፍል ጓደኛው) ጋር ቤታቸው ይመላለስ ነበር። ቤተኝነቱ እስከ አዲስ አበባ ቀጥሎ ደጅአዝማቹ ለወለዷት ልጅ እንደ አባት ሆኖ አሳድጓታል። “ጥልዬ እንደ አባት ጭኑ ላይ አስቀምጦ ያጫውተኝ ነበር” በማለት ጊዜውን ያስታወሰችው እንስት ዘፋኝ መሆኗንም ካደገች በኋላ ሳያስበው ነግራው ነበር ያስደነገጠችው። የደጅአዝማች ሰብስቤ ልጅ ተወዳጇ ድምጻዊ ኩኩ ሰብስቤ እንደነገረችኝ።

5 ጥያቄዎች ለክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ባለቤት

ወ/ሮ ሮማን ጥላሁን ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋም (IMF) ሠራተኛ ነበረች። ከክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ጋር በጀመረችው የፍቅር ግንኙነት (ትዳር) ምክንያት ስራዋን ለቅቃ ወደ ኢትዮጵያ መጣች። ከአርቲስቱ ጋር እስከመጨረሻው እስትንፋስ አብራው የነበረቸው እሷው ስትሆን በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ እንደመሆኗ በስልክ ላቀረብናቸው 5 ጥያቄዎች የሚከተሉትን መልሶች ሰጥታናለች።

ታዛ፡- ከክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ጋር የመጀመሪያ ትውውቃችሁ እንዴት ነበር?

የዛሬ 29 ዓመት አካባቢ እህቴ እዚህ ዲሲ “እጮኛዬን ላስተዋወቅሽ” ስትለኝ ቤቴ ድግስ አዘጋጀሁ። የእህቴ እጮኛ ሙዚቀኛ ነው። የተባለው ቀን ደረሰና በሩ ተንኳኳ፣ ከመጡት ሰዎች መካከል የወደፊቱ ባለቤቴ ነበረበት። ቀስ በቀስ ትውውቁ ተጀመረ። ይኸው ነው።

ታዛ፡- ጋሽ ጥላሁን አካሉን ካጣ በኋላ ያነበባቸው መጻህፍት እውነት ለመናገር አካሉን ከማጣቱ በፊት እንኳን ለመፅሐፍ ለቤተሰብም ጊዜ አልነበረውም። ከእግሩ መቆረጥ ጋር ተያይዞ ግን ጊዜ አገኘና ማንበብ ጀመረ። እንደውም “ሕመም የሰጠኝ ጓደኛ መፅሀፍ ሆነ” ይል ነበር። በተለይ ብዙ የታሪክ መጻህፍትን አንብቧል። ከልቦለድ ኦሮማይ አስታውሳለሁ። ግን አብዛኛውን ጊዜ የታሪክ መጽሐፍ ይመርጣል።

ታዛ፡- ጋሽ ጥላሁን ቤት ያንጎራጉራል? ካንጎራጎረ የነማንን ነዉ?

አዎ በተለይ ደስ ያለው ቀን ለጉድ ነው እንጉርጉሮው፣ የንጋቷ ከልካይ እና ኢዮኤል ዮሀንስን ይመርጣል። ታዛ፡- አስገራሚ ገጠመኝ ጥሌ ደቡብ አፍሪካ እያለ ከዚምባብዌ ስልክ ተደወለ። ደዋዩ የቀድሞ ፕሬዚደንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ሲሆኑ፤ ጥልዬን “አይዞህ ከአሁን በኋላ መቼም እግርህን ማራቶን አትሮጥበትም፣ ለሀገርህ በበቂ ሁኔታ አገልግሎትህን አበርክተሃል” ብለውታል።

ታዛ፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት አለ?

አዎ ጥላሁን የሚገባውን ያህል ክብር አግኝቷል ብዬ አላስብም። እርግጥ ሲያልፍ ህዝብ እጅግ በጣም አስደሳች ሽኝት አድርጎለታል። ያላለቀሰ አልነበረም፣ ያልተቆጨ አልነበረም። ግን ከዛ በኋላ የተገባው ቃል በሙሉ አልተፈጸመም። የተጀመረው አልተጨረሰም፡ እሱን የመሠለ አርቲስት እንዴት ሀውልት ይከለከላል? አሁንም የምለው ቃል የተገባለት ይፈፀም ነው። በተረፈ ባለቤቴም እድሜ ልኩን የተንገበገበላት ሀገር በኢትዮጲያችን ሠላም ፣ ፍቅር እና ደስታ ይስፈን። አመሠግናለሁ ።

