ጥበብ በታሪክ ገፅ

ጥላ-ኤል (ጥላሁን እና ኤልያስ አንድም ሁለትም)

መስከረም ለሙዚቃችን ጉራማይሌ ናት። በአሥራ ሰባተኛው ቀን ጥላሁን ገሰሰን አስተዋውቃ፤ በ24ተኛው ቀን ኤልያስ መልካን ነጠቀችን። ወሯ ተቃርኗዊ መሆኗ ውለደትና ሞትን በመያዟ ብቻ አይደለም። ይልቁኑ በሙዚቃችን ውስጥም የፈጠረችው ተጽዕኖ ለየቅል የሚታይ ነው። ሁለቱ ግለሰቦች የኢትዮጵያን ሙዚቃ የፍልስፍና መሰረት አብዝተው ተገዳድረዋል። ጥላሁንን ገሰሰን እናስቀድም። በዘመናዊ ሙዚቃችን ውስጥ ታሪክ ቀያሪ ተብለው ከሚጠቀሱ ወቅቶች መካከል 1948 ዓ.ም ግንባር-ቀደም ተደርጎ ይወሰዳል። ምክንያት አለው። ፋና ወጊው የክቡር ዘበኛ የቴአትርና ሙዚቃ ክፍል በአዲስ መልክ የተደራጀው በዚህ ዘመን ነበር። አጋጣሚው በጃዝና ፋንፋር ትርኢቶች ብቻ የታጠረውን ኦርኬስትራ ከድምጻዊያን ጋር እንድንመለከተው ዕድል ፈጥሯል።

