ታሪክ እና ባሕል

የጉራጌዎች የመስቀል በዓል አከባበር

መግቢያ

በቅድሚያ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሀነ-መስቀሉ አደረሳችሁ። የተከበራችሁ አንባብያን በዚህ ንባባችሁ የመስቀል በዓል አከባበር በጉራጌ ህዝብ ዘንድ ምን ገፅታ እንዳለውና እያንዳንዱ ክንዋኔም በማህበረሰቡ ህይወት ላይ ምን አንድምታ እንዳለው መረጃ እንለዋወጣለን።

ስለጉራጌ መስቀል በዓል አከባበር ጥቅል ጉዳዮች

ጉራጌ የሚለውን ቃል ስትሰሙ ተምሳሌት የሆነበት ጥንታዊና ዛሬያዊ ጠንካራ የስራ ባህሉ፣ በየደረሰበት ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ የመኖር ልምዱ፣ የክትፎ በቆጮ አስተዋፅዖው፣ የመስቀል በዓል ለየት ያለ አከባበሩ፣ በሀገራችን የዕቁብና የእድር ፍልስፍና ባለቤት መሆኑ፣ ወዘተ… ከፊታችሁ ድቅን ይላል ብዬ አምናለሁ። መስቀል በጉራጌዎች ዘንድ በተለየ ሁኔታ የሚከበረው ለበዓሉ የተለየ ፍቅርና ከበሬታ ስላላቸው ነው። ከዚህም የተነሳ ከመላው ኢትዮጵያና ከተለያዩ ሀገሮች ጭምር ተወላጆቹ በመስቀል ሰሞን በነቂስ ወደትውልድ መንደራቸው የሚተሙት። የጉራጌ ልጆች በህይወት እያሉ ችግር ካልገጠማቸው በቀር የገንዘብ አቅም ማነስ ቢፈታተናቸው እንኳን ተበድረውም ቢሆን ለመስቀል ወደ ወላጆቻቸው ከመሄድ አይቀሩም። ምክንያቱም እናትና አባት፣ ቤተሰብና ጎረቤታቸው በናፍቆት ይጠብቋቸዋል። በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር በማክበራቸው ምርቃትና በረከትን ይቀበላሉ። ጉራጌዎች ለመስቀል በዓል ምንም ቢሆን ሀገር ቤት ከመግባት አይቀሩም። ከሊስትሮው፣ ቅርጫት ተሸካሚው፣ ጉልት ቸርቻሪዋ፣ ሱቅ በደረቴው፣ የሰው ቤት ሰራተኛዋ፣ የሻይ ቤትና የሆቴል አስተናጋጆቹ፣ የበግና የሉካንዳ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴው፣ ከፍተኛ ባለኮከብ ሆቴል፣ አምራች ኢንዱስትሪ እስካላቸው ባለሀብቶች ድረስ ለመስቀል ሀገር ቤት ይገባሉ። በመስቀል ሰሞን አዲስ አበባና ሌሎች በርካታ የሀገራችን ከተሞች ለምን ቀዝቀዝ እንደሚሉ የሚያውቁት ያውቁታል። ጉራጌዎች ሙልጭ ብለው ወደሀገር ቤት ስለሚገቡ ነው።