ጥላሁን እንደሰው

ታማኝ በየነ

ጥላሁን የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሆኖ ነው ዝነኛ የሆነው። ስለዚህ ከዘጠኝ ዓመቱ ጀምሮ በሰው ዓይን ውስጥ ነበረ። ዝናንም ከዛ ዕድሜው ጀምሮ ነው የያዘው። እና ይህን ያህል ነገር የተሸከመ ሰውን፤ አብረኸው ስትሆን በዛው መንፈስ ነው ትልቅ ሰው አድርገህ የምትቀርበው። ነገር ግን ስትቀርበው የተለየ ሰው ነው። ያ ዝና፣ ያ እውቀት፣ ያ ችሎታ… መድረክ ላይ ሲወጣ ብቻ ነው የሚታየው። ከዛ ውጭ ከሁሉም ጋር ፍጹም ተራ ሰው ነው። የጥላሁን ትልቁ ብቃት፤ በመድረክ እና ከመድረክ ውጭ ሁለት የተለያየ ሰው መሆኑ ነው። አብረኸው ስትጫወት ስትቀልድ ቆይተህ፤ መድረክ ላይ ሲወጣ ደግሞ አንተ ታንስና እሱ ይገዝፍብሃል። የማታውቀው ይሆንብሃል። “ቅድም አብሬው ቡና ስጠጣ የነበርኩት፤ ቅድም የነበረው ጥላሁን ነው ይሄ?” ትላለህ። ይቆጣጠርሃል። በዛው ልክ ደግሞ የመድረክ ስራ ጨርሶ ሲወርድ፤ ከአንተ እኩል ሰው ይሆናል። የምትጠጣውን ኮካኮላ ከእጅህ ላይ ነጥቆ ይጠጣል። ክብር፣ ትልቅ ነኝ፣ ዝና አለኝ… የሚል ነገር የለውም። ብዙዎቻችን ቶሎ ዝናን ነው የምንፈልገው፤ በዛ ዝና ውስጥ ሆነን ነው ሌላውን ልናየው የምንሞክረው። እሱ ደግሞ ከመድረክ ላይ ሲወርድ ዝናውን ያወልቀዋል። እስከዛሬ ድረስ የሚገርመኝ የጥላሁን ባህሪ፤ የፈለግከውን ነገር ልትል ትችላለህ፤ በምንም መንገድ የትኛውንም ባለሞያ ፊቱ ላይ በፍጹም አያሳማም። በጣም ገናና ስም ያለው፣ ሁሉም ሰው የሚወድደው፣ ለሁሉም ሲቀርብ አብዛኛው ሰው የሚወድደው ዘፋኝ ነው። ክብሩን፣ ዝናውን ይጠብቃል ብለህ ታስባለህ። እሱ ግን እንዲህ አይደለም። ለምሳሌ አብረን ስንሰራ፤ እኔ ቡና እያልኩ እዘፍን ነበር፤ እናም ከጀርባ ሆኖ የሚቀበለኝ እሱ ነው፤ በድምጹ። በጣም ይገርመኛል። እንግዲህ አኔ መብራት ከሌለበት ከተማ የወጣሁ ሰው ነኝ። እሱንም የማውቀው በሬዲዮ ነው። ግን እግዚሃር ሰጥቶኝ ደግሞ አብሬው ስሆን፤ ከጀርባ ሆኖ እየዘፈንኩ እሱ ሲቀበለኝ፤ ይህ ሰው ምን ዓይነት ነው ብዬ ለማሰብ ይቸግረኛል። ሌላው በእሱ ዕድሜ ያሉ ድምጻውያን አሉ። መሐሙድ አሕመድ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ታምራት ሞላ፣ መልካሙ ተበጀ… የዛ ዘመን የምትላቸው አሉ እነ ሂሩትንም ጨምሮ አሉ። እንግዲህ የሰው ልጅ ባህሪ ይታውቃል። ሁሉም ጋር ቢደበቅም የሞያ ውድድር አለ። ሁልጊዜ በውስጥህ ባትናገረውም “እኔ ነው የምበልጥ” የሚል ስሜት አለው ሁሉም ሰው። ነገር ግን የሚገርመኝ፤ በምንም ዓይነት ይሁን ባለሞያዎችን ፊቱ አያሳማም። እኛ እኮ ተሰብስበን እናማለን፤ በሆነ ባልሆነ ስም እናነሳለን። እሱ ጋር ግን በፍጹም አንድ ጊዜም ሰምቼ አላውቅም። በምንም ዓይነት ይሁን ፊቱ ባለሞያዎችን አያማም። ከእሱ ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ከብዙ ሰዎች ጋር ሰርቼያለሁ። ይህን ባህሪ ሌሎች ጋር አላየሁም። ሌላው ሁሉም ሰው የሚያውቀው ይመስለኛል። በጣም ሆደ-ቡቡ ነው። ምክንያቱን ግን አስከዕለተ- ሞቱ ድረስ ለማወቅ ጥሪያለሁ፤ አላገኘሁትም ምክንያቱን። በጣም አልቃሻ ነው። አንተ ዓይን ላይ እንባ ካየ፤ የእሱ ሁለት እጥፍ ሆኖ ይወርዳል። ይህ እንግዲህ ከሞያው ውጪ የማውቀው ባህሪ ማለት ነው። አንድ ጊዜ ለህዝብ ለህዝብ ስንወጣ፤ “ጉብል” የሚለው አልበሙ ለገበያ ከወጣ በኋላ ነው። በወጣ በሳምንቱ ነው መሰለኝ እኛም የወጣነው። ከወጣን ሶስት ወር ከሆነን በኋላ በአጋጣሚ ሞንትሪያል የሚባል ከተማ ካናዳ ውስጥ ሆነን፤ ነዋይ ደበበ ወደሀገር ቤት ይደውላል። ደውሎ ሲያወራ ስለካሴት ስራ አንስቶ ሲጠይቅ፤ ኬኔዲ መንገሻ አዲስ አልበም ማውጣቱን ይሰማል። እኛ ከወጣንና የጥላሁን አልበም ከወጣ ከሶስት ወር በኋላ የኬኔዲ አልበም ይወጣል። የኬኔዲ አልበም በጣም ይገንናል፤ በጣም ይወደዳል። እናም ነዋይ ደበበ ስልኩን ጨርሶ ሲመጣ፤ ወደ ጥላሁን ቀርቦ “ጋሼ ጋሼ፤ እህ… ኬኔዲ የሚባል ዘፋኝ መጥቶ ካሴትህን አጠፋው አሉ። በጣም ጥሩ ሆኖለታል የእሱ፤ እየተሰማ ነው። ያንተን እየሸፈነው ነው” አለው። “ታዲያ ዘመኑ ሆኖ ይሆናላ፤ የእሱ ዘመን ሊሆን ይችላል። እኔ እኮ ብዙ ዘፈንኩ፤ ይሄ እኮ ያለ ነገር ነው” አለው። እንደቀላል ነገር ነው ያየው። ለነገሩ ነዋይም ሳያስበው ነው ያለው። ነገር ግን ጥላሁንን ምንም አልተሰማውም። ይሄ ዘመኑ የፈጠረው እና ዘመኑ የተቀበለው ሰው ነው፤ እኔም መቀበል አለብኝ ብሎ ነው የሚያስበው። እንዲህ መጣብኝ… እንዲህ ልሆን ነው… የሚል ስሜት የለውም።

የጥላሁን ዲሲፕሊን

ሌላው በሞያው ባህሪ በጣም የሚገርመኝ ዲሲፒሊኑ ነው። ይህ ሚሊተሪ ቤት ከማደጉ፤ ወይም በዘመኑ ያደገበት ስርዓት ይሆናል። ለምሳሌ እዚህ ባንድ ስንሰራ፤ ማታ ሶስት ሰዓት ሊሆን ይችላል ትርኢት የሚጀመረው። እሱ በ12 ሰዓት ለባብሶ ተዘጋጅቶ ጨርሷል። እኛ ገና አልጋ ውስጥ ነን። ዝግጁ ሆኖ እሱ ነው መጥቶ የሚያንኳኳው። አንድ ጊዜ “ብራቮ” የሚባል የእርዳታ ስራ ልንሰራ እዚህ አሜሪካን አገር… እንግዲህ አሜሪካን ሃገር ሁልጊዜ ሾው የሚጀምረው ወደ እኩለ-ለሊት ነው። እናም እሱ ለእኩለ-ለሊት ፕሮግራም በ12 ሰዓት (ከስድስት ሰዓታት በፊት) ሄዶ አዳራሹ ውስጥ ብቻውን ቁጭ ብሏል። ይህን ዓይነት ዲሲፕሊን አለው ጥላሁን።

የጥላሁን ዘመንተሻጋሪነት

ጥላሁን ተጽዕኖ ፈጣሪና ዘመን-ተሸጋሪ ነው ይባላል። ይሄ አባባል ብቻ ሊመስል ይችላል። እንግዲህ በዚህ ዓመት “ባለገሩ አይድል” የሚባል ውድድር በቴሌቪዥን እንደአዲስ ተጀምሯል። እሱን ፕሮግራም ሳይ ነበረ። እንግዲህ ጥላሁን ከተለየን 11 ዓመት አልፏል። አሁን የገረመኝ፤ አንዷ የ24 ዓመት ልጅ ነች፤ ማለትም ጥላሁን ሲሞት የ13 ዓመት ልጅ ነበረች። እሷን ጨምሮ ከቀረቡት 10 ዘፋኞች ዘጠኙ የጥላሁንን ዘፈን ነው የሚዘፍኑት። ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ቴዲ አፍሮ የእሱን ዘፍኗል፤ ጎሣዬ የእሱን ዘፍኗል። ዘሪቱ የእሱን ዘፍናለች… ብዙዎቹ ዘፍነዋል። ከእነሱ በፊት ያሉት ትውልድ ደግሞ አይተውታል። የነኤፍሬም፣ የነንዋይ፣ የነጸሐዬ… ትውልድ ደግሞ፤ አብዛኞቹ እሱን አይተን ነው ወደሙዚቃ የገባነው ይላሉ። እነታምራት፣ እነአለማየሁ… ደግሞ እሱ ስለጀመረ ነው ይላሉ። ጋሽ መሐሙድ፤ እሱ እየቆነጠጠ በሞያዬ ያሳደገኝ ነው ይለዋል። ከዛም በኋላ የነተሾመ ምትኩ፣ ጌታቸው ካሣ ትውልድ ደግሞ አለ። ለእነሱም አይድላቸው ጥላሁን ነው። አሁን የ20 ዓመት እና የ30 ዓመት ልጆች ጥላሁንን አይዶላቸው አድርገው ይዘፍናሉ። ለምሳሌ “ባላገሩ አይድል” ያሸነፉት 1ኛ እና 2ኛ የወጡት ልጆችን ብናይ፤ ከ60 በመቶ በላይ የዘፈኑት የእሱን ነው። በባህል ድምጻውያን እነሰማኸኝ በለው፣ እነሻምበል በላይነህ፤ ጥላሁን እንዲዘፍኑ እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ። እናም በትውልድም፣ በአጨዋወት ስልትም ዘመን ተሻግሮ… አሁን ህይወቱ ካለፈ ከ11 ዓመት በኋላም እንኳ መድረኩን ተቆጣጥሮ የሚኖር ሰው ነው።