ተዘራ ኃይለሚካአኤል፣ እሳቱ ተሰማ፣ ተፈራ ካሳ፣ መስፍን ኃይሌ፣ አየለ ማሞ፣ አስካለ ብርሃኔና አረጋሽ ኩምቴሳን ከወታደርነት ወደ መድረክ ድምጻዊነት ያሸጋገረው የወቅቱ እንቅስቃሴ፤ ጥላሁን ገሰስን ከሀገር ፍቅር ቴአትር አስኮበለለ። የኢተያው ተወላጅ ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ መድረስ የዘመናዊ ሙዚቃ ታሪካችንን ቀይሮታል። ሁለት ነገሮችን እንደ ማሳያ እንጥቀስ። ቀዳማዊ ጥላሁን ገሰሰ እንደ መጀመሪያ “ዘመናዊ” ድምጻዊ መቆጠሩ ነው። በእርግጥ ከ1948 ዓ.ም በፊት ዘመናዊ ሙዚቃዎችን የሚጫወቱ ድምጻዊያን መኖራቸው አያጠያይቅም። ነገር ግን የጥላሁን ገሰሰ ስር-ነቀል አብዮት ለእነሱም አልተመለሰም። ደብዛቸውን አጠፋው ። ሁለተኛው ጉዳይ ማኅበረሰቡ ለዘፈንና ዘፋኝነትን የሰጠውን ትርጉም በአዲስ መተካቱ ነው። ይህ ለውጥ ዘፋኝነት የሚባልን ጽንሰ-ሀሳብ ኢትዮጵያዊያን በሌላ መንገድ እንዲያስቡት አስገድዷል። አዝማሪነት የተዋረደ ሙያ ነው የሚለውን አስተሳሰብ በማለዘብ በኩል የማይተካ ሚና ተጫውቷል። ድምጻዊነትም ውርደት ሳይሆን የመኳንንቱ ልጆች ሳይቀር ተጋፍተው የሚመለከቱት ሞያ መሆኑን አስተዋውቋል። ጥላሁን በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የዘፋኝነት እሳቤ ከመሰረቱ ለማናድ ቢታትርም የዘፈን ትርጓሜ ግን እንቅፋት ሳይሆንበት አልቀረም። በመሆኑም ዘፈን ኃጢአት ነው መባሉ በዘፋኝነት አረዳድ ውስጥ የተፈጠረውን አብዮት ሙሉ እንዳይሆን አድርጎታል። ነገሩ ሃይማኖታዊ አስተምሮን የተንተራሰ ነውና ብልጭ ብሎ የሚጠፋ አልሆነም። ዘመናትን ተከትሎ እስከ አሮጌው ሚሊኒዬም ማብቂያ ዘለቀ። አሮጌው እልፍ ዓመት ግን ያላለቀውን አብዮት ተሸክሞ ሊሻገር የፈቀደ አይመስልም። ቦሌ ሬድዋን ህንጻ ውስጥ ሌላ የኪን አመጽ ተቀሰቀሰ። ኤልያስ መልካ የሚሉት ዘመነኛ ነባሩን የዘፈን ብያኔ አፈረሰ። በእርግጥም የዘሪቱ ከበደ “የእኔም ዓይን አይቷል” ሙዚቃ እንደ ቀደሙት ዘመን ሥራዎች ዘፈን ብቻ ተብሎ የሚጠቀስ አልነበረም። መዝሙረ ዳዊት እና መጽሐፈ ኢዮብን ያጣቀሰው ይህ ሙዚቃ መዝሙር ነው ወይንስ ዘፈን? የሚልን ጥያቄ አስነሳ። ሙግቱ የአድማጩ የምናብ ውጤት አይደለም። ደራሲዎቹ ይሁነኝ ብለው ያስነሱት አብዮት እንጅ። ለዜማ ማጥኛ ተብሎ የተጻፈው “የእኔም ዓይን አይቷል” የተሰኘው ሥራ በኤልያስ መልካ በኩል አስቀድሞም መዝሙር መሆኑ የታመነበት ይመስላል። በመሆኑም ዘሪቱ ከበደ ዜማውን ካጠናች በኋላ በቀረጻ ወቅት በሌላ ግጥም እንድትጫወተው አድርጓል። የኤልያስ ፍርሃት ግልጽ ነው። ድንገት የዘፈንና መዝሙርን ድንበር ማፍረስ አልፈለገም። አብሮት የነበረው ጊታርስቱ አስራት ኤፍሬም ግን ቀዳሚዎቹን ስንኞች ወድዷቸዋል። እናም መቀየር የለባቸውም ብሎ ተከራከረው። ኤልያስ ቢያንገራግርም የእግዚአብሔር ቃል ያለበት ስራ ነውና እምቢ አላለም። “የእኔም ዓይን ዓይቷል” በአልበሙ ውስጥ ተካተተ። የእውቁ አቀናባሪም የዘፈንና መዝሙር አረዳድ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ታየ። አላቆመም። በኢዮብ መኮንን እንደ ቃል አልበም ውስጥ ማኅበረሰባዊውን የዘፈንና የመዝሙር አረዳድ ዳግም ተገዳደረ። “እንደ ቃል” እንደ ስያሜው በእግዚአብሔር ቃል የተመሰረተ የሙዚቃ ሥራ ነው። ሰለሰ ከኃይሌ ሩትስ ጋር ችጌ የተሰኘውን አልበም ለገበያ አቀረበ። መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ የዘመናዊውን ዓለም ሳይንስ ሞገተ። ኤልያስ በጊዜው የሄደበት መንገድ ነባሩን የዘፈንና መዝሙር አረዳድ የሚሸር መሆኑ ባያከራክርም በግልጽ ግን ሊያረጋግጥለን አልደፈረም። በዚህ ምክንያትም ሙዚቃችን ልብ ባላለው አብዮት እየተለበለበ ጥቂት ዓመታትን ነጎደ። የብስራት ሃይለማርያም “ከምን ነጻ ልውጣ” አልበም ግን ክንብነቡን የሚገልጥ ነበር። “ማዝመር እንዲህ መዝፈን እንዲህ” ብሎ የቀደመው የዘፈንና መዝሙርን ትርጉም ስህተት ነው አለ። በስንኞቹም “ቀድሞ ባለ ነው የእኛ የእኛ መዝሙር” በማለት ለሁለቱ ቃላት ትርጉም የሰጡ አካላትን ወቀሰ። ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የነበረው ኪናዊ አብዮት ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል። ኤልያስ መልካም ዘፈንን መዝሙር አድርጎ ሙዚቀኛ ሁሉ የኃጢእት ባሪያ ነው መባሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለው እያለ አጣጥሏል። ነገሩ ኢትዮጵያዊያን ሙዚቃን እንደ ጽንሰ ሀሳብ የሚረዱበትን አዕማድ ያናጋ ነውና፤ ብቻውን በወጉ ሊፈተሸ ይገባዋል።

በዘፈን ማዘመርን …… !