የበዓሉ አከባበር

የጉራጌዎች የመስቀል በዓል አከባበር ከወረዳ ወረዳ በአንዳንድ ክንዋኔዎች ላይ በጣም መጠነኛ ልዩነቶች ቢኖሩትም አጠቃላይ ባህርዩ ግን ተመሳሳይ ነው። ክብረ- በዓሉ አመቱን ሙሉ ዝግጅት የሚደረግበት ነው። በሁሉም አካባቢዎች የዘንድሮ መስቀል እንዳለፈ በበጋው ለሚቀጥለው መስቀል ዝግጅት ይጀመራል። እዚህ ላይ የጉራጌዎች ባህላዊ ጋብቻና መስቀል ያላቸውን ጥብቅ ትስስር ማንሳቱ አስፈላጊ ይሆናል። በእንቁጣጣሽና በመስቀል መካከል ባሉት ቅዳሜና እሁዶች አብዛኞቹ የጉራጌ ልጆች ሀገር ቤት ሄደው የጋብቻ (የሰርግ) ስነ-ስርዓታቸውን ያከብራሉ። ከዚህም በመነጨ መስቀል በሰርጎች፣ ሰርጎች ደግሞ በመስቀል ክብረ-በዓል ልዩ ድምቀት ያገኛሉ። ስለዚህም የጉራጌዎች የጋብቻ ስርዓት ከመስቀል አከባበር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው ይነገራል። ክብረ- በዓሉ በሰርግ ጭፈራዎች ታጅቦ ድባቡ እየደመቀና እያማረ ወደመስቀል ይሸጋገራል ማለት ነው። ለመስቀል ዝግጅት በቤተሰቡ መካከል ግልፅ የሆነ የስራ ክፍፍል አለ። አባት በወንድ ልጆቹ እየታገዘ በበጋው ወቅት ለመስቀል የሚሆን በቂ የማገዶ እንጨት ያዘጋጃል። ቤቱ አርጅቶ ከሆነ ይጠግናል። በዓሉ ሲቃረብም በከተሞች ከሚኖሩ ልጆቹና ወንድሞቹ በሚላክለት ገንዘብ ካለዚያም በራሱ ወጭ የመስቀል የእርድ ከብት ይገዛል። እናት ደግሞ በሴት ልጆቿ እየታገዘች ለመስቀል የሚያስፈልገውን ቆጮ፣ ቅቤ፣ ቡላ፣ አይብ፣ ጎመን፣ ሚጥሚጣ፣ ቅመማቅመም ታዘጋጃለች። ሴት ልጆች ቤቱንና ደጁን ያሳምራሉ። ግድግዳውን የባህል ቀለም በጥብጠው በማዘጋጀት ይቀባሉ። ጉራጌዎች መስከረም 12 “የመስቀር ምኬር” ብለው በጎመን ክትፎ የበዓሉን መጀመር ያበስራሉ። በማግስቱ መስከረም 13 “ወሬተሐና” ተብሎ መስቀል በመድረሱ በጉጉትና በሐሴት ያለእንቅልፍ የሚታደርበት ቀን ነው። በዚህ ቀንም በተመሳሳይ ሁኔታ የጎመን ክትፎ ይበላል። በዚህ መንገድ በዓሉ ሳምንቱን ሙሉ ይቀጥላል። በሳምንቱም አዳብና ይከበራል። ከዚህ ቀጥሎ በጉራጌ መስቀል ውስጥ ጎልተው የሚከናወኑትን የተወሰኑ ዋና ዋና ጉዳዮች እናነሳለን።