ዜማ ደራሲው ጥላሁን

ሌላው በሞያው ላይ ብዙም የማይነገረው፤ ጥላሁን ዜማዎችን ይሰራል። ግን ዜማዎችን ለመስራት ግጥሙ ልቡን መንካት አለበት። ውስጡን ከነካው ዜማውን ራሱ ይሰራል። ለምሳሌ አሁን “በአካል ሳይፈተን በአካል ሳይለካ… የማን ምንነቱ ግብሩ ሳይለካ… እርግጥ በተፈጥሮ በወል ስም ይጠራል… በቁምነገር መድረክ ሰው ከሰው ይለያል” የሚለውን የክፍሌ አቦቸር ግጥም ዜማው የራሱ ነው። እንደዚህ የሚኮረኩሩትን ግጥሞች ዜማ ይሰራላቸዋል። ‹የጠላሽ ይጠላ› በጣም ምርጥ ግጥም ነው፤ ዜማው የራሱ ነው። አንዳንዴ በካሴት ዘመን ዝምብሎ የተጫወታቸው፤ ስሙ ብቻ የተሸጠበት አለ። ለምሳሌ “ምግብማ ሞልቷል” የሚለውን በ1985 ዓ.ም. ታህሳስ ወር አዲስ አበባ ስቴዲዮም ላይ እየዘፈነ፤ ያው እንግዲህ የመንግስት ለውጥ ነበር። አሁን የፈነዳው የብሔር ፖለቲካ ጥንስሱ ላይ ነበር። ለሌላ ስራ ብለን አስቀምጠን ያስጠናሁት ግጥም ነበር። ከዛ ውስጥ አንዷን መንቶ ግጥም አውጥቶ “ምግብማ ሞልቷል” ላይ ከተታት። “የምድራችን ስፋት ለእኛ መች አነሰን… የአመል ጠባብነት ነው የሚያናክሰን” የሚለውን ግጥም፤ ምግብማ ሞልቷል ውስት ከትቶ ዘፈነው። እንዲህ ዓይነት ስሜቱን የሚነኩ ነገሮች ሲያይ ደስ ብሎት ነበር የሚዘፍነው። ለምሳሌ በደርግ ጊዜ የኮሚኒስት ስርዓት ስለሆነ፤ ሳንሱር ነበረ። “ሞናሊዛዬ”ን አስጠንተን፤ የመጨረሻ ግምገማ ተብሎ ለሳንሱር ልንቀርብ “የአሁኗ እመቤት የፊቷ ተማሪ… እግዚአብሔርን አማኝ አካልሽን አክባሪ” የሚል ግጥም አለ ውስጡ። “እግዚአብሔርን..” ስለሚል አውጣው አሉት። ከማወጣው ግጥሙ ቢቀየር ይሻላል ሲል፤ “አንቺነትሽን አማኝ” በል አሉት። እሺ አለና “… አንቺነትሽን አማኝ አካልሽን አክባሪ” የሚለው ላይ ሲደርስ ሁለት እጆቹን ገጠመና ወደሰማይ ወደእግዚአብሔር እንደሚጸልይ ሆኖ ከወደእግሩ በርከክ አለና “አንቺነትሽን አማኝ አካልሽን አክባሪ” አለ፤ “ነገር ግን ብትችሉ ‹እግዚአብሔርን አማኝ› በሉት” ብሎ ቀየረው በሚታይበት ቀን።

የጥላሁን የመጨረሻ ጊዜያት

ደቡብ አፍሪካ ልናየው ሄድን። በጊዜው ባለቤቱ ከነበረችው ጋር በየቀኑ እንደዋወል ነበር። እናም ወደሰርጀሪ ከመግባቱ በፊት ደውላ “በቃ እግሩ ይቆረጣል” አለችኝ። ሰማይ ምድሩ ምን እንደሆነብኝ አላውቀውም። በጣም አዘንኩ፤ እያለቀስኩ ቆየሁ። ሰርጀሪው እስኪያልቅ ጠበቅኩ። ለሊት ላይ ደወልኩላት። “አዎ፤ እግሩ ተቆርጧል” አለችኝ። ዓለምጸሐይ ጋር ደወልኩ። ነዋይ ጋር ደወልኩ። በነገራችን ላይ ነዋይን አውቀዋለሁ። ከሃያ ዓመት በላይ ለረጅም ጊዜ ጓደኛዬ ነው። እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ አውጥቶ ሲያለቅስ ያየሁት ያኔ ነው። ነዋይ “ወንድ ልጅ ተደብቆ ነው የሚያለቅስ” የሚል ባህሪ አለው። እናም ብዙ ጊዜ አይቸዋለሁ፤ በፍፁም በአደባባይ ሲያለቅስ አይቼው ስለማላውቅ ደነገጥኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በጥላሁን ምክንያት ሲያለቅስ አየሁት። ወዳረፈበት ሆቴል እየሄድን ወደክፍሉ አካባቢ ስንደርስ በሩ ላይ ዊልቸር አየን። ወደክፍሉ ከእኛ መካከል ማንም ደፍሮ ለመግባት አልዳዳም ነበር። “ጥላሁንን የሚያህል ግዙፍ ሰው ተቆርጦ እንዴት ልናይ ነው” ብለን ሁላችንም ፈራን። እንደምንም “ግቡ ግቡ” ተባልንና ገባን። በቃ ሁላችንም ስናየው ያ ዋርካ የሚያህል ግዙፍ ሰውዬ አንዲት አልጋ ላይ በጣም ትንሽ ሆኖ ተጠቅልሎ ስናይ፤ የምናደርገውን አሳጣን። መሬት ላይ በሐዘን ስንንከባለል ሲያይ ተቆጣን። “እረፉ” አለ፤ ተቆጣን በጣም። “እኔ እኮ የሚገባኝን በሙሉ አድርጌያለሁ። ደግሞም ወታደር ነኝ። ስንቱን ወጣት አይዞህ ወደፊት ሂድ ስል ኖሬ፤ እግራቸው ሲቆረጥ ህይወታቸው ሲያልፍ አይቻለሁ። እናም በእኔ ሲደርስ… ምንድን ነው እንደዚህ መሆን?” ብሎ አረጋጋን? እናም በጣም ጠንካራ ሆኖ ታየን። ግን ምንም ቢሆን ከዛ በኋላ በርትቶ አልቀጠለም። ያ ስሜት አብሮ አልቆየም። እንዲያውም አርቲፊሻል እግር መጥቶለት፤ አልተመቸውም፣ ደስ አላለውም። ውስጡ እንደተጎዳ ታውቃለህ። አያሳይህም፤ ነገር ግን ሳያሳይህ ውስጡ መጎዳቱን ታያለህ።