እውቁ የሙዚቃ ቀማሪ አሸናፊ ከበደ (ፕ/ር) ከኢትዮጵያዊ አረዳድ ተነስተው ሙዚቃን በሁለት ይከፍሉታል። ዘፈንና መዝሙር ሲሉም ይጠሩታል። ዘፈንን ለዓለሙ ትተው መዝሙርን ለመንፈሳዊው መንገድ ያወርሱታል። ምደባቸው ግለሰባዊ አይደለም። ማህበረሰቡም ዘፈንና መዝሙርን ነጣጥሎ የሚመለከት ነው። ዘፋኝነትና ዘማሪነትንም ለየቅል ቦታ ይሰጣቸዋል። ቀዳሽን አክብሮ አዚያሚን ያወግዛል። ጥላሁን ገሰሰ የአዝማሪን የመከራ “መስቀል” መሸከሙ፤ ዘፋኝነትን እንደ ሞያ እንዲቆጠር ቢያደርገውም በዘፈን ትርጉም ላይ ግን ጥያቄ አልነበረውም። በመሆኑም የዕድሜ ጀንበሩ ማዘቅዘቅ በጀመረችበት ወቅት ፈጣሪዬን በመዝሙር ላመስግነው ማለቱ አልቀረም። የሕይወቱን የመጨረሻ ሙዚቃው ከኤልያስ መልካ ጋር ሲሰራም ደጋግሞ የተናገረው እውነት ይህንኑ ነበር። “አንድ አልበም ካንች ጋር ብሰራ እኮ ከዛ በኋላ ዘማሪ ሆኜ ቁጭ ማለት ነው የምፈልገው” የአብነቱ ብላቴና በጊዜው ምን እያሰበ እንደነበረ ለማወቅ ቢያዳግትም በኋላ ላይ የተጓዘበት መንገድ ግን ዘፈንን እንደ ኃጢአት የሚቆጥር ባለመሆኑ ጥላሁን የቆመበትን አስተሳሰብ ነቅፏል። አጋጣሚው የሁለቱን ሙዚቀኞች የዘፈን አረዳድ በአንብሮና ተቃርኖ የቆመ መሆኑን ያስገነዝባል። የኤልያስ መልካ የኋላ ሙግት ግን በዚህ አልተገታም። የቀደመውን ዘመን የዘፈን ትርጓሜ ጥሶ ዘፈንን እንደ መዝሙር መዝሙርን እንደ ዘፈን ተመልክቶታል። የፍች ለወጡ ዘማሪነትም ኃጢአት ሊሆን የሚችልበትን ነገር የጠቆሞ በመሆኑ ያስደነግጣል። በ2009 ዓ.ም ከሪፖርተር ጋዜጣ ያደረውገውን ቃለ-ምልልስ እንዋስ። “ቤተ-ክርስትያን ውስጥ የሚሰሩ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል ይስማማሉ ብዬ አላምንም። አሁን የምሰራቸው ከመዝሙር ጋር ይቀራረባሉ ብቻ ሳይሆን ይበልጣሉ ብዬ አስባለሁ። መዝሙር ለእኔ የእግዚአብሔርን ቃል የሚመክር ነው” ንግግሩ አብዮቱን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። የቀደመው አረዳድ የቤተ ክርስትያን ዜማን ሁሉ መዝሙር አድርጎ ከዛ ውጭ ያለውን በዘፈንነት የሚፈርጅ ነበር። ኤልያስ መልካ ግን ዘፋኝን ዘማሪ፤ ዘማሪን ዘፋኝ አደረገው። ሐሳቡን ይበልጥ ያብራራው በብስራት ኀይለማርያም ሙዚቃ ውስጥ ነው።

ቀድሞ ባለ ነው የእኛ የእኛ መዝሙር
በአዝማሪ አሳበው አዚመው ለምስል
በመዝሙር ዘፈኑ በዘፈን አዘመርን
ተረፍን እንጅ መቼ ተራፊም አከበርን