የመስቀል እርድ ስነስርዓት

በጉራጌ ማህበረሰብ የመስቀል ክብረ-በዓል የእርድ ስነ- ስርዓት የሚከናወነው በአመዛኙ መስከረም 15 ነው። ይህ ዕለት ወኸምያ ይባላል። በዚህ ዕለት ዝቅተኛም፣ መካከለኛም ሆነ የተሻለ ኑሮ ያለው የጉራጌ ተወላጅ በየደጁ የእርድ ስነ-ስርዓት ያከናውናል። የሚታረደው ከጥጃ እስከሰንጋ ሲሆን የእርድ ከብቱን ደረጃ የሚወስነው አንድም የቤተሰቡ የኢኮኖሚ አቅም ሌላውም የቤተሰቡ አባላት ብዛት ነው። አንድ ከብት ለብቻው፣ ለሁለት ወይንም ለአራት ቤተሰብ በጋራ ታርዶ ሊከፋፈል ይችላል። እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ቁምነገር የማህበረሰቡ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ ተፈቃቅሮ አብሮ የመኖር ትልቅ እሴት ነው። ይኸውም በሰፈሩ ውስጥ ልጆች የሌሉት ወይንም ያልደረሱለት፣ የእርድ ከብት ሊገዛለት የሚችል ምንም ዓይነት ዘመድ በከተማ የሌለው፣ የኢኮኖሚ አቅሙ በጣም ደካማ የሆነ ቤተሰብ በመንደሩ ውስጥ ካለ የተሻለ አቅም ያላቸው ቤተሰቦች “እኛ አርደን ስንበላ እነርሱ በበዓል ጦም ማደር የለባቸውም” በሚል በጎ ስሜት ከታረደው ከብት ድርሻቸው ላይ በማንሳት የተወሰነ ስጋ አቅሙ ደካማ ለሆነው ቤተሰብ ይሰጣሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ሚስትም ሆነች ልጆች ደስተኞች ከመሆናቸው በቀር ምንም ዓይነት ተቃውሞ አያቀርቡም። ጉራጌ ምንም ቢሆን መስቀልን ብቻውን አይበላም ለሚባለውም ኃይለ-ቃል አንዱ ማሳያ ነው። ሌላው አትኩሮትን የሚስበው ጉዳይ የታረደው ከብት ሽሉዳ (ስየ) የአራስ ድርሻ (የጭን ወረት) ተብሎ በመንደሩ ውስጥ በቅርቡ የወለደች አራስ ካለች ለእርሷ ይሰጣታል። የበሬው ሻኛ (ጭየ) ደግሞ የአባት ድርሻ (የአብ ወረት) ተብሎ ከእርዱ በ3ኛው ቀን አባት ወይንም አያት ቤት ተወስዶ ወይንም ደግሞ እነርሱ ተጠርተው ሻኛው ተቀቅሎ ቀርቦላቸው ተመርቆበት ለእንግዳው መስተንግዶ ይደረግበታል። በነገራችን ላይ በግም ቢታረድ ፍርምባው (ገገበት) የእናት ድርሻ (የአዶት ወረት) ተብሎ ይበረከትላታል። ይሄ ጉራጌዎች ከጥንት ጀምሮ ይዘውት የዘለቁት የመተሳሰብና የመከባበር የባህል እሴት ነው። ታዲያ የወኸምያ ዕለት የእርዱ ስነ-ስርዓት በጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁሉም ቤተሰብ አመሻሽ ላይ ቁርጥ ስጋ በቅቤ ይመገባል። እራት ደግሞ ዘግየት ብሎ ክትፎ በቆጮ ቀርቦ ቤተሰቡና ከከተማ የመጡ ሌሎች እንግዶች ካሉ በጉራጌ ባህላዊ መመገብያ (ይወደረ) ቀርቦላቸው ይመገባሉ። ሁሉም ሰው ይወደረውን ከብቦ ይቀመጣል። እናት በሴት ልጀቿ እየታገዘች ክትፎውን ከአባት ወይም ከትልቁ እንግዳ ጀምራ ታድላለች። ክትፎ የሚበላው የእንሰት ቅጠል ጠውልጎና በክቡ ተከርክሞ በተሰራ ጥለስ በሚባልና በእጅ ሲያዝ ጎድጓዳ ሳህን በሚመስል መመገብያ እና ከቀንድ በተሰራ ማንኪያ (አንቀፎ) ነው። የሚገርመው ነገር ቀደም ባሉት ቀናት እንኳን ተሳክቶላቸው ከተለያዩ አካባቢዎች ወደትውልድ መንደራቸው መሄድ ያልቻሉ የጉራጌ ተወላጆች ቤተሰቦቻቸውን፣ ጓደኞቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ይዘው ለአንድ ቀን አዳርም ቢሆን አገር ቤት ደርሰው የሚመለሱት በዚህ በወኸምያ ዕለት ነው። አብዛኛውን ጊዜ አገር ቤት ለሚገኙት ወላጆች የእርድ ከብቱን የሚገዙላቸውም በከተሞች ወይም ከአገር ውጭ የሚገኙ ልጆቻቸው፣ ወንድሞችና እህቶቻቸው ወይንም ዘመዶቻቸው ናቸው። ለመመረቅና ለመባረክ ማለት ነው። ጉራጌዎች ለሚወዱት ጎረቤትም ቢሆን ዓመቱን ሙሉ ሰርተው ካጠራቀሙት ገንዘብ ላይ ቀንሰው የእርድ ከብት መግዣ ወጪ ማገዝ በጣም የተለመደ አኩሪ ባህል ነው።

የመስቀል ደመራ ስነስርዓት

መስከረም 16 የሚከናወነው የደመራ ስነስርዓት (ይሳት ከረ) የክርስትና እምነት ተከታይ በሆኑ ጉራጌዎች ዘንድ ልክ እንደእርድ ስነ-ስርዓት ሁሉ የተለየ ክንዋኔ አለው። ጠዋት በቅቤ የተቅለጠለጠ ጣፋጭ የቡላ ገንፎ (ያጥሜጥ ኦዛት) ይባላል። ከዚያም የቅቤ ቡና (የቅብ ቃዋ) ይጠጣል። መሰንበቻውን በየአብያተ-ክርስትያናቱ ደጃፍ በአካባቢው ወጣቶች የተደመረው የአድባራት የደመራ ማህበራት ስነ- ስርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት ከቀትር በኋላ በድምቀት ይከናወናል። ምሽቱን ሁሉም ሰው በየደጁ (ጀፎረ) ላይ ማምሻውን ችቦ ያበራል። በቤተክርስትያንም ሆነ በየሰፈሩ ደመራ ላይ ይዘመራል። ይጨፈራል። ለደመራ ያለው ክብርና ፍቅር በልዩ ልዩ መንገዶች ይገለፃል። ስለጉራጌዎች የመስቀል ደመራ አንዱ አስገራሚ ነገር ትልቅነቱ ከሌሎች አካባቢዎች የሚለይ መሆኑ ነው። በተለይ በቤተክርስትያን እና በጀፎረ ላይ የሚበራው ደመራ ያለምንም ማጋነን በስፋቱም በጥልቀቱም አንድ ጎጆ ቤት ያህላል። የትኛውም መንደር ላይ ስትዘዋወሩ ትንሽ ደመራ ቆሞ አይታይም። ለቤት መስሪያ፣ ለማገዶና ለደመራ የተቆረጡትን ዛፎች ለመተካት በየዓመቱ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ማካሄድ ባለፉት ዓመታት በጉራጌ ምድር እንደባህል ሆኗል።

