ፍልስፍና

የዘመን መንፈስ የጋራ ህልውና እና ለውጥ

መግቢያ

ባለፈው ጽሑፍ ስለ ጊዜ እሳቤ በተወሰነ የዳሰስን ሲሆን፤ የጊዜ እሳቤን በዝርው ተመልክተናል። የጊዜ እሳቤ ለአንድ ማኅበረሰብ የሥልጣኔ ትርጉም የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተመልክተናል። በይደር ያቆየነው አንድ ጉዳይ የዘመን መንፈስን የሚመለከተው ሐተታ ነው። ገቢርን በዘመን እና በቦታ ካስማ ውስጥ አጥሮ ማስቀመጥ ከባድ ቢሆንም ስለአንድ ወቅት ሁለንተናዊ መስተጋብር ለመተንተን ከቦታና የጊዜ እሳቤ ባሻገር ስውር ሆኖ የሚመራውን ረቂቅ ውቅር መረዳት ያስፈልጋል። የዘመን መንፈስ (በጀርመንኛው Zeitgeist) ሲባልም በጊዜ አማካኝነት የተንጸባረቀውን ገዥ- ሐሳብ፣ አስተሳሰባዊ መዋቅር፣ ለገቢር መሪ ሆኖ የበርካቶችን ባህርይ የሚያስተሳስር ኃይል፤ የማይታይ መንፈስ ወይም ስውር ኃይል ነው። በጊዜ አማካኝነት ሲገለጽ ስውሩ በጉልህ እንዲታይ የሚያደርጉት የተናጠል ወይም የጋራ እንቅስቃሴዎች የዘመኑን መንፈስ የሚያንጸባርቁ፣ የሚገልጡት ወይም የሚለውጡት እና ወደ ሌላ የዘመን መንፈስ የሚያሸጋግሩት ይሆናሉ። የዘመንን መንፈስ መረዳት አንድን ባህል ለማወቅ፣ ታሪካዊ ሁነትን፣ የሰዎችን ተግባቦት ለመረዳት፤ እንዲሁም በጋራ ወይም በግል ባህርያት ላይ የምንሰጠውን ፍርጃ በማገዝ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የዘመን መንፈስ ትርጓሜ፣ የጋራ ህልውና፣ ለውጥና ቀጣይነትን መመልከት የዚህ ጽሑፍ ተቀዳሚ ዓላማ ነው። የዘመን መንፈስ የጋራ ህልውናን እንዴት ይበይናል? የዘመን መንፈስ ከለውጥ ውስጥ ቀጣይነትን እንዴት ሊያንጸባርቅ ይችላል? የሚሉት ጥያቄዎች የጽሑፉ መነሻ ናቸው።

1. የዘመን መንፈስ እና የጋራ ህልውና የዘመን መንፈስ በሰው ልጆች ባህል ገንቢነት ውስጥ ጎልምሶ፣ መልሶ ሰዎችን የሚቆጣጠር ስውር ኃይል ነው። እዚህ ላይ ሙለርን በረጅሙ እንጥቀስ እና የዘመን መንፈስ ሐቲታችንን ከጋራ ህልውና፣ ለውጥ እና ቀጣይነት አንጻር እንመልከት።

“The fundamental fact is that man is the only culture-building- animal. Culture means man made environment, which is primarily a mythical or ‘spiritual’ environment. […] And the most powerful influence on him is the unseen environment of his own creation. We may deny, for example, the validity of belief in the supernatural, but we cannot deny its tremendous power. […] Civilization, or culture grown more varied and complex, represents a more conscious, determined, resourceful effort to master the natural environment and set up a world of man’s own. Amid its complexities one may see only that the individual is a product of his society, which in turn is a product of impersonal forces. Nevertheless the whole enterprise of civilization is a rare human creation, a triumph of mind over will; and the impersonal forces work only through the ideas and beliefs of men.” (1952, 42)