አድናቆት የማያጓጓው ጥላሁን

አሁን ለምሳሌ ዋሽንግተን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ፤ ያኔ ደግሞ ብዙ ሰው ወደሃገሩ መመለስ ስለማይችል በጣም ትልቅ ዝግጅት ነበር የተደረገው እሱን ለመቀበል። በሊሞዚን ነበር ወደመድረክ የመጣው፣ ይገርምሃል አራት አምስት ፈረንጅ ቦዲጋርዶች እሱን የሚጠብቁ ነበሩ። የነበረው ሰውም በጣም ደስ ይል ነበር። በጣም የሚገርመው፤ ሲያልቅ እሱን በሊሞዚን አጅበው ሊወስዱት ሲፈልጉ፤ እሱ ሹልክ ብሎ ከሌላ ሰው ጋር አፍተራር የሐበሻ ምግብ ቤት አገኘነው። አይወድም በቃ፤ እሱ ከመድረክ ከወረደ በኋላ ጥላሁንን መሆን ነው የሚፈልገው። እንዲህ ነው ባህሪው በቃ። ስታውቀውና ስትቀርበው፤ እንዴት እንደዚህ ያደርጋል ብለህ ትቆጣዋለህ። ብሔራዊ ቴያትር ቤት እያለም ቢሆን በጓሮ ሹልክ ብሎ ወጥቶ፤ እዛ ከጀርባ ያለች ትንሽ ግሮሰሪ፤ በቦታው ካሉ ደላሎች፣ ጫኝ አውራጆች ጋር ተጫውቶ አብሮ በልቶ ጠጥቶ ነው ወደቤቱ የሚሄደው። መድረክ ካለቀ በኋላ ሰዎች ሊያገኙት እና አድናቆታቸውን ለመግለጽ ይፈልጋሉ፤ ፎቶ ለመነሳትም ይሁን ፊርማ ለማስፈረም ይፈልጉታል። እሱ ግን በጓሮ ሹልክ ብሎ ነው የሚወጣው። ጥላሁን ብዙ ጊዜ ከሚናገረው “ዝናን መሸከም የማይችል ዘፋኝ፤ ዘፋኝ አይደለም” ይላል።

ጥላሁን ከሙዚቀኛም በላይ

በህዝብ ለህዝብ ጊዜ የመጀመሪያ ሾው የሰራነው ዋሽንግተን ነው። ያኔ ተቃውሞ ያለ አይመስለንም ነበር። እናም ገና ከአውቶብስ እንደወረድን “ደርግ ፋሽስት ነው” የሚል መፈክር ይዘው የተሰበሰቡ ሰዎች አየንና ደነገጥን። ጥላሁን እና መሐሙድ ናቸው፤ ገና እንደወረዱ የሂሩትን “ኢትዮጵያ” ማለት ሲጀምሩ፤ ሲቃወም የነበረው ሰው ሁሉ “ሀገሬ” እያለ፤ መፈክሩን እየጣለ ወደአዳራሹ መግባት ጀመረ። ጥላሁንን ለማድነቅ የኢትዮጵን ሙዚቃ ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ሲጀምር “አካሌ ውቤ” የሚል ዘፈን አለው። በጭብጨባ የሚታጀብ ነው። ከእንደዚህ ዓይነት ስታይል ጀምሮ ነው፤ የህይወቴ ህይወት… አቋቋምሽማ… የሚሉ ዘመናዊ ሙዚቃዎችን መጫወት ችሏል። የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ለውጦታል። ለምሳሌ እኔ እስከማውቀው ድረስ በኦሮምኛ ለመጀመሪያ ጊዜ “አካም ነጉማ” በሚል ለስላሳ (slow) ሙዚቃ የተጫወተው እሱ ነው።

ዓለምፀሐይ ወዳጆ

ከጥላሁን ጋር ትውውቃቸው የሚጀምረው ገና ከልጅነት ዕድሜዋ ነው። ደራሲ መላኩ አሻግሬ ከመድኃኔዓለም 2ኛ ደረጃ ተማሪነቷ ጀምሮ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ወደ ክፍላተ-ሃገርም እየወሰደ ትያትር ያሠራት ነበር። ይህም አጋጣሚ ወጣቷ ተዋናይት ከአንጋፋዎቹ ባለሙያዎች ጋር የምትተዋወቅበትን ዕድል ፈጠረላት። በመድረክ ሲለማመዱም፣ ለሕዝብ ትርኢታቸውን ሲያቀርቡም ትመለከት ነበር። ብሔራዊ ቴያትር ከገባች በኋላ ደግሞ ከጥላሁን ጋር በአንድ መድረክ ከመሰለፍ አልፋ ወደውጭ ሀገርም አብራው ተጉዛለች። የዘፈን ግጥሞቿንም አንጎራጉሯል። ግንኙነታቸውም ከዕለት ወደዕለት እያደገ መጥቷል። ለዚህም ተጨማሪ ምክንያት አለ። “በዚያ ላይ” ትላለች ዓለምፀሐይ፣ “በዚያ ላይ ጥላሁን የታድዬ (ታደሰ ወርቁ፣ ባለቤቷ) እና የደቤ (ደበበ እሸቱ) የቅርብ ጓደኛም ስለነበር መቀራረባችን ቤተሰባዊ እየሆነ መጣ። ሌጎስ ናይጄሪያ ለጥቁር ሕዝቦች ፌስቲቫል ሄደን በነበረበት ጊዜ የሴቶቹን ማረፊያ ትቼ ታዴ፣ ጥልዬና ደቤ ካሉበት ክፍል አራተኛ ሆኜ ገባሁ። በአንድ ክፍል ውስጥ አራት አራት ሰው ነበር የሚመደበው። በቃ አራታችን ፈጽሞ አንለያይም ነበር። እንግዲህ አብረውን የተጓዙ የደህንነት ሰዎች አሉ። እና ይጠፋሉ ብለው የጠረጠሯቸውን ሰዎች ይከታተላሉ። ለምን እንደሆነ ባላውቅም ከጠፉ እነዚህ አራት ሰዎች ናቸው የሚጠፉት ብሎ አንደኛው እኛን ይከታተለናል። ደቤ ይህን ነገር አውቋል። ታዲያ “ኑ! ፈጠን ፈጠን በሉ!” ይልና የሆነ ሞል ውስጥ ያስገባንና እኛ ፎቅ ላይ ሆነን ያ ሰው ጠፍተንበት ግራና ቀኝ ሲማትር ያሳየናል። በቃ እንስቃለን። ደቤ መቼም ለምሳም ይሁን ለምን የማይወስደን ቦታ አልነበረም። አንድ ቀን እንዲሁ ስንዞር ውለን ደቤ በጊዜ ገብቶ ተኝቷል። በሆነ ወረቀት ላይ ደግሞ “አደራ እንደመጣችሁ ቀስቅሱኝ። በጣም አስደናቂ ዜና አለኝ፣ አለዚያ የምፈነዳ ነው የሚመስለኝ”የሚል መልዕክት ትቷል። ያን ሳይ ብቀሰቅሰው “ያ እኛን የሚከታተለን የደህንነት ሰው እኮ ጠፋ!” አለን፣ በቃ ስንስቅ አመሸን።