ሐሳቡ ለውጥና ነውጥ አንድ ላይ የገጠሙበት ብቻ አይደለም። ከየት መጣ ሳይባል እንደወደቀ መብረቅ ያስደነግጣል። ምን መዓት ነው ያስብላል። ልብ ብሎ ለሰማው ሰው ሙዚቃ ውስጥ እንዲህ ያለ አብዮት ሲደገስ የት ነበርን የሚል ጥያቄን ያጭራል። ትርጓሜ ውስጥ ገብቼ ሌላ ዓመፅ አልቀሰቅስም። ይልቁኑስ የመጨረሻዋን ስንኝ ብቻ ልድገማት። “ተረፍን እንጅ መቼ ተራፊም አከበርን” ይላል። “ተራፊም” ትርጉሙ የአማልክት ምስል ማለት ነው። ኤልያስ ነባሩን የመዝሙር አረዳድ ከአምልኮተ-ጣዖት ጋር አስተሳስሮ አዲስ ብያኔን ያስቀምጣል። በሙዚቃዬም ዘመርኩ እንጅ ለኃጢአት እስረኛ የሚያደርገኝን ዘፈንን አልሰራሁም ይላል። ክርክሩ በባዶው ከሆነ እርባና- ቢስ መሆኑ ገብቶታል። ስለሆነም የኢትዮጵያዊያን የመዝሙርና ዘፈን ድንበር የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ተውሶ ይሟገታል። ተለምዷዊ ብያኔያችን ከታላቁ መጽሐፍ የተቀዳ ሳይሆን ሰዋዊ ነው ይላል።

እንዲያው በሰው ወግ ብቻ
ባሉኝ ሚዛን በፍርጃ
በራስ ህግ በዓይን ዕይታ
አይጥፋ የልቤ ደስታ

ከላይ አንድ ከታች አንድ ስንኞችን እንፈክር። ኤልያስ ዘማሪ መሆኑን ቢነግረንም ሃይማኖት ግን አልነበረውም። ጥያቄ አንድ፡- ታዲያ እንደዚህ ከሆነ በመዝሙሩ የሚሰብከን የማንን ቃል ነው? ጥያቄ ሁለት፡- የእምነት ተቋም የሌለው ሰው ዘማሪ ይባላል ወይ? ምላሹን ሩቅ ሳንሄድ በመጨረሻው ስንኝ ላይ እናገኘዋለን። ኤልያስ በራስ ህግ በዓይን ዕይታ፤ አይጠፋ የልቤ ደስታ ይላል። የልቤ ደስታ የሚለን እግዚአብሔርን ነው። ሃይማኖትን ገፍቶ እግዚአብሔርን ይከተላል። ነገሩ ከፊል መጸሐፍ-ቅዱሳዊ ከፊል ፍልስፍናዊ እውነትን የያዘ ይመስላል። በታላቁ መጽሐፍ ሰዋዊው ስርዓትን ትታችሁ እኔን ተከተሉ የሚል ቃል ሰፍሯል። “በዋጋ ገዝታችኋልና የሰው ተጓዠች አትሁኑ” (ቆረንቶስ 7፡ 24) ኤልያስ መልካ የዘፋኝነትና ዘማሪነት መለያየትን ሰው የፈጠረው እንጅ መጽሐፍ-ቅዱሳዊ አይደለም ብሎ በማመኑ እሱን ሲታገል ኖሯል። በዘፈን የእግዚአብሔርን ቃል መስበክም ዘማሪነት ነው በሚል ነባሩን ትርጓሜ ሽሯል። ኪናዊ አመጹ ትናንት በአንድ ሰው ይመራ እንጅ ዛሬ ግን ግለሰባዊ ጉዳይነቱ አብቅቷል። በዘፈን ማዘመር የሚል መንገድ የዛሬው ትውልድ የኢትዮጵያ ሙዚቃ መገለጫ ሆኗል። በቅርቡ ኮሮናን አስመልክቶ ለገበያው የበቃውን ንጋት የተሰኘ አልበም በወጉ ካጤንነው የአልያስ አመጽ ፍሬ ማፍራቱን ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ ነገሩ የተገለጠው በሙዚቃዊ ሥራዎች ብቻ አይደለም። በገና ስቱዲዮ ውስጥ የተለኮሰው አብዮት የበርካታ ሙዚቀኞችን የዘፈንና ዘፋኝነት አረዳድ ቀይሯል።በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ እንደ አዲስ ክስተት የሚስተዋለውን ዘፈን መልካም ነገሮችን ብቻ ነው ማስፋፋት ያለበት የሚል አስተሳሰብንም አንግሷል። ዛሬ የአብነቱ ተወላጅ በቀየሰው ጎዳና በርካታ ታዋቂ አቀናባሪዎች አሉታዊ ስሜትን የሚፈጥር ሙዚቃ አንሰራም እያሉ ነው። ከዚህ አንጻር የኤልያስ መልካ ተጽዕኖ ዛሬያዊ ብቻ አይደለም። ነገ ምናልባትም ከነገ ወዲያም በታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ ይሰጠው ይሆናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top