የደንጌሳት ስነስርዓት

መስከረም 14 የሚከናወነው ደንጌሳት በአንዳንዱ አካባቢ የዴንጋ እሳት በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ይሽታ መስቀር ይባላል። በተለይ በምስራቅ ጉራጌ በሚኖሩ ተወላጆች ዘንድ የደንጌሳት አከባበር ልዩ ድምቀት ይታይበታል። ዋናው ነገር ዕለቱ የልጆች የራሳቸው የደመራ ቀን መሆኑ ነው። ልጆች በዚህ ዕለት የራሳቸውን ደመራ ቢያበሩም የዋናው ደመራ ዕለትም ከሌላው ህብረተሰብ ጋር ተቀላቅለው አብረው ችቧቸውን ይዘው መጥተው እንደሚያበሩ መዘንጋት የለበትም። የየአካባቢው ሴቶች ደግሞ በዚህ የራሳቸው መስቀል ተብሎ ተለይቶ በሚከበርላቸው ዕለት ራሳቸው በመመገባቸው ሳይሆን ለብዙ ቀናት ለፍተው፣ ደክመው በጭስ እየተጨናበሱና እሳቱ እየለበለባቸው አዘጋጅተው ያቀረቡትን የጎመን ክትፎና አይብ በቆጮ ቤተሰቡና ከከተማ የመጡ እንግዶቻቸው ሲመገቡ ማየት የተለየ ደስታን ይፈጥርላቸዋል። እነርሱማ ቅመማ ቅመሙን ሲያዘጋጁ፣ ቅቤውን ሲያነጥሩ፣ ሚጥሚጣውን ሲወቅጡ፣ ቆጮ ሲጋግሩ፣ ስጋ ሲከትፉ፣ ጎመን ሲቀቅሉና ሲጨምቁ፣ በአጠቃላይ ምግቦቹን ሲያዋህዱ ከምድጃው አጠገብ በስራ ተጠምደው ውለው ይህንን የበዓል ማዕድ ሊመገቡ እንኳን ቢፈልጉ ሊዋጥላቸው አይችልም። በጣም ስለደሚክማቸውና ደስታቸው እጥፍ ድርብ ስለሚሆንም የምግብ አምሮታቸው ይጠፋል። ታዲያ ደንጌሳት ከግብዣው በኋላ በጭፈራም ይታጀባል። በጣም ደማቅ ነው። “ሞላ – አልሞላም” የሚል በጣም አጓጊ የሆነ ስነስርዓትም አለው። ይህ በዓል በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞችም አገር ቤት መሄድ ያልቻሉ ጉራጌዎች በድምቀት ያከብሩታል።