ኮሊንስ የእንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላት የዘመን መንፈስ የሚለውን ሐረግ የአንድን የህዝብ አስተሳሰባዊ መዋቅር፣ እምነት እና መሻት የሚገልጽ የአንድ ወቅት ህልው ሁኔታ ነው በሚል ይተረጉመዋል። Spirit of the age/ the spirit of the times “is the set of ideas, beliefs, and aims that is typical of people in particular period in history.” በዚህም መሠረት የዘመን መንፈስ በአንድ ወቅት ለረጅም ወይም ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የጋራ አስተሳሰባዊ ዝንባሌን የሚመለከት ነው። ይህንን የዘመን መንፈስ በወቅቱ የሚኖሩ ሰዎች በግልጽ ላይረዱት ይችላሉ፤ ወይም በውስጡ የሚኖሩበት ሰዎች የዚያ ገዥ-መንፈስ ባሪያዎች፣ ፊታውራሪዎች መሆናቸውን አያውቁትም። የዘመን መንፈስ እየተገለጠ የሚመጣውም በጊዜ ስንርቀው ወይም በሌላ ገዥ-መንፈስ ሲተካ ነው። የዘመን መንፈስ በሁለት መልኩ መረዳት ይቻላል። አንደኛ አንድ ንጥል ማኅበረሰብ (particular community) በታሪኩ ውስጥ ያሳለፋቸው፣ በጋራ ሕልውናው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደሩበት መጥፎ ወይም በጎ ትውስታዎችን የሚያካትት ውሕድ ነው። ያ ገዥ-መንፈስ የዚያን አካባቢ ነዋሪዎች አጠቃላይ ሁለንተናዊ፣ አስተሳሰባዊ እና ገቢራዊ ሁኔታዎችን ይበይናል። ምናልባትም ከተፈጥሮ ጋር በመተባበር (በአደጋ ወይም በበረከት)፣ በሰው ሰራሽ ድንገት ደራሽ በሆኑ ኹነቶች በመቃኘት (በጦርነት ወይም ሆነ ተብሎ በሚደረግ ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ) ወይም ከባህሎች ውስጣዊ ለውጥ በሚወለዱ ቀያሽ ድርጊቶች የአንድን ማሕበረሰብ አስተሳሰባዊ እና ተግባራዊ ኹነቶችን ይበይናሉ። የዚያ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ግለሰቦች ከዘመኑ ሊያፈነግጡ ጥረት ቢያደርጉም በማወቅ ወይም ባለማወቅ ለዚያ የጋራ አስተሳሰብ ይገብራሉ። ሁለተኛው ደግሞ በቦታ አድማሱ ሰፋ ያለ እና በርካታ የዓለምን ማሕበረሰብ የሚያጠቃልል መንፈስ ነው። ከቦታ አንጻር ብቻ ሳይሆን መንፈሱ አግብሮቱን (ተጽዕኖውን/Influence) ለማበልጸግ፣ ለማስፋት በዘመንም ረዘም ያለ ወቅት የሚፈልግ ነው። በዓለም