ጥላሁን እኔ ሳውቀው

ጥላሁንን ሰው አያውቀውም። ከውጪ ለብሶ፣ ረጋ ብሎ፣ በጸጥታ ሲሄድ ሲያየው ዝም ብሎ ቀብራራ ነገር ሊመስለው ይችላል። ሆኖም ጥላሁንን እንደሰው ቀርበህ ስታየው ሆደ-ቡቡ፣ አልቃሻ ነው። በሰዎች ሐዘን የሚያዝን፣ የሚንገበገብ ነው። በጣም የሚያሳዝን ባህሪይ ነው ያለው። ከሚመስሉት ጋር ሲሆን መሳቅ መጫወት የሚወድ፣ ትንንሽ ነገሮች የሚያስቁት ሰው ነው። መኮፈስ የሚባል ነገር ጨርሶ አያውቅም። መድረክ ላይ ሲወጣ ደግሞ ይገዝፋል፣ ይለወጣል። አንዳንዴ አሁን ይህን ዜማ ሌላ ሰው ቢጫወተው እንዲህ የተሳካ ይሆናል ብለህ የምትጠይቅበት ጊዜ አለ። እሱ ስለሆነ፣ የራሱን ፈጠራ እየጨመረ ስለሚዘፍን ይወደዳል።

አድናቂ ነው!

መቼም ጥላሁን ለአድናቆት ንፉግ አልነበረም። ዝም ብሎ “ጥሩ ድምጽ አለህ” ብሎ አያልፍም። ጎበዝና ተስፋ ያለው ባለሙያ ሲያገኝ ከልቡ ያደንቃል። ሲያትል ውስጥ ይመስለኛል “መሄድ መሄድ አለኝ፣ መሄድ አይታክተኝ” የሚለውን ዜማ ደረጀ ደገፋው ሲጫወት ሰምቶ፣ እንባ በዓይኑ ሞልቶ የእጅ ሰዓቱን ሸልሞታል። ታዲያ ሲመለስ “አንቺ ጎጃሜ ሰዓቴን አስወለቅሺኝ አይደለም?” አለኝ። የማስታውሰው ግጥሙ የእኔ ስለነበር ነው። ያደንቃል! አቦነሽ አድነው ስትዘፍንም ተመስጦ አልቅሶ ያውቃል። በስሜት ነው የሚከታተልህ። ቆንጆ ሥራ ሲሰማ በደንብ ያደንቃል። ይሸልማል። ይሄ በብዙዎች ዘንድ የማይገኝ ትልቅ ስጦታ ነው።

የሶዶሬው ሽርሽር

ከባለቤቱ ከአሥራቴ ጋር የተለያየበት ጊዜ ነበር። አሥራቴ ማለት በክቡር ዘበኛ ውስጥ ብዙዎቹ ወዳጆቿ ናቸው። አበልጆቿም ነበሩ። እንደነ ተፈራ ካሳና ሌሎችም። እና በዚህ ምክንያት ጥላሁን ከእሷ ጋር ሲለያይ ከሙዚቀኛ ባልደረቦቹም ጋር ችግር ውስጥ ገባ። ሰላም አጣ። እና የማልረሳው ደርግ ጽ/ ቤት ሄደን ለሻለቃ ወንድሙ “እባክህ ጥላሁን እንዲህ ሆነ፣ አንድ ነገር ብታደርጉ?” ብለን ነገርነው። ከዚያ ጉዳዩ ለጓድ ፍቅረሥላሴ እንዲደርስ ተደረገ። መቼም ደርግ ያኔ ለጥላሁን ያደረገለት ትልቅ ነገር ነው። መኪና፣ ሾፌርና ገንዘብ ተመድቦለት ወደ ሶዶሬ ሄዶ እንዲዝናናና መንፈሱን እንዲያረጋጋ ተደረገ። እኛ በእውነቱ ይህ ይደረግለታል ብለን ጠብቀን አልነበረም። ከዚያ በኋላ ነው ወደናይጄሪያ የሄድነው።

ጥላሁን የማን ነው

በአንድ ወቅት ጥላሁን የመንፈስ ጭንቀትና መረበሽ ተፈጥሮበት ነበር። ብዙ የተጠራቀመ ችግር ነበረበት። አማኑኤል ሆስፒታል ሁሉ ገብቶ የነበረበት ጊዜ ነበር። ስለዚህ በባህል ሚኒስትሩ በሻለቃ ግርማ ይልማ መሪነት አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥላሁንን ወደ ሲቪል መ/ቤት ለማዛወር ጥረት ይደረግ ነበር። ሆኖም በጦሩ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመን። “ጥላሁን የሠራዊቱ አርማ ነው፣ ጦሩን ለቆ የትም መሄድ የለበትም” የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ አቀረቡ። ደርግም ቢሆን በጦሩ ዘንድ ቅሬታ ያስከትላሉ የሚባሉ ነገሮችን በጥንቃቄ ነበር የሚመለከታቸው። ሻለቃ ግርማና የሚመሩት ኮሚቴ ደግሞ ጥላሁን የጦር ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን የሲቪሉም፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃብት ነው ብሎ ጠንክሮ በመከራከሩ ተሳክቶ ወደኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ሊዛወር ችሏል። በልዩ ትዕይንተ-ጥበባት ዝግጅቶችና በሌሎች መድረኮች ላይ ተጫውቶም ተመልካቾቹን አስደስቷል። የደመወዙ መነሻም በማስተርስ ደረጃ እንዲሆን ነው የተደረገለት። በዚህ አጋጣሚ ሻለቃ ግርማ ይልማን ለተጫወቱት ሚና ሳላመሰግናቸው አላልፍም። በጦሩ ውስጥ በነበረበት ጊዜ በምሽት ክበባት መዝፈን አይቻልም ነበር፣ ዲስፕሊኑ ጥብቅ ነው። እንደው ኋላ ላይ ምናልባት ሹልክ እያሉ መሥራት ችለው ነበር መሰለኝ እንጂ፤ ከስምህና ከሥራህ ጋር በማይመጣጠን አነስተኛ ደመወዝ መኖር በጣም ከባድ ነበር። እርግጥ ማዕከላዊ እዝ ያደገበት፣ ብዙ ነገር የተማረበት ክፍሉ ነው። ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎን፣ ኮሎኔል ኃይሉ ወ/ማርያምን የመሳሰሉ ታላላቅ የሙዚቃ ሰዎች የነበሩበት ክፍል ነው።