የሴቶች በዓላት

ከዚህ የሴቶች መስቀል በዓል ጋር ተያይዞ ሌላም ነገር ትኩረት ተሰጥቶት ሊነሳ ይገባዋል። የጉራጌ ሴቶች በየዓመቱ የራሳቸው የሆነ የመስቀል ክብረበዓል ዕለት ብቻ አይደለም ያላቸው። በየዓመቱ በህዳር አካባቢ ወጣትና ታዳጊ ሴቶች የክት ልብሳቸውን ለብሰው፣ ልክ እንደእንቁጣጣሽ ከአካባቢው ሕብረተሰብ የቆጮ፣ የቅቤ፣ የአይብ፣ የጎመን፣ የስጋ፣ የገንዘብ፣ የመሳሰለውን ስጦታ አሰባስበው በየአካባቢያቸው ለአንድ ቀን በጋራ የሚያከብሩት በዓል (ነቈ) አንዱ ነው። ይህ ቀን በመስቀል መንፈስ የሚከበርና የወጣት ሴቶች የነፃነት ቀን ተብሎ ይታወቃል። የጉራጌ ሴቶች በዓለም ላይ ቀዳሚ የሆኑበት ሌላም በዓል አላቸው። በጥር አካባቢ የሚከበረው የእናቶች ቀን (አንትሮሽት) ነው። እናቶች ከዚህ ቀን በፊት የቤታቸውን ስራ፣ ምግብ ማዘጋጀቱን፣ የልብስ አጠባውን፣ ቤትና ደጁን ማሳመሩን፣ የመሳሰለውን ሁሉ ጥንቅቅ አድርገው ከሰሩ በኋላ በአንትሮሽት ቀን በቤታቸው ውስጥ ምንም ዓይነት ሌላ መደበኛ ስራ አያከናውኑም። ተጣጥበው፣ ፀጉራቸውን አበጥረው፣ የክት ልብሳቸውን ለብሰው፣ ጌጣጌጦቻቸውን አድርገው የአንትሮሽት በዓላቸውን ያከብራሉ። ከተወሰኑ አስርት ዓመታት በፊት እንዲያውም ከወገባቸው በላይ ራቁታቸውን ሆነው ቅቤ ይለቀለቁ ወይንም ይቀቡ እንደነበረም ፀሀፊው ያስታውሳል። በነገራችን ላይ የመጀመሪያዋ የሴቶች መብት ተሟጋች፣ የተደራጀ የሴቶች የፆታ ትግል ፋና ወጊና መሪ የነበረችውና ከ150 ዓመታት በፊት በጉራጌ ምድር የተከሰተችው የብሄሩ ተወላጅ ጀግናዋ የቃቄ ውርድወትና ሌሎችም ታላላቅ የጉራጌ ሴቶች በዚህ ህይወት ውስጥ አልፈዋል። ከዚህም የተነሳ እነዚህ ሴቶች በተለየ ሁኔታ ከፍ ተደርገው የሚወደሱባቸውና የሚከበሩባቸው የነፃነት ቀናት ካለፈው ጊዜ በተሻለና በተደራጀ መልኩ የመንግስትንና የህብረተሰቡን ትኩረት ይበልጥ አግኝተው ቢከበሩ ፋይዳቸው እጅግ የጎላ መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል።

የምርቃት ስነስርዓት

ምርቃት ወይንም በረከት ለጉራጌ ተወላጆች ልዩና ጥልቅ ትርጉም አለው። ንብረታቸው፣ ገንዘባቸው፣ ጤናቸው፣ የመንገድ ስንቅና የዘመናት ቀለባቸው፣ የነገና ከነገወዲያ ተስፋና ምኞታቸው፣ የቅርብና የሩቅ ግባቸው ማሳኪያ ተደርጎ ስለሚታይ በመስቀል ሰሞን ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ተደጋግሞ ይመረቃል። በየቀኑ፣ በየሰዓቱ፣ ጠዋትም፣ ቀንም፣ ምሽትም፣ በቤትም፣ በውጭም፣ በደመራ፣ በእርድ፣ በሻኛ መስተንግዶ፣ በቡና መጠጣት ስነስርዓት ላይ ሁሉ ይመረቃል። ለአገር ዳር ድንበር መከበር፣ ለልጅ ፍሬ በረከት፣ ለሰብል በሰላም መድረስ፣ በአገር ላይ ምንም ዓይነት ችግር፣ ሁከትና መከራ እንዳይደርስ ይመረቃል። አብዛኛውን ጊዜ መራቂዎቹ በዕድሜ ከፍ ያሉ እና ማህበራዊ ተቀባይነታቸው የተሻለ የአካባቢው ሰዎች ናቸው። እነዚህ የተከበሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ህብረተሰቡ የተስማማበት የሆነ ባህላዊ ማእረግ አላቸው። ማዕረጉ በጦር ሜዳ ተሳትፎና ገድል፣ በሀብት ስፋትና ችግረኞችን ለመርዳት ባሳዩት ዘላቂ ቁርጠኝነት፣ እርሻቸውንና ከብቶቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ይዘው ቤተሰባቸውን በተሻለ መንገድ በማኖራቸው፣ በእንግዳ አቀባበላቸው፣ በመሳሰሉት ጉዳዮች ከሌሎች የተሻለ ሁኔታ ከታየባቸው ወንዶቹ አጋዝ፣ ኤስሓርብ፣ ዳሞ፣ ወንዠትአርብ፣ መስቀር፣ ሙራበነስ፣ ሴቶቹም አጂየት፣ የመሳሰለው ባህላዊ ማእረግ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ደጃዝማች፣ ቀኝአዝማች፣ ፊታውራሪ፣ እንደሚባለው ማለት ነው። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ጉራጌዎች እርግማን ዘርን ያጠፋል፣ ለልጅ ልጅ ይተርፋል፣ ጥፋትና እልቂት ያስከትላል፣ ወዘተ. ብለው ስለሚያምኑ ከምንም ነገር በላይ ይፈሩታል። እንዳይረገሙ ብቻ ሳይሆን ትውልዳቸውን እንዳይረግሙም ብርቱ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።