ታሪክ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች በድንበር ተሻጋሪነትና በረጅም ጊዜ ጫና የሚጠቀሱ ናቸው። ለምሳሌ የክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት፣ የባሪያ ንግድ፣ የቅኝ ግዛት ወረራዎች፣ የነጻነት ትግሎች፣ የዓለም ጦርነቶች፣ የማርክሲዝም ፍልስፍና የወለዳቸው አይዲኦሎጂ እንቅስቃሴዎች እና ተከታይ አመጾች ወ.ዘ.ተ… የየዘመናቱን መንፈስ ስፋት እና ዓለማቀፋዊነት የሚመለከቱ ማሳያዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ መስፋፋት እና እሱን ተከትለው የሚመጡ አስተሳሰባዊ እና ተግባራዊ ለውጦች የዚህ ዓለማቀፋዊ ገዥ ምንፈስ ማሳያዎች ናቸው። በዚህም የፍልስፍና፣ የጥበብ፣ የሳይንስ እሳቤዎች በዚህ ገዥ-መንፈስ ሥር በመውደቅ ዘመኑን በመመገብ ውይም ጊዜውን በመሞገት የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ስሜትና ሐሳቦችን እንዲያንጸባርቁ ይገፋፋቸዋል። ፈጠራዎቹም በአዎንታ ውይም በአሉታ የዘመኑን ማዕከላዊ ባህርይ ያንጸባርቃሉ። አንዳንዶቹ በመደገፍ የዘመኑን መንፈስ “ይበል! ይበል!” እያሉ ፈረስ ሆነው ያስፈነጥሩታል፤ ሌሎቹ ደግሞ በአነዋሪነት (Critics) ወይም በፍጹም ተቃዋሚነት (Revolution) ያምጹበታል። ምንም እንኳን ለውጥ አይቀሬ ቢሆንም የዘመን መንፈስ ዋና መገለጫው የጋራ ህልውናን በግልጽ ወይም በህቡዕ ማወጁ ነው። ሰው ማኅበራዊ እንስሳ እንደመሆኑ የዘመን መንፈስ ይሕንን ማኅበራዊነት በመጠቀም ገዥ ይሆናል። ለአጭር ጊዜም ቢሆን የጋራ ህልውናን በማረጋገጡ ነው አንድን አስተሳሰብ፣ እምነት እና ዓለማ የዘመን መንፈስ የሚያስብለው። ለዚህ የዘመን መንፈስ በምንሰጠው እውቅና ወይም በዚያ የዘመን መንፈስ በሚደርስብን የጋራ በደል፤ …የጋራ ህልውናችን ይንጸባረቃል። የዚህ ዘመን ትውልድ ወይም የዚያ ዘመን ሰዎች የሚል የጋራ መጠሪያ የምንሰጠውም በዚህ የጋራ ህልውና ላይ ያለ ተሳትፎን ያሳያል። የዘመኑ መንፈስ ቀጣይነት ወይም ለውጥ በተሳታፊዎቹ ቁርጠኝነትና የልቡና ትባት፣ በዘመኑ መንፈስ ተፈላጊነት ወይም አይፈለጌነት ይወሰናል። አፈንጋጮች የዘመንን መንፈስ በመቃወም እና ባልገዛም ባይነት ዘመኑን ለመለወጥ ሌት ተቀን ይሰራሉ። የዘመኑን መንፈስ መለወጥ እና በለወጥ ውስጥ ያለውን አይበገሬነት፣ ቀጣይነት የሚወስነው ከብዙሃኑ በሚቸረው ቅቡልነት ወይም በመጤው (በአዲሱ) ሐሳብ ጥንካሬ ነው።