የደቡብ አፍሪካው ጉዞ

ከምሽቱ ስድስት ወይም ሰባት ሰዓት ይሆናል። ታማኝ ይደውልልኝና እንባ እያነቀው። “ጥላሁን እኮ እግሩን ተቆረጠ” ይለኛል። “እንሂድ” አልኩት። ከዚያ ፕላን ማድረግ ጀመርን። “ሳትነግሩን እንዳይሉ ሌሎችንም አሳውቃቸው” አልኩት። ከዚያ እየደወለ ነገራቸውና እኔ፣ ታማኝ፣ ነዋይና አብርሃም ብዙነህ ትኬታችን ቆርጠን ሄድን። ለጥላሁን አልነገርነውም፣ ድንገት ነው የሄድንበት። ምን ሆነ መሰለህ፣ ሰለሞን ክፍሌ በአሜሪካ ድምጽ እኛ ስለመሄዳችን ዜና ሠርቶ ስለነበር ያን ሰምተው ኮሎኔል መንግስቱ ስልክ ይደውላሉ። እኛ በአጋጣሚ ከሕንፃው ስር ቡና ልንጠጣ ወጥተናል። ባለቤቱ ሮማን ስልኩን ታነሳና “ማን ልበል?” ስትል “መንግስቱ”፣ “መንግስቱ ማን?” “መንግስቱ ኃ/ማርያም” ያስከትሉናም “ዓለምፀሐይ ነሽ?” ይሏታል። ያው ሬዲዮውን ሰምተዋል። “አይ አይደለሁም፣ ቆይ ላቅርባት” ትልና ስትሮጥ ትመጣለች። ጥላሁን አልጋው ላይ ሆኖ፣ “ማነው? ለምንድነው ስልኩን ከፍተሸ የምትሄጅው?” ይላታል። ወደእኛ እየተጣደፈች ስትመጣ “ምነው?” እንላታለን “ሊቀመንበሩ ናቸው”፣ “የምን ሊቀመንበር?” “ዓለምጸሐይ ነሽ ሲሉኝ ጊዜ ነው የመጣሁ” ትልና ተያይዘን እንሄዳለን። ከዚያ ስልኩን አነሳሁና “ጤና ይስጥልን፣ ጓድ ሊቀመንበር እጅ ነሳን፣ እንደምን ነዎት?” ስላቸው፣ “እጅግ በጣም ነው የኮራሁባችሁ! ይኼ ነው ኢትዮጵያዊነት ማለት!” ብለው አደነቁን። እኛም ምስጋናውን ተቀበልን። ከዚያ በተራ ላናግራችሁ አሉና መጀመሪያ ለጥላሁን ሰጠሁት። “አንተ ለሃገርህ ብዙ የሠራህ ታላቅ ሰው ነህ። ማዘን የለብህም፣ እግርህ ካሁን በኋላ ምን ይሠራልሃል? አትሮጥበት” እያሉ ሞራሉን አነሳሱት። ሲለወጥ እኮ ታየዋለህ። “እሺ ጌታዬ፣ እግዜር ይስጥልኝ፣ አመሰግናለሁ” ይላል። ከዚያ ወዲህ ይመስለኛል “ምን ያደርግልኛል አልሮጥበት” ማለት የጀመረው። ከዚያ ደግሞ የነዋይ ፓስፖርት ሊቃጠል ጥቂት ሳምንታት ቀሩት፣ ስንመለስ ታሳድሰዋለህ ተባብለን ነበር የሄድነው። ስልኩን እንደያዘ አየር ወለድም ስለነበር ቀጥ ብሎ ሰላምታ ሰጠና “አቤት ጌታዬ!” ካለ በኋላ “ይገርምዎታል ስንመለስ በእርስዎ በኩል ለማለፍ እቅድ ነበረን። እንጠይቃቸው እየተባባልን ነበር” ሲል እኔ ከማዶ ሆኜ “ኧረ ፓስፖርትህ” እለዋለሁ። እሳቸው ከወዲያ በኩል “በደስታ፣ መጥታችሁልኝ ነው” ይሉታል መሰለኝ “እርሶማ ከፈቀዱ በዚያው ነው የምናልፈው” ይላል። እኔ ከዚህ “ኧረ ፓስፖርትህ” እላለሁ። ከዚያ ታማኝ ይመጣና “ታማኝ ነኝ፣ እኔ እንግዲህ መንጌ ነው የምልዎ” ይላቸዋል። እሳቸው ደግሞ “ዓይናችን ስር ነው እኮ ያደግከው። ጎንደር እንዲህ እንዲህ እያልክ ስታስተዋውቅ” ይሉታል። “እንዴ ያስታውሱኛል?” ይላል። “በደንብ ነዋ!” ብለው ያኔ ያደረገውን የተናገረውን አስታውሰው ይነግሩታል።

ጉሮሮዬ ድር ሊያደራበት ነዉ እባክህን ላዚም”

ወንድሙ ቶላ

ወንድሙ ቶላ ብሔራዊ ትያትር በቴኖር ሳክስፎን ተጫዋችነት 33 ዓመታትን አገልግሏል። አብረው በብሔራዊ ትያትር ሲጫወቱ ጥላሁን ገሠሠ መድረክ ላይና ከመድረክ ባሻገር ሙዚቃን እንዴት ያሸሞነሙናት እንደነበር፣ ሙዚቃ ለጥላሁንና ጥላሁን ለሙዚቃ ምን እንደሆነ ነግሮኛል። ስሜቱ፣ ከእምባ ጋር ትንቅንቅ እየገጠመ “ነፍሴ ነው” ስላለው ሠው እንዲህ አጫወተኝ።

ልምምድ

“1960 ዓ.ም. ብሔራዊ ትያትር እኔ ኢንስትሩመንታል ቲዎሪ ስማር ነበር፤ እሱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት። ለመጀመሪያ ጊዜ አብሬ የተጫወትኩት በ1966 ዓ.ም. በኢሠፓኮ ምስረታ ላይ ሙዚቃዊ ድራማ ላይ ሲያቀነቅን ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ለረዥም ጊዜ አብሬው ሰርቻለሁ። ሰውዬው ትንግርት ነበር። ሲገባ ሽክ ብሎ ነው። ጢሙን ተስተካክሎና ጫማውን አስጠርጎ ነው:: ከዛ መጮህ ነው። ልምምድ በጣም ይሠራል። አይቀርም፣ አያረፍድም እስከ 3፡00 ሰዐት በቀን ልምምድ ያደርጋል። ‹አልመጣልኝም› እያለ አንድን ዜማ ብቻ 4 እና 5 ጊዜ ደጋግሞ ይለማመዳል። አፍን ዘግቶ ሲያንጎራጉር ይውላል። በቲቪ እንደምታየው ልምምድ ላይም ላቡ ያለማቋረጥ ይፈስሳል። መድረክ ላይ ሲዘፈን ቅልል የሚለው ከዚህ የተነሳ ነው። የቱ ጋር ሙዚቃ እንደተዛነፈ ያውቃል። አንዳንዴ የምናጅበው ሙዚቀኞች ተመስጠን ስራችንን ስንረሳ ማለትም መድረክ ላይ አድናቂ የሚሆነውን ስታይ ወይም በሌላ ነገር ስንዘናጋ ዞር ብሎ ያየናል። እኛም ገብቶን እንስተካከላለን። በጣም ስራው ላይ ያተኩራል። አንድን ድምፅ ለብዙ ደቂቃዎች ይዞ መቆየት ከመድረክ ጀርባ አድፍጦ በደጋገመው ስራው ነው ህዝብ ፊት ሞገስ የሆነው። የበዙ የዜማ ሐረጋትን በጥቂት አየር ለማለት ትንፋሽ ስለሚያስፈልግ፤ ያን ለማምጣት ራሱን ገንዳ ውሃ ዉስጥ ቀብሮ “ኡኡ” የሚሉ ቃላትን ያወጣ ነበር። በነገርህ ላይ ምፅዋ ጉርጉሱም ዋና ላይ ኃይለኛ እንደነበረ አይቼያለሁ። ዛሬ የእሱን ዜማ ደግመን እንስራ የሚሉ ሰዎች እንዴት ልምምድ እንደሚሰራ ቢያዩ ወይም መረጃው ቢደርሳቸው የሰሯቸውን ዘፈኖች እንኳን ሊሰሩት አያስቡትም ነበር። ለዚህ ነበር ለታዋቂና አንጋፋው መርአዊ ስጦት ልምምድ ላይ የሰነፈ ሲመስለው “ጉሮሮዬ ላይ ድር ሊያደራበት ነው እባክህ ላዚም” የሚለው።