የምሽት ሸንጎ ስርዓት

ጉራጌዎች በሀገር ቤት ከወትሮው በተለየና በበለጠ በመስቀል በዓል ሰሞን የሚጠቀሙበት የምሽት ሸንጎ (ውኬር) ነው። በየምሽቱ ከሰፈሩ ተለቅ ባለ ሰው ቤት ተሰብስቦ ቡና እየተጠጣ የመረጃ ልውውጥና ምክክር ይደረጋል። አገር እንዴት ዋለ? ዛሬ ገበያ እንዴት ነበረ? ምን ተወደደ? ምን ረከሰ? ከከተሞች የመጡ ሰዎች ካሉ አዲስ አበባ (ሸዋ) እንዴት ነው? እገሌ ልጆችህ እንዴት ናቸው? ደረሱልህ? ይረዱሀል? አዝመራው እንዴት ነው? ዘንድሮ የእከሌ ልጆች ለመስቀል ሳይመጡ የቀሩት በሰላም ነው? ወዘተ. እየተባለ ይመካከራሉ። ስለመንግስት ግብር አከፋፈል፣ ስለማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የአረም ማጥፊያ አጠቃቀም ውይይት ይደረጋል። ከከተማ የመጡት ዘመናዊ አስተሳሰቦችን፣ የሀገር ቤቶቹ ደግሞ ለከተሜዎቹ ባህላዊ ቁምነገሮችን ያጋራሉ። ውይይቶች የሚካሄዱት በጉራጊኛ ነው። ይህ ደግሞ ቋንቋው እንዳይጠፋና ወጣቶቹም እየተጠቀሙበት እንዲያድጉ የሚረዳ ሆኖ ተገኝቷል። ልጆችና ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ በትላልቆቹ ሰዎች መረጃ ካልተጠየቁ ወይንም ካልተፈቀደላቸው በስተቀር አይናገሩም። ሽማግሌዎቹ ሲያወሩ ማንም ሰው ጣልቃ እንዲገባም አይፈቀድለትም። ሸንጎ ክቡር ነው። አንዱ ሲያወራ ሌሎቹ ዝም ብለው ማዳመጥ ብቻ ነው። በምሽት ሸንጎ ጥፋትና በደል እንዳይፈፀም ይመከራል። ያጠፋና የበደለ ይገሰፃል። በጎ የሰራ ይመረቃል። ጎረቤታሞች (ኔሑ ቃዋ ተቃዎ) እየተባለ ቡና በየተራ እየተጠራሩ የሚጠጡበት ጠንካራ ስርዓት አለ። በመስቀል ሰሞን ደግሞ በጣም በተለየ ሁኔታ የሰፈሩ ሴቶች የቅቤ ቡናቸውን ከቡና ቁርስ (ሳፍራ) ጋር ይዘው ተለቅ ወዳሉት ሰዎች ቤት ወስደው የመጋበዝም የዳበረ ባህል አለ። በተለይ ልጆቻቸው ከከተማ ለመጡላቸው ወላጆች እስከ 3፣ 4 እና 5 ጀበና ቡና ሊመጣ ይችላል። ለእንግዶቹ ጭምር የፍቅርና የአክብሮት መግለጫ መሆኑ ነው።