2. የዘመን መንፈስ፣ ለውጥና ቀጣይነት (ትናንት ዛሬ አይደለም፤ ነገም ሌላ ቀን ነው?)

የጋራ ሕይወትን እና የግለሰቦች ባሕርያትን የመወሰን፣ የማገበር ኃይል ያለው የዘመን መንፈስ “ሽህ ዓመት ይንገሱ” የማይባልለት ነው። እንዲያውም ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል። የግለሰቦች በዘመን መንፈስ የትጋታቸው ትሩፋት የሚያስገኘውን ውጤት በተራዘመ ጊዜ መረዳት ይቻላል። መንፈስ በዛሬነት ጥቅልል ውስጥ ትናንትን፣ አሁንን እና ነገን ያሰረ ነው። ዛሬነት ደግሞ የማይያዝ የማይጨበጥ፣ በኡደት ውስጥ ያለ ኹነት ነው። እንዲያውም የዛሬነት ምስጢር የሚገለጠው ትናንትን ሰብስቦ በማስታወሱ እና ከትውስቱ የሚገጥመውን በመያዝ የሚያስበረግገውን በማግለል ወደ ነገ በሚያደርገው ጉዞ ነው። ‹ዋይትሄድ›ን ጠቅሶ ስለ ዛሬነት፣ አሁንነት (present) ጉዳይ ሙለር እንዲህ ይላል። “the present is a holy ground. It is all there is: the whole past is summed up in it, the future is implicit in it; and at worst, it contains the values and ideals that inspire men to condemn it.” የዛሬነት ግፉ ራሱን የሚያጠፋበት የለውጥ እሴቶች እና ሐሳቦች የሰዎችን ሕሊና እንዲቀሰቅሱ እረፍት መንሳቱ ነው። ሰዎችን ዛሬን እንዲያወግዙት፣ በዛሬ ላይ እንዲያመጹ፣ እንዲያኮርፉ የሚያደርጋቸውን ሐሳብ ሹክ የሚላቸው አሁናዊ መንፈስ ነገነትን በመጽነሱ ነው። ትናንትን እንደወረደ እንዳልቀበርነው ማሳያው ደግሞ አላፊውን ጊዜ በማንጠሪያነት ተጠቅሞ፣ የሚያዘውን በመያዝ ጥቅልል ትዝታን በመቋጠሩ ነው። ለዚህም ነው ለውጥ በቀጣይነት ውስጥ፣ ቀጣይነት ደግሞ በለውጥ ፈረስነት የሚጋልቡት። ለለውጥ መነሻው አንድም የዘመኑ መንፈስ በራሱ እንዲለወጥ ግድ የሚያስብለው ባሕርይን ሲላበስ ነው። መንፈሱ የረሃብ፣ የቸነፈር፣ የጦርነት፣ የስቃይ የሆነ እንደሆነ ከዚህ ጋር ተዋድዶ፣ ተላምዶ፣ ፈቅዶ የሚኖር የለምና ለውጥ ግድ ነው። ይህንንም በታሪክ አይተናል። ሰዎች ከመንፈሱ ይሸሻሉ፤ በውስጣዊ ዓመጽ ወይም በሚታይ ተቃውሞ። በጋራ እና በተናጠል መክረው ሰዎች ዘመኑን ሊያሻግር የሚችል ብልሃት ያፈልቃሉ። ለውጥ ያኔ ያለ ማመንታት አይቀሬ ሂደት ይሆናል። ሁለተኛው ይህ ነው ተብሎ በክፉ ያልተፈረጀ መንፈስ ሲሆን፤ ለውጥ ከመንፈሱ ባሕርይ ላይፈልቅ ይችላል። ይልቁን ቡድኖች ወይም ግለሰቦች በሚያፈልቁት ሐሳብ ላይ ይመሰረታል። መንፈሱ (The Hype) ለብዙሃኑ ምቾት የሚሰጥ ሆኖ፤ ለአስተዋይ ተመልካች ግን ገዥው-መንፈስ ሰዋዊነት የጎደላቸው መርሆዎች ሊኖሩት ይችላሉ። እናም ዘመንን የሚያኮርፉ አይጠፉም። እውቁን ገጣሚ ደበበ ሰይፉን እዚህ ላይ እንጥቀሳቸው፦

ለምን ሞተ ቢሉ
ንገሩ ለሁሉ
ሳትደብቁ ከቶ
ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመን ተጣልቶ