ኢትዮጲያዊነት

ሀገሪቷ ከሱ የምትፈልገውንና የሚጠበቅበትን አድርጓል። 1974 ዓ.ም በቀይ ኮከብ ዘመቻ ሁሉንም የሠው ልጅ ሳያዳላ እኩል ሲያከብር የማውቀው ጥላሁንን ብቻ ነው፡ ፡ አብረን የኢትዮጵያን ወታደር ለማበረታታት አስመራ፣ ከረን፣ ምፅዋ፣ አፍአበት ፣ አልጌናና አካለ ጉዛይ ሄደናል። ሆቴል አልጋ ይያዝልህ ሲባል እምቢ ብሎ ከእኛ ከኦርኬስትራው አባላት ጋር ካምፕን መርጦ hአራት ወር የምንበላውን በልቶ (በብዛት ፍርፍርና መኮረኒ) የምንጠጣውን ጠጥቶ ይኖር ነበር፣ ፔይሮል ላይ ከእኛ እኩል በቀን 3ብር እየተከፈለውና ጥይት ማስቀመጫ ሳጥን ዉስጥ የኮቾሮ ካርቶን ቀዶ እያነጠፈ እየተኛ መሣርያ እየተሸከመ እና እያወረደ ቆይቷል። ታዲያ ኢትዮጲያ “ኢትዮጲያ የኛ መመኪያ “ ማለት የሚያምርበት ከእሱ ወዲያ ማን ይኖራል?

አንዳንድ ሞራለቢስ ሙዚቀኞች

በህይወት እያለም ይሁን ካለፈ በኋላ በሙዚቃው የሚተዳደሩ አንዳንድ ወጣቶች ለልደቱና ላረፈበት ቀን መታሰቢያ እንዲያቀነቅኑ ብሔራዊ ትያትር ሲጋበዙ አስታውሳለሁ፤ “ይከፈለን” ማለታቸው ያሳዝናልም ያሳፍራልም። የምሽት ክበቦች ዉስጥ ስራውን እየተጫወቱ እና እንጀራ እየጋገሩበት መንገዳቸውን ግን ሊያወሱ አለመሻታቸው አሁንም ያስገርመኛል።