የቂጫ (ሴራ) ስርዓት

ጉራጌዎች የመስቀል በዓል ከጥንት ጀምሮ ሲሰራበት የቆየውንና የተከበረውን ባህላዊ የፍትህ አስተዳደር (ቂጫ) ስርዓታቸውን የሚያዳብሩበት አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። ቂጫ በአንዳንዱ አካባቢ ሴራ ይሉታል። በምስራቅና በምዕራብ ጉራጌ የተለያዩ ሴራዎች አሉ። ባህላዊ ስርዓቱ ከመንደር ጀምሮ፣ በወረዳ (ክፍለህዝብ) ና ከዚያም በከፍተኛ (አጠቃላይ) ደረጃ የተዋቀረ የዘመናዊ ፍርድ-ቤቶች ዓይነት አደረጃጀት ያለው ነው። ከታች እስከላይ በይግባኝ ይሄዳል። ከመደበኛ ፍርድ-ቤቶች የሚለየው ያጠፋውን መቅጣት ብቻ ሳይሆን የተበዳደሉትን አስታርቆ ወደህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉና እንደቀድሞአቸው አብረው እንዲኖሩ የማድረጊያ ስልትም ጎን ለጎን የሚሄድ ነው። በመስቀል ሰሞን የቂጫ/ሴራ ሸንጎ ሽማግሌዎች በየጀፎረው ባለው ዋርካና ዝግባ ስር የተጣላ ሲያስታርቁ፣ ሽምግልና ሲያዩ፣ ስለአካባቢያቸው ከከተማ የመጡ ልጆቻቸው ባሉበት ሲወያዩ ይታያል። ሌላው ቀርቶ በከተሞች የሚኖሩ ተወላጆች እንኳን በንግድ ወይም በሌላ ምክንያት ያለመግባባትና ግጭት ቢፈጥሩ የተበዳደሉትን በማገናኘት ጉዳዩ ታይቶ እንዲፈታ ይደረጋል። ክስ ሲሰማ ልክ እንደፍርድ ቤት ሁለቱ ወገኖች ዋስ (ቃማ) ጠርተው ክርክር (ሽር) አካሂደው፣ ምስክር (መሮ/ቃማ) አሰምተው፣ የመልስ መልስ ተሰጣጥተው ነው ጉዳዩ ወደፍርድ የሚሄደው። በነገራችን ላይ የጉራጌ ህዝብ የቂጫ/ የሴራ ስርዓት በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች አካባቢዎችም በሚኖሩ የማህበረሰቡ አባላት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል።

የአዳብና አከባበር

አዳብና መስቀል በዋለ በሳምንቱ የሚከበር የመስቀል አካል የሆነ ትልቅ በዓል ነው። በተለይ በምስራቁ የጉራጌ ክፍል ጭፈራን ጨምሮ ትልቅ ድምቀት አለው። ለመስቀል የታረደው ከብት ስጋ በኩሳዬ ላይ ተደርጎ ለ3 ቀናት ያህል በጥሬው ይበላል። በሳምንቱ የዝልዝል ስጋ ቅቅል ክትፎ (ትኩር ክትፎ/ትኩል) ዙሪያውን አይብ ተደርጎበት ሲመገቡት በጣም ይጥማል። ለመስቀል መገልገያነት ከግድግዳ ላይ ወርደው የነበሩት የባህል ቁሳቁሶችና የዕደጥበባት ውጤቶች ማለትም ጣባው፣ ሴራው፣ ቈርየው፣ አንቀፎው፣ ቢላው ሁሉ ታጥበው ወደነበሩበት የሚመለሱት ከዚህ ከአዳብና ቀን በኋላ ነው። ከዚያ በኋላ እየዞሩ ዘመድ መጠየቁ ይቀጥልና እንግዶች ወደየመጡበት ይመለሳሉ። በመስቀል ሰሞን የተዳረችው ሙሽሪትም ቤተሰቦቿን ጠይቃ ለመመለስ ትሄዳለች። ከዚያም ከተወሰኑ ቀናት ወይንም ሳምንታት በኋላ ለባሏ ቤተሰቦች የሚሆን ስጦታ (ጋቢ፣ ነጠላ፣ ጫማ፣ ጭራ፣ መቀነት፣ ወዘተ.) ከዘመዶቿ ሰብስባ ይዛ ወደተዳረችበት ቤቷ ትመለሳለች።

ምን እንማራለን?