በዚህች የስንኝ ቋጠሮ ውስጥ የምናገኘው ሐሳብ ዘመንን የሚያኮርፉ መኖራቸውን ነው። ዘመንን ማኩረፍ፣ ከዘመን መጣላት፣ እስከ ሞት የሚያደርስ መሆኑን ያሳያል። እነዚህ አኩራፊዎች የዘመንን መለወጥ የሚመኙ እና በፊታውራሪነት የሚመሩት ናቸው። እያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ፣ ንቡርን ለማስቀጥል ዘብ የሚቆሙ ደግሞ በአንጻራዊው ዳር አሉ። የሁለቱ ፍትጊያ ለውጥን በቀጣይነት ውስጥ ተሸብቦ እንዲያብብ፣ ወይም ቀጣይነትን በለውጥ ውስጥ ተወሽቆ፣ ታዝሎ እንዲቀር ያደርገዋል። አብዝሃኛዎቹ ቀጣይነቶች ከዘመን ጋር ስለሚያኳርፉን ይወገዱ ብለን እንድንፈርድ የሚያስገድደንን ያክል፤ ለውጦች እና ፈጠራዎችም የራሳቸው ተዛንፎዎች ስለሚኖሯቸው ‘ከማያውቁት መልአክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል’ ዓይነት ፍርሃት ያስከትላሉ። “All creative achievements are disruptive, and create new problems. All victorious creeds and policies have unintended by-products, which may defeat their purposes.” እንዲል ሙለር የለውጥና ቀጣይነት ነገር በትግል የተሞላ ፍትጊያ ነው። የረበበው የዘመን መንፈስ ተገፎ ሌላው እስኪዘረጋ ጸሐይ የሚያስመቱ፣ ዝናብ የሚያሾልኩ ቀዳዳዎች አይጠፉም። ይህ የዘመን መንፈስ ሽግግር በጥንቃቄ ካልተመራ እና ቁርጠኛ ባለቤቶች ካላገኘ የሚያመጣው ጣጣ ከባድ ነው። ከድሮውም ያልሆኑ፣ ለአዲሱም ያልተዘጋጁ ትውልዶች ያልፋሉ። ከአንዱ ወደ አንዱ በሚደረግ ሽግግር በሚፈጠር አለመግባባት እንቁ ህሊናዎች ይጋረዳሉ። በርካታ ጉልበት ያላቸው ወጣቶች ይረግፋሉ። ይህንን የሽግግር አደጋ እና በውስጡ ሳያመረጡ እንዲሁ የሚያልፉትን ትውልዶች ከረር ባለ አነጋገር ዶ/ር እጓለ ‘የመከነ ትውልድ’ ይሉታል። የመከነ ትውልድ ለማለት ባያስደፍርም በእርግጥም የእኛም ሀገር ታሪክ፣ የዓለምም ሁኔታ የሚያሳየው ይህንን ነው። ከዘመን የተኳረፉ ሰዎች ሞት ወይም ወደ ኋላ መቅረት ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንደዚህ ዓይነቶቹን ዘመኑን መምራት ወይም ከዘመኑ ጋር መራመድ ያልቻሉትን ነው መሰል በእውቀቱ ስዩም በስንኝ ቋጠሮች ሸንቆጥ ያደረጋቸው፦

እኛ’ኮ ለዘመን ክንፎቹ አይደለንም
ሰንኮፍ ነን ለገላው
በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው

በዚህ ግጥም የተጠቀሱት እኛዎች (ገጸ- ባህርያት) ዘመን በታደሰ ቁጥር አላስፈላጊ ቀጣይነትን መርጠው የሚገተሩትን ይመስላል። እንግዲህ በለውጥና ቀጣይነት እሳቤ፣ “ትናንት ዛሬ አይደለም፣ ነገም ሌላ ቀን ነው” ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም። በትናንት፣ በዛሬ እና በነገ መካከል በስውር የተሰፋ ቀጣይነት መኖሩን ያሳያል። ትናንትን አዝሎ የያዘ ግራጫ ለውጥም አይጠፋም። ዛሬ በትናንት አስተሳሰብ ውስጥ ወድሞ የተወጠነ ድርሳኑን ሲጽፍ፣ ወደ ነገ የሚያዘግምበትንም መስመር ቅያስ እያበጀ ነው ማለት ነው። ይህንን የዘመን ለውጥ በአግቦ ለመምራት ትንሽ (የስናፍጭ ቅንጣት ታክል) ኩርፊያ፤ ለመብረር የሚያስችለን የንስር ክንፍ ያስፈልጋል ማለት ነው። ሁሉም ነገር ይለወጥ፣ ያረጀው፣ ያፈጀው ይረሳ፣ ‘ሕደግዎ መንንዎ’ ገደል ይግባ እንዳንል ደግሞ በእባቡ ሰንኮፍ ሾልኮ የታደሰ አካል መኖሩን መዘንጋት አያስፈልግም። ክንፍም እኮ ቢሆን ሰውነትን አዝሎ ወንዝ የሚያሻግር ነው። ኩርፊያም በልክ ይሁን ሲባል የሚያዝን ለመያዝ፣ የሚጣልን ለመጣል፣ የሚመረጥን ለመምረጥ የሚያስችልን ቀልብያ፣ ምክንያታዊነትን እንዳይሸፍነው ነው። ለመሆኑ በዚህ የለውጥና ቀጣይነት እሳቤ አላፊ ዘመኖች ወይም የዘመን መንፈሶች እንዴት ይነበባሉ? እንዴትስ ከዛሬው ጋር ይናበባሉ? በቀጣይ የዘመን መንፈስን እሳቤ በታሪክ ንባብ ማሳያነት እንመለከታለን። እስከዚያው የወር ሰው ይበለን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top