እኔ፣ ጥላሁንና ብዙነሽ በዓለም ጤና

አበራ ለማ

በ1970 ዓ.ም. የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ለእናት ሀገር ጥሪ የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት ሞያዊ እገዛ ዓለም ጤና ከተማ ሄዶ ነበር። ዓለም ጤና ከተማ በሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ነበረች። ኦርኬስትራው ውስጥ ታዋቂዎቹ እንደ ተዘራ ሀ/ሚካኤል፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ተፈራ ካሣ፣ እሳቱ ተሰማ ያሉ ብርቅዬዎች ነበሩበት። ከጋዜጠኞችም፣ ከተለያየ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መምሪያዎች ተውጣጥተን ልንዘግብ እዚያ ነበርን። ከሬዲዮ እኔ ከቴሌቪዥን ኃይለ-ልዑል ይልማ ተመድበናል። እኛም ሙዚቀኞቱም አንድ ላይ አንድ ሆቴል ውስጥ አርፈናል። ዝግጅቱ የሶማሊያ ወረራ ለመመከትና ብሎም በአሸናፊነት ለመወጣት፣ ጦሩን በስንቅና ትጥቅ ለመርዳት በመላው አገሪቱ የተዘጋጀው የእናት አገር ጥሪ ምላሽ አንድ አካል ነው። የከተማው ህዝብ በገዛው የመግቢያ ትኬት እየበላና እየጠጣ ክብር ዘበኞች እሚያቀርቡትን ዝግጅት ይመለከት ነበር። ከአዲስ አበባ የመጣነው ሁላችንም ለዝግጅቱ ምሉዕነት መትጋት ያዝን። ቦታው ላይ ከደረስን ከሁለት ቀን በኋላ ግን አንድ ነገር ተፈጠረ። አንዲት የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተወዛዋዥ በድንገት ወደእኔ ጠጋ ብላ በፍቅር ዓይን እየተመለከተችኝ “መስታወት እባላለሁ። በጣም ወደድኩህ፣ ካየሁህም ቀን ጀምሮ ባይን ፍቅር ልሞትልህ ነው። እናም ፍቅረኛ እንድትሆነኝ እጠይቅሃለሁ” አለችኝ። “የትና መቼ አውቀሽኝ ለዚህ ጋበዝሽኝ?” ስላት፣ “መልክና ቁመናህ ደስ አለኝ። እባክህ ፍቅረኛሞች እንሁን” አለችኝ። እንደማስብበት ነግሬያት ወደ ሆቴሉ ሄጄ የቴሌቪዥኑን ጋዜጠኛ ወዳጄን ኃይለልዑል ይልማን ስለ ድንገቴው የፍቅር ጉዳይ አማከርኩት። ቆንጆ ከሆነች እሺ እንድላት ነግሮኝ ከሩቅ አሳየሁት። “እሺ በላት” አለኝና ጠርቼ እሺታዬን ገለፅኩላት። ከሁለት ቀን በኋላ ደግሞ ሌላይቱ የኦርኬስትራው ቆንጆ ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረበችለኝ። “መንበረ እባላለሁ። እልም ያለ ያይን ፍቅር ውስጥ ጥለህኛል – እባክህ ፍቅረኛሞች እንሁን…” አለችኝ። ይቺኛዋ ደግሞ ፈጣሪ ሌላ ሥራውን ሁሉ ትቶ እሷኑ ብቻ ሲሰራት፣ ሲያሳምራት፣ ሲኩላትና ሲያቆነጃት ውሎ ያደረ የምትመስል ውብ ልጅ ነች። ቁመናዋ፣ መልኳ፣ ጸጉሯ፣ ጥርሰና ዓይኖቿ ጌታ የተጠበበባቸው ነው የሚመስሉት። እና ወከክ አልኳ ባንድ ጊዜ!!! አሁንም ለኃይለ-ልዑል አማከርኩት። “የትኛዋ ትበልጣለች?” ብሎ ጠየቀኝ። በውጫዊ ውበት መሆኑ ነበር ጥያቄው። ሁለተኛዋ አቻም እንደሌላት ምራቅ የሞላውን አፌን እያጣጣምኩ ነገርኩት። አሁንም በርቀት አሳየሁት። “እቺማ አትታልፍም፣ እሺ በላት” አለኝ። ጠርቼ ነገርኳት። በደስታ እየተፍነከነከች ሮጣ ሄዳ ከጓደኞቿ ጋር ተቀላቀለች። ለካ በዚያን ቀን ምድር ሰማዩ ሲደበላለቅ ውሎ አድሮ ኖሯል። በማግስቱ ከቁርስ በኋላ፣ ታላቁ ሰዋችን ጥላሁን ገሠሠ “አበራ ላንድ ጥብቅ ጉዳይ እኔና ብዙዬ እንፈልግሃለን” አለኝና ወደ ብዙዬ መኝታ ክፍል ይዞኝ ሄደ። ከዚያም ካንዲት ወንበር ላይ አረፍ እንድል ጋበዙኝና ወደ ተፈለግሁበት ጉዳይ ገቡ። ሁለቱም እየተቀባበሉ የኦርኬስትራውን ገጽን መረበሽ ነገሩኝ። “እንዴት?” አል አልኳቸው። ሁለተኛዋ አፍቃሪዬ የመጀመሪያዋን ለማናዳድ “ተማረከልኝ፣ እጄ አስገብቸዋለሁ….” ብላ እንዳስወራች ነገሩኝ። ይህንን መርዶ የሰማችው የመጀመሪያይቱ አፍቃሪዬ ‹መስታወት ዱታ ነኝ› አለች። እኔም’ጋ ስትሮጥ መጥታ “ምነው እንዲህ ጉድ ታደርገኛለህ?” ስትል በእምባ-ቀረሽ ቅሬታዋ ወቀሰችኝ። “ፍቅር ነው። ምንም ማድረግ አልችልም” ስል አባብዬ በትህትና አሰናበትኳት። በዚህ አላበቃችም። እምባና እልክ እየተናነቃት እነ ጥልዬን “ይሄን ሰው አማልዱኝ። መንበረን ትቶ ወደእኔ ይመለስልኝ” ስትል ተማጸነቻቸው። የሴት ልጅ እምባ የሚያሸንፋቸው ሁለቱም (ጥልዬና ብዙዬ) “በል እቺን መንበረን እርግፍ አድረጋትና ወደ መስታወት ተመለስ” ሲሉ በብዙው ወተወቱኝ። አስጨነቁኝም። “ኦርኬስትራው ሰላሙን ስለሚያጣ እባክህ እሺ በለን” አሉኝ። በአእምሮዬ ሁለቱም ወይዛዝርት ይመላለሱብኝ ጀመር። ውዝዋዜያቸው፣ ቁመናቸው፣ መልካቸው፣ ለዛቸው… ሁሉ ነገራቸውን እያፈራርቁ “እኔን ምረጠኝ፣ እኔን እቀፈኝ…” የሚሉ ዓይነት ሆኑብኝና ተቸገርኩ። ሁለቱም ደስ ይላሉ። ሆኖም ምርጫዬ ከነጥልዬ በተቃራኒው ሆነ። እና እቅጩን ልነግራቸው ተገደድኩ። “ሁለታችሁም ፍቅርን ታውቃላችሁ። ምን ያህል ኃያል እንደሆነ አዚማችሁለታል። አድማጮቻቸሁን ማርካችሁበታል። እኔም የእሱ የኃያሉ ፍቅር ምርኮኛ ነኝ። መንበረ በዓይኔ ገብታ እልቤ ዉስጥ ተደላድላ ተቀምጣለች። ፍቅርን እንደራስ ማየት ጥሩ ነው። ይቺን ልጅ ከውስጤ ማውጣት አልችልም፤ እኔም በፍቅሯ ነድጄያለሁ” ብዬ ምርጫዬን ይፋ አደረግኩ። ቅር ተሰኙብኝ። ምርጫ አልነበረኝምና ይቅርታ ጠይቄ ተለየኋቸው። “ከጥሌም ከደጓና ከርሁርኋ ብዙዬም ጋር ለወደፊቱ የሚኖረኝ ግንኙነት ይሻክር ይሆን?” ብዬ የሰጋሁትም ሰጋት፣ ስጋት ሆኖ አልቀረም። ከዚያ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንገናኝ ጥሩ ወዳጆች ሁነን ቀጥለኛል። ወደነ መንበረ ልመለስና፣ ከዚያን ቀን ጀምሮ በየምሽቱ ሁለቱ አፍቃሪዎቼ (በሙያቸው ተወዛዋዦች ናቸው) በፉክክር ትኬት እየገዙ ለዳንስ እየጋበዙኝ ልቤን ያጠፉት ጀመር። ከአዳራሹ እንዳልጠፋ የጋዜጠኝነት ሥራዬ ሊዘነጋ ሆነ። የሚገዛውም ትኬት ለእናት አገር ጥሪ ገቢ ማሰባሰቢያ በመሆኑ፣ ትኬት የያዘ ዳንስ ጋባዥ ሲመጣ እምቢ አይባልምና፤ የሁለቱ “ጣውንቶች” ንዴት መወጫ ሆንኩኝ። ትኬት እየሰጡኝ ነጭ ላብ እሰኪያሰምጠኝ አስደነሡኛ! መቼም የማይቻል የፍቅር ዕዳ የለምና ቻልኩታ ለአንድ ሳምንት። ተልእኳችንን ጨርሰን ወደ አዲስ አበባ ከመጣንም ቀን ጀምሮ እኔና መንበረ የፍቅር ታንኳችንን እየቀዘፍን ሰነበትን። ዝነኛው ዛምቤዚ የምሽት ክበብ ሁሉ አልቀረንም። ያውንም ጓደኛዬን ተፈራ አስማረን አብሮን እንዲዝናና ጋብዤ። ወጣትነትን ተጌጥንበት። ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍን። ግን ከአንድ ወር ተኩል በኋላ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ለአብዮታዊ ሥራ ወደ አሥመራ ተላከ። የሙዚቃ ቡድኑ ኤርትራ ውስጥ ላለው የወገን ጦር የሙዚቃ ድግሱን ለማቅረብ፣ ከአዲሳባ ተነስቶ ወደ አሥመራ ሲገሰግስ፤ የተጓጓዘበት አውቶቡስ መንደፈራ ላይ በፈንጂ ተመታ። የእኔዪቱ መንበረ ከወቶቡሱ የፊት የቀኝ ጎማ ላይ የነበረው ወንበር ላይ ነበር አቀማመጧ። ፈንጂው ያንን ጎማ መታው። መንበረ ብቻ ስትሰዋ፣ እነጥልዬ ከከባድ እስከ ቀላል ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል። ተወዛዋዥ ነበረች። ውብ መንበረ ድንቅ ንግስት ነበረች። ሰፈሯ ሃብተ-ጊዮረጊስ ድልድይን ተሻግረን ወደአሜሪካን ግቢ ስናቀና ያለው መንደር ነው። በወቅቱ እናትዋ ዘንድ ልቅሶ ደርሼ እርሜን አውጥቻለሁ። አሁንም ነፍሷን ይማረው። ኖርዌይ መኖር ከጀመርኩ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ድግስ ላይ ተጋብዤ ነበር። ባንድ አምሽቼ ታዲያ ብዙ ኢትዮጲያዊያን ሲርመሰመሱ እያየሁ ሰደነቅ ሳለሁ፣ ከእንስቶቹ መካከል አንዷ ለየት ብላ ታየችኝ። ስትመለከተኝ እኔም አየኋት። ቀረበ አለችኝ። ፈገግ አለች፤ አወቅኋት። ዓመታት በኋላ ከብዙ ረዥም መተቃቀፍና ሠላምታ… ያኔ ካየኋት ብዙ ተቀይራለች። ጥቂት ዓይን ለዓይን ተያየን። ዓለም ጤና ከተማ በእናት አገር ጥሪው በዓል ላይ፣ መጀመሪያ ለፍቅር እሺ ያልኳት የክብር ዘበኛው ኦርኬስትራ ዳንሰሪ መስታወት ነበረች።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top