ከጉራጌ መስቀል በዓል አከባበር በርካታ ቁምነገሮችን መማር እንችላለን። ከሁሉም በላይ ግን ለወላጆች፣ ለቤተሰብ፣ ለጎረቤት፣ ለትውልድ አካባቢ፣ ለሀገር፣ ለባህል እሴቶች፣ ለችግረኞች፣ ወዘተ… የሚሰጥ ፍቅርና አክብሮት፣ ተቆርቋሪነት፣ መልካም ነገሮችን ሰርቶ ሰዎችን በማስደሰት ምርቃትና በረከት ማግኘት፣ በጎ ተግባራትን ማከናወንና እርግማንንና ቅሬታን መሸሽ፣ መጠየፍ፣ መፍራት፣ ማስወገድ ለነገ ከነገወዲያ ቀጣይ ህይወት ጠቃሚ እንደሚሆን ትልቅ ተሞክሮ ያካፍለናል። መከባበር፣ መደማመጥ፣ በርካታ ገንዘብ ቢወጣም፣ የጊዜና የጉልበት መስዋዕትነት ቢከፈልም፣ ስራዎች ቢበደሉም፣ ለቤተሰብ፣ ለአካባቢ፣ ለባህሉ ክብር የተከፈለው ክፍያ ትልቅ ዋጋ እንዳለው የማህበረሰቡ ፅኑ እምነት በመሆኑ ለመስቀል በዓል የተለየ ክብር እንዳለው፣ ሌሎችንም ቁምነገሮች መማር ይቻላል። የዘንድሮ መስቀል ወይንም የእርድ (የወኸምያ) ዕለት ባልየው ቤተሰቦችጋ ቢከበር በቀጣዩ ዓመት ወይንም የደመራና የንቅ ባር ዕለት (መስከረም 17) ሚስት ቤተሰቦችጋ በየተራ መከበሩም የሚያስተምረን ቁምነገር አለ። ከዚህም በላይ ለመስቀል ተሳክቶለት አገር ቤት መግባት ያልቻለውም የጉራጌ ቤተሰብ በያለበት በዓሉን ከሞላ ጎደል የሚያከብረው በተመሳሳይ ሁኔታ ነው። ብሄረሰቡ ለሴቶች የሚሰጠው ስፍራ ትልቅ መሆኑ ለሌሎችም አርአያነት ያለውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት፣ በምሽት ሸንጎ የመመካከርን ልምድ መዳበር፣ በቂጫ/ሴራዎች አማካኝነት ግጭት እንዳይፈጠር ማስተማርና መከላከል ፋይዳው ሰፊ እንደሆነ፣ ድንገት ግጭት በደልና ጥፋት ቢፈፀምም በፍትህ አስተዳደር ባህላዊ ስርዓቱ መሰረት ቀጥቶ መክሮ አስታርቆ በዳይና ተበዳይ እንደቀድሞአቸው ተከባብረውና ተፋቅረው እንዲኖሩ ማድረጊያ ትልቅ ባህላዊ እሴት መሆኑን ከዚህ ተሞክሮ መማር ይቻላል። ከዚህም አልፎ ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ወደሀገራችን ከገባ በኋላ ጉራጌ ምርመራ አድርጎ ነፃ መሆኑ በማስረጃ ያልተረጋገጠ ለመስቀል ከከተማ የሚመጣ ባል ከሚስቱ ጋር የግብረ-ስጋ ግንኙነት እንዳይፈፅም ለረጅም ዓመታት ባህላዊ ክልከላ መደረጉ ጉራጌዎች በአመዛኙ ከተሜዎች እንደመሆናቸው መጠን በዞኑ ውስጥ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ በእጅጉ ያገዘ እርምጃ ነው። ሌሎችንም መልካም ተሞክሮዎች ማንሳት ይቻላል። ጉራጌ የመስቀል በዓልን የሚያከብርበት መንገድ ከባድ ወጭን የሚጠይቅ፣ አድካሚ፣ በዝናብና በጭቃ ረጅም መንገድ መጓዝንና እንግልትን የሚጠይቅ፣ ስራን የሚበድል፣ በአጠቃላይም ብዙ ዋጋን የሚያስከፍል ቢሆንም የታሪኩ፣ የባህል እሴቶቹ፣ የህይወቱና የሩቅ ጉዞው አካል በመሆኑ ምንጊዜም በዓሉን በድምቀት ከማክበር ወደኋላ ሳይል ዛሬ ድረስ ዘልቋል። ስርዓቱ ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ሳይዛነፍ እንዲተላለፍም አጥብቆ ሰርቷል። ታዲያ የሀገራችን የባህል እሴቶች የሚባሉት የሁሉም ህዝቦች ባህሎች ተዳምረው በመሆኑ የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ባህል ሳናከብር የጋራ ሀገራችንን ባህል እየገነባን ነው ማለት ስለማይቻል እዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል። ኢትዮጵያውያን ብዙ ሀብቶች አሉን። ያሉንን ግን በወጉ አናውቃቸውም። አንጠቀምባቸውምም። ብዬ ነበር። አሁንስ የት ላይ ነው ያለነው ጎበዝ? ቸር ይግጠመን።

ፀሀፊው አቶ ተስፋዬ ጎይቴ ጉራጌንደ፣ ስንክርተነ፣ ቡር ቂጫ የተሰኙ በጉራጊኛ የተፃፉ መፅሀፍት ለአንባቢያን ያበረከቱ ሲሆን በጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር በመሆን 8 አመታት አገልግለዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top